July 24, 2020
14 mins read

የኦሮሞ ጠባብ ብሔርተኞች ለኦሮሞ ሕዝብ ያላቸው ጥያቄ ምንድ ነው? – በፈቃዱ ኃይሉ

“‹የኦሮሞ ጥያቄ› ምንድ ነው?” የሚለው ጥያቄ ቀላል የሚመስል ነገር ግን ከባድ ጥያቄ ነው፤ ተደጋግሞ ሲነሳም ይደመጣል። በዚህ ሳምንት ይህንኑ ጥያቄ በመያዝ ከደርዘን የበለጡ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ወይም ለመልሶቻቸው የሚሟገቱ ሰዎችን አነጋግሬያለሁ።

“‹የኦሮሞ ጥያቄ› ምንድ ነው?” የሚለው ጥያቄ ቀላል የሚመስል ነገር ግን ከባድ ጥያቄ ነው፤ ተደጋግሞ ሲነሳም ይደመጣል። በዚህ ሳምንት ይህንኑ ጥያቄ በመያዝ ከደርዘን የበለጡ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ወይም ለመልሶቻቸው የሚሟገቱ ሰዎችን አነጋግሬያለሁ። በዚሁ መሠረት ከዚህ በታች ጨምቄ የማቀርባቸው ጥያቄዎች ያነጋገርኳቸው ሰዎች “የኦሮሞ ጥያቄ” እነዚህ ናቸው በሚል በተደጋጋሚ ከነገሩኝ መካከል አራቱ ዋነኞቹ ናቸው። ለእያንዳንዱ ጥያቄ የማስቀምጠው ማብራሪያም በተጠያቂዎቹ የተሰጡኝን ማብራሪያዎች ለዚህ ጽሑፍ በተመቸ መልኩ አሳጥሬው ነው። የጽሑፉ ዓላማ በፖለቲካ ተዋስዖው ውስጥ የሚነሱትን ጥያቄዎች እና ውይይቶች ሊያግዝ የሚችል ፍሬ ሐሳብ ለማበርከት ነው።

መንደርደሪያ
ብዙዎቹ የጥያቄዬ መላሾች እያንዳንዱ ጥያቄ ያለ ጥቅል ዐውዱ ትርጉም እንደማይሰጥ ይናገራሉ። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት (ኦሮሚያ) እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት (ኢትዮጵያ) መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ ጉዞን በጥቂቱ ምሥል የሚሰጥ ዐውድ ለጥያቄዎቹ ግልጽነት የግድ አስፈላጊ ነው። የአንድ አስተያየት ሰጪ ገለጻ የሁሉንም ሐሳብ ይጠቀልለዋል። የኦሮሞ ጥያቄ የሚመነጨው አንድም ከአገረ መንግሥቱ የቅቡልነት ደረጃ፣ አንድም ደግሞ ከዴሞክራሲያዊነት ደረጃ ነው። የአገረ መንግሥቱ ቅቡልነት ቀውስ የሚመነጨው “አገሩ እኛን የሚወክል እሴት፣ ትዕምርት እና ትርክት የለውም” ከሚል ሲሆን፣ ‘የዚህ መልሱ ዴሞክራሲያዊ አይደለም’ ይላሉ። የፌዴራላዊ መዋቅሩ የተፈጠረውም ይህንን የቅቡልነት ችግር ለመቅረፍ ሲባል ነበር። የዴሞክራሲያዊነት ቀውሱ የሚመነጨው ደግሞ የተለወጠው መዋቅር የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለማድረግ ሲባል ነው። እንደ አስተያየት ሰጪው የአገረ መንግሥቱ ቅቡልነት ቀውስ ሲጎለብት ሉዓላዊ አገር መመሥረት እንደ ጥያቄና የመፍትሔ ሐሳብ እየጎላ ይቀርባል። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የቅቡልነት ቀውስ እየቀነሰ ሲመጣ ደግሞ የዴሞክራሲያዊነት ጥያቄ ይጎላል።
ጥያቄዎቹ በዴሞክራሲ እና በአገረ መንግሥቱ መሠረታውያን ላይ ወዲያ እና ወዲህ ከማለታቸውም ባሻገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡ መምጣታቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ። በ1950ዎቹ የተነሱ ጥያቄዎች እና ዛሬ ያሉት አንድ አይደሉም፤ ለዚህም ነው ጥያቄዎቹን ደጋግሞ ማንሳት እና መለየት የሚያስፈልገው።
በዚህ መሠረት የኦሮሞ ዛሬያዊ ጥያቄዎች ከታች የተዘረዘሩት ናቸው። በዝርዝሩ ውስጥ ቀድመው የመጡት መልስ በሰጡኝ ሰዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ድግግሞሽ ልክ ነው። የጥያቄዎቹ መነሻ ታሪካዊ እና ወቅታዊ ዐውዶች አንድ ዓይነት በመሆናቸው አራቱን ጥያቄዎች እርስ በርስ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ገለጻው እና ማደራጀቱ የእኔ ቢሆንም፣ ሐሳቡ ግን የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾቹ ነው።

ጥያቄ አንድ፦ የትርክት እና ትዕምርት ጥያቄ
የኦሮሞ ጥያቄዎች በአብዛኛው የሚመነጩት በምሥለ ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን አያገኝም ከሚል ይመነጫሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትርክቶችም ይሁኑ ትዕምርታዊ መገለጫዎች ኦሮሞን ወይ ይገድፋሉ አልያም በአሉታዊ መንገድ ይገልጻሉ። እነዚህ ትርክቶች ከታሪክ መጽሐፍት ገጾች እስከ ትምህርት ስርዓቱ፣ ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ፣ ከሰንደቅ ዓላማ እስከ አደባባይ ሐውልቶች ድረስ ይዘልቃሉ። ትርክቶቹ እና ትዕምርቶቹ የኦሮሞን ገጽታ አካታች እና በአግባቡ ገላጭ ተደርገው መስተካከላቸው ወይም መካተታቸው ለብዙዎቹ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
የትርክት እና ትዕምርት ጥያቄው ቀድሞ የነበሩትን ታሪካዊ ትርክቶች መከለስ እና የኦሮሞ ሕዝብ ትውፊታዊ እሴቶችንና ትዕምርታዊ መገለጫዎችን ማካተት ላይ ብቻ ላይ እንደማይወሰን ተሟጋቾቹ ይናገራሉ። የኦሮሞ ታጋዮች እነዚህን ጥያቄዎች ይዘው ትግል ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ በርካታ ሰብኣዊ እና ሥነ ልቦናዊ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፣ በርካታ ጀግኖችም ተፈጥረዋል። እነዚህ ትግሎች፣ መስዋዕትነቶች እና ጀግኖች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዕውቅና ማግኘት አለባቸው።

ጥያቄ ሁለት፦ የቋንቋ ጥያቄ
የቋንቋ ጥያቄ በኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾች ዘንድ እንደ እኩል አድራጊ (equalizer) ነው የሚቆጠረው። ኦሮምኛን የፌዴራል መንግሥቱ አንድ የሥራ ቋንቋ ማድረግ ከባሕል ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ጥያቄዎችንም የመመለስ አቅም አለው። ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች መግባቢያ ቋንቋቸው አማርኛ ነው። ይህም የተለመደው የከተሞች መሥፋፋት በሚከሰትበት ጊዜ በዙሪያው ያሉ ባሕላዊ ልማዶች እና ወጎች በከተሜው ልማድ ይዋጣሉ። በኦሮሚያ ደግሞ ከተሞቹ ዙሪያ ያሉት የኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሬዎች በመሆናቸው ቋንቋውም ባሕሉም አብሮ የመዋጥ አደጋ ይጋረጥበታል። ኦሮምኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ መሆኑ ከተሞችን ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ (Bi-lingual) በማድረግ ችግሮቹን በመጠኑ ይቀንሳል።
የቋንቋ ጉዳይ የኢኮኖሚ ጥያቄን ይመልሳል ብለው ተሟጋቾቹ ያምናሉ። የፌዴራል ተቋማት እና የግል ዘርፉ የተሠማራባቸው ከተሞች የመግባቢያ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በነዚህ ቦታዎች የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማግኘት አማርኛ ተናጋሪ መሆን አለባቸው። ይህ ተግዳሮት ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ቢሆን የሚቀረፍ ነው።

ጥያቄ ሦስት፦ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ
የኦሮሞ ሕዝብ የገዛ አገሩ ባለቤት አይደለም፤ መጀመሪያ ይህንን ማረጋገጥ አለበት የሚለው ጥያቄ አንዱ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የኦሮሚያ አገረ መንግሥትን ዕጣ ፈንታ ይወስናል እንጂ፣ ኦሮሚያ (እንደ አንድ ክልላዊ መንግሥት) የሥልጣን ባለቤት ሆና የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በሚገባት መጠን እየወሰነች አይደለም። የፌዴራል መዋቅሩ የተፈጠረው አባል መንግሥታቱ (ኦሮሚያን ጨምሮ) የኢትዮጵያን መንግሥት አካሔድ እንዲወስኑ ቢሆንም እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነው የሚል ነው።
ይህ በፖለቲካ ኢትዮጵያ ኦሮሚያን ቅኝ ገዝታለች ከሚል ትርክት የሚመጣ ሲሆን፥ ምላሹም ነጻ መውጣት፣ ወይም ሉዓላዊ አገር መመሥረት ነው የሚለው ነው። ይህ የሉዓላዊነት ጥያቄ የኦሮሞ ሕዝብ ያሉትን በአገር በቀል ስርዓት የመተዳደር ጥያቄ ጀምሮ፣ የመሬት ባለቤትነትን የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች፣ ባሕልን የማሳደግ ጥያቄ፣ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ እና የመሳሰሉትን መልስ ያስገኙለታል ተብሎ ይታመናል። በዚህ ረገድ የኦሮሞ ሕዝብ ኦሮሚያ ሉዓላዊ አገር ብትሆን የሚያገኘውን ነጻነት እና ጥቅም በፌዴራል መዋቅርም ይሁን በሌላ መንገድ ከኢትዮጵያ ማግኘት አለበት የሚል ጥያቄ ነው።

ጥያቄ አራት፦ የሰላምና ፍትሕ ጥያቄ
የኦሮሞ ሕዝብ ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚያስቀድመው ጥያቄ የሰላም ጥያቄ ነው። ‘ነጋ’ ማለት ‘ሰላም’ ማለት ሲሆን፥ የማኅበራዊ ሕይወቱም አስኳል የሆነ ቃል ነው። ከዕለታዊ ሠላምታ ጀምሮ እስከ አረጋውያን ምርቃት ድረስ የሚጠይቀው እና የሚመኘው ሰላም ነው። ሰላምታው በግል ደኅንነት ጀምሮ እስከ ሀብት ንብረትና አካባቢ የሚዘልቅ ነው። ሃይማኖታዊ ትውፊቶቹ ውስጥም የሚንፀባረቁት የሰላም ጥያቄዎቹ ናቸው። ነገር ግን ይህ የኦሮሞ ሕዝብ የሰላም ጥያቄው በፖለቲከኞች በቅጡ ግንዛቤ አላገኘም፤ ስለሆነም የሚፈልገውን ሰላም ማግኘት አልቻለም።
በሌላ በኩል ለመብት ተሟጋቾቹ ፍትሕ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ የኦሮሞ ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ በአስተዳደራዊ በደሎች ምክንያት መድልዖ ሲፈፀምበት የነበረ እንደመሆኑ እነዚያ መድልዖዎች እና በደሎች ፍትሕ ካላገኙ በስተቀር የሚመኘውን ሰላም አያገኝም።

መዝጊያ
ይህንን ጥያቄ ያቀረብኩላቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ተከራካሪዎች የተናገሯቸው ብዙ ቢሆኑም በኔ አረዳድ ሲጨመቁ ከላይ የተዘረዘሩት አራቱ ዋና ጥያቄዎች ሆነው ይወጣሉ። ከነዚህ በተጨማሪ ‘የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች ናቸው’ ብለው የሚያነሷቸው የነጻነት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የኢኮኖሚ እና ሌሎችም ጥያቄዎች አሉ። በተለይ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ብለው የነገሩኝን ለመለየት ሞክሬያለሁ። በተጨማሪም ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘት ይችላሉ በሚለው ላይ ሰፊ ልዩነት አላቸው፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ በመነጠል በሚል በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። ብዙዎቹ መልሶች የኦሮሞ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ይመለሳሉ በሚል የተሰጡኝ ናቸው።

በፈቃዱ ኃይሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop