ባዲሱ ዘመን ለሰው ልጅ ህይወት ክብር እንስጥ

የዘገየ ቢሆንም አሁንም ያለነው በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር በመሆኑ መልካም ምኞትን መግለጽ ትክክል ነው ብዬ ኣምናለሁ። በመሆኑም፣

አዲሱ ዘመን፡

  • የፈጣሪን ምህረት የምናገኝበት፣
  • ሰው ያለሃጢያቱ በርኩሳን የማይገደልበት፣ ሞትና መፈናቀል አንዳልታየ የማይታለፍበት፣ ፍትህ የሚሚገኝበት፣ የተጎዱ የሚካሱበት፣
  • ፈጣሪ በአምሳሉ የፈጠረውና ምድርን አንዲገዛ የፈቀደለት የሰው ልጅ፣ አንተ አንዲህ ነህ አንተ እንዲያ ነህ ተብሎ ተፈጥሯዊው የመኖር መብቱና አምላካዊ ስጦታው በሌላው እኩይ ሰው የማይነጠቅበት፣
  • የሚበላው ለሌለው ሰው ፊቱን ቅባት የማንቀባበት፣
  • የአገራችን ህዝብ በሁሉም የኣገራችን ስፍራ በሰላም ተኝቶ ያለሃሳብ የሚነቃበት፣
  • አንጋፎች መልካም አርአያነትን የሚያሳዩበትና የሚከበሩበት፣
  • የአገርና የህዝብ ወዳጆች የሚከብሩበትና አገርንና ህዝብን የሚጠሉ ከጨለማ የሚወጡበት

ዘመን ይሁንልን።

በኔ ምልከታ ያለፈው ዘመን በአገራችን ብዙ ጉዳቶች፣ ብዙ ስጋቶችና፣ ብዙ ያልተጨበጡ ተስፋዎች፣ ኣንዲሁም መልካም ነገሮች የታየበት ዘመን እንደነበረ ይሰማኛል።  ተጀምረው የተጠናንቀቁ ፕሮዤዎች፣ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተደረገው ርብርብ፣ ወገን ወገኑን ለመርዳት ያደረገው ኣስተዋጾ፣ ይበል የሚባል ነበር።

በኣንጻሩም ባለፈው ዘመን፣ ኣገራችን የግለሰብ መብቶች በጅጉ ተጥሶባታል፣ በጀርባ ያለ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ በዕውነታው ዓለም ብዙ ህዝብ በስጋትና በጭንቀት አንዲኖር ዳርጎታል። ለቀደሙት 27 ዓመታት ባገዛዙ ለመቆየት ሌላ ምንም ምክኒያት የሌለው አካል የዘራውና ኮትኩቶና ተንከባክቦ ያሳደገው ሰውን በዘር ከፋፍሎ አንዳይነጋገርና አንዳይተማመን አድርጎ የመግዛት ኣባዜ ፍሬ አፍርቷል። ስለልዩነቱ አምዛም ሳይጨነቅ ደስታውንና መከራውን አኩል ተካፍሎ ይኖር የነበረን ህዝብ በዘሩ አንዲያስብና ዘሩን ሳይጠራ አንዳያድር አድርጎታል። ቢያንስ ዘራችን በመታወቂያችን ላይ የማይጻፍበት አሰራር ተስፋ በማየታችን እንጽናናለን። ይህም ሲሆን ብዙ የህብረተሰቡን የግል መረጃዎች የያዙ የኮምፒዩተር የውስጥ መያዣዎች ቋቶች ባለፈው ዘመን ከየቀበሌው መዘረፋቸው ሳይረሳ ነው። ለምን ተግባር አንደዋለ መገመት ኣያዳግትም። ዘራፊዎቹ ኣልተከሰሱም ፍርድ ኣላገኙም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በልጠን ካልተገኘን….!!! - ቹቹ አለባቸው

ከጀርባ ማን አይዞህ እንዳላቸው ባናውቅም አሁንም ከስልጣን የተገለሉ ወገኖች በአጉራዘለልነታቸው ገፍተውበታል። ያሻቸውን ባሻቸው ጊዜ ይሰራሉ። አሁንም በሃይል ያለህዝቡ ፈቃድ የያዟቸውን ህዝቡን ሳይሆን መሬቱን የሚፈልጉትን አካባቢ ግዛቱን ይዘው ህዝቡን ረግጠው እየገደሉ፣ እያጋዙ፣ አያሰሩ፣ ንብረታቸውን እያቃጠሉ በግፍ ስራቸው ቀጥለዋል። ስለመፍትሄው የሚናገር የለም። አነዚህ የህብረተሰብ አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ከምክር ቤት ምክር ቤት ሲንከራተቱ ኖረዋል። አሁንም ሰሚ አላገኙም። በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አንኳን ሃሳብ ያለ አይመስልም። ቀስ በቀስ ህዝቡ እየተመናመነ እየጠፋ ሲሄድ ጥያቄውም በዚያው ይከስማል በሚል ዕቅድ የተያዘ ይመስላል። ጉዳዩ ግን የውስጥ ቅኝ ገዢነት ሆኖ ቀጥሏል።

የቤኒ ሻንጉል ግድያ ቀጥሏል።  አሁንም አልበቃም፣ ያለው ለውጥ ቢኖር በቀስት ከመገደል በታጠቁና በሰለጠኑ ሰዎች መገደል ይመስላል። ይህ በየቀኑ ሞት ሳይሰማ የማያድርበት ክልል አሁንም መንግስት አለው፣ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች አሉ፣ ሰራዊቱም ገባ ወጣ ይላሉ። ሆኖም አሁንም ሞት ሳይዘገብባት አይውልም፣ አያድርም። አሁንም ገዳዮች አነማን አንደሆኑ መንግስት አያውቅም፣ አንዳንድ ታጣቂዎች፣ ወዘተ እተባሉ ነው የሚጠቀሱት። ስንት በህዝብ ላይ የሚፈርዱ ታጣቂዎች ባገሪቱ ኣንደሚንቀሳቀሱ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። ደህነታችን ለምን ይሆን የዚህን ጉዳይ መሰረት ማወቅ የተሳነው? በጣም የሚያሳዝነው ይህ እንዲጠፋ የተፈረደበትና በየዕለቱ የሞቱ ዜና ሳይነገር የማያድረው የህብረተሰብ አካል አንደማንኛውም የአገራችን ህዝብ ባብዛኛው በገጠር በድህነት፣ በድካም ሲኖር ዘመናትን ያሳለፈ ህዝብ ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል እየተገደለ ያለው ባብዛኛው ከራሱ ይልቅ ሃይማኖቱን፣ ከራሱ ይልቅ አገሩን ስለሚያስቀድም ኣንዲሁም የሚኖርበት መሬት በቀደሙትም ሆነ በባለተርኞች ስለሚፈለግ ኣንጂ ሌላ ወንጀል የለበትም። ይህንን የቀደሙት የውጪ ወራሪዎችም ሆኑ አሁንም የተፈጥሮ ሃብቷን ለመመዝበርና ክብሯን ለማዋረድ የማይተኙ  ምዕራባዊያንም የሚያበረታቱት ይመስላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መውጫ አብጅቶ መግቢያ የከለከለን አሳዳጁ ማን ነው? - ከግርማ ሠይፉ ማሩ

በኣገራችን የተለያዩ ክፍሎች የሰው ዘር ማጥፋት ዘመቻ መቋጫ ኣላገኘም። ያለፍው መንግስት በልዩ ስልት የጀመረው ኣሁንም በተለየ መልኩ ቀጥሏል። ብዙውን ጊዜ ማምለጫ `ይጣራል` የሚለው ማዘናጊያ ነው። ለዚህ ማስረጃው ከሁለት ኣመታት በፊት ፍጹም ሰላማዊ የሚባል ሰላማዊ ሰልፍ በኣዲስ ኣበባ ከተደረግ በኋላ ተሳታፊው ወደቤቱ መበታተን ከጀመረ በኋላ በሰላም ከሚጓዘው ህዝብ መካከል የተወሰኑት ያለምክንያት ተገደሉ። ይህ ጉዳይ ይጣራል ተብሎ ኣንደተተወ ነው። የተወሰደ ርምጃ የለም። ክዚያ በመቀጠል በርካታ የሰውን ህይወት ያጠፉ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። ሁሉም ኣንዲጣሩ ቃል ተገብቷል የታየ ውጤት የለም። ያጠፉ ሲቀጡ ኣልታየም። በዚህ ሰላም ለመንሳትና ለግል ዓላማቸው የሚታገሉ ሃይሎች የተበረታቱ ይመስላል። እስከዚች ቀን ድረስ ጥፋቱ ቀጥሏል። የፍትህ ጉዳይ ኣይታይም። የተጀመሩ የፍርድ ሂደቶችም ኣስጊ የሆኑ ለጭፍጨፋ ምክንያት የሆኑና በተደጋጋሚ የረገጡት መሬት ሁሉ የሞት ምድር የሆኑባቸው ሰዎች የፍትህ ሂደትም የመቀዛቀዝ መልክ አየታየበትና ኣደገኛ የሚመስሉ ተጠርጣሪዎችም አየተለቀቁ ነው። ሆኖም አጅግ መተኮር ያለበት ኣንድም የሰው ህይወት የጠፋበት ክስተት ጊዜ ይውሰድ አንጂ ለፍርድ መቅረቡ የማይቀር መሆኑንና ሁላችን መዝገብ መያዝ ኣንደሚገባን ማወቅ ያስፈልጋል።  በወታደራዊው መንግስት ዘመን በተደረጉ ጭፍጨፋዎች ጊዜ ስልጣን ላይ የነበሩ ባለስልጥናት በወያኔ መንግስት ለዘመናት ወደ እስር ተውርውረዋል። በውጪ ኣገርም ተከሰው የተፈረደባቸው ኣሉ።

መንግስት ማዕከላዊ ስልጣንን የያዘው የአገርን አጠቃላይ ሰላም፣ የዜጎችን ክብርና አንድነት፣ ዳር ድንበርና የኢኮኖሚ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። ይህ ጉዳይ ባሁኑ ወቅት ካለፈው በተወረሰ መልክ ኣንድ ወገን በራሱ ክልልም በማዕከልም የበላይነት ይዞ የሌሎችን መብት የሚረግጥበትና ሌሎችን በውስጥ የቅኝ ኣገዛዝ የሚይዝበት ስልታዊ ኣሰራር የቀጠለ ይመስላል። ምግባሩ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ያገራችን ህዝብ ባጠቃላይ ግን ኣገር ከሰሜን ኣስከደቡብ ከምስራቅ እስከምዕራብ ተዘዋውሮ ሊኖርባት፣ ሊሰራባትና ሃብት ሊያፈራ የሚችልባት ኣገር መሆኗን ኣምኖ ኣየኖረ ሳለ ይጨፈጨፋል፣ ይባረራል። የራሱ የሆነው መሬቱ፣ ሃብቱና ንብረቱ ደግሞ በወስጣዊ ቅኝ ኣገዛዝ ይወረርበታል፣ ይወድምበታል፣ ይፈናቀላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሞረሽ እንቅስቃሴ ላልተገለጸለን አንዳንድ ነጥቦች

ከህዝቡ በብዙ ርምጃ ወደኋላ የቀሩ፣ ሌላ ቀርቶ ስለልጆቻቸው የነገ ዕጣ ፈንታ ኣርቀው ማሰብ በማይችሉና የሰለጠኑ አየመሰላቸው ሰፊው ህዝብ ፊት ሳይፈሩ ድራማ የሚሰሩ መሪዎች ሚሊዮኖችን ጨፍልቀን ኣንድን ወገን የበላይ እናደርጋለን ብለው ካለፈው ባለመማር በወደቀ ኣስተሳሰብ ጭቃ ውስጥ በመዳከር ላይ ይገኛሉ።

ነገር ግን ሊታመን የሚገባ ኣንድ ሃቅ ኣለ። ኣሁንም የሚበጀው በቀናው መንገድ መሄድ ነው። ፈጣሪ ይቅር ባይ ነውና ይቅር ኣንድትባሉ ከእኩይ ተግባራችሁና ከደም ማፍሰስ የሴራና ከንቱ ፖለቲካችሁ ታቀቡ። ሕዝብን ዝቅ ብላችሁ ኣገልግሉ፣ በሸፍጥ ሳይሆን በእውነት ቁሙ። የህዝብንና የኣባቶችን ምክር ስሙ፣ ያልሰሙ ሁሉ ጠፍተዋልና፣ ከመጥፋት ትድናላችሁ። ነገር ግን በፍጹም ኣትጠራጠሩ ይህችን ቅድስት ኣገር ለመምራት የተሰጣችሁ ታላቅ ዕድል ሳያልፋችሁ ካልተጠቀማችሁበት ግን ብትወዱም ባትወዱም የያዛችሁት መንገድ ኣያዛልቅም፣ ያጠፋችኋል። ኢትዮጵያ ግን ወደ ክብሯ ተመልሳ በክብር የሚወዷት ልጆቿን ይዛ ህዝቧም እጅለጅ ተያይዘው በሰላም ይኖራሉ። ያላከበሯትና ህዝቧን በሰላም ኣንዳይኖር የወደዱ ግን እንደባልንጀሮቻቸው ሳያውቁት ይበተናሉ። የምታሳድዱት ህዝብ ራሱን ትቶ ለኣገሩ ሲደማ የኖረ፣ ኣንደወንድሞቹ በድህነት የሚኖር፣ ለአገሩ ሰላም በየዕለቱ ፈጣሪውን የሚለምን መሆኑን አትርሱ። በየትኛውም ታሪክ ህዝብ ላይ ያመጹ መንግስታት ጸንተው ኣያውቁም። ለራሳችሁ እወቁ፣ ደምን የሚያፈሱ በሰይፍ ይጠፋሉ።

 

ዘመኑን የንጹሃን ደም የማይፈስበት መሪዎቻችን ወደ ልቡናቸው የሚመለሱበት ዘመን ያድርግልን!

በኣዲሱ ዘመን ለሰው ልጅ ህይወት ክብር እንስጥ!

እግዚአብሔር  ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ያድን!

ገብረ ኣማኑኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share