“መንገድህን ዘግቶ
ማለፍያ አሣጥቶ
በጡንቻው ተመክቶ
ዋርካ ቢሆን ተንሰራፍቶ።
ያ!…የሌለው ህሊና
በሀገረህ ላይ ቢሆን ገናና።
ሆኖ አፄ በጉልበቱ
ሁሉን እያለ ‘ምናበቱ!’
ምን ታደርገዋለህ?
አቅም ጉልበት ከሌለህ?”
ብዬ ብጠይቀው፣
ባለአገር ደነቀው።
“ከቶ በመንግሥት ሀገር
ምንድነው ማሥቸገር?
እዛም እዚም አጥር ማጠር?
ማለት አላሻግር?
ብሎ፣ ህግን ጠርቶ
ነገሩን አብራርቶ
አጥሩን እንዲያፈርስ
የበደለውን እንዲክስ
ማድረግ ነው፣
ህግ ከገዛው።
ህግ ካልገዛው
ዱላ ነው የሚገዛው።
እናማ…
አረገው ዠለጥ፣ዠለጥ
መለፊያ እንዲሰጥ።
እንዲያ ነው እንጂ አያ
ማን ይታገላል ከአህያ?
የአህያ ሥም ሲነሳ
ሁሌም የሚወሳ
አንድ ወግ ትዝ አለኝ
ከተሜ አድምጠኝ።
………………………
አንድ ልግመኛ አህያ
ባላገር ገዝቶ ከገብያ…
እቃ ጭኖበት እየነዳ
በሰላም እየሄደ በሜዳ…
ድንገት ሲደርስ ከዳገቱ
ለገመ አህያው በብርቱ…
‘ዳገቱን አልወጣም ተሸክሜ
ግደለኝ እንጂ እዚሁ ይፍሰስ ደሜ።’
ወጣቱ በዱላ ደጋግሞ ቢነርተው
ቡላ ሆዬ ቅምም አላላለው።
‘ኮበሌው’ ቁጣው ገንፈሎ
ዓይኑ በንዴት ተጎልጉሎ፤
የሚያደርገው ጠፍቶት ሲጎማለል
አየና አንድ ብልህ ከገብያተኞች መሐል፣
ጠጋ ብሎ የአህያውን ሥሥ ብልት
‘በአልቃሾ’ አንዴ ቢወጋበት…
ቡላ ሆዬ ተፈናጥሮ ተነሣ
ዳገቱን በአፍታ ወጣው እየፈሣ።
እናም ……….
እያሳዩት ‘አልቃሾን’ አንጠልጥለው በእጃቸው
እወቅ አንተ ወጣት ችግሮች ሁሉ
ዛሬም፣ነገም፣ሁሌም ይፈጠራሉ።
ለእነዚህ ችግሮችህ መፍትሄ ለማምጣት
አያሥፈልግም ንዴትና ጩኸት።
ከህግ በላይ የሆነብህን ጉልበተኛ
መርታት ካልቻልክ በዳኛ…
“ከሆነብህ አባቱ ዳኛ
ልጁ ደግሞ ቀማኛ።”
እውነትህ ወድቃ
ውሸት ከሆነች አለቃ።
ቢተናነቅህ ሢቃ
ጠላትህ ፊት ደረትህን አትድቃ።
የወንዶች ወንድነህና
ለእውነት ሟች ጀግና
ነገ ለሚሞት በተፈጥሮ
ለሚቀበር በጎሮ።
ነገ ለሚሞት በበሽታ
ለሚቀበር ያለ ወይታ።
ነገ ለሚሞት በአደጋ
ከሠል ሆኖ ያ-ሥጋ።
ከሞት በኋለም የክፋት ምሳሌ በሆነው
መናደድህ እና በሥጭትህ ዋጋም የለው።
ሁን ትዕግሥተኛ አንተ ሰው
በዘር የማታምነው፤
የቋንቋን ንግሥናን የምትፀየፈው፤
በሰዎች እኩልነት የምታምነው።
ሥትሆን ነውና አሥተዋይ ጥበበኛ
የምታመላክተው የዓለምን መዳኛ።
ሥትኖር ነውና መፍትሄ የምታመጣ
ከአንተ ይራቅ ንዴት እና ቁጣ።…”
በማለት በቁም ነገር
መለሰልኝ በለአገር።
ያኔ ታውሮ የነበረው አይኔ በራ
ነበርና በጨለማ ከባለጌ ጋር ላወራ።
የላኸጫምን የምላሥ ጉልበት
በንዴትህ ነው ለካሥ የምትሞርድለት።
በአደባባይ ከሚያቀለህ
መልሥ አትሥጠው ይቅርብህ።
ያለወቅቱ ሾተል አትምዘዝ
በነገር ከጅል ጋር አትሞዘዝ።
ድንቁርነውን ሊተፋብህ
አፉን ቢያሞጠሙጥብህ
ንቀህ እለፈው
ያኔ ነው ባለጌ የሚቆጨው፤
እንደአልቃሾ የሚለበልበው
የዚች ግጥሜ መታሰቢያነቷ ዘር፣ቀለም፣ቋንቋ ሳይመርጡ፣ ለሰው ነፃነት፣እኩልነት ፍትህ ዕዳሜያቸውን ሙሉ ሲታገሉ ኖረው ላለፉት እና ዛሬም ለሚታገሉት፤ ሰው መሆናቸውን ለተገነዘቡ ፣እውነታቸው ልክ እንደ “አልቃሾ “ውሸታሞችን በንዴት አሥፈንጥሮ ለሚያሥነሳቸው ከምር ሰው ለሆኑ ሰዎች ትሁንልኝ።
ጥቂቶቹን ልጥቀሥ
የአለም በለቅኔ እና ደራሲ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አብዬ መንግሥቱ ለማ
ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ
አቤ ጎበኛው
ጳውሎስ ኞኞ
በዓሉ ግርማ…
እሥርና እንግልት ያልበገረህ እሥክንድር ፈጣሪ ፅናቱን ይሥጥህ …
ሚያዚያ 17/2012 ዓ/ም
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ