April 25, 2020
10 mins read

የአራት ልጆች እናቷ ኢትዮጵያዊት አራስ ስንብት – በቨርጂኒያ መቃብር ቦታ

VOA ዜና
ጽዮን ግርማ

“እርሷ ለልጆቿ ሕይወቷን እንደሰጠች እኔም እሰጥላታለሁ። ልጆቹን ሰብስቤ አሳድግላታለሁ” – የ17 ዓመቷ የወገኔ ልጅ

የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረና ሥርጭቱን ለመግታትም አካላዊ መራራቅ ተግባራዊ እንዲሆን ከተደረጉባት አንዷ በሆነችው በዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች በኮሮናቫይረስም ይሁን በሌላ ሕመም ሕይወታቸው ሲያልፍ የሚወዷቸውን ሰዎች እንዲቀብሩ የሚፈቀደው ለአምስት ወይም ዐስር ሰዎች ብቻ ነው።

የወ/ሮ ወገኔ ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት በጥቂት ሰዎች ሲከናወን
የወ/ሮ ወገኔ ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት በጥቂት ሰዎች ሲከናወን

ትላንት አርብ ሚያዚያ 16/ 2012 ዓ.ም በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የቀብር ሥነ- ስርዓቷ በተፈፀመው በአራት ልጆች እናት ወ/ሮ ወንጌል ደበሌ ስንብት ላይም የተገኙት ሰዎች ቁጥር ቤተሰብን እና የቀብር አፈፃሚዎቹን ጨምሮ ከ10 እስከ 15 ይሆናል።

የ43 ዓመቷ ወንጌል ደበላ እና ባለቤቷ የ50 ዓመቱ አቶ ይታገሱ አስፋው፤ አሁን የ17 ዓመት ልጅ የሆነችውን ምህረት እና የዐሥር ዓመት ልጅ የሆነውን ናኦልን ይዘው ነበር ከዐሥር ዓመት በፊት በዲቪ ሎተሪ ከኢትዮጵያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡት። ወ/ሮ ወገን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመምጣቷ በፊት በአንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ ላብራቶሪ ቴክኒሺያን ነበረች።

አሁን ከተወለደ ሦስት ሳምንት የሆነውን አራስ ልጇን የስምንት ወር እርጉዝ እያለች መጋቢት 10 /2012 ዓ.ም ሆሊክሮስ ወደሚገኘው መደበኛ ሃኪሟ ጋር ለክትትል ስትሄድ ትኩሳት ስላላት ወደ ወደ ድንገተኛ ክፍል መርቷት ነበር። ባለቤቷ አቶ ይታገሱ እንደነገረን ራሷን ብቻ እንድትንከባከብ ነግረዋት ወደቤት እንድትመለስ አደረጓት። እቤት ከመጣች በኋላ ሁኔታው እየባሰባት ሲሄድ ከአምስት ቀን በኋላ መጋቢት 16 ወደ ሆስፒታል መለሷት። በወቅቱ የመተንፈስ ችግር ያጋጠማት በመሆኑም ልጇን ሌቪንን እንድትወልድ ተደረገ።

ባለቤቷና ልጆቿ ወገኔን ከዚያ በኋላ መልሰው አላዩዋትም። በኮሮናቫይረስ ምክኒያት በደረሰባት ሕመም ለከፍተኛ ሕክምና በተዘዋወረችበት ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ሚያዚያ 13/2012 ዓ.ም የወለደችውን ልጅ የማግኘት ዕድል ሳታገኘ ሕይወቷ አለፈ።

ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት
ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት

“እናቴን የመሰናበት ዕድል እንኳን አልነበረኝም” ትላለች የ17 ዓመቷ ልጇ ምሕረት ይታገሱ ወደ ሆስፒታል ስትገባ አንዴ ደውላላት የተባለችውን ከነገረቻት በኋላ መልሳ ድምጿን እንዳልሰማችው በሐዘን ትገልፃለች። “እርሷ ባታየንም ባትሰማንም አንድ ግዜ “ዙም” በተሰኘ የኢንተርኔት ላይ መደወያ እንዳየቻት ትናገራለች።

ለወትሮው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰው ሲሞትባቸው እንደየ እምነታቸው በአዳራሽ ወይም በቤተ እምነቶቻችቸው የስንብት ዝግጅት አሰናድተው ሲጨርሱ ነበር ወደ ቀብር ቦታው የሚወሰዱት። የቀብር ሥነ- ስርዓቱ ሲከናወንም በመቃብሩ ቦታ በጣም በዛ ያሉ ሰዎች በቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው ታጅበው ነበር ለሽኝት የሚሄዱት። ትላንት አርብ ጠዋት ከጠዋቱ አራት ሰዓት በተከናወነው የወ/ሮ ወገን ደበሌ አስክሬን ሽኝት ላይ ግን ይህ አልነበረም። በእርግጥ በሲልቨር ስፕሪንግ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ- ክርስቲያናቸው አንድ ወንጌላዊ ከጥቂቶቹ ቀባሪዎች አንዱ ሆኖ በዚያ ተገኝቶ ነበር።

ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት
ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት

ፊታቸውን በፊት መሸፈኛ ማስክ በከለሉ ጥቂት ሰዎች ታጅቦ በተከናወነው በዚህ የቀብር ሥነስርዓት ከተራራቁ ሰዎች መካከል ላይ ከልጁ ጋር ብቻ ቆሞ ሐዘኑን የሚገልፀው ባለቤቷ አቶ ይታገሱ ደግፎ የሚያፅናናው አልነበረም። ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክኒያት እንዳይጠጋጉ በመከልከሉም ይህን የእርሱን ሐዘን ቆሞ መመልከት ለሌሎችም ሰዎች እጅግ ከባድ መሆኖ ከፊታቸው ላይ በቀላሉ ማስተዋል ይቻል ነበር።

የ17 ዓመት ልጇ ምህረት ይታገሱ። የእናቷን ሳጥን ያለበት አስክሬን አንገቷን ሰብር አድርጋ በሰቀቀን ታለቅሳለች “ አንድ ሰው አይደለም ያጣሁት ሦስት ነው።እናቴን እህቴን እህቴን …ጓደኛዬ” ትላለች። “ሴት ልጇ እኔ ብቻ ስለነበርኩ በጣም እንቀራረብ ነበር። እናቴ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” በሚል በተፃፈው መሰረት ሩጫዋን ጨርሳ ወደ ፈጣሪዋ ወደ አባቷ እንደሄደች አምናለሁ። ይህንን እምነት እና ጥንካሬን ያስተማረችኝ እርሷ ናት።እዚህ የደረስኩትም በእርሷ ነው። ግን ቻው እንኳን ሳልላት ነው የሄደችው። ልጇን እንኳን አላየችውም።” ብላናለች።

ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት
ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት

አባቷ አቶ ይታገሱ፤ “ሕፃኑን የያዘችው እርሷ ናት ወተት እየበጠበጠች ታጠባዋለች፤ምክኒያቱም ከውጪ ሰው አይገባም። በዛ ላይ ልጆቹም ምናልባት በቫይረሱ እንዳይጠቁ ለጥንቃቄ ሲባል ማንም አይጠጋቸውም። እንደገን ደግሞ እኔ ከዱሮ ጀምሮ አራስ ልጅ መያዝ አልችልም” ብሎን ነበር። እርሷም እንደነገረችን የተወለደውን አራስ ልጅ መያዝ ከጀመረች ሦስት ሳምንቷ ነው።

“የተወለደውን ሕፃን ሳይ እናቴን ያሳታውሰኛል። ልጆቹን ሳይ እሷን ያገኘኋት ይመስለኛል። ከእንግዲህ በኋላ እነሱ ናቸው ያሉን። እሷ ‘አንቺ ስትወልጂ ልጅ የሚጠብቅልሽ ሰው አያስፈልግሽም እኔ ነኝ የማሳድግልሽ’ ትለኝ ነበር። እርሷ ለጆቿ ህይወቷን እንደሰጠች እኔም እሰጥላታለሁ። ልጆቹን ሰብስቤ አሳድግላታለሁ” ።

ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት
ባለቤቷና አቶ ይታገሱና ልጇ ምህረት

ከቀብር አስፈፃሚዎቹ አንዱ ጀሚስ ክሊክ፤ “ለወትሮው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ወደ ቀብር ቦታ ሲመጡ በእምነት አባቶቻቸው ታጅበው፣ ሻማ እና የመሳሰሉትን ነገር ይዘው በዛ ብለው ነበር የሚመጡት አሁን ግን ያው እንደምታዩት ወል ልክ እንደ ዛሬው ጥቂት ሰዎች ሆነው ይመጣሉ ወይም ደግሞ በስልክ ያስፈፅማሉ” ብሏል።

“ከወገኔ ጋር በጓደኝነትም በትዳርም ወደ 25 ዓመታችን ነው። የልጅነት ጓደኛዬ የልጅነት የትዳር አጋሬ ነበረች። ወገኔ ለልጆቿ እናት ብቻ አልነበረችም” ያለን ባለቤቷ አቶ ይታገሱ። ከታመመች ጀመሮ ላፅናኑት ለክርስትናም ለእስልምና እምነት ተከታዮች ቤተሰቡን ያግዛል በለው በጎ ፈንድ ሚ አማካኝነት ገንዘብ ላሰባሰቡ ሁሉ ምስጋናን አቅርቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop