December 28, 2019
ጠገናው ጎሹ
የዚህ አስተያየቴ ጭብጥ ፦
ሀ) ከኢህአዴግ የተገኙና የለውጥ (ለውጥ?) መሪዎች እያልን የምንጠራቸው ፖለቲከኞች ለሩብ ምዕተ ዓመት ስንሰማው የኖርነው በግብዝነት፣ በትእቢት፣ በሞራልና ሥነ ምግባር አልባነት፣ ሃላፊነት በጎደለው የፈጠራ ትርክት ልክፍት ፣ በጥላቻና ቂም አራጋቢነት ፣ በጋራ ተመካክረን የጋራ ምቹ መንገድ እንገንባ ሳይሆን “እኛ ያልነውንና የሆነውን ካልሆናችሁ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” በሚል የፖለቲካ ቋንቋ (ዲስኩር) የተበከለው አካሄድ ግዙፍና መሪር ዋጋ ያስከፈለን መሆኑንና ለእነሱም የተሃድሶ (የጥገና) ለውጥ እንደማይበጃቸው ተገንዝበው ለማስተካከል ያደርጉት ሙከራ ጨርሶ ፋይዳ የለውም የሚል አይደለም።
ለ) አንድና ሁለት እያልን የምንጠቅሳቸው የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች (መሪዎች) የህወሃትን የበላይነት በማስወገዱ ሂደትም ሆነ መንበረ ሥልጣኑ ላይ ከወጡ በኋላ አወንታዊ እውቅና የሚገባቸው እርምጃዎች አልታዩም የሚል ደምሳሳ ምልከታም አይደለም።
ታዲያ ከዚህ የተለየ ምን እያልኩ እንደሆነ ግልፅ ለማድረግ እንደሚከተለው ልቀጥል፤
አያሌ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ንፁሃን ዜጎች ለሩብ ምዕተ ዓመት ኢሰብአዊ የቁም ስቃይ ከመቀበል ጀምሮ ከቶውንም ተመን የማይገኝለትን የህይወት ዋጋ የከፈሉባቸው መሠረታዊ ጣምራ ምክንያቶች ሀ) ከላይ ከጭንቅላቱ እስከ ታች እግርና ጥፍሩ ለመግለፅ በሚያስቸግር አኳኋን ትውልድን በእውንና በቁም የመግደል ወንጀል የተጨመላለቀውን ሥርዓተ ኢህአዴግ ከነሰንኮፉ (ሙሉ በሙሉ) ማስወገድና አሳዛኝ ግን አስተማሪ ወደ ሆነ የታሪክ ሙዚየም ማውረድ ለ) ከፖለቲካ ወለድ ወይም ከሌላ አገርንና ህዝብን ከሚጎዳ ሴረኛነትና ወንጀለኛነት በስተቀር የኢህአዴግን ስም እንደያዙ ወይም ስሙን ቀይረው መሳተፍ የሚፈልጉትን ኢህአዴጋውያንን ጨምሮ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ ያገባኛል የሚልን ሁሉ በሚያሳትፍ ሁኔታ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ሽግግርንና ምሥረታን እውን ማድረግ ነበሩ ። አሁንም/ ዛሬም የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው።
እናም ከላይ ሀ እና ለ ብዬ የጠቀስኳቸውን መሠረታዊ ለውጥ እውን ለማድረግ የሚያግዙ አወንታዊ ዲስኩሮችንና እርምጃዎችን የመከረኛውን ህዝብ ቀልብ ይስባሉ በሚባሉ የአደረጃጀት ቅርፅ እና የስም ስያሜ (ብልፅግና) በማላበስ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን ፈፅሞ እውን ማድረግ አይቻልም ነው የአስተያየቴ ማጠንጠኛ ። አዎ! በሩብ ምዕተ ዓመት ታጥቦ የማይጠራ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨመላቀውን የኢህአዴግ ሥርዓት በተሃድሶ ስም እንደ ሥርዓት ለማስቀጠል ይቻላል ማለት በዴሞክራሲ መቀለድ ይሆናል ነው የአስተያየቴ ማእከላይ መከራከሪያ ነጥብ።
መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥን እውን ለማድረግ አልሳካልን ብሎ ዘመናትን ካስቆጠርንባቸውና አሁንም አዙሪቱን ሰብሮ መውጣት ካልቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ በመሬት ላይ ያለውን መሪር ሃቅ በምክንያታዊነትና ውጤታማ በሆነ ተግባራዊነት ሳይሆን ከስሜታዊነት በሚመነጭ የፖለቲካ ትኩሳት የምናስተናግድበት ክፉ አባዜ ነው። አዎ! አሁንም ዘመን ጠገብና ገና መቆሚያ ልናበጅለት ካልቻልነው እጅግ ክፉ የፖለቲካ አዙሪት (political vicious cycle) ሰብሮ ለመውጣት የምር ትግል ውስጥ አይደለንምና ልጓም ከሌለው የስሜታዊነት ፖለቲካ ፈረስ ላይ ወርደን መሬት ላይ ያለውን መሪር ሃቅ በሚመጥን አኳኋን መራመድ ይኖርብናል።
እጅግ አሰቃቂ በሆነ የሩብ ምዕተ ዓመት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ የተበከለውን የሥርዓተ ኢህአዴግ የፖለቲካ ምእራፍ አስተካክለን በእራሳቸው በኢህአዴግ/በብልፅግና ፖለቲከኞች አመራር ሰጭነት መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን እናደርጋለን ማለት ጨርሶ የሚሆን አይደለም። እንደ ለመድነው በስሜታዊነት እየተነዳን መልሰንና መላልሰን በመውደቁ አዙሪት መቀጠል ካልፈለግን በስተቀር።
ከዚህ ክፉ አዙሪት በአስተማማኝነት ለመውጣት በንፁሃን ሰቆቃና ደም የተበከለው ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ምዕራፍ በንፁህ ህሊናዎችና እጆች በሚዘጋጅ አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ (ፍኖተ ካርታ) መተካት ይኖርበታል ። ይህ አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ ከሰብአዊ ፍጡር በታች የሚያውልን እኩይ የፖለቲካ ሥርዓትና ከእርሱም ጋር የተያያዘውን ባህል/ ወግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ መጀመር ይኖርበታል። ይህን እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዘንድ ኢህአዴጎችን ጨምሮ የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚልንና ለዚህም የሚችለውን በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ የሆነን ወገን ሁሉ ለለማሳተፍ የሚችል መድረክ (plattform) ማመቻቸትን ግድ ይላል። ይህ አካሂድ ነው በፖለቲከኞች እፁብ ድንቅ ዲስኩርና በአንዳንድ አወንታዊና ለለውጥ ሊያግዙ በሚችሉ እርምጃዎችና ክስተቶች ልጓም በሌለው የስሜታዊነት ፈረስ ከመጋለብ አውጥቶ በመሬት ላይ ላለው እኛነታችን ትክክለኛና መሠረታዊ መፍትሄ እንድናበጅ የሚያስችለን ።
አዎ! ለዘመናት ከዘለቅንበት የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ አዙሪት ከምር መላቀቅ ካለብን ከዚህ ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ ፈፅሞ የለም። አይኖርምም። ህሊናችን “የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴጋዊያን የሸፍጥ ተሃድሶ (hypocritical and disingenuous reform) ሊያገኘው የሚችለው ፍርፋሪ ምን አነሰው?” የሚል እጅግ የወረደ አስተሳሰብ ሰለባ ካላደረግነው በስተቀር ለዘመናት ከዘለቅንበት የመከራና የሁለንተናዊ ውርደት ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተላቅቀን ታሪክን በአስተማሪነቱ ለመጠቀም ፣ የዛሬውን በአዲስ ሥርዓት አዋላጅነቱ ተቀብለን ለማጎልበት ፣ እና የነገውን ደግሞ ከዛሬው በላቀ ብሩህነት ለመቀበል የሚያስችለን ትክክለኛ መውጫ መንገዱ ይኸው ብቻ ነው።
ይህ አይነቱ የእራስ ነፃነትን፣ ፍትህን፣ ክብርን፣ ኩራትን ፣ ብልፅግናን ወዘተ በእራስ የአርበኝነት ወኔ (with a strong sensese of patriotism) እውን አድርጎ በዓለም ህብረተሰብ ፊት ያለአንዳች ዝቅተኝነት ስሜት መቆም ስንችል ብቻ ነው እኛ ሳንጠይቅ ሽልማቱም ሆነ አድናቆቱ ፈልጎን የሚመጣው ።
ስሜታዊነቱ ፋታ ሳይሰጠን ቀርቶ ልብ ባለማለታችን እንጅ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ሃዲድን እየሳትን የመንሸራተት አደጋ ሊገጥመን እንደሚችል የለውጥ መሪዎች ወይም ሐዋርያት ወይም ሙሴዎች ወይም ከሰማይ የተላኩ ሥጋ ለበስ መላእክት እያልን ያሞካሸናቸውን የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች ከተቀበልንበት ጊዜና አኳኋናችን ጀምሮ ግልፅ ነበር ።
“ጠባችን ከበከተውና ከከረፋው ሥርዓተ ኢህአዴግ ጋር እንጅ በጋራ መስዋእትነትና አብሮ ከመኖር በላይ በተቀላቀለ መወላለድ ከተገመዱት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር ባለመሆኑ ጥያቄያቻችንም የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ጥያቄዎች ናቸው” የሚለው የህዝብ ጥያቄ በኢህአዴግ ፖለቲከኞች መሪነት ወይም ዋና ተዋናይነት ትክክለኛና ዘላቂ ምላሽ ያገኛል የሚል ልክ የሌለው ስሜታዊነት (ቅዠት) ውስጥ የገባን እለት ነው የፖለቲካውን ማዕከላዊ አውድ በሸፍጥ ለተበከለው ለኢህአዴየጋዊ የፖለቲካ ጨዋታ ለቀን በሚያሳዝን ሁኔታ እራሳችንን በአጃቢነት/በተለጣፊነት ያገኘነው።
ይህን ጊዜያዊና እጅግ ግልብ ስሜታችንን አሳምረው የሚያውቁት የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞችም ለዚሁ ስሜታችን የሚስማማ ድንቅ የፖለቲካ ድርሰት እያደረሱና እያቀነባበሩ በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩና በየአጋጣሚው በሰላ አንደበት ሲያሰሙን (ሲደሰኩሩልን) ሥነ ልቦናችንን አኮስምነን (አጎሳቁለን) “እናንተ ከሌላችሁ አገር እንደ ሸክላ ትፈረካከሳለች ፤ ህዝቧም ለምፅዓተ ፍዳ ይዳረጋል” የሚል እጅግ አሳፋሪ የፖለቲካ መዝሙር እየዘመርን ተቀበልናቸው ።
እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ሊያደርግና ሊያስደርግ የሚችል የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) እና ማህበራዊ ንቅናቄ በፍጠርና በማጠናከር የኢህአዴጋውያንን “እኛ ከሌለን ምፅዓተ ፍዳ ይሆናል” የሚል እኩይና ሸፍጠኛ ትንቢት (ትርክት) ፉርሽ ማድረግ ተስኖት የግለሰብ ፖለቲከኞችንና መሪዎችን ስም በተለምዶ ሸምድዶ “እገሌ/እገሊት ከሌለ/ከሌለች አለቀልን” በሚል እጅግ አሳፋሪ የስሜታዊነት ፖለቲካ የሚናጥ (የሚረበሽ) ትውልድ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከተከፈለበት መሠረታዊ ጥያቄ እየተንሸራተተ ሲያለቅስና ሲላቀስ ማየት ያሳዝን እንደሆነ እንጅ ከቶ የሚገርም አይሆንም።
የተደጋገመውንና በእጅጉ አሳፋሪ የሆነውን የትውልድ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ/ሥነ ምግባራዊ ፣ መንፈሳዊ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገራዊ ማንነት ቀውስ በሩብ ምዕተ ዓመት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል (በንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና ደም ) በተዘፈቀው ሥርዓተ አሁንም ቅርፅና ስም እየቀየረ እንደ ሥርዓት በቀጠለው የኢህአዴግ ተሃድሶ ፈፅሞ እንደማይወገድ አውቆ የሚበጀውን ከማድረግ ይልቅ ከክስተቶች ጋር በስሜት የሚወድቅና የሚነሳ ትውልድ ዴሞክራሲን በቃልና በምኞት እንጅ በእውን ይረደዋል ማለት በእጅጉ ያስቸግራል ።
ለዚህም ነው ሽፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞችና በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ካድሬዎቻቸው ግልብ ስሜቱን በሚኮረኩሩ ዴስኩሮቻቸው እያደነቆሩ እና እዚያና እዚህ አስመዘገብን በሚሏቸው ለለውጥ አጋዥ ሊሆኑ በሚችሉ አወንታዊ እርምጃዎች እያደነዘዙ በጅምላ እንዲያስብና ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄው እየተንሸራተተ የሸፍጠኛና ሴረኛ የተሃድሶ ፖለቲካቸው ሰለባ እያደረጉት የቀጠሉት ።
የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን ከማድረግ ጥያቄ እየተንሸራተትን የተቸገርነው በሂሳዊ አስተሳሰብና በመርህ (principled and critical thinking) ላይ የተመሠረተ ድጋፍ በመስጠትና ስሜትን በሚኮረኩር የፖለቲከኞች ፕሮፓጋንዳ (ዲስኩር) መነዳት መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ስለተሳነን ወይም ስለተደበላለቀብን ነውና ቆም ብለን እራሳችን መመርመር ይኖርብናል ።
ምን? ለምን? እንዴት ?ከየት ወደ የት? ከመቼ እስከመቼ? በምንና በማን? ለነማን? ወዘተ የሚሉ የአንድን ጉዳይ ዓላማ ፣ አነሳስ፣ አካድሄድና መዳረሻ ለማወቅ የምንጠቀምባቸውን መጠይቃዊ ቃላት ከፖለቲካ አውዳችን ውጭ ያደረግናቸው ይመስላል። ኢህአዴጋውያን ለሩብ ምዕተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቀው የዘለቁበት የፖለቲካ ሥርዓት ህገ መንግሥት ተብየውን ጨምሮ መሠረታዊ ምሰሶዎቹ ጨርሶ ባልተነኩበት ሁኔታ በቅርፅና በስያሜ ቆንጅዬ አስመስሎ ለዚያው ለፈረደበት “ነፃና ትክክለኛ ምርጫ” ለማዘጋጀት(ለማቅረብ) የሚረዷቸውን የፖለቲካ ትእይንቶች (political show ) አጉልተው በማሳየትና በማስጮህ ላይ መሆናቸው የቀን ተቀን እውነታ ነው። መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እፈልጋለሁ የሚል ትውልድ በስሜታዊነት ማዕበል እየተናጠ እኩይና ሸፍጠኛ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ ሆኖ ከማየት የባሰ ውድቀት የለም።
በእጅጉ ልብ የሚሰብረው ደግሞ ከአብዛኛው ምሁራን ወገኖቻችን የምንታዘበው ይህንኑ እጅግ አስቀያሚ ውድቀት ወይም ቀውስ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ፖለቲከኞችም ይህን አሳምረው ስለሚያውቁ የምር የሆነውን የጠይቁንና እንጠይቃችሁ ወይም የእንጠይቃችሁና ተጠየቁ (የእንጠያየቅ ) የፖለቲካ አውድን (መድረክን) ጨርሶ አይደፍሩትም። እንዲያውም የዚህ አይነት መድረክ ይመቻች ዘንድ በነፃነትና በፍትህ የአርበኝነት ወኔ የሚጠይቁ ዜጎችንና ስብስቦችን አጥብቀው ስለሚፈሩ ሰንካላ ሰበብ እየፈበርኩ ማፈን ነው የሚቀናቸው።
በርካታ ግለሰቦችና የተቀዋሚ ተብየ ድርጅቶች መሪዎች በአድርባይነት (በልክክስነት) ወይም “ከለውጥ ሐዋርያት” የተሃድሶ ፍርፋሪ ተጠቃሚ እንሆናለን በሚል ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ እየዳከሩ መሆኑ የእለት ተእለት ግልፅ እውነት ነው።
ከዚህ በተፃራሪ መሠረታዊ የሰብአዊ መብት መከበር እውን ሊሆን ከሚችልበት መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አስፈላጊነት ጋር በሚያስገርምና በእጅጉ በሚያበረታታ አቋም ፀንተው የቆሙትን እስክንድር ነጋንና ባልደረቦቹን በመልካም አርአያነት መጥቀስ ቢያንስ እንጅ የሚበዛ አይሆንም ።
ለዘመናት በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ የነበረው ሥርዓተ ኢህአዴግ መሠረታዊ መዳላድሎቹ ጨርሶ ባልተነኩበት ሁኔታ ከራሱ የወጡ የለውጥ አራማጅ እያልን የምንጠራቸው ፖለቲከኞች ቅርፅና ስም እየቀየሩ ትውልድን ግራ በሚያጋቡበት በዚህ ወቅት በእውነት ቃሉ ፀንቶ የቆመን መልካም ዜጋ ከማየት የበለጠ የሚያበረታታ ጉዳይ የለም።
ንፁሃን ዜጎች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲጨፈጨፉና ቤተ እምነቶች እስከ አገልጋዮቻቸው በእሳት እንዲጋዩ ምክንያት የሆነው በሌሊት “እቤቴ ድረስ መጥተው ሊያፍኑኝ ነውና በአስቸኳይ ተነሱና አንድ ነገር አድርጉ ” በማለት ምክንያታዊነትን ጨርሶ ግምት ውስጥ በላስገባና በጎሳ/በዘውግ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላሰለጠነውና ላደራጀው የቄሮ ስብስብ በአስቸኳይ መልክት ጥሪ ያደረገው ጀዋር መሃመድ መሆኑ ምስክር ቁጠሩ የሚያሰኝ አይደለም ። ይሁንና እንኳን አግባብ ባለው ህግ ቀርቦ እንዲጠየቅ ማድረግ ቀርቶ አጃቢ አስመድቦ የሚንከባከብና አባ ገዳዎችን አኩራፊውን ጠይቁልኝ የሚልና ትልቁንና አሳሳቢውን አገራዊ ፈተና የመንደር ወይም የጎረቤት ጠብ የሚያስመስል ጠቅላይ ሚኒስትርን “ለሰላም ወይም ነገር ላለማባባስ ብሎ ነው” የሚል እጅግ ስንካላና የወረደ መከራከሪያ ማላዘን ከቶም ስሜት የሚሰጥ አይደለም።
በተቃራኒው ግን በጋዜጠኛና የሰብአዊ ተሟጋች እስክንድር ነጋና በባልደረቦቹ የተቋቋመው የአ.አ ባልደራስ ም/ቤት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ “ወደ ጦርነት እንባለን” መባሉን ፣ንፁሃን የምክር ቤቱ አባላትን በአሸባሪነት በመወንጀል በአካልና በመንፈስ አጎሳቁሎ እኔን ያየህ ተቀጣ ለማሰኘት መሞከሩን ፣ መንግሥት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ባልደራሱ በትንሿ ጽ/ቤቱም እንኳ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ በጀዋር መሃመድ ቄሮዎች ሲያውኩት ለምን ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ተባባሪ የተሆነበትን ሁኔታ ከምር ልብ ለሚል ቅንና ነፃነት ናፋቂ የአገሬ ሰው የህሊና ህመሙ በእጅጉ ከባድና ፈታኝ ቢሆንበት አይገርምም።
ጊዜና ተጨባጩ ሁኔታ ያቀረቡልንን መልካም አጋጣሚ ልጓም በሌለውና እጅግ ግልብ በሆነ ስሜታዊነት ለሚነዱን ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች አሳልፈን እየሰጠን ለዘመናት ልክ በሌለው የመከራና የውርደት ሥርዓት ሥር የኖርንበት እኛናታችን አሁንም ትምህርት አልሆነልን ብሎ አስከፊው የፖለቲካ ታሪካችን እራሱን እዲደግም ከማድረግ ፈተና ውስጥ እንገኛለን ።
የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ መርህና ተልእኮ አንሸራተትም የሚሉ የነፃነትና የፍትህ አርበኞች ተጋድሎ እያባነነ ባቃዣቸው ቁጥር ከቶ የማይፈፅሙት ሸፍጥና ሴራ አልነበረም። አሁንም የለም ።ወደ ፊትም አይኖርም። እንግዲህ ይህ አይነት የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ባለበት መሪር ሃቅ ውስጥ ነው ከመሠረታዊው የዴሞክራሲ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እየተንሸራተትን በልጓም አልባ የስሜታዊነት ፈረስ ሽምጥ የምንጋልበው።
በሚከተሉት ዋቢ ነጥቦች ይበልጥ ግልፅ ልሁን ፦
- የኦህዴድ/ኦዴፓ ፖለቲከኞች ከአጃቢነት/ከአሽከርነት ደረጃ ለማለፍ የፖለቲካና የሞራል ወኔው አልጠጋቸው ያሉትን በተለይም የብአዴን/የአዴፓ ፖለቲከኞች በደጀንነት በማሰለፍ የህወሃትን የበላይነት አስወግደው “ተረኝነቱ ይገባናል” በሚል እጅግ አስቀያሚና ለዚህ ዘመን ጨርሶ የማይመጥን የፖለቲካ ጨዋታ በመጫወት ላይ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ብዙ ወራት ተቆጠሩ ። “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሱሳችን ነውና ለበለጠ ገናናነቱ የማንከፍለው ዋጋ አይኖርም” በሚል የሸፍጥ ፖለቲካ ዲስኩርና ተውኔት ብዙሃኑን የአገሬ ህዝብ ልጓም የሌለው የስሜታዊነት ፈረስ እያስጋለቡ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እንዲንሸራት አድርገው የሸፍጥ ተሃድሷቸው ሰለባ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርጉት ጥረት ቢሳካላቸው የሚያሳዝን እንጅ ከቶ የሚገርም አይሆነም።
የአገሬ ህዝብ ልክ በሌለው ድህነት ውስጥ እየተጠበሰ በሚከፍለው ግብር ተማርኩና ተመራመርኩ ወይም እየተማርኩና እየተመራመርኩ ነው የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞችን ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩሮችንና አንዳንድ አወንታዊ ክስተቶችን ጠንካራና ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አቀራረብና አስተሳሰብ በመግራት የህዝብ መሠረታዊ የለውጥ ጥያቄ መነሻና መዳረሻ ፈሩን እንዳይለቅ ለማድረግ አልተቻለውም ። ከዚህ ይልቅ የትምህርትን የችግር መፍቻ መሣሪያነት በሚያኮሰምን አኳኋን የለውጥ መሪዎች የምንላቸውን ከማድነቅ አልፎ ወደ ማምለክ ነው እራሱን ዝቅ ያደረገው። ታዲያ ለዘመናት በድንቁርና እና በድህነት ቀንበር ሥር የኖረው የአገሬ ህዝብ የፖለቲከኞች ሸፍጠኛና ስሜት ኮርኳሪ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ቢሆን ከቶ ምን ይገርማል ?
- የኢህአዴግ “ተሃድሶ” ፖለቲከኞች ቀድሞውንም መታሠር ቀርቶ መወቀስ ያልነበረባቸውን ንፁሃን ዜጎች ሰቆቃ ይቆጥሩበት ከነበረው እሥር ቤት እንዲወጡ አድርገው “በችሮታችንና በይቅርታችን ብዛት እሥረኞች እንዲፈቱ አደረግን” ሲሉን ያለምንም የእንዴትነትና የከየት ወደ የትነት ጥያቄ “አዎ ወደ ፊትም የችሮታችሁ ብዛት እንዳይለየን ፈቃዳችሁ የሰማዩን ንጉሥ ያህል ይሁንልን” ብለን የተቀበልን እለት ነው ከስሜታዊነት ፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ግልፅ የሆነው ።
“አዎ ጥሩ አደረጋችሁ ፤ ነገር ግን እናንተንም ለዘመናት በንፁሃን መከራና ደም ከጨቀየው ሥርዓታችሁ ነፃ ትወጡ ዘንድ እልፍ አእላፍ ዜጎች ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከፍለዋልና ንፁሃንን ከጠባቡ እሥር ቤት እንዲወጡ ማድረጋችሁን የፖለቲካ ጨዋታችሁ መመፃደቂያ ማድረግ ጨርሶ ተገቢ አይደለም ፤ በግፍ የታሰሩ ንፁሃን ዜጎች ከእሥር እንዲወጡ ማድረግ የለውጥ መሪ ነኝ ለሚል መንግሥት የሃላፊነቱ መገለጫ፣ የተፈችዎቹ ደግሞ መብት እንጅ የችሮታ ሰጭና ተቀባይ ጉዳይ ጨርሶ አይደለምና ይልቁንም የገንዛ አገሩ ሰፊ እሥር ቤት ሆኖበት ዘመን ያስቆጠረውንና አሁንም ከተስፋና ከአንዳድ ምልክቶች በስተቀር እዚያው አዙሪት ያልወጣውን መከረኛ ህዝብ ተባብረን እንታደገው” ብሎ በግልፅና በቀጥታ ለመናገር (ለመሞገት) ወኔው ከድቶን ልጓም በሌለው የስሜታዊነት ፈረስ የመጋለባችን ክፉ አባዜ ይኸውና ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ቀጥሏል።
- የመሠረታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መብታቸውን የጠየቁ ንፁሃን ዜጎችን እስከ አሸባሪነት በሚደርስ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ወንጅሎ ለማጉላላት፣ ለማሰቃየት እና የእሥር ፍርድ ፈርዶ ለማጎር የሚያስችሉ ሌሎች ቦታዎች (ማጎሪያና ማሰቃያ ቤቶች/ህንፃዎች) የሌሉ ወይም የማይኖሩ ይመስል “ነባሩንና ትልቁን እሥር/ማሰቃያ ቤት ወደ ሙዚየምነት ቀየርናልና የፍትሃዊነት ትሩፋታችን ይድረሳችሁ” የሚል የግብዝነት ፕሮፓጋንዳ ሲግቱን ተንጋለን እየተጋትን “ስቃይ ደህና ሰንብች” የሚል ቅዠት እናቃዣለን። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ መሬት ላይ ያለውን ግዙፍና መሪር እወነት በምክንያታዊነት ተረድተን የሚበጀንን እንዳናደርግ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ግልብና ልጓም አልባ ስሜታችንን እየኮረኮሩ በጅምላ እንዲነዱን መፍቀዳችን ነው።
- ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች ከአገር ውጭ በሁለገብ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን እንደ ያኔው አርበኞች ግንቦት 7 የመሰሉትን የፖለቲካ ቡድኖች የመሣሪያ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካና የሞራል ትጥቃቸውን አስፈትተው (አስወልቀው) ወደ አገር ቤት በማስገባት ፣ እና እንደ ኦነግ የመሰሉትን ግን አገር ቤት ያሠማሩት የታጠቀ (ገዳይና ዘራፊ) ተዋጊ ቡድናቸው ማንም ሳይጠይቀው እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ሁኔታ ከኤርትራ ገባ የተባለውን “ጠመንጃ አልባ” ቡድን ለናሙና ይሆን ዘንድ በሚዲያ እያሳዩ ወደ አገር ቤት በማስገባትና በግድያና በዘረፋ ሲሰማራ ደግሞ ትርጉም ያለው እርምጃ ሳይወስዱ “ከአገር ውጭ በከንቱ ሲባዝን የነበረውን ተቀዋሚ ሁሉ ወደ አገር ቤት እንዲገባ ፈቅደን በነፃነት አንበሸበሽነው” ሲሉን “እንዴታ እደሜና ጤና ለእናንተ!” ብለን መቀበላችንንና የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ዓላማቸውንና አጀንዳቸውን ለመፈታተን የማንችል ዳካሞች መሆናችንን በሚገባ እንዲፈትሹን ፈቀድንላቸው።
- እራሳቸው መታረቅ ያቃታቸውን የሃይማኖት መሪዎች “አስታረቅሁ” በሚል አንቱ ከተባሉ አንጋፋ የአገራችን የሴኩላርና የሃይማኖት ምሁራን ሳይቀር “ከላይ ከሰማይ ተቀብቶ የተላከልን የለውጥ መሪ” የሚል አይነት እጅግ አስተዛዛቢ አድናቆት (አምልኮ) የተቸረው ፖለቲከኛ (ጠቅላይ ሚኒስትር) በጎሳ/በዘር/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ያበዱ ወገኖች በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥሉ፣ አገልጋዮቻቸውን ሲገድሉና ከነበሩበት ቤተ እምነት ጋር እንዲቃጠሉ ሲያደርጉ እና የእምነት መገልገያ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ የዶግ አመድ ሲያደርጉ “እኔ አላቃጠልኩም ፣ ድሮ ቢሆን ደፍራችሁ አትናገሩም ነበር ፣ ቤተ ክርስቲያን ወደ ፊትም ሊቃጠል ይችላል ፣ ወዘተ “ ሲለን ለጊዜው በስሜት ትኩሳት እንገነፍልና ውለን ስናድር ተመልሰን እየዘቀጥን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን መናፈቅ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።
አዎ! የሸፍጥ ፖለቲካ ዲስኩሮችንና ክስተቶችን እየተከተልን በስሜት የመጋለባችን እኛነት ወደ ለመድነው መስሎና አስመስሎ የማደር ክፉ አባዜ ውስጥ እየዘፈቀን መሆኑን መረዳትና የሚበጀውን የማድረጉ ጉዳይ ለነገ የሚተው ሊሆን አይገባም። ለሩብ ምእተ ዓመት በንፁሃን የቁም ሰቆቃና ደም የተጨማለቀውና በተሃድሶ (በብልፅግና) ስም የቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ መሆኑን ተረድቶ ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን ህዝቡን ከመርዳት ይልቅ ለዚያው ሥርዓት ደጅ እየጠናን ውይም እየተጎናበስን ስለ እምነት ነፃነት የምንሰብከው ስብከት፣ የምናነበንበው ምህላ፣ የምንፀልየው ፀሎት፣ የምናቀርበው መስዋዕት ፣ የምንሰጠው ቃለ ቡራኬ፣ እግዚኦ እያልን የምንቀድሰው ቅዳሴ ፣ ወዘተ ጨርሶ የትም አያደርሰንም።
በተግባር ያልታጀበ ቃልን (እግዚኦታን) ሰምቶ ምላሽ የሚሰጥ አምላክ እኛው እንዲሆንልን አድርገን በጭንቅላታችን ውስጥ የምንስለው እንጅ እውነተኛው የእውነት አምላክ አይደለም። በሰጠን ረቂቅ አእምሮ እና የተሟላ አካል ተጠቅመን ለምድሩም ሆነ ለሰማያዊው ህይወት የሚበጅ ሥራ እየሠራን ጥረታችን ይባርክ ዘንድ ስንጠይቀው መልካም ፈቃዱ ሆኖ አብዝቶ የሚረዳን ነው እውነተኛው አምላክ ማለት። የቤት ሥራችንን ባለመሥራታችን ምክንያት አይወድቁ ውድቀት ስንወድቅ እግዚኦ እያልን፣ እያለቀስንና እየተላቀስን የምንኖር ከሆነማ ለምን እኛን ከደመ ነፍስ ፍጡራን ለይቶ መፍጠር አስፈለገው? እናም ከፖለቲከኞች ስብከትና የተሃድሶ ፍርፋሪ ደጅ ጠኝነት ወጥተን በሰከነና መነሻውንና መዳረሻውን ጠንቅቆ ባወቀ የነፃነትና የፍትህ አርበኝነት መንፈስና የተግባር ውሎ ውስጥ እራሳችን ማግኘት ይኖርብናል ።
- “በሴቶች ሹመት ብዛት ሪኮርዱን ሰበርን ፣ የሰላም ሚኒስቴር በማቋቋም ዓለምን አስደመምን” ሲሉን “የእንስቶች ሹመት ተገቢ ቢሆንም ለፖለቲካ ፍጆታ ፐርሰንቱን ከፍ ማድረግ ግን አገር ይጎዳል እንጅ ጨርሶ አይጠቅምምና እየተስተዋለ ፤ የሰላም ሚኒስቴር የሚባለውም የለየለት የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታና በአስከፊ ድህነት ውስጥ በሚማቅቀው ህዝብ ገንዘብ መቀለድ ነውና ምናልባት ስህተትን አርሞ የግብር ከፋዩን ገንዝብ ከማባከን ማዳን ብልህነት ነው” ብለን ለማስገንዘብ ፖለቲከኞች ያስለከፉን በስሜት የመጋለብ ፖለቲካ ፋታ የሰጠን አይመስልም። በእውነት ከተነጋገርን የበላይ አለቆች (ካድሬዎች) ሲጠሯቸው አቤትና ሲልኳቸው ወዴት በማለት የቤተ መንግሥቱን የሸፍጥ ፖለቲካ በሚያጅቡ እንስት ባለሥልጣናት (ካድሬዎች) ሹመት በሹመት በማንበሽበሽ አገሩን ለወጥ በለውጥ አደረግነው ብሎ ያዙኝና ልቀቁኝ ማለት የህዝብን የመገንዘብ ችሎታ ወደ ደመነፍስ እንስሳ ደረጃ ማውረድ (dehumanization) ማውረድ ነው።
- የተወለዱበትንና ለዘመናት የእነርሱ ሆኖ የኖረውን እጅግ ሰፋፊና ለም መሬት ተነጥቀው ያለማንነታቸው ኖረውበት ወደ እማያቁት ክልል እንዲጠቃለሉ የተገደዱት ወገኖች ጩኸትና አቤቱታ በኦዴፓ ለሚመራው መንግሥት እራስ ምታት ስለሆነበት ህዝብን የሚያዘናጋበትና ቀስ በቀስም አድበስብሶ የሚያረሳሳበት ዘዴ (mechanism) መዘየድ ነበረበት ። ለዚህ ደግሞ የኢህአዴግ/የብልፅግና መሪና የአገሪቱ ጠቅላይሚኒስትር አንድን ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ሳይሆን ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው የሚያስታወስ (short memory ) በሚል የሚሳለቅበት ህዝብ ምቹ እንደሆነ ጥር ሱን ነቅሎ ካሳደገው እኩይና ሴረኛ ድርጅት (ህወሃት/ኢህአዴግ) ተሞክሮ አሳምሮ ያውቀዋል ።
ለዚህ ነው የሰልምና የእርቅ ኮሚሽን እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽን በሚል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተሳታፊ የነበሩና የራሳቸው (የህሊናቸው) የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሌላቸው የቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ፣ ለዚህ አይነት ገለልተኝነትንና ሚዛናዊነትን ለሚጠይቅ ሥራ ጨርሶ ሊመጥኑ የማይቻላቸውን የተቀዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ተብየዎችን ፣ የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኛ ፖለቲከኞችን ፣ እና የለውጥ መሪ የሚሉትን ግለሰብና ቡድን ለማምለክ ህሊናቸውን ያዘጋጁ ግለሰቦችን መልምሎና መድቦ የለየለት ህዝብን የማደንቆርና የማደንዘዝ የፖለቲካ ተውኔት ትወናን እየታዘብን ያለነው።
ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች በዚህ እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን በሚያስረሳ አኳኋን ግልብ ስሜታችንን በሚኮረኩሩ ዲስኩሮችና ክስተቶች ወደ የሚፈልጉት አቅጣጫና ግብ ሲነዱን ያልተጨናገፈ ይመስል ለወጡ እንዳይጨናገፍ የሚል የተንሸዋረረ መከራከሪያ በመደጋገም ፣ አገር ሸፍጠኞችንና የጎሳ ፖለቲካ ልክፍተኞችን በማባበል ይድን ይመስል አገር እንዳይፈርስ ተብሎ ነው የሚል ልፍስፍስ ምክንያት በመደርደር ፣ ሰላም ያለ ወይም የሰፈነ ይመስል የሰላምን ትርጉም ቆንፅሎ (ቀንጭቦ) በማነብነብ ሰላም እንዳይደፈርስ የሚልና መሪሩን ሃቅ የማይገልፅ ትንታኔ በመተንተን ወይም በማስተንተን ፣ ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት በየተራ እየተመጠኑ በችሮታ የሚሰጡ ይመስል ኢ-ዴሞክራሲዊ የሆኑትን ገዥዎች የህግ የበላየነትን እንዲያስከብሩልን ደጅ በመጥናት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል ብሎ መጠበቅ ልክ የሌለው የፖለቲካ ድንቁርና (ደደብነት) ነው።
- ከአሽከርነት ለመላቀቅ ፈፅሞ ያልተሳከለትን ብአዴንን/አዴፓን አጃቢ አድርገው ህወሃትን ከትከሻቸው ለማውረድ የተሳካላቸው ኦህዴዶች/ኦዴፓዎች በሚገርም ፍጥነትና ሁኔታ ቁልፍ (ወሳኝ) የፌደራል መንግሥት የሥልጣን ወንበሮችንና ርዕሰ ከተማዋን (አዲስ አበባን) በፖለቲካ ጨዋታ መረባቸው ውስጥ አስገብተዋል ።
ይህን ካረጋገጡ በኋላ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ነባሩ ስማቸውና ኢህአዴግ የሚለው የግንባራቸው ስም በህዝብ ጨርሶ የተሰለቼ (የተጠላ) በመሆኑ የጀመሩትን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ከፈለጉት ግብ ለማድረስ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ሲያውቁ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላም ከፖለቲካ ደደብነትና አሽከርነት አዙሪት መውጣት ያልተሳካላቸውን ብአዴኖች/አዴፓዎች አጃቢ በማድረግ ብልፅግና የሚባል ውህድ ፓርቲ ሆነናል በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ መሳለቃቸውን ተያይዘውታል ።
የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች የኢትዮጵያ የሚለውን ቅፅል ስለሚፀየፉ ከስያሜው አወጥተው ብልፅግና ብቻ እንዲሆን መስማማታቸውን ልብ ለሚል ቅንና በዴሞክራሲያዊት አገር በአብሮነት ለመኖር ለሚናፍቅ የአገሬ ሰው ካልበለፀገ ( ከመከነ/ከተበላሸ) የፖለቲካ አስተሳሰብና ሰብእና እንዴት አይነት አበልፃጊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው የሚወለደው? ብሎ ሳይጠይቅ የሚያልፍ አይመስለኝም ።
የኢትዮጵያ የሚለውን የማንነት አመልካች ቅፅል ተፀይፈው የአማራ ብልፅግና፣ የኦሮሞ ብልፅግና፣ የደቡብ ብልፅግና ፣ ወዘተ የሚል ስም ሰጥተውና የዋና ጽ/ቤቱን የሰው ኅይል በየጎሳው ኮታ አዋቅረው ” ውህድ የሆነ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን አበልፃጊ የፖለቲካ ፓርቲ አምጠን ወልደናልና ደስ ይበለን” ሲሉ የህዝብን የግንዛቤ (የመረዳት) ችሎታ ምን ያህል በእጅጉ ዝቅ (dehumanize) እንዳደረጉት ከምር ልብ ለሚል የአገሬ ሰው የፖለቲካ ጨዋታችን ለማስተካከል ያለብን ፈተና ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመገንዘብ አይቸግረውም ።
የተማረውና በመማር ላይ ያለው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ሳይማርና ሳይደላው ያስተማረው ህዝብ የህይወት (የአኗኗር) እውነታው በራሱ ነቅቶና ተደራጅቶ ነፃነቱን በዘላቂነት ሊያረጋግጥ የሚያስችለው እንዳልሆነ ከምር ተረድቶ የትውልድ ተልእኮውንና ሃላፊነቱን ለመወጣት ያለመቻሉ ፈተናም በእጅጉ የሚያም የውድቀት ፖለቲካ ታሪካችን አካል ነው። እንዲያውም ካልተማረው ወገኑ በባሰ አኳኋን ስንኩል ምክንያት (ሰበብ) እየደረደረ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ በመንሸራተት ከህአዴግ ተሃድሶ (ብልፅግና) ፖለቲከኞች ጋር የጫጉላ ሽርሽር ዓይነት ፖለቲካውን ተያይዞታል። አዎ! ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች በመሃይምነት ፣በድህነት እና በግፍ አገዛዛቸው መከራና ውርደት እያስቆጠሩ ሲገዙት የኖሩትንና አሁንም ቅርፅና ስም እየቀየሩ እና ከተሃድሷቸው ፍርፋሪ እየመፀወቱ ሊያስቀጥሉት የሚፈልጉትን ህዝብ ይታደጋል የሚባለው አብዛኛው የተማረው የህብረተሰብ ክፍል የአስከፊ የፖለቲካና የሞራል ቀውስ ሰለባቸው እንዳደረጉት በሚገባ ያውቁታል።
እናም ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ሥልጣን ላይ የሚወጡ ሁሉ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄውን እያዘናጉ የመከራውንና የውርደቱን ዘመን የሚያራዝሙበት የአገሬ ህዝብ ሳይማር ባስተማራቸው ልጆቹ ካልታገዘ በስተቀር ግዙፍና መሪር ዋጋ የከፈለበት የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ ሰሚ የሌለውና የማይመለስ ሆኖ ይቀጥላል።
አዎ! በድንቁርና፣ በድህነት፣ በርሃብ፣ በበሽታና በመብት እጦት እየተጎሳቆለ አፍንጫውን ተይዞ በሚከፍላት ግብር ያስተማረ ህዝብ የተማሩ ልጆቹን “እንደ ዜጋና እንደ ሰው መበቴ የሚከበርበት ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ተባብራችሁ አግዙኝ” ብሎ ቢጠይቅ ያንስበታል እንጅ ከቶ አይበዛበትም።
ይህ አይነቱ ልክ የሌለው ሰንካላና ትውልድ አደንቋሪ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ የልሂቅነት እውቀትና የተሞክሮ ባለቤት ነኝ በሚለው የህብረተሰብ ክፍል ሲስተጋባ መታዝብ ደግሞ ከፖለቲከኞች ባልተናነሰ ህሊናን ያማል።
ፊደል ከመቁጠር አልፎ ልሂቅና ሊቀ ልሂቃን ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ለሩብ ምዕተ ዓመት በጎሳ/በዘውግ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ ተመሥርቶ በልዩ ልዩ ፖለቲካ ወለድ ወንጀልና በንፁሃን ደም የተጨመላለቀው ሥርዓተ ኢህአዴግ የተመሠረተባቸው ምሰሶዎች ማለትም ህገ መንግሥት ተብየው፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት (ህግ አውጭ/ፓርላማ ፣ህግ ተርጓሚው/የፍትህ አካሉ እና ሥራ አስፈፈፃሚው /አስተዳደሩ ) ምንም አይነት ትርጉም ያለው ለውጥ ባላሳዩበት እና ገዥው ቡድንም የማታለያ ስም ስያሜና የአደረጃጀት ቅርፅ ለውጥ ብቻ እያደረገ በቀጠለበት መሪር ሃቅ ውስጥ በስሜት መነዳቱን ቀጥሏል።
- ከመከራውና ከውርደቱ ብዛትና ጥልቀት የተነሳ የተነገረው (የተሰበከው) ድንቅና ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩር ሁሉ እውነት እየመሰለው የተቸገረው የአገሬ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ሌላ መደስኮር (መናገር) የሚችል ፖለቲከኛ ወይም ባለሥልጣን በአገር የጠፋ እስኪመስል ድረስ ከከፍተኛው እስከ አነስተኛው መድረክና ሌላም አጋጣሚ ባደረጋቸው ዲስኩሮች (ንግግርሮች) ልጓም በሌለው ስሜታዊነት መነዳት ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከክርስቶስ ቀጥሎ ለኢትዮጵያ የመጣ “ክርስቶስ” አድርጎ እስከ ማየት (እስከ ማምለክ) ደርሶ የነበረ መሆኑን ለማስተባበል አይቻለንም።
በዚያ ልጓም አልባ በሆነው የስሜታዊነት ፖለቲካ ትኩሳት ወቅት ነበር የአገሬ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግግሮቹ ሁሉ መግቢያ፣ ማድመቂያና ማሳረጊያ (መሪ ቃል) አድርጎ ይጠቀምበት የነበረውን “መደመር” የሚል ቃል እንደ አቡነ ዘበ ሰማያት መድገም የጀመረው ። አዎ! በእንደዚያ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነበር ባለ ቅኔውም በቅኔው፣ ዘማሪውም በዝማሬው፣ ዘፋኙም በዘፈኑ፣ ገጣሚውም በግጥሙ ፣ ባለ መንዙማውም በመንዙማው ፣ ባለምህላውም በምህላው ፣ ሰባኪውም በሰበካው፣ ወዘተ “መደመር” የሚለው ቃል የለውጥ ሐዋርያት ለምንላቸው ፖለቲከኞች ብቻ የተሰጠ (የተገለጠ) ቅዱስ ቃል እስኪ መስል ድረስ ውዳሴውን ያዥጎደጎደው ።
ከማህበረሰብ አባልነቱ ብቻ ሳይሆን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከቆየበት እኩይ ሥርዓት ባገኘው ተሞክሮ የዚህን ህዝብ ስስ ሥነ ልቦና እና ስሜት በሚገባ የሚያውቀው ጠቅላይ ሚኒስትር “አሸጋጋሪ ዴሞክራትነቴን እየተቀበላችሁ ‘በመደመር ፍልስፍና’ ሽግግሩን እውን እናድርግ” የሚል ይዘት ያለው የትረካ መጽሐፍ በማሳተምና በማስመረቅ ምሁር ወይም ልሂቅ ወይም ሊቀ ሊቃውንት ነኝ የሚለውን በርካታ የአገሬ ሰው እራሱ የተማረና የተመራመረ አልመስለው እስኪ መስለው ድረስ በየመድረኩና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ “የመጀመሪያውና ዘመናዊው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ መሪ “ የሚል አይነት የመወድስ ምሥክርነት እንዲያስተጋባ አደረገው።
መደመር (synergy/working together) አንድን የጋራ ተልእኮና ዓላማ በተሳካ ሁኔታና ፍጥነት ለማከናውን በእጅጉ ከሚያስፈልጉን ስትራቴጅዎችና ሥልቶች አንዱ ሊሆን ይችላል እንጅ ከቶም በራሱ ፍልስፍና ሊሆን አይችልም ። ኢትዮጵያ እንደማነኛውም አገር የእራሷ (አገር በቀል) ማህበራዊ፣ ባህላዊና እና መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) እሴቶችና ትውፊቶች ያሏት አገር እንደመሆኗ መጠን ዓለም አቀፋዊ (universal ) የሆነውን የዴሞክራሲ ፍልስፍና እና መርህ ከእነዚሁ እሴቶቻችንና ትውፊቶቻችን ጋር አብሮ ሊያስኬድ በሚያስችል ሁኔታ ሥራ ላይ እናውለው የማለቱ ትክክለኛነት ጨርሶ የሚያጠያይቅ አይደለም። ዓለም አቀፍ (universal) ከሆነው የዴሞክራሲ ፍልስፍና እና መርህ ውጭ የሚቆምም ሆነ እውን የሚሆን አገር በቀል የፖለቲካ ፍልስፍና እና መርህ ግን የለም። የምናወራው ስለ የእያንዳንዳቸን (የየግላችን) የህይወት ስኬት ፍልስፍና ሳይሆን የእያንዳንዳችንን የህይወት ፍልስፍና ወይም ራዕይ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ የመስተጋብር አውድ አማካኝነት የጋራ እጣ ፈንታችንን በማያቋርጥ ሁለገብ እድገትና ብልፅግና እውን ስለምናደርግበት ሥርዓተ ፍልስፍና ከሆነ ያ እስከ አሁን መተኪያ (አማራጭ) ያልተገኘለት ሥርዓተ ፍልስፍና እና መርህ ዴሞክራሲ ነው።
የፖለቲካ ሥልጣኑን ከሚቆጠጠሩ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ትኩሳት ጋር እየውጣንና እየወረድን ለዚህ ዓለም አቀፍ (universal) ለሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ፍልስፍና እና መርህ እውን መሆን የሚያግዙ ባህላዊና ትውፊታዊ እሴቶቻችንን ዋጋ ዝቅ ማድረጋችን አሳሳቢ ቢሆንም አሁንም ተጨማሪ ጊዜ ሳንገድል ተገቢውን ካደረግን በአንፃራዊነት ከዘመን ጋር አብሮ የዘመነውን ዴሞክራሲያዊ ዓለም መቀላቀል የማንችልበት ምክንያት የለም።
በአደንቁሮ ገዥ ፖለቲከኞች ለዘመናት ፍዳውን ሲከፍል የኖረውን መከረኛ ህዝብ አሁንም ልክ የሌለው የፖለቲካ ሥልጣን ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያ ይረዳናል የሚሉትን ስሜት ኮርኳሪ ቃልና ሥነ ቃል ” አዲስ የአገር በቀል የፖቲካ ፍልስፍና” ትርጉምና ትንታኔ ቢጤ በማላበስ በዓለም አቀፉ (universal ) መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ፍልስፍና መሠረት እውን ይሆን ዘንድ ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ አልፈስፍሶ ለማለፍ መሞከር ርካሽ የፖለቲካ ንግድ ከመሆን አያልፍም።
የአገሬ ህዝብ የገሃዱ ዓለም ህይወቱን በማያቋርጥ የእድገት (የመሻሻል) ሂደት ለማስቀጠል የአብሮነት መስተጋብር አስፈላጊነትን እንደየ ቋንቋው እና እንደሚኖርበት አካባቢ ባህላዊና ትውፊታዊ ልምድ ሲገልፀው ኖራል ፤ አሁንም ይገልፀዋል ።
አሁን እንደ አዲስ የፍልስፍና ግኝት በሚገርም ሁኔታ የምናራግበውን የመደመር (synergy/working together) አስፈላጊነት የአገሬ ሰው ከእኛ አልፎ በዓለም አቀፍ የሥነ ቃል ጠበብት አድናቆት በተቸረው “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር” በሚለው አገላለፅ ጠቅለል አርጎ ከገለፀው አያሌ ዘመናት ተቆጠሩ።
እናም ለዘመናት የወደቅንበትና አሁንም ትርጉም ባለው ሁኔታ ከአዙሪቱ ያልወጣንበት መሠረታዊ ምክንያት ይህንን ከገሃዱ ዓለም ተሞክሮ የተገኘና የአብሮነት ሃያልነትን የሚገልፅ ጥልቅ የሆነ በጎ አስተሳሰብ ዓለም አቀፍ (universal) ለሆነው የዴሞክራሲ ፍልስፍና እና መርህ በወርቃማ ግብአትነት (input) ተጠቅመን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥርዓት እውን ከማድረግ ይልቅ መደመርና የመሳሰሉ ቃላትን እንደ አዲስ የፍልስፍና ግኝት በማጦዝ ፖለቲካ የህዝብን መሠረታዊ የትግል መነሻና መዳረሻ በእጅጉ ስለምናንሻፍፈው ነው።
- ከሰሞኑ ልክ የሌለው የስሜታዊነት ፖለቲካ ትኩሳት ከሚንተከተክባቸው ጉዳዮች አንዱ የኖቤሉ ሽልማት ጉዳይ ነው። አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በዚሁ ጉዳይ ላይ ፅፈው ያስነበቧትን አጭር አስተያየትና መልእክት አነበብኳት ።
በመሠረቱ እንኳን የአገሩ መሪ የሌላም አገር መሪ ቢሆን የሆነውንና ያደረገውን ወይም በመሬት ላይ የተጫወተውንና እየተጫወተ ያለውን በእውን የሚመጥን እስከሆነ ድረስ የትኛውንም አይነት ሽልማት ቢሸለም ጤናማ አእምሮና ቅን አስተሳሰብ ያለው የአገሬ ሰው ደስታ አይሰማውም ብሎ እንኳን ማመን መገመትም ያስቸግራል።
ከፕሮፌሰር መስፍንና ሌሎች ምሁራን የአድናቆትና የደስ ይበልን አስተያየት (መልእክት) ጋር የምስማማውም ከዚሁ መሠረታዊ እይታ አኳያ ነው። ፖለቲከኛ ግለሰብን ወይም ግለሰቦችን በመሬት ላይ ካለው መሪር ሃቅ አንፃር ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን ያስመዘገበውን /ያስመዘገቡትን ውጤት ሳይሆን በሚያስተጋባው/በሚያስተጋቡት እፁብ ድንቅ ዲስኩር ወይም ስብከት ወደ እንከን የለሽነት ወይም አገር ሌላ ሰው ጨርሶ የሌላት እስኪመስል ድረስ በተለጠጠ ሁኔታ ከሚቀርብ ውዳሴ ጋር ግን ጨርሶ አልስማማም ። ይህን አይነት ውዳሴ ማቅረብ እንኳን በእውቀትና በተሞክሮ አንቱ ለሚባሉ ወገኖች ለማነኛውም መሠረታዊ እውቀትና የህይወት ልምድ ላለው የአገሬ ሰው ጨርሶ አይመጥንም ።
በሁለመናው ግራ ለተጋባና ሸፍጠኛ ፖለቲከኘችም ይህንኑ ግራ መጋባቱን ተጠቅመው እንደ ደመ ነፍስ እንስሳ በስሜት እንዲነዱት ለፈቀደላቸው ለዚህ ትውልድ እንዲህ አይነት ሂሳዊ ያልሆነ (ወደ ማምለክ የተጠጋ) መወድስ እያስተማርን የመከራና የውርደት ዘመኑን በምክንያታዊነትና ከምር በሆነ ትግል ማሳጠር የሚችልበትን የአስተሳሰብና የህሊና ብርታት ማልፈስፈስ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ የምሁርነት ፖለቲካ ተምሳሌት ሊሆን አይችልም።
አዎ! ለዘመናት ከተዘፈቁበት ወንጀለኛ ሥርዓት ውስጥ እንዳሉ የህዝብን የነፃነት ትግል በመጨረሻዋ ሰዓት በመሪነት መቀላቀላቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። ተያይዞ ከመተረማመስና ከመጠፋፋት የተሻለ መሆኑም እርግጥ ነው። እናም ለዚሁ የሚመጥን እውቅና እና ሂሳዊ ድጋፍ በመስጠት ከኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) የፖለቲካ ሸፍጥ ወጥተው ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን የሚበጅ መውጫ መንግድ (መሸጋገሪያ) እንዲያመቻቹ በቀጥታና በግልፅ ለመናገር ወይም ለመሞገት የሞራልና የፖለቲካ አቅም ያነሰው አብዛኛው የአገሬ ምሁር የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀበለበት ፍፁማዊ የሚመስል ውዳሴ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም። አብዛኛው የአገሬ ምሁር በሽልማቱ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ በጥሩ ሥነ ፅሁፋዊ ውበትና አንደበት የተደሰኮሩ ዲስኩሮችን “የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለዓለም ያበሰሩ” በሚል አይነት ግልብ ስሜት መወድስ ያቀረበበት ሁኔታ እየተናነቀን ላለው ዘርፈ ብዙ ውድቀት (ቀውስ) ጨርሶ የሚመጥን አይደለም ።
በንፁሃን የቁም ስቃይና ደም የተዘፈቀውን ሥርዓታቸውን ለመቅበር ከመቃብር አፋፍ ቁመው ቢጠብቁም የተዘጋጀ ቀባሪ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ባለመገኘቱ ከመቃብር መልሰውና በተሃድሶ ስም እንዲያገግም ብቻ ሳይሆን እንደ ሥርዓት ተመልሶ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋጋሪ እንዲሆን አድርገው ሲያነግሡት ከምር ለምን እና እንዴት ብሎ የሚጠይቅና በመርህ ፀንቶ የሚቆም ምሁር በጣት የሚቆጠር መሆኑን ከምር ልብ ለሚል ቅን አሳቢና ነፃነት ፈላጊ የአገሬ ሰው ህሊናውን ቢፈታተነው የሚገርም አይሆንም።
“ ከእንግዲህ በጋራ ምክክር በሚመሠረት አሸጋጋሪ አካል እንጅ የበሰበሰውና የከረፉው ሥርዓተ ኢህአዴግ የተወሰኑ አባሎቹ በንስሃ ታጥበናል ስላሉ ብቻ እንደ ሥርዓት በመሪነት መቀጠል የለበትም” ብሎ በመሟገት ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እስከመጨረሻው ፀንተው ይቆማሉ የተባሉና ተስፋ የተጣለባቸው የተቀዋሞ ፖለቲካ መሪዎች በኢህአዴግ ተሃድሶ (በብልፅግና) ፖለቲከኞች ሽልማት የድል ብሥራት ነጋሪት እየታጀቡ አስቀያሚ የፖለቲካ ዳንስ ሲደንሱ መታዘብ ባያስገርምም የሃዘን ስሜቱ ግን ያማል። የእነዚህ ፖለቲከኞች የፖለቲካ አስተሳሰብና የአቋም ልፍስፍስነት አባዜ ውጤት አስከፊነቱ በእጅጉ የሚያሳስበው ደግሞ በህዝብ ላይ የሚያሳድረው ጎጅ ተፅዓኖ ነው። አዎ! ህዝብ ከመከራው ግዙፍነትና ጥልቀት የተነሳ የሚሰማው በጎ ቃልና የሚያየው ስሜት ኮርኳሪ ክስተት ሁሉ በእውነት ከመከራው የሚገላግለው እየመሰለው የሸፍጠኛ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ እየሆነ የመቀጠሉ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባል ።
ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ብዙሃኑ የአገሬ ህዝብ የሚነገረው እፁብ ድንቅ የተስፋ ቃል ሁሉ ከዘመናት የግፍና የሸፍጥ አገዛዝ ይገላግለው እየመሰለው “ነፃ አውጭዎቼ ከኢህአዴግ ማህፀን ተወለዱ ። ተአምርም ሆነ” ከሚል ቅዠት ጋር እራሱን እንዲያለማምድ በማድረግ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄው እየተንሸራተተ የተሃድሷቸው ፍርፋሪ ተመፅዋች ቢያደርጉት የሚገርም አይደለም።
ታዲያ የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ በሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ሃዲዱን እንዲስት መደረጉ መሆኑን አውቆ የሚበጀውን ለማድረግ የተሳነው ትውልድ ስለ ነፃነትና ፍትህ ሲደሰኩርና ባዶ ተስፋ ሲያልም ይኖራታል እንጅ የትም አይደርስም።
የሽልማቱን እሴትነት ከገሃዱ ዓለም መሪር ሃቅ ጋር በማመሳከር ከሂሳዊና ገንቢ አስተያየት ጋር ስሜትን ከመግለፅ ይልቅ “መተቸት ነውር ነው ወይም የአገርን ክብር መናቅ ነው” በሚል አይነት ጨርሶ ልፍስፍስ (clumsy) እና የዚህን ትውልድ አንድን ጉዳይ በምክንያታዊ አስተሳሰብ እና በተግባር ምሥክርነት ( reasoning power and evidence of practicality) የመፈተሹን አቅምና ችሎታ በሚያኮሰምን አኳኋን የቅኔ፣የዝማሬ፣ የዘፈን (የሙዚቃ) ፣ የመነባንብ እና ከአውሮፓ እስከ አገር ቤት በተካሄደ ትእይንተ ሽልማት ተአምራዊ ገፅታ ለመስጠት የተሄደበት መንገድ ፖለቲካችን ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነና በሰለጠነ ድባብ ውስጥ መሆኑን ጨርሶ አያሳይም ።
ዓለም በተግባርም ሆነ የታሪክ መዛግብትን በማገላበጥ ጠንቅቆ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሚያደንቀውን በቅኘ ግዛት ሥር ያለመገዛታችን እና እስከ አሁን ባለው መረጃ የሰው ዘር መገኛ አገር ሰዎች የመሆናችንን ታሪክ የሽልማት ድርጅቱ ኮሚቴ አባል በንግግራቸው ስለጠቀሱት “የአገራችን ክብርና ኩራት ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ (በዓለም) ከፍ ብሎ እንዲስተጋባ ያደረገ የዘመናችን ድንቅ መሪ” በሚል ልክ በሌለው የስሜታዊነት መንፈስ መጋለብን ምን ይሉታል?
ታዲያ የዚህ አይነት ባለ ታሪክ አገር ሰዎች (ህዝቦች) በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እየሆናችሁትና እያደረጋችሁት ያላችሁት ምንድነው? ከሰብአዊ ፍጡር በታች ከሚያውለው የእለት ጉርስ ተመፅዋችነት ለመውጣትስ ቢያንስ ትርጉም ያለው ሥራ ለመጀመር እንዴት ተሳናችሁ? ከዚህ ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች ከሚያውል አስከፊ ሁኔታ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ነው በሚል ግዙፍና መሪር ዋጋ ከከፈላችሁበት የተልእኮና የግብ ሃዲድ እየተንሸራተታችሁ የመከራና የውርደትን ዘመን ለምን ታራዝማላችሁ ? ለትውልድ የሚተርፍ አኩሪ የታሪክ ባለቤቶች ነን እያላችሁ ይህ ያለንበት ዘመን የሚጠይቀውን የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በእራስ መተማመንና ሠርቶ በማሳየት የዓለምን ድጋፍና አድናቆት ከማግኘት ይልቅ ለፖለቲካ ትርፍነት በሚውል ዲስኩርና እዚያና እዚህ ብልጭና ድርግም የሚሉ ክስተቶችን ተአምር የተሠራ ያህል እያጦዛችሁ በአድናቆትና በሽልማት ተንበሸበሽን በሚል ጮቤ መርገጥስ የት ያደርሳችኋል? ለመሆኑ ከየት ተነስታችሁ ፣ በየት በኩል አድርጋችሁ እና የት እንደምትደርሱ ተጨንቃችሁ የወለዳችሁት ፣ ህዝብ አውቆ የተረዳውና ይሁንታ የሰጠው ፣ እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ፍኖተ ካርታችሁ (road map) የት አለ? ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምድነው?
ንፁሃን ዜጎች በገንዛ አገራቸው ተፈነቅለው ለመከራ ሲዳረጉ፣ በጎሳ ፖለቲካ ልክፍተኞች ሲሳደዱ፣ ሲወገሩ፣ ሲዘረፉና ሲገደሉ በውጭ አገራት ሆኖ ይመለከትና ይሰማ የነበረ እና ከተመለሰም በኋላ ሃላፊነት እንደሚሰማው የአገር መሪ ሃላፊነቱን ከውጤትም ሆነ ከጊዜ አኳያ ትርጉም ባለው ሁኔታ ያልተወጣን ጠቅላይ ሚኒስትር “የሰላም ሽልማት ሲያገኝ ማሄስ (መተቸት) ነውር ነው ወይም የአገርን ክብር ዝቅ ማድረግ ነው ወይም ጭፍን ጥላቻ ነው” የሚለው መከራከሪያ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ።
የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች ያስደስትልናል የሚሉትን ሲያሳዩንና ሲነግሩን ጮቤ እየረገጥን እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀድመው መከላከል እንኳ ቢቀር ፈጥኖ በመድረስ መታድግ ባለመቻላቸው ንፁሃን ዜጎች ከተጨፈጨፉ በኋላ የአዞ እንባ ሲያነቡ አብረን እያለቀስን ከቶም የትም አንደርስም ።
ለመሆኑ የሽልማቱ የመጀመሪያው (ዋናው) መመዘኛ “ከለውጥ” ወዲህ የሆነውና እየሆነ ያለው የመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም እንዴ ?
በእውነት ከተነጋገርን በአገር ውስጥ እየሆነ ያለውን እጅግ አስከፊ ሁኔታ ቢቻል አስቀደሞ ለመከላከል ካልሆነም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተጨፈጨፉ የነበሩ ንፁሃን ዜጎችን በአስቸኳይ ለመታደግ እና የጭፍጨፋውን አነሳሾችና ፈፃሚዎችን በህግ ፊት ለማቅረብ ከመቻልና ካለመቻል የበለጠ መመዘኛ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ መሆን ነበረበት እንዴ?
በአደገኛ ሁኔታ ምስቅልቅሉ የወጣውን (ክፉኛ የሚናወጠውን) የእራስን ቤት እየሸሹ የአገራትን ግንኙነትና ሰላም ለማጠናከር በሚል በየቦታው መብረርና “ትሩፋቴ የአገሬ የለውጥ መሪነት ብቻ ሳይሆን ሰላም ላጡ የአፍሪካ መንግሥታትና ህዝቦችም ይተርፋል” የሚል አይነት የፖለቲካ ዘመቻ ላለንበት መሪር እውነት እንዴት ይመጥናል?
የኤርትራ መንግሥትስ ባድመን ያስረከበው የአልጀርስ ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት እስከ አገኘለት ድረስ ለምን የጦርነት ሥጋት ይደቅናል ? ለመሆኑ በሁለቱ አገሮች መካከል ግንኙነቱና ፍቅሩ ጦፏል የሚያሰኘው የስምምነት ሰነድ በየትኛው ኤክስፐርቶች ተጠንቶ መቼ ለህዝብ ግልፅ የሆነው ነው?
ለነገሩ የአፍሪካ መንግሥታት ግንኙነት የመሪዎች ግንኙነት እንጅ የህዝ ለህዝብ ሆኖ አያውቅምና የዶ/ር አብይና የአቶ ኢሳኢያስም ይህ መሆኑ አይገርምም ። ህዝብን የሚጠቀሙበት በየጎዳናውና በየአደባባዩ የፕሮፓጋንዳቸው አጃቢ ለማድረግ ነው። አዎ!እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እስካልሆነ ድረስ ይኸው የፖለቲከኞች እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ (ተውኔት) ይቀጥላል። ግንኙነቱ እየተሻሻለ ሊቀጥል የሚችል ነው ብለን ብንቀበልም ሲሆን በሁለቱም አገሮች ካልሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እስካልሆነ ድረስ የአገሮቹ ግንኙነት በገዥ ቡድኖች ፍላጎትና ፈቃድ የሚዘወር ሆኖ ይቀጥላል ።
“ከተገናኙ ወራት አለፋቸው ፤ አዳዲስ ወሬም የለም ፤ ምነው የመደባበር ነፋስ ገብቶ ይሆን ?” ለሚለው ጉምጉምታ (rumor) ምላሽ ይሆናል በሚል ከሰሞኑ ሁለቱ መሪዎች በአንዳንድ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተዘዋወሩ “በየእራሳችን ጉዳዮች ላይ በማተኮራችንና ግንኙነቱን እጅግ ወደ ላቀ ደረጃ በምናደርስበት ጥናት እና ፖሊሲ ላይ በመጠመዳችን እንጅ በፍቅራችን መሃል ሽው ያለ ነፋስ አለመኖሩን ውዳጅም ሆነ ጠላት ይወቅልን” የሚል መልእክት የማስተላለፋቸውን የፖለቲካ ጨዋታ ልብ ይሏል ። ምናልባትም ከተግባራዊነታቸው ይልቅ የፖለቲካ ፍጆታ ማድመቂያ የሚሆኑ የስምምነት ወሬዎችን ልንሰማ የምንችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ።
እንደ እውነቱ ቢሆን ኖሮ የሽልማቱ ዋና ዋና መመዘኛዎች፥ በለውጥ መሪነትህ ዜጎችህን ከአክራሪ ቡድኖች አስከፊ ሰይፍ ተወርውረህ (ፈጥነህ) በመከላከልህ ፣ በመርዳትህ እና ወንጀለኛ አክራሪዎችን ለፍርድ አቅርበህ ሰለባዎቹ ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግህ ፣ ሁሉን አሳታፊና አስተማማኝ የሽግግር ሥርዓት በመዘርጋትህ ፣ የመከራና የውርደት ሰነዳችሁ (ህገ መንግሥታችሁ) ላይ ትርጉም ያለው ማሻሻያ ለማድረግ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ወኔ በማሳየትህ፣ በሚሻሻለው ህገ መንግሥት መሠረት በገዥው ቡድንህ ካድሬዎች የተሞሉትን ሦስቱን የመንግሥት አካላት (ህግ አውጭውን ፧ ህግ ተርጓሚውን እና ሥራ አስፈፃሚውን/አስተዳደሩን) መልካም ህሊና ባላቸው ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች የማስታጠቅ ተግባራዊ ጥረት ላይ ስለምትገኝ ፣ በምትመራው የፖለቲካ ፖርቲ ውስጥ የሩብ ምእተ ዓመቱን ህወሃት መራሽ የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካን “ተራው የእኛ ነው” በሚል በባሰ ሁኔታ እየደገሙት ያሉትን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለማስቆም እንደ አንድ አገር መሪ በቁርጠኝነት በመነሳትህ፣ እና ከዚህ የተረፈህን ጊዜና እውቀት ደግሞ በአካባቢው ከሚገኙ መንግሥታት ጋር ስለ ሰላምና መረጋጋት የምትችለውን ጥረት በማሳየትህ ፣ ወዘተ የሚሉ መሆን ነበረባቸው ። ግን አልሆነም። ለዚህ ነው በሽልማቱ ዙሪያ ጥያቄ ማንሳትና ሂሳዊ ትችት መሰንዘር ከነውርነት፣ የአገርንና የፖለቲከኞችን ክብር ዝቅ ከማድረግ እና ከጭፍን ተቃውሞ ጋር ጨርሶ ግንኙነት የማይኖረው።
ለነገሩ የተፈጥሮ ስጦታው እንደ ተቸራት አገር ዜግነታችንና እንደ ጠንካራ ሠርቶ አዳሪነታችን ለነፃነት ፣ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለክብር፣ ለኩራት፣ ለፍቅር፣ ለሰላምና ለጋራ ብልፅግና የቆመና የሚታትር ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት እውን አድርገን በዓለም ፊት እኩል ከቆምን ሸልማቱ በአፍንጫችን ቢወጣስ!
አዎ! ምንም እንኳ የዓለም አቀፉ ጥሩም ሆነ መጥፎ ግንኙነት አካል እንደ መሆናችን ከውጭ የምናገኘው የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ መልእክት የእራሱ ተፅዕኖ ያለው ስለመሆኑ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ሀ ሁ ቢሆንም በእውንና በዋናነት እኛነታችን ከተዘፈቅንበት የግፍና ልክ የሌለው ድህነት አገዛዝ ነፃ የሚያወጣን እራሱ እኛነታችን እንጅ ከቶ ሌሎች አይደሉም ። ሊሆኑም አይችሉም። የገሃዱ ዓለም ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ አይነት መስተጋብር እውነታም ይህ አይደለም።
የመከራችንን ምንጭ በሚገባ የማወቅ እና ከዚህ ለመውጣት ማን/እነማን በእውነተኝነት ፣ በዘላቂነት ፣ በነፃነትና በፍትህ አርበኝነት መሩን ወይም እየመሩን ነው ወይም ሊመሩን ይችላሉ ? የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ በትክክል መመለስ የምንችለው እኛው እራሳችን እንጅ ከቶ ሌላ ሊሆን አይችልም።
“ለእናንተ ሲበዛባችሁ እንጅ ምን አነሳችሁ” በሚል የሚሰጡንን (የሚሸልሙንን) ሽልማት ሁሉ ለምንና እንዴት ? ብለን ሳይጠይቅ ልክ በሌለው የስሜታዊነት ፈረስ መጋለብ ግዙፍና መሪር ዋጋ ከተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እያንሸራተተ የመከራውንና የውርደቱን ሥርዓት ያራዝምብናል እንጅ ከቶ አያሳጥረውም።
የሚጠቅመው አካፋን አካፋ እስከ ማለት በሚደርስ ሃሳዊ ድጋፍ አደንቁረው (ያለመሠረታዊ እውቀት/ትምህርት) ሲገዙት የኖሩትን መከረኛ ህዝብ በስሜት ኮርኳሪ ዲስኩር (ሰበካ) እና እዚያና እዚህ ብልጭና ድርግም እያደረጉ በሚያሳዩት የሸፍጥ ተሃድሶ ፍርፋሪ ስሜቱን እያዋዠቁ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዕት ግብ የማዘናጋት አደገኛ ቀልዳቸውን እንዲተው መንገር ነው። መንገርም ብቻ ሳይሆን መታገልም የግድ ነው።
አዎ! እንደ እኔ ግንዛቤ ትክክለኛው የምሁርነትና የምሁራዊ እውቅት (intellectuality and intellect) ትርጓሜ እውነትን እውነት ብሎና ህብረተሰብን በዚሁ የእውነት መሣሪያነት ታድጎ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን በማስቻል መከረኛው ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመከራና ከውርደት ሥርዓት እንዲላቀቅ ማገዝ ነው። ይህን ግን የስሜታዊነት ፖለቲካችን በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነታ ላይ በሚመሠረት ምክንያታዊነት ካልገራነው እውን የሚሆን አይደለም።