ትናንት ሲያቀብጠኝ ከአንድ ጓደኛየ ሞባይል እነዚያ አይሲስ የሚባሉ ጉግማንጉጎች እነዚያን 21 ክርስቲያን የግብፅ ዜጎች በሊቢያ አንድ የባሕር ዳርቻ ላይ አንገታቸውን ሲቀሉ የሚያሣይ ቪዲዮ አየሁ – እስከመጨረሻው መዝለቅ አልቻልኩምና ግን ዋናው ባራኪ በግራ እጁ የያዘውን ጩቤ ወደ እኛ ወደተመልካቾቹ ዘርግቶ እያስፈራራ ሲዝት አጠፋሁት፡፡
የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ እስከዚህ መጨከኑ የሚያመላክተን ዋና ቁም ነገር የዚች ምድር ሰዎች የደረስንበት አጠቃላይ መንፈሣዊና ኅሊናዊ ኪሣራ ሊቀለበስ ወደማይችል ከፍተኛ የመጨረሻ ደረጃ መድረሱን ነው፡፡ ለምግብነት የተፈቀዱልንን እንስሳት እንኳን ስናርድ የሚዘገንነንና በዚህም ምክንያት የማናርድ ብዙ እንስፍስፍ ሰዎች አለን፡፡ ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጡር ሊያውም በሚከተለው ሃይማኖት ምክንያት ብቻ በስለት አንገቱን ቀንጥሰው ጀርባው ላይ ሲያስቀምጡ ሊሰቀጥጣቸው ይቅርና በደስታ የሚፈነጥዙ “ሰዎች”ን በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስናይ በሰዎች ተፈጥሮ መለያየት እጅግ እንገረማለን፡፡
“A Message Signed with Blood, to the Nation of the Cross” ይላል የቪዲዮው መግቢያ፡፡ አስፈሪ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በያዙት የመስፋፋት ሂደት ከቀጠሉ ሌሎቻችንም ይህ አስቀያሚ ዕጣ የሚቀርልን አይመስለኝም፡፡ ነገሩ “የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል” እንዳይሆን ያሰጋል – እየሆነም ነው እንጂ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ የተነሣ እሳት አፍሪካ ጫፍ ሊቢያና የመን ሲደርስ አያድርስ ብሎ ከመጸለይ ውጪ እኛስ ምን ዋስትና አለን? ይህን ቪዲዮ ከተመለከትኩ በኋላ ለረጂም ጊዜ ሥራየን በአግባቡ መሥራት አልቻልኩም፡፡ ሰው ሆኖ የመፈጠር ዕዳ የቀሰቀሰብኝ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መላ ሰውነቴን ወረረው – በአካልም፣ በመንፈስም፣ በኅሊናም እየኮሰመንኩ ስሄድ በምናቤ ይታየኝ ጀመር፡፡ አለመፈጠሬን የመረጥኩበት አንዱና ትልቁ አጋጣሚ ይህን ዘግናኝ ቪዲዮ በከፊልም ቢሆን ያየሁ ጊዜ ነው፡፡
ይህ በአስቀያሚነቱ ወደር የማይገኝለት ዓለም አቀፍ ክስተት በረድ እያለልኝ ሲመጣ ግን የሀገራችን አይሲስ ነጋዴዎች ታወሱኝና ስለነሱ አብዝቼ መጨነቅን ያዝኩ፤ ሁለቱ ተመሳሰሉብኝ፡፡ ደረጃውና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ጭካኔ ሁሉ መጠሪያውም ሆነ ጎራው ያው ጭካኔ ነው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያጵያውያን ኢይሲሶች የምላቸው በወያኔ የተፈጠሩ የዘመናችን ኅሊና ቢስ ነጋዴዎችንና ኑሯችንን ያመሰቃቀሉትን የሙስና አበጋዞችን ነው፡፡ ከወያኔ ቀጥለው የሀገራችንን የቀብር ሥነ ሥርዓት እያፋጠኑ የሚገኙት እነዚህ የቀን ጅቦች ናቸው፡፡
ወያኔ የዘራው ትልቁና መሠረታዊው ችግር የሀገር ብሔራዊ ስሜትን ማጥፋቱ ነው፡፡ ከዚህ በተያያዘም ሰብዓዊነትን ከሀገር አጥፍቷል፡፡ በምትኩ የተስፋፋው ዘረኝነት በወንዝ ልጅነትና በጎጥ፣ በቋንቋና በቤተሰብ መሳሳብ የጥቅም ትስስርን አንግሦ ጥቂቶች በሀብትና በሥልጣን ሽቅብ ሲመነደጉ አብዛኛው ሕዝብ እንጦርጦስ እየወረደ ነው፡፡ ወያኔ ዘረኝነትን በማስፋፋት ብቻ አልተወሰነም፡፡ ለሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳነት እንደ አያያዥ ስሚንቶ ይቆጠሩ የነበሩ ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ የሞራል ዕሤቶችን፣ መተሳሰብን፣ መፈቃቀርን፣ መቻቻልን፣ አብሮ መብላት መጠጣትን፣ … በጥቅሉ አንድን ሰው ሰው ሊያስብሉት የሚችሉ ሰብኣዊና ተፈጥሯዊ ክሮችን በጣጥሶ አንድያውን ሁላችንንም እንደራሱ ዐውሬ እያደረገን ነው፡፡ ከዚህ በሀገር ደረጃ ከታወጀብን የጥፋት ውርጅብኝ ለማምለጥ የምንውተረተር ዜጎች በጣም ጥቂቶች ነን፡፡ ዛሬ የብዙ ሰው መፈክር “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” ሆኗል፡፡ አንድ ማስታወቂያ ነበር – “መጀመሪያ ራስህን አድን ለጫማው በኋላ ይታሰብበታል” የሚል፡፡ እኛም “‹ሀ› ራስህን አድን” በሚለው የራስ ወዳድነት መርህ እየተመራን አንዳችን አንዳችንን በልተን ልንጨረስ የቀረን ጊዜ ኢምንት ነው፡፡ በጩቤ አለመተራረድ ብቻውን ከአይሲስነት ተፈጥሮ ነፃ አያወጣም፡፡ “እሳት ካየው ምን ለየው” ነውና በምንም ይሁን በምን የዘመናችን የጭካኔ መገለጫ አይሲስ ሆኗልና ነጋዴዎቻችንና ጃዝ ባዮቻቸውም የንግዱ ዘርፍ አይሲስ ናቸው – ሥውር አራጆች፡፡
ኑሮ በአዲስ አበባ ምን ይመስላል? ሰዎች ለምንና በምን ብልሃት፣ እንዴትስ ብለው በሀብት ይከብራሉ? ብዙኃኑስ ለምን በሀብት ይደኸያሉ? የሀገራችን የሀብት ክፍፍል ምን ይመስላል?አብሮ መኖር ሲቻል መጠፋፋትን ምን አመጣው?
በአሁኑ ወቅት “ሀገራችን ወዴት እያመራች ነው?” ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ይልቁንስ “በጉዞዋ የት ደርሳለች? በብርሃን ፍጥነት እያስነካችው ያለችውን ጉዞ ጨርሳ ወያኔና ታሪካዊ ጠላቶቿ ወዳቀዱላት የመጨረሻ ግብ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይቀራታል?” ብሎ መጠየቅ ይመስለኛል አግባብ የሚሆነው፡፡ እንጂ ዕድሜ ለወያኔ ካሣለፍነው የሃያ አራት ዓመታት የጥፋት ጉዞ በመነሣት ወዴት እያመራን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ጉልህ ክስተት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ስል በመላዋ ኢትዮጵያ እንደማለትም ቢቆጠርልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ለውጥ ሊኖር ቢችልም እንኳን ያን ያህል የጎላ አይደለምና፡፡ እናም በሀገራችን ኑሮ በአሁኑ ወቅት እጅግ የሚሰቀጥጥ መሆኑን በመጠኑ እንመልከት፡፡
በደመወዝ ብቻ መኖር ከቀረ ብዙ ጊዜ አለፈን፡፡ ደመወዝ ስልህ ደግሞ ይግባህ – የመንግሥትንና በሲፒኤ ደንብ የሚተዳደሩትን ማለቴ ነው፡፡ ትላልቅ ደመወዞችን አይመለከትም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከፈላቸው አሉና እነሱ የኑሮ ግርፋና ሰቆቃው አይነካቸውም፡፡
በአሁኑ ወቅት የዕቃዎች ዋጋ አይቀመስም፡፡ ሠራተኞች ከወር ወር መድረስ ስለማይችሉ ብዙዎች በተራድዖና በልመና እንዲኖሩ ተገደዋል፡፡ ዕቃዎች ስልህ የመብል ውጤቶችን ለማለት ነው፡፡ አንድ የመንግሥት ወይም የግል ድርጅት ተራ ሠራተኛ በሚያገኘው ደመወዝ ሌላውንና ለዘመኑ እንደቅንጦት የሚቆጠረውን ቤት መሥራትንና ማሳደስን ተውትና የምግብ ፍጆታውን እንኳን መሸፈን አይችልም – ሌላ የጎን ገቢ ካልተጨመረበት፡፡ “ሽምብራ ቆርጥሜ የሠራሁት ቤት” ይባል የነበረው ምሳሌያዊ አነጋገር አሁን የለም – ሽምብራም ከጤፍ በልጦ ተወዷል፡፡ በዚያ ላይ ሽምብራም ቆርጥም ባቄላ ከደመወዝህ ቤሣቤስቲን ተርፎህ ለክፉ ቀን አታስቀምትም፡፡ ሲጀመር ኑሮህ በብድርና በበዕዳ የተወጠረ እንጂ ከሽሮና ከጎመን ያለፈ አታስብም – ለዚህም ከበቃህ ታድለሃል፡፡ ዱሮ በአሥርና በአሥራ አምስት ብር ይገዛ የነበረው ሳልቫጅ ሸሚዝ ራሱ ዛሬ ከብር 130 በላይ ነው – በዚህ ዋጋ በቀደምለት እኔ ራሴ ስለገዛሁ ኅያው ምሥክር ነኝ – ለዚህ መብቃቴም ያስጨበጭብልኛልና እባካችሁን አጨብጭቡልኝ፤ የቢሮ ሠራተኛ – በሙስና ያልተዘፈቀ ማለቴ ነው – ሣልቫጅ ከመግዛት እንኳን አቅም ካነሰው ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ዛሬ ሳልቫጅ ራሱ ለመለስተኛ ሀብታሞች መዘነጫ ሆኗል፡፡ የኔ ቢጤ ሠራተኛ አዲስ ሸሚዝና ጫማ ለመግዛት ዕቁብ መግባት ይኖርበታል፡፡ በሌሎች ያደጉ ሀገራት በአፍሪካም ጭምር አንድ እኔን መሰል ለ20 እና ለ30 ዓመታት ሀገሩን ያገለገለ ባለ ሁለተኛ ዲግሪ ችግሩ ቤትና መኪና ሣይሆን ሌላ ነው፡፡ እኛ ግን ምን ቀምሰን እንደምናድር የምንጨነቅ የነጋዴና የወሮበላ መንግሥት የግዳይ ሰለባዎች ነን፡፡ ቆም ብለው ሲያስቡት ያሣዝናል፡፡ ይህን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ታዲያ ብዙ ዜጋ አግባብ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት አቅሉን ስቶ ሲራወጥ ታዩታላችሁ፡፡ ድህነት መጥፎ ነው፡፡ ድህነት ከሃይማኖትና ከጨዋ ባህል ያወጣል፡፡ ድህነት ዐውሬ ያደርጋል፡፡ ድህነት ያባልጋል፡፡
ነጋዴው እሳት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ነጋዴ ዐይንም፣ ጆሮም፣ ልቦናም የለውም፡፡ የለዬለት ዕውር ነው፤ የለየለት ደንቆሮ ነው፡፡ የንግድ ጽንሰ ሃሳብም የለውም፤ ምክንያቱም ወደ ንግድ የሚገባው የፊደል ዘሮች አልገባው እያሉ ሲያስቸግሩት እንጂ በትምህርትና በልምድ ዳብሮ አይደለም፡፡ ብዙው ነጋዴ በአቋራጭ መክበርን እንጂ በህጉ መሠረትና የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም ባገናዘበ ሁኔታ አይደለም፡፡ የሀገሪቱም ሕግ ሕግ-አልባነት በመሆኑ ማንኛውም ኅሊናቢስ ወንበዴ ወደሀብቱ የሚያደርገው ጉዞ የተቃና ነው፡፡ የመንግሥት ተብዬው ባለሥልጣናትም ከማይማን ነጋዴዎች ጋር እየተመሣጠሩ ሕዝቡን ባልተወለደ አንጀት ይገርፉታል፡፡ ማይም ባለሥልጣናትና ማይም ነጋዴዎች በእከክልኝ ልከክልህ የጥቅም ትስስር ሀገሪቷንና ሕዝቧን ወደ ገደል እየከተቷቸው ነው፡፡ አንድም ሃይ ባይ ሳይኖር ኢትዮጵያን የመሰለች የድንቅ ታሪክ ባለቤት እየጠፋች ነው፡፡ ማን ይድረስላት?
ዱሮ ስንጥቅ ትርፍ ሲባል እንሰማ ነበር፡፡ “እገሌ ስንጥቅ ትርፍ አተረፈ” ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንደዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ ስንጥቅ ማለት እንግዲህ ግማሽ በግማሽ ለማለት ይመስለኛል – ለምሳሌ መቶ ብር የተገዛን ዕቃ 150 ወይም ግፋ ቢል 200 ብር የመሸጥ ያህል፡፡ አሁን ግን መቶ ብር የተገዛን ዕቃ ጊዜ እየጠበቁና ሆን ብለው እያስወደዱ ከአምስትና ስድስት ሺህ ብር በላይ ካልሸጡ የነገዱ የማይመስላቸው አይሲሶች ተፈጥረዋል፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ንግድ በጀመረ በጥቂት ሣምንታትና ወራት ውስጥ አንቱ የተባለ ዲታ ይሆንና መኪና እንደሸሚዝ ሲለዋውጥ ታየዋለህ፤ በዚያ ላይ ወያኔያዊ የደምና የአጥንት ንክኪ ካለው ሣምንት ቀርቶ ደቂቃዎችም ሳይፈጅበት ቀጭን ጌታ ይሆናል – ትምህርት ዕርሙ በሆነበት ድባብ ውስጥ ለሚኖር አንድ ማይም ዘረኛ ደግሞ ይህ ዓይነቱ በሀብት የመወንጨፍ ዕድል ከባድ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር አእምሮን የማሳመን ጉዳይ ነው፡፡ የሃይማኖትና የግብረገብ ትምህርት የሌለው፣ የይሉኝታና የሀፍረት ስሜት ጨርሶ የሌለው፣ ከአንዲት ትንሽ ጎጥ በዘለለ ማሰብ የማይችል “ሰው” አጭበርብሮና አታልሎ ብቻም ሣይን ገድሎና አሥሮም ቢሆን ቢከብር የሚጠይቀው ኅሊና ወይም ምድራዊ ሕግ የለም፡፡ ሁሉም እርሱን ለመርዳት የቆመ ነውና፡፡ ሰው ደግሞ በተፈጥሮው ከኅሊናው ጋር ከተቆራረጠ የመጨረሻው ዐውሬ ነው የሚሆነው፡፡ በሁሉም መንገዶች ተጉዞ ወደሚፈልገው ማማ መውጣት ነው ጥረቱ፡፡
ትናንት ሰላጣ አማረኝ፡፡ ብዙውን ጊዜ ጥቃቅን የምግብ ፍጆታዎችን ከማንጠግቦሽ በተጓዳኝ እኔም እገዛለሁና ወደጉሊት ወጣ አልኩ፡፡ ገበያው በአንጻራዊ አነጋር ከቀደሙት የጾም ወራት አሁን ደህና ነበር ማለት እችላለሁ – በተለይ በአንዳንድ ዕቃዎች፡፡ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 16 ብር፣ አንዲት የጠወለገች ሙትቻ ሎሚ በአንድ ብር ከሃምሣ፣ ቲማቲም በጣም ቀነሰ ተብሎ ኪሎውን በ8 ብር፣ ቃሪያ (በጣም ጦፏል!) ግማሽ ኪሎ በ23 ብር፣ ሃቱም የተባለውን አንድ ሊትር ዘይት 78 ብር፣ አንዲት እግር ሰላጣ በ8 ብር ገዝቼ ፀጉሬን እየነጨሁ ወደቤቴ ተመለስኩ፡፡ ሰላጣ ለመብላት ስንት እንዳወጣሁ እናንተው አስሉት – ዘይቱ እርግጥ ነው ትንሽ ጊዜ ይቆያል፡፡ ይህን ኑሮ የትኛው የመንግሥት ሠራተኛ ችሎ ይኖራል? ሥጋንና ወተትንማ ጭራሽ አታስቡት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሉካንዳ ቤት ስናልፍ የተሰቀለን ሥጋ በሱቲ ጨርቅ እየሸፈኑ ገልጠው ለማሳየት ብቻ ሳያስከፍሉን የሚቀሩ አይመስሉኝም፡፡ ልብ አድርጉ – እኔ ባለደህና ደሞዝተኛ ተብዬው ለልጆቼ ብርቱካንና ሙዝ አንጠልጥዬ መግባት ካቆምኩ ዓመታት አልፈዋል – እንዳልዋሽ እጅግ አልፎ አልፎ በወረት ካልሆነ በስተቀር የምነግራችሁ እውነቴን ነው፡፡ አንዲት ኪሎ ሙዝ 14 ወይ 15 ብር ፣ አንድ ኪሎ ብርቱካን ከብር 22 በላይ ገዝቼ እንዴት እችላለሁ? ደግሞስ አንድና ሁለት ኪሎ መች ይበቃንና ወስፋት ላጩህ? ለመሆኑ ስንቱ ቤተሰብ ነው ሥጋና ወተትን የመሰሉ አልሚ ምግቦችን በቅጡ የሚመገበው? ብዙው ቤተሰብ ሥጋን የሚያውቀው ሃሊዮ ኮሜት በሰባ ስድስት ዓመት አንዴ እንደምትታየው ሁሉ በዓመት ሁለቴና ሦስቴ ብቅ በሚሉ ፋሲካን የመሰሉ ዐውዳመቶች ነው፡፡ ሞተናል እኮ፡፡ ገድለውናል እኮ፡፡ እንዳሰቡት ሆነንላቸዋል እኮ፡፡ ዕቅዳቸው እኛን ማጀታችን ውስጥ ወሽቀው ስለምንቀምሰውና ስለምንልሰው እንድንጨነቅ ማድረግ አልነበረም? ታዲያስ! እናሳ አልተሣካላቸውም? አለመረገማችንን የማናምን ከዚህም ባለፈ እኛ ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች መሆናችንን አዘውትረን የምንናገር ብዙዎች ልንሆን እንችላለን – ነገር ግን ሆዱን እንኳን መቻል በሚያቅተው ማኅበረሰብ መካከል መገኘት ከመረገሞችም በላይ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ የሰው ልጅ በሥልጣኔ የትና የት ደርሶ፣ “አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ከማዕዳቸው ተርፎ የሚጣለው የዕለት ምግብ ለአፍሪካውያን የዚህን ያህል ጊዜ ቀለብ ይሆናል” እየተባለ ሲነገር ትንሽም የማይቆጫቸው መሪዎች ያሉን አሳዛኝ ሕዝቦች ነን – አፍሪካውያን በጠቅላላው፡፡ የኛ ደግሞ ከሁሉም በባሰ ቆሎም ባቅሙ አርሮብን፣ ልብሳችን በላያችን ላይ አልቆ፣ አጥንታችን አግጥጦ፣ … እንዲሁ ኑሮ ብለነው እንንጠራወዛለን፡፡ ሞታችንን በቁማችን ጨርሰን በትሽ በሽታ ህቅታችን ስትወጣ መቼም ወግ ነውና ሞቱ ተብለን ድንኳን ተጥሎ ይለቀስልናል፡፡
እርግጥ ነው የፊት ለፊት ስዕላችን አሁን ከምለው ለየት ያለ ሊመስልና እኔንም እንዳጋነንኩ ሊያስቆጥርብኝ ይችል ይሆናል፡፡ እኔ እያወራሁ ያለሁት እውነተኛውን በወያኔ ሚዲያ ግን የተሸፈነውን ሀገራዊ ማንነት ነው፡፡ የኔን ሕይወት፣ የወንድምና እህቶቼን ሕይወት፣ የአብዛኛውን ሕዝብ መሪር ኑሮ ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ እንጂ የተመቸው ጥቂት የማይባል ዜጋ መኖሩን አውቃለሁ፡፡ ግን ያም ምክንያት አለው፡፡ የተሻለ ደሞዝ ያላቸው፣ በሥራቸው ምክንያት እጅ መንሻ የሚያገኙ፣ ቤት የሚያከራዩ፣ ቤትና ዕቃ የሚሸጡና የሚለውጡ፣ ከዲያስፖራው ገንዘብ የሚላክላቸው(እኚህኞቹ ቀላል ቁጥር አይደለም ያላቸው)፣ መኖሪያ ቤታቸውን ወደአነስተኛ የንግድ ቤትነት ለውጠው እንደነገሩ የሚውተረተሩ፣ በስርቆት፣ በማጭበርበርና በሙስና ትልቅ ገቢ ያላቸው፣… ወገኖቻችን መሬት ላይ ከሚታየው ህንፃና መንገድ ጋር ተደማምረው እውነተኛውን ሀገራዊ ምስል ለጊዜው ሊደብቁት ቢሞክሩም እስከወዲያኛው ግን ሸፍነው ሊያቆዩት አይችሉም፡፡ ከነዚህ ከጠቃቀስኳቸው የጎን ገቢዎች የራቀው ተራው ገበሬ፣ መምህሩ፣ የመንግሥት (የቢሮ፣የጽዳት፣ የጉልበት፣ የጥበቃ…)ሠራተኛው፣ ተራው ወታደር፣ ከጉቦ ጋር ብዙም የማይወዳጀው የፖሊስና የፀጥታ ሠራተኛ፣ ሥራ አጡ ወገን፣ ህጻኑ፣ ሽማግሌው፣ ለማኙ፣ በረንዳ አዳሪው፣ ሴተኛ አዳሪው፣ ወዘተ. እንዴት እንደሚኖር ብታዩ በኢትዮጵያ ያጡ የነጡ ድሆችን ሣይሆን በምሥኪኖች ላብና ደም የከበሩ ሀብታሞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ብቻ ተግቶ የሚሠራ ሥውር ምናልባትም መንፈሣዊ ኃይል መኖሩን እንድታምኑ ትገደዳላችሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሁሉ ተነግሮ በማያልቅ የኑሮ ውጣ ውረድና መሪር አገዛዝ እያረረና እየነደደ የሚገኝ ሕዝብ ርስ በራሱ ተባልቶ እንዳያልቅ ለመርዳት ሲል ፈጣሪ ጓዙን ጠቅልሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የከተመ እስኪመስለን ድረስ በፈጣሪ ጥበቃ እንድንገረም የሚያደርግ ሁኔታ እንታዘባለን – የዕንቆቅልሽ ምናውቅልሽ ሀገር፤ ኬንያ ወይም ደቡብ አፍሪቃ እኮ ቀን በቀን ነው ሰው የሚዘረፈው፡፡ እዚህ የምናየው ትግስት ልዩ ነው፡፡ ራሱ እየተራበ የሰው ወርቅ ሲጠብቅ የሚያድር ዜጋ የምታገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት፤ ራሱ በጠኔ እየተሰቃዬ ሀብታሞችን አንደላቅቆ የሚያኖር ሕዝብ የምታገኘውም በአፍሪቃ ቀንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፤ በ“አንተ ታውቃለህ”ና “አንተ ያመጣኸውን አንተው መልሰው” ነባር ጸሎት የሚኖር ብቸኛ ሕዝብ ቢኖር የኛው ሕዝብ መሆን አለበት፡፡ይሁንና ግን ጊዜ የማይወልደው ክስተት የለምና እየተንተከተከ ያለው ማኅበራዊ ቀውስና ፍትህ አልባው የሀብት ክፍፍል አንድ ቦታ ከተነፈሰ መመለሻ የለውም፡፡ “ማን እየኖረ ማን ይሞታል?” ከሚል አሳማኝ መነሻ ሆድ የባሰው ሁሉ ሀገሪቱን የሁከት ማዕከል እንዳያደርጋት ያሰጋል፡፡ ሊቢያና ሦርያም ከብዙ አሠርት ዓመታት ግፍና በደል በኋላ ነው የአሁኑን አስጠሊታ ቅርጽ ሊይዙ የቻሉት፡፡ እናም መፍራት ደግ ነው፡፡ “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን በያዝሽ” ነው ነገሩ፡፡ የናቁት ማስረገዙ፣ የጠሉት መውረሱ፣ … ከጥንትም ነበር፡፡
የሕዝባችንን ቁስቁልና ለመረዳት እስኪ ለአብነት የአውሮፓን ካምቦሎጆዎችና የሀገራችንን ካምቦሎጆዎች በእግር ኳስ ግጥሚያዎች ጊዜ ተመልከቱ፡፡ የአዲስ አበባ ኳስ ሜዳ በምን ዓይነት ደቃቃ ሰዎች እንደሚሞላ፣ የአውሮፓውያኑ ደግሞ በምን ዓይነት ሰዎች እንደሚሞላ ታዘቡና የደረስንበትን የድቀት ደረጃ አስተውሉ፤ በአለባበስ፣ በሰውነት ይዞታ፣ በቁመት፣ በወርድ … በሁሉም አስተያዩ፡፡ ሰው ምግቡን ይመስላል፡፡ አመጋገብ ብዙ ትርጉም አለው፤ በአስተሳሰብና አመለካከት፣ በፍልስፍና፣ በሥነ ልቦና፣ በአካላዊ ዕድገትና ጤንነት፣ ወዘተ. ምግብ ወሳኝ ነው፡፡ ካለ ተመጣጣኝ ምግብ ጤናማ አእምሯዊ ዕድገት አይገኝም፤ ካለተመጣጣኝ ምግብ ቁንጅናና ውበት የለም፡፡ ካለ ተመጣጣኝ ምግብ ትምህርት መማርም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሆድ ባዶ ሆኖ ወይም አሸርባሸር በልቶ ትምህርት ወደአእምሮ ይገባል ማለት ዘበት ነው፤ የሆዱን ጥያቄ ባግባቡ ያልመለሰ ተማሪ አካሉ ክፍል ውስጥ ይቀመጥ እንደሆነ እንጂ መንፈሱ ወደምናባዊ ኩሽናዎች መሸፈቱ አይቀርም፡፡ ዝም ብለን “ሀበሻ ምቀኛ ነው” ብንል ዋጋ የለውም፡፡ ይልቁንስ ከአመጋገባችን አንጻርም ችግር ይታየኛልና ይህን የተጣመመ የኑሮ ገመናችንን ለማስተካከል ልዩ ኮሚቴ ካሁኑ ተቋቁሞ ይሰብበት፡፡(ይቺ ጤፍ የምትባል ነገር የምቀኝነት መንስኤ ንጥረ ነገር ሳይኖራት እንደማይቀር የሚናፈሰው ወሬም ቢጠና አይከፋም፡፡ ማን ያውቃል?)
በሌላ አቅጣጫ ጥቂቶች መሬትን ተጠይፈው ጮቤ ይረግጣሉ፡፡ ከኛ አላግባብ በሚዘርፉት ገንዘብ አዲስ አበባ ምድር ቃጤ ስትሆን ታመሻለች፤ ታድራለችም፡፡ እኔን እየራበኝና አብዛኞቹ መሠረታዊ ፍላጎቶቼ ታፍነው እነዚህ ጥቂቶች ብሩን ለየምናምኑ ሲረጩት ይታያሉ – ካለድካም የመጣ ገንዘብ ደግሞ እሳት ላይ የወደቀ ቅቤ እንደማለት ነው፡፡ ሀብታሞች ቅጥ አጡ – የኛ ድሀነትም ቅጥ አጣ፡፡ በሀገራችን ሁለት ፍጹም ተቃራኒ ጫፎች ተፈጥረው ለዳኝነት ብቻ ሣይሆን ለታዛቢም ሳይቀር አስቸገሩ፡፡ ሀብታሙ እንዴት እንደሚኖር ስናይ ድሃው ደግሞ ቆሼ ተራ ለፍርፋሪና ለሙዝ ልጣጭ እንዲያ በሺዎች እየተራኮተ ሲታይ የገነትንና የሲዖልን ኅልውና እስክንረሳ ድረስ እንደመማለን – ገነትንም ሲዖልንም በተግባር የምናያቸው ያህል ይሰማናልና፡፡ሙስናው ደግሞ ጣሪያ ያለው አይመስልም፡፡ በደሞዙ ከእኔ ታች የሆነ አንድ የቀበሌ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ወር እስከወር ከቡና ቤቶች እንደቆርኪ ተጠርጎ ነው ውድቅት አካባቢ ወደቤቱ እየተወላገደ የሚሄደው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደሞዛቸውን አያውቁትም፡፡ ከትንሹ እስከ ትልቁ ባለሥልጣን ያለሙስና ቢኖሩ እስትንፋሳቸው ቀጥ የሚል ይመስላቸዋል፤ ይላልም፡፡ ሙስና የሀገራችን የደም ዝውውር ሆናለች፡፡ ካለሙስና የሚኖር የመንግሥት የሥራ ኃላፊ አለ ማለት ያስቸግራል፤ ካለም በድህነት እየተሰቃዬ በመኖር የበይ ተመልካች ለመሆን መርጧል ማለት ነው – ጥሩና አዋጪ ምርጫ፡፡ የአብዛኛው የወቅቱ ምርጫ ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መክበር ነው፡፡ ጨረታና ግዢ ደግሞ ዋናዋ የግል ብልጽና ማሳለጫ ናት፡፡ በቡድንም ይሁን በግል ሀገርን መዝረፍና በአቋራጭ መክበር የብዙዎች ምኞትና የዕለት ተለት ድርጊትም ነው፡፡ ምን ይሉኝ የለም፡፡ የሚሠሩ ነገሮች ደግሞ ብዙዎቹ የጥራት ደረጃቸውን አያሟሉም፡፡ የጨረታ አሸናፊዎች ከዘርና ከሙስና ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው – ጥራትና አመክንዮ፣ ሀገርና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ዋጋ የላቸውም፡፡ ሥራዎች ተጠናቀው ርክክብ ይፈጸማል፡፡ በሙስና የተሠራ አንድ የግንባታ ዕቅድ ወይ መንገድ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ፍርስርሱ ይወጣና ኪሣራ ብቻ ይሆናል – ያኔ ጠያቂም ተጠያቂም የለም፡፡ ለምን ቢባል ማን ማንን ይጠይቃል? ሁሉም ሌባና ራስ ወዳድ ነው፤ ሁሉም በተመሳሳይ የሙስና ቁስል የነፈረ ነው፤ ቂጥኛም ውርዴን፣ ውርዴም ቂጥኛምን የመጠየቅ ሞራላዊ ብቃትም ሆነ ሕጋዊ መደላድል የለውም – በክት ለበክት እየተጠቃቀሰ ይጠቃቀማል፤ ሀገርና ሕዝብ ግን ያለቅሳሉ፡፡ በመቶ ሺዎች ወጪ ሊሠራ የሚችል አንድ ግንባታ ብዙ ሚሊዮኖች ፈሰውበትም ከሚፈለገውና ከሚጠበቀው የጥራት ደረጃ እጅግ የወረደ ነው፡፡ በእንጨት ባላ የተደጋገፈ አንድ የሕዝብ ትምህርት ቤት አውቃለሁ – ባለ አራት ፎቅ፡፡ እንዲያ ስንጥቅጥቁ የወጣው ደሞ ገና ከርክክቡ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ተማሪዎቹ እንዳይወድቁ ወይም ከናካቴው እንዳይደረመስባቸው ያሰጋል – በዚያ ትምህርት ቤት የዘመዴ ልጅ ይማራልና እኔም በዐይኔ አይቼ ተገርሜያለሁ፡፡ ለሀገር ማሰብና መቆርቆር ቀርቷል፡፡ የትም ፍጪው ነው የነገሠው፡፡ ሀገርህ በቁም ሞታለች፡፡ ሀበሻ በያለህበት ዕርምህን አውጣ፡፡ ነገር ግን “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” ነውና ተረቱ ያለች ትመስላለች – ሞታ ሳለች፡፡ ሞት ዓይነቱ ብዙ መሆኑን ተረዳ፡፡
ወደሚሰቀጥጠው ኑሯችን ልመልስህ፤ ያንተ ኑሮ የተያዘለት ሊሆን ይችላል – ማለፊያ ኑሮ ማለቴ ነው፡፡ ቢሆንም እኛም ያንተው ወገኖች ነንና እሮሮኣችንን ስማልን፤ እዘንልንም፡፡ ከአንተ በላይ ለኛ ማን ሊያዝንልን ይችላል?፡ እንደዱሮው በተወሰነ ጊዜ ጫማ መግዛት፣ ልብስ መግዛት፣ የቤት ዕቃ መቀየር፣ ወዘተ፣ ዛሬ በተራው ሠራተኛ ዘንድ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ገንዘብ ልታገኝ ትችል ይሆናል፡፡ ዘመድም ሊሰጥህ፣ ጓደኛም ሊለግስህ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚሰጥህ የገንዘብ መጠን በመቶ ሺዎችና በሚሊዮን የሚገመት ካልሆነ በስተቀር በመቶዎችና በጥቂት ሺዎች የሚገመት ከሆነ ከተወሰኑ ቀናት የምግብ ፍጆታ ውጪ የሚያልፍ አይደለም፡፡ የገንዘቡን የመግዛት አቅም ምች አጠናግሮት ተሽመድምዷል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብዙዎች በሚያገኙት መጠነኛ ገንዘብ ምንም ዓይነት ሻል ያለ ነገር መሥራት እንደማይችሉ ከመገንዘብ አኳያ እምብርታቸውን ወትፈው ሌት ከቀን ሲጠጡና ሲሰክሩበት የሚታዩት – ይህ ደግሞ እውነተኛ የደስታ ስሜት መገለጫ ሣይሆን የተስፋ መቁረጥ ስሜት የወለደው ጊዜያዊ መጠለያን የመሻት ፍላጎት የፈጠረው ነው፡፡ እና መጠጥ ቤቶች ሞልተው ቢታዩ አገር አማን ነው ማለት አንችልም፡፡ በነገራችን ላይ ይህን መሳይ በሁሉም ረገድ የወደቀና ከሆዱ ባለፈ ምንም ነገር ማሰብ የማይችል ሕዝብ መግዛት ለአምባገነኖች ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ የተማረና የሠለጠነ፣ በሀብትም በትውፊትም የዳበረ ማኅበረሰብ ገዢዎቹን ብዙ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ መብቱን ያስከብራል፡፡ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች የሚገኙ ማይም ገዢዎች ግን ሕዝቡ እንዳይነቃና ከዕለት ጉርሱ ባለፈም ሀብት እንዳይኖረው በማድረግ እንደእንስሳ እየገረፉ ይገዙታል፡፡ የኛ ግን ባሰና ለዕለት ጉርስና ለዓመት ልብስብም መድረስ አቃተን፡፡ ፈራጁ ኃያል አምላክ በመጨረሻው የድርሻቸውን አይከለክላቸውም፡፡ በዚያ ብቻ እንጽናናለን፡፡
ሰዎች ሀብታም የሚሆኑባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን ሕገወጥ፣ ኢ-ሞራላዊና ኢ-ሃይማኖታዊ ናቸው፡፡ በነዚህ መንገዶች ለመክበር መሞከር መጨረሻው ባያምርም ብዙዎቹ የሀገራችን ሀብታሞች ይጓዙባቸዋል፡፡
በህጋዊ መንገድ ነግደህ በአሁኑ ሰዓት አትከብርም፡፡ ምክንያቱም ውድድሩ ከባድና ፈታኝም ነው፡፡ ወያኔዎች ደግሞ የዋዛ አይደሉም፡፡ ሌሎችን ለማደኽየት፣ እነሱንና የነሱን ግን ለማክበር አጥብቀው ስለሚሠሩ የውድድሩን መንፈስ ይበልጥ ሕገወጥና አድልዖዊ ያደርጉታል፡፡ በዚህ የተንሸዋረረ ተናግዶት ነግደህ የትም አትደርስም፡፡ ለምሳሌ ቀረጥ ከፍለህ ያስገባኸውን አንድ ዕቃ ከ15000 ሺህ ብር በታች ብትሸጠው ሊያከስርህ ይችላል፡፡ አንዱ የወያኔ ንክኪ ነጋዴ ግን 10000 ሺህ ብር ሲሸጠው ታያለህ፡፡ የተያዘው ጥረት አንዱ ከሌላው ተባብሮ ለማደግ ሣይሆን አንዱ አንዱን ገድሎ በተናጠል የመመንደግ ነው – በተለይ ከዘር አኳያ የሚታየው ዐይን ያወጣ ጠንጋራ አሠራር በኢትዮጵያዊነትህ ብቻ ሣይሆን በሰብኣዊ ፍጡርነትህም እንድታፍር ትገደዳለህ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የለየላት ሲዖል እየሆነችባቸው ብዙዎች የተማሩ ዜጎቿ ወደምዕራቡ ዓለም የሚሰደዱት፡፡ ለዚህም ነው ብዙም ያልተማሩት ዜጎቿ የሚያልሙት እውን ባይንላቸውም እንኳን የበረሀና የባሕር እንስሳት ሲሳይ ወይም የህገወጥ የሰውነት መለዋወጫ ሰለባ ሆኖ የመቅረትን መጥፎ ዕድል እየተረዱም ጭምር በሀገራቸው የሚገኘውን የባንዳዎች መንግሥት አምርረው ከመጥላታቸው የተነሣ ወደውጪ በገፍ የሚፈልሱት፤ በየትኛውም ሚዛን ቢለካ ከዚህ የበለጠ የሀገር ውርደት ሊኖር አይችልም፡፡ ሀገሪቱ ጠማማ ሚዛን ላይ የተቀመጠች ራሷም የተጣመመች ሆናለች፡፡ የጨረባ ተዝካር፡፡ ወደላይ ብትጮኸ የሚሰማህ የለም፤ ወደታች ብትጮኽ የሚሰማህ የለም፡፡ ጩኸትህ ሁሉ የቁራና የምድረ በዳ ጩኸት ሆኖ ይቀራል፡፡ አማራጭ ስታጣ ታዲያ ትሰደዳለህ ወይም ታብዳለህ – ሁለቱም መጥፎ አማራጮች ናቸው፡፡
የወያኔ ሰብኣዊ ንብረት ከሆንክ ቢያንስ እንዳትራብ እነሱው የሚቆጣጠሩት መቁነን ይሠፍሩልሃል – እንዳትሞት እንዳትድን፡፡ በሀብትና በሥልጣን ወደላይ ብቅ ካልክ ለነሱም እንደማትበጃቸው ስለሚገምቱ ይመስላል ያን አይፈቅዱልህም፤ አንተ ግን የማንም ሥጋት እንደማትሆን ቢያንስ ልቦናህ ያውቀዋል፤ ለምን ብለህ? ሀገር ሰፊ ናት፤ ለሁሉም ትበቃለች፡፡፡፡ እነሱ ግን በሀብትም በሥልጣንም ከነሱ አጠገብ እንዳትደርስ አጥብቀው ይከታተሉሃል፤ ይቆጣጠሩሃል፡፡ ወያኔዎች ምድራችን ከፈጠረቻቸው ክፉ ፍጡሮቿ የመጨረሻዎቹ አደገኛ የሲዖል ትሎች ናቸው፡፡ ነግድም፣ የመንግሥትን ደሞዝ አግኝም በርቀት መቆጣጠሪያቸው እየለኩ ዘወትር ስላንተ ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ በሚባሉ የሚያደራጇቸውን ምሥኪን ዜጎችም በዚህ መልክ ነው ለነሱው መሣሪያነት የሚጠቀሙባቸው፡፡ ሲፈልጉ ቸርቺል ጎዳና መሃል ላይ ድንኳን ተክለው እንዲነግዱ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፤ ሲፈልጉ አንዱን የመንግሥት አዳራሽ ሰጥተው ለተወሰነ ጊዜ ሊያስነግዷቸው ይችላሉ፡፡ አንተን ግን ጫካ ውስጥ እንኳን ዛፍ ሥር ተቀምጠህ ልነግድ ብትል መጥተው ነግደህ ልታገኝ ከምትችለው አጠቃላይ ገቢ በዕጥፍ ድርብ የሚበልጥ ቀረጥ ይጥሉብሃል፡፡ ወያኔዎች ብልጥም ናቸው – ሂድ አይሉህም እንድትሄድ ግን ያደርጉሃል፡፡ ውጣ ላይሉህ ይችላሉ – እንድትወጣ ግን የማያደርጉብህ ግፊት የለም፤ ያኔ መሮህ እያለቀስክ ትወጣለህ – ካገርህም ጭምር ብን ብለህ ትጠፋላቸዋለህ፡፡ ሌላውና ከወያኔ ጋር የተሞዳሞደው ሀገርንም የሸጠው ወገን ግና መንገዱ ሁሉ ቀኝ በቀኝ ሆኖ በአጭር ጊዜ ይከብራል፡፡
አንዱ የመክበሪያ መንገድ እንግዲህ ወያኔን መጠጋትና በሕገወጥ ንግድ፣ ዐይን በሌለው የዋጋ ንረት በአጭር ጊዜ ቱጃር መሆን ነው፡፡ በዚህ ሂደት ከሕዝቡ አጠቃላይ ቁጥር አንድ መቶኛ የማይሆኑት ጥቂቶች ሽቅብ ሲወነጨፉ ሌሎች በቁማቸው መቀመቅ ይወርዳሉ – በሸፋፋ ጫማ፣ በነተበ ሸሚዝ፣ በቀዳዳ ሱሪ፣ በተጠገነ ፓንትና ካልሲ ወደቢሮ የሚሄዱ ዜጎችን ብታስተውል ሥርዓቱ የፈጠረው ሸፋፋ አካሄድ እንጂ የነሱ ጥፋት እንዳልሆነ ሊገባህ ይገባል፡፡ እንዲያውም እነዚህን የመሰሉ ዜጎች ሊከበሩና ሊወደሱ ይገባቸዋል፡፡ በ”ሀገርህ ስትወረር አብረህ ውረር” ፈሊጥ ተወስደው ከጠላት ጋር በማበር የድርሻቸውን ያልዘረፉና በሚያገኙት እውነተኛ ገቢ ብቻ ለመኖር የሚፍጨረጨሩ ንጹሓን ዜጎች በመሆናቸው በእጅጉ ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ እነዚያኞቹ ግን ገና በታሪክ ይዋረዳሉ፤ ትውልዳቸውም አንገቱን የሚደፋባቸውና የሚያፍርባቸው ይሆናሉ፡፡
ሌላኛው የመክበሪያ መንገድ ሰይጣናዊ ነው – በለየለት ሁኔታ ማለቴ እንጂ ማንኛውም ኅሊና ቢስ አሠራር ከክፋነቱ አንጻር ሰይጣናዊ መሆኑን ዘንግቼው አይደለም፡፡ በዚህ ሥልት መተት፣ ትብታብ፣ ጥንቆላና የመሳሰሉት ይካተታሉ፡፡ ማመን አለማመን ያንተ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ መንገድ በዓለም ደረጃ ከጥንት ጀምሮ በስፋት የሚታወቅና ብዙዎችም የሚመላለሱበት ሰፊ መንገድ ነው፡፡ በጥንቆላና በመተት -ለጊዜውና ነፍሱን ለሰይጣን ሸጦ – የሚያልፍለት ወገን እጅግ ብዙ ነው፡፡
ከሀብታሞቻችን፣ ከሯጮቻችን፣ ከአርቲስቶቻችን፣ ከባለሥልጣኖቻችን፣ ከታዋቂ ሰዎቻችን፣ ከታዋቂ የሃይማኖት አባቶቻችን … መካከል ስንቶቹ ይሆኑ በሰይጣን ጎታቾች ደጅ፣ በአውሊያና ከራማ ጠሪዎች ክድሚያ ቤት፣ በመጣፍ ገላጮች ቀየ፣ በሞራ አንባቢዎች ጎጆ ያልተንከራተቱና የሀብትና የሥልጣን ጫፍ እንዲደርሱ ያልተጎናበሱ? ገመናችን ብዙና ተቆጥሮም የማይዘለቅ ነው፡፡ ይህ ልማዳዊ ነገር ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሣይሆን በመላው ዓለም በተለይም በሕንድ፣ በሱዳንና በምዕራብ አፍሪካ በጣም የተለመደ ነው፡፡ ሰይጣን በተለይ በአሁኒቷ ዓለማችን ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ኃይል ነው፡፡ ያከብራል፤ ያደኸያል፡፡ ይሰጣል፤ ይነሣል፡፡ እርሱን የፈለጉ ከችሎታና ከሥልጣኑ እንዲቋደሱ ከፈጣሪ ሥልጣን ተሰጥቶታል ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ለምሳሌ በአሥር ዓመት ከሚመጣ የእግዚአብሔር ፍርድ ይልቅ በደቂቃዎች ለሚመጣ የሰይጣን “በረከት” እየተሸነፉ ብዙዎች ፈጣሪን ችላ ብለው ወደዚህ ቦርቃቃ መንገድ እንደሚገቡ ይነገራል፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ የመረጠ ይገባበታል፤ የፈራ ይመለሳል፡፡ እንደኔ የፈራ ከነድህነቱ እያከከ ይኑር፡፡ ልከክ፡፡ ሀብት ማናባቱ! (እንዲች ልጽናና አይደል?)
ይህ መንገድ እንዴት ያከብራል እነማን በዚህ ከበሩ ምን ማሟላት ያስፈልጋል … የሚሉት ጥየቄዎች ብዙ ስለሚያናግሩ ወደዚያ መግባት አያስፈልግም፡፡ እንጂ በስንቱ ሕንፃ ሥር ምንና እንዴት እንደተቀበረ፣ ማን በጅብ መንጋ መሀል እያስካካ አድሮ ሊነጋጋ ሲል ሰይጣናዊ ማንነቱን ለዋውጦ ሰው በመምሰል ወደንግድ ቤቱ እንደሚመለስ፣ እነማን በየትኞቹ ጠንቋዮችና አበጋሮች ዘንድ ሲፈናደሱ አድረው ሲወጡ እንደታዬ፣ … ብዙና ብዙ ዝግንትል ነገር ከነምሳሌዎች መናገር ይቻላል፡፡ በጥቅሉ ግን በዘመናችን ሰዎች በኑሮ ከመጨነቃቸው የተነሣ ከኅሊናቸውና ከነፍሳቸው ጋር እየተጣሉ ከጤናማ መስመር በመውጣት ወንድምና እህቶቻቸው ላይ ግፍና በደል እየፈጸሙ መሆናቸውን፤ ይህም ግፍና በደል እየቆዬ ወደራሳቸው ይዞርና በምድርም ሆነ በሰማይ የሚጎዳቸውን መጥፎ ድርጊት እያስቀመጡ መሆናቸውን በመጠቆም ባጭሩ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ሰላም፡፡
ለጠቃሚ ምክርና ገምቢ አስተያየት የምገኝበት አድራሻ፡- [email protected]