ከይገርማል ታሪኩ
(የመጨረሻ ክፍል)
የአባጃሌው ልጅ ሀይሌ ከፊታቸው ጥንቃቄ የሚጠይቅ ስራ ይጠብቃቸዋል:: መዐሕድ ድርጅቴ ነው: ቤቴ ነው ብሎ የተቀበለውን አባል አሳምኖ ወደመኢአድ ማሰባሰብ ቀላል ነገር አይሆንም:: ወያኔ መራሹ መንግስት የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ ያላቸው በርካታ ሰዎች ከፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ ጋር በእስር ላይ ናቸው:: የእስረኞች ቤተሰቦች: ዘመድ አዝማዶች እንዲሁም መላው አባላት መስዋእትነት የተከፈለበት ድርጅት ሲፈርስ ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም:: ጊዜ ወርቅ ነው:: ማንኛውም ነገር በትክክለኛው ወቅት ያለእንከን መፈጸም ይኖርበታል:: የወያኔና አንጋቾቹ የፈጠራ ወሬ የየዋሆችን ልብ ሊፈትን ይችላል:: የፖለቲካ ፓርቲወችም ቢሆኑ እንዳሸን ነው የሚፈሉት:: ጊዜ ከተሰጠ አይደለም የተራው አባል የየወረዳ አስተባባሪወችንም በነበሩበት ማግኘት ይከብዳል:: ጥቃትን ለመመከት ሁሉም የየመሰለውን አማራጭ ሊከተል ይችላል:: መፍጠን ይኖርባቸዋል::
ጠ/ ሚኒስትሩ “ለስልጣን የበቃነው ጀርባችንን በእሳት አስገርፈን ነው” ብለው ያሉት ሀሰትነት የለውም:: ደርግ ከስልጣን የወደቀው እንዲህ በቀላሉ አልነበረም:: የትግራይ ወጣቶችን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ደርግን ለመጣል እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ አድርጓል:: በትግሉ ወቅት ይህ ነው የማይባል ንብረት ወድሟል:: ከሁሉም በላይ የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል:: ነገር ግን ደርግን ለመጣል በተደረገው ትንቅንቅ መስዋእት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ለትግል የተነሱት ወያኔ የሚያዝ የሚናዝዝበትን አምባገነን ስርአት ለመመስረት አልነበረም- የአምባገነኑን ስርአት አፍርሰው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚያስከብር ስርአት ለመተካት እንጅ:: ወያኔ ግን የህዝብ ልጆች በመስዋእትነታቸው ያስገኙትን ድል ለራሱ በሚመች መልኩ አዘጋጀው:: ለተሰውት የህዝብ ልጆች ካሳ የሚገባኝ እኔ ነኝ ብሎ ድርቅ አለ:: በርግጥ ወያኔ ደረቅ ብቻም አይደለም- ብልጥም ነው::
የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሞቱም ሆነ እንዲጠነክሩ አይፈለግም:: ተቀናቃኝ ፓርቲወች አሉ መባሉ የገዥውን ፓርቲ መልካም ገጽታ በአንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል:: የዴሞክራሲ ስርአት አንዱ መገለጫ ከገዥው ፓርቲ ሌላ የተደራጁ ተፎካካሪ ፓርቲወች መኖር ነው:: ታማኝ የሆኑ ፓርቲዎች ከመንግስት ልዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይችላል:: ታማኝ ፓርቲዎች ታማኝ ተቃዋሚ ያላቸው ናቸው:: ታማኝ ተቃዋሚ በሆነ ባልሆነው መንግስትን አይጐንጥም: የሰጡትን በጸጋ ይቀበላል:: ሕዝብንና መንግስትን ለመነጠል አይሞክርም:: በዚህ ስሌት መሰረት መኢአድም ሆነ ሌላ ፓርቲ ቢመሰረት ችግር የለውም:: ችግር የሚሆነው ፓርቲዎች ገንነው መውጣት ከጀመሩ ነው:: ሕዝብ የሚደግፋቸው ፓርቲዎች ቀይ መስመርን የተሻገሩ ናቸው:: ቀይ መስመር ማለት ኢሕአዴግ ለተቃዋሚዎች ያስቀመጠው የመንቀሳቀሻ ዳራ ነው:: ቀይ መስመሩን አይደለም ማለፍ መንካት ቀይ ካርድ ያሰጣል:: ቀይ ካርድ ያየ ግለሰብ ወይም ድርጅት ከጨዋታ ውጭ ይሆናል:: በጥፋትም ይቀጣበታል:: ኢህአዴግ በወረቀት ላይ ያሰፈራቸው የፖለቲካ: የኢኰኖሚና የማህበራዊ ጉዳይ ፖሊሲዎች በትክክል በስራ ላይ ቢውሉ ህልውናው ሊያከትም እንደሚችል ያውቀዋል:: የነጻና የገለልተኛ ማህበራዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች መኖር ለህልውናው ጸር ናቸው:: ትክክለኛ ምርጫ ቢካሄድ እንደማይመረጥ ይረዳል:: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይደግፈው እንዲያውም እንደሚጠላው ያውቃል:: ስልጣኑን ከለቀቀ ደግሞ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ለሰራቸው ወንጀሎች ሁሉ መጠየቅ ይመጣል:: ባለስልጣናቱ ያላግባብ ያከማቹት ንብረት ሊወረስ ይችላል:: ስልጣን ከሌለ አይደለም ሀብት ንብረትን ህልውናንስ እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል? ተተኪው መንግስት ያለፈውን ሁሉ ይቅር ብሎ የያዙትን ይዘው ከስልጣን ብቻ ገለል እንዲሉ ስለመፍቀዱ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? ስለዚህ ወረቀት ላይ ያለው ለተመልካች ፍጆታ የሚውል ነው:: በስራ ላይ የሚውለው በስውር የሚተላለፈው የውስጥ መመሪያ ነው:: ወረቀት ላይ የሰፈረውንና በተግባር እየታየ ያለውን አለመጣጣም የተመለከተ “እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?” ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ቀላል ነው:: “ፖሊሲወቻችን እንከን የላቸውም:: ዴሞክራት ናቸው የሚባሉ ሀገሮችን በጎ ተሞክሮወች ሁሉ ያካተቱ ናቸው:: ችግሩ የአፈጻጸም ነው:: አፈጻጸምን ለማሻሻል አቅምን ማሳደግ የግድ ይላል:: እና ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እጃችሁን ዘርጉ” የሚል መልስ ይሰጥና ሌላ የገቢ ማሰባሰብ ስራ ይሰራል:: የመናገር: የመሰብሰብ: ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ: የመምረጥ: ወዘተ መብቶች በወረቀት ላይ ያሉ እንጅ በተግባር የሚተረጎሙ አይደሉም:: እኒህን በወረቀት ላይ የተጻፉ መብቶች ለመጠቀም የሞከረ ማንኛውም አካል ቀይ መስመሩን የተሻገረ ነው::
መኢአድ ዳዴ ማለት እስኪጀምር ድረስ ከመንግስት ምንም አይነት ጥቃት ሊሰነዘርበት እንደማይችል የተረዱት ሀይሌ ካለምንም ስጋት እንደበፊቱ ሁሉ ጎንደርንና ጎጃምን ከዳር ዳር አዳረሷቸው:: በመኪና የሚኬደውን በመኪና: ለፈረስ የተመቸውን በፈረስ ካልሆነም በእግር:: “ግዴላችሁም እኔ ያጠፋኋችሁ ልሁን” ይላሉ ሻለቃ ያገነገኑ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው:: ባርኔጣቸውን ከጭንቅላታቸው ላይ አንስተው ፍጹም ትህትና በተመላበት አኳኋን “ጤና ይስጥልኝ ጌታየ” ብለው ሲቀርቡ አይሆንም ብሎ ገፍቷቸው ሊሄድ የሚችል ሰው አይገኝም:: ቀልቡን ሰብሰብ አድርጎ ያዳምጣቸዋል:: በዚህ መልክ ቀደም ሲል የመዐሕድ አባል የነበሩትን ሁሉ ወደመኢአድ አስገቧቸው:: የየወረዳ ኮሚቴዎችንም አጠናከሩ::
’የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲወች ግንባር’ ለመፍጠር የተደረጉት ብዙ ሙከራወች ገንዘብ: ጉልበትና ጊዜ በልተው ሳይሳኩ ቀርተዋል:: በሀገር ውስጥ ከኦብኮና ከደቡብ ሕዝቦች ጋር ተመስርቶ የነበረው ህብረት ብዙ መሄድ ሳይችል ቀርቶ ፈርሷል:: በውጭ ሀገር የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያካተተው የተቃዋሚ ሀይሎች ህብረትም ቢሆን አባል ፓርቲዎችን ሰብስቦ ይዞ መቀጠል አልቻለም:: ኢዴፓና መኢአድ ተከታትለው ከህብረት ጋር ተፋተናል ሲሉ አውጀው የየራሳቸውን መንገድ ተከተሉ:: በመሰባሰባቸው ተስፋ አሳድሮ የነበረው ሕዝብ ተስፋው ጫጨ:: ሻለቃ ከህዝብ ጋር ተመሳስለው ኗሪ በመሆናቸው የህዝቡን ስሜት ይከታተላሉ:: ይህ የፓርቲወች ህብረት መፍረስ መሰራት እርሳቸውንም አበሳጭቷቸዋል:: “እንዲያው ምን ይሻላል? የልጅ ጨዋታ አደረጉትኮ” ይላሉ ከመሰሎቻቸው ጋር ሲያወጉ:: እንዲህ እንዲህ ሲል ቆይቶ በአራት ፓርቲዎች (መኢአድ: ኢዴፓ: ቀስተደመና: ኢዴሊ) ጥምረት ቅንጅት ተመሰረተ::
የቅንጅት መመስረት በየአካባቢው ይደረጉ የነበሩትን የፓርቲዎች የጎንዮሽ ሽኩቻ አስታገሰ:: ባህርዳር ጽ/ቤት የከፈቱት መኢአድና ኢዴፓ መድህን መጠላለፋቸውን ትተው በአንድነት ቆመዋል:: ቀደም ባሉት ጊዚያት አንዱ የሌላውን ጽ/ቤት ረግጦ አያውቅም ነበር:: አሁን ሁኔታው ተለውጧል:: ሁለቱም ጽ/ቤቶች የጋራ አገልግሎት እየሰጡ ነው:: ኢዴፓዎች ድንቅ ድንቅ ሰዎች አሏቸው:: ጥሩ ሀሳብ ማመንጨት: በሳል አመራር መስጠት የሚችሉ ሰዎችን ያካተተ ስብስብ ነው ኢዴፓ:: መኢአድ በአደረጃጀት ከኢዴፓ በእጅጉ ይበልጣል:: በሻለቃ ሀይለየሱስ ሀላፊነት ስር የሆነው ባህርዳር ልዩ ዞንና ምእራብ ጐጃም ዞን እስከቀበሌ ድረስ ተደራጅቷል:: በየአንዳንዱ የገጠር ቀበሌ አምስት አምስት አባላት ያሏቸው አመራር ሰጪ ኰሚቴዎች ተቋቁመዋል:: የባህር ዳር የመኢአድ ወኒያምና ቆራጥ አባላት ኢዴፓዎችን ወደዋቸዋል:: በመሀል የነበረው የመፈራራትና የመጠራጠር ስሜት አሁን የለም:: አንድ ላይ ተሰብስበው ይመክራሉ: መክረውም በጋራ ይወስናሉ::
የቅንጅት አመራር ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚያደርጋቸው ክርክሮች የሁሉንም ቀልብ ስቧል:: አርሶ አደሩ ሳይቀር ክርክሩን ለመከታተል ሬዲዮ ገዝቶ ጆሮው ላይ ለጥፎ ይውላል:: የሰላ አንደበትና የበሰለ ትችት የኢሐዴግን ተከራካሪዎች ያንተፋትፍ ይዟል:: ፖለቲካው ነፍስ እየዘራ ነው:: ባሕር ዳሮች የበለጠ ተነቃቅተዋል:: አሁንም ባሕርዳሮች እንደማእከል እያገለገሉ ነው:: ከየዞኖች በሚመጡ ችግሮች ዙሪያ መግለጫ ይሰጣል:: የቅንጅት ኮሚቴው ለችግሮች መፍትሄ ፍለጋ ከፖሊስና ከአስተዳደር ጋር ውይይት ያደርጋል:: መፍትሄ ግን የለም:: ያም ሆነ ይህ ቅንጅት በያንዳንዱ ልብ ውስጥ ቦታ ይዟል:: ትልቅ ስኬት! የቅንጅት የምርጫ ምልክት የሆነው ሁለት ጣት የሰላምታ መለዋወጫ ሆኗል:: መቸም ፌስታ ነው:: እስካሁን ስር የሰደደ ችግር አይታይም::
የኢትዮጵያ አርሶ አደር የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ከ80%-85% ያህል ይሆናል:: ኢሕአዴግ የትግል አጋሬ ነው የሚለው አርሶ አደሩን ነው:: አርሶ አደሩ የሚኖረው በገጠር ነው:: ስለዚህ ቢያንስ 80% የፓርላማ ወንበር እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኗል:: ቢሆንም እኒህ መአተኛ ቅንጅቶች ወደገበሬው መጠጋት የለባቸውም:: መርዛቸው እንዲህ በቀላሉ የሚነቀል አይሆንም:: ስለዚህ ባህርዳሮች ወደገጠር ተጉዘው አርሶ አደሩን እንዳያሰባስቡ ሆደ ሰፊው ብአዴን መንገዶችን ሁሉ ጥርቅም አድርጐ ዘጋ::
አርሶ አደሩ ተሰባስቦ የሚገኝበት የእረፍት ጊዜ የደብሩ ታቦት የሚከበርበት ቀን ነው:: ለምሳሌ አዴት ታቦቱ መድሀኔአለም ከሆነ አዴቶች የወሩን 27ኛ ቀን ስራ ፈትተው ያከብሩታል:: በእለቱ ቤተክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስ: የታመመን መጠየቅ: የተጣላን ማስታረቅ: ዘመድ ወዳጅን መጐብኘት ነው ዋናው ስራ:: ሌላውም ቢሆን እንዲሁ የየራሱን የበአል ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚያሳልፈው:: ይህች ቀን አርሶደሩ ቤተክርስቲያን ተሰባስቦ የሚገኝባት ናት:: ቅንጅቶች ይህችን ቀን እንደሚጠብቁ ግልጽ ነው:: የየደብሩ ታቦት ከሚውልበት ቀን የተሻለ አይገኝምና ወደዚያው ይገሰግሳሉ:: ታዲያ ይህን የሚያውቁት ብአዴኖች እለቷን በተለያየ ፕሮግራም (ጤና: ጸጥታ: ልማት ወዘተ) ወጥረው ይይዛሉ:: ባሕር ዳሮች አርሶ አደሩን አሰባስበው የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለማስተዋወቅ አልተቻላቸውም:: ከወር አንዲት የበአል ቀን ጠብቀው ተጉዘው ሲደርሱ ፖሊሶች ቀድመው ቦታው ላይ ተገኝተው ’ቤተክርስቲያን ውስጥ የፖለቲካ ስራ መስራት አይቻልም’ በማለት ይከለክሏቸዋል:: ከቤተ ክርስቲያን መልስ ገበሬው ምሳውን እንኳ መብላት አልፈቀድለት ብሎ እስከ ምሽት ድረስ በስብሰባ ይጠረነፋል:: ይህ ቀደም ሲል ያልነበረ ልምድ የተፈጠረው ቅንጅቶች ገበሬውን እንዳያገኙትና እንዳይበክሉት በሚል ነው:: “ቀደም ብለን የያዝነው ፕሮግራም ስለሆነ በእኛ ፕሮግራም ማንም የፖለቲካ ስራ እንዲሰራ አንፈቅድም:: ከፈለጋችሁ በሌላ ቀን ልትጠሩ ትችላላችሁ” እየተባሉ ቅንጅቶች ድካም ብቻ አትርፈው መመለስ ጀመሩ:: ይህንን የተገነዘቡት ሻለቃ አንድ ብልሀት ዘየዱ:: ሀይሌ የማንንም ሀሳብ አይንቁም:: “ከአንድ ራስ ሁለት ይበልጣል: ለእኔ ያልታየኝ ለአንተ ሊታይህ ይችላል” የሚሉት ሀይሌ የሁሉንም ሀሳብ ካዳመጡ በኋላ “ሁሉም የነርሱ ነው:: በየቦታው ሄደን አቤት ብንልም መፍትሄ ልናገኝ አልቻልንም:: በየገጠሩ ለፍተን ሰውን እንዳናገኝ ስለተከለከልን ካለምንም ውጤት ደክመን እየተመለስን ነው:: አርሶ አደሩ እንዳይከዳቸው በጣም ሰግተዋል:: ፈርተውናል:: እንግዲህ አንድ የሚታየኝ አማራጭ አለ: የቤት ለቤት ቅስቀሳ” ሲሉ ተናገሩ:: ይህ ሀሳብ መተኪያ የሌለው ነው ተብሎ በመታመኑ የቤት ለቤት ቅስቀሳ እንዲካሄድ ተወሰነ:: የየቀበሌው ኮሚቴ አባላት የዚህን ስራ ሀላፊነት ወሰዱ:: በዚህ መሰረት የቤት ለቤት ቅስቀሳው ተጀመረ:: የየቀበሌው ኮሚቴ አባላት ከቤት ቤት እየዞሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ ቀጠሉ:: “እናንተ ቅንጅትን እንድትመርጡ የምንፈልገው በምርጫው ቀን በምርጫ ወረቀቱ ላይ ብቻ ነው:: ከዚያ ውጭ እነርሱ የሚሏችሁን ሁሉ እሽ በሏቸው:: ተሰብሰቡ ሲሏችሁ እሽ: ማንን ነው የምትመርጡ ሲሏችሁ እናንተን በሏቸው:: ማን ማንን እንደመረጠ የሚያሳይ መሳሪያ ተክለናል የሚሉት ውሸታቸውን ነው:: እንዲህ አይነት መሳሪያ የለም” እያሉ አስጠኗቸው::
በከተሞች አካባቢ የሚደረገው ህዝባዊ ስብሰባ በአንጻራዊነት በእጅጉ የተሻለ ነው:: ቅንጅቶች የምርጫ ምልክታቸውን የያዘ ቲሸርት አሰርተው ለብሰዋል:: ትግሉ ኢሕአዴግን በሰላማዊ መንገድ ከስልጣን ለማስወገድ ነው:: አለበለዚያ መብቶች የሚከበሩባት: ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመመስረት አይቻልም:: ኢሕአዴግን ከመንበረ ስልጣኑ ለማንሳት አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ የግድ ይላል:: ስለዚህ የእኔ የእኔ ብሎ ነገር የለም:: ቅስቀሳው መካሄድ ያለበት በጋራ ነው:: በጋራ ወጪ መኪና መከራየት: የቅስቀሳ ወረቀቶችን ማባዛት: ሁሉንም- በጋራ መከወን:: ሕዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ከቅንጅቶች ጐን መቆሙን በግብር እያሳየ ነው:: ጽ/ቤቶች በሰው ተጣበቡ:: ማን ማን እንደሆነ አይታወቅም:: ሁሉም ይወጣል ይገባል: ይሰራል:: አንዳንዶች ስጋት ገብቷቸዋል:: ይህንን እድል ተጠቅሞ ብአዴን ብዙ ነገር ሊያበላሽ ይችላል:: ሻለቃ እንዳባት ይገስጻሉ: ይመክራሉ:: “ቢመጡ እኛ ምን ቸገረን:: በድብቅ የምንሰራው ስራ የለን! ሚስጥር ባይኖርባቸውም ጥንቃቄ የሚጠይቁ አንዳንድ ሰነዶቻችንን ከእይታ አርቀናቸዋል:: እዚህ ያለው ጽ/ቤቱና መገልገያ እቃወች ብቻ ናቸው:: የሚያስፈራን ምንም ነገር የለም:: እንዲያውም እንግዶችን መቀበል ያለብን በትህትና ነው:: አያችሁ በአንድ ሰው ብልጫ አንድ ወንበር ይገኛል: በአንድ ወንበር ብልጫ ደግሞ ገዢ ፓርቲነት:: ያላወቅነው ሰው ሁሉ ጠላታችን ነው ብለን ፊት የምንነሳው ከሆነ ምናልባት ያ ሰው በእውነት ሊያግዘን የመጣ ሰው ቢሆን ሊሸሸን ማለትም አንድ ድምጽ ሊያሳጣን ይችላል” በማለት የአባላትን የጎፈነነ ስሜት ገፈፉ:: ጥድፊያ ነው:: ሁሉም ይሰራል:: ቅንጅቶች ሰርግ የሚደግሱ መሰሉ:: ከሁሉ ከሁሉ ባህር ዳር የተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ አስገራሚ ነበር:: የባሕርዳር ኗሪ ለስብሰባው ንቅል ብሎ ወጥቷል:: የፖሊና የፔዳ ተማሪወች ቀድመው ስቴዲዮም ደርሰዋል:: የባሕርዳር ስታዲዮም የቅንጅትን እድምተኛ ሰብስቦ መያዝ ባለመቻሉ አካባቢው ሳይቀር በሕዝብ ተጨናንቋል:: እለቱ የጥምቀት በአል የሚከበርበት እንጅ ስብሰባ የሚደረግበት አይመስልም:: ከአዲስ አበባ የቅንጅት አመራር ተወካዮች ተገኝተዋል:: የመድረክ መሪው ሰላማዊ መፈክሮችን ያሰማል:: በዚህ ወቅት አንድ ለየት ያለ ነገር ተከሰተ:: “አንድ በኢትዮጵያ ባንዲራ ያጌጠች መኪና ክላክስ እያሰማችና ከሰው ጋር እየተጋፋች በቀስታ ወደስታዲዮሙ ዘለቀች:: በመኪናዋ ላይ ያሉት ሰዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መፈክር ያሰማሉ:: የመድረክ መሪው ጩኸት በተቀላቀለበት መንፈስ ደስታውን ገለጸ:: “በጭብጨባ ተቀበሏቸው” አለ:: ስታዲዮሙ በጩኸትና በፉጨት ድብልቅልቁ ወጣ:: በዚያች መኪና የመጡት ሰዎች የሙገር አግሮ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ነበሩ:: ስብሰባው ከታሰበው በላይ በደመቀ ሁኔታ በስኬት ተጠናቀቀ:: በበነጋታው ጠዋት የሙገር አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤት የሬዲዮ ቃለመጠይቅ እየተደረገላቸው ነበር:: “ቅንጅት መኪናችንን አስገድዶ በመውሰድ ለቅስቀሳ ተጠቀመባት” ብለው እርፍ አሉ:: ምን ያድርጉ? ተይዘዋል ማለት ነው:: የእውነት ዴሞክራሲ አለ መስሏቸው መብታቸውን ተጠቅመው ድጋፋቸውን የሰጡት አግሮ ኢንዱስትሪዎች በወያኔ ተስፈኞች ጥርስ ውስጥ ገቡ::
የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች በየጽ/ቤቶች እየተገኙ እየተደረገ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ይከታተላሉ: አስተባባሪወችን ይጠይቃሉ:: በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ኦሪያል ብራዚል በጣና ሆቴል የቅንጅትና የህብረት ተወካዮችን አግኝተው አነጋግረዋል:: ሁለቱ ድርጅቶች እያከናወኗቸው ያሉትን ተግባራት: በገዥው ፓርቲ እየደረሱብን ነው ያሏቸውን ችግሮች ገልጸው እኛን ለማፈን ከበላይ አካል ተዘጋጅቶ በተዋረድ እስከቀበሌ ድረስ እንዲሰራበት የተላለፈ የውስጥ መመሪያ ነው በማለት ሰነድ አስረክበዋል:: አሜሪካም ሆነች ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ግንባራቸውን ኮስተር አድርገው ወያኔን “ዋ!” ብለው ከእኩይ ተግባሩ እንዲታቀብላቸው ሊያስፈራሩላቸው አሻፈረኝ ካለም አርጩሜ ቆርጠው ሾጥ ሾጥ አድርገው ሊያስተካክሉላቸው እንደማይችሉ ያውቃሉ:: ግን ተግባሩ መገለጽ ስላለበትና ለፎርማሊቲም ያህል መሆን ስለሚገባው ተደረገ:: በወያኔ እኩይ ተግባር አንጀቱ ያረረ ሁሉም ነው: የራሱ አባላት ጭምር:: ስለዚህ የወያኔን ብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ ሰነዶችን ማግኘት ከባድ አልነበረም::
አይደርስ የለምና የምርጫው እለት ግንቦት 7 1997 ደረሰ:: ሁሉም በጠዋት ተነስቶ ስፍራ ስፍራውን ይዟል:: የቅንጅት ጽ/ቤት በጣም በጠዋት እንዲከፈት በተወሰነው መሰረት ጽ/ቤቱ ውስጥ እንዲሰሩ የተመደቡት ሰዎች በጠዋት ተገኝተው ስራቸውን ማከናወን ጀምረዋል:: ሪፖርት ይቀበላሉ: ሪፖርት ያደርጋሉ:: በምርጫ ጣቢያወች በታዛቢነት የተመደቡት የቅንጅት ሰዎች ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷቸው ተሸኝተዋል:: “ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት የምርጫ ኮሮጆው ባዶ መሆኑን አረጋግጡ: ብአዴኖች ሊያበራግጓችሁ ስለሚሞክሩ በምንም መልኩ ሳትደናገጡ በትእግስት ማጠናቀቅ አለባችሁ:: መራጩ ህዝብ ላይ የሚደረገውን ወከባ ተጋፈጡ:: የሚስጥር ድምጽ መስጫው አካባቢ የኢሕአዴግ ሰዎችን እንቅስቃሴ ተከታተሉ: የድምጽ ቆጠራው እንደተጠናቀቀ የምርጫ ጣቢያው ማህተም ያረፈበት ውጤት ተቀብላችሁ በፍጥነት ወደጽ/ቤት እንድትመለሱ —” ተብለው ተመክረው ነው ቀድመው በየምድብ ቦታቸው እንዲገኙ የተደረጉት:: በሌላ በኩል ከኗሪው ጋር ተመሳስለው በምርጫ ጣቢያወች አካባቢ የሚደረጉ ሁኔታወችን እየተከታተሉ በስልክ ጽ/ቤት ላሉት ሰዎች እንዲያስተላልፉ የተመደቡት ሰዎች በንቃትና በጥንቃቄ ግዳጃቸውን እየተወጡ ነው:: ሁሉም ነገር አሪፍ ነው:: ኢሕአዴግ በምእራብ ጐጃሞች ላይ ተደጋጋሚ የፍተሻ ተኩስ አካሂዶ ችግር የለም ብሎ ደምድሟል:: በወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት የፍተሻ ተኩስ ማለት አንድ ጠላት ሊኖርበት ይችላል ተብሎ የተጠረጠረ አካባቢ ላይ የሚደረግ የሩምታ ተኩስና አሰሳ ነው:: ተኩስ በተደረገበት አካባቢ ጠላት ካለ የአጸፋ ተኩስ ይከፍታል:: ምእራብ ጐጃሞች ይህን የፍተሻ ተኩስ አልፈውታል:: በየስብሰባው ላይ እየተገኙ የገዥው ፓርቲ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል:: ደረሱብን ብለው ያሏቸውን ችግሮች አሰምተው በሚቀጥሉት አምስት የስልጣን ዘመናቸው ችግሮቻቸው እንደሚቀረፉላቸው በብአዴኖች ቃል ተገብቶላቸዋል:: የየተሰበሰቡበት የውሎ አበል ተከፍሏቸው ተቀብለዋል:: በየስብሰባው ማብቂያ ላይ የቀረበውን ድግስ በደስታ ተጋብዘው ተመራርቀዋል:: ቅንጅት ጸረ ልማት ድርጅት እንደሆነ ተነግሯቸው ልክ ነው ብለው ቅንጅትን አውግዘው ፈክረዋል:: ስለዚህ ብአዴኖች በምእራብ ጐጃም ላይ ስጋት የለባቸውም:: ሙሉ ሀይላቸውን እነርሱን በሚነቅፉና አስተማማኝነታቸው በሚያጠራጥር ዞኖች ላይ ብቻ ማሳረፍ እንዳለባቸው አምነዋል:: እና ለምእራብ ጎጃም የየምርጫ ጣቢያ አስመራጮች የተለየ መመሪያ አልተላለፈም::
የምርጫው እለት ማታ መላው የባሕርዳር ህዝብ እንቅልፍ በአይኑ አልዞረም:: በንቃት ይጠብቃል:: መብራት አሁንም አሁንም ይቋረጣል:: “ሌባ ሌባ” ሲል ሕዝቡ ይጮሀል:: ብአዴኖች ወያኔ የሚሆነውን የሚሆኑ: አድርጉ የሚባሉትን የሚያደርጉ ሮቦቶች ናቸው ብሎ ስለሚያምን ሁሌም ይጠራጠራቸዋል:: መብራት የሚያጠፉ ቀድመው ባዘጋጁት የተሞላ የምርጫ ኮሮጆ ሕዝብ ድምጽ የሰጠበትን ኮረጆ ለመቀየር ነው ብሎ ይጠረጥራል:: እና መብራት ሲጠፋ “ሌባ ሌባ” እያለ ግር ብሎ ወደየምርጫ ጣቢያዎች ይተማል:: አንዳንድ ባለመኪኖች የመኪናዎቻቸውን የፊት መብራቶች ወደምርጫው ቦታ ቦገግ አድርገው በማብራት ሌብነቱን ለመከላከል ይጥራሉ:: በጥበቃ ብዛት ሕዝቡ ተሰላችቶ ወደየቤቱ እንዲመለስ ይመስላል ጊዜን በአግባቡ አለመጠቀም ይታያል:: እሁድ በጠዋት ወረፋ ይዞ ቀድሞ መርጦ ወደጉዳዩ ለመሰማራት ያሰበው ሕዝብ ወረፋው አልደርስ ብሎ እስከእኩለ ሌሊት ድረስ ተጉላላ:: ቢሆንም ሁሉም በእልህ: በጽናትና በትእግስት የፍላጎቱን አሳካ- መረጠ::
ሻለቃ ልጃቸውን እንደሚድሩ አባት በደስታ ብዛት የሚይዙትን የሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል:: ይህን ይዘው ያን ይጥላሉ:: ወዲያ ሄድው ወዲህ ይመለሳሉ:: ሳያስቡት ብድግ ይሉና ተመልሰው ቁጭ ይላሉ:: እርሳቸው የሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል መራጭ ወገኖቻቸው አይዞህ ብለዋቸዋል:: ደራወች ጥለው አይጥሏቸውም:: ምእራብ ጐጃም በርሳቸው የተደራጀ በመሆኑ በአሸናፊነት እንደሚወጡ ሙሉ እምነት አላቸው::
ሰኞ እለት ከጠዋት ጀምሮ የቅንጅት የምርጫ ታዛቢወች እየተንጠባጠቡ ወደቅንጅት ጽ/ቤቶች መምጣት ጀመሩ:: የየምርጫ ጣቢያው ማህተም ያለበት የድምጽ ውጤት በእጃቸው ይዘዋል:: የቅንጅት አስተባባሪወች የየምርጫ ክልሎችን አሸናፊ ለማወቅ ከየምርጫ ጣቢያወች የመጡትን ውጤቶች መደመር ቀጠሉ:: ለማመን ይከብዳል:: ምእራብ ጐጃም ላይ መቶ በመቶ (100%) ቅንጅት አሸንፏል:: ቅንጅቶች ብዙ አይነት ስሜት እየተሰማቸው ነው:: ደስታ: ስጋት: ፍርሀት:: ደስታቸው:- የትግላቸው ፍሬ መልካም ከመሆኑ የመጣ ነው:: ስጋታቸው:- ምእራብ ጐጃም ላይ የተገኘው ውጤት በሌሎች ዞኖችና ክልሎች ያልተገኘ እንደሆነ ከሚል የመነጨ ነው:: ፍርሀታቸው:- ሕዝብ በድምጹ የጣለው መንግስት ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል ካለማወቃቸው የተነሳ ነው:: ምናልባት ምክንያት ፈጥረው በድርጅቱና በአባላቱ ላይ የጥፋት ስራ ቢሰሩስ? ሕዝቡንስ ይበቀሉት ይሆን? ወይስ ምን?
ሻለቃ ወታደር በመሆናቸው ጠርጣራ ናቸው:: በተለይ ወያኔ ከቶውንም ሊታመን የማይችል ድርጅት ነው:: ብአዴኖች ደግሞ የራሳቸው ህሊና የላቸውም:: አስፈራራ ሲባሉ የሚያስፈራሩ: ደብድቡ ሲባሉ ሙልጭ አድርገው የሚገርፉ: እሰሩ ሲሏቸው የሚያስሩ: ግደሉ ሲባሉ የሚገድሉ ናቸው:: ለእነርሱ ሕዝብ: ሞራል: ምናምን ቦታ የላቸውም:: ስለዚህ ወያኔ ሱርፍ ብሎበት ‘ለየታዛቢወች የሰጣችኋቸውን የውጤት መግለጫ ሰነዶች በአስቸኳይ ቀሙ’ ካላቸው እሳት ጐርሰው እሳት ለብሰው እንደሚመጡባቸው ያውቃሉ:: አሁንም ፍጥነት ያስፈልጋል:: የውጤት መግለጫ ሰነዶችን ሰብስቦ ማራቅ::
የምእራብ ጐጃም አርሶ አደር ታሪክ ሰራ:: እንዲህ ያለ ውጤት በየትኛውም የሀገሪቱ የየክልል ዞኖች አልታየም:: ሻለቃ በምእራብ ጎጃም ኮርተዋል:: ቃሉን የማያጥፍ: ለእውነት የቆመ: የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ስብስብ ሲሉ ያሞካሻሉ:: ወያኔ ደግሞ ‘ጐጃም በከፋ ሁኔታ አጠቃን:: ጉድ ሰራን:: ጐጃምና ተልባ እያደረ ሸርተት ነው የሚባለው ተረት ሀሰት መስሎን ነበር’ ሳይል አይቀርም:: ጐጃም በፍርሀትና በጥቅም ቃሉን አይለውጥም:: በነጻነት ለመወሰን እድሉን ሲያገኝ ሁሌም ከእውነት ጐን የሚሰለፍ ባለማተብ ሕዝብ ነው:: ’ውሻ በበላበት ይጮሀል’ የጎጃሞች መለያ አይደለም::
ቅንጅት በበርካታ የምርጫ ክልሎች ተጭበርብረናል ባለበት ወቅት አያልቅበት ወያኔም “ካላችሁስ ኧረ እኔም ተጭበርብሬአለሁ” ብሎ ቀረበ:: ይሉኝታና ሀፍረት አልፈጠረበትም:: ለነገሩ ይሉኝታና ሀፍረት የፋራ ነው: ወያኔ ደግሞ አራዳ:: ቅንጅት ቅሬታ ካቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች በዳግም ምርጫው አንድም ሳያገኝ ቀረ:: ወያኔዎች ተጭበርብረናል ብለው ቅሬታ ያቀረቡባቸውን ቦታወች አስመለሱ:: እንዲህ ናቸው ወያኔዎች:- ታግለው የሚጥሉ: አባረው የሚይዙ: ሮጠው የሚያመልጡ: ተናግረው የሚያሳምኑ: ተከራክረው የሚረቱ:: እና ሁሉም ሆነ:: በዳግም ምርጫው ምእራብ ጐጃም በድምጹ አስከብሮት የነበረውን አንድ ወንበር አጣ:: ም/አፈ ጉባኤ ሽታየ ምናለ በዳግም ምርጫው በክንዳሙ ወያኔ እገዛ አንድ የፓርላማ ወንበር ከህዝብ ነጠቁ::
-ጐጃም በመጀመሪያወች የወያኔ የግዛት አመታት በተጭበረበረ ገንዘብ ምርቱን ተነጥቋል::
-በ1989 ዓ.ም አካባቢ የጐጃም ሕዝብ ‘የደበቅኸው መሳሪያ አለ’ ተብሎ ታስሯል: ተገርፏል: ተገድሏል::
-ከምርጫው በኋላ ኢሕአዴግ የአማራ ክልልን እንደተሸነፈ አምኖ ሊለቅ ነው የሚል ወሬ ባ/ዳሮች ዘንድ ደረሰ:: ቀጥሎ “እስከቀበሌ ድረስ የሚዘልቅ የክልሉን መንግስት መዋቅር ሰርታችሁ በቶሎ አቅርቡ:: ከዘገየን ቅንጅት ሊያስተዳድር አልቻለም ብለው ተመልሰው ሊወስዱብን ይችላሉ” የሚል መልእክት ከቅንጅት ላእላይ ምክር ቤት መጣ በመባሉ: ኮሚቴ ተቋቁሞ ኰሚቴው የክልሉን መንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ሰርቶ ሰነዱ ፋክስ ተደርጐ ነበር:: ፋክስ የተደረገው ጊዮን ሆቴል በሚገኘው የፋክስ ሜሽን ነበር:: ፋክሱ ለቅንጅት ላእላይ ምክር ቤት መድረስ አለመድረሱ አልተረጋገጠም:: ብአዴኖች ግን እንዴት እንዳገኙት ሳይታወቅ ኮፒው ደርሷቸዋል:: እና በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያስቀመጡትን ሁሉ ሰብስበው አሰሩ:: እስረኞች ሌሊት ሌሊት በሽፍን መኪና ወደመሸንቲ መንገድ እየተወሰዱ ጫካ ውስጥ ተገረፉ::
-በጥቅምት 1998 የባሕርዳር ኗሪዎች በጥይት ተደበደቡ::
-በሚኒሊክ ጊዜ በደል ተፈጽሞብናል በሚል በአሁኑ ዘመን ያለውን አማራ ለመበቀል ያላፈረው ወያኔ የትናንቱን የምእራብ ጐጃም ጥቃት እንዴት ሊረሳው ይችላል? እና ጐጃሞች ዛሬም በሰበብ አስባቡ እየተሳደዱ ነው::
ሻለቃ ሀይለየሱስ እጅጉ በሀላፊነታቸው ስር የተቀመጡትን ባ/ዳር ልዩ ዞንና ምእራብ ጎጃም ዞንን እድሜና ተሞክሮ ባጐናጸፋቸው ዘዴ ተጠቅመው ከሁሉም አባላት ጋር አሸንፈዋል:: የድሉ ባለቤትና የትግሉ አራማጅ የነበሩትን መላው የቅንጅት ቤተሰቦች: መላው የባህርዳርና የምእራብ ጎጃም እንዲሁም የራሳቸውን መራጭ የደራ ህዝብ ከልባቸው የክብር መዝገብ ላይ አስፍረዋል:: የቅንጅት አባላትም ሻለቃን በክብር ያስቧቸዋል::
አማሮች ዛሬም ሁነኛ ሰው ያስፈልጋቸዋል::
ረጅም እድሜ ለሻለቃ (ሻቃ) ሀይለየሱስ እጅጉ!