September 5, 2020
2 mins read

ህልም አየሁ ፍቱልኝ (ዘ-ጌርሣም)

ህልም አየሁ ተኝቸ
በአደባባይ ቁሜ ተሟግቸ
የመሐል ዳኛው ህግ ጠቅሶ
አጥፊውን በጥፋቱ ወቅሶ
ይመስላል ሊመክረው
አለያም ሊያስተምረው

ህዝብ ሞልቶታል አዳራሹን
ለማዳመጥ ውሳኔውን
ይግባኝ የማይኖረውን

አቃቤ ህጉ ተነስቶ
ግራና ቀኙን ቃኝቶ
ጭብጥ ሃሳቡን ዘረዘረ
የሞቱትን ስም ብዛት ደመረ
የተሰወሩትንም ጨመረ
የተዘረፈውን ሀብት ለየ
በአኃዝ አስደግፎም አሳየ

እንዲህም አለ በመቀጠል
አብዛኛው ንብረት ከአገር ሸሽቷል
ያለበት ቦታም ይታወቃል
ይህ ብሔራዊ በደል ነው
ለወንጀለኛው ቅጣት ይሰጠው
የዘረፈውንም ይመልሰው

የተከበረው ፍርድ ቤት
ጉዳዩን መርምሮ በአፅንዖት
ውሳኔው ይበል ጠንከር
ሌላውን የሚያስተምር

በማለት ሃሣቡን ቋጭቶ
የበኩሉን ተወጥቶ
ተመልሶ ተቀመጠ
ቤቱም ያን ጊዜ በጩኽት ተናወጠ

የታዳሚው ድጋፍና ጩኽት
ፍርድ ቤቱን ኳስ ሜዳ አስመሰሉት
ተመልካችንም አስደመሙት
ብይን ለመስማት በጉጉት

ከዚያም የመሐል ዳኛው ተነስቶ
ግራና ቀኙን በደንብ ቃኝቶ
በህዝቡ ስሜትም ተነቃቅቶ
ብያኔው ፍትሐዊ እንደሚሆን ቃል ገብቶ
የዕለቱን ችሎት አቆመው
ለሌላ ቀንም ቀጠረው

የቀጠሮውን ቀን እየጠበቅሁ
በጉጉት ላይ አንዳለሁ
ከእንቅልፌ ብንን ብየ ነቃሁ
ቅዠት ነው ወይስ ህልም ያየሁ ??
ብየ እራሴን አነጋገርኩ
የሚመጣውን እየጠበኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop