ትኋኑን ለማጥፋት ቤቱን ማቃጠል አይኖርብንም! – የኢትዮጵያን ነቀርሳዎች ለማከም ኢትዮጵያ መፍረስ የለባትም!!!

አንድነት ይበልጣል
ሐዋሳ – ነሐሴ 12/12/12

መንደርደሪያ

በሕይወታችንና በታሪክ ውስጥ ተመልሰው ሊመጡ የማይችሉ ክስተት ቀናትን እየጠበቁ የደምና የሞት ድግስ የሚደግሱልንን ጆሮ መከልከል ብቻ ሣይሆን በቃ! ተው! ማለት አለብን፡፡ አምና 11/11/11 ብለው ኤጀቶዎች የንጹሃን ደም አፈሰሱ፡፡ አሁን ደግሞ 12/12/12 ብለው የነ ጀዋር/በቀለ ገርባ፣ ኦነግ-ሸኔና የወያኔ ጽንፈኛ ቡድን ሌላ ዙር የደምና የሞት ድግስ እንድንሳተፍ ጠርተውናል፡፡ ይህን እኩይ ጥሪ መንግሥትም ሆነ ሰላም፣ አንድነትና ነጻነት ፈላጊ ዜጋ ሁሉ ቀልብና ቦታ እንደማይሰጠው እየታየ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ በበጎዎችና በክፉዎች መካከል ያለው የኃይል ሚዛን በጥሩ ተቀይሯል፡፡ ሰይጣን ሰይጣን ነው፡፡ እኩይ ሃሳብና ድርጊትንም ሲዖል እስካልወረደ ድረስ አይተውም፡፡ ባሀርይ ነው፡፡ በቅርብ ሣምንታት 4 ጊዜ የደምና የሞት ግብዣ አዘጋጅቶ የታደመለት የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሌላ ሐገር ቪዲዮ ቆርጦ በመለጠፍ (ቨርቹዋል ፓርቲ በማሳየት) “ተመልከቱ! ድግሳችን ተሳክቷል” ብለው ሲዋሹ ታዝበናል፡፡ በጎ ዜጎች  ክስተት የሆኑ እንደ 12/12/12 ያሉ ቀናትን በበጎ ሥራና አሻራ ማስተናገድ አለብን፡፡ አሁን አልፏል፤ ሰዓታት ነው የቀሩን፡፡ በእጃችን ያለው ዕድልና አቅም – ከእኩዮችና ከሰይጣኖች ጋር ወደፊት፣ ምንጊዜም ቢሆን አንተባበርም ማለት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ሠይጣኖች ሐገር አፍራሽ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ማስገደድ ይኖርብናል፡፡ እዚህ የቀረበው የክፍል አንድ ጽሁፍም ይህ መንፈስ አለው፡፡ ፈጣሪ ትዕግሥቱን ይስጠን! መልካም ንባብ፡፡

 

መግቢያ

የትኋኑ ወግ – መነሻና ግብ

በዚህ ጽሁፍ ትኋን የምለው የዘመናት ችግሮቻችንን፣ ዋነኛ ፈጣሪዎቻቸውንና ተሸካሚዎቻቸውን፣ ተቋሞቹን፣ ሕጎቹንና አሠራሮችን እና በሐገር፣ በወገንና በትውልድ ላይ እያደረሱት ያለውን ጥፋት ነው፡፡ ዛሬ ሐገራችን እጅግ ሥር በሰደዱ፣ በበዙና በተወሳሰቡ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች፤ እርግጥ ከወዲሁ ግልጽ ለማድረግ – ከፊታችን የሚታየውም ተስፋ ለኔ ብሩህ ነው፡፡ ወደ መጨረሻ እናየዋለን፡፡ ሆኖም ችግርና ተግዳሮትን መንስኤና ውጤቱን በትክክል ለይቶ ማወቅ የመፍትሔውን ግማሽ እንደማግኘት ስለሚቆጠር የትኋኑን ወግ በግልጽ እናወጋለን፡፡ ይህ የትኋኑ ወግ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ፣ የፍትሕ፣ የጸጥታና የሰብዐዊ መብቶች አውዶች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያግዛል ብዬ አምናለሁ፡፡ አኩሪ በሆነው የ10 ሺህ ዓመታት የጋራ ታሪካችን ውስጥ በጎም ክፉም ነገሮች መጥተው ሄደዋል፡፡ በተለይ በቅርቡ የ150 እና 200 ዓመታት ታሪካችን ውስጥ በተለያዩ ሰዎችና ቦታዎች (ጥሩም ይሁን ነውር) ያልተፈጸመውን ድርጊት እንደተፈጸመ፣ የተፈጸመውን ደግሞ እንዳልተፈጸመ አድርገው የፈጠራ ትርክት እያዘጋጁና እየነዙ “ዓይናችሁን በግድ ጨፍኑ እናሞኛችሁ” ሲሉን፣ እንዳንረሳው ሲጨቀጭቁን፣ ሲያጨቃጭቁን፣ ሲያስጨንቁንና ሲያሸማቅቁን መኖራቸውን እናስታውሳለን፡፡ ዛሬ ደግሞ ከ2 ተኩል ዓመት (ከለውጡ) በፊት በነበሩት 30 – 40 የቅርብ ዓመታት ውስጥ የፈጸሙብንን ግፍና በደል ለመማሪያም ቢሆን አታንሱ አታስታውሱ ይሉናል፡፡ ዛሬ እያጨድን ያለነው፣ የወያኔ ገዢዎች ለዓመታት የዘሩትን የዘረኝነት፣ የጽንፈኝነት፣ የሥራ አጥነት፣ የድህነትና የጥላቻ መርዛማ ፍሬ ነው፡፡ ዛሬ እየተሰቃየን ያለነው እነርሱ ራሳቸው የቀበሩብን የጥላቻ ቦምብ ጊዜውን ጠብቆ እዚህም እዚያም እየፈነዳ በመሆኑ ነው፡፡ ያለፈው ነውር አልበቃቸውም፤ አሁንም አዳዲስ ጥላቻ፣ ጥቃትና ግጭቶችን ይቀይሳሉ፣ ስስ ብልቶችን ያሸቱና ረብሻ ያቅዳሉ፣ በየክልሉ ያሏቸውን የድሮና አዳዲስ የግንኙነት መረቦችና ተላላኪዎችን ተጠቅመው፣ በገንዘብም እየደገፉ ሐገር ማተራመሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ የቀድሞው ሆነ የአሁኑ ወንጀላቸው እንዲነሳባቸው ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ እጅግ ፈርተዋል፡፡ አሁንም ራሳቸው ለሚለኩሱት የጥፋት እሳትና ለሚደርሰው ውድመት ሁሉ ከሥልጣን ያባረራቸውን መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግና ዕዳውን ለማላከክ የማያባራ ጨኸት ያሰማሉ፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል”፡፡ የወያኔ ቁንጮዎች እነ ስብሐት ነጋ፣ አባይ ጸሐዬ፣ ስዩም መስፍን፣ ዓለም ገ/ዋሕድ፣ አስመላሽ ወዘተ “አሐዳዊውና አምባገነኑ የአቢይ መንግሥት” ሲሉ አያፍሩም፤ ለኛ ግን አይገርምም?!፡፡ ራሱ በደም የጨቀየና ሐገርን በደም ያጨቀየ ገዳይና ዘራፊ ሁላ ደርሶ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ – ጠበቃ ሲመስል ያስቆጣል፡፡ ወያኔ፣ ትናንት ብቻ ሣይሆን ዛሬም ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን እየደፈጠጠና እያስደፈጠጠ የመብት ተሟጋች መስሎ ለመታየት የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ለፈጸመው የዘር ማጥፋትና ጄኖሳይድ፣ ከሐገር ውስጥ ፍርድ ቤት አልፎ ገና በዓለም የፍትሕ አደባባይ የሚገተር ወንጀለኛ ቡድን ነው – ወያኔ፡፡  “ባድመ ለኛ ተፈረደልን” ብሎ ዋሽቶ ካድሬዎቹንና የዋሆችን ለሰልፍ አደባባይ ያስወጣው ውሸታሙ ስዩም መስፍን (ስድብ አይደለም- ግብርን መግለጽ ነው)፣ ዛሬ በሱ ብሶ “ውሸታቸውን ነው ዓባይን ሸጠውታል …” አለ፤ የዘር ጥቃትና የእርስበርስ ግጭት መሐንዲሱና ፀረ-ሰላሙ ስዩም መስፍን፣ ሌሎች ጎበዞችን “የሰላም ኖቤል ሽልማታቸው ይነጠቅ” ለማለት የሞራል ብቃቱን ከየት ሊያመጣው ይችላል?! የሌባ ዓይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ!! ዕውነቱማ ተደጋግሞ መነገር አለበት!! ያውም የማያባራውን የነርሱን ዓይን ያወጣ ክህደት፣ ቅጥፈትና ድርቅና እያየን እንዴት ዝም ልንል ይቻለናል? ዝም እስኪሉ ድረስ (እንደነርሱ በመግደል ሣይሆን) አካፋን አካፋ በማለት በቃችሁ ማለት ይገባናል፡፡ እዚህ የሚቀርበው የትኋኑ ወግ መነሻና ግቡ ይህም ጭምር ነው – የችግራችንን ዕውነተኛ ምንጭ፣ መገለጫዎቹን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መጠቆም – ለዚህም ብጥስጥስ ሁነቶችና ጭብጦችን ሳይሆን ትልቁን ሥዕልና አጠቃላይ አውዱን ማሣየት፡፡ መፍትሔዎቻችንን ለዛሬ የሚደርሱና የማይደርሱ ብለን ከጊዜና ከአውድ አንጻር ለሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ ውጤታቸው ለዛሬ/አሁኑኑ የማይደርስ ነገር ግን ዛሬውኑ መጀመር ያለባቸው መፍትሔዎችን እንዲሁም ውጤታቸው ለዛሬ የሚደርስና አሁኑኑ መገኘትና መተግበርም ያለባቸውን መፍትሔዎችን (ክፍል ሁለት) አንድ በአንድ እናያለን፡፡ አሁን እያሰቃዩን ላሉ ሐገራዊ ቀውሶች የዳረጉንን እና እንደሐገር የደረሱብንን ጉዳቶች ከነመቼታቸው ለማየት እንሞክር፡፡

 

እርግጥ ኢትዮጵያን የሚጎዳና እንዲያውም ወደ ጥፋት የሚወስድ ሥራ የተጀመረው ከወያኔ በጣም በጣም በፊትም ነው፡፡ የአፄዎች አብርሓና አጽብሐ የጋራና የፈረቃ የዙፋን ዘመን (310 – 409 ዓ.ም.) እንዳበቃ የተጀመረ የአክሱም ሥልጣኔ የድክመት ታሪካችን አለ፡፡ አፄ ዋዜብ (409 – 440) በወዳጅነት ስም ራሱን በሮማው ቄሣር ቴዎድስዮስና በእስክንድርያ መንበር (ግብጽ) የፖለቲካና የኃይማኖት ተጽዕኖ ሥር ከጣለ ጊዜ የሚጀምር ነው …፡፡ እዚህ ለተነሳንበት ዓላማ እንዲጠቅመን፣ የቅርብ ዓመታቱን ስህተትና ጥፋት ብቻ በወፍ-በረር እንይ፤ ደርግ በሥልጣን ላይ፣ ወያኔ በበረሃ የነበሩበትን ጊዜና ወያኔም ሥልጣን ላይ የቆየባቸውን ጊዜያት ማለቴ ነው፤ 45 ዓመታት ናቸው፡፡ ችግሩ እጅግ የተባባሰውና አስፈሪ ደረጃ የደረሰው በወያኔ የአገዛዝ ጊዜ ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያ ላይ እንደ ሐገር የፈጸመው ጥፋት እንዲሁ በዋዛና በግብታዊነት የተፈጸመ አይደለም፡፡

 

የኢትዮጵያን ደም መጦ-መጦ አጥንቷን ያስቀራት ትኋን እንዴት ያለ ነው? መገለጫዎቹስ?

ሐገርን ለማፍረስና ትውልድን ለማምከን፣ በመርሐግብር፣ በሕገ መንግስት፣ በአዋጅ፣ በፖሊሲ፣ እንደገና በመርሐግብር፣ በአሠራርና በደንቦች፣ በመመሪያዎች፣ በባለብዙ እርከን መዋቅር፣ በከፍተኛ ንዋይና የሰው ኃይል የተደገፈ እኩይ ሥራ ያለማቋረጥ ለአሠርታት ተሠርቷል፡፡ በትኋን የሚመሰሉት፣ በደም የጨቀዩትና ዘራፊዎቹ የወያኔ ክፉ ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ክፉ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍናና ግባቸው፣ የልቡና ውቅራቸው፣ ሕጋቸው፣ ተቋማቸው፣ አሠራርና ሥልታቸው፣ ድርጊታቸው፣ ዝንባሌያቸው፣ መሻታቸውና ዕቅዳቸውም ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡ የትልቁ ትኋን መንስኤ፣ ሂደቱ፣ መዘዙ፣ ውጤቱና አዝማሚያውም ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡

 

ትምህርትና የትምህርት ተቋማት፡ የወያኔ የትምህርት ፖሊሲና ሥርዓተ ትምህርቱም እንዲሁ ትውልዱን አቅመ ቢስ አደረገው፤ የግብረገብ ትምህርት እንደነውር ተቆጥሮ ገለል ተደረገ፣ የሥነዜጋ ትምህርት አፋዊ ብቻ ከመሆኑም በላይ የወያኔን መመሪያ መጋቻ ብቻ ተደረገ፡፡ ድካም በሞላው የአንደኛና የአጠቃላይ ደረጃ ትምህርት አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል ወደ መምሕራን ማሠልጠኛ ገብተው “ተመርቀው” የኢትዮጵያን ሕጻናትና ልጆችን እንዲያስተምሩና ለሕይወት እንዲያዘጋጁ ተደረገ፤ እነዚህ አስተማሪዎች የሚወክሉት ግዙፍ ኃይል ነው፡፡ አደራ የተቀበሉትም የብዙ ሚሊዮን የ1ኛ ደረጃ ህጻናትን፣ የሐገርና የትውልድ ዕጣ ፈንታ፣ የዕድገት ሁኔታ ነው፡፡ ሊከተል የሚችለውንና የተከተለውን ጨርሱት…፡፡ በጊዜው ኧረ አይሆንም ያለ የደረሰበትን ቢያንስ ራሱ ያውቀዋል! እዚህ ላይ ተቃርኖ የሚመስል ገራሚ ነገር አለ (Paradox)፤ ልጆቹ በ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዝቅተኛ ውጤታቸው ምክንያት መሰናዶ ት/ቤት (በኋላም ዪኒቨርሲቲ) መግባት አይችሉም ነበር፡፡ በዚህ አሠራር ምክንያት መምሕራን ማሠልጠኛ ገብተው ከተመረቁት መካከል እጅግ ጥቂቶቹ ዛሬ የምር “የትና የት” ደርሰዋል፡፡ ችግሩ የምልመላው ሥርዓት ብልሹነት ብቻ አይደለም፤ የትምህርት ፖሊሲውና ሥርዓተ ትምህርቱ ትውልዱን ከታች እስከ ላይ ከታሪኩ ነቅሎ፣ ከወገኑ ነጥሎ በሐሰት ትርክት አደንቁሮ በአጠቃላይ ባዶ አደረገው፤ ከሐገሩ፣ ከገዛ ሕዝቡና ከወገን ዘመዱ አቃቃረው፤ አስተዋይ ችግር ፈቺና የመፍትሔ አካል ሣይሆን ዋና ችግር ፈጣሪና አቀጣጣይ አድርጎ ሠራው፡፡ ሌላም ችግር እንጠቁም፤ ከወያኔ መሪዎች ጥቂት የማይባሉት የንጉሡ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አንድ በራሳቸው ላይ ደርሶ የሚያውቁት ዕውነት አለ፡፡ የተማሪዎች የመብት ጥያቄ አብዛኛውን ጊዜ የሚቀሰቀሰው የማሕበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች በስፋት ከሚገኙበት አዲስ አበባ ከ6ኪሎ ዋናው ግቢ ነበር፡፡ 4 ኪሎ ግቢ የሚማሩት የተፈጥሮ ሣይንስ ተማሪዎች ናቸው፤ እናም 6 ኪሎ የተጀመረውን ትግል የሚቀላቀሉት ብዙውን ጊዜ ዘግይተው ነው ይባል ነበር፡፡ ራሳቸው ያለፉበትን ይህን አካሄድና ውጤቱን የተረዱ የሚመስሉት የወያኔ ሤረኛ መሪዎች ሊነሳባቸው የሚችለውን የተማሪዎች ተቃውሞ ሊያስቀሩ ወይም ሊቀንሱ የሚችሉበትን ሥልት ሲፈልጉ ያገኙት የሚከተለውን የነበረ ይመስላል፤ የሽፋን ሰበቦቹ ሌላ ቢሆኑም፣ የከፍተኛ ትምህርትን የቆይታ ጊዜ በአብዛኛው 3 ዓመት ብቻ ማድረግ፣ በተጨማሪም 70 በመቶ የሚሆነውን መርሐ ግብር እና ተማሪ በተፈጥሮ ሣይንስ መስክ እንዲሆንና 30 በመቶ ብቻ የሚሆነውን መርሐ ግብር እና ተማሪ በማሕበራዊ ሳይንስ መስኮች እንዲሆን ማድረግ፡፡ ጭልጥ ብሎ ወደ ተፈጥሮ ሣይንስ ያደላውን ይህን አመዳደብ ተከትሎ የታሪክ ትምህርት ክፍሎች እስከመዘጋት ደርሰው ነበር፡፡ በወያኔ የመጀመሪያ ዓመታት 42 የሚደርሱ ጉምቱ ፕሮፌሰሮችን ከሥራ የማባረሩ ተንኮልም አይረሳም፡፡ የተማሪዎች፣ የመምሕራን፣ የአመራርና የአስተዳደር ሠራተኞች የዩኒቨርሲቲ ምደባም ባብዛኛው ሐገራዊ ስብጥሩና ውህደቱ ቀረ፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢያቸው የተውጣጡ የአንድ ብሔር ተማሪዎች … የበላይነት ጎልቶ የሚታይባቸው እንዲሆኑ ሆን ተብሎ ተደረገ፡፡ የተከተለውን ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የትምህርት ፖሊሲና ሥርዓቱ ሥራ አጥ ትውልድ ለመቀፍቀፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በዚህ መጠን ትውልዱን ካኮላሹ በኋላ ወጣቶችን “ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ በምክንያት የማይመሩ፣ በስሜት የሚነዱ፣ መንጋዎች በመንጋ የሚያስቡ ወዘተ” ብለን ስንኮንናቸውና ስንፈርድባችው አልመች ይላል፡፡ የማይመቸው ለሥርዓቱ/ለራሳችን የጥፋት ሥራ፣ ውጤቶቹን ማለትም ሰለባዎቹን መልሰን መኮነንና ማውገዝ ስለሚሆንብን ነው – Blaming the Victims:: ያጠፋቸው ወያኔ (የእኛም አስተዋጽዖ ሳይዘነጋ) ሆኖ ሳለ የሚኮነኑት ግን ወጣቶቹ ብቻ! ይህ ልክ (Fair) አይሆንም፡፡ ያም ሆነ ይህ ዛሬ በስሜታዊ፣ ጭፍንና ጽንፈኛ ወጣቶች እኩይ ድርጊት እየተጎዳን ነው፡፡ እንደቀድሞው ሀሉ አሁንም ቢሆን የወጣቶቹን የእኩይ ድርጊት ዋነኛው ቀያሽ፣ መሪ፣ አሰማሪና በገንዘብ ደጋፊ ወያኔ ነው፡፡ ትኋኑን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልም፡፡ ልጆቹንም ተቋማቱንም ማከም፣ ማስተካከልና ሥርዓት ማስያዝ ነው መፍትሔው፡፡ በዚህም ረገድ መንግሥት አበረታች እርምጃዎች እንደጀመረ እያየን ነው፡፡ ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡

 

የሜዲያ ተቋማት፡ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን የሜዲያ ተቋማቱ ትኋን ነበሩ! ትውልዱን እንዳይሆን አድርገው በውሸት ፕሮፓጋንዳ አሳስተው አደነዘዙት፤ “የሕዝብ ኑሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በኢትዮጵያ መሬት ላይ” በሚል ርዕሥ ከ10 ዓመት በፊት የጻፍኩት ባለ 2 ክፍል ጽሁፍ አለ፡፡ የሜዲያቸውን የፕሮፓጋንዳ ክፋት፣ ክርፋት፣ ድርቅናና አስቀያሚነት የገለጽኩበት ይመስለኛል፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የመንግሥት ሜዲያ ተቋማቱ ብቻቸውን ተንሠራፍተው ያለተቀናቃኝ ትውልዱን ሲያደነዝዙ “ኖሩ”፡፡ ሌሎች ለትውልዱ ትክክለኛና ጠቃሚ መረጃ እንዳያቀርቡ፣ እንዳያስተምሩት ተከለከሉ፡፡ ዕውነቱን በመናገርና በማሳየት ትውልድ ለማነጽ የሞከሩ የግል ጋዜጦች ተዘጉ፤ አዘጋጆቹ ከሚወዷት ሐገራቸው ተሰደዱ፤ አንዳንዶቹም ወህኒ ተወረወሩ፤ በጸረ-ሽብር ሕግ ተከሰው በሌሉበት ከፍተኛ ቅጣት እንደተፈረደባቸው እናስታውሳለን፡፡ የመንግሥታዊው የማሠራጫ ሜዲያው ትኋን ያሰለቸውና ያስመረረው፣ በሳተላይት የቴሌቪዥን ሥርጭት የጣቢያዎች ዝርዝር ላይ EBC የሚለውን ስም አጥፍቶ YENNESU TV (የነርሱ ቴቪ እንደማለት) በሚል ለውጦ የኖረ ሰው አውቃለሁ፡፡ አንዳንድ ብልጥ ጋዜጠኞች ደግሞ የወያኔን ቅዝምዝም ጎንበስ ብለው ለማሳለፍ ሲሉ የሚዲያ አቅርቦታቸውን ሁሉ ተግሳጽ እንኳን በማያስከትሉ፣ ለስላሳና “ገብስ-ገብስ” የመዝናኛና ማሕራዊ ጉዳዮች ገድበው ክፉውን ጊዜ እንደሸወዱት እናውቃለን፡፡ ሰው የኢሳት ጣቢያን እንዳይከታተል ዲሽ እስከማስወረድ የደረሰ ከትትልና ስለላ ይደረግ ነበር፤ በቴሌቪዥናቸው ላይ የኢሳትን የጣቢያ ስም ቀይረው በሳሎን ያቆዩ ወይም የሳሎኑን አጥፍተው በጓዳ ቴሌቪዥን ጣቢያውን ሲከታተሉ ያን ክፉ (የትኋን) ጊዜ ያሳለፉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በጎና ክፉ ሜዲያዎች ትውልዱን ለማነጽ ወይም ለማደንዘዝ ቀላል ተጓተቱ?! ከሰብዓዊነት፣ ከግብረገብነት፣ ከእምነታችንና ከባህላዊ እሴቶቻችን ተቃራኒ የሆኑ ነውሮችና ብልግናዎችን በአደባባይ ያሰራጩ የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ተስፋፍተው የታዩበት ዘመን የወያኔ ዘመን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውንና የደረሰውን ጉዳት ከመገመት ሌላ ምን ልናደርግ እንችላለን? ዛሬ እግዚአብሔር ይመስገን – ጊዜው በጥሩ ተቀየረና የድሮዎቹ ክፉዎቹም፣ ብልጦቹም አሰላለፍ አስተካክለው ተከስተዋል፤ ዋናው የሚፈለገው ይኸው ነው! እኛም መመልከት ጀምረናል፡፡ አሁን YENESU TV የሚለው ተለውጦ ETV በሚለው ተተክቶ በዝርዝሩ የመጀመሪያ ረድፍ ይታያል፡፡ በትናንት በጎነታቸው ለቀጠሉ ጀግና ሜዲያዎችና ጋዜጠኞቻችን (ኢሳት፣ ፍትሕ..) ፈጣሪ ጤናና ክብረት ይስጥልን! መንግሥትም ለሜዲያው አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ያወጣቸውን የሜዲያ ሕግጋት በቁርጠኝነት ማስፈጸም ይኖርበታል፤ ተገቢው ድጋፍ ሳይለይ፡፡ የሙያ ሥነምግባራቸውን አክብረው በኃላፊነትና በገለልተኛነት የማይሠሩ የ”በለው-በለው” ሜዲያ ተቋማትን በሕጉ መሠረት ማከምና ሥርዓት ማስያዝ ይገባል፤ ካልሆነም ህጉ የሚፈቅደውን የመጨረሻ እርምጃ መውሰድ ነው! ትኋኑን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ የለም! - ጠገናው ጎሹ

 

የኃይማኖት ተቋማት፡ የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸው እጅ-እግራቸው ታስሮና ታፍነው ኖሩ፣ ከምእመኖቻቸው ተራርቀውና ሌላው ቀርቶ እርስ በርስም እየተናቆሩ ባዶአቸውን በአስፈሪ ጸጥታ “ቆዩ”፤ የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች የሐገር ውስጥና የውጭ ሲኖዶሶች ተብለው ተከፋፈሉ፤ ሁሉም በአንድነትም ሆነ በያሉበት ሆነው የመንፈስ ልጆቻቸውንና ትውልዱን ለምድሩም ለሰማዩም ሕይወት ማዘጋጀት ሲገባቸው፣ እርስ በርስ እንዲናቆሩ ተደረገ፡፡ እንዳይታረቁ እንኳ የነበረው የወያኔ አሻጥርና ዕንቅፋት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ “ኢትዮጵያን ለመበተን አንዱ መፍረስ ያለበት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነው” ተብሎ በዕቅድ የተጀመረው የሕወሐት ዘመቻ በስብሐት ነጋና በአንድ መምሕር ፊታውራሪነት ለበርካታ ዓመታት ቀጥሎ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ Political History of TPLF በሚለው፣ የዓይን እማኙ የዶ/ር አረጋዊ በርሔ የምርምር ጽሁፍ ውስጥ ይህን ጉዳይ በቀጥታ የሚዳስስ ክፍል ከአመታት በፊት ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ወያኔ ከበረሐ ጀምሮ እግሩን ባስገባባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ገዳማት ውስጥ ሰላዮቹን መነኩሴ አስመስሎ አስርጓል፣ ወይም በውስጥ የነበሩትን መልምሏል፡፡ በዚህ አሠራሩ የኦርቶዶክስን መዋቅር እንዴት እየወረረ እንደመጣና በአገዛዝ ዘመኑም ይህ እንደቀጠለ እናውቃለን፡፡ “አቡነ ጳውሎስና መለስ ዜናዊ የወንድማማች ልጆችና ናቸው፤ ስብሐት ነጋ የመለስ ዜናዊ “ክርስትና” አባት ነው”፣ የሚሉት የሰሞኑ ዜናዎች አንደምታቸው ብዙ ነው፡፡ ሁለቱም በሕይወት በነበሩ ጊዜ፣ አቡነ ጳውሎስ አንዳንዴ በስጨት ሲሉ እስቲ ልጄ (መለስ) ጋ ደርሼ ልምጣ እያሉ ያስፈራሩ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ፓትርያርክና አምባገነን ገዢ በዚህ ልክ እፍ ካሉ የኃይማኖት ነጻነት እንዴት ሊኖር ይችላል? ስብሐት ነጋ (የዛሬን አያድርገውና አይባልም)፣ አ.አ. በነበረበት ጊዜ፣ ከአባይ ጸሐዬ ጋር ሆኖ ቤተክህነትንና አንዳንድ መንፈሳዊ ተቋማትን እንዴት ይዘውርና ያተራምስ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ቤተክህነቱ በሕወሐት ደህንነቶች ተወርሮ ነበር! “የዋልድባ ገዳምና የሕወሐት” ታሪክም በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅም አይመስልም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ መሃል ቤተክርስቲያኒቱስ እንዴት ብላ ለምዕመናኖቿ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ልትወጣና ልጆቿን በግብረገብነት ኮትኩታ ልታሳድግ ትችላለች? ለማንኛውም ትኋን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልም! – የተዋሕዶ/ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሆነች ሌሎቹ የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን በደንብ ማከም ነው የሚበጃቸው፡፡ በዚህ ረገድ ምዕመኖቻቸውም የበኩላችንን ግፊትና አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን፡፡ የኢትዮጵያን ነቀርሳዎች ለማከም ኢትዮጵያና ትልልቅ ምሰሶዎቿ መጎነታተልና መፍረስ የለባቸውም!!! በኢትዮጵያ የእስልምና ተቋምና ክፍሎቹ ላይ የተፈጸመው ግፍና መከፋፈልም ከዚህ ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይመስለኝም፡፡ የእስልምና መሪዎችና መምሕራን ለስደትና ለእሥር ተዳርገው፣ ተቋሞቻቸውን ተነጥቀው፣ መስጊዶች ከላይ እስከታች ምዕምናን ባልተቀበሏቸው “የመንግሥት ሰዎች” ተወርረው ነበር፡፡ በአፈና ተይዘውና “በድምጻችን ይሰማ” ትግል ተወጥረው ምዕመናኖቻቸውንና ትውልዱን እንደምን ማነጽ ይቻላቸዋል? የትኋኑን መንስኤ፣ መዘዝና ጦስ እየተመለከታችሁ ነው? ትውልድ እንዴት ይዳን?! … የኃይማኖት ተቋማት ቀኖናቸውን የጠበቀ የተኃድሶ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ መንግሥት ለኃይማኖት ተቋማት ያለአድልዎ የሰጠው ዕውቅናና ድጋፍ ለሐገር ህልውናና ግንባታ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ስለሆነ ሊመሰገን ይገባል፡፡ ቀሪው ሥራና ኃላፊነት የኃይማኖት ተቋማቱ የቤት ሥራ ነው፡፡

 

የመከላከያና የጸጥታ ተቋማት፡ የወያኔ 27 ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ሐገራዊ ተቋሞቿና እሴቶቿ ፈራርሰው ለአንድ እኩይ ቡድን ብቻ አገልጋይ ሆነው የቆዩበትና አዳዲስ ተቋማትም ሳይገነቡ የቀሩበት ዓመታት ናቸው፡፡ በተለይም ለጤናማ ሐገርና መንግሥት ግንባታ እጅግ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ፣ የደህንነትና የመከላከያ እንዲሁም የፍትሕና የዲሞክራሲ ተቋማት እንዳይኖሩ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይመራበት የነበረውን “ቀዩን” የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሃፍ በቅርቡ አያችሁት አይደል?! የደህንነት፣ የጸጥታና የፖሊስ መስሪያ ቤቶች መተዳደሪያ ከዚህ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል?! ዕውነት ለመናገር የመከላከያ፣ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማቱን ድሮ እንፈራቸውና እንጠላቸው ነበር፡፡ EBCን ድሮ እንደምንጠራው መከላከያና መሰል ተቋማትንም “የነሱ” ነበር የምንላቸው፤ የጨቋኝ መንግስት ደህንነት፣ የጨቋኝ መንግሥት መከላከያና ጥበቃ አድርገን ነበር የምናያቸው፡፡ ነበሩም፡፡ አሁን ደግሞ ቀዩ መጽሀፍም ወደ መዝገብ ቤት (ለታሪክ) መመራቱን እኔ አምኛለሁ፡፡ ከለውጡ አንስቶ ዕውነትም የሕዝብ ደህንነት፣ የሐገር መከላከያና ጥበቃ አድርጌ ማየትና ማክበር እየጀመርኩ ነው፡፡ እንደው የመከላከያን ነገር ከነካካሁት አይቀር፣ በአዲሱ የሪፎርም መንፈስና ማዕቀፍ ውስጥ ምናልባት “አግአዚ” የሚባለው ጦር ስሙ ቢቀየር ይሻል ይሆን? መንግሥት እኛ ከስም ጋር ወሳኝ ጉዳይ የለንም ይል ይሆናል፡፡ እናም “በመለስ ዜናዊም አካዳሚ” በሪፎርሙ ዙሪያ (ለካድሬዎች ነው?) ጠቃሚ የአቅም ግንባታ ሥራ እየተሰራበት ነው ሊለንም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ስሙ ሳይሆን “ሶፍት ዌር” መቀየሩ ነው እየተባለም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በዚህ ይስማማል? እሳቤው የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ይመስላል፡፡ ነገር ግን የሥነልቡናና የሞራልም ጉዳይ ቅንጦት አይደሉም፤ አብሮ ቢታሰብባቸው አይከፋም፡፡ በጥሩ ስም፣ መልክና ቁመና ወደ ጥሩ ግብ መገስገስ ይሻላል፤ አንዳንዴ – The Means justifies the End- ይላሉ፡፡ እርግጥ የጥገና ለውጥ ፈተናና ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ግድ ካልሆነ በስተቀር ለጊዜው ሊያስቀይሙት የማይፈልጉት ወይም የማይችሉት አካል ሊኖር ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በወያኔ አገዛዝ ጊዜ ትኋኑ ያላቆሰለውና ያላገማው ተቋም የለም፡፡ ይህም ትውልዱን በክፉ ሳይነካው ያለፈበት አጋጣሚ የለም፡፡ እዚህም ትኋን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልም እንበልና እንቀጥል፡፡

 

እስር ቤቶች፣ የማጎሪያና የማሰቃያ ተቋማት፡ አንዳንድ የሕዝብ ዕውነተኛ ተቋማት በጽናታቸው ምክንያት ባይጠፉ እንኳን ቀጭጨዋል፤ ብዙ ጎበዞች ያለፍላጎታቸው ከሐገራቸው ተሰደዋል፤ ከፊሎቹም ወደበረሃ አቅንተዋል፡፡ መብታቸውን ብቻ የጠየቁ ንጹሃን ዜጎች ከአውሬ ጋር የታሰሩት (ጄይል ኦጋዴን)፣ በሽንት ማጠራቀሚያ ኩሬ./ ገንዳ ውስጥ የተዘፈዘፉት (ፍኖተሰላም እስር ቤት)፣ በእስር ቤት ወንድ ልጅ የተደፈረውና የተኮላሸው፣ የሴት ልጅ ማኅጸን የተበላሸው፣ ዜጋ በብሔር ማንነቱ እንዲሸማቀቅ የተደረገው፣ የተጠቃው፣ የተፈናቀለውና የተሰደደው በወያኔ ጨቋኝ ሕጎች፣ ተቋማትና ሠራተኞቻቸው አማካኝነት ነው፡፡ በማዕለካዊ፣ በቂሊንጦ፣ በቃሊቲ፣ በዝዋይ፣ ሸዋ ሮቢትና በአዲስ አበባ የምሥጢር እሥር ቤቶች ጥፍራቸው የተነቀለ፣ እጅ እግራቸው የተሰበረ፣ ጡታቸው በዱላና በቦክስ የተመታ፣ ሽንት የተሸናባቸው …፣ ወንዶችና ሴቶች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ከአማርኛ ተናጋሪዎችና ከአማራ ብሔር ተወላጆችም ተለይቶ እስር ቤቱ ሁሉ “ኦሮሚኛ መናገር ከጀመረ ሰነበተ” የተባለለት ጊዜ የጨካኞቹ የወያኔ ገዢዎች ጊዜ መሆኑ ይረሳል እንዴ? እርግጥ በቀለ ገርባ በወያኔ እሥር ቤቶችና አሳሪዎች የደረሰብኝ የከፋ ነገር የለም ብሏል፡፡ በወያኔ አገዛዝ ጊዜም የነበሩት ብዙ ስቅየት የተፈጸመባቸው የትግራይ የሚስጥር እሥር ቤቶች አሁንም ድረስ ስቅየት እየተፈጸመባቸው እንዳሉ ነው፡፡ በነዚህ የምሥጢር እሥር ቤቶች፣ ያኔ የራሳቸው የወያኔ አባላት፣ የኢሕአፓ መሪዎችና አባላት፣ የኢዲዩ አባላትና ደጋፊዎች ስቅየት ተፈጽሞባቸዋል፤ ዛሬ ደግሞ በዋነኛነት አማራ ነን ባሉ የወልቃይትና የራያ … ተወላጆች ላይ ሥቅየት እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ስቅየትና መዓት የደረሰባቸው ወጣቶችና ጎልማሦች ሰቆቃው አልልረሳ ብሏቸው ቂም ይዘው፣ ለይቅርታ ዝግጁ ሣይሆኑ፣ አቅጣጫ በሳተ የጥላቻና የበቀል ዕቅድ ላይ ተቸንክረው፣ ከበቀል ውጭ ምንም ነገር አልታይና አልጥም ብሏቸው ይሆናል፡፡ ትውልዱ በዚህ መልክና ልክ ተበድሏል፡፡ በደልን መርሳት ከባድ ቢሆንም ይቅር ማለት ግን በምድርም በሰማይም ትርፍ ያስገኛል፡፡ የሚበጀው ከትናንት ተምሮ ለዛሬ የሚታረመውን አርሞ ነገን በተስፋ እያማተሩ ወለም ዘለምና መለስ ቀለስ ሳይሉ በቀጥታ ወደፊት መጓዝ ነው፡፡

 

የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት፡ ሌላ የትኋኑን ወግ ከግል ገጠመኝ ጋር ጨለፍ አድርገን እንይ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን ይመለከታል፡፡ በወያኔ ዘመን አፍቃሪ ሰብዓዊ መብት እንደሆነ የተነገረለት የአንድ “የሐያል” ሐገር ከፍተኛ ባለሥልጣን በአንድ አጋጣሚ አብረውት የነበሩ ሰዎችን እንዲህ ሲል ጠየቀ፤ “በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከቡና እኩል ወደውጭ የምትልከው ምርት ምን እንደሆነ ሊነግረኝ የሚችል ከመካከላችሁ አለ?” … ለራሱ ጥያቄ መልስ የሰጠው እርሱ ራሱ ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ ከቡና እኩል ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ነገር አፋኝ ሕጎችን ነው” አለ፡፡ የሣቀ ሣቀ፤ በዕውነቱ ግን አያስቅም ነበር፡፡ ከዚህ ብዙም ባልራቀ ጊዜ ውስጥ (በፊት/በኋላ?) በአንድ የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ሐገር ውስጥ በሲቪል ማሕበረሰብ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበር አንድ ሰው ይህንኑ የፈረንጁን ምልከታ የሚያጠናክር የግል ተሞክሮ ለአጋሮቹ አካፈለ፡፡ ይህ ሰው “በግሌም በድርጅቴም ስም  አንድ አግባብ የነበረውን መሥሪያ ቤት የሚመራ ሚኒስትር በቢሮው ተገኝቼ አነጋገርኩት” አለ፡፡ ፍሬነገሩን ሲያብራራ “ከኢትዮጵያ በቀጥታ የቀዳችሁትን አፋኝ የሲቪል ማሕበረሰብ ሕግ በግድ ልትጭኑብን እየሠራችሁ መሆኑን ደርሰንበታል፤ አንፈቅድላችሁም፤ አንላቀቅም” አልኩት አለ፤ “ብዙ ሆነን በተደጋጋሚ ባደረግነው የጋራ ትግል ረቂቁን ሕግ ሳይጸድቅ አከሸፍነው” ሲል በኩራት ንግግሩን ደመደመ፡፡ የሚመለከታቸውን ወገኖች አንገት ያስደፋ የጀብድ ታሪክ ነበር፡፡ ስለገዛ ሕዝብህ ውርደትና ሐገርህን ስለሚገዛው መንግሥት ነውር (ስለራስህም ድክመት) ስትሰማም ሆነ ስትናገር ፈጽሞ ጥሩ ስሜት አይሰማህም – አይመችም ነበር፡፡ በወያኔ ዘመን በመሬት ላይ  ሊኖሩ ይችላሉ የተባሉ አፋኝ ሕጎች ሁሉ በኢትዮጵያ በሁሉም ማሕበረሰብ አባላት (ፖለቲካ፣ ሲቪል ፣ ሜዲያ ወዘተ) ላይ ተጭነው ነበር፡፡ ወያኔ በአገዛዝ ዘመኑ ያነበራቸው አፋኝ ሕጎች የባለሥልጣን የበላይነት፣ በህግ መግዛትና መጨቆን (Rule by men and Rule by law) ነበሩ፡፡ እነዚህም የትኋኑ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የሕግ የበላይነት ወይም በሕግ ማስተዳደር ለኢትዮጵያ ብርቅ ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በዘመኑ “ከዛሬ (መስከረም 1967) ጀምሮ ሰልፍ፣ ስብሰባና ሃሳብ መግለጽ ተከልክሏል” አለ፡፡ አምባገነኑ መለስ ዜናዊም ከመንግሥቱ እንዳያንስ “ከዛሬ (ግንቦት 1997) ጀምሮ የአደባባይ ተቃውሞም ሆነ ስብሰባ አይፈቀድም”፣ “ጣት እንቆርጣለን” አለና በጭካኔም አስፈጸመው፡፡ ኋላም ከርሱ የማይሻሉት ጓደኞቹና ጭፍሮቹ (ሌጋሲ አስፈጻሚዎቹ) የሲቪል ማሕበረሰብ ሕግ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ፣ የፕሬስ ሕግ፣ የጸረ ሽብር ሕግ የሚባሉ የጥንቱ አምባገነን የንጉሥ ድራኮንን የመሰሉ ጨቋኝ ሕጎች ጭነውብን እስከ መጋቢት 2010 ግፍና ስቅየት ፈጸሙብን፤ (ወያኔ ከዚህም በላይ ዕድሜው ይጠርና!) የፖለቲካና የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት ሕዝቡንና ትውልዱን ለመታደግና ለማነጽ የነበራቸው ትልቅ ዕድል ባይመክንም ኮሰሰ፡፡ ትውልዱ የወያኔ ሥርዓት ሰለባ ነው ስንል በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ነው፡፡ እናም ትውልዱን እንደገና ማነጽና ሥርዓት ማስያዝ፣ ተቋማቱንም መልሰን መገንባት ሊኖርብን ነው፤ ትኋኑን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልምና፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  መንፈሳዊ ወኔና ስልጣን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

 

የመርዛማው ዘርና የትኋኑ የቅርብ ጊዜ ተጨባጭ መገለጫዎች

የባለተራነት ፖለቲካ፡  እርግጥ የባለተራነት ፖለቲካ የሺህ ዓመታት ታሪክ አለው፡፡ ከቋንቋ አንጻር በታሪክ የጊዜ መሥመር ላይ የሚታዩትን ለውጦች ብንጠቅሰ፣ ቀዳማዊ ምኒልክ (ከ3ሺህ ዓመታት  በፊት) ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመጣ ጊዜ አጅበውት ከመጡት ነገዶች መካከል አጋዝያን ይገኙበታል፤ በቀዳማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት ውስጥ ክብርና ሞገስ (ባለተራነት) ስላገኙ ቋንቋቸው ግዕዝ፣ አማርኛን ገፍቶ እንዲስፋፋ አደረጉ፤ በዚሁ የጊዜ መሥመር በፍጥነት ወደፊት እንሂድ፣ ይኩኖ አምላክ (1262 – 77፣ ከ750 ዓመት በፊት) በእናቱ ኦሮሞ ነው፤ ሆኖም ለዘመናት በዛጉዬዎች እጅ የኖረውን የአባቶቹን ሥርወመንግሥት በማስመለስ ጥረቱ የረዱት ከኦሮሞዎች ይልቅ አማሮች ስለነበሩ ዙፋን ላይ ሲወጣ የአማራ ሠራዊትና መሪዎች ክብርና ሞገስ አገኙ፤ ስለዚህ አማርኛ ዳግም የቤተመንግሥትና የሕዝብ፣ ግዕዝ ደግሞ የቤተክህነት ቋንቋዎች ሆኑ፡፡ ዕውነት ለመናገር ከቋንቋ አንጻር (ከቋንቋ አንጻር!) አጼ ዮሐንስ (1864 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ፣ መለስ ዜናዊ  ፕሬዚዳንት (1983) ኋላም ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ጨሞሮ ሁሉንም ነገር ሲሆን ትግርኛን ሣይሆን አማርኛን ነው በብሔራዊ ቋንቋነት እንዲቀጥል የተዉት፡፡ አሁን “ለውጡን እኛ ብቻ ስላመጣነው ባለተራ ነን” የሚሉ በመንግሥት ውስጥና ከውጭም ያሉ የኦሮሞ ጽንፈኞች ቀሽሞች ናቸው፡፡ ባይሆኑ ኖሮ ማድረግ የነበረባቸው መላ ሐገርና ሕዝብ የሚግባባበትን አማርኛን ለማዳከም ማሴር አይደለም፡፡ ቅን ሰዎች፣ ሐገር ወዳድ አመራሮችና የበሰሉ ፖለቲከኞች ቢሆኑ ኖሮ አማርኛን ሳይነኩ ሌሎች ቋንቋዎችም ወደፊት እንዲመጡና ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆኑ ከልብና ከካዝናም ይሠሩ ነበር፡፡ እኔ እኮ ከአማርኛ ሌላ አንድ እንኳ ብሔራዊ ቋንቋ የሚችሉ ሰዎች እንዴት ያስቀኑኛል መሰላችሁ? ጥቅሙስ?! በመንግሥት ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ጽንፈኞች የበሰሉ ፖለቲከኞች ቢሆኑ ኖሮ አዲስ አበባን “ትርጉም አልባ” (Irrelevant) ለማድረግ ከመዳከር ይልቅ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ዋና ማዕከል የሚሆኑ ሌሎች ትልልቅ ከተሞችን በተመጋጋቢነት ለመፍጠር በደከሙ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ የበቀለ ገርባ ዓይነት፣ ሐገርና ሕዝብ-ጠል የበታችነት ስነልቦናና የባለተራነት ፖለቲካ ምርኮኛ ናቸው፡፡ እንደተባለውም “የሮሮ”ም ሆነ የባለተራነት ወያኔያዊ የቁማር ፖለቲካ ማራመድ ትርፉ ወያኔ ጀምሮ መጨረስ ያቃተውን ሐገር የማፍረስ ፕሮጀክት ተልከውም ሆነ ሳይላኩ ማስቀጠል ብቻ ነው፡፡ እነዚህ አሁኑኑ ሊታረሙ ይገባል፡፡ ሐገራችንና ሕዝባችን ከበቂ በላይ ግፍና ውርደት ደርሶባቸዋል፡፡ እንደዛም ሆኖ ትኋን ለማጥፋት ቤት አይቃጠልም! የሚበጀን ከአዙሪት ውስጥ መውጣት ነው፡፡ ከጠባብ ሣጥናችን ውስጥ ወጥተን በስፋት በማሰብ ያሉትን አማራጭ መፍትሔዎች ሁሉ በዕውቀት አጢነን የጋራ መግባባት የሚደረስባቸውን መፍትሔዎች ይዘን መቀጠል ነው፡፡ የሚሻለን በይቅርታ፣ በራስ መተማመንና በእኩልነት፣ የጠፋውን እያረሙ፣ የጎደለውን እየሞሉ፣ ሁሉንም ተጠቃሚ እያደረጉ ጊዜው በሚጠይቀው ልክ ወደፊት መራመድ ነው፡፡ እርግጥ ከይቅርታ ጋር ዕውነትን ማውጣት አብሮ መሄድ አለበት፡፡ ይህን ተከትሎም በደልን የመካስና የዕርማት ሥርዓት ተቋማዊ በሆነ መልክ መዘርጋት አለበት፡፡

 

 

 

ዕውነት ማፈላለግና እርቅ የማውረድ ፖለቲካ

የሰቆቃችንና የስቅየታችን ዝርዝሩና ጠባሳው ብዙ ነው፡፡ ግፉ ገና አልተነገረም፣ አልታየም፡፡ እነ ሙስጠፌ (ጀግና!)፣ በሶማሌ ክልል የወያኔ “አዛኝ ቅቤ አንጓችነት” እና አይን አውጣነት (ለይቅርታ ዝግጁ አለመሆን) ቢታክታቸው ጊዜ፣ እያወቁ ዝም ያሉትን ነውሩን ሁሉ እንደገና ተገድደው መዘርገፍ ጀምረዋል (ፋና …)፡፡ እንደኔ ግን ይህም አይበቃም!! የወያኔ ግፍ ገና በደንብ ተደራጅቶ በስፋትና በተደጋጋሚ መገለጽ አለበት፡፡ ግፉ ቢገለጥም ወያኔ አያፍርም፣ አያርፍም፡፡ የርሱ ማፈር ይቆይ፤ በአገዛዙ ዘመን በፍርሐትም ሆነ ግፍ በራሳቸው ስላልደረሰ፣ ስላልተነኩና “በዓይናቸው ስላላዩ” የወያኔን ግፍ በሩቁ (ኢሳት ሲገልጽ) እንጂ በቅርብና በዝርዝር አላወቅንም ነበር የሚሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ለነዚህ ወገኖችም ሲባል ቢሆን ግፉ በስፋትና በተከታታይ መገለጡ ግድ ነው፡፡ ሃፍረት የሚሰማውም ሆነ ገና አሁን ዘግይቶ የሚባንን ማንኛውም ወገን ከተገኘ የኅሊና ፍርድ ለመስጠት፣ ለማውገዝ፣ እንዳይደገምና በቃ ለማለትም ጉልበት ይሰጠው ይሆናል፡፡ ለተበዳዮችና ለሐገር ተገቢውን ፍትሕ በሙሉ ሞራል ለመጠየቅም ይረዳል፡፡ አለበለዚያ “በኢሕአዴግ/በመለስ ጊዜ እንዳሁኑ ያለ ረብሻ፣ ትርምስ፣ ጥቃትና መፈናቀል አይተንም-ሰምተንም አናውቅም” እያለ ወይ ድርቅናውንና አውቆ መተኛቱን አለያም መደንዘዙን ይነግረናል፡፡ በዝምታ ከቀጠልን፣ የሕወሐት አስተዳደር ተመልሶ ቢመጣ ይሻለናል የሚሉ አስመሣይና አላዋቂ “ሰዎችን” እየሰማን ልንታመም ነው፡፡ ይህ ሊሆን አይገባም!!!

 

ወያኔ ለ27 ዓመታት የፈጸመው ግዙፍ ጥፋት ልጆችና ወጣቶችን አንጋዶ ማሳደጉ ብቻ አይደለም፤ (በነገራችን ላይ ወያኔ አሁን መቀሌ ከመሸገም በኋላ የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘምና ከተጠያቂነት ለማምለጥ፣ በታዳጊዎች ላይ ሌላ ዙር ግፍ እየሠራ ነው፡፡ የ12 – 14 ዓመት ወንድና ሴት ህጻናትን አሁንም የጥላቻ መርዝ እየጋተ፣ ያለዕድሜአቸው የጦር መሣሪያ እያስታጠቀ፣ በጦርነት ሊማግዳቸው እያዘጋጃቸው ነው)፡፡ እንዴ ተው! የሚል የለም እንዴ?! ወያኔ በአገዛዝ ዘመኑ እጅግ ብዙ  ወጣቶችን ሥራ አጥ አድርጓል፡፡ በግልጽ እንነጋገር፤ ከእነዚህ ልጆች የሚበዙት የሚበሉትና የሚለብሱት የላቸውም፣ የሚውሉበትና ሱሳቸውን የሚያስተናግዱበትም ይፈልጋሉ፤ (ሱስ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም)፡፡ እንኳን ልጆቹ ቤተሰብም አብሮ የሚያየው ተስፋ የለም፡፡ ሥርዓቱ በፈጠራና በሐሰት ትርክት፣ በጥላቻ ሞልቶ አሳደጋቸው፣ ለምንም በጎ ነገር ግድ-የለሽ አድርጎ አሳደጋቸው፤ ሥራ-አጥ አድርጎ አስራባቸው፣ ተስፋ አሳጣቸው፤ እኛ ደግሞ የሚሆኑትን እያየን እንደ ማሕበረሰብ ፈርተን አገለልናቸው፡፡ እናም ብዙዎቹ ልጆች ማሕበረሰብን በጅምላና ከነርሱ ውጭ የሆነውን ሁሉ የመጥላት ችግር አለባቸው፡፡  በዚህ ስሜት ላይ የክፉዎች የደም ገንዘብ፣ ክፉ ቅስቀሳና የማይጨበጥ የደም ኃብትና የውርስ ተስፋ ሲሰጣቸው ሊሆኑ የሚችሉትን ገምቱ፡፡ አካል ሲያጎድሉ፣ ሕይወት ሲያጠፉ፣ ሕይወታቸው ሲጠፋ፣ ኃብት ንብረት ሲዘርፉና ሲያጠፉ፣ የዘረፉትን በመከፋፈል ጊዜ ሲጣሉም፣ አንዳንዶች በዘረፉት የንጹሃን ሐብት ሕይወታቸውን ሲለውጡ ሁሉ እኛ ዜጎች እያየን ነው፡፡

 

እዚህ ላይ የሐጫሉን የግፍ ግድያ ተከትሎ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ላይ የተስተዋለ አንድ ገጠመኝ እናንሳ፡፡ እርግጥም በአንዳንድ ቦታዎች (ሻሸመኔን ጨምሮ) ጥቃቱ ሐይማኖት ተኮር፣ ተጠቂዎቹም ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ እዚህ አጥቂዎቹ አክራሪ ሙስሊሞች ናቸው ተብሏል፡፡ እስኪ እንጠይቅ፣ በሐይማኖት ተኮር ጥቃት ውስጥ የተሳተፉት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ነበሩ? እርግጥ ነጭ ቆብ ያደረጉ 1-2 ጎልማሦችና መላ ፊታቸውን የተሸፈኑ 1-2 ወጣት ሴቶች በእያንዳንዱ አጥቂ ቡድን ውስጥ ይገኙ ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ አጥቂዎቹ ካጠቁት የክርስቲያን ሥጋ ቤት ውስጥ ቆመው ሥጋ ተሻምተው ሲበሉና ሽንጥ-ሽንጥ ሥጋ ተሸክመው ሲጋልቡ ታይተዋል፡፡ በክርስቲያን ሥጋ ቤት ሥጋ የሚበላና በመጠጥ ቤት ውስጥ አልኮል አውርዶ የሚጠጣ ምን ዓይነት ሙስሊም ነው? እኔ የማውቃቸው የሚበዙት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ፈሪሐ-ፈጣሪ ያላቸው ጨዋ አማኞች ናቸው!  እናም ጥቃቱና ጭፍጨፋው ሁሉ ብሔር እና/ወይም ኃይማኖት ተኮር ቢሆንም፣ ከሁሉም ግፍ ጀርባ ያሉት ግን ከሥልጣን የተባረሩና ሕዝብ ባይፈልጋቸውም በድርቅና ለመመለስ ችክ የሚሉ፣ በመንግሥት ውስጥ ያሉ ቀልባሾችና ሌቦች፣ አዳዲስ የሥልጣን ናፋቂዎች፣ የብሔርና የፖለቲካ ጽንፈኞች፣ አሸባሪዎችና የሐገር አፍራሾችና ባንዳዎች ናቸው፡፡ ከጥቃቱ በፊት፣ በጥቃቱ ጊዜና ከጥቃቱም በኋላም የነበረውን የነድምጺ ወያነ፣ የኦኤምኤን፣ ናይል ቲቪና መሰል ክፉ ሜዲያዎች፣ የጭራቅ አክቲቪስቶችና የጭፍንና ችክል ዲያስፖራዎች የአሳደህ በለው ጫጫታን ማስታወስ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የብሔር-ብሔር (ነፍጠኛ-ነፍጠኛ) እና የኃይማኖት-ኃይማኖት ጨዋታው ሽፋንና ማቀጣጠያ ፈንጂ ብቻ እንደነበረ ነው፡፡ ወጣቶቹ “ብሔርህ ወይም ኃይማኖትህ ተናቀ፣ ተጨቆነ፣ የብሔርህን ልጅ ገደሉት” በሚሉ የፖለቲካ ጽንፈኞችና ሐገር አፍራሾች እየተነዱና እየተረዱ ነበር ያን ሁሉ ጥፋት የፈጸሙት፡፡ የጅምላ ጥቃት ሰለባ ከነበሩት አካባቢዎች በአንዳንዶቹ፣ ከ7-8 ቀን በፊት፣ በአካባቢው መስተዳድርና የጸጥታ ተቋም የሚታወቅ፣ ለታቀደው ጥቃት ዒላማ የተደረጉ ነዋሪዎችን አስቀድሞ መሣሪያ የማስፈታት ሥራም ተሠርቷል፡፡ ቅድመ ዝግጅት መሆኑ ነው፡፡

 

በዚህ ሁሉ ጥቃትና ጥፋት ውስጥ ስለወጣቶች ሚና ስናነሳ ሁለት ነገሮችን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አንደኛ በጭፍጨፋው ውስጥ ዋና ተዋናይ የነበሩት ሁሉም ዓይነት ወጣቶች አይደሉም፡፡ ይህን መሰሉን ነውር የሚጠየፉና ለመከላከልም የሞከሩ መልካም ወጣቶች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ለበጎዎቹ ወጣቶች ተገቢውን ዕውቅና መስጠት አለብን፡፡ ሊያሳስበን የሚገባው ግን የመጥፎ ወጣቶች ባህርይና ድርጊት ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ለሁሉም ጥፋት ወጣት-ወጣት ብለን ኮነን እንጂ ወጣቶቹን የሚመሩ ጥቂት የማይባሉ ጎልማሦችም ከፊትና ከጀርባ ሆነው፣ ከወጣቶቹ ጋር መታየታቸውን ተጎጂዎች ይመሰክራሉ፡፡ ተስፋ በመቁረጥ፣ በጥላቻና በደም ለሚገኝ ሐብት በመታለልና በመጓጓት ጭምር ጥቂት የማይባሉ  ወንዶችና ሴቶች ልጆች ራሳቸውን እየሸጡ ነው፡፡ የከፈላቸው ሁሉ ሲገዛቸውና ሲጠቀምባቸው እያየን ነው፡፡ ለማያምኑበት ብቻ ሣይሆን ፈጽሞ ለማያውቁትም ዓላማ ተሸጠው ይገድላሉ፣ ይገደላሉ፤ ያጠቃሉ፣ ያቃጥላሉ፣ ይዘርፋሉ፡፡ በአሸባሪ የፖለቲካ ጽንፈኞች ተከፍሏቸው፣ ስምሪትና የኢላማዎች ዝርዝር ተሰጥቷቸው፣ በተሸከርካሪ ተጓጉዘው፣ ለጊዜው ከሕግ ፊት ሲሰወሩም መደበቂያ ተመቻችቶላቸው (ማረፊያ ፔንሲዮን ምግብና ሺሻ … ቀርቦላቸው) የክፉዎችን ተልእኮ ይፈጽማሉ – ዘግናኝ ጥቃትና ጥፋት ይፈጽማሉ፡፡ በዚህም ወዲያውኑ ከሚያደርሱት ጉዳት በተጨማሪ በሚፈጠረው ውዥንብር የጎረቤት ለጎረቤት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይሻክራል፤ ተጠቂዎችን ብቻ ሣይሆን፣ መላ ሐገርና ሕዝብን እንዲሁም በስሙ የሚነገድበትን ማሕበረሰብና ትውልዱን ሁሉ ለሚያሳፍርና ለሚያሸማቀቅ ታሪክ ይዳርጉታል፡፡ ይህ የውርደት አዙሪት በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ግን እንዴት? አሁንም ወደመፍትሔ ጥቆማ ከማቅናታችን በፊት ችግሩን ከሥር መሠረቱ በተጨማሪ መመርመርና ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡

 

የአጥቂዎቹና የአጥፊዎቹ ማንነትና ቁመና፤ ወጣቶቹ በክፉ ጎልማሦች ስምሪት ተነድተው፣ ንብረት (የንግድ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎች …) ሲያወድሙ የራሳቸውን፣ የቤተሰቦቻቸውን፣ የዘመዶቻቸውንና የጓደኞቻቸውን የእንጀራ ገመድ እየበጠሱ መሆኑን አያስተውሉም፡፡ የሚያወድሙት ለማኅበረሰባቸውና አንዳንዴም ለራሳቸው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን መሆኑን አያስተውሉም፡፡ ማስተዋሉን የሚከለክላቸው  አለመብሰላቸው፣ ስሜታዊነታቸውና ሥራ አጥነታቸው ብቻ አይደለም፤ የሚቀበሉት የደም ገንዘብ፣ የሚዘራባቸው የጥላቻ ቅስቀሳና የሚሰጣቸውና በምናብም የሚያዩት የደም ውርስ ተስፋም አስተዋጽዖ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ የሚያወድሙትና የሚዘርፉት ንብረት አስቀድሞ ተለይቶ እንደሚነገራቸው አረጋግጫለሁ፡፡ ይህ ከላይ ከላይ ሲያዩት በአስገራሚ ተቃርኖ የተሞላ ይመስላል፤ ሥራ አጥና ሥራ ፈላጊ ወጣት እንዴት የእንጀራ ምንጮችን፣ የሥራ ዕድል እያቀረቡ ያሉ ተቋማትን መልሶ ያፈርሳል?  ወጣቱ ይህን አሳፋሪ ነውር እንዲፈጽም የሚያደርጉትን ምክንያቶች ቀደም ብለን ዘርዝረናቸዋል፡፡ የወያኔ ሥርዓት ልጆቹንና ወጣቶቹን ኪሳቸውን ብቻ ሣይሆን አእምሮና ልቡናቸውን ባዶ አድርጎ ነው የሠራቸውና “ያሳደጋቸው”፡፡ አብዛኞቹ፣ ከሥራ አጥነቱና ከድህነቱ ጎን ለጎን፣ በምክንያትና በእርጋታ አያስቡም፣ በሐሰተኛ ትርክት ተሞልተዋል፤ በጥላቻ ቅስቀሳ ተወናብደው እየተነዱ ነው፡፡ በዚህ ላይ በሚያኮራ የነጻነት ትግል ሜዳና ጀብድ ላይ እንደተሰለፉ ቆጥረው እንዲንቀሳቀሱ ተቀስቅሰዋል/ይቀሰቀሳሉ፡፡ የልጅነት ትኩሳት አለ፡፡ የሚያጠቋቸው ማኅበረሰቦች የችግራቸው ሁሉ ምንጭና መፍትሔውም እነርሱን ማጥቃትና ማፍረስ ብቻ እንደሆነ በደመ ነፍስ እንዲያምኑ ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ክፉ ድርጊታቸውን ተከትሎ ከቀናት፣ ከወራትና ከዓመታት በኋላ በራሳቸውም ሆነ ባጠቁት ማኅበረሰብና በአካባቢያቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በምናባቸው ቀድሞ ማየት አይችሉም፡፡ ሲገድሉ መገደል፤ ሲያጠቁ መጠቃት ሊኖር እንደሚችል የሚያውቁም አይመስለኝም፡፡ አለበለዚያ ከአጥቂዎች መካከል በቀኑ መጨረሻ  ስንቶቹ የት እንደገቡ እንኳን የሚያውቅ ላይኖር ይችላል፡፡ የተከፈላቸውን የደም ገንዘብም ሆነ የዘረፉትን ሳይበሉ መጨረሻቸው እስር ቤት ወይም ሌላ ጋ የሚሆን አለ፤ ከጥፋታቸው በኋላ ላለመታሠር በየሥርቻው ተሸጉጠው ሲባንኑ የሚውሉና የሚያድሩ እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡ ተልእኮአቸውን ከፈጸሙ በኋላ አምልጠው፣ በአሰማሪዎቻቸው ተረስተው፣ የሚበሉትን እንኳን አጥተው፣ መፈጠራቸውን ጠልተው የሚለምኑም አሉ፡፡ የደም ገንዘብ የሚረጩትና በደም ተስፋም ልጆቹን የሚያማልሏቸው የፖለቲካ ጽንፈኞችም ወጣቶቹን ወዲያውኑ ይረሷቸዋል፡፡ እነርሱን ረስተው  ለሌላ ዙር ጥፋት ሌላ ጭዳ ማፈላለጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ድሮም ያስተሳሰራቸው ዓላማ ሣይሆን የደም ገንዘብ ብቻ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  HR6600 ፤ የ666 ተግበርን ከሳች ነውና መተግበር የለበትም ። መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊሰ

“የዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ትርጉምና አንደምታ፡፡ በኦሮሚያ ከተሞችና ወረዳዎች በአማሮች ላይ ያነጣጠረው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ “ነፍጠኛውን አሳደህ ግደለው” ማለት በኛ አውድ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ይህ አውዳዊ ትርጉም ነው፡፡ ከዚህ እኩል የነጠረውና ምናልባትም የባሰው ሌላ ዕውነት ግን፣ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” በሚሉት ሰይጣናዊ የጥላቻ ቅርሻት ተገልጧል፡፡ በሐገር ውስጥ ቢያስቡት እንጂ ሊያደርጉት የማይችሉትን ጭልጥ ያለ የጥላቻ ቅርሻት ጠያቂ “በሌለበት”  የውጭ ሐገር አቀረሹት፡፡ በአንዳንድ ሐገሮች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች የሰጡትን ምላሽ ዘንግቼ አይደለም፡፡ ጠላቶቻችን ያወረዱብንን እርግማንና የደገሱልንን ጥፋት ፍርጥርጥ አድርገን ደግመን እንስማው፤ በምናባችንም ለማየት እንሞክር! ምናልባት በጊዜ እንድንባንንና ቆፍጠን እንድንል ይረዳን ይሆናል፡፡ ዳውን ዳውን ዓቢይ ማለት ለኔ (ለኔ ነው ያልኩት) ዳውን ዳውን ለውጥ ማለት ነው!  በተለይ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ማለት ዳውን ዳውን  ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ወላይታ፣ ሐዲያ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ አማራ፣ ጋሞ፣ አፋር፣ ጌዴዖ፣ ከንባታ፣ ከፋ ወዘተ ወዘተ ማለት ነው!!!  ዳውን ዳውን ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ እናቶች ወዘተ ማለትም ነው፡፡ እንጨምር፤ በትንሹ ለመግለጽ፤ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ማለት ዳውን ዳውን አፋር (ሉሲ)፣ አክሱም ሐውልት፣ ጎንደር የፋሲል ቤተመንግሥት፣… የሐረር ግንብ፣ …የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ዳውን ዳውን ሼህ ኡመር ዋሻ፣ የኮንሦ እርከኖች፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ ዳውን ዳውን የአድዋ ድል፣ ዳውን ዳውን የአባይ ወንዝና ግድብ፣ ዳውን ዳውን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል፣ ዳውን ዳውን የከፋ/ይርጋጨፌ ቡና …፣ ዳውን ዳውን ለውጥ፣ የአንድነት/ዩኒቲ፣ የእንጦጦና የወንድማማችነት ፓርኮች፣ የሸገር መናፈሻዎች፤ ዳውን ዳውን ክስተት የሆኑት አዳዲሶቹ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች፣ ዳውን ዳውን ትልቋን ኢትዮጵያን የመስራትና እንደዱሮው ለአፍሪካ ኩራትና በዓለም ተወዳዳሪ የማድረግ ህልም ..  ፡፡ በዕውነቱ ዝርዝሩን ችዬ የምጨርሰው አይደለም፡፡ አንደምታው በሚያስፈራ መልኩ ግልጽ እንዲሆንልን የጎደለውንና የምታውቁትን እየሞላችሁ አንብቡት፡፡  እኛ ሐገራችን እንደነየመን፣ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ ሊባኖስ እንዳትፈርስ እየሰጋን ነው፡፡ በጽንፈኛ ወያኔዎች የሚነነዱት የኢትዮጵያ ጠላቶች እኮ የፈረሱ ሐገራትን ናሙና በደጃችን ደጋግመው አሳይተውናል፡፡ አብዲ ኢሌና ሔጎ ከ2 ዓመት በፊት የፈጸሙትን ጭፍጨፋና ውጤቱን በጅጅጋና በሶማሌ ክልል፣ አጄቶ የፈጸመውን ጭፍጨፋና ውጤቱን ካቻምናና አምና በሐዋሳና በሲዳማ አንዳንድ ወረዳዎች፣ ኦነግ-ሸኔ፣ ጃዋርና በቀለ ገርባ ከቄሮዎቻቸው ጋር በተከታታይ የፈጸሙትንና ያስፈጸሙትን ጭፍጨፋና ውጤቱን ካቻምና፣ አምናና ዘንድሮ በተወሰኑ የኦሮሚያ ከተሞችና ገጠሮች በአይናችን አይተናል፡፡ በምዕራብ ሸዋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጌዴዖ፣ በጉራጌ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በአማሮ … የደረሱት የዜጎች መፈናቀሎችም “በኢትዮጵያ ትውደም” እርኩስ ምኞትና ቅዠት አውድ ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡

 

በነገራችን ላይ፣ የሐገረ-መንግስት መፍረስ ሰለባ የሆኑትና ግልጽ አደጋም የተጋረጠባቸው ሐገሮች ሁሉም በሚባል መልኩ የጥንታዊ ሥልጣኔ ሐገሮች መሆናቸው አሳስቦአችሁ አያውቅም? ለምን እነርሱ ላይ ተተኮረ? አጋጣሚ ብቻ ይሆን? እኔ ከወያኔ በላይ አስፈሪ ሰይጣን ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ መጠርጠር ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ኢራቅ ባልተረጋገጠ መረጃ እንዳትነሳ ሆና ወደቀች፣ በኢራን ላይ ያንዣበበው አደጋም ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ ዳውን-ዳውን ኢትዮጵያ የሚል ዘፈንና እስክስታ ተጀምሯል፡፡ … ኢትዮጵያ ግን አትፈርስም!! ምክንያቱም ከአጉል ትዕቢት አይወሰድብኝና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ነች!! የእምነት ጉዳይ ሆኖብኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብንደክምም ፈጣሪ ራሱም የኢትዮጵያን መፍረስ አይፈቅድም፡፡ ፈጣሪአችንን አጉል ላለመፈታተን ግን ከመፍረስ ወዲህ ያለውን ግርግር ኢትዮጵያውያን በንቀት መተው አይኖርብንም፡፡

 

በእርግጥ መፍትሔው ምንድነው?  ለዛሬ መድረስ ያለበትና የማይደርሰው  መፍትሔስ የትኛው ነው? ቅድሚያ ለየቱ እንስጥ?

መፍትሔው፣ ትኋኑ እስካሁን ካደረሰውም በላይ ችግር እንዳያደርስ በየዘርፉ ከሥር መሠረቱ እርማት ማድረግ፣ መከላከል፣ ማከም፣ ተገቢውን ኬሚካል መርጨትና የማይድን ደረጃ የደረሰውን ደግሞ ለይቶ ልዩ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ ትኋኑ የታየበትን፣ ያረፈበትን ሁሉና መላ ቤታችንን ማቃጠል መፍትሔ አይሆንም፡፡ ዋናው፣ አስተማማኙና ዘላቂው መፍትሔ ለዚህ ሁሉ ጥፋት መንስኤና መሣሪያ የሆኑትን ነገሮች ከሥር መሠረታቸው አውቆ ማስተካከልና የሚጠገነውን መጠገን ነው፡፡ መተዳደሪያ ሕጎች (ከሕገመንግሥት ጀምሮ)፣ ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ የሥራ መመሪያና ደንቦች (የሥነ ምግባር ጭምር)፣ ተቋማት፣ ሰዎች፣ አደረጃጀቶች፣ አሠራሮች፣ የሥራ ድርሻ መዘርዝሮች፣ የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች (የዕለት ዕቅድ ሣይቀር)፣ የአፈጻጸም ክትትል መሥፈሪያዎች፣ የግምገማ መነሻና መድረሻዎች፣ ማንጸሪያዎች እነዚህና የመሣሠሉትን ሁሉ በጥንቃቄ አጥንቶ፣ በቂ ዝግጅት አድርጎና ተገቢ ጊዜ ወስዶ መቅረጽና ሥራ ላይ ማዋል .. ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሠራው ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ፣ የሐገርን፣ የተገልጋይ ሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅና በትውልድ ዕጣ ፈንታም ላይ ግልጽ የሆነ በጎ አሻራ ለማሳረፍና ሐገርን ለማስቀጠል ነው፡፡

 

በሐገራችን የእርማት ሥራ ተጀምሯል? ምን ዓይነትና ምን ያህል? አዎ! ሐገራችን እኔ እዚህ ላስቀምጠው ከምችለው በላይ ዝርዝርና ጥልቅ የሆኑ የለውጥ ጅማሮና የእርማት ጥረቶች ላይ ትገኛለች፡፡ ከሰውና ከመሪዎች እንጀምር፡፡ በመንግሥት ውስጥ ከላይ እስከታች ያሉ የፖለቲካ ቁማርተኞችን፣ ባለተራ ነን ባዮችን፣ አድፋጮችንና አስመሳዮችን ለጊዜው እናቆይ፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ፈጣሪያቸውን የሚያውቁና የሚፈሩ፣ ሐገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የሚወዱና ሕዝብን የሚያከብሩ፣ ቅን ልቡና፣ ብሩህ አእምሮ፣ ንጹሀ እጅ ያላቸውና ግንባር ላይ የቆሙ ልባምና ባለህልም መሪዎችን አግኝታለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን ስል እንከን አልባ ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እነዚህ መሪዎች በሕዝብ አልተመረጡም፡፡ ቢሆንላቸው ለዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ አስፈላጊውን ሁሉ መደላድል አመቻችተው በአንድ ዓይነት የፖለቲካ ሜዳ ከተወዳዳሪዎቻቸው ጋር እኩል ተነስተው፣ ተወዳድረው፣ አሸንፈው የመመረጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው እያሳዩ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ ተለውጧል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ ወጥቷል፣ የምርጫ ቦርድ ዋና ዋና የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአዳዲስ ሰዎች ተተክተዋል፡፡ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከመርህ ባፈነገጠ ጉዳይ፣ እንኳንስ ለለስላሳው ዓቢይ ዓሕመድ፣ ለጣት ቆራጩና ለዓይን ቀለም መራጩ መለስ ዜናዊም እንደማትበገር ሐገር ያወቀው … ነው፡፡ በምርጫ ምሕዳሩ፣ በሕጉና በአስፈጻሚዎቹ ገለልተኛነት፣ ብቃትና የእስካሁን አካሄድ ላይ ትልቅ ቅሬታና ጥያቄ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኔ አላጋጠሙኝም፤ ኃላፊነት ከሚሰማቸውና ከብዙዎች የተሻለ የተፎካካሪ ፓርቲነት ቁመና ካላቸው ድርጅቶች መካከል ማለቴ ነው፡፡ እንጂ ወያኔ፣ ኦፌኮና እነ ልደቱም ቅሬታና ጥያቄ ቢኖራቸው አይገርመኝም፡፡ የለውጡ አመራር የፍትሕ፣ የጸጥታ፣ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትን እንዲመሩ ከየአቅጣጫው ያሰባሰባቸው ባለሙያዎችም የሚያስመኩ ናቸው፡፡ መዓዛ አሸናፊ – ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ አዳነች አቤቤና ታዲዮስ (ዶ/ር) – ጠቅላይ አቃቤ ሕጎች፣ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) – ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ አደምና ብርሐኑ ጁላ፣ እንደሻው፣ ስለሺ በቀለን (ዶ/ር-ኢንጂነር) የመሰሉ ጎበዞች የኢትዮጵያን አዲስ የለውጥና የዕድገት ጅማሮ እያሳለጡና ነቅተው እየጠበቁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

 

ዶክተር አቢይና መንግሥታቸው መረጃ ለማግኘት፣ ሐሳብን በነጻነት ለመግለጽ፣ ለመሰብሰብና ሰልፍ ለመውጣት፣ ለመደራጀትና ለመቃወም ወይም ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የሚያስችሉ ጥሩ ሕጎችን በሚያሠራ መጠን እንዲሻሻሉ ማድረጋቸውን እያየን ነው፡፡ ከሕግ የበላይነትና ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ ተቋሞችን ለውጡን ሊያሳልጥ በሚችል መልኩ እንዲደራጁና እንዲመሩ፣ የአሠራር ሥርዓታቸውን እንዲያስተካክሉ እየተደረገ ነው፡፡ በልማት በኩል የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትና የድርድሩ ስኬት፣ አረንጓዴ አሻራ (5/9 ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ ተከላ)፣ የአንድነት፣ የእንጦጦ፣ የወንድማማችነት … ፓርኮች፣ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቶች፣ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ በኮቪድ 19 የተስተዋሉ የመከላከልና የመቋቋም ሥራዎች፤ የኢትዮ ቴሌኮም (ፍሬሕይወት)፣ እንደገና የከንቲባ ታከለ ኡማ ስኬቶች ሌላ ሳይሆን ክስተቶች ናቸው!! የኢትዮጵያ አየር መንገድስ ቢሆን?! (በነገራችን ላይ ኢትዮቴሌኮም ይሸጥ ሲባል ሰማሁ ልበል? እየተስተዋለ!!)፡፡ በሕዳሴው ግድብ ግንባታና በአረጓዴ አሻራ ፕሮጀክቶች ስሙ የማይጠራ ማን አለ?!! መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ (ከውስጥም ከውጭም)፣ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ሁሉም ንቁ ተዋናዮችና ከዋክብት፣ በተለይ ደግሞ መሐመድ አልአሩሲ፣ ኡስታዝ ጀማል በሽርና ጓደኞቻቸው፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ የምንጊዜም ጀግናችን ቴዲ አፍሮ (“ደሞ በአባይ!”) እና ሌሎች የሙያ ጓደኞቹ፤ ወዘተ ሁላችሁም ፈጣሪ ይባርካችሁ፡፡ ደህንነት፣ መከላከያና ፖሊስም የእነዚህንና የሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ደህንነት በሚያስመካ ሁኔታ ሲጠብቁ እያየን ነው፡፡ አጠቃላይ የነዶ/ር ዓቢይን የለውጥ ፍላጎትና ጥረቶችን አይቶ ከመቀበል፣ ከመመስከር፣ ከማበረታታት አንጻር የጉምቱዎቹን ፕሮፌሰሮች ዓለማየሁ ገ/ማርያም፣ ፍቅሬ ቶሎሣና መስፍን ወ/ማርያም እና የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን (Endorsement)፣ እንዲሁም የጎበዞቹን የነታዬ ቦጋለ፣ ስዩም ተሾመ፣ ናትናኤል መኮንን፣ “ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ” ሚና አለመጥቀስና አለማመስገን ፈጽሞ አይቻለኝም፡፡

 

መውጫ፡

እንደ ክስተት የሚቆጠሩ ግዙፍና ፈጣን የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች አስፈላጊነት፡

ትውልዱን ለማስተካከልና ኢትዮጵያንም ለማዳን በአጣዳፊ መሠራት ካለባቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የኑሮ ውድነትን ማሻሻልና የሥራ ዕድል መፍጠር ይገኙባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ከኢኮኖሚ ጥቅሙም አልፎ የፖለቲካ፣ የሰላምና ጸጥታ፣ ማሕበራዊና ባሕላዊ፣ ሞራላዊና ስነልቡናዊ ፋይዳው ልዩ ነው፡፡ ፋይዳው ግለሰባዊ፣ ቡድናዊና በጠባብ አካባቢ የተወሰነ ብቻም አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ሐገርን ብቻ ሣይሆን ምናልባት ጎረቤቶችንና ቀጠናውንም ጭምር ይጠቅማል፡፡ ከሰላም፣ ከጸጥታ፣ ከሐገር ህልውናና ሉዓላዊነት አንፃር ግዙፍና ፈጣን የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶችን ዕውን ማድረግ ማለት፣ ሰው፣ ሕዝብና ሐገር- ጠል ጸረ ሰላም ኃይሎችን (አራዊቶችን) እንዲሁም የውጭ ጠላቶችን እጅና እግር እንደመቁረጥ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ቢፈቅድ የዚህን ዝርዝር በክፍል ሁለት ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

ፈጣሪ ብርታቱን ይስጠን፤ ኢትዮጵያን ይጠብቅልን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share