July 29, 2020
3 mins read

መስሎህ ነበር (ዘ-ጌርሣም)

የረጅም ጊዜ ተንኮላቸው ሳይገባህ
አጀንዳቸውን ሳታነብና ሳይረዳህ

በቋንቋና በባህል አሳበው
መገንጠል አለብህ ብለው አታለው
አንድ ርምጃ ወደፊት አራት ርምጃ ወደኋላ ስበው

የልጆችህን ዕድል አጨልመው
ያንተንም ህይወት አደንቁረው
ከአቅምህ በላይ ክቡር ብለው
ከህዝብ ጋር አጣልተው
የጥላቻ መርዝን ረጭተው

ባልና ሚስትን አለያይተው
ቤተሰባቸውን በትነው
አንተንም አስረውና ገርፈው
ሰብዕናህን አዋርደው
እንደከብት በሜዳ ላይ ነድተው

በእግረ ሙቅ ሲጠብሱህ
በጥይት ሲደበድቡህ
ዘቅዝቀው ሲያሰቃዩህ
ምን ፀፀትና እሮሮ ተሰማህ ??

አንተማ መስሎህ ነበር
ኢትዮጵያ የምትበተንና የምትገነጣጠል

ዓላማህ አንተኑ የሚያጠፋ ሳይመስልህ
አገር መበታተን እንዲህ ቀላል መስሎህ
ታሪክን በደንብ ባለማንበብህ
ወንድሜ ለዚህ ሁሉ ስቃይ በቃህ

ብልሁን የኢትዮጵያን ህዝብ መበተን
እንደማይቻል ጠላት መረዳቱን
ማውቅና ማጤን ይገባል
አልፋና ኦሜጋ ሆኖ ታትሟል

እንኳንስ የዘር ፖለቲካ አራጋቢው
የውጭ ጠላትም አፍሯል በሙከራው
ኢትዮጵያን መበተን ከንቱ ምኞት ነው

ኢትዮጵያ ማለት ጠይም ህዝብ ነው
የሀበሻነት መለያ ያለው
ከመንፈሳዊ ህግጋት ጋር አብሮ የኖረ
መንግሥት ሳይኖር እራሱን ያስተዳደረ

ተዋልዶና ተካብዶ የሚኖር
ለጠላት ሴራ የማይበገር
ብልህና አስተዋይ ህዝብ ነው
ሊከበርና ሊደነቅ የሚገባው

አንተማ መስሎህ ነበር
ህዝብን በማጣላትና በማናቆር
ደልቶህና ተደስተህ የምትኖር

ስልጣን ከደጅህ ድረስ ሲመጣልህ
ለይስሙላ ፕረዝደንት ተብለህ
በልዩ ልዩ ማዕረጎች ሲክቡህ

ጀኔራል ኮሎኔል ሻለቃ ሲሉህ
መትረየስና ክላሽንኮ ያለጥይት ተሽክመህ
መልሶ አንተኑ የሚያስመታህ

ከወገንህ አጣልተው
የጥላቻ መርዝ ግተው
በዘርና ጎጥ ሁከት አስነስተው

እንደ ጭቃ አቡክተው
አንደ ብረት አቅልጠው
መልሰው ሲያጠቁህ ተረዳኸው ??

ሲያዘጋጁህ ለዕኩይ ተግባር
ማጣፊያ ለሌለው መደናበር
አንተማ መስሎህ ነበር
ኢትዮጵያን መበተን ቀላል ነገር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop