እንኳን ለቡሄ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በዚች ጽሑፍ ላነሳላችሁ የፈለግሁት የቡሄ ትዝታ ብዙዎቻችን ወንዶች ልጆች በሰፈር ውስጥ ጨፍረን እያከበርን ያደግንበትን የቡሄ በዓል አከባበር የሚመለከት አይደለም። ያንን ከጅራፍ መግመድ እስከ ችቦ መሥራት፣ የቡሄ ግጥም ማውረድ ልምምድ አድርጎ፣ የሰዎችን ስም አጥንቶ፣ በጥቃቅን ተደራጅቶ ሠፈሩን ተከፋፍሎ በጭፈራ የመውረር ባሕል በተለያየ መልኩ ሁሉም ትውስታውን እያጋራ ነው። የአሲዮ ቤሌማው ድምቀት፣ የጅራፉ ጩኸት፣ የሙልሙሉ ሽታ፣ ከነሐሴው ጭጋግ የሚቀላቀለው የዳቦው ጭስ ይሄ ሁሉ በማይገኝበት ቦታም በስደት ላለን ሰዎች በምናባችን የሚመጣ የበዓሉ መዓዛ ነው።
እኔ ላወሳ የፈለግኩት ከጎለመስኩ በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ ባጋጣሚ በተገኘሁባቸው የቡሄ በዓላት ያጋጠሙኝን የተለዩ ትውስታዎች ነው። ከእነዚህም ለዛሬ የማካፍላችሁ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የተያያዙ ትውስታዎች ናቸው።
ጥቂት ሙስሊሞች በሰፈራችን ቢኖሩም እኔ ሳድግ ሰፈር ተከፋፍለን ቡሄ በምንጨፍርበት አነስተኛ ቀጠና በአጋጣሚ ሁላችንም ክርስትያኖች ነበርን። ታድያ ከስደት በተመለስኩባቸው በነሐሴ አሥራ ሁለት ምሽት (የቡሄ ዋዜማ) ላይ ቡሄ የሚጨፍሩ ልጆች መንገድ ላይ አየሁና ብዙ ቤቶችን እየዘለሉና እያለፉ ሲሄዱ አስተውዬ
ለምን መደዳውን አትጨፍሩም አልኳቸው።
አንዳንዶቹ ቤቶች አምና ተቆጥተው አባርረውናል። አሉኝ።
እኔም በጣም አዝኜ፣ እንዲህ እያሉ ልጆቹን ማሳቀቅ ተገቢ አይደለም አልኩ ለራሴ። ነገ እቤት ጠብቄ እንዲያውም ራሴ በር ከፍቼ ነው የምቀበላቸው አልኩና በበነጋታው ሆያ ሆዬ! እያሉ ሲመጡ ቶሎ በሩን ከፈትኩላቸው። የማታዎቹ አይደሉም ሌሎች ናቸው። የግጥማቸው ነገር መቼም በሳቅ ነው የሚያፈነዳው። ኮምፒውተር፣ ቪ8፣ ኦባማ ምናንም ነው። እንደኛ ጊዜ ጥጃ፣ ሙክት፣ ፍሪዳ፣ ጦጣ፣ አንበሳ፣ የሉም። ያው “አጋፋሪ ይደግሳል” አልቀረችም። እስኪደክማቸው አስጨፍሬ ግጥሞቹ ሲያልቁባቸው ሞቅ ያለ የሽልማት ብር አወጣሁና አሳይቺያቸው “አመት አውዳመት” ብለው እንደመረቁ ማን ነው ገንዘብ ያዥ አልኳቸው።
ከማል ነው! ከማል ነው! ተባባሉ።
ድንጋጤዬን እንደምንም ደብቄ ለአውራጁ አድናቆቴን ገለጽኩና
ትንሽ ጉርሻ ብሰጠው ቅር ይላችኋል? አልኳቸው። እሱ ቀደመኝና ሁሉም ሽልማት ለከማል ነው የሚሰጠው አለኝ። አሁንም ተገርሜ ማን ነው ስምህ አንተ አልኩት። አውራጁን።
ኢድሪስ።
እር…ፍ! ሰፈራችን የገበያ ማእከል ከመሆኑም ሌላ እኔ ከሀገር ከወጣሁ በኋላ በአቅራቢያችን አንድ መስጊድ ተሠርቷል። ይሁንና በዚያን ወቅት አክራሪ እስልምና ሊበላህ ነው የሚል ድራማ እነመለስ እየተወኑ የነበረበት ወቅት ስለነበር የአርብ ሶላት እንኳን ሳይቀር በመቶ ፖሊስ (እያጋነንኩ አይደለም) እየታጀበ ነበር የሚሰገደው። እና በዚህ ድባብ እያሉ መሠረታዊ አመጣጡ የክርስትና በሆነ በዓል ላይ ቤተሰቦች ፈቅደው ልጆቻቸውን ለቡሄ ጭፈራ ይልካሉ ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም። ልጆቹ ቡሄ የሚጨፍሩት በራሳቸው ተነሳሺነት ቤተሰብ ሳይጠይቁ ወይም ሳይፈቅድላቸው ይሆን?
ይሄንን ጥያቄ የመለሰልኝ ደግሞ ቀጥሎ ያጋጠመኝ ነገር ነው። የኤሌክትሮኒክ እቃ ተበላሽቶብኝ ሰዎች ስጠይቅ ጎላጎል ፊትለፊት መንገድ ተሻግሮ ያሉ አርከበ ሱቆች ውስጥ በጣም ጥሩ የኤሌክትሮኒክስ እድሳት የሚሰራበት ሱቅ አለ ብለውኝ ወደዚያው አመራሁ። የነገሩኝ ሱቅ ስደርስ የእቃውን ችግር አስረዳሁና እሺ እሰራልሃለሁ አለችኝ ባለሱቋ። ይቅርታ አድርጉልኝና የጠበቅኩት ቴክኒሺያን ወንድ ነበር። ይቺ ግን በእስላማዊ አለባበስ ሙሉ በሙሉ የተሸፋፈነች ሴት ናት። ወዲያው እቃውን ብትንትን አድርጋ መስራት ጀመረች። ጠባቧ ሱቅ ውስጥ መሬት ላይ ልጇ ቁርዓን ይቀራል። በግምት የአሥር ዓመት ልጅ ይሆናል። ወዲያው ሱቁን “መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ” በሚል መግቢያ የቡሄ ጨፋሪዎች በጭፈራ ደበላለቁት። ሴቲቱም ጥቂት ሰማቻቸውና ብዙ ብሮች አውጥታ ሰጠቻቸው። መርቀው ሊሄዱ ሲሉ ድንገት ከሰመመን እንደነቃች ወደልጇ ዞራ “አንተ፣ በቃህ እስኪ ደግሞ ከልጆቹ ጋር ውጣና ተፍታተህ ና” ብላ አጣድፋ “ልጆች ጠብቁት” ብላ የመጥረጊያ ዱላ አስይዛ ላከችው። ያየሁትን ማመን ነበር ያቃተኝ። እስኪ ልመራመር አልኩና “ታውቂያለሽ ይሄ እኮ የደብረ ታቦርን መገለጥ የሚያዘክር የክርስትና በዓል ነው” አልኳት። “ኧረ ተወኝ! እነዚህ ልጆች አሁን ምኑን ያውቁታል? እሱም ተለይቶ ከሚቀር ከነርሱው ጋር ተዘዋውሮ ጨፍሮ ቢመጣ ይሻላል። ” ብላኝ ወደ ሥራዋ ተመለሰች።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ይሄንንም ትመስላለች። አውቀን አንጨርሳትም። ሁል ጊዜ ያላወቅነውን አንድ ሌላ ገጽታዋን ታሳየናለች። እጅግ በጣም ለምወደው የቡሄ በዓል እጅግ የሚገርምና አስተማሪ መልካም ትዝታ ተጨምሮልኛልና ደስተኛ ነኝ።
መልካም የቡሄ በዓል።
አሁንገና ዓለማየሁ