ሞት ፍርደ ገምድሉ! – በላይነህ አባተ

የሆሳዕና እለት ታስሮ እንደታመመው፣
ጎልጎታ ተራራ ነፍሱ እንዳለፈችው፣
በቃሉ እሚጠና ታርባም አይበልጥ እድሜው።

ጠሎተ አሙስ ማግስት ግፍ እንደፈጠመው፣
የዓለምን መድሀኒት በጦር እንደ ወጋው፣
ብሩኮችን ጠርጎ እርጉም እሚተወው፣
እንደ ምድር ችሎት ሞት ፍርደ ገምድል ነው፡፡

ሄሮድስ ሊያጠፋው ሲል እንደተሰደደው፣
በምስር በርሃ እንደተሰቃየው፣
በቃሉ የሚያድር ግማሽ ስንዝር እድሜው፣
ሞት ፍርደ ገምድሉ እየጎማመደው፡፡

የጣኦት ማምለኪያ ዛፉን ገንድስ ቢባል፣
ሞት ፍርደ ገምድሉ ሺደብር ያፈርሳል፡፡

ሞት ፍርደ ገምድሉ የግፈኞች አንበል፣
ጨለማን ተምድር አንሳ ግፈፍ ሲባል፣
የዓለም ብርሃንን ጠራርጎ ይወስዳል፡፡

ችሎት ተቀምጦ ሞት ፍርደ ገምድሉ፣
ሌባዎች ቀማኞች በአየር ሲንሳፈፉ፣
ጥረው አዳሪዎች በቃሬዛ አለፉ፡፡

ሞት ፍርደ ገምድሉን ከሳሽ ስለጠፋ፣
ባለማተብ አንቆ ሌጣውን አፋፋ!

ደሞ እንደ ልማዱ ሞት ሰብሮ ሚዛኑን፣
እድሜውን አርዝሞ የመስቀል ነጋዴን፣
ዘመኑን ጨምሮ ነፍስ አጥፊ ዘራፊን፣
በጥድፊያ ወሰዳት ብሩኳን አንቺዋን፡፡

ተእውነት ጋር ቀጥ ያሉ ሲጨሱ ሲነዱ፣
ታጣፊ ዋሾዎች እሳት ይሞቃሉ፡፡

ሞት ፍርደ ገምድሉ በመሲህ ጨክኖ፣
ምስማር ሲመታበት አንስቶ መርቴሎ፣
አመንኩ ያለው ሁሉ ከዳ እንደ ጉም በኖ፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ ክርስትያኑ ምሁር፣
በእነ ሳኦል ምድር እውነትን ሲያስተምር፣
ጨካኝ ፈሪሳውያን አስጎርቶ እንደ ዛር፣
ሞት አስቀጠቀጠው በድንጋይ በብትር፡፡

ግፈኞቹ እረብተው ቅዱሳን አለቁ፣
ጣኦቶቹ ቆመው ሺደብሮች ወደቁ፣
የዓለም ዳኛ ሆኖ ሞት ፍርደ ገምድሉ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሚያዚያ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

1 Comment

  1. In Ethiopia the once who are currently recovering in hospital beds are the lucky ones ,soon only one person out of a hundred of thousands will be getting a hospital bed in Ethiopia and ten out of a thousand will get a chance to consult a medical health provider provider from within the country.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.