እምቢ ለአፋኝ ወታደራዊ አገዛዝ፤ የሽግግር መንግስት አሁን ይቋቋም !!

 

ሸንጎ ሕወሃት መራሹ የኢሕአዴግ መንግስት ያወጀውን ቀጥተኛ ወታደራዊ አገዛዝ እጅግ በጣም አጥብቆ ይኮንናል። አፋኙ ስርዓት አሁንም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ማፌዙን አላቆመም፤ አንድም ሕዝባዊ እንቅስቃሴው ባሳረፈበት ምት ተደናግጦ ግራ ስለተጋባ የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፍቶታል፤ አንድም እንደቀድሞው መግዛት እቀጥላለሁ በሚል ቅዠት ውስጥ እየዳከረ ነው። ትናንት ብሄራዊ መግባባትን አመጣለሁ ብሎ ከወተወተ በኋላ ጥቂት እስረኞችን ለቆ፤ ህዝቡ በደስታ ፈንድቆ ሲጨፍር የረገጠው ሳር እንኳን ቀና ሳይል፤ በማግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር ተብየው ከስራ ተሰናብቻለሁ አሉ፤ እንዲሁም ከአንድ ቀን አዳር በኋላ ኢሕአደግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጌለሁ አለ።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ አካባቢ ላይ በተከታታይ የታዩትን እነዚህን ሶስት ክስተቶች (ጥቂት ታዋቂ እስረኞችን መልቀቅ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ መሰናበትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መለፈፍ) መጠነ ብዙ ተንታኞች በተለያየ መንገድ ተመልክተዋቸዋል። በተለይም የጠቅላይ ሚንስትር ተብየውን ሰንብት ተከትሎ ከዚህስ በኋላ ምን ሊመጣ ይችላል በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ከህብረተሰቡ በርካታ መላ-ምቶች ተሰንዝረው ነበር። ይሁን እንጂ ከአንድ ቀን በኋላ የአንደኛው መላ-ምት ትክክለኛነት እየተረጋገጠ መጣ፤ ይኸውም ሕወሓት መራሹ መንግስት፤ እድሜውን ለማራዘም “ቀጥተኛ ወታደራዊ አገዛዝ” ሊያውጅ ይችላል የሚለው ነው። ለካስ አሉ የሰሞኑን ታንክና መትረየስ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ሲርመሰመሱ ያስተዋሉ ነዋሪዎች፤ ለአገር መከላከያ ተብሎ በህዝብ አንጡራ ሃብት የተገዛ መሳሪያ በከተማ ወስጥ እንደ ሸቀጥ እቃ ሲታይ የዋለው ለካስ ህዝብን ለማስፈራራት ኖሯል። ይኸው እንግዲህ የታኮች ጋጋታም አለፈ፤ ወታደራዊ አገዛዝም በሬዲዮ ፋና ተለፈፈ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ወይ ፍንክች፤ ያው እንድ ትላንቱ ዛሬም በወታደራዊ ሃይል ቢከበብም አልገዛም ባይነቱን እንደቀጠለ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከአንድ ወር ተኩል በኃላ ይሟጠጣል!!!

ግን፤ ግንኮ የስርዓቱ ዘዋሪዎች ያልተረዱት ብዙ ነገር አለ፤ ያላወቁት ብዙ ታሪክ አለ፤ ሁሉንም እዚህ መዘርዘር አስፈላጊ አይደለምና አንድ ሁለቱን መጥቀስ ለአብነት በቂ ይመስልናል። ከዚሁ ካገራችን፤ እስክአሁን ቀጥሎ ካለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ብንጀምር፤ ከሶስት ዓመት ለበለጠ ጊዜ ተቀጣጥሎ የቆየው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እስከ አፍንጫው በታጠቀ ጨካኝና ስበእና የጎደለው ፌዴራል ፖሊስና አጋዚ ጦር እየተገደለ፤ እየቆሰለና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ እየታሰረ ትግሉ ወደፊት እየገፋ፤ አድማሱ እየሰፋ ሄደ እንጂ ወደኋላ በፍጹም አልተመለሰም። አለፍ ብለን ትላንት በግብጽ፤ በቱኒዚያ፤ በሊቢያና ሌሎችም ቦታዎች የነበሩትን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ብንመለክት፤ ህዝብ ባዶ እጁን ወጥቶ ታንክና ሙሉ ትጥቅ ካለው ወታደር ጋር ተፋልሞ ለብዙ ዓመታት ጨቁነው የገዙ አምብገነኖችን ከስልጣን አውርዷል። የኛ አምባገነኖች ያልተረዱትም ይህንን እውነታ ነው፤ ህዝብ ግፍና በደል መሮት ከተነሳ፤ ጨቋኞች የጫኑበትን  ቀንበር አውልቆ ከጣለ፤ አንድ ጊዜ ፍርሃቱ ከለቀቀው፤ አስር ታንክ ቢደረደር፤ አስር አዋጅ ቢለፈፍ ወደኋላ አይመለስም። በኢትዮጵያም የህዝቡ ቁርጠኝነት እዚህ ደረጃ ላይ ስለደረሰ በምንም ተዓምር ጥያቄዎቹ ሙሉ በሙሉ መልስ ሳያግኙ ትግሉ እንድማይቆም ወይም ወደኋላ  እንድማይመለስ አንጠራጠርም።

በርግጥ የሰብዓዊ መብት ረገጣና አስተዳደራዊ ጭቆና ለኢሕአዴግ አዲስ ነገር ባይሆንም፤ የአገሪቱ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በመንግስት በኩል ተስፋ የሚጭር እርምጃ ሲጠብቅ፤ መልሶ መላልሶ የእመቃና የአፈና መርዶ ማድረስ ጎጠኛውን የገዢ ቡድን በቅጡ ለማያውቅ   ህብረተሰብ አስገራሚም አስደንጋጭም ነው። ይሁን እንጂ ልብ ብሎ ላስተዋለ አድማጭ አዋጁ ክቀደሞው የደርግ አስተዳደር በቀጥታ የተቀዳ፤ ለመሳለቅ ሲባል የተጠቀሰ መሰሎ ስለሚሰማ አስደንጋጭ መሆኑ ቀርቶ ወደ ቀልድ ያመዝናል፤ “ያሰበ ያሳሰበ፤ የጻፈ፤ ያነበበ ያስነበበ እያለ ይቀጥላል….”

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወንጭፍና ድራጉኖፍ

አስቡት እንግዲህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፤ ያውም ዴሞክራሲያዊ ነኝ እያለ ከሚንጠራራ ቡድን እንዲህ ያለ ቅሌት ሲፈጸም ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር እጅግ በጣም የወረደ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ሸንጎ አሁንም ለአምባገነኑ ቡድን አንድና አንድ መልእክት ብቻ ነው ያለው፤ ህዝቡ የአፈና አገዛዝ ስላንገፈገፈው ከዚህ በኋላ በተመቸው መንገድ ሁሉ መብቱን ለማስከበር፤ የአገሩን ክብር ለማስጠበቅ እንደሚታገል ግልጽ ነው። መብቱን ለማስከበር ለተነሳ ህዝብ ደግሞ አስር ሺ አዋጅ ቢደረደር እንድማይሰራ ከብዙ አገሮች የተገኙ ተመክሮዎች አሳይተዋል። ኢሕአዴግ ሲጓዝበት የቆየውና አሁንም የሚጓዝበት በሃይል ጨቁኖ የመግዛት አጥፊ መንገድ መቆም አለበት። ሸንጎ ከህባችን ጎን ቆሞ በትግሉ ይሳትፋል፤ በሚችልው ሁሉም ትግሉን ያግዛል። በአገር ውስጥና በውጭ አገር ካሉ አጋሮቻችን ጋር ተባብረን በመታገል የጎጠኝነት ስርዓት እንዲያከትም፤ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና በሰላማዊ አካሄድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ለማስገደድ ቃል እንገባልን።

የህዝባችን ትግል ያሽንፋል !!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!

1 Comment

  1. መፈክሮቻችን ሁሉ ከግል ጥቅም ወይንም ከአደረ ቅያሜ ሳይሆን ከስር መሰረታዊ ጠቅላላው ህብረተሰብ ጥቅምና አገልግሎት አንፃር ለመሆናቸው ማስተዋል ይኖርብናል!

    እኔ በበኩሌ በዴሞክራሲ መፈክር ማጭበርበር ስም ጠበንጃህን አስረክበኝና ከዚያን በኋላ እኔ ልግደልህ ከሚል እርግብ ሁኑልኛና እኔ አይናችሁ እያየ እባብ ልሁንባችሁ ባዮች ጋራ ሆኘ ያለውን ሃይል ለማባረር ዝግጁ አይደለሁም:: ንቃትና ሶሊዳሪቲ ከቂም በቀል ይቅደም፣ ከዚያም ህብረተሰባችን ሁሉ አብረው በሰላምና በመደጋገፍ ጎን ለጎን ሆነው ለመኖር ዝግጁ ሲሆኑ የፈለገው ሃይል መሃከለኛውን ፖለቲካዊ መስተዳደር ይቀበላል::

    ቸር ቸሩን !

Comments are closed.

Share