ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ/ም
የጎጃም ሊቃውንት ተቀኝተው ነበረ
የኢትዮጵያም እረኞች ሲያዜሙ ነበረ!
ከሺህ ዓመታት በላይ ሲናፍቁ ቆዩ
ሲይሞካሹት ኖረው፤ ቀሩ እንደ ለወዩ።
እንዲህ ሲሉ ነበር፤
ዓባይም ሞላልሽ፤ ሞላልሽ!
ያሰብሽው ሆነልሽ።
ዓባይም ቢሞላ፤ ቢሞላ!
አለው መላ መላ።
ዓባይ ይህን ሰምቶ መች ተገረመና
መቼስ ፋታ አግኝቶ ሊያዳምጥ ቆመና!
ፍቅሩን አልተረዳ፤ የአገሬውን ሥቃይ
ጭፍሮቹን ጠቅልሎ ነበር የግብጽ ሲሳይ።
የሴራው መሐንዲስ ግብጽ ብቻ አይደለች
የዓለም ነቀርሳዋ እንግሊዝ እያለች።
ፊትም በቅኝ ግዛት በካርታ ሸንሽና፤
ቀጥሎም በሠነድ ጥቅሟን አስተንትና!
ኢትዮጵያን ከውሉ በተንኮል አግልላ
ዘመናት አለፉ ጊዜው እስኪምላ።
የጎጃም ሊቃውንት ተቀኝተው ነበረ
የኢትዮጵያም እረኞች ሲያዜሙ ነበረ!
ከሺህ ዓመታት በላይ ሲናፍቁ ቆዩ
ሲይሞካሹት ኖረው፤ ቀሩ እንደ ለወዩ።
እንዲህ ሲሉ ነበር፤
ዓባይም ሞላልሽ፤ ሞላልሽ!
ያሰብሽው ሆነልሽ።
ዓባይም ቢሞላ፤ ቢሞላ!
አለው መላ መላ።
ከእኛው በፈለቀው በገዛ ወንዛችን
አትገድቡትም ምነው መባላችን?
ሴራውን ተንኮሉን ለሺህ ዓመት ቻልነው
የአምላክ ፈቃድ ሲደርስ ተገድቦ አየነው።
ለኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሆነ
ከእንዲህ አይዘልቅም ጨለማ እንደሆነ።
ዓባይ ተገደበ ትንቢቱ ደረሰ
መች ይቀራልና ከንቱ እየፈሰሰ።
የኢዱስትሪ አብዮት ማካሄድ አለብን
ሥራ አጥ ድኅነት ሙድ እንዳይዙብን።
የዓረብ ፓርላማ ለግብጽ ቢያደላ
የትራምፕ መንግሥት ሊያዘገይ ቢያሰላ
የሰማዩ ዳኛ ፍርዱ የተሟላ
ማንም አይለውጠው ከእንግዲህ በኋላ።
ግብጽ በጌታዋ በእንግሊዝ ተቃኝታ
ተስቦ ወረርሽኝ በዜዴ አስገብታ
የእህል አረም ሳይቀር የከብት በሽታ
አማፂ ኃይላትን በገፍ አሠማርታ።
ኢትዮጵያን ስታምስ ዘመናት አለፉ፤
በቡትሮስ ጋሊ ጊዜም፤ ኤርትራን ጠለፉ።
አሁንም ኦነግን፤ ጀዋርን መልምለው
ያተራምሱናል መሀላችን ገብተው።
እንግዲህ ሀገሬ ተንኰሉን እወቂ
ከከሐዲ ባንዳ በጣም ተጠንቀቂ።
ብርሃንሽ ዛሬ ነው ዕድገትሽም ነገ
ኑሮሽ ያምራል ሲታይ እየበለጸገ።
የጎጃም ሊቃውንት ተቀኝተው ነበረ
የኢትዮጵያም እረኞች ሲያዜሙ ነበረ!
ከሺህ ዓመታት በላይ ቆዩ
ሲይሞካሹት ኖረው፤ ቀሩ እንደ ለወዩ።
እንዲህ ሲሉ ነበር፤
ዓባይም ሞላልሽ፤ ሞላልሽ!
ያሰብሽው ሆነልሽ።
ዓባይም ቢሞላ፤ ቢሞላ!
አለው መላ መላ።
የአገሬ ወጣቶች ከእንግዲህ ዕወቁ
ያልተረዳችሁም አዛውንት ጠይቁ
ከሐሰት ቅስቀሳ በጣም ተጠንቀቁ
ከጎጥ ፖለቲካ ፍጹም ተጠበቁ።
አይጠቅመንምና የዘር ክፍፍሉ
ለእኛ ቀርቶ ለእኔ ደግሞም መባባሉ።
ከወገን አይደለም ይህ የሰይጣን ሥራ
ስንተባበር ነው ኃይል ያለን በጋራ።
የአባቶቻችንን አድዋን አስታውሱ
ድላቸው በሕብረት መሆኑን አትርሱ።
የጎጃም ሊቃውንት ተቀኝተው ነበረ
የኢትዮጵያም እረኞች ሲያዜሙ ነበረ!
ከሺህ ዓመታት በላይ ቆዩ
ሲይሞካሹት ኖረው፤ ቀሩ እንደ ለወዩ።
እንዲህ ሲሉ ነበር፤
ዓባይም ሞላልሽ፤ ሞላልሽ!
ያሰብሽው ሆነልሽ።
ዓባይም ቢሞላ፤ ቢሞላ!
አለው መላ መላ።
-//-