November 2, 2020
2 mins read

ወይ አገሬ ሆይ ዝንታለም መከራ ሁልጊዜ ዋይ ዋይ (ዘ-ጌርሣም)

ወይ አገሬ
(ዘ-ጌርሣም)
ወይ አገሬ ሆይ
ወይ ወገኔ ሆይ
ዝንታለም መከራ ሁልጊዜ ዋይ ዋይ
ሰላም ከዓይን ዕርቃ መኖር ይህ ነወይ
ትናንተ መደመር
ዛሬ መደናበር
ይቅርታው ተረስቶ
ኽውከት ተተክቶ
ሁሌም የናፈቅነው የሰላም አየር
አገኘነው ስንል ይርቀን ጀመር
ትናንት በአንድ ሁነን
ግፍን ተቋቁመን
ህይወትን በመክፈል
ለአንድነት ስንምል
ከጥላቻ ፍቅር
ለትውልድ እንዲቀር
ብለን ተማምለን
ያለፈውን ትተን
ወደፊት በማየት
ደግ ደጉን በማውሳት
ግንቡን አፈራርሰን
በድልድይ ተክተን
አልነበረም ወይ በቃል የተገባው
ድንገት ምን መጣና ምላስ የታጠፈው
ወይ አገሬ ወይ
ወይ ወገኔ ሆይ
ዝንታለም መከራ ሁልጊዜ ዋይ ዋይ
እስኪ ምን ጎደለ
ምኑ ጎረበጠ ያልተደላደለ
የትናንቱ ደስታ
እንዴት ተቀየረ በዛሬው ዕሪታ
ተጋብተው ተዋልደው
ልጆችን አፍርተው
መከራና ደስታን በጋራ ተካፍለው
በጋራ ዕድር ታቅፈው
አብረው እንዳልኖሩ
ምን ሰይጣን ገብቶ ነው
ህዝብ የሚያጫርሰው
ያውም በአሁኑ ውቅት
መቅሰፍት በበዛበት
እንዲህ መጨካከን
ለጥቅም ተገዝተን
ትናንት የበሉን
እኛኑ ሲያባሉን
በቃ የማንለው
ምን ቢጉልብን ነው
ወይ አገሬ ሆይ
ወይ ወገኔ ሆይ
ዝንታለም መከራ ሁልጊዜ ዋይ ዋይ
ሰላም ከዓይን ዕርቃ መኖር ይህ ነወይ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop