ዋናው የመንግሥት ትኩረት የዐማራውን ጭፍጨፋ ከማስቆሙ ላይ መሆን አለበት – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“በማንኛውም ላይ ጸረ-ፍትህነት ከተፈጸመ የሚያስክትለው ስጋት ለሁሉም ነው (Injustice anywhere is a threat everywhere”

The Reverend Dr. Martin Luther King

ክፍል አራት

“አንድ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል፤ ይሻላል የሚባለው እምነት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ ካልተወገደ” ሰላም፤ እርጋታ፤ የጋራ ደህንነት ስኬታማ እንደማይሆን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለጠተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንዳሳሰቡ ታሪክ መዝግቦታል። ይህን ለምናስታውስ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅን በማያሻማ ደረጃ ደግፈው “የሕዳሴ ግድብን ቦምብ አድርጊ” ብለው የመከሩት አደገኛ አቋም በዲፕሎማሲ ታሪክ የጥቁር ነጥብ ሆኖ እንደሚጠቀስ አልጠራጠርም።

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ግን ትራምፕ አይደሉም። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ዋና አደጋ የሆነው የዘውግና የኃይማኖት ጽንፈኞች/ሽብርተኞች ክፍሉ ነው። ይህ ኃይል መወገዝ ብቻ ሳይሆን መደምሰስ አለበት።

ኦነግ ሽኔ የተባለው በኦሮሞ ሕዝብ ስም ተደራጅቶ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ትጥቁን ሳይፈታ ሲንቀሳቀስ የቆየው የሽብርተኞች ምሽግ የሆነው ድርጅት በተከታታይ አመጽና ጭፍጨፋ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል። የዐማራ ሴቶች ተማሪዎችን ከደምቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ጠልፎ ሲያሰቃይ ቆይቷል፤ እነዚህ ወጣቶች በህይወት ይኑሩ አይኑሩ አይታወቅም።

በኦሮምያ ክልል ብቻ ከአስራ ሰባት በላይ የሚሆኑ ባንኮችን ዘርፏል። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እየተዘዋረ፤ ከህወሕትና ከውጭ ኃይሎች ጋር በጋራ እየሰራ በተለይ በዐማራውና በክርስትያን እምነት ተከታዮች ላይ እጅግ የሚዘገንን እልቂት አካሂዷል። የሚቃወሙትን ኦሮሞዎችም ጭምር ጨፍጭፏል። በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት አውድሟል። ይህ የሽብርተኞች፤ የጅሃዲስቶችና የውጭ ጠላቶች ምሽግና ደጀን ድርጅት የተለየ ኢላማ ያደረገው “ነፍጠናውን” የዐማራውን ህዝብ ነው። የዐማራው ብልጽግና ፓርቲ አመራር የወለጋውን ጭፍጨፋ/እልቂት/ጥቃት በሚመለከት የህወሓት እጅ አለበት የሚለውን ዘገባ ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ።

በ November 1, 2020, በወለጋ የኦነግ ሽኔና በቀጥታም ሆነ በቸልተኛነት ምክንያት የተባበሩት ወይንም ችላ ብለው ያዩት የኦሮሞ ልዩ ኃይልና የፌደራል ኃይል አካላት በንጽሁ የዐማራው ሕዝብ ላይ ኦነጎች የፈጸሙት የሚዘገንን ጭፍጨፋ/እልቂት፤ አብን የተባለው ለዐማራው ሕዝብ ድምጽ የሆነው ድርጅት እንዳስቀመጠው የሚዘገንን “የደም ጎርፍ” ነው”። የዐማራው ብልጽግና አመራርና ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ የተሰማቸውን ሃዘን መግለጣቸው እንዳለ ሆኖ፤ መላው የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀውና በመረጃ እንዲያዘው የምፈልገው የሚከተለውን መረጃ ነው።

ድርጊቱ የተፈጸመው በኦሮምያ ክልል በግንቢ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ነው። የኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ንጹሃኑንና ያልጠረጠሩትን የዐማራ ዘውግ አባላትን ከበውና አስገድደው በትምህርት ቤት ሰበሰቧቸው/አጎሯቸው። ይህ የሽብርተኞች ቡድን ይህንን ሲያደርግ ክፍተት መኖሩን ገምግሞ ነው። ባለፉት ሶስት ወራት በአካባቢው የመሸገው የፌደራል የመከላከያ ኃይል ቦታውን ለቆ ነበር። ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ነዋሪውን ሕዝብ –ህጻናትን፤ እናቶችን፤ አባቶችን፤ ደካሞችን–እንዲሰበሰቡ አደረገ። ከ300 በላይ የሚገመት የዐማራ ሕዝብ ተሰበሰበ።

ከተሰበሰበው የዐማራ ነዋሪዎች መካከል 200 የሚሆኑትን ኦነግ ሽኔ ጨፈጨፋቸው። የተረፉት በመበታተን “መንግሥት ካለ ይድረስልን” የሚል ጩኸት አሰምተዋል። እኔ የምጠይቀው ግን፤ የፌደራሉ መከላከያ ኃይል ለምን ቦታውን ትቶት ወጣ? ማንን ተማምኖ የሚለውን ነው። ዋናው የመንግሥት ሃላፊነት የዜጎችን ደህንነት መታደግ ነው። በዚህ መስፈርት ሲገመገም ኢትዮጵያ መንግሥት አላት ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም።

የዐማራው ዘውግ እንዲጠፋ ተፈርዶበታል።

ኦነግ ከኤርትራ ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ለምን ትጥቁን እንዲፈታ አልተደረገም? ሁኔታው የሚያሳየው አለ። ይኼውም የዐማራውን ሕዝብ እንዲያጠፋ ተፈቅዶለት የተደረገ ሴራ ይመስላል። ህወሓት መቀሌ ከመሸገ በኋላ በተከታታይ በዐማራው ሕዝብ ላይ እልቂት ሲያካሂድ የቆየውና የዐማራውን ሕዝብ ህይወት ወደ “የደም ጎርፍ” ያሸጋገረው ማነው? ዋናው ኦነግ ሽኔ ነው። ይህ ቡድን ግን በተናጠል አይሰራም፤ የሚሰራው ከህወሓትና ከውጭ ኃይሎች ጋር ነው። ስልሀሆነም፤ ይህ “የደም ጎርፍ” ኢትዮጵያን ፈጽሞ እንዳያጠፋት እሰጋለሁ። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት የማያሻማና ጠንካራ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ ያለበት።

እኛ ኢትዮጵያዊያን በመላው ዓለም፤ በተለይ በጥቁሩ ሕዝብ የምንታወቀው ነጭ ይሁን ቀይ፤ ጥቁር ይሁን ሌላ፤ የማንም ዘር ወይንም ብሄር ከሌላው አይበልጥም የሚለውን እሴት ይዘን መኖራችን ነው። “ነጭ አንደኛ ዘር፤ ቀይ ሁለተኛ ዘር” ወዘተ የሚል ስርዓት የተካሄደባቸው የተወሰኑ አገራት አሉ። ከእነዚህ መካከል የአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካና ገና የጥቁር ሕዝብ እውነተኛ እኩልነትና ፍትህ ያላገኘባት የትርራምፕ አሜሪካ ይጠቀሳሉ።

ትራምፕ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን በሚያሳፍርና የነጮችን ትእቢተኛነት በሚያሳይ መልኩ “እኛ ያልነውን ካልተቀበላችሁ” ግድባችሁን ግብፅ “ቦምብ” የማድረግ መብት አላት ብለው ጠብ ጫሪነቱን አሳይተውናል። ይህ እትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን መላውን የጥቁር ሕዝብ የመናቅና “እናንተ እኮ በዘር መስፈርት ስናያችሁ ሶስተኛ ደረጃ የያዝችሁ ሕዝቦች ናችሁ” የሚል ብሂል ከዚህ በፊት የጥቁር አፍሪካን አገሮች “የሰገራ ጉድጓድ አገሮች (Shithole countries) ናቸው ያሉትን ስድብ  ያስታውሰኛል።

በተጨማሪ፤ ትራምፕ ይህንን አሳፋሪና አደገኛ አስተያየት ሲሰጡ፤ አብዛኛው የአሜሪካ ሕዝብ የማይጋራውን አቋም ይዘው ነው የተናገሩት። እኔ በምኖርበት በሜሪላንድ ሴናተር ቫን ሆለንና ሴናተር ካርደን የትራምፕን አቋም አውግዘዋል። እኔም በእንግሊዝኛ ጽፌ ባሰራጨሁት ትንተናየ አውግዠዋለሁ። የሚያስከትለውን አደጋና ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለዲያስፖራው ያለኝን ምክር አቅርቢያለሁ።

የመጣላቸውን ሁሉ ምንም ሳያስቡበት የሚናገሩት ትራምፕ፤ ሲናገሩ ከጀርባ ሆነው አድሏዊና ዘረኛነትን የሚያሳይ አቋም እንዲወስዱ ያደረጓቸው ኃይሎች አሉ። ቀደም ሲል የኤምሬትን፤ አሁን ደግሞ የሱዳንን መንግሥት ሲያባብልና ሲያግባባ የቆየው የትራምፕ አማችና አማካሪ ጀሪ ኩሽነርና የትሬዠሪው ዋና ሃላፊ ስቲቭን ሙኒቸን መሆናቸው ይታወቃል። ስለ ሕዳሴ ግድብ በዋሽንግተን ዲሲ ይደረግ በነበረው ድርድር ኢትዮጵያን በሚጎዳ ደረጃ ጫና እንዲደረግ ያደረጉትም እነዚህ ናቸው።

ትራምፕ ለግብፅ ወግነው ግድቡን “ቦምብ” ታድርግ ብለው ሲመክሩ፤ ባልተለመደ ሁኔታና ደረጃ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይንም ስቴት ዲፓርትመንት ሃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር አድርገው ግብአት ቢሰጡበት ኖሮ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገንዘቡ የሚሰራውን፤ በኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ “ግብጽ ቦምብ ብታደርገው” አግባብ አለውና መልካም ነበር አይሉም ነበር። ጥሪያቸው እኮ በዓለም ህግጋትና ልምዶች የተከለከለ የውንብድና መልእክት ነው። ግብጽ ይህን ግድብ “ቦምብ” ብታደርገውና ኢትዮጵያ በምላሹ የአስዋንን ግድብ ቦምብ ብታደርገው ትራምፕ ደንታ ያላቸው አይመስልም። የሚጎዱት ግን የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መሆናቸውን ተገንዝበውት ይሆን? አይመስለኝም። ግድም አይሰጣቸውም።

የራሳቸውን ሕዝብ የማያከብሩት ትራምፕ፤ በተለይ ጥቁር አሜሪካኖችን፤ እኛን የጥቁር ሕዝቦች ያከብራሉ የሚል እምነት አይኑረን። ፕሬዝደኑቱ  “ትክክልኛ አእምሮ የላቸውም” የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች አሉ። የራሳቸው የወንድም ልጅ ሚሪ ትራምፕ “Too Much And Never Enough” በተባለው መጽሃፏ እንዲህ ብላለች። “A case could be made that he (Trump) also meets the criteria for antisocial personality disorder, which in its most severe form is generally considered sociopathy but can also refer to chronic criminality, arrogance, and disregard for the rights of others…”

ለእኔ የተለየ ትኩረት እንድሰጠው የፈለግሁት ስውየው ከራሳቸው የግል ጥቅም ውጭ ለማንም መብትና ለፍትህ ደንታና ርህራሄ የሌላቸው መሆኑን ነው። በተጨማሪ ግን፤ ራሳችን በዘውግና በእምነት ተከፋፍለን፤ በተረኛነት ሽሚያዎች ተሰማርተን ያስናቅናትን ኢትዮጵያን እንድትበደል ቢያደርጉ እንዴት ልንፈርድ እንችላለን? የሚለውን ጥያቄ አስቡበት። ተንቀናል፤ አገራችንን አስንቀናታል።

ባይደንና መላውን ቤተሰባቸውን በውድድሩ ወቅት ሲሳደቡ ለሰማ ሰው ሰውየው “አብደዋል” ከማለት ውጭ ምን ለማለት ይቻላል። ቢመረጡም፤ ባይመረጡም የተናገሩት ለአሜሪካ መንግሥት ጥቁር ቀለም ሆኖ ሁልጊዜም በታሪክ ሲጠቀስ ይኖራል።

ቢያንስ ቢያንስ እንዲመዘገብ ስለምፈልግ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ማድረግ ያለበት፤ የትራምፕን አቋም ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ድርጅትና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት አስመቶ አቤቱታ ማቅረብ ግድ ይላል። ትራምፕ ይቅርታ አይጠይቁም።  የዓለም መንግሥታት እንዲያውቁት የማድረግ ግዴታ ግን አለብን። በተጨማሪ፤ በአሜሪካ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትራምፕ እንዳይመረጡ ከፍተኛና የተቀነባበረ ዘመቻ ማካሄድ አለብን።

እኛስ ከዚህ ከትራምፕ ሁኔታ ምን እንማራለን? ትራምፕ እንዴት እኛን ቢንቁን ነው የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ በራሱ ገንዘብ አዋጥቶ የሚሰራውን የልማት መሰረታችንን የሕዳሴ ግድብን ግብፅ “ቦምብ” ታድርገው ብለው የመከሩት?

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንዳርጋቸው ጽጌ ሣይቀር የሚሣለቅበት አማራ ይህችን የጨለማ ዘመን ካለፈ ምንም አይል - ሥርጉት ካሣሁን (አዲስ አበባ)

የትራምፕን ትእቢተኛ ጥሪ ወደ ጎን ልተውና፤ ለታዳሚዎች የማቀርበው ተጨማሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘውግና በኃይማኖት የተከፋፈለ መሆኑ ለኢትዮጵያ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳዎች መፍጠሩን አሰመርበታለሁ። ማንም የውጭ ኃይል የማይደፍራት አገራችን በልዩ ልዩ መንገዶች እየተደፈረች ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዲፕሎማሲ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ፕሬዝደንት ትራምፕ በኋይት ሃውስ የኢስራኤልንና የሰሜን ሱዳንን ስምምነት አስመልክተው ሲናገሩ በማይታመን ደረጃና የዲፕሎምቲክ ስንስርዓትን፤ መርሆዎችን መስመር ትተው “የሕዳሴ ግድብ ግብጽን ይጎዳል፤ ግድቡ ግብጽን የሚጎዳ መሆኑን ያወቁት ግብጾች ከጅምሩ ቦምብ ማድረግ ይገባቸው ነበር፤ እኛ ያዘጋጀነውን የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ እርዳታ አቋርጠናል” ወዘተ እያሉ ተናገሩ።

የሱዳንን ጠቅላይ ሚኒስትር አቅርብልኝ ብለው በካርቱም ተሳታፊ የነበረውን የኢስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር ወዳጃቸውን ጠየቁት። የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አግባብ ባለው ደረጃ “ችግሩን ለሁሉም በሚጠቅም ደረጃ ለመፍታት እየሞከርን ነው (We are trying to arrive at a win-win solution)” ብሎ ለትራምፕ መለሰ። ዋናው ጥያቄ፤ በጉዳዩ ምን አገባቸው? የሚለው ነው።

የትራምፕ አድሏዊና አደገኛ አቋም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ሕዝብ፤ በተለይ ለመላው የጥቁር አፍሪካ የሚዘገንና ተቀባይነት የሌለው አቋም መሆኑን አሰምርበታለሁ። ሁሉም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ዜጋ ትራምፕ የሚያደርጉትን የበላይነትና የአዛዢነት አቋም አንቀበልም የማለት ግዴታ አለበት። ከዚህ ላይ ልጠቁመው የምፈልገው ግን፤ የትራምፕን አቋም የሚደግፉ የብሄር ስብስቦችና ጽንፈኞች መኖራቸውን ነው። እርዳታ እንዲቋረጥ ደብዳቤ የጻፉ ጽንፈኞች፤ በተለይ የጃዋር ደጋፊዎች እንደ ነበሩ አውቃለሁ፤ ህወሓቶችም የሚደግፉት እንደሚሆኑ አገምታለሁ።

የቤታችን መከፋፈልና የአስተዳደር፤ የአመራር ወዘተ ድክመት ለኢትዮጵያ መዳከም ግብዓት እያደረገ ነው። ይህን አንካድ!

በኢትዮጵያ የሚታየውን የአስተሳሰብና የፖለቲካ ግብግብ እንዴት ታየዋለህ ተብየ ብጠየቅስ

በእኔ ጥናትና ምርምር በኢትዮጵያ የጦፈው ትግል የሚያሳየው አደገኛ ክስተት በአንድ በኩል በብሄርተኞችና በጽንፈኞች የሚመራውና የተቀነባበረው ሲሆን፤ በሌላው በኩል ደግሞ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት በሚያምነው ጎራ መካከል የሚደረግ ወሳኝ ትግል ነው። ከዚህ በፊት በሶስቱ ሃተታዎቸ እንዳሳየሁት ሁሉ የዐማራው ሕዝብ የሚጋራው ሁለተኛውን አካል ነው። ግን፤ የዐማራው ዘውግ በዚህ እምነቱ ተጠቂ ሆኗል። ተጨፍጭፏል፤ ተስዷል።

እኔ ስገመግመው፤ አሁንም የማስምርበት እምነቴ፤ የዐማራው ሕዝብ ህልውና በቀጥታ ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው። እኔ ሁለተኛውን ጎራ የሚያንጸባርቅ አቋም የወሰድኩት በስድሳዎቹ የመጨረሻ አመታት የተማሪውን እንቅስቃሴ ከተቀላቀኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው። በዚያ ወቅት ከምቀርባቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር እንከራከርባቸው የነበሩ ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። የብሄር ልዩነት ስላልነበር፤ ትዝ የሚሉኝ ለልማት አስጊ የሆኑ አመለካከቶችን እንድናስወግድ ትኩረት የሰጠኋቸውን ተራዎቹን ላቅርባቸው፤

 1. ሰው በሞያው የሚሰራውን ማነወር ከልማት ጋር አይሄድም የሚል፤
 2. ባደግሁበት አካባቢ ለገበሬው ሞፈር ተሸካሚ፤ ማጭድና ሌላ የሚሰራውን “ጠይብ” ፤ ልብስ ሰርቶ ለሕዝቡ የሚያቀርበውን “ቁጢት በጣሽ”፤ ጸሃፊውን “ጠንቋይ”፤ አራሹን “አፈር ገፊ”፤ ነጋዴውን “መጫኛ ነካሽ”፤ ቤተ ክህነት አገልጋዩን “ደብተራ” ወዘተ ብሎ መሳደብ ድንቁርና መሆኑን እንወያይበት ነበር። እነዚህ ሁሉ ጥናትና ምርምር ቢደረግላቸው እየተሻሻሉ ለኑሮ የሚያገለግሉ የምርትና የአገልግሎት ውጤቶች ለልማት ወሳኝ መሆናቸውን እንወያይባቸው ነበር።
 3. ጃፓን እንዴት ሰለጠነች የሚለው አርእስትም ትምህርታዊ ነበር። በሶቪየቶችና በአሜሪካኖች መካከል የሚካሄደው “የቀዝቃዛ ጦርነት” ለአፍሪካ ይጠቅማል ወይንስ ይጎዳል የሚለውም የጦፈ ውይይት ይካሄድበት ነበር።

ቀስ በቀስ ከእነዚህ ለአገር ከሚጠቅሙ አርእስቶች ሸሸን። ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካው ለውጥ በመሸጋገር ስለ መንግሥት ለውጥ፤ ከዚያም ስለ መደብ ጭቆናና የገቢ ልዩነት ሄድን። የለት የለቱን ሆነና ከዚያ አገር ቤት በፍጥነት በዩንቨርስቲ ተማሪዎች ወደሚካሄደው ወደ ብሄር ጭቆና አለ ወይንስ የለም? ወደሚለው አርእስት ተሸጋገርን።

በአጭሩ ላስቀምጠው። ዛሬ ህወሓትና ኦነግ የተቀበሉትና መመሪያ ያደረጉት የብሄር ጭቆና ጉዳይ መነሻው የተማሪው እንቅስቃሴ ነው፤ ከስታሊን የወረስነው የተውሶ ርእዮት መሆኑ ነው። ያኔ ግን የብሄር ጭቆና አለ ተብሎ ሲነገር ትዝ የሚለኝ የትግራዩና የዐማራው ብሄር ነገስታት እየተፈራረቁ ኢትዮጵያን ገዝተዋታል የሚል ነበር እንጂ የዐማራውን ዘውግ ብቻ ለይቶ ገዝቷል የሚል አልነበረም። ይህም ሆኖ ቢያንስ የገዢውን የፌድዋል መደብ ከተራው ሕዝብ የሚለይ ሁኔታ ነበር። ትዝ ይለኛል። ከእኔ ወላጆች ጋር ተጋርቶ የሚሰራው፤ እኔን አሽኮኮ ብሎ ወደ ግብርናው የሚወስደኝ ዐማራ “ጋሸ ውበት” እንዴት ጨቋኝ ነው ብላችሁ ትናገራላችሁ እያልኩ እሟገት ነበር።

ያለፈው የዘውግና የዘውድ አገዛዝ ትርክት እንዳለ ሆኖ፤ እኔ ዛሬ ትኩረት የምሰጠው ትንተና አንድ ነው። ይኼውም፤  ዐማራው ያለ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ያለ ዐማራው ሕዝብ ህልውና ሊኖራቸው አይችልም የሚለው ሰብሳቢ ሃሳብ።

ህወሓትና ኦነግ ዘውግንና ቋንቋን መሰረት ያደረገውን ሕገመንግሥትና ከፋፍሎ ለመግዛት አመቻች የሆነውን የአስተዳደር ስርዓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑት ለምንድን ነው? ማንን ለማጥቃት?

አጭሩ መልስ በማያሻማ ደረጃ ኢትዮጵያን ደሙን አፍስሶ፤ አጥንቱን ከስክሶ ሉዐላዊነቷን የታደገውን የዐማራውን ሕዝብ ለማጥቃት ነው።

ይህንን ትንተና ለማጠናከር ጥያቄዎችን ላቅርብ።

አንደኛ፤ በችግሩ መንስኤ ላይ የጋራ ግንዛቤ ይኑረን።ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ ወዘተ እያልን በመንደርተኛነት ከተበከልን ይህን የዐማራ ግዙፍ ችግር የጋራ ለማድረግና የጋራ መፍትሄ ልንቀይስ አንችልም። መንደርተኛ አስተሳሰብ ስላለን፤ አቅማችን ስለተበታተነ፤ እርስ በእርሳችን ስለምንናናቅ፤ ዐማራውን እየለያዩና እየነጣጠሉ እያጠቁት ነው።

ሁለተኛ፤ የትም ይኑር የትም፤ የዐማራው ችግር የሁላችንም ነው የሚለውን መርህ እንቀበል። የዐማራው ችግር የህልውና ጥያቄ ሆኗል የሚለውን ከተቀበልን፤ ዐማራው ራሱን ከእልቂት የሚያድንበትን ዘዴ በጋራ ልንፈልግ የምንችልበት እድል አለን። ወሳኙና አስተማማኙ ዘዴ፤ የተበታተነው የዐማራው ምሁራን፤ ልሂቃንና አክቲቪስት ነን የሚሉት ለአንድ ዓላማ እየተናበቡ ሲደራጁና ሲሰሩ ነው።

ይህ የሚደረገው በዘዴ እንጅ በመለፍለፍ፤ አንዱ ሌላውን በመጥለፍና በመዝለፍ ሊሆን አይችልም። በተለይ፤ ዐማራውን ከእልቂት የሚያድነው ዐማራው ብቻ ነው የሚለውን መርህ እንቀበል።  እየተናበብን አቅሙን ካጠናከርንለት ራሱን ለመከላከልና ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ተባብሮ አገሩን ከጥቃት ለማዳን እምቅ ኃይል አለው።  ለምሳሌ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ከሚያምኑ ኃይሎች ጋር።

ሶስተኛ፤ በዐማራው ላይ የሚካሄደው እልቂት በጠላቶቹ የተቀነባበረ ነው። በሰሜን በህወሓት፤ በደቡብ በሽኔ ኦነግና በጀሃዲስቶች፤ በምእራብ በግብፅና በሌሎች የውጭ ኃይሎች። ግልጽ ላድርገው። የዐማራው ጉረሮ እየተናቀ ነው የምልበት ምክንያት የዐማራው ሕዝብ ከጥንት ጀሞሮ የራሱ ከሆኑት መሬቶች በተከታታይ እየተፈናቀለ መሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው ፈልጌ ነው። መሬቱና ኃብቱ ሲነጠቅ ጉረሮ ተዘጋ ማለቴ ነው (Economic strangulation). ማንኛውም የዓለም ሕዝብ ለኑሮው መሬት፤ ውሃና ሌላ ለህይወት ወሳኝ የሆኑ መገልገያዎች ያስፈልጉታል። እስራኤሎች ጀሩሳሌምን የራሳቸው ያደረጉት ለምንድን ነው? የጆርዳኖስን ወንዝ ለመቆጣጠር የሚሞክሩት ለምንድን ነው? ከግብፅ፤ ከሱዳን፤ ከኤምሬትስ ጋር የሚደራደሩት ለምንድን ነው? ህልውናቸውን ከአደጋ ለመከላከል ነው። የግዛት የበላይነታቸውን አረቦች አምነው እንዲቀበሉ ለማድረግ ነው።

አራተኛ፤ በየትኛውም አገር፤ በሰብአዊ መብት ተቋማት መስፈርትና ህግጋት በዜግነትና በእምነት መለያዎች ንጺህ ዜጎች ሲጨፈጨፉ፤ ሲባረሩ ወዘተ የማእከላዊ መንግሥትም ሆኑ የአካባቢ ባለሥልጣናት “የተጨፈጨፉት ወይንም ከቀያቸው የተባረሩት ቁጥር ዝቅተኛ ስለሆነ ሁኔታው እንዳይባባስ” በሚል አሳፋሪ ብሂል ጭፍጨፋውን ቸል አይሉትም። ከዚህ ላይ የማሳስበው ታዳሚዎች ስለ ዐማራው ጭፍጨፋ (ጀኖሳይድ) የተጠቀምኩበትን መስፈርት እንዲመለከቱት ነው። አንድ ዜጋም ቢሆን በማንነቱ መገደል የለበትም የሚለውን መርህ ከተቀበልን፤ በማንነትና በእምነት የሚደረገው የዐማራው ጭፍጨፋ ቀይ መስመር ካለፈ ወደ አርባ ዓመታት ይሆነዋል። እኔን የሚዘገንነኝ ህወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የዐማራው ሕዝብ  በተከታታይ በጋምቤላ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በመላው ኦሮምያ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝና በዐማራው ክልል ተጨፍጭፏል፤ ቆስሏል፤ አካለ ስንኩል ተደርጓል፤ ተባሯል።

ይህን አስመልቶ ትዝብቴን ልናገር። የፌደራሉ መንግሥት፤ የዐማራው ሕዝብ በማንነቱና በእምነቱ እየተለየና እየተነጠለ በተደጋጋሚ ሲጨፈጨፍ፤ ከቤትና ከንብረቱ ሲፈናቀል ለምን?

 1. የሃዘን መግለጫ አላወጣም?
 2. ጭፍጨፋውን አላወገዘም?
 3. ጭፍጨፋው እንዳይደገም የሚያስችል ድርጅታዊና ተቋማዊ እርምጃ አልወሰደም?
ተጨማሪ ያንብቡ:  አስጸያፊው የነዳጅ ዝርፊያ ከመርሓጽድቅ - መኮንን አባይነህ

ፕሬዝደንት ትራምፕ ግብፅን ደግፈው የኢትዮጵያን ግድብ “ቦምብ አድርጉ” ሲሉ፤ ከጀርባ ያለውን ሁኔታ መገምገም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ በዘውግና በእምነት የተከፋፈለች አገር መሆኗን ያውቃሉ። ይህችን በመውደቅ ላይ የምትገኝ አገር ከመደገፍ ይልቅ የሚያዋጣን ግብጽን መደገፉ ነው ብለው አስበው እንደሆነ ማጤኑ ይበጃል።

ለእኔ የግድቡና የዐማራው ህልውና የተያያዙ ናቸው። የዐማራው ሕዝብ በገፍ እየተጨፈጨፈና የራሱ አንጡራ መሬት በሆነው ግን ሆነ ተብሎ  ከቤኔ-ሻንጉል ጉሙዝ ጋር እንዲቀላቀል የተደረገው መተከል ተመልሶ ወደ ዐማራው ክልል መቀላቀል አለበት። ይህ ሲሆንና የዐማራው ህይወት ደህንነት ሲረጋገጥ የሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል። አሁን ግን እኔ ስገመግመው፤ ሽመልስ አብዲሳ እንደ ተናገረው አንድ ሶስተኛው የቤኒ-ሻንጉል ሕዝብ ኦሮሞ ክሆነ ዝንባሌው ክልሉን አጠቃልሎ የኦሮሞ ነው የሚባልበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። አዲስ አበባም ያለው አቅጣጫ ተመሳሳይ ነው።

አምስተኛ፤ የዐማራው ሕዝብ ከአንጡራ መሬቱ ተፈናቅሏል። የተፈናቀለበት መሰረታዊ ትርክት “መጤ ነህ” ስለተባለ ነው። መጤ ማን እንደሆነ፤ ፕሮፌሰር ሃብታሙ የጻፈውን በራራን ስገመግም ያቀረብኩትን መረጃ ማየቱ ብቻ በቂ ነው። “መጤና ነፍጠኛ” እያሉ ታላቁን፤ ኩሩውን፤ አገር ወዳዱን የዐማራውን ሕዝብ ከሞተላት ሃገሩ የሚያስወጡት ከሆነ ኢትዮጵያ ሌላ ስም በያዘ አገር እንደምትተካ የምንገምት ብዙ ኢትዮጵያዊያን ታዛቢዎች አለን። ይህ አይሆንም ብየ ከአንድ ምሁር ጋር ስከራከር ያለኝ፤ “አንተና ሌሎች ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሌሎች መሆኑን መቸ ነው የምትገነዘቡት?” ነው ያለኝ። ያሳፍራል፤ ያሳዝናል። ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም ዐማራውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም እያጠፋት ነው።

ስድስተኛ፤ ልዩ ልዩ ዘውጎች በብዛት በሚገኙበት ሁሉ፤ ለምሳሌ ኦሮሞውች፤ መብታቸው እንዲከበር ልዩ አስተዳደር ወይንም ቀጠና ተሰጧቸዋል። በኦሮምያ ክልል በግምቱ አስራ አምስት ሚሊየን የሚሆን ዐማራ ይኖራል። በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ግማሹ ዐማራ ነው ወዘተ። እኔን የሚያሳስበኝና ሁኔታው እንዲስተካከል አደራ የምለው ልክ እንደ ሌሎቹ ዘውጎች የዐማራው ሕዝብም በእነዚህ ክልሎች እስከኖረ ድረስ የራሱ ማንነት በሕግ እንዲከበርለትና ራሱን ለማስተዳደር እንዲችል የራሱ ልዩ ዞነ ወይንም ቀጠና ሊሰጠው ይገባል። የፌደራሉ መንግሥት ይኼን ለማድረግ የማይችልበት ምንድን ነው?

ሰባተኛ፤ የዐማራው ሕዝብ የተጎዳው በባጀት አመዳደብ ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ የዐማራው ክልል በፌደራል ባጀት አመዳደብ ሲገመገም ከሌሎቹ፤ በተለይ ከትግራይና ከኦሮምያ ክልሎች ጋር ተመጣጣኝ አይደለም። የዚህ ክፍተት አንዱ መነሻ በመለስ ዜናዊ መንግሥት ወቅት የዐማራው ሕዝብ ቁጥር በሁለት ሚሊየን ሶስት መቶ ሽህ ቀንሷል የሚል ውሳኔ ስለተደረገበት ነው። ባለሞያዎች ባደረጉት ተጨማሪ ጥናት የቀነሰው ቁጥር ከዚህ ሶስት ጊዜ ይሆናል የሚል መረጃ እንዳቀረቡ አውቃለሁ። ባጠቃላይ ስገመግመው የዐማራው ክልል ባጀት ከአስፈላጊው የማህበረሰባዊ እድገት ዝቅተኛነት (Human development index) ጋር አይመጣጠንም። በዚህም መስፈርት ስገመግመው፤ ይህ ክልል ተቆርቋሪ አለው ለማለት የምችልበት መስፈርት ፈልጌ አላገኘሁም።

ስምንተኛ፤ የጅዖ-ፖለቲካውን ይዘት ትኩረት እንስጠው። ይህም ማለት በሰሜንም ሆነ በደቡብ፤ የዐማራው ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በሚኖርበት ሁሉ ሲጨፈጨፍና ከመኖሪያው ሲባረር የሚታነቀው ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ የዐማራው ሕዝብ ጉረሮ ነው የታነቀው የሚል መልስ እናገኛለን። ከላይ በሶስት ቁጥር ያቀረብኩትን በአእምሮ ካርታ አውጥታችሁ ተመልከቱት። ይህ ሕዝብ መፈናፈኛ  እንዳይኖረው መሬቱና ንብረቱ ሲወሰድ ጉረሮው በመታነቅ (Economic strangulation) ላይ ይገኛል። አዲስ አበባም ቢሆን በዐማራው ነዋሪዎች ላይ ሲካሄድ የቆየው ጫናና ሁኔታ አስጊ ነው። “ልዩ ጥቅም” በሚል ሰበብ የሚደረገው ግፍና በደል ምሳሌ ነው።

በተጨማሪ፤ ጃዋርና ደጋፊዎቹ ጽንፈኞችና ትምክህተኞች ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍሉ (Heavy Price)” ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉትን እናስታውስ። በጭፍጨፋው ተከታታይነት ሲታይ፤ ክህይወት በላይ ምን ከፍተኛ ዋጋ ይከፈላል? በኢኮኖሚው ሲገመገም፤ ለህይወት ወሳኝ የሆነውን መሪቱን፤ ቤቱንና ሌላውን ንብረቱን ካወደሙት እንዴት ሊኖች ይችላል? ሻሸመኔ የሆነው ሌላ ቦታ አይሆንም ልንል የምችልበት ምን የታመነ መረጃ አለን? የለንም።

ዘጠንኛ፤ ስርዓቱ፤ ማለትም፤ ፖሊሲውና መዋቅሩ ካልተለወጠ በስተቀር የዐማራው ህልውና እንዴት ሊጠበቅ ይችላል? ሁኔታውን ያባባሰው ራሱ በዘውግና በቋንቋ የተዋቀረው ሕገመንግሥትና የክልሉ አስተዳደር ነው። ይህ ሕገ መንግሥት የዜግነትን መብት ቅድሚያ በሚሰጥ ሕገመንግሥት ካልተቀየረ በስተቀር ችግሩ ሊፈታ አይችልም። ዐማራው ኢላማ መሆኑ ይቀጥላል። እኛ ስንት ሰው ሞተ? እያልን ከማልቀስ በስተቀር ፋይዳ ያለው ነገር ለመስራት አንችልም። ፋይዳ ያለው ነገር ማለቴ የዐማራው ሕዝብ እልቂት እንዲያቆም በተለያየ መንገድ ስራችንን መስራት ይገባናል ለማለት ነው።

አስረኛ፤ የዐማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ መኖሩና መስራቱ ለኢትዮጵያ ታላቅነት፤ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ወሳኝ ነው። ክብር ነው። አብሮነትን ያጠናክራል፤ ልማትን ያጠናክራል። በተለይ ኢትዮጵያዊነትን (ማለትም ብሄራዊ መለያችን) ያጠናክራል። ዘጠኝ መንግሥታት ኢትዮጵያን ሊወክሏትና ሊታደጓት አይችሉም። ይህን እንቀበል።

ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ከውስጥ ወደ ውጭ በሚደረግ ትንተና ነው (Fundamental structural and organizational change from within). በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄድው ጭካኔ፤ ጭፍጨፋና ተዛማጅ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በግልጽ እየሰፋና እየተባባሱ ሄዱ እንጅ የዐማራው የህልውና ችግር ሁኔታ የተጀመረው ከዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመታት በፊት ነው።

ለምሳሌ፤ ከፋፍሎ ለመግዛትና ለማጥቃት ካልሆነ በስተቀር፤ ዐማራው ባልለመደውና በማይፈልገው መንገድ ለምን በአዴን የተባለ የዘውግ ፖለቲካ ድርጅት ተመሰረተለት? ማን መሰረተው? ለማን ጥቅም? ይህ ድርጅት ለዐማራው ሕዝብ ተጠቂነት ግብአት እንዳደረገ ምን መረጃ አለ? ሁኔታው ተለውጧል ወይንስ እንዳለ ነው?

በሕገመንግሥት፤ በስርአትና በፖሊሲ ደረጃ ምንም የተቀየረ ሁኔታ የለም። ሰሞኑን የሆነውን ብቻ ምሳሌ ላቅርብ። አብን የተባለው ድርጅት የዐማራው እልቂት መቆም አለበት በሚል የተቀደሰ ምክንያት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያቀደውን ማንነው የከለከለው? በዐማራው ክልል የሚካሄደውን የከለከለው የዐማራው ብልፅግና ፓርቲ ነው። በአዲስ አበባ የታቀደውን የፌደራሉ መንግሥት እንደሆነ እገምታለሁ። ሁለቱ ግን ሳይመካከሩ ይህን ውሳኔ አያደርጉም። ዐማራው እየተጨፈጨፈ ብልፅግና ሊኖር ይችላል? አይችልም!!

ጥቃቅን ለውጥ መኖሩን ከላይ አቅርቤዋለሁ። በማንኛውም አገር ቢሆን ጥቃቅን ለውጥ የማያደርግ መንግሥት ህልውና የለውም። እስከማውቀው ድረስ የውጭ እርዳታ ለማግኘት ቢያንስ ጥቃቅን ውጤት ማሳየት የተለመደ ነው። ህወሓትም እኮ በኢኮኖሚው ብዙ ለውጥ አሳይቷል፤ ያውም ሌባ ሆኖ።

የችግሩ እምብርት ግልጽ መሆን አለበት። ህወሓት በዐማራው ስም የፖለቲካ ድርጅት የመሰረተለት ለራሱ አጎብዳጅና አገልጋይ ሆኖ እንዲያገለግል መሆኑን ብዙ ጥናቶችና ምርምሮች ያሳያሉ። ይህ ህወሓት አመቻችቶ የፈጠረው ድርጅት የዐማራው ሕዝብ በያለበት ኢላማ እንዲሆን ያመቻቸው በ1986 ዓ.ም. የፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ነው።

ይህ ድርጅት ምን አለ? ዐማራውን በጅምላ ነፍጠኛውና ትምክህተኛው ዐማራ ነው ብሎ ካወገዘው በኋላ፤ የሌሎቹን ዘውጎች መሬቶች ነጥቋል፤ ወሯል፤ ሰፍሮባቸዋል፤ ወርሷቸዋል ብሎ ከሰሰው። መፈክሮችን አወጣና በተነ። ደጋፊዎችን አስፋፋ። ይሕ ክስ ወያኔ በማኒፌስቶው ካወጣው ጋር ተመሳሳይ ነው። ተደጋጋሚ ቢሆንም ላጠናክረው። ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ትርክቱን ሕዝብ እንዲቀበለውና በወጣቱ ትውልድ ሰርፆ እንዲገባ ህወሓትና የፈጠረው ድርጅት፤ ማለትም በዐማራው ስም በነ በረከት ሰምኦን ይመራ የነበረው ህወሓት-ፈጠር ድርጅት ነፍጠኛውንና ትምክኽተኛውን ዐማራ የሚያወግዙ መፈክሮችን በጎንደር፤ እንደ ፋሲል ባሉ ታላላቅ ግንቦች፤ በወረታ በጋይንት ከተማዎች፤ በደጀን ተራራና በዐባይ ወንዝ አፋፎች ላይ ለጠፉ። በዐማራው ክልል የተለጠፉበት ዋና ምክንያት፤ የስነ ልቦናው ጦርነት በራሱ በዐማራው ሕዝብ ወጣት ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዲካሄድ በማሰብ ነው።

ይህንን የአመለካከት ትርኢትና ትርክት የተቀበሉ የዐማራ ካድሬዎች ተለውጠዋል ብሎ ማሰብ ራሱ ችግር ነው። የአስተሳሰብ ለውጥ ከግል ጥቅም ጋር ሲያያዝ መዘዝና አደገኛ ነው (It is lethal)። በቀላሉ ይፈታል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው። ካድሬዎቹ ዐማራም ቢሆኑ በጥቅም የተበከሉ ስለሆነ በቀላሉ ሊለወጡ አይችሉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የለሊት ወፍን ማን ገደላት? - (ከደራሲና ገጣሚ መኳንንት ታዬ)

የዐማራው ሕዝብ በራሱ ስም በተመሰረተው በዐማራው ክልል ሳይቀር ክስ ተመሰረተበት፤ ነፍጠኛና ትምክህተኛ የሚል ክስ። ቀስ በቀስ ጥቃቅን ዘውጎች ብቅ ብቅ አሉ። ዐማራው “ቅማንት፤ አገው፤ ዐማራ” ወዘት በሚሉ የማንነት መጠሪያዎች እንዲበታተንና እርስ በእርሱ እንዲናከስ ተደረገ። መንደርተኛነት ልክ እንደ መሳፍንት ዘመን ስር ስደደ። ስሜን ጎንደር፤ ደቡብ ጎንደር የሚሉት ልዩነቶች ስር እንዲሰዱ ተደረገ። የስነልቦናው ጦርነት ጥልቀት እየያዘ በዐማራው እምብርት ላይ አተኮረ። በቅርቡ፤ የጎጃም ፓርቲ የሚል ተመስርቷል ተብሎ ሲለፈፍ፤ ጎንደሬዎችም “እኛም የጐንደር ፓርቲ እንመስርት ሲሉ” ከስብሰባው ወጥቻለሁ። የዐማራውን ሕዝብ ብሶት ለሕዝብ ያቀርባል ተብሎ የተመሰረተው የአስራት ሜድያ ደክሞ ሲንገዳገድ ሌላ አስራትን የሚተካ ሜድያ ይመስረት ሲሉም ሰምቸ ታዝቤያለሁ። የዐማራው ችግር በታላቁ በዐማራው ሕዝብ ስም የሚነግዱት ጭምር ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ።

በዐማራው ስም የተቋቋመው ፓርቲ ያባባሰው ሁኔታ ምንድን ነው?

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በዐማራው ላይ የተደቀነውን የሃሰት ትርክት ሌሎች የዘውግ የፖለቲካ ድርጅቶች በሰፊው አስራጭተውታል፤ አዛምተውታል። በተለይ በደርግ መጨረሻና በሕወሓት መራሹ ሃያ ሰባት ዓመታት የተወለደውና ያደገው ወጣቱ ትውልድ እንዲያምነውና እንዲታገልበት አድርገውታል። ዐማራውን እየለዩ መጨፍጨፍ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተፈጠሩ ማለት ነው።

ሁኔታውን ደግሞ ያባባሰው በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ሲደነገጉ ነው። “አሳዳጅና ተሰዳጅ” ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ያደረገው ይህ የኢህአዴግ ሕገ መንግሥስትና የተከተለው የፖለቲካ ሂደት ነው። የፌደራሉ ባለሥልጣናት ዐማራው በገፍ ሲጨፈጨፍ መግለጫ የማያወጣበትና ሁኔታው ይባባስል ብሎ ችላ የሚልበት ምክንያት የራሱ በዐማራው ስም የተመሰረተው ፓርቲ ካድሬዎች ለዐማራው ሕዝብ ደንታ ስለማያሳዩ ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ ለሃጫሎ ከፍተኛ ሃዘን፤ ውግዘትና ሌላ ተደርጓል። አግባብ አለው። ይህን ወጣት የገደሉት ለፍርድ መቅረባቸውም አግባብ አለው። በተመሳሳይ ግን፤ ለዐማራው እልቂት ለምን የሚፀፀት ባለሥልጣን ጠፋ? ብየ እጠይቃለሁ። መግለጫ “ብናወጣና ጭፍጨፋውን ብናወግዝ ሁኔታው ይባባሳል” የሚለው ምክንያት ተመጣጣኝ መልስ ሆኖ አላገኘውም።

ለማጠቃለል፤

 1. ዘውግንና እምነትን መለያዎች አድርጎ በዐማራው ላይ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ/እልቂት/ጥቃትና ተመሳሳይ ሰብአዊ ጭካኔዎች እንዳይባባሱ ያደረገውን ሁኔታ ስገመግመው ተስፋ የሚሰጠኝ መስፈርት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነትና አብሮነት ነበር፤ ግን ይህ የቆየ ትሥስር እየላላና ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት እየተሸጋገረ ነው። እልቂቱ በሁላችንም ላይ እንደተፈጸመ አየዋለሁ። የማያሻማ እርምጃ ካልተወሰደ የብዙ ሽህዎች ደም መፍሰሱ አይቀርም።

 

 1. በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን ጭፍጨፋ ማውገዝና መተቸት “የዐማራ ብሄርተኝነት ነው” ብሎ መተቸት አግባብ የሌለው የችግሩን ጥልቀት ማሳነስና መሸሽ ነው። መምህር ታየ ቦጋለ፤ ኦባንግ ሜቶና ሌሎች ጭፍጨፋውን ማውገዛቸው ትክክልና እውነተኛ የኢትዮጵያዊነት መለክያ መስፈርት ሆኖ አየዋለሁ። ለማስታወስ፤ ጎንደሬው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ካለው ጋር ተመሳሳይነት አለው። የዐማራው ሕዝብ ንጹህ ደም ደማችን መሆኑን መቀበልና ማውገዘ የተቀደሰ አቋም ነው። ለሰብአዊ መብት ወይንም ለፍትህ ቆመናል ብለን ለመናገር የምንችለው የኦሮሞ ሆነ የዐማራ፤ የጉራጌ ሆነ የሶማሌ፤ የአኟክ ሆነ ወይንም ሌላ ህይወት ዋጋ አለው የሚል ሁሉን አቀፍ መርህ ስንቀበል ብቻ ነው። በተጨማሪ፤ ዘውግ ወይንም እምነት ተኮር ጭፍጨፋን ከግጭት መለየት አለብን። እንድፈር፤ “የዐማራው ደም ደማችን ነው” እንበል።

 

 1. የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያ ስራው መንግሥት መኖሩን የሚያሳይ እርምጃ በማያሻማ ደረጃ መውሰድ ነው። በወለጋ የተካሄደው የ 200 ዐማራዎች ጭፍጨፋ ራሱ ለዶር ዐብይ መንግሥት መኖር አለመኖር ዋና መስፈርት ሆኗል። ስለዚህ፤ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ይህን እልቂት ያካሄዱትን ሽብርተኞችንና መዋቅራቸውን መስበር ነው። ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። መግለጫ ማውጣት ብቻ በቂ አይደለም። ጊዜ ቢወስድም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለእልቂቱ በሃላፊነት መጠየቁ የማይቀር ነው።

 

 1. በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ በኦሮምያ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የተካሄዱት እልቂቶች/ጥቃቶች እንጅ ግጭቶች አይደሉም። የተጨፈጨፉት ግለሰቦችና ቤተሰቦች ገጀራ፤ ካላሺንኮቭ ወይንም ሌላ መሳሪያ ይዘው ወገኖቻቸውን አልገደሉም። ለዚህ ነው ጭፍጨፋ እንጅ ግጭት አይደለም የምለው። ብዢታዎች ይታያሉና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶችና ሌሎች በኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ላይ በተከታታይ የሚጽፉ ተቋማትና ምሁራን የዐማራውን እልቂት ትኩረት ያልሰጡበት መስረታዊ ምክንያት ምን እንደሆነ ጥያቄ የማቅረብ ግዴታ አለብን።

 

 1. ለዐማራውና ለሌሎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው ለሚያምኑ ንጹህ ወገኖቻችን ጭፍጨፋ/እልቂት/ጥቃትና መፈናቀል የፖሊሲ፤ የተቋማትና የመዋቅር ሰንሰለቶችን የጣለውና ወጥመዶችን የዘረጋው አካል በአንደኛ ደረጃ ህወሓት ነው። በሁለተኛ ደረጃ አጋር የሆኑት እንደ ኦነግ ያሉት የብሄር ጽንፈኛ አካላት ናቸው። በውጭ ሆኖ የሚደግፋቸው ኃይል ደግሞ የግብፅ መንግሥት ነው። እነዚህ አጥፊ ኃይሎች የሚሰሩት እየተናበቡ ነው።

 

 1. የዐማራውን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ ዙሪያ ህወሓትና ኦነግ ምንም ልዩነት የላቸውም፤ የመሬት መስፋፋትንም ጨምሮ። በሰሜን ህወሓት ሰቲት ሁመራን፤ ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትን፤ ራያንና አዜቦን ወደ ታላቋ ትግራይ ለማጠቃለል አቋም ወስዷል። በተመሳሳይ፤ ኦነግና መሰል የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላው ቀርቶ ወሎ የኦሮሞ አካል ነው የሚል የጋራ አቋም አላቸው። ሽመልስ አብዲሳ “37 በመቶ የሚሆነው የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪዎች ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው” ያለው አካባቢውን ወደ ኦሮሞያ ለማጠቃለል ባለው እቅድ መሰረት ነው ብል የተሳሳኩ አይመስለኝም። በአዲስ አበባ ላይ የሚካሄደውም ሽሚያም ቢሆን ከዚህ የዘውግ የበላይነት ሽሚያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

 

 1. የኢትዮጵያን የወደፊት እድልና በዐማራውና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር ምኞትና ተስፋ ያላቸው ወገኖቻችን ኦሮዐማራ የሚለው፤ ለአሁኑ ለውጥ ወሳኝ ሚና የተጫወተው የፖለቲካ ዘዴ (Tactical alliance between Amhara and Oromo political elites) ቀላል አይደለም። ስኬት አምጥቷል። ሆኖም፤ የብዙ ዘውጎች አገር በሆነችው ኢትዮጵያ ኦሮአማራ የሚለው የፖለቲካ ስልት በዘላቂነት አይሰራም። የሚያዋጣው አማራጭ በዜጎች መብት ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ውይይትና ድርድር (All-inclusive national dialogue and consensus) ማድረግ ብቻ ነው። በዘውግና በቋንቋ የተዋቀረው ስርዓት ለኢትዮጵያ አይመጥንም።

 

 1. ህወሓትና ኦነግ በፖለቲካ ስልጣንና በኢኮኖሚ የበላይነት ስልት ቢለያዩም አሁንም ቢሆን የዘውጉ ስርዓት ይሰራል በሚለው ግን ይስማማሉ። ብልጣ ብልጡ ህወሓት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የፋይናንስ አቅም አውድሞና መዝብሮ፤ የአገራችንን ካዝና ቀፎ አድርጎት ነው ወደ መቀሌ ሄዶ የመሸገው። እኔ የምቀበለው አንድ ሃቅ፤ ህውሓትን የተካው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህችን አገር መልሶ ለመታደግና እንዳትፈራርስ ለማድረግ የገጠመው ተግዳሮት ቀላል አለመሆኑን ነው። በቀጥታም ሆነ በረቂቅ፤ የዐማራው እልቂት ከህወሓት፤ ከኦነግ ሽኔ፤ ከጅሃዲስቶችና ከግብፅ ረዢም ክንድና፤ በተለይ ህወሓት በገፍ ከዘረፈው ብዙ ቢሊየን ዶላር የመግዛት አቅም ጡንቻማነትጋር የተያያዘ መሆኑን አምናለሁ።

 

 1. ለኢትዮጵጵያ ፌደራል መንግሥት መሪዎችና ባለሥልጣናት የማቀርበው ምክር ለዐማራው እልቂት ትኩረት የምትሰጡብት ወቅት ዘግይቷል። የዐማራው ሕዝብ ህልውና በቀጥተኛ ደረጃ ከኢትዮጵያ ህልውናና ከኢትዮጵያአዊነት እሴት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተቀበሉ እላለሁ። አለያ፤ እናንተም ቢሆን ለእልቂቱ ተጠያቂዎችና ሃላፊዎች ናችሁ።

ይህንን ምክር የማቀርብበትን ምክንያት በአጭሩ ላቅርበው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐብይ ሲመረጡ የዐማራው ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዘጠና በመቶ በላይ በሚገመት ደረጃ ደግፏቸው ነበር። የዚህን ግዙፍ ድጋፍ ዋጋ ማጤን ለሃገራችን ቀጣይነት ይጠቅማል።

 1. ማንም የማይክደው ሃቅ አለ። ይኼውም ኢትዮጵያ በያቅጣጫው ተከባለች። ኦነግ ሼኒና ህወሓት የሽብርተኛው አካል ናቸው። ይህች ታሪካዊና ጥንታዊ አገር በዘላቂነት እንድትቀጥል፤ ከድህነት፤ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት፤ ከኋላ ቀርንት መጥቃ እንድትነሳ ለምንመኝ አገር ወዳዶች ሁሉ ከምርጫና ከዲሞክራሲ በፊት በዐማራው ዘውግ ላይ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ/እልቂት/ጥቃት በማያሻማ ደረጃ መወጣት ታሪካዊ ግዴታችን ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት ከንጹሃን የዜጎቿ ደህንነትና ፍትህ ጋር አብሮ የሚሄድ እንጅ ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን አሰምርበታለሁ።    

ኢትዮጵያን የደም አውድማ የሚያደርጉ ኃይሎች በሙሉ ይወገዙ!!

የመጨረሻው ክፍል አምስት ስለ ሰብሳቤ ብሄራዊ አማራጭ ያለውን ሁኔታ ያቀርባል።

November 2, 2020

 

1 Comment

 1. The lazy sissy Abiy Ahmed’s administration chooses to attack the victims than the genociders.
  The failed Abiy Ahmed’s administration found it easier to intimidate and quiet down the Amara victims rather than going after the criminals , so the Abiy Ahmed’s administration is commiting state terrorism promoting the Amara genocide instead of working to bring justice to the ethnic Amara victims of genocides de , Abiy Ahmed’s administration need to be brought to justice for the crimes against humanity they committed.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share