ልዩ ጳጉሜ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ጳጉሜ በኢትዮጵያ 13ኛና ብርቅዬ ወር ናት። የክረምቱ የመጨረሻ ቀናትን የያዘችና የጸደይ ደጃፍ ላይ የቆመች በተስፋ የተሞላች ወር መሆኗ በጉጉት የምትታይ ያደርጋታል። ብዙ ሰው ያለፈውን አመት ቃኝቶ መጪውን እያሰበ የሚያሳልፍባት በመሆኗ ጳጉሜ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ልዩ ናት።  ለምሳሌ በተዋሕዶ ምእመናን ወደ ወንዝ ወርዶ በመጠመቅ የመንጻት ሥራ ይዘወተራል። በክረምቱ የገባውን ተሕዋስያን ከሰውነት ለማጽዳትም በጳጉሜ ማብቂያ ነው የፌጦ ፍትፍት የሚበላው።

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻ ዘመናት ጀምሮ የአዲስ ዓመት መዳረሻ (እና ሌሎችም ታላላቅ የቤተክርስትያን በዓላት ዋዜማዎች) በከተሞች በዳንኪራ እና በአስረሽ ምቺው ነበር የሚከበሩት። የአባቶቻችን የአበው መንገድ ግን እንደዚህ አልነበረም።

አባቶቻችን ግን ከአዲስ አመት በፊት ያሉትን የጳጉሜ ቀናት በጸሎት የሚያሳልፉበት፣ ባለፈው ዘመን ለሠሩት ንሥሐ የሚገቡበት፣ ለመጪው ዘመን ጤናማ እና ሰላማዊነት ደግሞ ልመና የሚያቀርብቡት ወቅት ነበር። በተጨማሪ ጳጉሜ በቅኔ ቤት ምጽአትን የሚመለከቱ ቅኔዎች የሚዘረፉበት፣ የዮሐንስ ራእይ እንዲሁም የጌታም የምጽአት ትምህርት እና ትዕምርት የሚራቀቅበት ወቅት ነው። አርጅቶ እንደሚያልፈው አመት ሰውም ማለፍና መሞትን ትንሣኤንም አስቦ ሕይወቱን በትክክለኛ መንገድ ላይ ስለማድረግ የሚያስብበት ጊዜ ነው ማለት ነው። እንግዲህ ራሳችንን፣ ሀገራችንን እና ፈጣሪያችንን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ባለማድረግም እንበድላለንና ያንን ለማስተካከል ምን ምን ነገሮችን አለማድረግ ምን ምን ነገሮችን ደግሞ ማድረግ እንደሚገባን ግምገማና እቅድ በማውጣት የጳጉሜን አጭር ወር መልካም ጠቀሜታ ላይ ልናውላት ይገባናል።

የዘንድሮ ጳጉሜ በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ የተለየ ሥፍራ ያላት ናት። ሀገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት ከሚባለው አባባልም ገደል አፋፍ ላይ ናት የሚባለው እውነት በሚመስልበት በዚህ በ2012 ዓም መዳረሻ ላይ መገኘቷ ግልጽ ነው። ሁለት ሺህ አሥራ ሁለት 2012 እጅግ ከባድ የፈተና፣ የእልቂት፣ የጄኖሳይድ፣ የወረርሽኝ፣ የስደት፣ የመፈናቀል፣ የአንበጣ፣ የጎርፍ፣ የክህደት፣ የወረራ፣ የፉገራ ዘመን ሆኖ በማለፍ ላይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢህአዴግ ብሔርተኝነትና የተቀናጀ ማሰተር ፕላን ……..?

በዚህች በጳጉሜ ደግሞ ሰላሣውን ዘመን የመዓትና የእርስ በእርስ እልቂት መደገሻ አድርጋ የከረመችው ሕወሃት የትግራይን ሕዝብ አሸንፋ የግንጠላ ፕሮግራሟን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ቀን ቆርጣ የተቀመጠችበት ነው። እንግዲህ በትግራይ መገንጠል የምትጎዳው ትግራይ ብቻ ሳትሆን መላው ኢትዮጵያም ጭምር ነው። በኤርትራ መገንጠል እንደታየው ገንጣዮቹ ቃል የገቡልን ሰላም ሳይሆን የተከተለው የሕዝብ በደል፣ ግፍ እና ሌላም የእርስ በእርስ እልቂት ነበር። ያውም ኤርትራ የታወቀና በቅኝ ግዛት ታሪክ ምክንያት የትከለለ ድንበር የነበራት ሆና። የሕወሃቷ ትግራይ ከሕወሃት በፊት ባልነበራት ካርታና ድንበር ነጻ ስትወጣ ወዲያውም ባይሆን ውሎ አድሮ ምን ዓይነት ችግር ይከሠት ይሆን? ይህስ ግንጠላ በጦርነት የታጀበ ይሆን ወይስ ያለ ጦርነት የሚጠናቀቅ? ክርስትያኑስ ማሕበረሰብ የትግራይን የክርስትና ማእከሎች በደንበር ውዝግብ ምክንያት እንዳይጎበኝ ታግዶ መቅረቱ የሚቻለው ነው? የወልቃይት የራያ ሕዝብስ እንዳለቀሰ ሊኖር ይፈረድበት ይሆን? የትግራይስ ሕዝብ ከገዛ ሀገሩ ከኢትዮጵያ ተለያይቶ መኖር ይቻለዋል ወይስ እንደ ኤርትራውያን በጀርባው ጥይት እየተተኮሰበት ድንበር እየተሻገረ ሀገሩ (ኢትዮጵያ) ይገባል?

ይሄስ ወረርሽኝ ድንገት እንደመጣ ድንገት ይጠፋል? ወይስ ሰው ሰራሽ ነው ተብሎ እንደታማው ፍጻሜው ስውን መቆጣጠሪያውን ክትባት በመውጋት ይጠናቀቃል? ክትባቱ ሴራ ነው ብለው የሚያምኑ ከመከተብ ይድናሉ ወይስ በራእየ ዮሐንሱ ”አይሸጥም አይለውጥም” ተገድደው ይከተባሉ?

መንግሥታችንስ እየተጠናከረ የቀጠለውን የኦርቶዶክስ ጄኖሳይድ ያስቆማል ወይስ ምን ያደርጋል? ተጠቂዎችን ያቋቁማል ወይስ እንዳላየ ያልፋቸዋል? ያዲስ አበባን አድላዊና ሕገወጥ ወረራስ አደብ ያስገዛል ወይስ አጠናክሮ ይቀጥላል? አስጨናቂ ጊዜ ነው።

በመጪውስ ዘመን ብጥስጥሳችንን ለማውጣት በተዘጋጀው የአፓርታይድ ሰንድ እንበጣጠሳለን ወይስ ሰነዱ ይበጣጠሳል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮምያ ቤተ ክህነት፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ - ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

በዚህ ድባብ ሆነን ይቺን ጳጉሜን ያለፈውን መዐት በቃችሁ ብሎን፣ እኛም እርቅ አውርደን፣ እግዚአብሔርም ታርቆን 2013 የሰላም፣ የፍቅር፣ የምሕረት ዘመን እንዲሆንልን በጸሎት፣ በልመና እና በንስሐ እናሳልፋት። ይቅር እንባባል። በገንዝብ ተደልለው፣ በጥላቻ ተገፋፍተው፣ በስስት ተቅበዝብዘው ያልደረሱባቸውን ወገኖቻቸውን የበደሉና የገደሉትን ይቅር ልንል እና ልንጸልይላቸው ይገባል። በቁሳዊ ጥቅም የነሆለሉትን እና በጥላቻ ስብከት የተመረዙትን ወጣቶችም ልናዝንላቸው ለነሱም ልንጸልይ ግድ ይለናል።  መሪዎቻችንም ባለማስተዋልና በፈርዖናዊ የእብሪት ጉዞ እንዳይቀጥሉ በጸሎት ልንለምን ያስፈልጋል። ፤ለሕወሃት አዛውንትም በመቃብር አፋፍ ላይ ሆነው ሀገራችንን ወደ መቃብር እንዳይገፏት ልቡና ይስጣቸው ብለን ብርቱ ጸሎት ልናቀርብ ይገባል። ለሁላችንም የፍቅር፣ የሰላም የእርቁን መንገድ ይገልጽልን ዘንድ እንጸልይ። ሁላችንም በዳዮች ነን እና የፈጣሪንም  ምሕረቱን  እንለምን።

ቤተክርስትያን “ጸልዩ በእንተ ሰላም” የሚል እጅግ በሚያምር ዜማ የሚሰማ በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርብ የግዕዝ የጸሎት ጥሪ አላት። በቅጽሯ ቆማችሁ ያንን መስማት አልናፈቃችሁም?

ጸልዩ፣ እንጸልይ

የሩፋኤል ዝናብ ዘንቦ የፈሰሰውን የንጹሐን ደም፣ ጥላቻና ኃጢአትን የሚያጥብልን ያድርገው።

መንግሥት የታሰሩትን ንጹሐን ይፍታ! ቢሆን ለፍርደኞችም ምሕረትን ያድርግ።

አዲሱን አመት የሰላም፣ የጤና፣ የእድገት (ሀ!ሀ!ሀ!) ያድርግልን። የፓርቲ ስም ልታስጠሩኝ ነበር።

 

 

2 Comments

  1. Why do you have to bring The Haile Selassie era and blame those precious years. Those years were a time where individual rights were entrenched and the law was fair to all. Criminals were punished and innocents were free. That is what is needed not blind forgiveness as you try to preach. Sorry man that is the right way to go. Or else history will repeat itself.

  2. ቢቻል 2012 ዓመተ ምህረትን ከ ኢትዮጵያውያን ህሊና ውስጥ ጨርሶ መፋቅ ነው። ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያሳዘነ ኢሰብአዊ ድርጊት የተፈፀመበት ዓመት ነውና። ይህ ዓመት ወጥቶ 2013 ዓም የምንመኘው የ ሰላም እና ፍቅር ዓመት ይሆንልን ዘንድ ጳጉሜን ሱባኤ ገብተን በ ጸሎት የምናሳልፍበት ጊዜ ሊሆን ይገባል። እኔ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ የ ከተማው የ አስተዳደር ውሃ ቧንቧዎች ሁሉ ጳጉሜ 5 ተከፍተው ሲፈሱ ያድሩ ነበር፤ የ ከተማው ሰዎች ገላቸውን ሌሊቱን ሙሉ እንዲታጠቡ በ ማሰብ። ከዚያ ሁሉም ሰው ለ አዲስ አመት አዲስ ልብስ ይለብስ ነበር። አዲሱን አመት በ ንጽህና ለ መቀበል በ ጳጉሜን ወር ሙሉ ዝግጅት ይደረግ ነበር። መንፈስን ለ ማጽዳት ሱባኤ መግባት፣ ከ ሰውነት ውስጥ ተውሳክን ለ ማስወገድ ፌጦ ፍትፍት መብላት፣ ገላን ለ ማጽዳት ጳጉሜ 5 ሌሊቱን ገላ መታጠብ እና መስከረም 1 ላይ አዲስ ልብስ መልበስ የተለመዱ ድርጊቶች ነበሩ።
    አዲሱን አመት የ ሰላም እና ደስታ ዘመን ያድርግልን። አሜን!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share