አንድነት ይበልጣል ከሐዋሳ – ጥቅምት 11 / 2013
ይህን ትዝብት እንድጽፍ ያነሳሳኝ፣ አቶ ታዬ ደንደአ በፌስ ቡክ ገጹ ¨ማህበራዊ ህክምና!¨ በሚል ርዕስ የለጠፈው ትልቅ ቁምነገር ያዘለ አጭር ጽሁፍ ነው፡፡ ጽሁፉ ማኅበራዊ ሕክምና በሚያስፈልጋቸውና ወያኔ ጥሎ ባለፋቸው ሦስት ¨ከባባድ ጠባሳዎች¨ ላይ ያተኩራል፡፡ ለአቶ ታዬም ማስታወሻ መነሻ የሆነው በትናንትናው ዕለት (10/02/13) በካፒታል ሆቴል፣ በኢሰመጉ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የታዘበው ነገር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ታዝቦአል፡፡ እዚህ ለመዳሰስ የወደድኩት ስለሁሉም ጠባሳዎችና ሊደረግላቸው ስለሚገባው ማሕበራዊ ሕክምና አይደለም፡፡ በተለይ የሕዝባዊ ተቋማትን ጠባሳና ሊደረግላቸው ስለሚገባው ተቋማዊ ሕክምና (መንግሥታዊ ድጋፍ) ነው፡፡
የቅርቡን ጊዜ ብቻ እንኳን ብንወስድ (27+17) ለ 44 ዓመታት ኢትዮጵያን የደፈጠጡ አገዛዞች ካደረሱብን ከባድ ሐገራዊ ጉዳቶች ዋነኛው ሕዝባዊ ተቋማትን ሽባ ማድረጋቸው ነው፡፡ በተለይ አብዛኞቹ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምን ያህል እንደተሽመደመዱ ለማወቅ በይበልጥ የአመራሮችንና እንዲሁም የሠራተኞቻቸውን ሰብዕና፣ የሥነምግባር ቁመናና የአገልጋይነት ስሜት እንዲሁም አደረጃጀታቸውንና አሠራራቸውን መፈተሸ ይበቃል፡፡ ወያኔ ከውጭና ከውስጥም ሰርጎ ያደረሰባቸው ጉዳት እንዳይበቃ፣ የበጎ አድራጎትና የሰብዓዊ መብቶች ነጋዴዎች ደግሞ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን ከውስጥ ሆነው እንደ መዥገር ደምና ኃብታቸውን እየመጠጡና እያተረፉባቸው ኖሩ/ አሉ …፡፡ ¨ወደገደለው¨ ለመግባት፣ ድርጅቶቹን እንደ ተቋም ተጠያቂ ማድረግና መግፋት ጥቅም የለውም፤ ሰለባውን መኮነን ይሆንብናል፡፡ ይልቁንስ በተቻለ ፍጥነት ታድሰውና አንሰራርተው ወደ ተፈጥሮ ተልእኮና ሥራቸው እንዲገቡና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ዋናው ቁምነገር፡፡
መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሕግና ተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን ማስተካከሉ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ የድርጅቶቹ ችግር ግን በነዚህ እርምጃዎች ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ድርጅቶቹን ለማከምና ለውጥ ለማምጣት ረዥም ጊዜ፣ የተባበረና የተቀናጀ የውስጥና የውጭ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ጥረቱ የአመለካከት ለውጥንም ይጨምራል፡፡ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ለመንግሥትም ሆነ ለገዢው ፓርቲ (ለነገሩ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ) እንኳን ተቃዋሚ ሊሆኑ ተፎካካሪም አይደሉም፤ አጋር መሆናቸውን ሁሉም ወገን በሙሉ ልብ ሊቀበል ይገባል!! ስለዚህ ጠንክረው ሥራቸውን እንዲሠሩና የተቋቋሙለትን ማሕበረሰብ (የማሕበረሰብ ክፍል) በተገቢ እንዲያገለግሉ በመንግሥት በኩል በአቅም ግንባታና በክትትል የታጀበ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
አቶ ታዬ፤ ገና በቂ ትኩረት ያላገኘውን ትልቁን የሐገራችንን ሕመም ነው ያነሣው፡፡ የሚበዙት ሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት ተሸመድምደዋል፡፡ ማሕበረሰብ ከማገልገላቸው ይበልጥ መሪዎችና ሠራተኞቻቸው ራሳቸው የሚገለገሉባቸው ሆነዋል፡፡ ከሚሰቃዩበት ከዚህ በሽታቸው እንዲያገግሙና ለውጥ ወደሚያመጣ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ብልህ ከሆነ የለውጥ መንግሥት የሚጠበቅ ትልቅ ተግባር ነው፡፡ መንግሥት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሚገባ የተጠና፣ የተደራጀና ዘላቂ ድጋፍ ማድረግ ያለበት አንድም ሕዝብን ማገልገል ዓላማውና ግዴታው ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛ ከመንግሥት የማመቻቸትና የማሣለጥ አገልግሎት ማግኘት መብታቸው ነው፡፡ ሦስተኛው ሥልታዊ ምክንያት (ጥቅም) ደግሞ መንግሥት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባደረገላቸው ድጋፍ ልክ እነርሱም አስተማማኝ አጋር ሆነውት ስለሚደግፉትና ሸክሙንም ስለሚያቃልሉለትም ጭምር ነው፡፡ እንደ ወያኔ ያለ ጸረ ሕዝብ መንግሥት፣ ጠንካራ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን ወይ ቀድሞውንም እንዳይፈጠሩ ያደርጋል፣ አለያም ያጠፋቸዋል ወይም አድክሞ ስማቸው ብቻ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ለሕዝብ ወገንተኛ የሆነ መንግሥት ግን የሲቪል ማሕበረሰብ ምህዳሩን ከማስፋትና ከማመቻቸትም አልፎ ለድርጅቶች አስተማማኝ ምርኩዝና አለኝታ ይሆናል፡፡ የሲቪል ድርጅቶች ኤጀንሲ በዚህ መንፈስ የተቃኘ የድጋፍ ሥራ ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ቢፈተሽ ጥሩ ነው፡፡
በመንግሥት ኃላፊነትና ሚና ላይ ማተኮሬ የየድርጅቶቹን ውስጣዊ የተኃድሶ ኃላፊነትና ሚና ዘንግቼ አይደለም፡፡ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ አባላትና በአጠቃላይ ተደራሽ የማሕበረሰብ ክፍሎችም ሊወጡት የሚገባው የተኀድሶ ሃላፊነትና ሚና ወሳኝና ቀዳሚም ነው፡፡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቅድሚያ ወደውስጥ ወደራሳቸው መመልከት መጀመር አለባቸው፤ በተጨማሪም ትናንት ስለደረሰባቸው ጉዳት መቆዘማቸውንና ሮሮ ማሰማታቸውን አቁመው ወደፊት በመመልከት ልዩነትና ለውጥ አምጪ ሥራን መጀመርና መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በቅድሚያ ውስጣቸውን ፈትሸው ራሳቸውን ማስተካከልና ለጊዜው በሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ላይ መገኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ይህንን በስፋትና በጥልቀት ልናየው ይገባል፡፡ ፈጣሪ ይርዳን!