መንግሥቱ ጎበዜ
ሉንድ ዩንቨርሲቲ፣ ስዊድን
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሪዎች በአገር ግንባታ፣ የሕዝብ ትሥሥርና አንድነት በመፍጠር፣ አገርን ከጠላት በመከላከል፣ የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ በመሆን፣ እንዲህ እንደዛሬው አገራዊ ቀውስ ሲፈጠር ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች የነበራቸውን ከፍ ያለ ሚና ከታሪክ እንገነዘባለን። በቀደመው ጊዜ የቤተክርስቲያን አባቶች በአገራዊ ጉዳዮች ከእውነት ጋር የሚቆሙ፣ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ፣ ተናግረውም የሚደመጡ ነበሩ። መሪ እንጅ ተከታይ ፤ ሽማግሌ እንጅ ታራቂ፣ ችግር ፈች አንጅ ችግር ፈጣሪ አልነበሩም። በተለይ ልክ እንደዛሬው ጊዜ የከፋ አገራዊ ቀውስ ሲከሰት የቤተክርስቲያን አባቶች ከፊት በመቆም ነገሮች ፈር እንዳይለቁ፣ አቅጣጫ እንዳይስቱና አገር ችግር ላይ እንዳትወድቅ የከፈሉትን መስዋዕዋትነት የሚመሰክሩ በርካታ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት በዛጉዬ ሥርወ መንግሥት ማብቂያ አካባቢ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ምክኒያት በተከስተው አለመግባባትና ግጭት አገርን ከባድ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ተፈጥሮ ነበር። በመሆኑም የደብረ ሀይቁ ገዳም መስራች አባ ኢየሱስ ሞዓ እና የደብረ ሊባኖሱ አባት አቡነ ተክለ ሐይማኖት ባደረጉት ከፍተኛ መንፈሳዊ ተጋድሎና አባታዊ ጥረት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ በመደረጉ ሊመጣ ይችል የነበረው አደጋ ከስማል።
በጎንደር ዘመነ መንግሥት በካቶሊክ ሚስዮናውያን ሰርጎ ገብነትና በአጼ ሱስንዮስ አዋጅ ምክኒያት የተፈጠረው ከፍተኛ ደም መፋሰስና ትርምስ ሊቆም የቻለው የቤተክርስቲያን አባቶች ባደረጉት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ነበር። በተለይም ደግሞ ከታላቁ የማኅበረ ስላሴ አንድነት ገዳም የመጡ አበው ከአጼ ሱስንዮስ ወደ አጼ ፋሲለደስ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ ተጽእኖ በማሳደር በአገር ላይ አንዣቦ የነበረውን አደጋ በአጭሩ ቀጭተውታል።
የቤተክርስቲያን አባቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት ከመነሻው እስከመጨረሻው፣ ከዘመቻው እስከ ድሉ፣ ከዋዜማው እስከጦርነቱ በመሪነትና በተሳታፊነት ነበሩ፡፡ ለአድዋ ድል መገኘትም የነበራቸው ሚና እጅግ የላቀ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከጾም፣ ከጸሎትና ከመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት ባሻገር እነዚህ አባቶች ሕዝቡን በመቀስቀስ፣ አመራር በመስጠት፣ አብረው በመዝመት፣ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖር በማድረግ፣ በጦርነቱ በመሳተፍ፣ መረጃ በመስጠትና በማስቀመጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
በ1953 ዓ. ም የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ ሊከሰት ይችል የነበረውን አገራዊ ትርምስ በማስቆም በኩል ፓትርያርክ አባ ባስሊዎስ የነበራቸው የላቀ አስተዋጽኦ የሚታወስ ነው።ውጤቱ በፖለቲከኞች ሚዛን በምንም መንገድ ይታይ የቅዱስነታቸው ሚና ግን ጎልቶ የታየበት ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ሁለተኛው ፓትርያርክ ታላቁ አባት አቡነ ቴዎፍሎስ የስልሳ ስድስቱን አብዮት ተከትሎ የመጣው የደርግ መንግስት ሰለባ የሆኑት ከእውነት፣ ከሕዝብና ከአገር ጋር በመቆማቸው ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዛሬስ