“ተው ልጓሙን ያዘው ፡ ቀዳማ¹ ለቀህ፣
በሁዋላ እንዳይከፋ ፡ አወዳደቅህ።”
የሕዝብ ግጥም
የፈረንጆቹም ዓመትም ባተ ። አሮጌው በአዲስ ተቀየረ ። እኛ ግን “ወይፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ” እንደተለመደው እኛው ነን። የሚገርመው ነገር የሸሚዛችን ቅድ እንኳ አልተቀየረም። ወያኔን ከማውገዝ ያለፈ ፋይዳ ያልው ሥራ አልሠራንም፦ 1991 . . . 1992 . . . 1993 . . . 2015 . . . 2016 . . . . እያልን ዓመታት እንደቆጠርን እዚህ ደረስን። … መድረሻ የሌለው ተሰፋ ሰንቀን፣ ውል የሌለው የትግል ስልት ነድፈን፣ ቋት የማይሞላ ፖለቲካ ገርድፈን፣ ወንዝ የማይሻገር እጅና እግር ይዘን፣ እልባት የሌለው ጥላቻ እያጃጃለን አለናት! አለን!
የሃገሬ ገበሬ በደርግ ዘመን በደረስውን ድርቅ ተማሮ በግጥም እንዲ ብሎ ነበር ።
ይህንን 77 እሰሩት በገመድ ፤
ወደ 78 እንዳይረማመድ።
አንዳንድ ዓመቶች ወደሚቀጥለው ዓመት ባይሸጋገሩ ፣ እንደቆሙ ቢቀሩ እንዴት ደስ ይላል።
2015 መጥፎ ወይስ ጥሩ ነበር እንበል ? ለነገሩ ሁለቱም ነበር ማለት ይቻለል። ብዙ አውርተን፣ ብዙ ተስፋ አንግበን፣ ሳንጠግብ ተስፋችን ጠውልጎ፤ ብዙ አስተዛዝቦን አልፏል “ተዛዚብና” እንዲል ያገር ሰው ። ለማንኛውም እንኳን ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አደረሰን! በእኛም በእነርሱም ብንቆጥረው እኛ’ እኛው ነን ። የሚለውጠን ነገር ይኖር ብላችሁ ?
ያለፈን ወቃሽ አያድርገንና 2015 በእውነትም መጥፎ ነበር ። 30 ዜጎቻችንን ሊቢያ ላይ ገብረናል ። በዚያም እጅግ አዝነናል ፣ አልቅሰናል ፣ አንብተናል ፣ ዝክራቸውን ረስተናል ። እነርሱ ሳይሆኑ እኛ የቁም ሙቶች እንደሆንን አስመስክረናል ። ደግሞም ተመልሰን ልማታዊ ቱሪስቶች ሆነናል። አቦ! እኛ’ እኛ ነን ! ያኔ! ማለዳ በዘመን መለወጫ የቀመስነው ፌጦ አለት ድንጋይ ላይ ቆመን ነው መሰል፣ ዓመታት እያስወነጨፈ ይሰዳል እንጅ እኛ ምን በወጣን የምንቀየር? ይኸው ራሳችንን ”አስከብረን” እየኖርን ነው። እነዚያን ምስኪኖች ወዲያው ረስተን ወያኔ በጠራው የዲያስፖራ ስብስባ ከወያኔ ጋር አሸሼ ገዳሜ ስንል ፣ ዳንኪራ ስንረግጥ ከርመን ተመልሰን የለ ። ወያኔ ደሃውን እያፈናቀለ መሬት ለእኛ እንዲሰጠን ለምነናል ። መሬት ላራሹን አውግዘን ፣ መሬት ለመራሹ! ብለናል። ይህ ታላቁ 2015 ድላችን ነው ብንለውስ? ያንስበት ይሆን?
ወያኔማ እንዳለው ረዥም መንገድ መጥቶ ይኸው እየተቀበለን አይደል እንዴ? ቀጣዩ ማን እንደሆነ ባናውቅም የመን ድረስ ሄዶ አንዳርጋቸው ፅጌን አንከብክቦ ተቀብሎ የለ። በዚያ ሰሞን እኔም አንዳርጋቸው ነኝ ብለን በፌስ ቡክና በመግለጫ አንደኛ ሆነን ነበር ። ትንሽ ቆይተን ያው
¹ ቀዳማ – የኮርቻ ቀዳማ – በፊት የሚገኝ – እንቢአጉስ የሚገባበት ።
እንዳመላችን ረሳነው ። እንኳን አንድ ሰው የወያኔ ሰለባ ይሆኑ ብዙ መቶዎችን፣ ብዙ ሽዎችን እረስተን የለ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረሃብተኞችን እንደረሳነው ዓይነት፣ . . . ሌሎች ብዙ ብዙ ነገሮችን እንደምንረሳው ዓይነት፣ 2015 ሳያልቅ የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ እርግፍ አድርገን ከተውን ሰነበት እኮ ።
እኛ አንዱን መጨበጥ ፣ የጨበጥነውን መልቀቅ የለመደብን የዘመን ፖለቲከኞች መሆናችን አይደል ትልቅነታችን ። በኤርትራ በኩል መሄዱ ያዋጣል አያዋጣም ክርክሩስ ቢሆን እንደው አንድ ሰሞን! አንድ ሰሞን! አዘፍኖን ነበር እኮ ። የመረጃዋች ጋጋታ፣ እሰጥ አገባው እንቅልፍ አሳጥቶን ነበር ። እሱም አሁን ፋሽኖ አልፎበታል መሰል ፣ ሮጠው የሄዱት ሮጠው ሲመለሱ እየታየ ነው ። ችግር የለም እኛ ፣ እኛ ነን።
በዚህ ሁሉ እኔ የዓመቱ ታላቅ ቀልድ ብዬ የወሰድኩት የካሳ ከበደን ቀልድን ነው። ባለፈው ቪዥን ኢትዮጵያና ኢሳት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ “ ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያ አንድነት ይታገላል “ ያሉት። እንዴት ደስ የሚል የዓመቱ ታላቅ አባባል ነው። በሻዕብያ አንቀልባ የኢትዮጵያ አንድነት ሲጠበቅ ! ደስ አይልም! … ያውም ተስፋዬ ገብረ እባብ (የኢሳያስ አፍወርቂ የኢትዮጵያ ጉዳይ አማካሪ) ልቡ ራርቶልን ለኢትዮጵያ አንድነት ሲያስብ ታየኝ! በተለይም አማራ ለሚባለው የህብረተ-ሰብ ክፍል ። … እውነት እውነት እላችኋለሁ ተስፋዬና ጓደኞቹ ቢችሉ ቆዳችንን ገፈው በቁም ስጋችንን ቢቸበችቡት ምንኛ ደስ ባላቸው። … “ እባበ ሲወድም ሲጠላም በሰው ላይ ይጠመጠማል ” እንዲሉ።
ድሮም ካሳ ከበደ ተጫዋች ናቸው። ወያኔ ሲገባ በበሽተኛ ወሳንሳ ሆነው ነው ከፈላሻዎች ጋር ከአዲስ አበባ የፈለሱት ። ከዚህ የበለጠ ምን ቀልድ አለ ? የኢሠፓው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ግንባራቸው ላይ የቤተ እሥራኤሎች ታርጋ ተለጠፎላቸው ታሪክ የሰሩ ሰው ናቸው ። … እንዴት ይረሳል? … እንማ እንዴ! እንማ …?
መቼም ካሳ የምራቸውን ከሆነና እኛም ካመንን በኤርትራ የተሰዋው የኢትዮዮጵያ ሠራዊት አጥንት ይወጋናል ። ይህን ሊያምንም የሚችል በነዋይ ሃገሩን የሚቸበችብ ብቻ ነው ። ከዛ ውጭ ማንም አያምንም ። የዓመቱ ቀልድ ብለን እንለፈው ። … እኛ ብናልፈውስ 2015 እንደገና“መሰባሰብ“የጀመረው የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህን ቀልድ ያምናል? ምን ይታወቃል የሚገኘው ነዋይ አዕምሮን መሸበብ ከቻለ ለይሉኝታ ደግሞ መከላከያ ጭንብል አይጠፋለትም።
2015 እውነትም ጥሩ ነበር ። ለሃያ ከምናምን ዓመታት ዋሽንግቶን ዲሲን ያማከለው ትግላችን ወደ ሃገራችን ጠጋ ብሏል። ይክፋም ይልማም አሥመራ ደርሷል። ከ24 ዓመታት በኋላ አሥመራ በመድረሱ ድልን አውጀናል፣ በሳምንት ፣በወር አዲስ አበባ የሚደርስ መስሎን ነበር ። አለመሆኑን ስናውቅ ቀኝ ኋላ ዙር ያልን አለን። ምን ችግር አለ ሌላ ጥሩ ልብ ወለድ ታሪክ መጻፍ ነው ። የሚያስለቅስ ፣ የሚያዝናና ። መቸም “ ጡትና መንግሥት ጊዜውን ጠብቆ መውደቁ አይቀር “ ምን ጣጣ አለው። ዛር እንደቆመ ነው መቆመር!!!
2015 መልካም ምግባር የነበራቸው ሰዎችም ይዞ ሄዷል ። ሙሉጌታ ሉሌ ፣ ዘውዴ ረታ ፣ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻውል) . . . ሌሎችም ። አሁንስ እንኳን ተገላገሉ ያስብላል ። ዩኒቨርስቲ በዘር ተከፋፍሎ ግማሹ ሲያምጽ፣ ግማሹ ሲማር ከሚያዩ ፣ ምሁር እንዲህ ሲዘግጥ ከሚታዘቡ፣ እኛ በክልል ተገዝተን፣ በክልል ነገሮች ስንተነትን ከሚመለከቱ፣ ትላንት ለኢትዮጵያ አንድነት የሚሉ ዛሬ ለክልል መጠናከር ሲያሸረግዱ ከማየት መገላገል ሳይሻል አይቀርም ። ከዚህ የደም ግፊትን፣ ስኳር … ገለመሌ ከሚያባብስ ንዴት ፣ በጊዜ ማለፉ መልካም ነው።
በ2015 ስንት አሪፍ አሪፍ መጽሐፎች ለንባብ በቅተዋል ። የፍስሐ ደስታ ቀዳሚውን ቦታ ይዟል ። ፍሰሐ ደስታ አራዳ ናቸው ። የዘመኑ ምሁሮቻችን መጽሐፍ እንደማያነቡና ከሽፋኑ እንደማያልፉ የተረዱና የገባቸው የደርግ አባል ሆነው አግኘቻቸዋለሁ። በመጽሐፉ ውስጥ ሙልጭ አድርገው የሚሰድቡትን ሕዝብ በሽፋኑ ላይ የይስሙላ ይቅርታ ይጠይቃሉ ። አቤት ያድናቂው ብዛት ፣ አቤት የቃለ መጠይቁ ብዛት . . . ። አንድ የኢሕአፓ መሪ ነኝ የሚሉ ግለስብ አልፈው ተርፈው “ሚዛን የደፋ” ብለውት ነበር ። ለመሆኑ በየትኛው ሚዛናቸው መዝነውት ይሆን ? የእኛ ምሁሮች ከሽፋን ባሻገር መጽሐፍ ገልበው እንደማያነቡ ጸሐይ አሳታሚ በውል የተረዳው ይመስለኛል ። ለማ በገበያ የአማርኛ መማሪያን ያላነበበው የወያኔ አሽቃባጭ ሰይፉ ፋንታሁን የሚባል እንኳን ሳይቀር ቃለ ምልልስ ከፍስሐ ደስታ ጋር አድርጎ ነበር ። መቸም አንዳንዱ መኖሩ ለማንም ካልጠቀመ መሞቱ ማንንም አይጎዳም። ቪቫ ፍስሃ ደስታ በመጸሀፉ ሽፋን ላይ ይቅርታ መጀመሩ አንድ እርምጃ ነው። የሚሻለው ግን በእርስዎ ትዕዛዝ የተገደሉትን ንፁሃን በማሰብ ቄስ ፈልጎ ንስሃ መግባት ነው ። እዚህ ላይ ነበር ጥፋቴ ብሎ መጀመር ነው ታላቅነት። የጅምላ ይቅርታ ብዙም አያስኬድም።
2015 አሪፍ ነበር ። በተለይ መጨረሻው ላይ ። ዳግማዊ ታዕሳስ ግርግር ታይታ ነበር ። የመንግስቱ ነዋይን ታዕሳስ ግርግር ከዚህችኛዋ ታህሳስ ግርግር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር ነው። ሁለቱም ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ ኃይሎችን አሳጥተውናል ። የመንግሥቱ ነዋይ ግርግር ክቡር ዘበኛን ብቻ በመያዙና ሌሎች ክፍሎችን ባለማካተቱ ሲከሽፍ፣ የሰሞኑ ደግሞ ክልላዊ ስለነበር ውጤቱመ ያው ተከልሎ ቀረ።
በሌላ በኩል 2015 እንዴት የሚያሳዝን ዘመን ነው። ከአምቦ ዮንቨርሲቲ የኦሮሞ ተማሪዎች አመፁ። የእከሌ ዩንቨርስቲ ኦሮሞ ተማሪዎች ተነሱ! የሚለው ዜና በጣም የሚገርም ነው ። ሌሎቹስ ? አንድ የተሳሳተ ነገር አለ። ወያኔ በቀረጽው የክልል ክፍፍል መገዛት ራሱ ስህተት ነው። ይህ ነውአሳዛኙ የ2015 ክስተት ። ይህ ክስተት ጃዋርና ተስፋዬ ገብረ እባብ ትንቢታችን ተሳካ ፣ ኢትዮጵያ ፈረሰች ብለው ጮቤ እንዲረግጡ አድርጓል ። እኛም እኛ ነን፣ ከበሮቻንን ይዘን አብረን ደልቀናል። ምን ጣጣ አለው! “ዘሎ የወረደ ዋጋው ይቀንሳል” ዓይነት የወያላ ጨዋታ ተጫወትን አይደል።
እኛ 25 ዓመታት ታግለን ምንም አልተማርንም። አሁንም ከጠላቶቻችን ጋር አብረን እንጨፍራልን ። ከሕዝብ በሰበሰብነው ገንዘብ በከፈትነው የመገናኛ ዘዴ ለሕዝብ ጠላቶች መድረክ እንሰጣለን። እኛ እኛ ነን፣ ዓመት ቢቀያየር የማንቀየር ። ሃላፊነት የማይሰማን የሠለጠን ዘመናዊ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ታጋዮች ።… አቤት ስማችን መብዛቱ ፣ ተግባራችን መክሳቱ።
የዓመቱ ታላቅ ቃለመጠይቅ ሳይሆነ ይቀራል ብላቸሁ ነው? . . . መሳይ ለጃዋር በኢሳት ያቀረበው ። በጣም ያስቅም ያናድድም ነበር ። መሳይ ጥያቄው እየጠፋው በፍርሃት ሲርበተበት ለተመለከተ ተጠያቂው ጥያቄውን ያወጣው ይመስላል። ። ጃዋር ግን ጥያቄውን ቀድሞ እንደተነገረው ሳይደነግጥ ፣ ሳይሸበር ነበር የሚመልሰው ። በእኔ በኩል የዓመቱ ታላቅ ቃለ መጠይቅ ብየዋለሁ ።
ለነገሩ መሳይ ደስ የሚል እሳት የላሰ የኢሳት ጋዜጠኛ ነው (ተከታታዩ ስልሆንኩ እንደማይቀየመኝ ተስፋ አለኝ)። መሳይ ለጃዋር ካቀረበው ጥያቄ መካከል “በእኔና በአንተ እድሜ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ” ብሎ የሚጀምረው ጥያቄው ሌላ ጥያቄ አጫረብኝ ። ውድ መሳይ ለመሆኑ እድሜያችሁ ስንት ነው? የ97 ምርጫ ጊዜ ኩፍኝ አልወጣላችሁም ነበር ? አየህ መሳይ ጃዋር ስንዝሮ ፖለቲከኛ የሚባለው ለዚህ ነው። ሰኞ ተረገዝኩ፣ ማክሰኞ ተወለድኩ የሚለው ተረት ተረት ዓይነት። አንዳንዴ እድሜን በመልክ መገመት ይከብዳል። ውድ መሳይ ለኢንፎርሜሽን ያህል በ1997 ምርጫ ከዚህ የበለጠ እንቅስቃሴ ነበር ።
2015 ብዙ ነገሮችን ሳንረሳ ስላስታወሰን “ልናመሰግነው” ይገባል። ተስፋዬ ገብረ-እባብንና ጃዋርን ከሰመመናቸው ነቅተዋል፣ 56 ድርጅቶችን መኖራቸውን ሰምተናል ፣ የተለያዩ መግለጫዎችን ፣ አዳዲስ ስሞችን ፣ አዳዲስ ዓርማዎችን . . .ውዘተ አይተናል። የ56 ድርጅቶች መሪዎች ሱዳን ድንበር ላይ ሄደው ቢደረደሩ ኖሮ ስጋት ከቶ ባልገባን ነበር ። ድርጅቶቹ ግን “ለስሟ መጠሪያ ምን ሰፋች” እንደሚባለው ቢጤ እንዳይሆኑ ከወዲሁ አንድ ቢባል ጥሩ ነው።
ከአስር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ሳለ፣ በዚህ በታህሳሱ ግርግር ሰሞን ስለድርቁ ማውራት የተረሳ ነበር ። ይህ ወያኔን ሳይመቸው አልቀረም። ድርቁ የተረሳው የሰሞኑ ፖለቲካ ስላልሆነና ለሥልጣን ስለማያበቃ ይመስላል። በሌላ በኩል ስለድርቅ ማውራት እንደ አፍሮ ፣ እንደ ቤል ቦተም ሱሪ በፖለቲካው ፋሽን የተረሳ ነው። በልምድ እንደምናውቀው የራበው ሰው ይሞታል እንጂ በምን ጉልበቱ መንግሥት ላይ አምጾ ድንጋይ ይወረውራል! ከየትስ አምጥቶ ለፖለቲካ ድርጅቶች የኢኮኖሚ ተቋማት የማዳበሪያ እዳ ይከፍላል! ከየትስ አምጥቶ ገንዘብ ለመሪዎቹ ፌሽታ ያዋጣል ! እንደው ለታዘበው የአንድ ሳምንት ዜና የሆነው ድርቅ የጠፋ ነው የሚመስለው ። እነዚያ በረሃብ የሚሰቃዩ ዜጎቻችንን ምግብ ዘነበላቸው እንዴ ? “ጉድ ያለው ገንፎ አድሮ ይፋጃል” እንዲሉ መቼም ለታዕምር ነው የፈጠረን ። ድርጅቶችስ ምነው መግለጫቸው በረሃቡ ጉዳይ አነሰ ? እኛ ካፒታሊዝምን ስለምንወድና ካፒታሊዝም ደግሞ ለደሃው ግድ ስለሌለው? አይ መከራችን መብዛቱ ። ምነው ሶሻሊስት ፣ ኮምኒስት ሆነን እንዳማረብን በሞትን ኖሮ።
2015 ደግ ዘመን ነው። ስማቸውን የረሳናቸው እነ መኢሶን እንኳን መግለጫ አወጡ። የመኢሶን አርማ መቀየሩ አሁን ነው ልብ ያልኩት። ማጭድና መዶሻው በአበባ ተቀይሯል ። ሶሻሊስቶች ማጭድና መዶሻን ጣሉ እንዴ? ። ስለ ድርቁ መኢሶን መግለጫ ያላወጣው ማጭዱን ከአርማው ስላነሳ ይሆን? የገበሬው ጉዳይ አይመለከተኝም ዓይነት! ጋሼ ነገደ ጎበዜን ማጭድና መዶሻውን እንዳይጥለው በቅርብ ስለማገኘው እነግረዋለሁ። የካፒታሊዝም ወዳጅነታችን ካከተመ ምናልባት ተመልሶ ፍለጋው እንዳያስቸግረን ባይሆን በቅርብ ያስቀምጥልን እንጅ ። ዓርማው ላይ ስለሚታዮት 13 ከዋክብት ትርጓሜም ቢነግረን ደስ ይለናል ። እኛ እንደሁ አንዱም አልሆነልን።
ያም ሆኖ ግን እኛም እኛ ነን ። ከ1991 እስከ አሁን ምንም ያልተቀየርን ። ይችም ታዕሳስ ግርግር ሆና ስንት አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች አየን። ስንት የመሳሪያ ትግል የጀመሩ እንዳሉ ሰማን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ታሪካዊው ነገር 56 ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው መግለጫ አወጡ የሚለው ዜና መስማታችን አስደሰተን። እስከዛሬ ከተፈጠሩት ሕብረቶች ሁሉ ከፕሮፖጋንዳው ጥቅሙ አንጻር ግዙፉና በዓይነቱ ልዩ ነው መሰለኝ ። በተግባር ወደፊት የምናየው ነው ። ብራቮ! ጥሩ ጅምር በ2015 ።
በመግለጫው ውስጥ በእከሌ የሚመራው ኦነግ ፣ በእከሌ የሚመራው ኢሕአፓ ፣ በእከሌ የሚመራው የአማራ ድርጅት፣ የሚለው ግን “ደስ አይልም” ። 2015 ትልቁ ግባችን ይህ ነው መሰለኝ ። ወደ መሳፍንት ዘመን ለምናደርገው ጉዞ ከአሁኑ ደጅአዝማቾቹን ፣ ፊት አውራሪዎቹን ፣ ቀኝ አዝማቾቹን፣ አጋፋሪዎቹን እና ሌሎቹንም እየተዋወቅን መሄዳችን ጥሩ ነው ። ስለድርጅቶች ስናነሳ ለአማራ የተቋቋሙ ድርጅቶች ፣ ለኦሮሞ የተቋቋሙ ድርጅቶች . . . እንደው ሌሎቹም፣ ሌሎቹም… አንድ ላይ ወደ መሳፍንት ዘመነ መንግሥት ጉዞ እየተጣደፍን አይመስልም ። ሥልጣን ላይ ቢደርሱስ እንዴት ነው የሚስማሙት? ሁሉም ክልሉን ይዞ ሊታኮስ?… ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ ወያኔ ከወረደ በኋላ እንወስናለን የሚለው ነጠላ ዜማ የማይጥመው እዚህ ላይ ነው።
እኔ እንደሚመስለኝ በ2015 ግለሰብ ሆነን የቀረን በጣም ጥቂት ነን። እንዳንዶች ድርጅት ነን የሚሉ ከግለሰብነት አያልፉምና ይህ ቀልድ ሊቆም ይገባል ። አለበለዚያ በቅርብ ጊዜ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ድርጅት እንዳይኖረን ሰጋቴ ነው ። .. እየተስተዋል እንጅ!
2016 ቀልዶቻችን ትተን ወደ እኛነታችን ተመልሰን ያላረስነውን ለማፈስ፣ ያልዘራነውን ለማጨድ እንደ ሰሞኑ መግለጫ ባንሞክር ጥሩ ነው ። በሕዝባችን ላይ እምነት ጥለን ፣ ከሕዝባችን ጋር ተደራጅተን መታገልን ነው መመኘትና መሥራት ያለብን ። ቆቡን ጣለ እንጅ መኢሶን አንቅሮ የተፋው መፈክር ዛሬ ነበር የሚሰራው “ ለነቃ ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል” የሚለው። ይህ መፈክር 1967 አይሰራም ነበር ። ጠንካራ ሠራዊት ፣ ጠንካራ የሠራተኛ ማህበር ፣ መኢሶን ፣ ኢሕአፓ ፣ ደርግ ፣ኢዲዩ ሌሎችም በነበሩበት ወቅት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ሊሠራ ይችላል። ዛሬ ሃገሪቷ በክልል ተከፋፍላ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች በደከሙበት ወቅትና አደገኛ አዝማሚያ ባለበት ሁኔታ፣ በሕዝብ አመጽ ብቻ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት መጓዝ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ። ይቻላል ከተባለ ቀመሩን ምሁራን ሊያሳዩን ይገባል። እኔ በበኩሌ የሽግግር መንግሥት ፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የሚለው በዚህ በለየለት ከፍፍል ወቅት ይሰራል የሚል እምነት የለኝም ። ምክንያቱም በድርጅቶች መካከል እንኳን አንድ ዓይነት ዓላማ አይታይም ።
በአንድነት ላይ የተመሰረተ እምነት ያለው ንቃት ፣ በዚህ እመነት ላይ ዴሞክራሲን ግቡ ያደረገ ድርጅት ወይም ሕብረት ፣ በዚህ ድርጅት ወይም ሕብረት ሥር የሚደረግ የመሣሪያ ትግል ብቻ ነው መፍትሔው ። ይህንን ወደ ጎን አድርገን በየጎጡ ፣ በጎበዝ አለቃ የሚመራ ፣ ወደ መሳፍንት ዘመን የሚመራ ትግልን መቀስቀስ ሃገር ከማፈራረስ ባሻገር ምንም ፋይዳ አይኖረውም የሚል እምነት አለኝ ። … ልብ ያለው ልብ ይበል !
ስለ ሃገራቸን በጎ የሚያስቡ ሁሉ መልካም ዓመት ይሁንላቸው ።
ፍረንክፈርት 01.01.2016