ኮሮና “ኩሩና” እና “ይህም ያልፋል” – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

/

ሁለት ወቅታዊ ግጥሞችን ዛሬ ሚያዚያ 1/2012 ዓም ፅፊ እንሆ በረከት ብያለሁ።
መልካም ንባብ።
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ኮሮና-“ኩሩና”

በጨርቅ ተለጉሞል ፣ታፍኗል አፋቸው።
እኚህ ከተሜዎች ከጥንት ሳውቃቸው
ጥርስ አያሥከድንም ተረብ ጫወታቸው
ዛሬ እንዲህ በጨርቅ ምነዋ፣ ታፍነሳ አፋቸው?
እያልኩኝ ሳዘግም፣ እህል ላስፈጭ ከተማ ዘልቄ
“ኩሩና፣ኩሩና” ፣እያሉ ሲያወሩ ሰማሁ ተደንቄ።
ወፍጮ ቤቱ ውስጥ እግሬ ገና እንደዘለቀ
ምንድ ነው “ኩሩና” ?ሲል አፌ ጠየቀ?
አስፈጪው በሙሉ ገንፍሎ በሣቅ….
” ‘ኩሩና’ ትላላች አልሰምቶም ናት እቺ
መሆኖ አይቀርም ከእኛ ቀድሞ ሞቺ።”
እያለ አረገደ፣ ዙሪያዬ ያለው- ከተሜ አሥፈጪ
አውቆና ተራቆ ፣ በእኔ አለማወቅ ሆነ አላጋጪ።
“አያ ሞኝ ከተሜ ሳቅህን ተውና
አሥረዳኝ በቅጡ ምንድነው ኩሩና?”
ብዬ በጥያቄ አይኔን ባጉረጠርጥ
ምድረ ከተሜ ሁላ ፣ አለ ፍጥጥ፣ፍጥጥ።
አንዷ ከተሜ አፏ ላይ ጨርቅ መርጋ
ፈንጠር ብላ ቆማ እኔ እንዳልጠጋ
“እቱ እዛው ሁኚ ፣ ወደእኔ አትጠጊ
ሥለ ኮሮና ለማወቅ በመሆንሽ ጠያቂ
ሳይገባው ገባኝ ከሚል- አንቺነሽ አዋቂ።
ካልሰማሽ ላሥረዳሽ- ሥለ አዲሱ በሽታ
ዓለምን ሥለወረረው- ያለአንዳች ኮሽታ።
ወደሀገር ሥለገባው- ተሳፍሮ በጢያራ
አልሰማሺም እንዴ ሣር ቅጠሉ ሲያብራራ?
በፈረንጅ ሥሙ አሥሬ እየጠራው- እያለ “ኮሮና”
ዓለምን በመሥጨነቅ ሆኗል ና ቀብራራ ገናና
በአንድ ቀን ሺ ገዳይ ሆኗል በአውሮፓ
ከቶም አልገታችውም ታላቋ አሜሪካ።”
በማለት “ኩሩና ” በሽታ መሆኑን ለእኔ ሥታሥረዳ
እህሌን ለመመዘን ላሥቲክ አጥልቆ ሚዛኑን እያሰናዳ
ባለወፍጮው ባለአገርነቴን ተረድቶ በዘዬዬ ጥቆማ
አለ “እንዴት ሳታቂ ገባሽ ወደዚህ ከተማ?”
መለሥኩለት እኔም አንዳች ሳላቅማማ
“ሩጫ ነው የእኔ ኑሮ እረፍት የሌለው ቀንም ሆነ ማታ
ከዶሮ፣ከበግ፣ከፍየል፣ከከብት፣ከምድጃ ጋር የሚንገላታ።
መሽቶ መንጋቱን የማላሥታውሥ ምሥኪን ነኝ አውታታ
መች ከቶ አድሎኝ ቁጭ ብሎ ለማውራት ለወሬ ሥልቅታ።
መች እንደእናንተ ደለኝ፣መች ቂጤን አመመኝ
በመዘፍዘፍ ብዛት፣በበዛ ቁጭታ።
ደሞስ በእናንተ ነው የበዛው፣ወሬኛ ሀሜተኛ
ቀማኛና ሌባ ቀጣፊ ወስላታ።
በከተሜ ጦስ ነው ለገጠሩ የሚተርፍ
እንዲሃል በሽታ።”
በማለት ብመልስ፣የተጠየቅሁትን በቅጡ ባብራራ
ለእነዚህ ከተሜዎች መልሴ ሆኖባቸው ግራ
ወፍጮቤቷን ወረራት የነገር አቧራ
ተዘርቶ ታጨደ የጫጫታ አዝመራ።
አብዛኛው “ትክክል ናት ።” አለ ፣የከተማን ኑሮ እየረገመ
ሴረኝነቱን፣ሐሜቱን፣ጭራ መቁላቱን፣ሰብቁን፣እያለመ።
በነውረኝነት የተጨማለቀ ህይወቱን መልሶ እየቃኘ
ቀልቡ ተመልሶለት በፀፀት የንስሐ ሞትን እየተመኘ።
በማመን በራሱ ዳተኝነት ከወረርሹኙ ጋር እንደተሰናኘ
ዛሬ ሐጢያቱ ተትረፍርፎ ፣በፈጣሪ ቁጣ ፍርዱን እንዳገኘ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያድርሱልኝ ለመጋቤ ሐዲስ ቡሩክ የኦሜጋ ቲቪ ባለቤት - ቀሲስ አስተርአየ

ይህቺ ግጥም የኮቪድ 19 ቫይረስን በማዋጋት ላይ ላሉ የጤና በለሙያዎችና በበጎ ፍቃደኝነት በንፁህ ልብ ድሆችን ለሚያገለግሉ በዓለም ለሚገኙ ሰዎች ይሁንልኝ።
“ይህም ያልፋል”
ተቃቅፈን የምንወዳደሰበት
አብረን፣ ፀሐይ የምንሞቅበት
አበረን፣ ጨረቃዋን የምናይበት
አበረን፣ ኃይቅ ላይ የምንዝናናበት።
አብረን፣ የምንፀልይበት
አበረን፣ የምንቀድስበት
አበረን፣ አዛን የምንልበት
አብረን፣ ልደታችንን የምናከብርበት
አበረን፣ ሙታናችንን አልቅሰን የምንቀብርበት
አብረን፣ ደግሰን ልጅ የምንድርበት
አበረን፣ ማህበር የምንጠጣበት
አበረን፣ ኳሥ የምነጫወትበት
አበረን፣ ሥቴዲዮም የምንጨፍርበት
አብረን፣ ቲያትር፣ፊልም የምናይበት…
ያ የአብሮነት ቀን ይመጣል
ይህ የሞት ንግሥና ያከትማል።
ኮረና “ኮ ቪድ 19” ተረት ይሆናል
የምንወዳቸውን ቢነጥቀንም
ለዘላለሙ ይረሳል
አዎ “ይህም ያልፋል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share