August 20, 2020
14 mins read

ከሰኔ 23፣ 2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስለተፈጸመው ወንጀል የተሰጠ መግለጫ – ድልድይ በአወሮፓ ያኢትዮጲያዊያን መድረክ

ባለፉት ሁለት አመቶች ሀገራችን ኢትዮጵያ ደስታና ሀዘን፣ ተስፋና ስጋት ተፈራርቀውባታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን በያዙ ማግስት የታሰሩ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎች ተፈቱ፣ ስደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው አገር ቤት መግባትና በይፋ መንቀሳቀስ ጀመሩ፣ ባጠቃላይ ሀሳብን በነጻ የመግለጥ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት ነጻነት እውን ሆነ።

ይሁን እንጂ፣ የተገኘው ሀሳብን የመግለጥና የመደራጀት መብት ለሀገር ሰላምና እድገት፣ ለህዝቦች እኩልነትና አንድነት፣ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ለህግ የበላይነት ማስከበሪያ ከማዋል ይልቅ አንዳንድ አካላት በማህበረሰቡ ውስጥ ስጋት እና መጠራጠር እንዲነግስ፣ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥላቻ እና ግጭት እንዲስፋፋ ለማድረግ ተጠቀሙበት። የተወሰኑ ሚዲያዎች እና የማህበራዊ ድረገጽ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ህዝቦች መሀል ጸንቶ የኖረውን የወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ፣ ተከባበሮና ተፋቅሮ አብሮ የመኖር ባህል ለመሸርሸር፣ ቂም በቀል መስበኪያና አንዱ ህዝብ በሌላው ላይ እንዲነሳሳ መቀስቀሻ አደረጉት። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችም ምህዳሩን የዘርና የሃይማኖት ጥላቻ የድርጅታዊ ተልእኳቸው ማጠንጠኛ አደረጉት።

ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት፤ ሰኔ 22 ሌሊት ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ በሰዎች እጅ ተገደለ። በዚህ አጋጣሚ ድልድይ የዚህን ወጣት አርቲስት ግድያ እያወገዘ  በግድያው የተሰማውን ሀዘን በመግለጥ ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል። አርቲስ ሃጫሉ በግፍ  ከተገደለ ማግስት ጀምሮ በተከታታይ ለብዙ ቀናት በአንዳንድ የኦሮሚያ ክፍሎች በኗሪዎች ላይ ለመስማት የሚቀፍና ለማየት የሚዘገንን አረመኔያዊ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ አገሪቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። በዚህ የቅርብ ጊዜ ጥቃት 239 ሰዎች ተገደሉ፣ በሺ የሚቆጠሩ ቆሰሉ። ሆቴሎች፣ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ተዘረፉ፣ ተቃጠሉ። አንድ ኮሌጅ፣ በረካታ ፋብሪካዎች፣ ሰፋፊ የግል ድርጅቶች፣ ባንኮችና በመቶ የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ ባጃጆችና ሞተር ብስክሌቶች ተቃጠሉ። ሺዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ።

ይህ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመው በዘር እና በኃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በድንገት በደም ፍላት የተፈጸመ ተራ የዝርፍያና የግድያ ወንጀል እንዳልሆነም የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች በተለያዩ አካላት ተጠናቅረው እየወጡ ነው። የእነዚህ ጥቃቶች ባህሪ በግልጽ እንደሚያሳየውም በDecember 9, 1948, የተባበሩት መንግስታት አጽድቆ ባወጣው የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀለኛን ለመቅጣት (the Convention on the Prevention and Punishment of the Crime of Genocide)፤ በሚለው ሰነድ ላይ በዝርዝር የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ መሆኑን ነው። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፤

ሀ) ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት በነበሩት በርካታ ወራት ዘርና ሃይማኖት ላይ ያተኮረ የጥላቻ ንግግርና መልእከት በህዝባዊ ስብሰባ፣ በአንዳንድ የግል ሬድዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች ይተላለፍ ነበር።

ለ) በህዝብ ላይ የደረሰው ጥቃት በቅድሚያ ታስቦበትና ዝግጅት ተደርጎበት የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችም ወጥተዋል። ጥቃት የሚፈጸምባቸው ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ድርጅቶች በቅድምያ ተለይተው ዝርዝራቸው በጽሁፍ የተዘጋጀ ነበር። በመሆኑም በርከት ካሉ ቤቶችና ድርጅቶች መሀል እየተለዩ የተጠቁት በብሄራቸው ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች እና ከኦሮሞዎች መሀል ደግሞ የክርስትና እምነት ተከታዮች ቤትና ንብረት ነው።

ሐ) ጥቃቱ አፈጻጸም ተመሳሳይነት የድርጅት ስራ መሆኑን ያመላክታል። በአብዛኛው አካባቢ የድርጊቱ ፈጻሚዎች የሰፈር ሰዎች ሳይሆኑ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ፣ የመጓጓዣ መኪና አቅርቦት የነበራቸው እና ከሌሎች አካባቢዎች ተጭነው የመጡ ናቸው።

መ) ከአጋርፋ እስከ ኮፈሌና ሻሸመኔ፣ ከዚያም አልፎ እስከ ዝዋይና ጂማ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈጸመ የተቀነባበረ ጥቃት ነው።

ሠ) ጥቃት የተፈጽመባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በሰጡት ምስክርነትም ሃጫሉ ከመገደሉ አንድ ቀን በፊት በመንግስት ተመዝግቦ ንብረታቸውን እና ድርጅቶቻቸውን ለመጠበቂያ በእጃቸው ላይ ይገኝ የነበረውን ፍቃድ ያለው የጦር መሳሪያ በአካባቢዎቹ ፖሊሶች ያለምንም ምክንያት ተለይተው ትጥቁን እንዲያስረክቡ ተደርገዋል። ወዲያው ትጥቁን ባስረከቡ ማግስት በተደራጁ ኃይሎች ጥቃት ተፈጸመባቸዋል።

ረ) በየደረጃው ያሉ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣኖች በመካሄድ ላይ ስለነበረው ጥቃት ቢያውቁም ጥቃቱን ለማስቆም እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል። በአካባቢው ላይ የሰፈሩ አንዳንድ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃቱን እያዩ፣ ምንም እርምጃ እንዳትወስዱ ተብለናል በሚል ሰበብ፣ በሕግ የተጣለባቸውን የዜጎችን ደህንነት ከማንኛውም ጥቃት የመታደግ ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ የሚያመላክቱት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ  አካባቢዎች ኦሮሞ ባልሆኑ እና/ወይም የክርስትና  እምነት ተከታይ በሆኑ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ታስቦበትና ቅድሚያ ዝግጅት ተደርጎበት የተከነወነ በመሆኑ በዘር ማጥፋት ወንጀል አለም አቀፍ ድንጋጌዎች መስፈርት መሰረት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ነው።

 

ስለዚህ፤

  1. በቀጥታ ወንጀሉን የፈጸሙት፣ እቅዱን ያወጡትና ያስፈጸሙት፣ እንዲሁም ሃላፊነታቸውን ባለመወጣት፣ ሽፋን በመስጠት የተባበሩት ከቀበሌ እስከ ክልል አመራር ያሉ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የፖሊስና የክልሉ ልዩ ሀይል አባሎች በግልጽ ችሎት ለፍርድ እንዲቀርቡ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
  2. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ንብረታቸው ለወደመባቸው ሙሉ ካሳ እንዲከፍል፣ የተፈናቀሉትንም ወደ ቀያቸው መልሶ እንዲያቋቋም እንጠይቃለን።
  3. በአለም አቀፍ የሰባዊ መብቶች ድንጋጌ መሰረት፣ ዜጎች በብሄር ምንጫቸው ልዩነት ሳይደረግ፣ ሰባዊ ክብራቸውና መብታቸው መጠበቁን፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር መብታቸው መከበሩን ማረጋገጥ የፌዴራል መንግስትና የክልል መንግስረታት መንግስታዊ ግዴታቸው መሆኑን በአጽንኦት እናሳስባለን ።
  4. በማናቸውም ማህበራዊና ፖለቲከካዊ መድረክ የጥላቻ ንግግር በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን፣ የፖለቲካ አመራሮች እና የማህበራዊ ድረ ገጽ ጦማሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እና አጥፊዎቹ ተለይተው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ እንጠይቃለን።
  5. የተፈጸመው ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት የኢትዮጵያን ህዝቦች እርስ በርስ በማጋጨትና የህዝብን ሰላማዊ ኑሮ በማደፍረስ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ድረጊት በመሆኑ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማናቸውንም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አጣርቶ በስድስት ወር ውስጥ ለመንግስት የሚያቀርብና በቀጥታ ለህዝብ  ይፋ የሚያደርግ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚስዮን በአስቸኳይ አንዲቋቋም እንጠይቃለን።
  6. ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተካሄደውን ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በማውገዝ አቋማቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ህዝብ እንዲጠይቅ እናበረታታለን።
  7. በመላ ሀገሪቱ የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ ማረጋገጥ የመንግስት ቀዳሚና ዋነኛ ተግባር በመሆኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሰትም ሆነ የክልል አስተዳዳሪዎች ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲያከብሩና ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአጽንኦት እንጠይቃለን።

በመጨረሻም፣ ይህ መግለጫ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ እህመድ፣ ለወ/ሮ መኣዛ አሸናፊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ ለአቶ ታገሰ ጫፎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ ለወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር፣  ለአቶ ሽመልስ አብዲሳ  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት፣ ለአቶ ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ  መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲላክ ወስነናል። እንዲሁም ለክብርት ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የኢትዮጵያ አምባሳደር በቤልጅየም፣ ሉክሰምበርግና አውሮፓ ህብረት ግልባጭ እንዲላክ ወስነናል። በተጨማሪም፣ መግለጫው ተተርጉሞ ለሚስ ሚሼል ባሽሌ የተባበሩት መንግስታት የሰባዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ለሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ለሚስተር ዴቪድ ሳሶሊ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት እንዲላክ ወስነናል።

 

ድልድይ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ከቡሄ ትዝታዬ – አሁንገና ዓለማየሁ

Next Story

የህዳሴው ግድብን በተያዘለት ጊዜ በ2015 ዓ.ም አጠናቆ ለማስመረቅ ሁሉም በትኩረት እንዲሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop