አገርን ለማዳን ሲባል የተቃቃሩ ወንድማማቾችን ማስታረቅ – በገ/ክርስቶስ ዓባይ         

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ/ም

አገራችን ኢትዮጵያ ዕድገቷን እና አንድነቷን በማይሹ የውጭና የአገር ውስጥ የተቀነባበረ ሴራ ከመቸውም በላይ ከባድ ፈተና ታጋርጦባታል። ለዚህ አስተሳሰብ ብዙ ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም የወቅቱን የዓቢይ ግድብ ጉዳይ ግን መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል። የታላቁን የዓባይ ግድብ አስመልክቶ እየተጠነሰሰብን ያለውን ሸርና ደባ ለአፍታም ቢሆን ከአእምሮአችን ልናወጣው አይቻለንም።

የኢትዮጵያን መሪዎች ከሌላው አገር ልዩ የሚያደርጋቸው በሰላም ወቅት ለሥልጣን እርስ በእርስ መፎካከራቸው ሲሆን፤ የውጭ ወራሪ ኃይል ሲመጣ ደግሞ፤ የነበራቸውን ልዩነት ወደ ጎን ትተው በጋራ በመሰለፍ ጠላታቸውን ድባቅ የሚመቱ መሆናቸው ነው። ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ እንደ ቀድሞው ለሥልጣን መራኮታቸውን ይቀጥላሉ። እንግዲህ የኢትዮጵያ አንድነት ታሪክ ሲመረመር ከዚህ የተለየ ሆኖ አይታይም።

ይሁን እንጂ ሁሉም መሪዎች ለአገራቸውና ለወገናቸው የተሻለ አመራር ከመስጠት አኳያ ከሚያደርጉት ፉክክር በስተቀር፤ በአገር ሉዓላዊነትና ኅልውና ላይ ግን ሁሉም ያላቸው አቋም አንድና አንድ ብቻ ነው። ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደርጋሉ እንጂ ለግል ሥልጣንና ዝና ሲሉ በአገርና ወገን ክኅደሽ ላይ የተሠማሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከእነዚህም በዋናነት የሚጠቀሱት ካሣ ምርጫ (አፄ ዮሐንስ አራተኛ) እንደሆኑ ይታወቃል።

አፄ ዮሐንስ ለእንግሊዝ መንግሥት በማደር፤ ጀኔራል ናፒርን ከቀይ ባሕር ጀምሮ እስከ መቅደላ አምባ በመምራት፤ የአፄ ቴዎድሮስን መንግሥት በማፍረስ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ይቅር የማይባል ክኅደት ፈጽመው አልፈዋል። ታሪክ ራሡን ይደግማልና ከዚያው አካባቢ የተወለዱት የሕወሃት ወያኔ ዓባላት በአብዛኛው የባንዳ ልጆች ስብስብ፤ በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያፈራርስ ምስጢራዊ አጀንዳ ቀርጸው አብሯቸው ሲዋጋ የነበረውን ታጋይ ሁሉ ሲያታልሉ ቆይተው፤ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ዓላማቸው ቀስ በቀስ በተግባር ሲገለጽ፤ ቁጭት ላይ የወደቁ ታጋዮችን በማደን ሲያጠፏቸው፤ ሌሎችንም ከምድር በታች ባለ እስር ቤት ሲያሰቃዩዋቸው ኖረዋል።

ለዚህም እንደ አብነት ጄኔራል ኃየሎም አርአያን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። ጄኔራሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ስለአሰብ ወደብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ሕወሃት ስለሚኖረው አቋም ጠይቀው፤ ‘አሁን ስለአሰብ ጉዳይ የምንጨነቅበት ወቅት አይደለም፡በቅድሚያ ከሻብዕያ ጋር ተባብረን ደርግን መጣል አለብን፤ ከዚያ በኋላ የአሰብ ጉዳይ ቀላል ነው’ እየተባሉ ሲሸነገሉ መቆየታቸው ይነገራል።

ቁርጡ ሲታወቅ ግን ሕወሃት የአሰብን ጉዳይ ችላ በማለት ለሻዕብያ አሳልፎ በመስጠቱ ጄኔራል ኃየሎም አርአያ እጅግ በጣም መበሳጨታቸውንና መቆጨታቸውን፤ ስለዚሁ ጉዳይ ተነስቶ በተደረገ ውይይት ላይ ጄኔራሉ ሲገልጹ “ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይመክርበት የአሰብን ወደብ አሳልፈን የመስጠት ሕጋዊ ማንዴት የለንም። አሁንም እኛው እንደሰጠን በማንኛውም አስፈላጊ በሆነ መንገድ አስመልሰን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማስረከብ ኃላፊነትና የሞራል ግዴታ አለብን!” የሚል ጠንካራ አቋም በማያዛቸው ከሥልጣን ጠማኙና ከከሃዲው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት መለስ ዜናዊ ጋር በመጋጨታቸው ቂም ተይዞባቸው ሲያበቃ አመቺ ወቅት ተጠብቆ መገደላቸው የአዳባባይ ምስጢር ነው።

ሕወሃት ወያኔ በሥልጣን ላይ በቆየበት የ27 ዓመት ጊዜ፤ በጎሣ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ አገዛዝ፤ የአገሪቱን ፖለቲካ፤ የመከላከያ ኃይል፤መሬትን፤የኢኮኖሚና የፍትሕ ሥርዓቱን በሞኖፖል በመቆጣጠር፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ በቋንቋና በዘር፤ እንዲሁም በክልል፤ ነጣጥለው ሆድና ጀርባ በማድረግ በ ‘የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ’ በማራመድ፤የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሲሰብኩትና ሲግቱት ቆይተዋል።

ለዚህም እኩይ ተግባራቸው እንደ ዋነኛ መሣሪያ አድርገው የተጠቀሙበት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የታሪክ ዲፓርትመንት በመዝጋትና፤ የትምህርት ካሪኩለሙን በመለወጥ ከእውነት የራቀና የተዛባ አዲስ የፈጠራ ታሪክ ሆን ተብሎ በከርስ አደሮች እየተዘጋጀ፤ የአዲሱን ትውልድ የማንነት እሴት ሲያጠፉ ኖረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደንጋራው ብአዴን

ከዚህም የተነሳ በአማካኝ ከ1978 ዓ/ም ወዲህ የተወለዱት የማኅበረሰብ ዓባላት የሕወሃትን የጥላቻ ስብከት እንጂ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነትና የአብሮነት ታሪክ እየሰሙ ያላደጉ በመሆናቸው የማንነት ጥያቄ (Identity Crisis) ስለባ ሆነዋል።

የወቅቱ ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ይህንን የተሳሳተ ፖሊሲ በጥልቀት ተረድተው ለማረም ቀን ከሌት እየሠሩ መሆናቸው ቢታወቅም፤ እነዚህ በአማካይ እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች፤ከልጅነታቸው ጀምሮ የጠፉ ስለሆነ ለመንግሥታቸው እጅግ በጣም አደገኛ ሆነው ይገኛሉ። ይህንኑም በመረዳት ጥቂት የማይባሉ በሳል ኢትዮጵያውያን የሽግግሩን ተግዳሮት አስቀድመው በመረዳት፤ በየጊዜው አስተያየታቸውንና ምክራቸውን ለግሰዋል። ነገር ግን የጠፋውን ትውልድ ለመፈለግና ወደ ቀድሞዋ የኢትዮጵያ ባህልና አንድነት ክብር ለመመለስ በዶ/ር ዓቢይ መንግሥት የተሠራው ሥራ እጅግ በጣም ከሚፈለገው በታች በመሆኑ የችግሩን ግዝፈት የሚመጥን ሆኖ አልተገኘም።

አሁንም ቢሆን በሰላም ሚኒስቴር ሥር የሆነና ራሡን የቻለ አንድ መምሪያ ሊቋቋም በተገባው ነበር። ይህ መምሪያ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ዓባላት የተውጣጡ በዕድሜም በዕውቀትም የበለጸጉ ምሁራን ተስባስበው በአገሪቱ ያሉትን የሚዲያ ዘርፎች በመጠቀም ወጥ የሆነ የተሐድሶ ትምህርት በተለያዩ ቋንቋዎች በመስጠት አዲሱን ትውልድ ከገባበት የማንነት ቀውስ የሚመልስና የሚታደግ ተግባር ተግተው በመሥራት፤ በአገሪቱ ያሉትን የሚዲያ ዘርፎች በመጠቀም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።

በእርግጥ እንዲህ ያለውን የአገር ጉዳይ፤ በአገር ወዳድ ጋዜጠኞች የሚሸፈን መሆን ቢገባውም፤ በሚዲያ ዘርፉ ላይ ተሠማርተው የሚገኙት አብዛኛዎቹ፤ ለስሙ ጋዜጠኛ ከመባል ያለፈ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኙት ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

አብዛኛዎቹ ግን አደንዛዥ ጋዜጠኞች (ፕሮፓጋንዲስቶች) ሲሆኑ፤ የቆሙበትን ዓላማና የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ለይተው ያልተረዱ ናቸው። ለምሳሌ አብዛኛዎቹ፤ ስለሴለኢብሪቲ ወይም የዓለም ታዋቂ ሰዎች አንስተው ሲያወሩ፤ ባለታሪኩ ራሱ እንኳ የእነርሱን ያህል ስለራሱ የሚያውቅ አይመስልም። ስለሚነዳው መኪና ፤ስለሚበላው ምግብ፤ ስለሚያዘወትርባቸው ቦታዎችና ከማን ከማን ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳደረገ ሲተነትኑ አሰልቺ ከመሆኑም ባሻገር የሚወስዱት የአየር ጊዜ እጅግ በጣም ረዥም ነው። በተለይ የእስፖርት ዘጋቢዎች ነን የሚሉት ደግሞ፤ ስለ አርሰናል፤ሊቨርፑል፤ ስለማንቸስተርና፤ ባርሴሎና ተጫዋቾች የግል ሕይወት እያነሱ አርቲ ቡርቲውን ሲደሰኩሩ የሚያቃጥሉት ጊዜ በጣም ይዘገንናል።

ዘገባውን አጠር ባለ መልኩ ከአቀረቡ በቂ ሆኖ እያለ የማያስፈልግ መረጃ በማቅረብ በወጣቱ ትውልድ ሕይወት እና በአገር ሉዓላዊነት ላይ ይቀልዳሉ። ይህ ጉዳይ መታረም አለበት። በሚዲያ ዘርፍ ተሠማርተው የሚገኙ ድርጅቶች  በሳምንት ቢያንስ የአንድ ሰዓት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ተከታታይ ዝግጅት እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ አዋጅ ሊወጣ ይገባል።

በደርግ ወቅት እያንዳንዱ ድምፃዊ አዲስ የዘፈን ካሴት (አልበም) ሲያወጣ ከዘፈኖቹ መካከል ቢያንስ አንዱ የአገር ሉዓላዊነትንና የሕዝብ አንድነትን የሚያሞግስና የሚያጠናክር ሆኖ መካተት እንዳለበት የሚያዝ አስገዳጅ መመሪያ ወጥቶ እንደነበረ ይታወሳል። አሁንም ቴሊቪዥኖችም ሆነ የሪዲዮ ጣቢያዎች እንዲህ ያለው መመሪያ ሊደርሳቸው ይገባል።

በአንፃሩም ሆነ ብለው ተደራጅተው በቀጥታ አገር ለማፍረስ እየሠሩ የሚገኙትን ጣቢያዎች ለአገር ጸጥታና ለሕዝብ ሰላም ሲባል ያለምንም ማወላወል መቅጣትና አደገኛነታቸው የሚያመዝን ሆኖ ከተገኘም እስከነአካቴው መዝጋት ተገቢ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምንድነው ጉዱ?

ቀደም ሲል ሕወሃት ለእዚህ እኩይ ተግባሩ፤ በኢትዮጵያዊነታቸውና በማንነታቸው የማይሸማቀቁትን በተለይ በሥራ የሚያምኑ ኩሩ የአማራና የጉራጌ ሕዝቦች ላይ ዋና ማነጣጠሪያ አድርጎ ጥላቻውን ሲያራምድ ከርሟል። አማራውን ነፍጠኛና ትምክህተኛ የሚል ቅጽል ስም በመስጠት፤ የጉራጌ ማኅበረሰብም ላይ ደግሞ የኢኮኖሚ ጫና በመፍጠር ከንግድ እንቅስቃሴያቸው እንዲገደቡ በማድረግ የተደራረበ ግፍ ሲሠራ መቆየቱ አይዘነጋም።

ለሁሉም ጊዜ አለውና የሕወሃቱ መሪ መለስ ዜናዊ ከሕዝቡ ልቅሶ የተነሳ በኃያሉ አምላክ በድንገት ሲጠራ፤ ሕወሃት ‘እራሱን እንደ ተመታ እባብ’ በመሆን እሱን የሚተካ መሠሪ መሪ ማቅረብ ተስኖታል። ከዚህም የተነሳ ማንም ባልጠበቀው መንገድ በድንገት ሥልጣን ከእጃቸው አፈትልካ ወጣች። የሕወሃት ወያኔ ዓባላትም እንደመብረቅ ባጋጠማቸው ዱብ ዕዳ ተጠራርተው መቀሌ መመሸጋቸው የማይታበል ሐቅ ነው።

የኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት፤ ከአሥራ አምስት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ በሕወሃት አመራር ሥር ሆነው ባደጉት በዶ/ር ዓቢይ አሕመድ እጅ ስትወድቅ በማየት፤ ቁጭትና እያደር የእግር እሳት ሆነባቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ በሕዝብ ላይ ሲሠሩት የነበረው ግፍና መከራ የኅሊና ዕርፍት ሊሰጣቸው አልቻለም እንጂ፤ የአገርን ሰላም ከማስፈን አኳያ በዶ/ር ዓቢይ አመራር የደረሰባቸው የከፋ ማሳደድ አልታየም።  ሆኖም፤ ሁሉም የሕወሃት ዓባላት በተንኮል ተኮትኩተው ያደጉ በመሆኑ የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሰላማዊ ተግባራቸውን መቀጠል አልደፈሩም።

የሕወሃት ወያኔዎች ውድቀታቸው መቼ እንደሚሆን ባይረዱም፤ አንድ ቀን ግን እንዲህ ዓይነቱ ያልታሰበ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስቀድሞ በመገመት፤ እንደ አገር ሊያደርጋቸው የሚችል አንዳንድ የመሠረተ ልማት መዋቅሮችን አዘጋጅተው ጨርሰዋል።

ዩኒቨርስቲዎች፤ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፤ የመድኃኒት ፋብሪካ፤ ኤለክትሪክ ኃይል ማመንጫ፤ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፤ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ሌሎችንም አስፈላጊ የልማት ተቋማት ሁሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ፤ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። በተለይም ለበቂ ጊዜ የሚያገለግል የእህል ክምችት አሰባስበዋል። በተጨማሪም የአገሪቱን አንጡራ ሀብት በጆንያ በማጨቅ አግበስብሰዋል፤ በቂ የወርቅ ህብትም ዘርፈዋል።

ይህ ሁሉ ዝግጅት ቢኖራቸውም እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር የሚያደርጋቸው ጉዳይ ግን የተራራ ያህል ሆኖባቸዋል። አንደኛ ከሕወሃት ወያኔ የፖለቲካ ካድሬዎች በስተቀር ሠፊው የትግራይ ሕዝብ እግር ከወርች ታፍኖ ተይዞ እንጂ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚደራደር እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው። በሁለተኛ ደረጃም የተባበሩት መንግሥታትን የአገር ሉዓላዊነት ቻርተር ድንጋጌዎችን መመዘኛ ማሟላት አይቻላቸውም። በሦስተኛም ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ያለፍላጎቱ በኃይል የታፈነውን ወገኑን የትግራይ ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ሲል ሊዘምትባቸው እንደሚችል ስለሚያውቁ ያላቸው አማራጭ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሌላ አጋር በመፍጠር የዶ/ር ዓቢይ አሕመድን መንግሥት ሰላም የማሳጣት አጀንዳ ቀርጸው ወቅት እየጠበቁ ማወክ በሚል ተግባር ላይ ተጠምደዋል።

የሕወሃት የግፍ ቀንበር ሲያሰቃያቸው የነበሩት ሁሉም ክልሎች፤ በአንድ ላይ ቆመው ወያኔዎችን ዓይናችሁ ላፈር ስላሏቸው፤ የእነርሱ ሰላዮች ምንም መግቢያና መውጫ የላቸውም። አማራውን ለማተራመስ ሲሉ በጥቅም የተገዙ ጥቂት የቅማንት ዓባላትን በመያዝ፤ በሰውና በሕዝብ ሀብት ላይ የተቻላቸውን ሁሉ ሲገድሉና ሲያወድሙ ቆይተው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ሕዝቡ ተላላኪዎችን መንጥሮ በማውጣቱ እንዳሰቡት ሊሳካላቸው አልቻለም።

በመሃል አገር ግን ሁልጊዜም እንደ ጭነት መጋዣ የእነርሱን አጀንዳ ሲያስፈጽም የቆየውን የኦነግና ሌሎችንም ለጥቅም ያደሩ አንዳንድ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲ መሪዎችን፤ እንዲሁ በገንዘብ ኃይል በማታለል ሕዝብ ተቀጥሮ የሚሠራባቸውን፤ በክልሉ ያሉ ፋብሪካዎች፤ ሕንፃዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ ለማመን የሚቸግር ከፍተኛ ውድመት አስፈጽመዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮማራ ብዙ እያነጋገረ ነው (የሕብር ሬዲዮ)

ለዚህ ዕቅድ አንደ እርሾ የተጠቀሙት የየትኛውም ፖለቲካ ፖርቲ ዓባል ያልነበረውን ንጹሑን የሕዝብ ልጅ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በግፍ በማስገደል፤ የዋሁ የኦሮሞ ወጣት በግብታዊነት ተነሳስቶ በተለይ ዋናው ዓ ላማቸው በሆነው በአማራና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙና ሩዋንዳ መሰል የዘር ፍጅት ለማካሔድ እንደነበር ማንም የፖለቲካ ሀሁ የሚያውቅ ሁሉ የሚረዳው ሐቅ ነው።

ይህ ዕቅድ ግቡን እንዲመታ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ያሉ ፀረ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ አቋም ያላቸውን የኦሮሞ ልሂቃንን በድምፀ ወያኔና በኦ.ኤም. ኤን ቴሌቪዥኖች በቅብብሎሽ የኦሮሞን ወጣት ልብ ለማሸፈት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ተስተውሏል። የኦ.ኤም.ኤን. ቴሌቪዥን ባለቤት፤ በፀረ ኢትዮጵያዊነቱና በዘረኝነቱ በግልጽ የሚታወቀው የጃዋር ሞሐመድ መሆኑ ይታወቃል። ከአሁን ቀደምም በቡራዩ፤ በሻሸመኔ፤በድሬ ዳዋ፤በሐዋሳ፤ በኬሚሴና በሌሎችም አካባቢዎች፤ እንዲሁም ‘የዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ደኅንነት ሊያፍኑኝ ስለሆነ አድኑኝ’ የሚል ቅስቀሳ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ላይ አራምዶ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የበዙ ንጹሐን ዜጎች ሕይወት በግፍ ሲቀጠፍ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት አላግባብ መውደሙ አይዘነጋም።

ከአሁን ቀደምም በተለያዩ አካባቢዎች የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት፤ የእምነት ተቋማት ላይ ሳይቀር እጅግ ዘግናኝ የእሳት ቃጠሎዎች መካሄዳቸውን የምንረሳው አይደለም።

በዚህ ሁሉ ጊዜ የመንግሥት ደኅንነት፤ እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ተልዕኮ ከመከናዎኑ በፊት አስቀድሞ የማክሸፍ ተግባር ካለመሥራቱም በላይ ጥፋቱ ከተፈጸመ በኋላም የዶ/ር ዓቢይ አስተዳደር፤ የሕግን የበላይነት ተጠቅሞ ፍትህ የማሰጠት ቁርጠኝነቱ የላላ እንደነበርና በዚህም ከደጋፊዎቹ ጭምር ሳይቀር ለከፍተኛ ትችት ተጋልጦ እንደነበር የምናስታውሰው ነው።

እንግዲህ ዋናው ጉዳይ ይህ ሆኖ እያለ፤ ‘እባብን ያዬ በልጥ ይደነግጣል’ እንዲሉ፤ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በግፍ መገደል ተከትሎ ከላይ በጠቀስናቸው ሚዲያዎች፤ የኦሮሞን ወጣት ለዕልቂት ለማነሳሳት ይሰበኩ የነበሩትን ቅስቀሳዎችና፤ ቀደም ሲል ከታዘብናቸው ታሪኮች በመነሳት፤ የባልደራስ ፓርቲ፤ ሕዝቡ ራሱንና ንብረቱን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትን ከጥፋትና ከውድመት እንዲጠብቅ ማሳሰቡ፤ እንዲያውም በዶር ዓቢይ አስተዳደር ሽልማትና ምስጋና ሊቸረው ሲገባ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም።

ጉዳዩን በጥልቀት ስንመረምረው ግን፤ ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድና የባልደራሱ መሪ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸው ራዕይና ግብ ተመሳሳይ መሆኑን እንረዳለን። መዳረሻቸው አንድ ሆኖ፤ ምናልባት ልዩነቱ አንዱ ‘መንገዱ አባጣ ጎርባጣ ስለሆነ በእግር አንሂድ’ ሲል፤ ሌላው ደግሞ ‘በእግር ከምንሄድ በፈረስ ብንጓዝ ቶሎ እንደርሳለን’ የሚል ‘የቀልቀሎና የስልቻ’ ዓይነት ካልሆነ በስተቀር የሁለቱም የኢትዮጵያዊነት ክብርና የወገን ፍቅር አስተሳሰብ ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን።

ስለዚህ እነዚህ የአገር የቁርጥ ቀን ልጆች በምንም ሁኔታ እንዳይግባቡና ተቀናጅተው እንዳይሠሩ ለማድረግ የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ ተስፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶችን ጨምሮ፤ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና፤ ለአገርና ለወገን እንቆረቆራለን የምትሉ የሃይማኖት መሪዎች፤ የስቪክ ተቋማትና ታዋቂ ምሁራን ሁለቱ መሪዎች ተቀራርበው እንዲወያዩና ለአገር ዕድገትና ለወገን ሰላም ኃይላቸውን አቀናጅተው እየተረዳዱ እንዲሠሩ ብትሸመግሉ፤ በተያዘው ለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘውን ዲሞክራሲ፤ ፍትሕና ሰላም በአጭር ጊዜ ሊጎናጸፍ ይችላል የሚል ዕምነት አለን።

 

 

5 Comments

 1. ድንቅ ነው እስክንድር ለዶር አብይ ለኦነግ በውጭ አገር ሲንከራተቱ ከርመው ወደ ሀገር ቤት ገብተው እፎይ ብለው ለሚኖሩት ጁዋር መሀመድን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ባለ ውለታ ነው። አረጋዊ በርሄ ሌንጮ ለታን ዲማ ነገዎን ዳውድ ኢብሳን አርከበ እቁባይ ሀይለ ማርያም ደሳለኝ አገር ቤት ካለ ታምራት ላይኔን አባ ዱላን አስቀምጠህ ኡንጅነር ይልቃል፣አስቴር በዳኔ፣እስክንድር ነጋን ማሰር ነገሩን ሁሉ። አስቂኝ ትያትር ያደርገዋል ታማኝነትምያሳጣዋል።
  እነዚህ ሰዎች ይፈቱ አክራሪ ኦሮሞዎችን ለማስደሰት ጭዳ መሆን የለባቸውም።

 2. ጊዜው ረዘመ እንጂ እውቁ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በጊዜው ለቤዛ መጽሄት ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ እንዲህ ብሎን ነበር። “ሁሉም አንደበታቸው እንባ አዘል ነው። እሮሮ ያፈልቃል ልሳናቸው። ህይወታቸው ሁሉ ብሶት ነው። ይሄ ነው ባጠቃላይ የሃገሪቱ ገጽታ። ብእሬን ወደ ትራዴጂ የሚስበውም ይሄው ነው”. ዛሬ ይህ እጽብ ድንቅ ሰው በህይወት ቢኖር ምን ይለን ነበር? ሌላው ኢትዮጵያዊ ባብሌ ቶላ ” To kill a Generation” በተሰኘው መጽሃፉ ያካፈለን የደርግ የመከራ ዘመናትም የሚያንጸባርቁት የህዝባችን ሰቆቃ ነው። “ቀዳዳ ጨረቃ” በተሰኘው መጽሃፉ ሃማ ቱማ ያስነበበንም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው። ሌሎችንም ያለፉና ያሉ ጸሃፊዎች እየጠቀሱ ትላንትም ዛሬን እንደሚመስል ማመላከት ይቻላል። ያው በርዪተ- ዓለም ከፋፍሎ ሲያላትመን የነበረ ጭካኝ አውሬ አሁን ደግሞ በዘርና በጎሳ በሃይማኖት አሰልፎ አቅጣጫ እንደጠፋበት እንስሳ ያንጋጋናል። የችግራችን መዘዙ ብዙ ነው። በየዘመናቱ የተነሱ አለቆቻችን የዚሁ እንባ አፍላቂዎች ናቸው። ግን ያለፈውን የሚያስመኝ ጊዜ ይመጣል ብሎ ሰው አስቦ አያውቅም። አሁን እንሆ ሁሉም ባንዲራ አውለብላቢና ባለ ክልል በቋንቋው ተናጋሪ በመሆኑ ሃገሬ ነው ብሎ ያልመሰለውን ሲገድልና ሲያባርር ህግን ያስከብራሉ የተባሉት ቆመው ሲያዪ ያለዚያም ሲያስተባብሩ ምንኛ የጥቁር ህዝብ ጠላቱ ራሱ እንደሆንን ተግባራችን ያሳያል።
  ወንድማችን ገ/ክርስቶስ ዓባይ የጻፈውን አየሁት። እኮ በለ “የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል” ይሉ የለ አበው። እንዴት ሆኖ ነው በክልልና በዘር፤ በቋንቋ እንዲሁም በፈጠራ ወሬ ለጥፋት በሚንጋጋ ህዝብ መካከል ሰላም ማስፈን የሚቻለው? እኔ ፓለቲከኛ አይደለሁም። የዘር ፓለቲካ ግን አይገባኝም። የክልል ፓለቲካ አስተሳሰብና እይታ ሳይቀየር በሃበሻው መሬት ሰላም ይኖራል ብዬ አላምንም። የኤርትራው መሪ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር። “ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰተናል” ይህን ያሉት የወያኔን ክፋትና ተንኮል ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነበር። አሁንም የሃገሪቱ የጎን ውጋት ወያኔ ነው። የወያኔ የነፍስ አባት ሻቢያ ተራራ ላይ ቆሞ እየሳቀባቸው ነው። ያም ያንገበግባቸዋል። ግን የማይገፉት ተራራ ላይ ስለቆመ ምንም ማድረግ አይችሉም። ወያኔና ሻቢያ በተንኮል የተቃመሱና ሌላውንም ያቀመሱ ለመሆናቸው ያለፈና የአሁን ታሪካቸው አስረግጦ ይናገራል። አሁን የምናየው የኦሮሞ ግርግርም እነርሱ በቀደድት መንገድና አስተሳሰብ የሚራመድ ነው። ግን ያኔ እና አሁን ነገሮች ይለያሉ። ብዙ የሚያራምድ አይሆንም።
  ሻቢያ በበረሃ እያለ አብረውት የተሰለፉትን በዚህም በዚያም እያሳበበ ይገልና ያሰር እንደነበር በህይወት ያሉ የፓለቲካ ጽዋውን ሙሉ ለሙሉ ያልጨለጡ የእውነት ሰዎች ይናገራሉ። አንድ ጊዜ አንድ የሃይል መሪ የታሰሩ ሰዎች ሲነድ አይቶ ያስቆምና ምን ሰርተው ነው ብሎ ይጠይቃል። አስሮ የሚነዳቸው ታጋይም “አመራርን በመቃውም”ይለዋል። ከዚያ በህዋላ በእነዚያ ወገኖች ላይ የተፈጸመውን ለመጻፍ ይዘገንናል። በነገራችን ላይ የደረቀ ትልቅ አጠና ተሸክመው ነበር የሚጓዙት። መገመት ይቻላል የአጣናውን ተግባር … ግን ለማገዶ አይደለም። ሰዎች ስንፈጠር የሆነ ችግር አለብን። ከእንሥሳት እንለያለን እንላለን እንጂ ሥራችን ከእንስ ሳት በላይ ነው። አሁን እስክንድር ነጋ፤ አቶ ልደቱ አያሌውን፤ ሌሎችንም ምንም ሃገር አፍራሽ ያልሆኑ ሰዎችን እያጋፈፉ ማሰር ለኦሮሞ ሽብርተኛ ፓለቲከኞች ማጣጫ ካልሆነ በስተቀር በጭራሽ በጉዳዪ የሉበትም። የችግሩ ፈጣሪና አቀናባሪ ሶስት ሃይሎች ናቸው። ግብጽ፤ ወያኔና የኦሮሞ ጽንፈኛ ፓለቲከኞች ከአክራሪ እስላማዊያን ጋር በመተባበር የተሰራ ግፍ ነው። ሌላው ሁሉ ዘጥ ዘጥ ነው። ጠ/ሚሩ እየቆዪ ወያናዊ መልክ እንዳይኖራቸው ያስፈራል። በጊዜ ቃልና ሥራ እስካልተገናኙ ድረስ አንድ አንድን መግደሉና ጥፋቱ ይቀጥላል። ተገኘ የተሻወርቅ ሰው እንቆቅልሽ ነው በሚለው ላይ ከጻፈው ግጥም በመጥቀስ ልሰናበት።
  ንገሩኝ እናንተ ገባን የምትሉ
  ይሄ ነው ብላችሁ የሰው ልጅ ባህሉ
  ክፋቱን ጥፋቱን ባንድ ፊት አርጉና
  ልማት ደግነቱን ወደዚህ ለዩና
  አንፍሱ አንጓሉና ብጥር አድርጋችሁ
  ንገሩኝ የሰው ልጅ ይሄ ነው ብላችሁ።
  ለእኔ የሰው ልጆች እድል ፈንታና የገበጣ ጫወታ ጭራሽ አይገባኝም። ለመኖር የምንገዳደልበት ዓለም አይጣፍጠኝም። የሌላው እንባና ሞት፤ የሃብት መውደም ጉሮ ወሸባዬ የሚያሰኘው የሰው ስብስብ ሰውነቱ አይታየኝም። የራስን መብት ለማክበር የሌላውን መናድ ዞሮ ለመናናድ ካልሆነ በስተቀር ቋሚነት የለውም። ዛሬ ሱቅ ወጥቼ ማር ገዛሁ። ስገዛው ማሩ የመጣው ከስፔን ነው ይልና ግን ከሜክሲኮ፤ ከብራዚል፤ ከሩማኒያ የመጣም ታክሎበታል በማለት ይናገራል። ዓለም አንድ እየሆነች ነው። ዛሬ ክልል የሚባል የኋላቀር እይታ ነገ ሲፈራርስ በክልል ስም የበደሉ እነርሱ ጋ ባይደረስ በልጅ ልጆቻቸው ላይ ብቀላን ያመጣል። አብሮ መኖር አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ነው። አለማችን ጠባለች። በቻይና ተወራለች። ነገ ቻይና ኢትዮጵያን ያራሴ አካል አረጋለሁ ብትል ምን እንል ይሆን? የሃበሻው ፓለቲካ ሁሉን እስካላቀፈ ድረስ የእብደት ፓለቲካ ነው። ለእብዶችም ሆስፒታሉ ስፍራ የለውም። እናስተውል። መገዳደላችን ይቁም! በቃኝ!

 3. ረጅም ታሪክ ቢሆን ተረሳ ይባላል:: እስቲ ወደ 4 አመታት ልመልሳችሁ : ዛሬ አዲስ አበቤ ነው ብሎ የተነሳው ሀይል ትናንት በሚያስገርም ሁኔታ ለወያኔ ፀጥ ለጥ ብሎ ይገዛ የነበረ ስብስብ ነው:: ያለ የሸዋ ኦሮሞ ቄሮ ና የአማራ ፋኖ የህይወት መስዋእትነት እስክንድር ከእስር አይፈታም ነበር:: ይህ ያፈጠጠ የማይካድ ሀቅ ነው::እሱ ግን ውለታ ቢስ ስለሆነ በእሱ ጀግንነት የወጣ ይመስለዋል:: በሽግግር ወቅት ግጭትን ከመጋበዝ ውጪ ወያኔ የከፋፈለውን የአማራንና ኦሮሞን ህብረተሰብ ሲያቀራርብ አላየንም:: ወያኔ ያላቋረጠ ለ2 አመታት ሀገርን በሚያፈራርስበት ወቅት ዐቢይን መቦርበር ከጊዜያዊ ጀብደኝነት በስተቀር አርቆ ከሚያይ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ አልነበረም::
  አሁን ከታከለ ኡማ ጋር በሽግግር ጊዜ ጦርነት መክፈት ማንን ለመጥቀም ነው?

  የእስክንድር ድጋፍ አዎ በስሜት ብቻ በሚነዳው ዳያስፖራ መንደር ገዝፎ ይታያል:: በአዲስ አበባና ኢትዮጵያ ዐቢይና እስክንድርን ማወዳደር ጅልነት ነው:: ህዝብን የሚያነሳሳ ወንጀል ከሌለበት እስክንድርም እንደማንኛውም ወገን ተጣርቶ ይለቀቃል:::የእስክንድርን ፍፁም ኢትዮጵያዊነት አልጠራጠርም ለእኔ የማልቀበለው ጊዜያዊ ጀብደኝነቱን ብቻ ነው::ለነገሩም ቢሆን የእስክንድርና ጃዋር ፖለቲካ በተከታታዮቻቸው ላይ ያለ አመለካከት ልዩነት ነው: :የጃዋር ፀረ ኢትዮጵያ መንጋ ለመግደልና ለመጨፍጨፍ ወደሗላ አይሉም:: የእስክንድር ተከታዮች ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስቀድማሉ:: እስክንድር ለዐቢይ አጋር ከሚሆን በዚህ ወቅት የመረጠው practically I see him as a useful weapon for TPLF’s destruction of the ethiopian state.
  እርቅ ሳይሆን እስክንድርና ጀሌዎቹ ከጊዜያዊ ብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥተው ከዐቢይ ጋር በመሰልፍ ወያኔ የጀመረውን ሀገር ማፍረስ በጋራ እንመክት! በአርሲና ባሌ የሚጨፈጨፉት ወገኖቻችን እንታደግ!!

 4. መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ
  የሚባለው ሀቅ ነው ። እውነቱ የሚል ስም ይዘህ ስትዋሽ አለማፈርህ ያስደንቃል ።

 5. Dear Habesha online Editor
  Can you please post the original Amharic comment I posted under this commentary? My original posting was in the Amharic Language, not in English.
  Thank you,

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.