February 17, 2016
57 mins read

አርጋኖንና እንዚራ፤ ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ – ከሸዋንዳኝ አበራ

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ባቆዩልን እምነትና ሥርዓት መሠረት የራሷ የቅዳሴ፥ የማኅሌትና የዝማሬ ሥርዓት አላት፤ ቅዳሴያችን ማኅሌታችንና ዝማሬያችን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ አቀብሎት ቅዱስ ያሬድ ባስተማረን በግእዝ፥ በእዝልና በአራራይ ዜማ  መሠረት  ቅዳሴውን ካህናትና ምዕመናን በድምጽ ብቻ በመቀባበል፥ ማኅሌቱን ሊቃውንቱ  ለዛ ባለው ቅላጼ በከበሮና በጸናጽል አጅበው እንዲሁም ዝማሬውን መዘምራኑ ከምእመኑ ጋር ጣዕም ባለው ዜማ ከከበሮ ጋር አስማምተው  ሲያቀርቡ ምን ያህል ውብ እንደሆነና የቱን ያህል የውስጥ እርካታ እንደሚሰጥ ለአምልኮ ብቻ የተሰባሰበው ያውቀዋል።

የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን  አገልግሎቶች በሙሉ  ማለትም  ቅዳሴው፥ ማኅሌቱ፥ ዝማሬውና ስብከተ ወንጌሉ አንድ ዓላማ ብቻ ነው ያላቸው፤ እርሱም ምእመኑ ቅዱስ ወንጌልን በሚገባ ተረድቶና ሃይማኖቱን ጠብቆ በእምነትና በምግባር ጎልብቶ በንስሐ ጸድቶ ለቅዱስ ቁርባን እንዲበቃና በእርሱም  እንዲጸና እና ለሰማያዊት ኢየሩሳሌም እንዲበቃ ማድረግ ብቻ እንጂ ለከንቱ ውዳሴ አይደለም። በእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ የቀዳሹ ወይም የዘማሪው መንፈሳዊነት፥ የድርሰቱ ይዘት ማለትም የሚያስተላልፈው መልእክት፥ የዜማው ስልትና የተቀባዩ መንፈሳዊነትና አብሮነት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፤ ከዚህ በተጨማሪ የማጀቢያ መሣርያዎች ኅብር አስፈላጊ ሲሆን አዳማቂ የዜማ  መሣሪያዎችን ከሕዝቡ የዜማ  መሣሪያዎች ውስጥ ተስማሚውን መርጦ መጠቀም ተገቢ ነው፤ እዚህ ላይ  ዘማሪው፥ ድርሰቱ፥ ዜማውና ተቀባዮቹ በፍጹም መንፈሳዊነት ከተቀናጁ የመሣርያ ውሰት ቦታ አይኖረውም ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን።” (መዝ. ፻፶፥፮) እንዳለው ለምስጋና የተፈጠረው ሰው ነው። የዜማ መሣሪያ አስፈላጊነት መዝሙርን ከማድመቅ ያለፈ ጉልህ ስፍራ አይኖረውም።

በመንፈሳዊ ሀብት የከበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፊደል ቀርጻ፥ ብራና ዳምጣ፥ ቀለም ቀምማ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቋንቋችን ጽፋ ያቆየች ለቅዳሴ፥ ለማኅሌትና ለዝማሬ የምነጠቀምባቸውን ዜማና ምልክቶች በማዘጋጀት ለትውልድ እንዲተላለፍ ልጆቿን ያስተማረች የእምነት ቤት ብቻ ሳትሆን የማንነታችን መገለጫም ናት። ባህላዊ ቅርሶቻችን የሆኑት በገና፥ ክራር፥ ማሲንቆ፥ ዋሽንት፥ ከበሮና ጸናጽል እንዲሁ በራሳቸው  ማንነታችንን ይመሰክራሉ፤ ለያሬዳዊ ዜማዎችም እጅጉኑ ምቹ ሲሆኑ አንዳንድ ወገኖች አሁን ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች ጥንተ ማንነት ላይ ጥያቄ አለን ሊሉ ይችላሉ፥ እንዲሁም ዘመን ባፈራቸው የውጪ የዜማ መሣሪያዎች ብንጠቀም ምን አለበት? ሊሉ ይችላሉ፤ ጥያቄው አሁን የኛ ናቸው የምንላቸውን መሣሪያዎች መጀመሪያ እነማን ተጠቀመባቸው? ከየትስ መጡ? የመሳሰሉትን ማንሳት  ሳይሆን ዛሬ ላይ በሕዝቡ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ዜማዎች ላይ እና  ስነ ልቦና ውስጥ ያላቸውን አዎንታዊ ተጽእኖ፥ የሃገሪቱ ብሔራዊ ቅርስነት ወዘተ… አንጻር ነው  መታየት ያለበት።

እያንዳንዱ ሀገርና ሕዝብ የራሱ መገለጫ ልዩ ልዩ ምልክቶች አሉት፥ ኢትዮጵያችንም እንደ ሃገርነቷ የምትታወቅባቸው ልዩ  የራሷ የሆነ ባህል አላት ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ ከሕዝቡ ባህል ጋር የተቆራኘ የመገልገያ የዜማ መሣሪያዎች አሏት እነዚህም ዜማና የዜማ መሣሪያዎች የማንነታችንም አሻራ ስለሆኑ ለመጪው ትውልድም  እንዲተላለፉ ማድረግም ሃይማኖታዊና ሃገራዊ ኃላፊነታችንና ግዴታችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም። አጠር ባለ አገላለጽ ለእኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትገለገልበት  ያሬዳዊ ዜማ እና ሃገር በቀል የዜማ መሣሪያዎቻችን የማንነታችን መገለጫዎችና ማንም ባሻው ጊዜ ሊያጠፋው የማይችለው  የታሪክ አሻራችን ናቸው፥ ያሬዳዊ ዜማችን ከነምልክቱ እና ሃገር በቀል የማጀቢያ መሣሪያዎቻችን ብሔራዊ ቅርሶቻችን ናቸው፥ አባቶቻችን ጠብቀው አቆይተውልናል እኛም በተራችን ይህን አኩሪ የማንነት አሻራ ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ ኃለፊነትን በወጉ የምንወጣ እንጂ የትውልድ አደራ በሊታዎች መሆን የለብንም።  ቅዱስ መጽሐፋችንም ላይ “አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ።” (ምሳ. ፳፪፥፳፰) ተብሎ እንደተጠቀሰው ድንበር አፍራሽ ሲመጣ ተው ተመለስ ማለት ይገባናል፥ እዚህ ላይ የራስን ጥሎ የሰውን ማንጠልጠል ዘመናዊነት የሚመስላቸው የዋሆች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ማስተማርም የእውነተኛ አባቶች ኃላፊነት ነው።

ዘመናችን ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ተዳክሞ  በቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ያየለበት፥ ዓላማችን ሰማያዊ መሆኑ የተዘነጋበት፥ መንፈሳዊነት በጀብደኝነት ተተክቶ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ ቤዛ ሆኖ የመሠረታት አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች ለፈተና የተዳረገችበት ጊዜ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አለመታደል ሆነና ዛሬ እንደ ዘመነ መሳፍንት በየቀጠናው አለን አለን በሚሉ የጎበዝ አለቃ አባቶች መከፋፈሏ ሳያንስ፥ ስለ አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልና  ስለ አንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሰባኪ ከእኛ በላይ ለአሳር ያሉና በየጎጡና በየስርቻው በገሃድና በኅቡዕ ራሳቸውን  ያደራጁ ወገኖች በነጻ የተሰበኩትን ቅዱስ ወንጌል በነጻ መስበክ ሲገባቸው ቃሉን በመቆነጻጸል የሚሸቅጡ፥ ከመቼውም በላቀ ሁኔታ የማያንጽ የሚያደናግር መንገድ የተከተሉ፥ ፍቅርንና እውነትን ሳይሆን ጥላቻና አሉባልታ የሚያስፋፉ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዓት የሚንድ አዲስ ትምህርት ይዘው ምእመኑን የሚበትኑ፥ አላስፈላጊ ርእሶችን በማንሳት ማስተማር ሳይሆን ማወዛገብ የተያያዙ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉ የአስቆሮቱ ይሁዳ ልጆች በየአድባራቱ ሲታዩና ሲስፋፉ በወንጌል ታጥቀን የቤተ ክርስቲያናችንን እምነትና ሥርዓት እንዲሁም የልጆቿን ሁለንተናዊ አንድነት መጠበቅ ሲገባን በነገሮች ሁሉ ምን አገባኝ፥ ምን አለበት? በማለት ሁላችንም የማፍረስ ድርሻችንን እየተወጣን ያለን በደለኞች መሆናችንን የተረዳነው  አይመስለኝም።

አይ ዘመን ስደት ከሃገር፥ ስደት ከማንነት… ያሁኑ ይባስ ያጽናኑናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸው ባለመስቀሎች  ከማንነታችን ሊያሰድዱን ላይ ታች ሲሉ ማየት  የከፋ ዘመን…  ግልገሎቹን ከበረት አባሮ ለቀበሮ የሚሰጥ እረኛ የሰለጠነበትና ለመንጋው አሳቢ የተጠላበት ዘመን፥ ክርስቶስ ሳይሆን ጥቅም የነገሠበት፥ ለሁለት አምላክ መገዛት፥ ጎጠኝነትና ጠባብ አመለካከት የገነነበት፥ ኑፋቄ የተስፋፋበት ዘመን፥ መተራረም ሳይሆን መጠላለፍ የተለመደበት፥ በልጁ ላይ ጥላቻና አሉባልታ የሚያናፍስ አባት፥ አባቱን በአደባባይ የሚያዋርድ ልጅ የታየበት ዘመን፥ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አንደበቱ ያለተገራ ትውልድ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቈላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።” (ሮሜ ፲፮፥፲፯-፲፰)። ያለውን በገሃድ ያየንበት ዘመን…።

ወደ ተነሣሁበት ርዕስ ልመለስና ምን ጊዜም ስለ አንድ ነገር ስናወራ ወይም ስንጽፍ በነጥላ ትርጉሙ ወስደን ሳይሆን ቃሉን አግባብ ባለው ዓረፍተ ነገር እና አገባቡን ጠንቅቀን ስናውቅ ብቻ መሆን አለበት፤ ይህን ለመጻፍ ያስገደደኝ ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ የሰማነው አንድንነታችንን የሚሸረሽርና ማንነታችንን የሚያጠለሽ ጉዳይ ነው። በቅርቡ በአራተኛው ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመራውና ራሱን ሕጋዊ ሲኖዶስ የሚለው በተለምዶ ስደተኛው ወይም የአሜሪካው ሲኖዶስ ፀሐፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ መልኬ ጼዴቅ ቤተ ክርስቲያን በኦርጋን ስትጠቀምም እንደነበር ገልጸው አሁን ሁሉም እንዲጠቀሙና ካህናትም በመሣርያው ለመጫወት መለማመድ እንዳለባቸው መመሪያ በመስጠታቸው የዘንድሮው ፳፻፰ ዓ.ም. የጥምቀት በዓል አሜሪካ ባሉ አባቶች በሚመሩት ደብሮች የቤተ ክርስቲያን መዘምራን በኦርጋን ታጅበው ሲዘምሩ፥ እንዲሁም በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለብሰ ተክህኖ የለበሱ  ካህንን በመስቀልና በጽና ምትክ አኮርዲዮን ታቅፈው ሲጫወት የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ የወሬ አውታሮች ተለቀው አይተናል።

እንደሚታወቀው አሜሪካ ያሉ አባቶች የቤተ ክርስቲያናችንን ዝማሬ በአውሮፓውያኑ ኤሌክትሮኒክ ኦርጋን ማጀብ ከጀመሩ ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ  አስቆጥረዋል። ከዚህ ቀደም ሲልም አፍቃሬ ኦርጋን በሆኑ ግለሰቦችና አርጋኖን የተሰኘው ቃል ትርጉም ግልጽ ባልሆነላቸው ወገኖች አካባቢ በኦርጋን መጠቀም የሚከለክል ሁኔታ አለመኖሩን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተለያዩ ጦማሮች በየድረ-ገፁ ማስነበብ ከጀመሩ ቆየት ብለዋል፤ “አርጋኖን” የምትለዋን ቃል ከብሉያትና ከሊቃውንት መጻሕፍት በመልቀም በሰፊው ጠቋቁመውናል፥ ስለ ትጋታቸው አድናቆቴን እቸራቸዋለሁ። ግን ለምን ይኸን ያህል ደከሙ? በእርግጥ አርጋኖን ማለት ኦርጋን፥ እንዚራ ማለት አኮርዲዮን ማለት መሆኑን አምነውበት ነውን? ወይስ ቤተ ክርስቲያን ለመዝሙር አጃቢነት የምትጠቀምበት መሣሪያ አጥታ ወይስ አንሷት ነውን? ወይስ መዝሙር በኦርጋን ቢታጀብ የሚያገኙት ልዩ ጥቅምና የሚያተርፉት ትርፍ አለን? ገና ብዙ እናያለን በመጽሐፍ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ ይህን በፊት እወቁ፤” (፪ኛ ጴጥ. ፫፥፫) ተብሏልና።

በመጀመሪያ የታሪክና የስነ ልሳን መዛግብት ስለ አርጋኖንና ስለ እንዚራ ምን ይሉናል? በእርግጥ በአሁኑ ዘመንስ እነዚህ መሣሪያዎች አሉ? የሚለውን እንመልከት፤ አርጋኖን ፦ (በግሪክ Organon ኦርጋኖን፥ በላቲን Organum ኦርጋኑም፥ በዕብራይስጥ Ugab ዑጋብ፥ በእስፓኞል Organo ኦርጋኖ፥ በዐረብኛ Arqenun አርቀኑን፥ በፋርስ Urghun ዑርጉን) ተብሎ የሚታወቀው ቃል ትርጉም ምን ማለት ነው?  በእንግሊዝኛው Organ  የተሰኘው ቃል እንደ ቃሉ አገባብ አራት ያህል የተለያየ ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፦ ሀ፦ የሰውነት ክፍል ወይም ብልት፥ ለ፦ ልሳን ወይም መገናኛ ዘዴ እንደ ጋዜጣ መጽሔትና በራሪ ወረቀት የመሳሰለ ሐ፦ አንድ ዓላማ ያለው ቡድን ወይም ተቋም  መ፦ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ በጥቅሉ Organ ሲሰኙ ወደ ተነሳንበት ርዕስ ስንመለስ ደግሞ የሙዚቃው ክፍል ብቻ እንዲሁ የተለያየ ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን ለምሳሌ ሀ፦ በውዥሞ ውስጥ በሚያልፍ አየር ግፊት ድምጽ የሚፈጥር በእጅ ጣትና በእግር በመጫን የሚጫወጡት መሣሪያ፥ በአሜሪካ (pipe organ) የሚሉት፤  ለ፦ ድምጹ እንደ ክላርኒርትና ፓይፕ ኦርጋን የሆነ በንፋስና በአውታር የሚሠራ (reed organ ወይም church organ)፤ ሐ፦ እንዲሁም በአጠቃቀም ወይም በድምጽ ፓይፕ ኦርጋንን የተኩ እንደ ኤሊክትሮኒክ ኦርጋን ያሉ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች፤  በማለት የእንግሊዝኛውና የእስፓኝ (ስፓኒሽ) መዝገበ ቃላትም ተመሳሳይ ትርጉም የሰጣሉ።

እዚህ ላይ የሁሉም የወል ስም አንድ ኦርጋን ቢሆንም ሁሉም የየራሳቸው የተለያየ ስም አላቸው በአሠራርም በጣም ይለያያሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም አርጋኖን እያሉ ይጠቀሙበት የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ብቻ ናቸው። አሁን አሜሪካ ባሉ ደብሮች ለመጠቀም ተፈቀደ የተባለው ሦስተኛው ማለትም ፓይፕ ኦርጋን እና ቸርች ኦርጋንን በተካው ኤሌክትሮኒክ ኦርጋን  ነው፤ ይህን መሣሪያ የሚጠቀሙባቸው በአብዛኛው ከ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ በተሀድሶ ስም ከሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተለይተው የወጡት ቡድኖች ሲሆኑ እነርሱም በኦርጋን ጀምረው ወደ ሙሉ የባንድ መሣሪያ በመሻገራቸው በአሁኑ ጊዜ በዓለማዊ ዘፈንና በመንፈሳዊ መዝሙር መሃከል ያለውን ልዩነት ሙሉ በሙሉ አጥፍተው አማኙን ግራ እያጋቡት እንደሆነ እያየን ነው።

ይህን የኛዎቹ ዱሮ ማለትም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ጊዜ ጀምሮ በመዲናችን እንጠቀምበት ነበር የሚሉት ኦርጋን በአሜሪካ የሚገኙት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን “ድምፁ መንፈስን የሚረብሽ፥መንፈሳዊነት የጎደለው ወዘተ… በማለት” ከቤተ ክርስቲያን እንዲወገድ  ካስፈለገም ጥንታዊው Pipe Organ  ወይም Church Organ  ብቻ በአገልግሎት ላይ እንዲውል ፊርማ አሰባስበው በአሜሪካ ለግሪክ ኦርቶዶክስ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዲሚጥሮስና ለስምንቱ ሜትሮፖሊታን አቤቱታ አስገብተዋል። (ለማረጋገጥ በዚህ ርዕስ Google ላይ ቢፈልጉት ያገኙታል Abolish the use of Electronic “Organs” in Greek Orthodox Churches)

ዛሬ ካለስሙ ስም ሰጥተው አርጋኖንን ኦርጋን ነው፥ እንዚራን አኮርዲዮን ነው በማለት የሚከራከሩት መሳሳታቸውን መስማት የማይፈልጉ፥ ስህተታቸውንም ከማረም ይልቅ ሃያሲያቸውን ሁሉ የአንድ ማኅበር አባል ነው ብለው በጅምላ ስም የሚለጥፉ እውነትን ሳይሆን እልህን የተጎናጸፉ ወገኖቻችን ትላንት በፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነትና በአባቶች የሥልጣን ሱስ መነሻነት በውግዘት የተለያዩትን አባቶች ተገን በማድረግ ልዩነቱን በማስፋት ዛሬ የቀኖና ልዩነትን እንደተከሉ ሁሉ ነገ ደግሞ የዶግማ ልዩነት በመፍጠር ዳግም አንድ ላይሆኑ ተማምለው እንዲለያዩ ቀን ከሌሊት እየሠሩ መሆኑን ግብራቸው ይመሰክራል።

እዚህ ላይ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር በኦርጋንም ሆነ በአኮርዲዮን፥ በሳክስፎንም ሆነ በጊታር፥ በክራርም ሆነ በማሲንቆ፥ በበገናም ሆነ በከበሮ፥ በዋሽንትም ሆነ በእንቢልታ መዘመር በራሱ ጽድቅም ሆነ ኵነኔ ሊሆን አይችልም፤ እግዚአብሔር የሚያየው የመሣሪያ ጋጋታ ሳይሆን ሽንገላ የሌለበት ንጹህ ልብን፥ ንጹህ አንደበትንና እውነተኛ አምልኮን ብቻ ነው። እዚህ ላይ ስለ ዜማና የዜማ መሣሪያዎች ስናነሳ አብሮ ማታየት የሚገባው ሕዝቡ  በመንፈሳዊም ሆነ ሕዝባዊ በዓላት ላይ የሚጠቀምባቸው ዜማ እና የዜማ መሣሪያዎች ምንነት፥ ስለ ሕዝቡ ባህልና ስነልቡና አመለካከት፥  ዜማው ወዴት ያመራል?  ያንጻል ወይስ ይረብሻል? ወደ መንፈሳዊነት ይስባል ወይስ ያሸፍታል? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ማጥናትና መቃኘት ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው ከዓመታት በፊት በሃገራችን አንዳንድ አድባራት ማለትም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በሌሎችም በጣት በሚቆጠሩ ጥቂት አድባራት ውስጥ ኤሌክትሮኒክ ኦርጋን የነበረና ከመዝሙርም አልፎ በቅዳሴም ወቅት መጠቀም ተጀምሮ ነበር፤ የክብር ዘበኛና ጦር ሠራዊት ኦርኬስትራም  በኦርጋን ብቻ ሳይገደቡ ባላቸው ሙሉ የኦርኬስትራ መሣሪያ እየታጀቡ መንፈሳዊ ዜማ ያዜሙ ነበር። በወቅቱ የሙዚቃ መሣርያውን እንተወውና አጠቃላይ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የማይቀበሉትን የካቶሊካውያን ሥርዓት የሆነው ሃውልት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐጸድ  ተቀርጾ ሲተከል (የአራቱ ወንጌላውያን ሃውልቶች) አባቶች ቢቃወሙም ሰሚ አልተገኘም፤ ለሁሉም ጊዜ አለውና ካለቦታቸው  ተደንቅረው የነበሩት የአውሮፓ የሙዚቃ መሣሪያዎች (የባህል ወራሪዎች) በሃገራችን ከሚገኙት አድባራት በአባቶች ትጋት ተወግደዋል። (ኦርጋንና አኮርዲዮን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የቀረው በእነገሌ ውሳኔ ነው የሚሉት ባዶ ተረት ነው፥ ባይሆን እንኳ አፈጻጸሙ ላይ እንዲተገበር ተሳትፎ ነበራቸው ቢሉ ወደ እውነት ጠጋ ይሉ ነበር።)

አርጋንና አኮርዲዮን ለአጭር ጊዜ የተወሰነ ቦታ በአገልግሎት ላይ የነበረ መሆኑን እየጠቀስን እንደገና ይመለስ፥ ይስፋፋ ከማለታችን በፊት መዝሙር በምእመናኑ ዘንድ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቶ ከዕለት ዕለት ሕይወቱ ጋር የተቆራኘው  የተወሰኑ አድባራት ሰንበት ትምህርት ቤቶችና መዘምራን ያኔ በኦርጋንና በፒያኖ በዘመሩበት ወቅት ወይስ አሁን በባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች በተቀነባበረበት ጊዜ? መዝሙራትን ከገበያ አንጻር ሊሚያዩት ወገኖች በገብያ ላይ ተፈላጊው በኦርጋን ወይስ በክራር፥ በማሲንቆ፥ በዋሽንትና በከበሮ የተቀነባበረው? የሚሉትንና የመሳሰሉትን በንጹህ ልቡና መመልከት ይኖርብናል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  የሕዝቡ የመዝሙር ፍላጎት እየጨመረ የመጣው መጤው ፒያኖና ኦርጋን ተወግደው በራሳችን ባህላዊ የዜማ መሣሪያ መቀነባበር ከጀመረ በኋላ መሆኑን ጠላት ሳይቀር የሚመሰክረው ሃቅ ነው።

ይህ የሚያሳየን ሕዝባችን በያሬዳዊ ዜማና በባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ላይ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ሲሆን በሂደቱም ውስጥ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ጳጳሳት፥ ሊቃውንት ካህናትና  መዘምራን በጋራና በግል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ውጤት መሆኑን የማይረዳ ካለ  አሰላለፉ ከወዲያኛዎቹ የሆነው ብቻ ነው። በኦርጋንና በአኮርዲዮን ከዚህ በፊት ስለተጠቀምንና መሣሪያውም ዘመናዊና ዓለም አቀፋዊም ስለሆነ ዛሬ እነዚህ መሣሪያዎች ወደቀደመ ስፍራቸው ይመለሱ እንዲያውም ቢስፋፉስ ምናለበት እንደተባለው ሁሉ ነገ ደግሞ በአጼ ሱስኒዮስ ጊዜ ሁለት ባሕሪን ተለማምደን ነበር የምዕራቡም ዓለም ያመነበት ነውና ዛሬ ብንመለስበት ምን አለበት እንዳይባልም እፈራለሁ።

እስኪ ስለ አርጋኖንና እንዚራ የስነ ልሳን ሊቃውንት በልሳነ ክልኤ መዝገበ ቃላት የሰጡትን ትርጉም እንመልከት፦ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከ፲፱፻፳፱ በፊት ጽፈውት በ፲፱፻፵፰ በታተመው መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሀዲስ አርጋኖን፦ “ኪታራ፥ ሙዚቃ፥ የዘፈን የማኅሌት ዕቃ፤ መዝሙር፥ በገና፥ ውዳሴ፥ ምስጋና፤  መልካም ዜማ ለዦሮ ለልብ የሚጣፍጥ፤ ደስ የሚያሰኝ ድምጥ።”  ይሉና Pipe organ ምስል ያሳያሉ። የአርጋኖንን ትርጉም ሲገልጹ መጀመሪያ የጠቀሱት ”ኪታራ” የግሪክ ቃል ሲሆን Kithara ማለት በእንግሊዝኛው ጊታር (Guitar) ማለት ነው።  ከዚህ የምንረዳው አርጋኖን ባለአውታር መሣሪያ መሆኑን ሲሆን በሌላም በኩል የሙዚቃ መሣሪያ፥ ምሥጋና እና መልካም ዜማ በማለት ሦስት ትርጉም እንዳለው እንገነዘባለን።  እንዲሁም እንዚራ፦ “ንዋየ ማኅሌት፤ የሚነፋ፥ የሚመታ፥ የሚደረደር ክራር በገና ሙዚቃ የመሰለ ሁሉ” ይሉና የክራር ምስል አስቀምጠዋል።

ደስታ ተክለ ወልድ ያማርኛ መዝገበ ቃላት በ፲፱፻፶ የታተመው ላይ  አርጋኖ፦ የዜማና የዘፈን ማሣርያ ፥ ባለሰባት ረድፍ፤ የመጽሐፍ ሥም፥ የጸሎት መጽሐፍ የኢትዮጵያ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሱ በመቤታችን ስም የደረሱት። በብዙ ቁጥር ሙዚቃዎች፥ መጽሐፎች ይሉናል። የሙዚቃ መሣርያና መጽሐፍ በማለት ሁለት ትርጉም ሰጥተውታል።

ከሳቴ ብርሃን ተሰማ ሀብተ ሚካኤል በ፲፱፻፶፩ በታተመው የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ  አርጋኖን፦ ከነሐስ፥ ከብረት ከእንጨትም እየተሠራ በልዩ ልዩ ድምጽ የሚአነዝር እንዚራ ፥ በገና፥ ሰላምታ፥ የበገና ድርድር፥ የበገና ሰላምታ፣ የጌታ የኢየሱስን እናት ማርያም ድንግልን አባ ጊዮርጊስ ምሥጋና ያመሰገበት መጽሐፍ ይሉና የአኮርዲዮን (Accordion) ምስል አስቀምጠዋል። ለአርጋኖንና እንዚራ አንድ ዓይነት ፍቺ ሰጥተው የዜማ መሣሪያ፥ ድምጽና መጽሐፍ በማለት ሦስት ትርጉም ሰጥተውታል።

ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ለአራተኛ ጊዜ ፳፻፯ በታተመው ሕያው ልሳን ግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ አርጋኖን፦ ምስጋና መዝሙር፥ በገና የሙዚቃ የክር መሣሪያ በማለት ይፈቱታል።   የዜማ መሣሪያና በቁሙ ምስጋና በማለት ባለ አውታር እንደሆነ አስቀምጠዋል። እንዲሁም እንዚራ፦ አንዘረ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን “ነዘረ፦ መታ፥ ነዘረ፥ ናረ። መታ፥ ነፋ፥ ጮኸ፥ አንዘረ፦ አስመታ፥ አስጮኸ፥ ቀነቀነ፥ አዘመረ ብለው ይፈቱታል።

በአጠቃላይ አርጋኖን የሚለው ቃል አራት ትርጉም  መያዙን እንረዳለን እሱም፦ ሀ፦የባለ አውታር ሙዚቃ መሣሪያ  ለ፦በቁሙ  መዝሙር፥ ምስጋና  እንዲሁም  ሐ፦ የድምጽ ዓይነት መልካም ዜማ እና መ፦ የምስጋና ወይም የመዝሙር መጽሐፍ ማለት ነው። እንዚራ ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያ ሆኖ ሳለ አለቃ ኪዳነ ወልድ ባለ አውታር በማለት ክራር እና የመሰለው ብለው ሲፈቱት፥ ከሣቴ ብርሃን ተሰማ አኮርዲዮን ብለውታል። እዚህ ላይ የመዝገበ ቃላት አዘጋጆቹ እንዚራን በተመለከተ ተመሳሳይ ፍቺ አላስቀመጡም፥ እኛ የትኛውን እንከተል? ወይስ እንደዘመኑ ብዙኃኑን? (በአዲሱ አማርኛ አብላጫውን) ወይስ ውጪ ቀመስ የሆኑ ሰዎች የተናገሩትን? እንደ በገና ባለአውታር የሚያነዝር? እንደ ማሲንቆ (የሚመታ)፥ እንደ ዋሽንት የስትንፋስ (የሚነፋ)፥ ወይስ አኮርዲዮን?

አርጋኖንና እንዚራ የሰኙት ቃላት በቅዱስ ያሬድና በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰቶች ውስጥ ተጠቅሰዋል፤ ትርጉማቸውንም ለማወቅና ለማሳወቅ ከዚያን ዘመን እና ቃሉ ከተጠቀሰበት ዓረፍተ ነገር በማነጻጸር ተስማሚና ትርጉም ሰጪ እንዲሆን አድርገን እንጂ ለራሳችን በሚመቸን መልኩ መሆን የለበትም ለምሳሌ፦  “ሰባኬ ወንጌል ዮሐንስ አርጋኖነ ትንቢት ዘይደምጽ ለቤተ ክርስቲያን” የሚለውን ዓረፍተ ነገር “የወንጌል ሰባኪ የሆንከው ዮሐንስ መልካም የሆነውን የትንቢት ቃል ለቤተ ክርስቲያን ያሰማል።” ወይም “የወንጌል ሰባኪው ዮሐንስ ለቤተ ክርስቲያን ትንቢትን የሚያሰማ መጽሐፍ ነው።” በማለት መተርጎም ሲገባቸው ሰባኬ ወንጌል ዮሐንስ ለቤተ ክርስቲያን መልካም ድምጽ የምትሰጥ በትምህርትህ የምትመስጥ ኦርጋን ነህ”?  ብለው የሚተረጉሙም አሉ፥ በዚህ ዓረፍተ ነገር የአርጋኖን ትርጉም እንደ ቃሉ አገባብ ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ ፍርዱን የማያዳላ አእምሮ ላላቸው ለቋንቋ ሊቃውንት እተወዋለሁ።

የሰው ልጅ በሙዚቃ መሣሪያዎች መጠቀም የጀመረበት ዘመን እንደየአካባቢው ይለያያል፥ ጣኦታትንና ገዢዎችን ለማመስገኛ፥ ራስን ለማስደሰቻ፥ እግዚአብሔርን ለማመስገኛ ይጠቀሙባቸው እንደነበሩ ከታሪክ እንረዳለን። ዛሬ ወቅታዊ የመነጋገሪያ ርዕስ ወደ ሆነው አርጋኖን ነው ስለሚሉት የኦርጋንን ታሪክ ስንመለከት በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ በውኃ የሚሠራ አርጋኖን (Water Organ) ከጌታ ልደት በፊት ከ፪፻፹፭ እስከ ፪፻፳፪ በግብፅ አሌክሳንድሪያ ሙዚየም ኃላፊ የነበረው ግሪካዊው Ctesibius  ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈለስፈው በማከታተልም ብዙ ጠቢባን በማሻሻሉ በኩል ተጠብበውበታል። የዛሬው ኤልክትሮኒክ ኦርጋን የጥንቱን ዋተር ኦርጋን፥ ፓይፕ ኦርጋንና ሪድ ኦርጋንና የመሳሰሉትን በመተካት በግሪጎሪያውያን አቆጣጠር በ፲፱፻፴፬ ጀምሮ ሲመረት በአሁኑ ጊዜ ያለው አሥራ አምስተኛው ስሪት ዲጂታል ኦርጋን ደግሞ በግሪጎሪያውያን ቀመር ከ፲፱፻፸ ጀምሮ ወደ ገበያ ብቅ ሲል፥ አኮርዲዮንም እንዲሁ ቱላ በተሰኘች የሩሲያ መንደር  Timofey  በተባለ ሰው በነርሱ አቆጣጠር በ፲፰፻፳ ተፈልስፎ በተከታታይ ዓመታት በሌሎች የሩሲያና የጀርመንና የፈረንሳይ ከተሞች ተሻሽሎ ዛሬ ላይ አምስተኛው ስሪት ፒያኖ አኮርዲዮን የተሰኘው በብዛት ተመርቶ ገበያውን እንዳዳረሰው ታሪክ ያስረዳናል።

እዚህ ላይ  እንዚራ አኮርዲዮን ነው እንዳይባል እንዚራ በማለት ቅዱስ ያሬድ “ወስምዐ በህየ ቃለ እንዚራ ወቃለ አርጋኖን ወቃለ መሰናቅው እንዘ ይሴብሕዎ ወይዌድስዎ ወየአኵትዎ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር በስብሐት ወበማኅሌት በቅኔ ወለልዑል ዜማ ነግሀ ወሠርከ ይሴብሕዎ ለንጉሥ ዐቢይ በዓውደ መንበሩ ቅዱስ….  “ በማለት የጻፈው በ፭፻፴፬ ዓ.ም. አካባቢ ሲሆን ኢለክትሮኒክ ኦርጋን ከመፈልሰፉ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዘጠና አራት ዓመታት በፊት እና አኮርዲዮን ወደ እዚህ ዓለም ብቅ ከማለቱ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ስምንት ዓመታት በፊት መሆኑ፥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት መዝሙሩን የደረሰውና በዑጋብ አመስግኑት ያለው አርጋኖን ከመፈልሰፉ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት፥ ኦርጋን ከመሠራቱ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመታት በፊትና አኮርዲዮንም ከመፈልሰፉ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ዓመታት በፊት በመሆኑ ዑጋብ  ማለት ኦርጋን እንዲሁም አኮርዲዮን ማለትም እንዚራ ማለት አለመሆኑን ዘመን በራሱ ምስክርነቱን ይሰጣል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍትን እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።” (፪ኛ ጴጥ.፫፥፲፮) በማለት ያስተላለፈው  መልእክት ልብ ይሏል።

ኦርጋን በቅዱሱ መጽሐፍ ተጠቅሷል ስለሚሉት፦ በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የጥንቱ ትርጉም  “King Jemes version” ውስጥ አራት ጊዜ “Organ” የሚል ሥም ሲገኝ ይኸውም፦ ዘፍ. ፬፥፳፩  የአማርኛው መለከት ብሎ ሲተረጉመው ኢዮብ ፳፩፥፳፩ እና ፴፥፴፩ እንዲሁም መዝ. ፻፶፥፬ ደግሞ እምቢልታ የሚል ሲሆን  በፊት ኦርጋን ተብሎ የነበረው ቃል በአዲሱ  ኪንግ ጀምስ ትርጉም ላይ  ፍሉት  “flute”  (ዋሽንት) ተብሎ እናገኘዋለን። በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው የዕብራይስጡ ዑጋብ የተሰኘው መሣሪያ ትርጉም ለምሳሌ፦ መዝ. ፻፶፥፬  በግእዝ፦ “ሰብሕዎ በአውታር ወበእንዚራ።”  በአማርኛ “በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት::” በትግሪኛ “ኣውታርን እምቢልታን ኣመስግንዎ” በእንግሊዝኛ ቆየት ባለው ትርጉም፦ “praise him with stringed instruments and organs.”  (በክር መሣሪያና በኦርጋን አመስግኑት”) በተሻሻለው ትርጉም፦ “praise him with pipe and strings. (“በፓይፕ” በውዥሞ እና በአውታር አመስግኑት) Psl.150;4 (King James Version) በአዲሱ ትርጉም፦ “praise him with stringed instrument and flutes.” (በአውታር መሣሪያና በዋሽንት አመስግኑት) (New King James Version) በላቲን አሜሪካ እስፓኝ፦ Alabenlo con mandolinas y flautas.  (Salmos 150:4) (Spanish latin America)  (በማንዶሊንና” በክር መሣርያና በዋሽንት አመስግኑት)  በእስፓኝ፦ Albadle con flautas e instrumentos de cuerda! (Spanish) (በዋሽንትና በክር መሣሪያ አመስግኑት) በማለት እያስተካከሉት መጥተዋል።

የትንፋሽ መሣሪያው ዑጋብ አርጋኖን በግብጽ አሌክሳንድሪያ በግሪካዊ ጠበብት ከመፈልሰፉ ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ በእስራኤልና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በአገልግሎት ላይ የነበረ ሲሆን በሌላም በኩል አርጋኖን ደግሞ ባለ አውታር የዜማ መሣሪያ ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰው መዝ. ፻፶፥፬ ላይ በዕብራይስጡ ዑጋብ፥ በግእዝ እንዚራ የሚለውን አማርኛውና ትግሪኛው እምቢልታ ሲለው እንግሊዝኛውና እስፓኛው ዋሽንት ይሉታል። ከ፲፫፻፶፯ እስከ ፲፬፻፲፫ የነበሩት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ  “እለይነፍሑ እንዚራተ”  ማለታቸው እንደ ዋሽንት፥ መለከትና እምቢልታ የመሰለ የትንፋሽ መሣሪያ ለመሆኑን ያረጋግጣል።  ከነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደምንረዳው ዑጋብ፥ እንዚራ፥ መለከት፥ እምቢልታ፥ ዋሽንት ተመሳሳይ የትንፋሽ መሳሪያዎች መሆናቸውን እንጂ ዑጋብ ኦርጋንም ሆነ አኮርዲዮን አለመሆኑን ነው።

እዚህ ላይ አርባ ስድስቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከጌታ ልደት በፊት ፪፻፷ አካባቢ በአሌክሳንድሪያ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ሰባ ሊቃውንት ሲተረጎሙ  ዕብራይስጡ ዑጋብ ያለውን ተመሳሳይ መሣሪያ በግሪኩ ባለማግኘታቸውና በወቅቱ የነበረው የመጀመሪያው ዋተር ኦርጋን ከዑጋብ ጋር በሚያወጣው ድምጽ በመጠኑ ስለሚመሳሰል ዑጋብ የሚለውን አርጋኖን ብለውት ነበር፥ በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በታተመው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ግሪኩን በመከተል ኦርጋን ሲሉት ኋላ ላይ የኦርጋን “አርጋኖን” አሠራር ከመጀመሪያው በጣም እየራቀ የበፊቱ እየተተወ በአዲስ ዓይነት እየተተካ ልዩነት ስለሰፋ ከዑጋብ ጋር በመጠኑ በሚመሳሰለው በዋሽንት ተክተውታል።

ኦርጋን በእንግሊዝኛው በአጠቃላይ የብዙ የሙዚቃ መሣርያዎች የወል ስም ነው። keyboard  የጣት ገበታ የሙዚቃ መሣሪያ  እና በአውታር የሚሠራ እንደ Water Organ, Pipe Organ ቸርች ኦርጋን (Church Organ) እና ፒያኖ ያሉ፥ በትንፋሽ የሚሠራ እንደ ሀርሞኒካ ያሉ (Mouth Organ)፥ በአየር የሚሠሩ እንደ አኮርዲዮን (Accordion) እና ሪድ ኦርጋን (Reed Organ) እንዲሁም አዲሶቹን ኤሌክትሮኒክ ኦርጋን፥ ዲጂታል ኦርጋን እና ሌሎችንም ያጠቃልላል። አርጋኖን  ኦርጋን እንዚራም አኮርዲዮን ማለት አይደለም። አርጋኖን ጥንታዊ ባለአውታር የሙዚቃ መሣሪያ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ምናልባት በጥንታዊ መዘክሮች (ሙዚየም) ካልሆነ በቀር አይገኝም ዛሬ አርጋኖን ነው በማለት ካለስሙ ስም ሰጥተው የሚከራከሩበት ኦርጋን በጽርዕ (በግሪክ) ኢሌክትሮኒኮን ኦርጋኖን (Ilektronikon Organon) ይሰኛል። በብሉይ ኪዳን አራት ቦታ የተጠቀሰው ዑጋብ የውዥሞ (የቀርከሃ) አሥር ዋሽንቶች በአንድነት ተጣምረው የተሠራ መሣሪያ የነበረ ሲሆን፥ የግሪኩ አርጋኖን ደግሞ ባለ አውታር (የክር) መሣሪያ ነበር  (ፒያኖ የመሰለ)። ድምጽን በተመለከተ ግን በተወሰነ መልኩ እንደሚመሳሰሉ ከሙዚቃ መሣሪያዎች ታሪክ እንረዳለን። እነዚህ አርጋኖን እና እንዚራ እያልን ስማቸውን የምናነሳቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች በመላ እንጂ በትክክል የትኞቹ እንደሆኑ እንኳን መናገር በማይቻልበት ሁኔታ የቅዱስ ያሬድና የአባ ጊዮርጊስን ድርሰቶችን ዋቢ እያደረጉ መጥቀሱ ብቻውን ማረጋገጫ ሊሆን አይቻልም። ዘመን በዘመነ ሲተካ የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታም ሲዘምን የጥንቱ አርጋኖን በየዘመኑ ቦታውን፥ ለፓይፕ ኦርጋን፥ ለቸርች ኦርጋን፥ ለአኮርዲዮን፥ ለሀርሞኒካ (ማውዝ ኦርጋን)፥ ለፒያኖ እየሰጠና የጥንቶቹ ሁሉም ቀርተው ዳግም እንዳይመለሱ ተጥለው ቦታቸውን ለዘመነኞቹ ኤሌክትሮኒክ ኦርጋን እና ዲጂታል ኦርጋን ተክተው አልፈዋል።

የዛሬው ዲጂታል ኦርጋን (piano, saxophone, flute, pan pipes, srings, guitar, steel dram, double base) የተሰኙትንና የሌሎችንም መሣሪያዎች ድምጽ በማስመሰል እንዲጫወት ተደርጎ ተሠርቷል ሆኖም ግን በማንኛውም መልኩ ቅኝታቸው ፈጽሞ ያሬዳዊም ሆነ ድምጹም የማሲንቆ፥ የዋሽንት፥ የክራር፥ የበገና እና የከበሮ ድምጽ መሆንም ሆነ መምሰልም አይችልም። ዛሬ ከወደ አሜሪካ ያሉት ወገኖቻችን እንደሚሉት ሳይሆን የግሪክ ኦርቶዶክስ ወንድሞቻችን እንዳሉት የኤሌክትሮኒክ ኦርጋን ድምጽ መንፈስን የሚያውክ ለጸሎት የማይስብ መንፈሳዊነት የሌለው ስለሆን ወደ ልባችን ተመልሰን ማንነታችንን እንመልስ በዚሁ ከቀጠልን  ነገ ደግሞ ክራር በሊድ ጊታር፥ በገና በቤዝ፥ ዋሽንት በክላርኔት፥ ከበሮ በአውሮፓውያኑ ድራም ወዘተ… ይተካ ማለታችን አይቀሬ ነው። ነገር ግን ማንኛውም ምእመን በኦርጋንም ሆነ በሌላ በሚችለው የሙዚቃ መሣሪያ እየተጫወተ በግል ለራሱ መዘመር፥ አኮርዲዮንም ሆነ ሀርሞኒካ እየተጫወተ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ዜማዎችን በጥምቀተ ባሕርም ሆነ በሌሎች የንግሥ በዓላት ወቅት ማዜም መብት ነው፤ ካህን ግን ካህንነቱ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሆነና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የራሷ ያሬዳዊ ዜማ እና የራሷ የዜማ ምልክትም ስለ አላት ለነጮቹ ኖታ ቦታ መስጠት አይኖርበትም፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዜማና የዜማ ምልክቶች ከከበዱት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን አያሌ የአገልግሎት ቦታዎች ስለአሏት ራሱን ከቦታው ጋር ማረቅ እንጂ በኦርጋን በአኮርዲዮንና በነጮቹ ኖታ እንጠቀም ብሎ ማልቀስ ትክክል አይደለም።

ከላይ እንደጠቀስኩት በማንኛውም ዓይነት መሣሪያዎች መጫወት በራሱ ጽድቅም ሆነ ኵነኔ ሊሆን አይችልም፤ አርጋኖን የምትላዋን ማደናገሪያ እንተውና በዲጂታል ኦርጋን መዝሙራችንን መታጀብ የለበትም የሚል ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባል ወይም ደጋፊ ብቻ አይደለም የሁላችንም ድምጽ እንጂ፤ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ ኦርጋን እና በአኮርዲዮን እንጠቀም የሚል ሁሉ ተሀድሶ ሊሆን አይችልም፥ ተሀድሶዎቹ በኦርጋን ብቻ የሚቆሙ ሳይሆኑ ዶግማና ቀኖናችንን ለመናድ የተነሱ መሆናቸውን ከአካሄዳቸው እየተመለከትናቸው ነው። በሌላም በኩል ኦርጋን በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስባ በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ወዘተ…  ጊዜ ጀምሮ ተጠቅመንባቸዋልና እነርሱም ተሐድሶ ነበሩን? የሚል ተራ ቧልት ማስፋፋት ክርስትናም አይደለምና መቆምም አለበት፤ ጥያቄው መሆን ያለበት ቅዳሴያችን፥ ማኅሌታችንና መዝሙሮቻችን በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ቢቀነባበሩ በያሬዳዊ ዜማና በምልክቶቹ ላይ የሚያመጡት ተጽዕኖ ምንድን ነው? የራሳችንን ያሬዳዊ ዜማና ባህላዊ መሣሪያዎቻችንን ለትውልድ የማስተላለፉ ሂደት ላይ ያለው ትጽዕኖ እና የማንነት ጥያቄ እና ሌሎችም ተዛማጅ ሁኔታዎች ጋር መታየት ይኖርበታል። ነገር ግን ዋናው ቁም ነገር እና ሚዛን መሆን ያለበት ከመሣሪያው የሚወጣው ድምጽ ከቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ዜማ ጋር ይሄዳልን? ወይስ ዜማውን ይሰብራልን? የመሳሪያው ድምጽ በምእመናኑ ስነ ልቡና ላይ ሚኖረው ተጽዕኖ ምንነት፥  የመሣሪያው ድምጽ  ምእመናንን ያንጻል ወይስ ያሸፍታል ወዘተ… ላይ ጥናት ማድረግ አስፈላጊና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው፤ አንድ መዝሙር የሚመዘነው ምእመናኑን ወደ ንስሐ እና ወደ ቅዱስ ቁርባን መመለስ መቻሉ እንጂ የቸብቸቦው መድመቅ መሆን የለበትም።

የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኦርጋን ስለሚጠቀሙ እኛስ ብንጠቀምበት ምን አለበት የሚል እንሰማለን በተለይ ከግሪካ ከራሺያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የዶግማና የቀኖና ልዩነት ያለን መሆኑ መታወቅ አለበት፥ ከግብጽ ከሶሪያ እና ከአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የዶድማ አንድነት ቢኖረንም ሙሉ በሙሉ በቀኖና አንድ አይደለንም ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የቅዳሴም ሆነ የመዝሙር ዜማ የላቸውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ግን የራሷ ልጅ የደረሰላት ዜማ፥ የራሷ ልጆች የሠሩላት ሥርዓትና የዜማ መሣሪያ ያላት ስለሆነ የነጮቹ ኦርጋን አያስፈልጋትም። ቤተክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓቷን ጠብቃ መቆየት ይኖርበታል፤ ዋሽንት፥ ክራር፥ በገና፥ ማሲንቆ፥ ከበሮ፥ ነጋሪት፥ እንቢልታ እና ሌሎችም የብሔረሰቦቻችን የዜማ መሣሪያዎች እንደ ቅዱስ ያሬድ ዜማዎች የማንነታችን መገለጫ ልዩ አሻራችን ስለሆኑ እያንዳንዳችን እንድንጥብቃቸው፥ የሃይማኖት አባቶችም ጠባቂነታቸው እግዚአብሔር በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው እንጂ ሰው ለሠራው ኦርጋንና አኮርዲዮን አለመሆኑን እንዲያውቁ ልዑል እግዚአብሔር ለሁላችንም ልቡና ይስጠን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ከሸዋንዳኝ አበራ

የካቲት ፳፻፰ ዓ.ም.  ለንደን ታላቋ ብሪታኒያ።

 

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop