በትንሿ ዕድሚያችን መቶ በማትሞላው
ስንቱን ውጣ ውረድ እንግልት አየነው
ስንወድቅ ስንነሣ
ስንጠቁር ስንከሣ
መኖር ደጉ ነገር ራስን ያሳያል
ገመናን ሳይሸሽግ ለታሪክ ያቀርባል
አሮጌ ዓመት አልቆ በአዲሱ ሲተካ
የትናንቱ ዛሬ ሲቀርብ ለትረካ
የባሰ እንዳይመጣ ተመስገን በማለት
መቀበል ይገባል ሲጠባ አዲስ ዓመት
ልንል ይገባናል የከርሞ ሰው በለን
የምንጠብቀው ቁምነገር ስላለን
የትናንቱ ጅምር ለነገው ስንቅ ነው
የከርሞ ሰው በለን ብለን ከለመነው
ከዛሬ ለይ ቁሞ ትናንት ሲታወስ
ያ ሁሉ መከራ ወድቆ መንከላወስ
ተመስገን ያሰኛል አታምጣ የከፋ
ለልጅ ልጅ እንዳይደርስ አንገት የሚያስደፋ
የትናንቱን ስቃይ ስንቋጥር ስንፈታ
ለነገው አብሮነት ይገባል ይቅርታ
በዕድሜ አትቸኩብን አኑረህ አሳየን
ታሪክ ለመናገር ለመመስከር አብቃን
ኑሮ ባይመችም ከመሞት ይሻላል
ለሚመጣው ትውልድ እርሾ ያቀብላል
ቢከፋም ቢደላም ታሪክ ቅብብል ነው
ቀን ጎደለ ተብሎ ካልደረቀ ተስፋው
ልንል ይገባናል የከርሞ ሰው በለን
የምንጠብቀው ቁም ነገር ስላለን
ዛሬ ስንገንባ ነገን በማሰብ ነው
ለተተኪ ትውልድ እንዳይጎረብጠው
የትውልድ ውዴታ
የትውልድ ግዴታ
የታሪክ አውንታ
ተረካቢ ኑሮ ማሻገር ሲቻል ነው
ዘመን ተሻጋሪ ሕያው የሚሆነው
ልንል ይገባናል የከርሞ ሰው በለን
የምንጠብቀው ቁም ነገር ስላለን