አንድነት ይበልጣል – ሀዋሳ ታህሣሥ 2012
መግቢያ
የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ ሰብዓዊ መብቶችንና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት ታሪክና ሁኔታ መተንተን አይደለም፡፡ ይህ ሰፊ ጥናትና መድረክ ስለሚጠይቅ ለጊዜው እናቆየዋለን፡፡ በዚህ መጣጥፍ፣ ዛሬና ትናንት በሐገራችን በተከሰቱት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በጥሰቱ ተዋናዮች መካከል ያለውን ተመሣሣይነትና ልዩነት እንዲሁም የድርጊቶችን ተያያዥነትና ተከታታይነት (Pattern) ለማሣየት ሙከራ ይደረጋል፡፡ ወያኔ ከፌዴራል አንስቶ እስከያንዳንዱ ጥግ ድረስ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ባሰፈነበት የ27 ዓመት ጊዜ ውስጥ በታዩትና አሁን ከሁለት ዓመት ወዲህ ወያኔ ከማዕከል ተገፍቶና በክልል መሽጎ ፈላጭ ቆራጭ ከሆነ በኋላ በኢትዮጵያ በሚታዩት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በተዋናዮቻቸው መካከል ያለውን ተመሣሣይነትና ልዩነት እንዳስሳለን፡፡ ለዚህም መሠረትና መንደርደሪያም እንዲሆኑን የሚከተሉትን ሀሳቦች ገረፍ እናድርግ፡፡
ሰብዓዊ መብቶች
የሰው ልጆች ሌላ ሣይሆን ሰው በመሆናችን ብቻ ማለትም በተፈጥሮአችን ምክንያት የምናገኛቸው በርካታ ሰብዓዊ ባህርያት አሉን፡፡ ሰው ሕይወት/ነፍስ፣ አካል፣ ልዩ ልዩ ተግባርና ጥቅም ያላቸው የሰውነት ክፍሎች – አንጎል፣ አይን፣ ጆሮ፣ አፍ፣ እጅ፣ እግር፣ አእምሮ፣ ህሊና፣ ልቡና፣ ስሜት ወዘተ አለው፡፡ የሰው ልጅ ከነዚህ የተፈጥሮ ጸጋዎቹ የሚመነጩ ነጻነቶች አሉት፤ ሰብዓዊ መብቶች እንላቸዋለን፡፡ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት የመጠበቅ፣ በነጻነት የመዘዋወር፣ የማሰብና ሀሳብን የመግለጽ፣ የሰውነት ልዩ ልዩ አካላትና የስሜት ህዋሶች ሁሉ የተፈጠሩበትን ተግባር የማከናወን ለምሳሌ በአይንና ጆሮ መረጃ የማግኘት፣ ሀሳብና ስሜትን በአፍና በሌሎችም መንገዶች የመግለጽ የማይገሰሱ ተፈጥሮአዊ ነጻነቶች አሉት፣ ሥራ ለሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህርዩ፣ አቅሙና ግዴታው ነው፤ የመሥራት፣ ሐብት የማፍራትና ፍላጎቶቹን የማሟላት መብት የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ “ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም ይከበሩ” ሲባል የሰው ልጅ በተፈጥሮ (ዕድሜ፣ ጤና፣ አደጋ) ምክንያቶች እና በሕግ ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን ሊያጣ አይገባም (መገደል የለበትም)፤ አካሉ ሊጎዳና ሊጎድል አይገባም (መደብደብ፣ መሰቃየት፣ መቁሰል የለበትም)፤ ሊታገት፣ ሊታሠር፣ ሊጉላላና ሊሰቃይ፣ በግድ ውጣ፣ አትግባ፣ አትውጣ ሊባል፣ ሊዘረፍ፣ ሊሳደድና ሊሰደድ፣ ሊታፈን፣ ሊከለከል አይገባም ማለት ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ ሲባል የሰው ልጅ ሊራብ፣ ሊጠማ፣ ሊታረዝ፣ በበሽታ ሊማቅቅ፣ የትም ሜዳ ሊወድቅ፣ ሰብዕናውን የሚገነባባቸው ዕድሎች ሊነፈጉት አይገባም ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ መከበር ይገባዋል እንጂ ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅ፣ ማዋረድ ሊደርስበት አይገባም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትግልና ጩኸት ሌላ ሣይሆን መላ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ግዛት የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እነዚህና መሰል ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ ያለአንዳች አድልዎ ሊከበሩላቸው (Respect)፣ ጥበቃ ሊደረግላቸው (Protect) እና ሊሟሉላቸው (Fulfill) ይገባል በማለት ነው፡፡
ከሰብዓዊ መብቶች አንጻር የመንግሥታት ግዴታዎችና ኃላፊነቶች
በዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የኢትዮጵያን ጨምሮ የየሐገሩ መንግሥት፣ የዜጎቹን ሰብዓዊ መብቶች በሚመለከት ቢያንስ ሦስት ግዴታዎች ተጥለውበታል፡፡
1ኛ) የዜጎችና የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር – አለመጣስ (Respect)፣
2ኛ) የማንምና የሁሉም ዜጋና ሰው መብቶች በሌሎች ወገኖች እንዳይጣሱ ጥበቃ ማድረግ (Protect)፣እና
3ኛ) የዜጎችን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ደረጃ በደረጃ ለማሟላት መትጋት (Fulfill) ናቸው፡፡
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚመለከት፣ በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ውስጥ ማራኪ አንቀጾች እንዲካተቱ የተደረገው የወያኔን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ነው፡፡ በሕገመንግሥቱ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች አንቀጾች በተሟላ ሁኔታ መደንገጋቸው በራሱ ጥሩ ነው፤ ቢያንስ ቢያንስ የወያኔ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን ያከብር፣ ያስከብር እና ያሟላ ዘንድ፣ የራሱን ሕጎችና ተቀበልኩ ያላቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎች አንድ በአንድ እየጠቀሱ ለመሞገት አስችሏል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሣያ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ባለፉት 27 ዓመታት ያወጣቸው በርካታና ልዩ ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መግለጫዎች ናቸው፡፡ ከሞላ ጎደል የሁሉንም የኢሰመጉ መግለጫዎች መግቢያዎች የተመለከተ ሰው፣ ድርጅቱ በዚያ መግለጫው ለሚዘግባቸውና ለሚያጋልጣቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ቀዳሚ ማጣቀሻ መሠረት የሚያደርገው ተዛማጆቹን የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጾች እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ እርግጥ ወያኔ እነዚህን አንቀጾች ለረዥም ጊዜ በማስመሰያነትና በማታለያነት እንደተጠቀመባቸውም እናውቃለን፡፡ በተግባር የታየ እንደሆነ፣ ወያኔ ትናንት አዲስ አበባን ማዕከሉ አድርጎ፣ በፌዴራል ደረጃ ፈላጭ ቆራጭና የሰብዓዊ መብት ረጋጭ መንግሥት ነበር፤ በትግራይ ክልል የሚኖረው ሕዝብም የዚህ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ሰለባ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ወያኔ ማዕከሉን ወደ መቀሌ እንዲያዛውር ተገዶና በአንድ ክልል መሽጎ በፈላጭ ቆራጭነት ሰብዓዊ መብቶችን እየረገጠ ይገኛል፡፡
ወያኔና ከመንግሥት ውጭ ያሉ ሰብዓዊ መብት ረጋጮች – ዛሬና ትናንት
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የጊዜ መሥመር ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውጥኖችንና ተፈጻሚነታቸውን እንዲሁም የፈጻሚዎቻቸውን ተመሣሣይነትና ልዩነት ብሎም ተያያዥነትና ተከታታይነት (Pattern) ለማጤን፣ እዚህ ላይ ሁለት-ሦስት የዛሬና የትናንት ንጽጽሮችን ማየት፣ አንደምታቸውንም አስረግጠን መረዳትና ማሳየት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡
አንደኛ፡ ዛሬ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በይበልጥ የሚፈጸመው በመንግሥት ሣይሆን ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት መሆኑ፣
ሁለተኛ፡ ዛሬ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በስፋት የሚፈጸመው በዋናው ፌዴራል መንግሥት ሣይሆን በይበልጥ በክልል መንግሥታት ደረጃና አቅም መሆኑ፣
ሦስተኛ፡ ትናንትም ዛሬም የሰብዓዊ መብቶች ዋነኛ ረጋጭ ወያኔ መሆኑ፤
አንደኛ፡ ዛሬ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በይበልጥ የሚፈጸመው በመንግሥት ሣይሆን ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት መሆኑ፤
በቅጡ የተጠና ጥናት መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን እንደ ኢሰመጉ ባሉ የሐገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ሽፋን አግኝተው ይፋ የተደረጉ በርካታ የመብት ጥሰቶችን መነሻ አድርገን መጠነኛ ዳሰሳ ብንሠራ ልንደርስበት የምንችለው አንድ ድምዳሜ ይኖራል፡፡ ይኸውም እስከ መጋቢት 2010 ድረስ በነበሩት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ከተፈጸሙት የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ውስጥ ወደ ሰማንያ እጅ (80%) የሚሆኑት የተፈጸሙት በመንግሥት መሆኑ ነው፡፡ 20 በመቶ የሚሆኑት የመብት ጥሰቶች ደግሞ ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት የሚፈጸሙ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ “ከመንግሥት ውጭ” ስንል ለምሣሌ አገዛዙን በኃይል (በትጥቅ ትግል) ለመቀየር ይታገሉ የነበሩ ኃይሎችን ይጨምራል፤ በተለይ ደግሞ በዋነኛነት በሰላማዊ ትግል አውድ ውስጥ ሆነው ትግላቸውን በቀጥታ ከመንግሥት ጋር ብቻ ማድረግ ሲገባቸው ከመሥመር እየወጡ ወደ ጎን በአካባቢያቸው በሚኖሩ የሌላ ብሔር ሠላማዊ ዜጎች ላይ ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ጥቃት ይፈጽሙ የነበሩ አካላትንም ይጨምራል፡፡ የተሻለ ጥናት የተደረገበት ቢሆንም በቂ ትኩረት ያላገኘው ሌላው ለየት ያለ ምሳሌ ግን በጎጂ ባህላዊ ልማዶችና አሠራሮች ምክንያት በአንዳንድ ማሕበረሰቦች በራሳቸው የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ ለምሳሌ በሴቶችና በተገለሉ ማሕበረሰቦች ላይ የተጫነ የመሬት ባለቤትነት መብት ክልከላ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ህጻናትን መጣል (ሚንጌ – (ኦሞ ቻይልድን እናመሰግናለን!)) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲህ እያለ የሠራተኞች መብት ጥሰትንም ይጨምራል – በሐገር ውስጥና በውጭ የግል ባለኃብቶች የሚፈጸመውን ማለት ነው፡፡
ይህን መሠረት አድርገን ከመጋቢት 2010 ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንመልከት፡፡ ከመጋቢት 2010 ወዲህ ባሉት 21 የለውጥ ጅማሮ ወራት በኢትዮጵያ ከደረሱት የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ውስጥ እጅግ የሚበዙት እየተፈጸሙ ያለው ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት ነው፡፡ በንጽጽር ሲታይ በዚህ ጊዜ ውስጥ በዶክተር ዓቢይ መንግሥት እየተፈጸሙ ያሉት ጥሰቶች አነስተኛ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ለዚህ የማይናቅ መሻሻል ዕውቅና መስጠት ብዙ ጥቅም አለው፡፡ በዋነኛነት ወያኔንና ሌሎቹን ጽንፈኞች ያሳፍራል፣ አቅማቸውንና የድጋፍ መሠረታቸውን ያመነምናል፣ በሂደትም ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በዚሁ መሥመር የአልሚዎችን ገጽታ ያሻሽላል፣ የድጋፍ መሠረታቸውንም ስለሚያሰፋ ቀሪ ሥራዎችን ለማስኬድ ጉልበት ይጨምርላቸዋል፡፡ በዚህ አውድ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ አካላት ስንል በዋነኛነት የሚከተሉትን ያካትታል፡
- እንደ “ዲጂታል ወያኔ” ያሉ በሕወሐት ጽንፈኞች ስምሪትና ክፍያ የሚሰጣቸውን ሐገር አፍራሾችና ሌሎች ተላላኪዎችን (“Followers”)፤
- “ኦነግ ሽኔ”ን የመሰሉ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም የሚጥሩ የታጠቁ ኃይሎችና ደጋፊዎቻቸውን፤
- የተጀመረውን ለውጥ ለመንጠቅና ኃገሪቱን ለመበታተን የሚፈልጉ እንደ ጃዋር መሐመድና፣ በቀለ ገርባ የመሰሉ ጽንፈኞችና መንጋቸውን፣
- ለውጡ እየጠነከረ ከሄደ የለመዱት ጥቅማቸው እንደሚቀርባቸውና ለፈፀሙት ዘረፋና ግድያ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የፈሩ በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ የመሸጉ ቀልባሾችና ተባባሪዎቻቸውን፤
- በአድልዎና በእከክልኝ ልከክልህ ልዩ ተጠቃሚ ሆነው በሕገ ወጥ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበለጸጉና ይሄንኑ ልዩ ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ሲሉ ሁከትና ብጥብጥን በገንዘብ የሚደግፉ የብሔር ባለኃብቶችን (Ethnic Entrepreneurs) እንዲሁም
- ለአመታት የተጠራቀመ ዕውነተኛ ችግርና ብሶት ያላቸው፣ ይህንኑ በማሰማትና በመተንፈስ ሂደት ውስጥ ግን፣ በትግል የተገኘውን ነጻነት አጠቃቀምና ከነጻነቱ ጋር ያለውን ግዴታ በቅጡ ያልተረዱ ግለሰቦችና ስብስቦችን ሁሉ ይመለከታል፡፡
- በአጠቃላይ ብሔርተኛነትንና በተለይ የአንድ ብሔር ጥላቻን በሜዲያ፣ በሥርዓተ ትምህርትና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተጋቱ ያደጉ ህጻናትና ወጣቶች (ጎልማሦችም ቢሆኑ) በለውጡ ያገኙትን የነጻነት አጋጣሚ ሁሉ በብሔር ለመበሻሸቅ፣ ለመገፋፋትና መጤና ሰፋሪ ተብሎ የተነገራቸውን ሁሉ ለማሸማቀቅ፣ ለማጥቃትና፣ ለማሣደድ ተጠቀሙበት፡፡ አስቀድሞ በወያኔ የተቀበረውንና ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳውን ይህን ፈንጂ፣ ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ እነ ጃዋርን የመሰሉ በየብሔሩ የተሰገሰጉ ጸረ ዴሞክራሲና ጸረ አንድነት ኃይሎች በጥድፊያና በርብርብ ተጠቀሙበት፡፡ ተከትሎ የመጣውን እንደ ቀውስ የሚቆጠር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከነአዳሪ መዘዙ ሁላችንም ያየነው ነው፡፡
ሌላውን አቆይተን በቅርብ ዓመት፣ በወራት፣ ሣምንታትና ቀናት ውስጥ ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት ከተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል ጥቂቶቹን እናስታውስ፤
- በሰኔ 2010 እና በሐምሌ 11 2011 ዓ.ም የሲዳማን የ”ክልል እንሁን” ጥያቄን በማስታከክ በልዩ ልዩ የሲዳማ ዞን አካባቢዎችና በሐዋሳ ከተማ ውስጥ አረመኔያዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በነዚህ ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች (ሕጻናትና አረጋውያን ሳይቀሩ) በጭካኔ ተጨፍጭፈዋል፤ በቤተክርስቲያናት፣ በንግድ ድርጅቶችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ የቃጠሎ ጥቃትና የንብረት ዘረፋ፣ የሲዳማ ተወላጅ ባልሆኑ በርካቶች ላይ ድብደባና ማሸማቀቅ ተፈጽሟል፡፡ የዚህ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ዋነኛ ተዋናዮች ኤጄቶ የሚባሉት ወጣቶች ሲሆኑ ከጎናቸው ደግሞ የደቡብ ክልል፣ የሲዳማ ዞንና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት እና የጸጥታ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደነበሩ በግልጽ ታይቷል፡፡ በጀርባቸውና በኪሳቸው ውስጥ ደግሞ ጃዋርና የወያኔ ጽንፈኞችና ተከታዮቻቸው መኖራቸው የበርካቶች እምነት ነው፡፡ የዚህ የጭካኔ ድርጊት ሰለባዎች የወላይታ፣ የአማራ፣ የስልጤና የጉራጌ ብሔረሰቦች አባላትና ሌሎችም ዜጎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
- በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ደግሞ “ተከብቤአለሁ ድረሱልኝ” የሚል (የወያኔና የጃዋርን) ሤራ ተከትሎ ለ86 ዜጎች መገደል፣ ለበርካቶች አካል መጉደል፣ ለኃይማኖት ተቋማት (ቤተክርስቲያናት) መቃጠልና ለዜጎች ንብረት መውደምና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ኃይማኖትና ብሔር ተኮር የመንጋ ጥቃት ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ አካላት በተደጋጋሚ ከሚፈጽሟቸው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሌላ መንገድ መዝጋት፣ መንገደኞችን ማገት፣ ማጉላላትና ማስጨነቅ፣ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውቶቡሶችን መስበርና ማቃጠል፤ የግል ፋብሪካዎችን ማጥቃት ይገኙበታል፡፡
- አሁን ከጥቂት ቀናት በፊት (ታህሣሥ 11) ደግሞ በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ በሦስት መስጊዶችና በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመው የቃጠሎ ጥቃት፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች ንብረት በሆኑ በርካታ የንግድ ሱቆች ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ጥቃት፣ ውድመትና ዘረፋ ሌላው ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥቃት ማሳያ ነው፡፡ ቀጥተኛ ወንጀለኞቹ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ፣ ለፍትሕ አካላት ጊዜ መስጠትና መታገስ እንደሚኖርብን እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህም ሴራና ጥቃት ጀርባ ወያኔ በአንድ ወይም በሌላ መልክ ስለመኖሩ እኔ አልጠራጠርም፡፡ የወያኔ እጅ እንዳለበት ከተጠራጠርን በእርግጥም የወያኔን ማንነትና ምንነት በተለይም በዚህ ሰዓት ስለነደፈው በጥድፊያና በተስፋ መቁረጥ የታጀበ የአጥፍቶ-መጥፋት አይነት ሤራ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለወያኔ ባህርያዊ ፍላጎትና ግብር ተያያዥነትና ተከታታይነት (Pattern) በቅጡ አልተረዳንም ማለት ነው፡፡
ሁለተኛ፡ ዛሬ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በስፋት የሚፈጸመው በዋናው ፌዴራል መንግሥት ደረጃ ሣይሆን በክልል መንግሥታት አቅምና ደረጃ መሆኑ፣
የተደራጀ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣን በሚመለከት ቀንደኛው ነዳፊ፣ ሥልት አውጭ፣ በጀት መዳቢ፣ መልማይ፣ አሰማሪና አስፈጻሚ በትግራይ ክልል መስተዳድር ውስጥ የመሸገው ወያኔ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል መስተዳድርና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ የተሰገሰጉ ጸረ ለውጥ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ አመራሮችና ካድሬዎችም ቀላል ረጋጮች አይደሉም፡፡ ለዚህ ማሣያ ፍለጋ ሩቅ ማለትም ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምዕራብ ጎንደርና ቤኒሻንጉል ወዘተ መሄድ ሳያስፈልግ በዋና ከተማችን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ለምሳሌ በቡራዩ እንዲሁም በሐዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን ባለፉት በርካታ ወራት የተፈጸሙትንና እየተፈጸሙ ያሉትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች (እንዲሁም የብሔር መድልዎ፣ ማፈናቀል፣ ለአገልግሎቶችና ለሥራ የእኩል ዕድል መጉደል) መመልከት ይበቃል፡፡ የአዲስ አበባን ጉዳይ ስናነሳ እግረመንገዳችንን ብናጤነው የምለው ነገር አለኝ፡፡ ከላይ ስለ አዲስ አበባና አካባቢዋ የተጠቀሰው ጉድፍ እንዳለ ሆኖ፣ ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋ በግል የማየው ቅንነትና ትህትና፣ የለውጥ ቁርጠኝነትና የእድገት ትጋት እንዲሁም ከፍተኛ የአንድነት ስሜት ቀልቤን የሚስብ መሆኑን ላለመግለጽ አይቻለኝም፡፡ ገና ትግል የሚጠይቁ ብዙ ጉድለቶችና ጥፋቶች እንዳሉ ሆነው በነዚህ 21 ወራት በአዲስ አበባ የታዩና የተጀመሩ ለውጦችን ቆጠራ እናድርግ እንዴ? ከትምህርት ቤቶች ማሻሻያ በተለይም ከተማሪዎች ምገባና ዩኒፎርም እንጀምር ወይስ ለደካሞችና አረጋውያን ከተደረጉ ድጋፎች? ወይስ ልጆቻችንን ከጎዳና ከማንሳትና መልሶ ከማቋቋሙ ሥራ? እነዚህን የመረጥኩት በጣም ሰው-ሰው የሚሸቱኝ ጥረቶችና ውጤቶች ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ እንጂ … (አሁንም በነገራችን ላይ ሊቀመንበሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ጨምሮ ኢሕአዴግ ወይም ብልጽግና ፓርቲ በሕዝብ ባይመረጡም ሐገራችንን እስከ መጪው ምርጫ እንዲያሸጋግሩ ከመቀበል የተሻለ አማራጭና አስተዋይነት አለመኖሩን በመረዳት ብዙዎች ጥረታቸውን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን ዕውነታ የተቀበለ ወገን (ያልተቀበለን አይመለከትም!) የከንቲባ ታከለ ኡማን በሕዝብ ያለመመረጥ ሁኔታ እንደ ልዩ ነውርና በደል ቆጥሮ “አይንህን ላፈር” የሚልበት አመክንዮ ለኔ ግልጽ አይደለም፤ እንደገና ቢታይ፡፡) ወደ ዋና ጉዳያችን እንመለስ፤ ኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜውን የነውር ክብረወሰን ያስመዘገበችበት ከፍተኛ የሐገር ውስጥ የሕዝብ መፈናቀል፤ ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ጥቃት፣ ግድያና አካል ማጉደል፣ ዘረፋ፣ መሠረተ ልማቶችን የማጥፋትና የማስተጓጎል ሻጥር እየተፈጸመ ያለው፣ ዛሬ በለውጥ ሂደት ውስጥ በሚገኙት በሐገር መከላከያ ሠራዊት ወይም በፌዴራል ፖሊስ ወይም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት አይደለም፡፡ በማንነት ጥያቄ፣ በግጦሽ መሬት፣ በድንበር ክርክር፣ በወሰን ማስከበር፣ ሕገ ወጥ ግንባታን በመከላከል፣ በአስተዳደር መዋቅር ለውጥ ጥያቄ ወዘተ ሰበብ ልዩ ኃይሎችን፣ የዞን ፖሊሶችን የአካባቢ ሚሊሻዎችንና በኢመደበኛ አደረጃጀት ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በማሰማራት ዜጎችን የሚያሰቃዩት ሁሉም ባይባሉም የክልል መንግሥታት፣ የዞንና የወረዳ መስተዳድሮች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በወያኔ የውክልና ረብሻና ማተራመስ ምክንያት የባዕድ አጀንዳና የእሳት ማጥፋት ሥራ የበዛባቸው ሶማሌና አፋርን የመሰሉ የክልል መንግሥታት መኖራቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡
ሦስተኛ፡ ትናንትም ዛሬም የሰብዓዊ መብቶች ዋነኛ ረጋጭ ወያኔ መሆኑ፤
- “ባትዋጋ እንኳ በል እንገፍ እንከፍ፣ የመለስ ሤራ ትኋኑ ይርገፍ”
በኢትዮጵያ ዋነኛው የግድያና የሽብር ተዋናይ እናም የሰብዓዊ መብቶች ረጋጭ ትናንትም ወያኔ ነበር (ማለትም ከለውጡ በፊት በዋናው መንበር ላይ በነበረበት ጊዜ)፤ ዛሬም ዋነኛው የሰብዓዊ መብቶች ረጋጭ ወያኔ ነው (ማለትም በለውጡ ከዋናው መንበር በተባረረበት ጊዜም)፡፡ ወያኔ ዋናው መንበር ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ሁሉ ሰብዓዊ መብቶችን አያከብርም፣ አያስከብርም እንዲሁም ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ለማሟላት ፍጹም ዳተኛ ነበር፡፡ ወያኔ ትናንት ሰብዓዊ መብቶች ይረግጥ የነበረው በፌዴራል መንግሥት ቁመናውና አቅሙ ነበር፡፡ የተለየው ነገር፣ ዛሬ ወያኔ ጥሰቱን የሚፈጽመውና የሚያስፈጽመው በክልል መንግሥት ቁመናና እየደከመም በሚሄድ አቅም መሆኑ ነው፡፡
ወያኔ ሥልጣን ከመያዙ በፊት ያለውን ጊዜ እናቆየውና፣ ሥልጣን ከያዘበት 1983 ዓ.ም. ከቀን አንድ ጀምሮ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ይህ አገላለጽን ለማሳመር ያህል የተባለ ሳይሆን የዓይን እማኝ ዕውነት ነው፡፡ ግንቦት 21 1983 በአዲስ አበባ ማንም ሰው ከቤቱ (ከሠፈሩ) እንዳይወጣ ወያኔ ከልክሎ ነበር፡፡ ዕለቱ (21) በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ የቅድስት ማርያም በዓል የሚከበርበት ቀን ነበር፡፡ ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በክልከላው ምክንያት ከቤተክርስቲያን መቅረትን ሊቀበሉት እንዳልቻሉ ታይቷል፡፡ ብዙዎች ከቤተክርስቲያን መልስና ሌሎች ደግሞ አጋጣሚውን በመጠቀም በወያኔ ላይ እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ድረስ የአደባባይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የአራት ኪሎ፣ የፒያሳ፣ የመርካቶ፣ የልደታና የሰሜን ማዘጋጃ ወዘተ አካባቢ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምሕራን በልዩ ልዩ ቦታዎች ላይ በመገናኘት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ ወያኔ በመኪና ላይ የተደገነ መትረየስ አነጣጥሮ ሰልፈኛውን ከመከተል ውጭ የወሰደው እርምጃ አልነበረም፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ እየቀጠለና እየሰፋ በሄደ ጊዜ ግን የተወሰኑ ሰዎች በወያኔ ጥይት ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ በርካቶች በሰደፍና በዱላ ተደብድበው ተጎድተዋል፡፡ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን (መስቀል አደባባይ) አጠገብ ያለው ወንዝ ውስጥ የነበረው ነፍስ አድን ሩጫ ሊረሳ አይችልም!! ታዲያ ወያኔ በዚያው ምሽት የሬዲዮ ዕወጃው “የደርግ ኢሰፓ ሌቦችና ዱርዬዎች ለመረበሽ ሞክረው … ” ብሎ የስንቱን ጨዋ ዜጋ ግብርና ስም ጥላሸት ቀባ፡፡ ወያኔ ከማዕከላዊ የሥልጣን መንበሩ እንዳይመለስ አድርገው እያባረሩት ያሉትን ሰዎችና ብስጭቱን ለመግለጽ ዛሬም የተጠቀመበት ቃል ያኔ ሲመጣ የተጠቀመበትን ቃል ነው “ሌቦችና ዱርዬዎች” – አጋጣሚው አይገርምም!? (በ1983 ከቀን አንድ ጀምሮ የተደረገውን ትግልና የተከፈለውን መስዋዕትነት እዚህ ላይ ማስታወስ ሌላም ተጓዳኝ ጥቅም አለው፤ ይኸውም ወያኔ የተሸነፈውና የወደቀው ቄሮና (ፋኖ?) ብቻቸውን ከ2007/8 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ግብግብና መስዋዕትነት እንደሆነ ተደርጎ ዛሬ በ2012 ዓ.ም በጃዋርና ኩባንያው የሚለፈፈውን የታሪክና የውለታ ሽሚያ ለማስተካከልም ይረዳል)፡፡
ወያኔ ዛሬም ለውጡ ስር እንዳይሰድና ለመቀልበስም አጀንዳ ፈጥሮ ከመስጠትና የሌሎችንም አጀንዳ ከመጥለፍ ጀምሮ የተገኘውን ሁሉ ክፍተት፣ አጋጣሚና ሰበብ በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሁከት፣ ሽብርና ትርምስ እንዲሰፍን እየሠራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት የለውጥ ጅማሮ አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከታዩ ሤራዎች፣ ሁከትና ብጥብጦች እነዚህንም ተከትለው ከተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች መካከል ወያኔ ያላቀነባበራቸውን፣ ያልመራቸውን ወይም ያልደገፋቸውን ወይም በሆነ ደረጃና መልክ ያልተሳተፈባቸውን ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ምንም እንኳን አሁን እየተመናመነና እየተዳከመ ቢመጣም ወያኔ ቢያንስ ለ30 ዓመታት የዘረፈው ኃብት፣ በአድልዎ የፈጠረው የሚሊተሪ፣ የደህንነትና የጥገኛ ነጋዴ አቅምና ትስስር፣ በየክልሉና ጎጡ ያሰማራቸውና የሚነዳቸው የጥቅምና የስጋት ተጋሪዎቹ በይበልጥም በሕገመንግሥት፣ በፖሊሲ፣ በሕግ፣ በመዋቅርና በአሠራር ተደግፎ ያሰፈነው ሁለገብ ብልሽት የፈጸመውን ለመፈጸም ክፉ ወረትና አቅም እንደሆኑት ማስተዋል አይከብድም፡፡ በዚህ ልክ ከቡራዩ ጭፍጨፋ፣ እስከ ሐዋሳና የሲዳማ ዞን ጭፍጨፋ፣ ከጃዋር ትንኮሳዎችና ጭፍጨፋ እስከ አማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ቀውስ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉልና በአፋር ክልሎች ለበርካታ ወራት እስከታዩት ትርምሶች ወዘተ ድረስ የወያኔ “ረጅም እጆች” ከጀርባቸው መኖራቸውን ማን ይጠራጠራል? ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሐገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚስተዋለው ብሔር ተኮር መገፋፋትና ሁከት የወያኔ የእጅና የኪስ ሥራ እንዲሁም “የፌዴራሊስት” ነን ባይ አጋሮቹና ተላላኪዎቹ የቤት ሥራ አይደለምን?
ዛሬ በወያኔና በመሰል ጸረ ዴሞክራሲና ጸረ አንድነት ኃይሎች የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣ (Abuse)፣ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ከሚፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት (Violation) እጅግ ልቆ እየተገኘ ነው፡፡ እንዲያውም በድፍረት ለማስቀመጥ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የዶክተር ዓቢይ መንግሥት በይበልጥ ሊወቀሰ የሚችለውና የሚገባው፣ ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር – በመጣስ (Respect) ጉድለት አይደለም፤ ይልቁንም ዜጎችንና ሰዎችን በነወያኔ፣ በክልል መንግሥታት፣ በዞንና በወረዳ መስተዳድሮችና በጸጥታ አካሎቻቸው፣ በነጃዋርና ሽኔ፣ በየቦታው በሚርመሰመሱ የብሔርና የኃይማኖት ጽንፈኞች እንዲሁም ኢመደበኛ በሆኑ አደረጃጀቶችና መንጋዎች ከሚፈጸሙ ጥሰቶች መጠበቅ (protect) ባለመቻሉ ነው፡፡
ወያኔ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ጨምሮ ሁሉንም የክፋትና የጥፋት ድርጊቱን የሚፈጽመውና የሚያስፈጽመው ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ፣ የውስጥና የውጭ (የባዕድ ሐገርና ሜዲያ) የቅርብና የሩቅ (ዲያስፖራ) አጋሮች፣ የጥቅም ተካፋዮችና ተላላኪዎችን ሁሉ አስተባብሮና ተጠቅሞ ነው፡፡ እዚህ ላይ አየለ ጫሚሶና ትዕግሥቱ አወልን የመሰሉትን የፖለቲካ መካኖች ንቀን ብንተዋቸው እንኳ ለውጡን ለመጥለፍና ኢትዮጵያን ለመበታተን እንቅልፍ ያጡትን እነ ጃዋር መሐመድን፣ በቀለ ገርባን፣ ሕዝቅኤል ጋቢሳና፣ ጸጋዬ አራርሳን የመሰሉ የወያኔ የስትራቴጂ አጋሮችን መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እነዚህና ከላይ የተመለከትናቸው ጸረ ለውጥና ጸረ አንድነት ኃይሎች እየፈጠሩት ያለው ሽርክና (“የፌዴራሊስቶች ህብረት”)፣ የለውጡ ጅማሮና ሂደት ውስብስና ፈታኝ ሆኖ ለተወሰኑ ጊዜያት እንደሚቀጥል ያመላክተናል፡፡
“ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል”
መደበኛ ስልታቸው መሆኑን በውል ለተረዱ ንቁዎች እምብዛም ባያስገርምም፣ እነዚህ ሁሉ ሻጥረኞች ራሳቸው ባቀነባበሩትና ወጪውን በሚሸፍኑት ሴራ ዜጎችን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን እየዘረፉና እያቃጠሉ (ሰብዓዊ መብቶችን እየጣሱና እያስጣሱ) መልሰው ለእኩይ ዓላማቸው ባደራጇቸው ሕገወጥ ስብስቦች፣ መደበኛና የማሕበራዊ ሜዲያ አውታሮች አማካኝነት “አዲሱ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶች ይጥሳል፣ አያስከብርም (ዜጎችን አይጠብቅም)፣ ሐገሪቱ ልትበተን ነው” እያሉ የውሸት እንባ ያነባሉ፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉ፡፡ ዋናው መልእክታቸው “እኛ እንሻላችኋለን” ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማመዛዘንና የመምረጥ አቅም በዚህ ደረጃ መናቃቸው የሚያሳየው ምንም ዓይነት ልጓም እንደሌላቸው ነው፡፡ በጎ ሰው የፈሪሃ እግዚአብሔር፣ የኅሊና፣ የሕግ እና የሰው-ይሉኝታ ልጓሞች (ሁሉም ወይም በከፊል) ይኖሩታል፡፡ እነዚህ ባዶ – ቀፎ ሆነው ቀርተዋል፡፡
ወያኔ የሚነዳው “የፌዴራሊሰቶች” ሕብረት ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ኢትዮጵያ ሤራ ይከሽፋል!!
ወያኔ የሚመራቸው የጥላቻና የጥፋት ኃይሎች በኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ ጥረት ላይ በየጊዜው እየፈጠሩት ያለው ሻጥርና እንቅፋት በእርግጠኛነት የሚታለፍ ነው፡፡ ይህንን ጽኑ ዕምነት የሚደግፉ ዋና ዋና ምክንያቶችን እንመልከት፡፡
- አንደኛ፡ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ቀስ በቀስ ተቋማዊ ቁመና እየያዘ መምጣቱ ለመንግሥት የተሻለ አቅምና ተአማኒነት እያስገኘ፣ ለለውጥ ፈላጊው ሕዝብ ተስፋ እየሰጠ ለወያኔ ግን ከባድ ፈተና እየሆነ በመምጣት ላይ ነው፤ በተለይም የኢሕአዴግ መክሰምና የስምንቱ ክልሎች ፓርቲዎች ውህደት (ብልጽግና ፓርቲን መፍጠር) ትልቅ ስኬት ነው፤ የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር ወያኔን ከምንጊዜውም በላይ ያጥወለወለውና ያንገዳገደው ከባድ ምት ነው፡፡ ወያኔ እውን እንዳይሆን ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ካሻጠረባቸው የገዢው ፓርቲ ዕቅዶች መካከል ዋነኛው ይህ የብልጽግና ፓርቲ ስኬት ይመስለኛል፡፡ የወያኔን ኮማ ውስጥ መግባት ያበሰረ (ለነርሱ ያረዳ) ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደገዢም ሆነ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ በብሔርና በዜግነት መብቶች መካከል ሚዛን የጠበቀ መርሐግብር ይዞ መምጣቱ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የእኩል ዕድልና የእኩል ተጠቃሚነት ተስፋን አሳይቷል፡፡
- ሁለተኛ፡ እንደ ኢዜማ፣ አረና፣ ትዴፓና አብን የመሰሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች የተሻለ ቁመና እየያዙ መምጣትም ወያኔን አየር እያሳጡ ከመጡ ስኬቶች ውስጥ ይደመራል፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሠረታቸውና ቁርጠኝነታቸው እየሰፋና እያደገ በመሄድ ላይ ነው፡፡
- ባለው ልዩ ፋይዳ ምክንያት እዚህ ላይ ለብቻውና በድጋሚም ሊገለጽ የሚገባው፣ ለወያኔና አጋሮቹ መድከምና መሸነፍ እጅግ የላቀ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ትልቅ ዕድል አለ፤ ይኸውም የእነ አብርሐ ደስታና የነአምዶም ገ/ስላሴ አረና ፓርቲ፣ የነ አረጋዊ በርሔ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እንዲሁም በሕወሐት ውስጥ የሚገኙ ለውጥ ፈላጊ አካላት፣ ገብረመድኅን አርአያን የመሰሉ ብርቱ ግለሰቦች በጋራም ሆነ በተናጠል ሆነው የአንድነት፣ እኩልነትና ሰላም ፈላጊውን የትግራይን ሕዝብ አስተባብረው የሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡ ይህ ትግላቸው ግን እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እሳት የሚሆንባቸው ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ወቅት ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለኢትዮጵያ አንድነት በጽናት እየታገሉ ላሉ የትግራይ ወንድምና እህቶቻችን ልዩ ክብር አለኝ፡፡ መንግሥትም ሆነ መላ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም የበለጠ ዛሬ ከነዚህ ወንድምና እህቶቻችን ጎን ልንቆምና በምንችለው ሁሉ ከልባችን ልንደግፋቸው ይገባል፡፡
- ሦስተኛ፡ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ልዩ ልዩ ተዋናዮች (None State Actors) በየዘርፉ የጀመሩት የብሔራዊ መግባባት ማስፈኛ ጥረትም ለወያኔና ለ”ፌዴራሊስት” ሕብረቱ መርዶ ነው፡፡ ምሑራን፣ ባለሐብቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት መሪዎችና አባቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሜዲያ ሰዎችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ታዋቂ ዜጎች መድረክ ሲፈጥሩና ጸረ ሰላምና ጸረ አንድነት ኃይሎችን አደብ ለማስገዛት ሲመክሩ እያየን ነው፡፡ ይበል፣ ይጠንክር ይቀጥል የሚያሰኝ ነው፡፡
- አራተኛ፡ ከበረሐ የተመለሰው፣ ከእስርና ከስደት ነጻ የወጣው እንዲሁም ከተያዘበት የባርነት ቀንበር የተገላገለውና ተስፋ የሰነቀው ሰፊ ኃይል በአጠቃላይ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንዛቤና ፍላጎት የደረሰበት ደረጃ ወደ ኋላ መመለስን ፈጽሞ የሚፈቅድ አይደለም፡፡
- አምስተኛ፡ ከነዚህ በተጨማሪ የወያኔን ታላቅ ሤራ ባጭር የሚያስቀረው ሌላም ዕድል አለ፤ ይኸውም ዛሬ ወያኔ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የሚፈጽመውና የሚያስፈጽመው እየደከመ በሚሄድ አቅም መሆኑ ነው፡፡ ቀንደኞቹ የወያኔ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተዋናዮች – የደህንነት ኃላፊዎቹ፣ ጄኔራል-ኮሎኔሎቹ፣ ነጋዴዎቹ፣ የቢሮክራሲ ቁንጮዎቹ፣ የሤራ ንድፈ ሀሳብ አመንጪዎቹ፣ የፕሮፓጋንዳ መሐንዲሶቹ ዛሬ ወይ በአፈር ውስጥ፣ ወይ በእስር ቤት፣ ወይ በመቀሌ ሆቴል ቤት የቁም እሥር፣ ወይ አምልጠው በስደት ሆነው አለያም አድፍጠው ከአቅም በታች በመጫወት ላይ ናቸው፤ የመለስን የሤራ ጋሻ አውርደው እንገፍ የሚሉት እንከፎች እየተመናመኑ ነው፡፡ ዕድሜ፣ ተንኮልና ዕርግማን-አመጣሽ በሽታ እንዲሁም የትናንት ኃጢአትንና የዛሬ የለውጥ ዕውነትን ላለማየትና ላለመቀበል የሚደበቁበት አልኮልም ቢሆን በሙሉ አቅም አያሠሩዋቸውም፡፡
ስለዚህ ወያኔና ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነው “የፌዴራሊሰቶች” ሕብረት መሸነፋቸው የማይቀር ነገር ነው!!
ለማጠቃለል፤ በተለይ የኢህአዴግ የለውጥ ኃይሎች ወደአመራር ከመጡ ወዲህ በዜጎች ህይወት፣ አካልና ንብረት፣ ተስፋና ህልም ላይ እጅግ አስከፊ ጥቃትና ውድመት በተደጋጋሚ ሲፈጸም በከፍተኛ ሐዘንና ቁጭት እየተመለከትን ነው፡፡ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመው እስካሁንም በሕግ ያልተጠየቁ አካላት በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ዜጎች በለውጡና በፌዴራል መንግሥትም ላይ ያላቸውን እምነት እየሸረሸረው ይገኛል፡፡ መንግሥት ችግሮችና ቀውሶችን በለመደውና ባላዋጣው አሮጌ መንገድ ከመያዝና ውጤት ከመጠበቅ ይልቅ በአዲስ፣ በተሻለና በሚሠራ ዘዴ ለማስተናገድ በሚል ትዕግሥት እያሳየ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ትልልቅ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድም አዋጪነታቸውን ወይም አክሳሪነታቸውን፣ የጊዜውን ትክክለኛነት፣ የራሱንና የችግር ፈጣሪዎችን የኃይል ሚዛን የሕዝቡንም አእምሮአዊና ስነልቦናዊ ዝግጅት በመፈተሽ ብዙ ጥረትና ጊዜ እየወሰደበት ያለም ይመስላል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ በፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዛሬ ያልተጠየቁ አካላት ነገ መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸው ሰዎች ያለይቅርታና ምሕረት ፍርዳቸውን ይቀበላሉ፡፡ ይህ እውን እንዲሆን፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲና አንድነት ያልን ሁሉ እንተማመን፣ እንተባበር፡፡ አንዳችን ለሌላችን የግድ እናስፈልጋለን፡፡ ልባችንን፣ ቀልባችንን፣ አቅምና ኃብታችንን ሁሉ እርስ በርስ በመገፋፋትና የለውጡን ኃይል በመግፋት ላይ አናባክን፡፡ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ የማንሞላውን የሥልጣን ክፍተት እንዳንፈጥርና ተያይዘን ገደል እንዳንገባ እንጠንቀቅ፡፡ የምንወስደው አቋምና እርምጃ ለጸረ ዴሞክራሲና ጸረ አንድነት ኃይሎች ማንሰራራት በርና ዕድል እንዳይከፍት ልዩ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ፣ ጥረታችንን ይባርክ!