የጳጉሜ ወር – ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)

ዛሬ የጳጉሜ ወር ይጀምራል። አንዳንዴ ስለ ጳጉሜ ወር የሌለ አይነት ትርክት እንሰማለን። የዚህ ትንሽ ማስታወሻ አላማ… ሌላ አይነት ትርክት የሚናገሩትን ለመሞገት ሳይሆን፤ እውነተኛውን እና ግልጽ የሆነውን የጳጉሜ ወር ምንነት ለማሳወቅ ነው። እናም ትንሽ ስለ ጳጉሜ ወር እንጨዋወት። አንድ አመት 365 ¼ ቀናት ሲኖሩት፤ በኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ ህግ መሰረት ደግሞ፤ እያንዳንዱ ወር 30 ቀናት አሉት።
እነዚህ 12 ወራት ወይም 360 ቀናት ካለቁ በኋላ ግን፤ ሽርፍራፊና ቀሪ 5 ቀናት ይኖራሉ። እነዚህ ትርፍራፊ ቀናት በእንግሊዘኛው epagomenal days ይባላሉ። በግሪክ ደግሞ ፓጉሜን ይሉታል፤ የግሪክ አቻ ትርጉም “የተረሱ ቀናት” ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ… እነዚህ አምስት ቀናት ያሉበትን የቀናት ጥርቅም አንድ ላይ አድርገው፤ 13ኛ ወር አድርገውታል። ቃሉንም ከግሪክ በመዋስ፤ ፓጉሜን ጳጉሜ ብለነዋል።

እዚሁ ላይ እያለን፤ ስለጳጉሜ የተገረ የግሪክ አፈ-ታሪክ እናጫውታቹህ። በድሮ ጊዜ ነው። የግብጿ የሰማይ አማልክት በሆነችው ወ/ሮ ነት ላይ፤ የግሪኩ የጸሃይ ንጉስ ሄሊዮስ… እንዲህ ብሎእርግማን ያወርድባታል። “አንቺ የግብጽ ሰማይ አምላክ የሆንሽ ወ/ሮ ነት ሆይ! በሁሉም 12 ወራት አትውለጂ አትክበጂ።” ይላታል። ይሄን እርግማን የሰማው… አንድ የግብጽ ሊቅ ግን፤ ይህን እርግማን ለማክሸፍ አዲስ መላ ዘየደ። እርግማኑ እንዲደርስ የተደገመው በ12ቱ ወራት ስለሆነ፤ 5 ቀናት ያሉት 13ኛ ወር ፈጠረ። ወ/ሮ ነትም በያንዳንዱ ቀን አንዳንድ ልጅ በመውለድ፤ አምስት ልጆች ተገላገለች። ስማቸውም ኦሲሪስ፣ አይሲስ፣ ኔፕቲስ፣ ሴት እና እና አፖሎ ተባለ” ይለናል የግሪኩ አፈ-ታሪክ። ይሄን ታሪክ እንቀጥል ካልን በዚያው መስከረም ይጠባል። ምክንያቱም እነዚህ አምስት ልጆች እርስ በርስ የነበራቸው የስልጣን ሽኩቻ በራሱ ትልቅ መጽሃፍ ወጥቶታል። እንግዲህ የግሪክ እና የግብጽን ነገር፤ ከአባይ ማዶ ትተን ወደራሳችን ጳጉሜ እንመለስ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ ይባላል - አሁን ይላል

እንሆ የጳጉሜ ወር ተጀምሯል፤ ሃሙስ ምሽት ላይ ያበቃል። በኢትዮጵያ አምስቱ የጳጉሜ ወራት፤ የፍትህ እና የበጎ አድራጊዎች ቀን ተብሎ ተሰይመዋል። የፍትህ ቀን የሚለውን ጨዋታ ቃሊቲ ላይ እንተወውና… ወሩ ለበጎ አድራጊዎች መሰየሙን ግን በሙሉ ድምጽ እንደግፈዋለን። ብዙ መሰራት ያለባቸው በጎ ድርጊቶች ከፊታችን ስላሉ፤ ጳጉሜ ለበጎ አድራጎት መሰየሟን አሁንም በድጋሚ እንደግፋለን። እንዲያውም ይህ የጳጉሜ ወር… የበጎ አድራጊነት ወር በመሆን፤ ለትውልድ ቢተላለፍ እንዴት መልካም ይሆናል~*

ሌላው በጳጉሜ ወራት የሚዘንበው ዝናብ ጉዳይ ነው። በተለይም ጳጉሜ በገባ በሶስተኛው ቀን የሚዘንበው ውሃ፤ የሩፋኤል ጸበል በሚል ይወደሳል። እንዲያው የሩፋኤል ጸበል ስለሚገን ነው እንጂ፤ የጳጉሜ ዝናብ የተቀደሰ ነው ተብሎ ስለሚገመት፤ ሰዎች ያለ ዣንጥላ በጳጉሜ ካፊያ ሲመቱ፤ ህጻናቱም “እሩፋኤል አሳድገኝ” እያሉ በማውካት በዝናብ ሲበሰብሱ፤ አንዳችም ከልካይ የላቸውም ነበር (የአሁኑን አላውቅም ለማለት ሳይሆን…)። ሌሎች ደግሞ ይህን የጳጉሜ ዝናብ በንጹህ እቃ ውስጥ በማስቀመጥ እንደጸበል ይጠቀሙበታል። ስለጳጉሜ እና ስለዝናቡ ስናወጋ ጨዋታችንን ወደ ዘር ወይም ወደ ሃይማኖት የሚመነዝሩ ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ እነሱን “ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድላቹህ። የጳጉሜ ጸበል አይለያቹህ!” በማለት ወደ አዲሱ አመት የምታሸጋግረን ጳጉሜ ወር ስለጀመረች፤ መልካም ጳጉሜ – መልካም አዲስ አመት እንላለን።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share