ሤራና ግድያ ሀሤራና ግድያ ሀገርን ያፈርሳል እንጂ አይገነባም! – አሣምነው ጽጌ

ትንቢቱ ደረሰ (ከአዲስ አበባ)

ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ የከተብኩት ከአንድ ዓመት በፊት እ.አ.አ ኦገስት 20/2019 ነው፡፡ ያኔ የተረኞች ቅብጠት እንዳሁኑ ወጥ አልረገጠም ነበር ወይም ለብዙዎች ዜጎች ስሜቱ የአሁኑን ያህል ወደ ውስጥ ሰርፆ አልገባም፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ! ሀገራችን ከቀን ወደ ቀን ወደ ሞት አፋፍ እየሄደች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ሁላችንም ፈዘንና ደንግዘን ቁጭ ብለናል፤ አንዳንዶቻችን ከአሁን አሳዛኝና አስደንጋጭ ልምምዶች ተነስን ወደፊት የሚሆነውን ስለምንረዳ ራሳቻችንን በጭንቀት ልናሳብድ የደረስን አለን፤ አንዳንዱ ምንም የማይመስለው ደነዝ ቢጤም አለ – የማይሞቀው የማይበርደው፡፡ ተረኞችም ተያይዘን የምናልቅበትን ብልሃት ሁሉ እየፈለጉ በተግባር እያሳዩን ነው – ማን ምን ያመጣል በሚል ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ዕብሪት ተሞልተው አማራን ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ እስከመከልከል ደርሰዋል፡፡ ዶ/ር ‹አሻግሬ›ም ሀገር ስትጠፋ የእግር ኳስ ዳኛ ይመስል መሀል ቆሞ እርሱ የሚደግፈው ወገን ግብ እንዲያስቆጥር የሚሻ መሆኑን በሚያሳብቅ ፍርደ ገምድል ዳኝነት የማይቀር የሚመስለውን ሤራና ተንኮል የተሞላበት የፖለቲካ ጨዋታ የመጨረሻ ግጥሚያ እየመራ ነው፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፣ አሸናፊው የትኛውም ወገን ይሁን ተጎጂዎቹ ግን ሁሉም ወገኖች መሆናቸውን የተረዳ ወገን ያለ አይመስልም፡፡ እልህ ቤት ያጠፋል፤ እልህ ትዳርን ያፈርሳል፤ እልህ የወዳጅነትን ክር ይበጥሳል፤ እልህ ሀገርን ብትንትኗን ያወጣል፡፡ ወያኔን እልህ ቢያሳብጠው፣ ኦነግ/ኦህዲድን እልህና ዕብሪት ቢያናፍለው፣ አክራሪ ኦሮሞን ተረኝነት ቢያሳብደውና ይሠራውን ቢያሳጣው … የቁርጥ ቀን የመጣለት ግን ሁሉም ደብቁኝ ደብቁኝ ማለቱ አይቀርም፡፡ ጉዳቱ ደግሞ በተለይ ለተራው ዜጋ ተትረፍርፎ ይደርሳል፡፡ ዛሬ ትግራይ በዘረፋ በተካኑ ልጆቿ ምክንያት ከአፍ እስካፍንጫዋ ስለታጠቀች አሸናፊነትን ማረጋገጥ አትችልም፤ ዛሬ ኦነግ/ኦህዲድ የሀገሪቱን ካዝናና ጓዳ ጎድጓዳ ልክ እንደሕወሓት በአባላቱ ስለተቆጣጠረ አሸናፊነትን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ አሸናፊነት በጉልበትና በሤራ አይረጋገጥም፡፡ “ሕወሓት ለምን ወደቀ? ደርግ ለምን ወደቀ? አፄዎች ለምን ወደቁ? የአምባገነኖች መጨረሻ ብዙውን ጊዜ አስጠሊታ የሚሆነው ለምንድንነው?” ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል፡፡ የኋላ ቁጭት ዋጋ የለውም፡፡

አሁን መደረግ ያለበት ዋነኛ ነገር ራሳቸው ከማይስማሙ የሥልጣን፣ የሀብትና የዝና ሱስ ከሚያናውዛቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ብዙ ከመጠበቅ ይልቅ በነፃ መስመር በሚላከው የጸሎት መርሐ ግብር ብሶትን ወደ ጽርሃ አርያም መስደድ ብቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የማንም ፈቃድና ይሁንታ አያስፈልግም፡፡ በየእምነት ቤቶችና እንደዬእምነቱ እየተሰባሰቡ እግዚዖ ማለት ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪ ፈጥሮ አይረሳምና ወደርሱ በመጮህ፣ በንጽሕናና በጸጸት ወደ አምላክ ቀርቦ በመጸለይና ሱባኤ በመግባት ይህን ያንዣበበብንን መከራና ስቃይ ቢያንስ በብዙ መቶኛ መቀነስ እንችላለን፡፡ አለበለዚያ ሦርያና ሩዋንዳን የሚያስንቅ የዕልቂት ዶፍ መጥቶብናል፡፡ ግን አልታየንም፡፡

መልካም ንባብ

የባህር ዳሩን የአማራ ባለሥልጣናት ጭፍጨፋ አስመልክቶ በዩቲዩብ አንዳንድ ሀተታዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ወያኔዎችና ከፌዴራል መንግሥቱ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህን ግድያ ማቀነባበራቸውን በፊትም የምንጠረጥረው ነገር ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተገለጸው የአማራ ጠላቶች እጅግ ከመብዛታቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ወፍዘራሾች “ከናካቴው የለም” የሚሉትን ይህን ጎሣ በማጥፋት ረገድ ሁሉም ይተባበራሉ — እነሱ ራሳቸው የማይስማሙና እንደዐይጥና ድመት አጥፊና ጠፊ ሆነውም ቢሆን – ቤንዚንና እሳት ሆነውም ቢሆን በአማራ ላይ ያላቸው አቋም ግን አንድ ነው – ይህንን የኢትዮጵያ አንድ ፈርጥ የሆነ ነገድ ከሥሩ መንግሎ ለማጥፋት ተማምለው ተነስተውበታል፡፡ ትልቅ ምክንያትም አላቸው – እርሱ ወደ ሥልጣን ከመጣ እንደልባቸው የሚዘባነኑበት በሙስናና በዘረፋ የሚገኝ የሀገር ሀብት፣  ካለብቃትና ችሎታ ለየደናቁርት የጎሣ አባሎቻቸው እንደገና ዳቦ እንዳሻቸው የሚያቃርጡት የይስሙላው የፌዴራል ሥልጣን አይኖርም፤ “ወርቃማ ጊዚያችን ይህች ናት!” ብለው ስለሚያምኑ ይህን የኳስ አበደች ዘመን በፍቅር ይወዱታል – በዚህ ዘመን የሚመጣባቸውን ሁሉ ግም ለግም እየተረዳዱ “አንድ ሰውና አንድ ጥይት” እስኪቀራቸው ይዋጉታል፡፡ ለዚህም ነው “በህገ መንግሥታችን አንደራደርም” በሚል እንደ አሠርቱ ትዕዛዛት ጉያቸው ውስጥ ወትፈው ያን ከሽንት ቤት ወረቀትነት ያነሰ ዋጋ ያለውን ሕወሓታዊ ሠነድ ጣዖታዊ ቤተ መቅደሳቸው ውስጥ አኑረው የሚፎክሩበት፡፡ ህዝብ ያለቀውና ለውጥ ተብዬው መጣ የተባለው እኮ ይህን ሸፋፋ ህገ መንግሥት ቀድዶ ለመጣልና ለሁሉም የሚመች አዲስ ህገ መንግሥት በምትኩ ለማኖር ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘር ማጥራት ወይስ ኢህአዴግን ማፍረስ ? (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

አማራ ካልጠፋላቸው ዕንቅልፍ የሚባል በዐይናቸው አይዞርም፡፡ እነዚህ የአማራ ጠላቶች የትግራይ ወያኔዎችና የኦሮሞ ኦነጋውያን ናቸው፡፡ እነዚህን የሚያሰማሩ የአዲሱ ዓለም ሥርዓት አዋላጅ የሆኑት ዓለም አቀፍ ኃይሎችም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ እነዚህን ሆዳም ዜጎች በአማራ ጠላትነት እያነሳሱና እያደራጁ፣ በበጀትና በዘመናዊ ጦር መሣሪያም እያጠናከሩ፣ ዘመናዊ የሣተላይት መረጃ እየመገቡ በኢትዮጵያ ላይ ጃዝ ብለው ይለቋቸዋል፡፡ ይህም ሁሉ የሚሆነው እንዳንዳንዶቻችን ሃይማኖታዊ ግንዛቤ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ የፈዘዝነውም ሆነ የተበታተንነው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ አንድ ያልሆነውም ሆነ በትንሹም በትልቁም የምንንነታረከው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ብዙ ሆነን ሳለ ጥቂት የሆንነው፣ ኃያል ሆነን ሳለ ደካማ የሆንነው፣ ሀብታም ሆነን ሳለ ድሃ የሆንነው፣ አንበሣ ሆነን ሳለ ከዝንጀሮም ያነስነው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ይህን ካልኩ ዘንዳ የትንቢቱን ፍጻሜ ልንገርህ፡፡ የሀገር ጠላቶችም መከራቸውን የሚያዩትና ከዳር እዳር ኅብረት ፈጥረው አማራንና የአማራን ብቸኛ መመኪያ ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚራወጡት የመጨረሻውን ትንቢት እነሱም ስለሚያውቁና ያንን የማይቀር ትንቢት የቀለበሱ መስሏቸው ነው፡፡ ይህን እያስገመገመ በመምጣት ላይ የሚገኝን ገሃድ እውነት መናገር ድፍረት ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡

አማራ ማንሠራራቱ ዕንቅልፍ እንደነሳቸው ገልጸናል፡፡ እነአሣምነው እየተጓዙበት የነበረው ሀገርን የመፍጠር እንቅስቃሴ እነአቢይንና አክራሪ ኦሮሞዎችን፣ አክራሪ ትግሬዎችን፣ ከየጎሣው ያሉ ሆዳምና ነቀዝ ዜጎችን በጠቅላላው ዕረፍት ነስቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ያንን ግልጽ የግድያ ዘመቻ ካላንዳች ይሉኝታና ሀፍረት በመፈንቅለ መንግሥት ሰበብ ማካሄድ ነበረባቸው – ያ “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” የምንለው የአዲሲቷ ዓለም መሥራችም በሚዲያው ሽፋንና በስንቅ ትጥቅ ከጎናቸው ስለሆነ ማንንም አይፈሩም፤ አያፍሩምም፡፡ ትናንሽ ፖለቲከኞች ከኒዚህ የዓለም ገዢ ኃይላት የሰይጣን ጭፍሮች ትዕዛዝ አንድ ኢንችም ዝንፍ አይሉም – የሚደርስባቸውን ያውቃሉ፡፡ “Confessions of the Economic Heat Man” የሚለውን መጽሐፍ አንብብ ከፈለግህ፡፡

“የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” ይባላል፡፡ እነአቢይ የሚገድሉትን ሁሉ ከገደሉና መረጃ ካጠፉ በኋላ ያን ከእውነት የራቀ ነገር መደስኮራቸው በሕዝብ ንቃተ ኅሊና ላይ ጢባጢቤ ከመጫወታቸውም በላይ የነሱን ድንቁርናናማዊ ዕብሪት አጉልቶ ያሳያል፡፡ አክራሪ ኦሮሞዎች በከሚሴና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል ሊሠሩት ያቀዱትንና የጀመሩትንም አማራን በጎጥና በሸንተረር የመከፋፈል እንዲሁም በሳል አመራር የማሳጣት እንቅስቃሴ እነአሣምነው ቀድመው ነቅተውባቸው ሊያከሽፉባቸው በመነሳታቸው በአማራ ልሂቃንና አመራሮች ላይ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ወረደ፡፡ መሆን ስለነበረበት ነው የሆነው ብለን በአርምሞ እንቀበለዋለን፡፡ አንድ መሆን ያለበት ነገር ደግሞ ይዘገያል እንጂ ከመሆን አይዘልም፡፡ አሁን እንደምንሰማው ያ በአክራሪ ወያኔዎችና ኦህዲድ/ኦነጎች የተጠነሰሰ ዘመቻ “ዘመቻ ቅንጸላ” ይባል ነበር፡፡

ቅንጸላ ምን ማለት እንደሆነ በውል አላውቀውም፡፡እንደሚመስለኝ ግን “ማምከን፣ ማስቀረት፣ መቀምጠል፣ ማጉደል፣ ማክሸፍ…” ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአማራን ትንሣኤ ለማስተጓጎልና እስከወዲያኛው ለመቅበር የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ወዲያና ወዲህ ከሚያቅነዘንዛቸው ዕረፍት ያጣ ተግባራቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁን አሁንማ ይሠሩትን አጥተዋል፡፡
ይህ አማራን የማጥፋት ሁለገብ ዘመቻ በነአቢይ አህመድ ይመራ እንጂ አንዳንድ ሆዳም የብአዴን አባላትም የጥፋት ዘመቻውን መተባበራቸው የታወቀ ነው፡፡ ዱሮውንም ሆዳም ፍቅር አያውቅም፡፡ ሆዳም ሚስቱንም፣ ልጁንም፣ አባቱንም፣ እናቱንም ለገንዘብና ለጥቅም አሳልፎ ይሸጣል፡፡ ይሁዳ ጌታውን በ30 አላድ እንደሸጠ ሁሉ የባሰበት ሆዳም አማራም አማራን አይሸጥም ተብሎ አይታሰብም፡፡ የአማራ መከራ የበዛው የራሱ ልጆች ሳይቀሩ ከታሪካዊው ጠላቶቹ ጋር በመተባበር ለከርሳቸው ሲሉ ስለሸጡት ነው፡፡ ያለ ነው፡፡ ወደፊትም ይህን መሰሉ አስቀያሚ ክህደትና ሽርሙጥና አይቀርም፡፡ ዋጋቸው ግን በሠፈሩት ቁና ልክ ይሠፈራል፡፡ እንጂ ለክህደት ለክህደትማ እነክፍሌ ወዳጆንና ገነት ዘውዴን ማን ይረሳቸዋል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስሜቱ ይቁምና እስቲ አማራጮችን በእርጋታ እንመልከት - ግርማ ካሳ

ዘመቻ ቅንጸላ ያደረገውን አድርጎ ለጊዜው የተሣካ ይመስላል፡፡ በዚያም ምክንያት በአማራው አካባቢ አሁን ለጊዜው መፍዘዝ ይታያል፡፡ ግን በዚህ መልክ አይቀጥልም፡፡ ምክንያቱም ትንቢቱ ደርሷልና፡፡ ንግርት ቢዘገይ እንጂ አይቀርም፡፡
ይህ ነው ትንቢቱ፡፡ መጀመሪያ ከሰሜን የመጡ አንበጦች ኢትዮጵያን እንደተምች ይወሯታል፡፡ ወርረውም እስከ አጥንቷ ይግጧታል፡፡ መሣሪያ ከትከሻቸው የማይወርድ እረኞች በሽምብራ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ጠማማ ፍርድን ይሰጣሉ፡፡ እህል በሸሃኔ ይሠፈራል፡፡ ቀጣና ይበዛል፡፡ ርሀብና መከራ ይናኛል፡፡ ትልቅ ሰው ይዋረዳል፤ ትንሽ ሰው ይከበራል፡፡ በመጨረሻቸው ግን እነዚያ ጉዶች እንደጢስ በንነው፣ እንደጤዛ ረግፈው ይጠፋሉ፡፡ ይህን አሁን አይደለም እኛ የምንለው፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ በ50 እና 60ዎቹ ዕድሜ የምንገኝ ሁሉ የምናውቀው የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው፡፡

ቀጥሎ ፊጋ ከብቶች ባዶውን በረት ይወርሳሉ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ባዶ ያገኙትን በረት እውነት መስሏቸው እምቡር እምቡር ይሉበታል፡፡ ዕውቀትና ጥበብ ባለፈበት መንገድ ያላለፉ የለዬላቸው ቅብዝብዞች ናቸው፡፡ መሪያቸው ሃይማኖት አለው ማለት አይቻልም፡፡ የሥልጣን ዕድሜው ከሦስት ዓመታት እምብዝም አያልፍም፡፡ የነሱም የመጨረሻ ዕጣ ልክ እንደአንበጣዎቹ ይሆንና ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ አከርካሪያቸውን ተመትተው ወደ ታሪክ ትቢያነት ይለወጣሉ፡፡ ያንን ጊዜ አንተ ወይም አንቺና እኔ ላናየው ብንችልም የማይቀር ስለመሆኑ ግን ከተነገረው በጣም ጥቂቱ ብቻ የመቅረቱ እውነት ምሥከሬ ነው፡፡  ዝምዝማቱ እንጂ የቀረው ምን ተብሎ ምን ያልሆነ አለ!

በመጨረሻው መጨረሻ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተጠራርተውና ኃይላቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያን ይረከባሉ፡፡ በነሱም የኢትዮጵያ የቀድሞ ክብር ይመለሳል፡፡ ያም ጊዜ እጅግ ቀርቧል፡፡ይህን እውነት መናገር ማንንም አይጎዳም፤ ለማንምም የሥጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም የምሥራች ነው፡፡ ለወፍ ዘራሾች ግን መርዶ ነው፡፡ (ባይገርምህ የተጠፋፉ እናትና ልጅም ተገናኝተው ጥጃዋ ከእህትና ወንድሞቿ ጋር የእናቷን ጡት የምትጠባበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ምን ያስቅሃል?)

እነዚህ የአሁኖቹ ከንቱዎችና ጌቶቻቸው ወያኔዎች ግን ትልቅ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የነሱን የዓመታት መርዝ ለመንቀል ብዙ ትግልን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሕዝብ መስዋዕት ይሆናል፡፡ የደም ጎርፍ የማናመልጠው ዕዳችን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ጸሎት ግን ወሳኝ ነው፤ ነነዌ ከጥፋት የዳነችው በዮናስ መላክተኛነት ሕዝቡ ምህላ ይዞ ነውና ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ልንማር ይገባናል፡፡

“ለኃጥኣን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” እንዲሉ በመሆኑ አምላ ጣልቃ ገብቶ ልባችንን ካላሟሸሸው ብዙ አሣር ያገኘናል፡፡ መስዋዕቱን ለመቀነስ እንዲቻል ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት (ትንቢትን ማስቀረት ባይቻልም) ወደ ፈጣሪ ተመልሰን በፆምና በጸሎት ብዙ መድከም ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ ቃል የተገባላት ምድር ናት፡፡ ጠላቶቿ ቀበርናት ሲሉ አፈሯን አራግፋ የምትነሣ፣ ገደልናት ሲሉ የምትድን ልዩ ሀገር እንደሆነች በተደጋጋሚ አስመስክራለች፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ብዙ ዕልቂት ቢኖርም ከህመሟ ተፈውሳ በሚተርፏት ጥቂት ዜጎች ልዕልናዋን እንደገና ታስከብራለች፡፡ አራሙቻዎችም ተጠራርገው የጨለማው ንጉሥ ግዛት ወደሆነው ወደ መጡበት መቀመቅ ይወርዳሉ፡፡

በየከተሞች የሚታየው የሴቴኒዝም እምነትም በነፃነታችን ቶሎ አለመምጣት ላይ የበኩሉን ጽላሎት ማሳረፉ አይቀርም፡፡ ከጥግ እስከጥግ የቆሸሸውና በዘረኝነት፣ በሙስናና በድንቁርና የተበከለው ቤተ መንግሥታችን ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንንና የእምነት ቤቶችን በጥቅሉ ሰይጣን ስለተቆጣጠራቸው እውነተኛ እረኞች የሉንም፡፡ ሰይጣን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስያንን ጨምሮ የእስክንድርያዋንና የኢትዮጵያዋን ኦርቶዶክስ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥሯል፡፡ ልጅ እየወለደ በድብቅና አንዳንዴም ልክ እንደቫቲካኑ የ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ ሊቀ ጳጳስ (ፖፕ ሮድሪጎ) በማን አለብኝነት በግልጽ የሚያሳድግ ፓትርያርክና ጳጳስ ባለባት ሀገራችን ውስጥ የእግዚአብሔር በረከትና ጥበቃ በቀላሉ ይገኛል ማለት ቀልድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መዳን ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተሠራ እያለ አንድም የሃይማኖት አባት በግልጽ ወጥቶ አይቃወምም፤ ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም፤ ፈስ ያለበትም ዝላይ አይችልም፡፡ “አባቶቻችን”ም በጠባያቸው ሰይጣናዊነት የተነሣ ብዙዎቹ ፀጋ እግዚአብሔር በእጅጉ ጎድሏቸዋልና በጎቻቸውን ተኩላና ቀበሮ ሲቦተራርፍ፣ ሀገርን ማንም ወስላታና ወለፈንዴ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ሲጫወትባት ትንፍሽ አይሉም፡፡ ምክንያቱም በሆነ ነገር አፋቸው ተሸብቧል፡፡ ለነፍሳቸው ያደሩ እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ አባቶች ሞታቸው ሰማዕትነት እንጂ ተራ ዓለማዊ የሥጋ ሞት እንዳልሆነ ስለሚረዱ እውነትን መስክረው በጥይት ተደብድበው ሞተዋል፡፡ አሁን ግን የምዕመናንንና የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ገንዘብ እየዘረፉ፣ በዘረኝነት አሮንቃ እየዳከሩና በሴሰኝነት የወሲብ ንዳድ እየነፈሩ ስለነፍስና ስለሀገር ማሰብ የማይቻል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በቅርጽ እንጂ በይዘት አለች ማለት አንችልም – የምለው ሀሰት ቢሆን ደስታው ባልተቻለኝ፤ ግን ምኖት ነው የሚሆንብኝ፤ በሁሉም ዘርፍ በቁማችን ሞተናል፡፡ ድንጋይ ይክባሉ እንጂ አእምሮ ላይ የሚሠሩት አንዳችም ነገር የለም፤ የነሱ የራሳቸው አእምሮም ባዶ ቀፎ ነው፡፡ አብዛኛው ካህንና ደብተራ ዐይኑ የሚጎለጎለው፣ መረዋ ድምጹ የሚጎላው፣ ቅኔውና ወረብ ሽብሸባው የሚተጋው ገንዘብ ላይ ነው፡፡ ከሁለት ሰዓት የዐውደ ምሕረት ስብከት ውስጥ 30 እና 40 ደቂቃው ብቻ በተግባር ለማይተረጎም ሃይማኖታዊ ቃል የሚውል ሆኖ ሌላው ገንዘብ ስጡ ላይ ነው – መስጠት ብቻውን ያጸድቅ ይመስል፡፡ “ብዙ አየን” አለች አሉ ቦለቅያ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እውን ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ጥቁር አይደለንም ይላሉ? | ይህን ቪዲዮ ይመልከቱ

እንግዲህ እውነቱ እንዲህ ነው፡፡ ሴቴኒዝምን እንዋጋ፡፡ ዝርዝሩን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው( Romans 1:18-32, Leviticus 20:13, 1 Corinthians 6:9-10, 1 Timothy. 1:9-10)፡፡ ነገር ግን ይህ የጨለማ ዘመን በቶሎ እንዲነጋ ለማድረግ የእውነት ዘገርን እንጨብጥ፡፡ ከላይ እስከታች የሠፈነውን ሙስና እንዋጋ፡፡ በመደበኛ ገቢያችን መኖርን እንለማመድ፡፡ በልጆች አእምሮ ላይ ብዙ እንሥራ፡፡ እንደሀገርም እንደሕዝብም እየጠፋን ነውና ከተሳሳተ መንገድ በቶሎ እንመለስ፡፡ ከሰሞነኛ ቅሌታችን ብጠቅስ ለምሣሌ – ፈተናን እየሠረቅንና በመምህራን እያሠራን መልስ በመበተን ትውልድን ከማደደብ በላይ ምን ወንጀል አለ? በምግብና በልብስ እንዲሁም በሌሎች የንግድ ዕቃዎች የሚሠራውን ፌክና አሻጥር አናንሳው፡፡ የጀሦና የሴጋቱራን እንጀራ፣ የቀይ ሸክላ በርበሬንና የሞራ ቅቤን መመገብ ለምደን ሰው መሆን ቢያቅተን በርግጥም አይፈረደብንም፡፡ የምንገርም ሆነናል እኮ …. ሀገርና ሕዝብ በ30 ዓመታት ውስጥ ብቻ መጥፋት የሚችሉ ተራ ነገሮች ናቸው ማለት ነው? ከነአቢይ አህመድ የሕይወት መመርያ ቀጣዩን ለአብነት ያህል እንመልከት፡-

Politics has nothing in common with moral. The ruler who is governed by the moral is not a skilled politician, and is therefore unstable on his throne. He who wishes to rule must have recourse to both cunning and to make believe. Great national qualities, like frankness and honesty, are vices in politics, for they bring down rulers from their thrones more effectively and more certainly than the most powerful enemy. (Source: Secret Societies and their Power in the 20th Century, by Jan Van Helsing)

ለዚህ ነው የሁሉም ችግር ማስወገጃ መንገዳቸው ውቃው ሆኖ የቀረው፡፡ ሰው ሰው የማይሸት ፖለቲካና ሃይማኖት፣ ከምክንያት ይልቅ ከራስ ወዳድነትና ከስግብግብነት ጋር የተቆራኘ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተራክቦ ገጥሞን ወደ ሮቦትነት እየተለወጥን ነውና ጨርሰን ሳንጠፋ እንምከር፤ እንነጋገር፤ ለዚሁ ጉዳይ መድረኮችም ይዘጋጁ፡፡ የኑሮ ውድነቱንም ለማብረድ ወደ ሰውነት እንመለስ – ለሆዳችንና ለሥጋዊ ፍላጎቶቻችን መቆጣጠሪያ ቫልቭ እናብጅ፡፡ ሰውነት እጅጉን ርቆናል፤ ናፍቆናልም፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share