ሸገር
ዳር እስከዳር ነዶ ሀገር
ሞቋል ደምቋል
የፈረንጅ ሣቅ መስሏል ሸገር
ማሽላኛ
ውስጡ ከስሎ
በከበባው ተሸብሮ
በወረራው ልቡ ቆስሎ
ከተሰነይ ናቅፋ አፋፍ
ከወለጋ ሐረር ጠረፍ
ተወርውሮ የሮም ቋያ
አራት ኪሎ ሲፈነዳ
ማየት ሆኗል የርሱ እዳ
ተፈራርቆ ሲጸዳዳ።
ያሁኑ ግን መጥቶ አያልፍም
ያልከሰለ ሳያከስል
ያልፋመውን ሳያፋፍም
እንዳለፉት መጥቶ አይሄድም
ሁላችንን ሳያወድም።
(ለምን? ካልሽኝ የኔ እህት
ለምን? ካልከኝ የኔ ወንድም)
ወራሻችን ባሕር ከቦ
መሞቱ ነው ተቁለጭልጮ
ቶሎ በሉ አታቁሙት
ማቱን አምጡት እነ ሌንጮ*
*ትውልዱንና አስተሳሰቡን የባእድ ተልእኮ ተሸካሚነቱን (ደቀ መዛሙርቱንም) ወክሎ የገባ ስም፣ ለቤት መምቻ እንዲመች የተመረጠ (አዎ ቅኔ ነው)።
ምርጫ
አህያና /ዱላ ይዘህ
አንተ ስትሞት/ ተወዝውዘህ
ዝሆን ጭኖ ጥሩር ለብሶ
ሕግ አውጥቶ ሕግ ገስሶ
ምርጫ መጥቷል ብሏል ንጉሥ
ተዘጋጁ ለፈረስ ጉግሥ
ወሳኝ ክስተት ነው ሚሆነው
ምርጫው መኖር ወይ መሞት ነው።
መኖር ካሻህ እኛ ጋር ና
ተደማሪ ብልጽግና
መሞት ካሻህ ያው ጎዳና
የቆንጨራ የአጣና
የክትባት የኮሮና።
ባልደራሱ*
አንዱ በታንክ አንዱ በእግሩ
ከሆነማ ውድድሩ
ሁሉም ካልገባ ከጉግሡ**
ተቀምጦ በፈረሱ
ምን ይሠራል ባልደራሱ?
ፈረስ በሌለበት ሜዳ
በእግረኛ ላይ ታንክ ሲነዳ
ጭፍለቃውን ከመመስከር
ፍንቀላውን ከመዘከር
የሚያልፍ ተግባር አለው ፋይዳ
ባልደራሱ የሀገር ኦዳ?
* ባልደራስ = የፈረስ ሹም
ደራስ = ፈጥኖ ደራሽ ፈረስ
** ጉግሥ = በፈረስ የሚደረግ የአባሮሽ ግጥሚያ
ፊርማ
ብራና አትጨርሱ አይለቅ ቀለሙ
አትፈራረሙ
እናንተ ሳትመጡ ገና ከመቅድሙ
የአንድነቱ ፊርማ ተጽፏል በደሙ።
ወክሉኝ ሳይላችሁ — ኖራችሁ በስሙ
ለሚድያ ፍጆታ — ድራማ ስትደርሙ
በምርጫ ጨዋታ — በፌዝ ልትከርሙ
አበል እንዲከፍል — ይሄ ማነው ስሙ?
በሉ አታላግጡ — እነ ጸጸት እርሙ
በናንተ ጦስ መስሎን — ሲያልቁ የከረሙ።
እኛ አንፈልግም ፊርማ በየወንዙ
ይታወቃልና ጦስና መዘዙ
የሩቁን ብንተወው ጋዲሳ ሆጋንሳ
ስንት እልቂት አመጣ ስንት እሳት አስነሳ?
ካሥሩ ፊርማችሁ
ይሻለናልና ያ አሠርቱ ቃላት
በሰላም ያኖረን የኦሪቱ ጽላት
ሁለት ብልጽግና
ከኦነግ እስክ አብን
ምእመን ተቃጥሎ እርር ሲል ድብን
አትደርሱለትም እንዳትደርሱብን
አትፈራረሙ
አትፈርሙልን አትፈርሙብን!