May 21, 2014
59 mins read

ጅብ ቲበላህ… በልተኸው ተቀደስ – ከጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ (የቀድሞው ጦቢያ መጽሄት አምደኛ)  

ወያኔዎች አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ የነበሩትን ዕለታት ክንውኖች በሥርዓት የመመዝገብ ልምድ ያለው ሰው የሚያሰፍራቸው ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ይኖሩታል። ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ። የእኔን የመጀመሪያ ዕለት አጭር ማስታወሻ ልንገራችሁ። በማለዳ ተነስቼ ጋቢዬን አጣፍቼ ከበሬ ላይ ቆሜ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አህዮች ወደ መሐል ከተማው (አዲስ አበባ) ሲጓዙ አያለሁ። ያንኑ ያህል ባራባሶ ጫማ የተጫሙ፣ የአካል ዝለት የሚታይባቸውና ከእህል ጋር ከተለያዩ አያል ቀን የሆናቸው የሚመስሉ “ሰብአዊ ፍጥረቶች” አብረዋቸው ይሮጣሉ። ሲያሳዝኑ! ቆይ ቆይ…ከፓስተር ኢንስቲቱት በር ላይ አንድ ጥይት ተተኰሰ። ሌላ ጥይት- ሌላ ጥይት! ሰዎቹ ካለፉ በኋላ ወጣ ብለን ያየነው ሟች በሰፈሩ እንደ ሕሊና ሕመምተኛ የሚታወቅ ነበር።
 እንግዶቹ አልመው የሚተኩሱ፣ አስበው የሚገድሉ አልመሰሉኝ አሉ። የሚያስቡበትና የሚያልሙበት ሕሊና የሌላቸው ፍጥረታት አድርጌ ላያቸው አልደፈርሁም። ባይሆን ሁሉም ጠላታችሁ ነውና አንዲት ጥይት ጮኸች ወይም አንድ ሰው ትንሽ ድምፅ አሰማ “በለው” በሚል መዘውር የተዘወሩ “መዘውራን” በመሆን በሳሩም በቅጠሉም ኤኬ47ቱን ማንጣጣት ያዙ። ያን ጊዜ በአእምሮዬ ጥግ በምትገኘው የማስታወሻ ሰሌዳዬ ላይ “ይኽ ቀን ገሐነም ባዶውን ያደረበት ዕለት ነው” ብዬ መዘገብሁ። እነዚህ ሰዎች እንደ መሪዎቻቸው በጥላቻ የተጠመቁ ከሆኑ መመለሻው ይቸግረናል። ከቶ ከየት ተነሥተን የት እንደርስ ይሆን? የማልረሳው ማስታወሻዬ ነው።
 የጥንቱ ጋዜጠኛ ግዮን ሐጐስ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ተከሰው ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ሪፖርተር ሆኖ ተመድቦ ነበር። ያን ጊዜ እኔ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበርሁ። መሬቱ ይቅለለውና ግዮን ሐጐስ ስለ ጄኔራል መንግስቱ ሲያወራኝ “በንግግራቸው መሐል ኰራ ብለውና ችሎቱን እየቃኙ ዓይናቸውን- አራት ማዕዘን እየወረወሩ- “ የተናቀ ከተማ በአህያ ይወረራል” ይሉ ነበር። ( በነገራችሽን ላይ ጄኔራል መንግስቱ አንድ ዓይናቸው ጠፍቶ ነበር። በወንድማቸው በአቶ ገርማሜ ንዋይ በተተኰሰባቸው ጥይት)
 
 የአህያን ሠራዊት ወግ – በቁሙና በእርቃኑ -እንደገና የሰማሁት ከባድመ ጦርነት በኋላ – ከባድመ ጦርነት ጋር ሲዘገብ ነው። የጦርነቱን ዳፋ- ድልና ሽንፈት – ውጤትና ሰብአዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ ያካተተ አንድ ጥናት እንደሚለው በራስ ስዩም የፈረስ ስም በምትጠራዋ “በይርጋ ጉብታ” ትራያንግል- በባድመ በተደረገው ጦርነት በፊተኛው ረድፍ ተሰልፈው የቀዳሚ- ሰማዕትነትን ሙያ የተወጡ 36ሺህ ኢትዮጵያውያን አህዮች ናቸው። ግፍ የተፈፀመባቸው እንስሳት ይባሉ?..ከጥናቱ እንደ ተረዳሁት ከአርባ ሺህ በላይ የሚሆኑ የሰሜን- ምዕራብ ኢትዮጵያ ገበሬዎች የኢሳይያስ ሠራዊት እንደ ድንች በዚያ አካባቢ የቀበራቸውን ፈንጂዎች እንዲያመክኑ ተደረገ። በአጭሩ አህያውም “ሰውም”- በወያኔ ትርጉም አማራ ሰው ከተባለ- በፈንጂ ማሳ ላይ እየተንደባለሉ አለቁ። አንድ ቀን ነፃነት ከተመለሰ ለዚያ ሁሉ ሕዝብ ውሎ ይደረግ ይሆናል። ለአህዮቻችንም ጭምር!
 ይህን የጦር ሜዳ መረጃ በቅርቡ ያገኘሁት አይደለም። ዜናው ከዓለም ኅብረተሰብ ተደብቆ የቆየበትን ሁኔታ ሳስብ ግን በውስጤ ያለውን ክርስትና ጌታ ፍትሕ ወደ መጠየቁ አዘነብላለሁ። በዚህ ዓይነት ይህን ሁሉ ሕዝብ ያስጨረሱትን እኩያን ወገኖች ተፋረዳቸው ማለት ኅጢአት ነውን? ብሎ ግማሽ እኔ ይጠይቃል። ግማሽ እኔ ደግሞ ክርስቲያን ፍርድ አይጠይቅም። ምሕረት እንጂ። ጌታም ገዳዮቹን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ይለኛል። አሁን ከሕሊናዬ ጋር ወደ መታረቁና ትክክለኛውንም መንገድ ወደ መከተሉ ነኝ። ከሰባት ጊዜ ሰባት በላይ ይቅር ብለናቸዋል። ስለዚህ ወሎዬ ዘመዴ እንደሚለው “ጅብ ቲበላህ በልተኸው ተቀደስ” ይስማማኛል። እናንተንም ይስማማችሁ። እስኪጨርሱን እንቆይ? ጋንዲንና ማርቲን ሉተር ኪንግን እንርሳቸው። ሙሴ ይሻለናል።
 እንዲህ ዓይነቱን ዜና ታላቅ ወንድማችን (ቢግ ብራዘር) አልስማም? አላወቀም? በቢሊዮን በሚቆጠር የሳር ክምር ውስጥ የወደቀች መርፌ ዋሽንግተን ተቀምጦ ዴዴሳ በረሃ ለሚያይና ለሚለይ የሲአይኤ ሰላይ ሠላሳ ስድስት ሺህ አህያና አርባ ሺህ የሰሜን ምዕራብ ነዋሪ ህዝብ በፈንጂ ማሳ ውስጥ ተንከባልሎ ሲያልቅ አያውቅም “አላወቀም” ብለን የምንገኝ ተላላዎች ነን..? ሐቁ ወደዚህ ሳይሆን ወደዚያ ነው። ይልቁንም የሾሙአቸው አምባገነኖች በመድረኩ ላይ እስካሉ ድረስ ምንኛ እንደሚቆረቆሩላቸው፣ ምንኛ ምሥጢር ጠባቂያቸው ሆነው እንደሚቆዩ..ነው የሚገባን። አቶ ተስፋዬ ገብረ አብ ከኢትዮጵያ በኩል ያለውን ሰብአዊ ኪሣራ በአንዱ መጽሐፉ ይገልጥልናል። 98ሺህ ይለናል። በመቆርቆር ይሁን ወይም የኤርትራን አሸናፊነት ለመግለጥ አይታወቅም። ሃይማኖቱን አልጠይቅም። ከሕሊና ጋር አልተፈጠረም ደግሞ አልልም። አለዚያ በማን ላይ ትከስሰዋለህ? ከአነስተኛ የሚሊተሪ ሳይንስ ንባቤና ከኤርትራ ግንባር ሰልፌ እንደምረዳው ግን አንድ ሠራዊት ሁነኛ የማጥቂያ ግንባር ይዞና ቀጣናውን በፈንጅ አጥሮ ከተቀመጠ ለማጥቃት የሚመጣው ኅይል ሌላ ስልት መከተል አለበት። ጥበቃው የሳሳ ስፍራ መምረጥ አለበት። እርድ አዘጋጅቶ የተቀመጠውን ኅይል ከዚያ ምሽግ ማስወጣት ዋናው ታክቲክ ነው። በአድዋ ማርያም ሸዊቶ ላይ አጤ ምኒልክ ይህን ነበር ያደረጉት። ለወያኔና ለመለስ ዜናዊ ያንን ያህል “አማራና ኦሮሞ” ማስጨረስ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ኪሳራ ሆኖ አልታየም። ኖሮ አይጠቀምበትም በሞቱም አይጐዳም!
 በፈንጂ አማካይነት ብቻ ሳይሆን እንዲሁ የወያኔ ሰፈርም ሆነ የኤርትራው ግንባር ዘመናዊ መሳሪያ ማገዶ ሆነው ያለቁት ስንት የሚሆኑ ይመስላችኋል? እንደ ወጡ የቀሩትን ወገኖቻችንን የእልቂት ሁኔታ (ወሬ) የሚያቃምሰን ለምንና እንዴት ጠፋ?..ከጦርነቱ – ከእሳቱና ከእልቂቱ አምልጦ መርዶውን የሚያሰማንማ አልነበረም። እነዚህ በየዕለቱ በእጃቸው ላይ ትኩስ ደም ያለባቸውና ራሳቸውም “ትኩስ ደም ትኩስ ደም” የሚሸቱት አምባገነኖች እኛ ከምናስበው በላይ የሰለጠኑባቸው ተንኮሎች ሞልተዋል። ዊንስተን ቸርችል ከጆሴፍ ስታሊን ጋር የሰነበቱባቸውን ቀናት የምታውቁ ይመስለኛል። በጦርነቱ ወቅት ጄኔራ ሊዝሞ ስታሊን፣ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ዊንስተን ቸርችል ለተወሰኑ ቀናት በካይሮ በቆዩበት ጊዜ የተፈጠረ ነው። ቸርችልና ስታሊን በጨዋታ ተጠምደው ሳለ ንጥረ ነገሩን (ቮድካና ብራንዲ) ክፉኛ አጥቅተው ኖሮ የሚናገሩት ሁሉ የማይያያዝ – የእብድ ወግ ይሆናል። እንዲያውም ራሳቸውን መቆጣጠር ስላልቻሉ ከአስሩ የስታሊን አንጋቾች አምስቱ ቸርችልን፣ አምስቱ ደግሞ ስታሊንን ክንፍ ክንፋቸውን ይዘው ወደየ ክፍላቸው ወስደው ያስተኙቸዋል። በማግሥቱ ማለዳ ስካሩ ብዙም አልተለያቸውም። ቸርችል ደግሞ በታሪክ ጸሐፊዎቻቸው እንደሚነገረን ገላቸውን ሲታጠቡ እንኳ ሲጋርና ብራንዲ አይለያቸውም። ስለዚህ ከሶቪየቱ መሪ ጋር ሲገናኙ ‘እንደ መጠጥ ያለ አዋራጅ ነገር የለም! ትናንት ተዋረድን። ቢያንስ የርስዎ አጃቢዎች አይተውናል። ተዋርደናል!” ሲሉ ስታሊን “ኒየት! ኒየት! ማንም አያወራብንም። ትላንት የነበሩት ሰዎች እኮ የሉም” አሉ ይባላል። የሰው ነፍስ እጅግ ርካሽ በሆንበት ኢትዮጵያ ሥርዓቱ አንድ ሰሞን ሰማየ- ሰማያት ያጓናቸው ሰዎች በሌላ ወቅት አይኖሩም። ይልቁንም አንዱ ፍልስፍናቸው “ለወሬ ነጋሪነት ማንንም አለማትረፍ” የሚል ነው። እንዲያውም ለታላላቅ የስለላ ድርጅቶች (ኬጂቢ በተለይ) ይነገርላቸው እንደነበረው “ወያኔ እስከመቃብርህ ይከተልሃል” የሚል የውስጥ አዋቂዎች ግምት አለ። አደገኛ ከሆንክ የሞራልን ሕግጋት ሁሉ እየጣሱ ይከተሉሃል። ያጠፉሃል። እስከ ገሐነመ እሳት ይሸኙሃል።
  የአዲስ አበባ ቃጠሎ ተብሎ ከሚጠቀሰው የግንቦት መድኅኔ ዓለም ማግስት የነበረውን እናንተ ከረሳችሁት እኔ አስታውሳችኋለሁ። በዚያን ዕለት በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ተገናኝተን አሳብ ለአሳብ የተለዋወጥነው የቀድሞ አምባሰደርና የሃይማኖት ትምህርት እውቀቱ ላቅ ያለ ወዳጄ ምናልባት እንደኔው ያወራው ይሆናል። ልዩ ትርኢትና ልዩ መገለጥ ተብሎ የተወራለት- ማርያም ልጅዋን ታቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) በሰማዩ ላይ እየታየች ነው መባሉ ሲሆን ያንን አየን የሚሉትን ልዩ ቅዱሳን እንበላቸውና ሁለተኛው ከነትርጓሜው አብሮን አለ። በአእምሮዬ ቀርቶአል። ነገሩ እንዲህ ነው። በዚያን ዕለት የታየው ቀስተ ዳመና በቀጥታ ከሰማይ ላይ ወርዶ ምድሪቱ ላይ ተተክሎአል። አጠገቤ ያለ ሰው ሁሉ “እግዜሩ ሊታረቀን ነው። የደግ ቀን ምጽአት ምልክት ነው። እግዜአብሔር ዳግመኛ ምድርን በጥፋት ውኅ አላጠፋትም ብሎ ለኖህ ቃል ኪዳን ሲገባለት እንዲህ ያለ ቀስተ ዳመና በምልክትነት ሰጥቶታል..” ሲሉ እሰማለሁ። ይሁንና ያ የቀድሞ አምባሳደር ወዳጄ ጐተት አደረገኝና “በእኛ ቤተክርስቲያን እምነትና በተለይም በአበው ሊቃውንት ትርጉም መሠረት ይህ ቀስተ ደመና በጥሬው አይተረጐምም። የእልቂት፣ የስደት፣ የደም መፋሰስ ምልክት ነው። ስለዚህ ከሚመጣው አደጋ ሁሉ እንዲሰውረን መጸለይ አለብን፡፤ ቃሌን እንዳትረሳ” አለኝ። ስሙን ብገልጸው ደስ ባለኝ ነበር። የወቅቱ መኳንንት ያንገላቱታል ብዬ ፈራሁለት እንጂ።
 እንደ ሕልም፣ ትንቢትና ከላይ የጠቀስሁትን የተፈጥሮ ንባብ (ከነትርጓሜው) በተመለከተ አንዳንድ ሳይኪያትሪስቶችን መጠቃቀስ ይቻላል። ፍሮይድን፣ ፓቭሎቭን..በማንበብ ከትርጓሜው ላይ ለመድረስ -አለዚያም ከንቱ እምነትነቱን ለመግለጥ አይመችም። እነሱም አላጠኑትምና። ለምሳሌ እጅግ ጣፋጭ የሆነችውን የሐዲስ አለማየሁን “ትዝታ” ያነበባችሁ ትዝ የሚላችሁ ቁም ነገር አለ። አቶ ሐዲስ እንደሚገልጡት ከጠላት በፊት በደብረ ማርቆስ ከተማ አስኳላ ሲያስተምሩ አንድ ጥቁር እንግዳ ከቤታቸው ከች ይላል። እንዲያው በችኮላና በቁሙ “ሐዲስ! ኢትዮጵያን ጠላት ይወርራታል። አንተም ትዘምታለህ!” ብሎአቸው ይሄዳል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ይኸው ወዳጃቸው ከአባ አሥራት ገዳም ሲመለስ ወደ ሐዲስ ዓለማየሁ ቤት ይሄድና “ላጫውትህ አልችልም። እቸኩላለሁ። ሐዲስ! ኢትዮጵያ ትወረራለች። አንተም ወደ ጦር ሜዳ ትሄዳለህ። ትዘምታለህ!” ይላቸዋል። ከጥቂት ወራት በኋላ የጠላት ከምሥራቅና ከሰሜን መንቀሳቀስና ኢትዮጵያን መውረር ወሬ አየሩን ሞላው። የጐጃሙ ገዥ ራስ እምሩ የጐጃምንና የጐንደርን ጦር እየመሩ ወደ ሽሬ ግንባር ይዘምታሉ። ሐዲስ ዓለማየሁ የጦር ሜዳ የፕሮፓጋንዳ ሃላፊና ለጥቆም የብርቱ ምሥጢር ተላላኪ ሆነው ሲሠሩ ቆዩ። ሰውና ከብት በመርዝ ጋዝ ጢስ ያለቀበትን- የከብትና የሰው ደም ተቀላቅሎ ወንዙን (ተከዜን) ያስነፈጠበትን ሁኔታ ጥሩ ገላጭ የሆነችውን የሐዲስ ዓለማየሁን “ትዝታ” ያነብቡአል። (ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በዚሁ መጽሐፍ ቀስቃሽነት የፈጠራትን “እስከዳር” መጽሐፍን ልመርቅላችሁ። ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ወንድሜ የሆነው ሻለቃ ዳዊት በቅርብ ጊዜ የተጻፉ ታሪካዊ ልብ ወለዶች አንጋፋ ልትባል የምትችል መጽሐፍ በመድረሱ ባርኔጣዬን አነሳለታለሁ)
 “አምልኮ ወይም ምልኪ ነው” ልትሉኝ ትችላላችሁ። የፈቀዳችሁትን በሉኝ። ያ አምባሳደር (አ.ወ.አ) ግንቦት 28 1983 የነገረኝ የቀስተ ደመና ትርጉም እንደ ወንጌል ቃል አብሮኝ አለ። ወያኔ በምንም ጊዜና ቦታ፣ ሁኔታና እቅድ ረገድ የሚፈጽመውንና ያቀደውን ከመግለጥ ሸብረክ ያለበት ጊዜ የለም። ደበሎ ሰቅሎ ፍላጐቱንና ግቡን ይለፍፋል። ከዚያ ዓላማው ደግሞ ፈቀቅ ያለበት ወይም በመጠኑም ቢሆን አቋሙን ያለዘበበት አጋጣሚ አልነበረም። ከዚህ ውስጥ- ማለትም ከዚህ ጽንፈኛና ሕመምተኛ መንግሥት አውራ ግብ (ማስተር ፕላን) ውስጥ ዋነኛው አንዱን የተወሰነ ሕዝብና ሃይማኖት ማጥፋት ነው። ሕዝብን ለማስተዳደር (በመሰረቱ ለመግዛት) የመጣ አካል አንዱን የቋንቋ ክፍልና (ብሔረሰብ ለማለት የትርጉም ስሕተት አያለሁ) ሃይማኖቱን (ኦርቶዶክስ ተዋህዶ) ለመደምሰስ እቅድ እንዳለው ሲናገር – በግልጽ በአደባባይ ሕዝቡና ምሑሩ፣ ወጣቱና አእሩጉ፣ ቤተ ሃይማኖቱና ዓለምም በነቂስ አንዲት ትንፋሽ ተቃውሞ አላሰሙም። እንደኔም እንዲህ በሰላም ወጥተው ለመግባትና ሕሊና የሚያዝዘውን አውጥተው ለመናገር የሚችሉ ሁሉ ስለ “አማራው” እልቂት ማውሳት ከወቅቱ የፖለቲካ ፋሽን አንጻር ኋላ ቀር ስለሚያሰኝ ዝምታን መርጠዋል። ሁላችንም- ኦሮሞውም፣ አማራው ራሱም፣ ከምባታውም፣ ሌላ ሌላውም ኢትዮጵያዊ -እኛም የምንጫጭር ሰዎች ስለማንም- በተለይም ስለ አማራው ሕይወትና ንብረት፣ መብትና የግለሰብ ነፃነቱ መጻፍን- ልድገመውና ከፖለቲካው ፋሽን ወደ ኋላ መቅረት አደረግነው። ይኸ ደግሞ አዲስ “ግንዛቤና” አዲስም የፖለቲካ ፈሊጥ አይደለም።
 
 መለስንና አቋሙን የሚያውቁ ሰዎች በምስክርነት እንደሚያረጋግጡት የሰውዬው ቀዳሚ እምነት “አማራ ከገጸ – ኢትዮጵያና ከገጸ- ምድርም መጥፋት አለበት። አንዳንድ ጊዜ አስተዳደጋችሁና ባሕላችሁ በፈጠሩባችሁ ስሜትና ዝንባሌ ምክንያት ወንጀሉን የሚሰሩት ሰዎች የማያፍሩበትን ኅጢያት እናንተ በመጻፋችሁና በመቃወማችሁ ጭብጥ ታህል ትሆናላችሁ። እዚህ አካባቢ እንደታዘብሁት አንድ ጠንካራ ዜጋ “ አንድ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ለምን የጥፋት ዒላማ ይሆናል? ” በማለቱ አንዳንዱ ሰው “የትግሬ ጠላት” አድርጐ ይስለዋል። መለስ ዜናዊ፣ ታምራት ላይኔ…አማራንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ስለማጥፋት ሲናገሩ ምን ተሰማን? ምንስ አልን? ለመሆኑ ትግራዩን ሕዝብ በጠቅላላውም ባይሆን አድዋውያንን ስለ ማጥፋት ቢነሳ ዝምታ የዜግነት ግዴታ ነው እንላለን? ከፖለቲካው ፋሽን ውጭ ነውና በዚያው እንቀጥል ይባላል? የዛሬው የፖለቲካ ፋሽን አማራን ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ መክሰስ፣ በኅላፊነት ማጋለጥና መዝለፍ ነው። ያ ቢበቃ ደግ ነበር። አንዳንዶች በእምነት፣ አንዳንዶች ለጣቢታ (ኩርማን እንጀራ) አንዳንዶች ደግሞ “እንደ ንጉሡ አጐንብሱ” በሚለው ፍልስፍና መሠረት የሚያሰሙት አዝማች ነው። ለመሆኑ ሕዝብ እያለቀና የበለጠም እንደ ተደገሰ ይሰማችኋልን?
  ፕሮፌሰር አሥራት የመላው አማራ ድርጅትን ሲመሰርቱ ከምሁራን መካከል ወዳጆቻቸው የሆኑ ጥቂት ሰዎች በግል እንዳነጋገሩአቸው አውቃለሁ። እኔም በግሌ ከእሳቸው ጋር ባለኝ ራፖርና በተጨማሪም ምክትላቸው ከነበሩት ከአቶ ኅይሉ ሻውል ጋር ፖለቲካ ወደ ጐሳ በሚወርድበት ጊዜ ስለሚከተለው ጣጣና በተለይ የእነሱ ወያኔ በፈጠረው ጉድጓድ ውስጥ መግባት አርአያነቱ የሚያስከትለውን ችግር ሁሉ ዘርዝሬ ሞግቻቸው ነበር። ሙግቴ የበለጠውን ከፕሮፌሰር አሥራት ጋር ሲሆን በእሳቸው በኩል ያለው ጥረት በአርሲ፣ በሐረርጌ..ወዘተ እያለቁ የሚጮህላቸው ያጡትን አማሮች መብት ለመጠበቅ መሆኑንና የፖለቲካ ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ እንዳላሳዩና ወደፊትም እንዳማያሳዩ ገለጡልኝ። ለሁለቱም አንጋፋ ዜጐች  በተለያየ ሥፍራና ጊዜ በኢትዮጵያ ስም የሚቋቋም የፖለቲካ አካል (ግንባር፣ ድርጅት ወይም ፓርቲ) ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መብትና ነፃነት ስለሚቆም መአሕድ ወደ ፓርቲ የሚያደርገውን ሽግግር ቢያቆሙት እንደሚሻል ለመምከር ሞከርሁ። ምከሬ ደካማ ሆኖ የመአሕድ ፓርቲ ተመሰረተ። ከኢትዮጵያዊ ሁሉ ልብ ሊጠፉ የማይችሉት ታላቅ ዜጋም የዘመናቸው የአገር ሰማዕት ሆኑ። ወያኔ እስከመቃብር ተከተላቸው። በፖለቲካው አምባ እንደ አባዩ የሩሲያ መነኩሴ እንደ ራስ ፑቲን ይቆጠሩ የነበሩት አባ ጳውሎስ ደግሞ ለአሥራት በተቆፈረው መቃብር ዘልለው ለመግባት ፈልገው ነበር ይባላል። አይ ደበበ እሸቱ! በሞታችን ቴያትር እየተሰራብን ነው። ይኸ የአንድ ሰው ሞት አልነበረም። የሺዎች እልቂት እንጂ!
 በእኔና እንደኔ ከቀዩ ፍልስፍና መልስ ወደ መንደር መውረድን ዝቅጠት አድርገን ለተመለከትነው ወገኖች በመለስ ዜናዊ በተዘጋጁልን የጐሳ ጉድጓዶች ውስጥ እየሮጡ መወሸቅ አገሪቱን በመበጣጠስ ረገድ ተባባሪ መሆን ይመስለኛል። ይሁንና በዚያው ጊዜ ውስጥየታዘብሁት አንድ አስገራሚ ነገር የማላስባቸው ሰዎችን ከማላስባቸው ሰፈሮች ማግኘቴ ነበር። ለተወሰኑ ሳምንታት ሳይታሰር የቆየና በነበረው ሥፍራ እኔንና ሌሎችን የኢንፎርሜሽን ድርጅቶች ኅላፊዎች እየሰበሰበ ከማለዳ እስከ መንፈቀ ሌሊት እጅ እጅ የሚል ገለጣ ሲሰጠን የኖረን የደርግ አባል ከአንድ የጐረቤት ልቅሶ ላይ አገኘሁ። “ነፍጠኛ….ነፍጠኞች…ብሔር- ብሔረሰብ..ሕዝቦች ” ሲል ሰማሁትና “ጓድ ማለቴን ትቼ ኦቦ ልበልህ…እንደ አመጣጥህና ፍጥነትህ ወደፊት አንዳች አደጋ ካልደረሰብህ የኢህአዴግ አመራር አባል የማትሆንበት ምክንያት አይታየኝም። ቋንቋቸውን ብቻ ሳይሆን ጽንሰ-አሳቡንም …ዓላማቸውንም ዓላማህ በማድረጉ ረገድ ፈጥነህ ራስህን አስተካክለሃል። በእኔ በኩል ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ በጐሳ በመሸንሸኑ ረገድ የለሁበትም። እነሱ ይዘውት የመጡትን ይህን በሽታ ደግሞ ሁላችንም መድን ተከትበን የምንከታተለው መስሎኝ ነበር” አልሁት። የደርግ አባሉ ሌሎቹ አንጋፋ የደርግ አባላት ከተያዙ በኋላም ለሳምንታት በከተማው ውስጥ ሲነዳ ዓይን ስቦ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። በአጭሩ ግን ጥቂት የማይባሉ ከእኛው “የአብዮቱ ሰፈር” ጭቃው ሳይነካቸው፣ ርእዮተ ዓለሙም ሳይጠልፋቸው በአንዳች ኀይል ወደ ወያኔ ሰፈር- የድል አምባ – የተሻገሩ በርከት ያሉ ነበሩ። አሁንም የሉም ትላላችሁ? ሌሎችም አሉ እንጂ! የኢሰፓ አባል ለመሆን ብዙ መከራ አድርገው በሞራላቸው፣ በሥራ አፈጻጸማቸው፣ በየቢሮውና ፋብሪካው በነበራቸው ነውር ተንቀው የቀሩም ግመልና ዝሆን የሚያስገባ አዳራሽ አግኝተው ሲሣይ ማፈስና የጠሉትን መርገጥ ሆነላቸው። የልዩ ዐቃቤ ሕግ ሹም የነበረውን ግርማ ዋቅጅራን ለአብነት ይጠቅሱአል። እነዚህ ሁሉ ዜጐችን ተበቅለው፣ አዋርደውና ገድለው ቢበቃቸው አንድ ነገር ነበር። አገርን በማፍረስና በመናዱ ረገድ ርኅራኄ የተለያቸው ሆኑ! እስመ ዓለም ምሕረቱ!
 የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ሲሰባሰቡ በአብዛኛዎቹ በጋዜጠኝነት ተገኝቻለሁ። ገና በነፃነት ጎዳና ብዙ ያልተጓዙት “የአፍሪካ አባቶች” ተብለው የሚጠቀሱት መሪዎች መላልሰው ሲናገሩ እንሰማቸው የነበረው ጐሳ በፖለቲካ፣ ፖለቲካም በጐሳ ውስጥ ሲገባ ሰፊ ራእይ ያየንላት አኀጉራችን መመለሻ ወደሌለው እንጦሮጦስ ትወርዳለች እያሉ ነበር። ያ ልክፍት በእኛ ዘንድ እንደ ልዩ ነገር ሳይቆጠር አልቀረም። እንዲያውም የረጅም ዘመን የነፃነት ኑሮአችን ሰፋ ካለ “ኢትዮጵያዊነት”ና አገራዊ አመለካከት እርከን ላይ አድርሶናል ብለን እንወያይ ነበር። በኩራት!
 ወያኔ ከከፍተኛ ማማና ኅብረተሰባዊ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰናል፣ ሕዝባችን የአንድነት መሰረቱ ጽኑ ነው በምንልበት ሰዓት ነው የተናቀና እጅግ ኋላቀር የፖለቲካ ሥርዓት አምጥቶ የዚያ ባዕድ አምልኮ “ጊኒ ፒግ” ያደረገን። በእኔ በኩል ይህን ሒደት የኢትዮጵያ ውርደት፣ የፖለቲካም መዝቀጥ አድርጌ አየዋለሁ። የመለስ ዜናዊ አድናቂዎችንም የምፋለማቸው በዚህ ዓቢይ ነጥብ ነው። በዚያ ላይ ነው እልቂቱ፣ አገር ሸንሽኖ መሸጡ፣ ታላቂቱን ኢትዮጵያ በአረቡ፣ በሕንዱ፣ በፓኪስታኑ..በቻይናው እግር ሥር ማውረዱ የመጣው። እኔ የመጣሁበት ፖለቲካ (ኢሠፓ ነው አትበሉኝና) ሁሉን ሠርቶ አደሮች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዜጋ የሚያስተሳስረው – በአንድነትና በአንድ ዓላማ የሚያስተባብረው፣ የኢትዮጵያ ልጅነትን የሚያራምደው አንድ ለሁሉም ሁሉም ለአንድ የሚያቆመው የዜግነት መሠረት ነው። እኔ ከአድማስ ባሻገር የማየው ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፍትሕ የነገሠበት፣ ሰው በሰው የማይበዘበዝበት ሥርዓት ነው። ሰውን የሚያከብር፣ የዜጋውን ሰብአዊነትና ሉአላዊነት – ባለስልጣንነት የሚያውቅ ሥርዓተ መንግሥት ነው። የኮሚኒስት ሥርዓት ማለት አይደለም። ከዚያ በላይ የሚያበራ፣ ከዚያ በላይ እምነት የሚጣልበት ሥርዓት ነው። የፖለቲካ ሥርዓት ወይም ሥነ መንግሥት “ኢዝም” ብቻ አይደለም። ከኢዝም በላይ አስባለሁ። አስቡ! ከ1960 ጀምሮ እንዲህ እንዲህ እያለ እየተጠረቃቀመ የሚመጣውን አደጋ በማጤን ኢትዮጵያዊነትና ብሔራዊ ስሜት ከምንም በላይ የሚያበራ ኮከብ ይሆን ዘንድ በግንባር ቀደምትነት ሞክረን ነበር። ውስጥ ለውስጥ ይህን ሲታገሉ የነበሩ ኅይሎች ናቸው ይፋ ወጥተው – ይፋ ግፍ የሚፈጽሙት። አልተኙልንም። አንተኛላቸው። እየገደሉን ናቸው። ጠላትህን መግደል ነው ያልጀመርኸው።
 ልምዱንና የፖለቲካ ዓላማውን ከተማሪ እንቅስቃሴ ጋር ከሚያዛምደው ትውልድ መሐል አይደለሁም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሕግ እውቅናና የማይገሰስ ሕዝባዊ ሥልጣኑ ከታወቀ የምርጫ መብቱና ክብሩ ከተረጋገጠ እንዲበቃኝ ወስኛለሁ። ስለዚህ ከአጠቃላዩ ነጠላውን በመውሰድ እገሌ መታወቅ ያለበት በጐሳው መሆን አለበት ከሚለው ሰፈር ሥፍራ እንዲኖረኝ ፈልጌ አላውቅም። አንዳንድ ሰዎች ይኸ “ናኢቭ አሳብ ነው” ይሉ ይሆናል። የዋህነት አይደለም። የኦሮሞ ነፃነት፣ የአማራ ነፃነት፣ የጉራጌ ነፃነት፣ የትግሬ ነፃነት በሚለው ሰፈር የለሁበትም። በቶሎሳ፣ በጫኔ፣ በጠንክር፣ በሐጐስ…ነፃነት ግን አምናለሁ። እዚህ ላይ እንረፍ።
 አሁን ደርሶ የመጣው ልክፍት ለአንዱ ተሰጠ የሚባለው ነፃነት ሌላውን ከገጸ- ምድር የሚያጠፋው ሲሆን ወጣ ብለህ (አፈፍ ብለህ) ከትግሉ ግንባር ውስጥ የሚያሰልፍህ ነው። የፖለቲካው ፋሺን የሚጋብዘው የተወሰኑት የቋንቋ ክፍሎች ተነስተው ከተላለቁ በኋላ የተወሰኑት ደግሞ የመላዋ ኢትዮጵያ ገዢዎች ይሆኑ ዘንድ ነው። ወጣ እናድርገውና አማራና ኦሮሞ ሲጫረሱ፣ ይልቁንም የገዥነት ሚና ነበረው የሚሉት አማራ እስኪያልቅ ድረስ ከተመታ አብዛኛው የአገዛዝ ችግር ይቀረፋል። ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ሰዎች በአእምሮ ቅልጥፍናና በምሁራዊ ዝንባሌው ሲያደንቁት እሰማለሁ። እንዲህ ያለ የተበላሸ እንቁላል በአእምሮው ውስጥ ይዞ የኖረ ሰው “ቀልጣፋ፣ ምሁር..አሳቢ..ፈጣን…” የሚሉ ቃላትን በእሱ ላይ የሚነሰንሱ ሰዎች ናቸው ሊታዘንላቸው የሚገባ። ትልቁና ዋና ዓላማው የሕዝብ ፍጅት፣ የአገር መበታተንና የሚጠላውን ሁሉ ማጥፋት የሆነውን ሰው እስከ ማወደስ የሚደርስ ሰው በግድ ሳይክያትሪስት ማየት የሚገባው ነው።
 ከቀን አንድ ቀን ጀምሮ የነበረው ሁሉ አስደንጋጭ ነው። እንደዚያ ግንቦት 28 ቀን 1983 የታየውን ቀስተ ደመና የእልቂት ደመና አድርጐ እንደ ተረጐመው አምባሳደር በአማራውና በኦሮሞው መካከል የሚፈጠር ፍጅት ያሳሰባቸው አባቶችም ነበሩ። “የፖለቲካውን ፋሽን” ሳልፈራ ሁለት የተከበሩ ዜጐች መኖሪያ ቤት ሄድሁ። አንደኛው ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳ ነበሩ። ሁለተኛው ደግሞ ቢተወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ሲሆኑ ከጠላት በፊት ጀምሮ በአስተማሪነት፣ በዲፕሎማሲና በአገር አመራር ሰፊ ልምድና እውቅት ያካበቱ አባት ነበሩ። ሁለቱንም በተለያዩ ጊዜያት ቀጠሮ ይዤ አነጋገርኳቸው። ያን ጊዜ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ ዲማ የሚባል ሰብአዊ ፍጡር አማራ እያባረረ ይገድላል፤ በሐረርጌ በአሰቦት ነፍጠኛ ሁሉ እየተረሸነ ነው የሚባልበት ጊዜ ነበር። ያንን ደግሞ የሚያራግቡ፣ ትልልቁንና በጀግንነቱ የሚታወቀውን ኦሮሞ ጄኔራልና ራስ ሳይቀር በዘላን ቋንቋ የሚዘልፉ ጋዜጦች ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩበት ነበር። ይኸ አካሄድ ለቢትወደድም ለኮሎኔል ዓለሙም አልጣማቸውም ነበርና ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በማሰብ በሰፊው ተወያየንበት።
 
 ሁለቱንም ጐምቱ ዜጐች ገጽ ለገጽ ማገናኘት አልቻልሁም። ዓላማችን ግን ኮሎኔሉ በኦሮሞ አባትነት፣ ቢተወደድ ደግሞ በአማራ አባትነት አደባባይ ወጥተው “ሕዝቡን ለማጫረስ የተጠነሰሰውን ሴራ በሚያጋልጥ መልክ እንዲያወግዙ ነበር። ሁለቱም የሚወክሉትን ኅብረተሰብ ባሕልና ሥርዓት ስለሚያውቁ ተቃቅፈው ፍቅራቸውን በመግለጥ፣ የሁለቱንም ታሪክና የደም ትስስር በማብራራት እያሳሰበ የመጣውን የፖለቲካ ደመና እንዲያከሽፉት ለመሞከር ነበር። በሦስተኛው ቀን ኰሎኔል ዓለሙ “ሁሉም ነገር ጥሩ ነበር። ትናንትና ከበቀለ ነዲ ጋር ስንነጋገርበት ከእኛ መካከል ወደ እብደት የወሰዳቸው አክራሪዎችን ይጠንቀቁ። እዚሁ አጠገባችን ያለውን..ሰው ይህን ቢያዋዩት ሊገድልዎ ይችላል። አላወቁትም መሰለኝ እንጂ አለኝ” አሉ። በዚህ የተነሣ ፕሮጀክቴ ወደቀ። እኔም አሜሪካ ከሚሉት አገር ገባሁ። ከአንድ የብስጭትና የጭንቅ መንፈስ፣ ከአንድ ማንም ያለመልሰልኝ ጥያቄ ጋር ቀረሁ። እንዲህ ያለውን ጭካኔና ጥላቻ ከቶ ከየት አመጡት? የተወሰኑ ባለስልጣኖች ልትጠላ ትችላለህ። አገር ሙሉ ሕዝብ- ግዑዝዋ አገር..እንዴት የጥላቻ ዒላማና የእልቂት ሰላባ ይሆናሉ? ለመሆኑ እነዚህ ዛሬ በወያኔ ገፋፊነት ከፍልፈል ዋሻ ወጥተው የሚጫጩት ትንንሽ ነፍሳት መጫረስና መፋጨት ለሕዝብ አንዳች መፍትሔ ይሰጣል ብለው እንዴት ሊያስቡ ቻሉ? ወይስ አጀንዳቸውንና የወደፊት ጉዞአቸውን ለምን በግልጽ አይነግሩንም? ሌላውም ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ በቀር ሌላ አጀንዳ ስለሌለው ጅቡ- ቲበላው በልቶት ቄደር ለመጠመቅ ዝግጁ ሊሆን ይችላል።
 በሰፊው ሲታይ ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የወያኔን ጡጫና ካራ ያልቀመሰ የለም። ኦሮሞዎች አውቀውታል። ጉራጌው፣ የደቡቡ ኅብረተሰብ፣ አኝዋኩ…ጋምቤላው ተራ በተራ ሰይፍ ተመዞባቸዋል። ችግሩ አንዱ በሚረፈረፍበት ጊዜ ሌላው ሊጮኽለት አለመቻሉ ነው። ከእነዚህ የሕዝብ ክፍሎች መካከል የወጣነው አንዳችም ጩኸት ማሰማት ቀርቶ ጥቂት ጥቂት ተቆርቋሪነት የሚሰማቸውን ጭምር ተቃዋሚዎች መሆናችን ነው። አለዚያ በኢትዮጵያ አብዮት ዘመን የነበርን ሁሉ የወያኔን “ታላቅ ሴራ” እናውቃለን። ሰምተናልም። ከቶውንም እንደማስታወሰው የቀድሞው መሪያችን ጓድ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኅይለማርያም ሦስት ቀን በራቸውን ዘግተው የጻፉትን ዲስኩር እንድንሰማ ተደርጐ ነበር። የዚያን ዕለት ንግግራቸው “ወያኔ በአማራው ላይ ያነጣጠረ፣ እልቂት ማቀዱ..ከቶ ምክንያቱ ምንድነው?” የሚል ነበር። ከዚያ መንግስት የማይሻል የለም በሚል ብቻ የጓድ መንግሥቱን ንግግር አጣጣልነው።
 ከሩዋንዳ የ1994 እልቂት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየትኛውም አገር ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት መከላከያ መዘየዱን ገልጦ እንደነበረ እናስታውሳለን። እንደ እውነቱ ደግሞ በዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ አባላት የነበሩ አምባገነን ሥርዓቶች በሕዝቦቻቸው ላይ ወደር የሌለው ጭካኔ ሲያሳዩና እልቂቶችንም ሲፈጥሩ ድርጅቱ የወሰዳቸውን ርምጃዎች አናውቅም። ከ1975- 1979 በካምቦዲያ ከአንድ ሚሊዮን እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በገዥው (ካይመር ሩዥ) ሲጨፈጨፍ አንዳች ጠያቂ አልነበረበትም። በኋላም አረመኔው ፓልፓት ፍትሕን ፊት ለፊት ሳያይ በእርጅናና በበሽታ ሞቶአል።
 በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ በወለጋ፣ በጋምቤላ..በጉራፈርዳ..በወያኔና ባሰለፋቸው ጭፍሮቹ በጥይት የተቆሉትን ዜጐች ..ከዚያም በፊትና በኋላ በየሰበቡ በየአደባባዩ የወደቁትን ዜጐች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን የሚያስበልጡ ሰዎች አሉ። ብዙዎች እልቂቶች ደግሞ አደባባይ እንዳይወጡ፣ በየአገሩ በሚታወቁ የመገናኛ አውታሮች እንዳይነገሩ ተደርገዋል። ይኸም ባሰለፋቸው ልዕለ ኅያል ግፊት መፈጸሙ ምሥጢርነት የለውም። እስከናካቴውም ግዙፋን ማስረጃዎችን ይዘው የዓለምን ፍርድ ቤት ጥሪ የሚጠብቁ እንደ ሒዩማን ራትስዎች፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ጄኖሳይድ ዎች ወዘተ ያሉ ድርጅቶች ከነመለስና መንግሥታቸው ደጋፊዎች የሚደርስባቸው የጨለማ ጡጫ የሚቻል አይመስልም። ስለዚህ “አማሮችንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በጠላትነትና በአላስገዛም ባይነት ገዥም ተባባሪም ተስማምተዋል። ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን ዲሲ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ ተሳትፌ አውቃለሁ። ለስቴት ዲፓርትማንት ተወካይ መግለጫ የሚሰጥ ሲፈለግ እኔና ወዳጄ አረጋዊ በርሄ በግንባር ቆመን የሰልፉን ዓላማ መግለጥ ጀመርን። ወዲያው የአማራን የጠላትነት አቋም እንደ አንድ ነገር የተጋተው የመሥሪያ ቤቱ ሰውዬ “የአማሮች ሰልፍና የአማሮች አላማ ይገባናል” ይላል። ወደ አረጋዊ በርሄ እያሳየሁ “እሱ ወንድሜ ትግራዊ ከመሆኑም በላይ ቲፒኤልኤፍንም የመሰረተ ነው። የራሱን ድርጅት ፀረ ሕዝብነት በመረዳት ራሱን ያገለለም ነው። እኔ ደግሞ እንዲሁ ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ” አልሁት። “አገር አገር፣ ነፃነትና አንድነት…መብትና..”  የሚል ሁሉ በአማራነት ይመደብ ጀምሮአል። ኢትዮጵያዊነትንም ሰብስበው ለአማራው አሸክመውታል። ስለዚህ ከአንዳንድ ፈረንጆች ጋር ስትነጋገሩ ስለኢትዮጵያ አንድነትና ስለ አገሪቱ ክብር ካነሳችሁ “ማን መሆንህን አወቅሁት። አማራ ነህ” ትባላላችሁ። በእኔ በኩል ይህ አነጋገር የኦሮሞውም፣ የከንባታውም፣ የትግሬውም መሆን አለበት። እነዚህ ወገኖቼ በወያኔ ሰንሰለት እግር ከወርች ካልታሰሩ በቀር ይኽ እምነት የሁላችንም ነው። ከፋም ለማም፣ ጊዜ ፈጀ አልፈጀም ኢትዩጵያ የሁሉም እናት ትሆናለች። እስከዚያው የሚከፈለው ሰማዕትነት ግን በዛ። ከበሮ እየተመታ ነው። አላጋንንም። አንዲት ሰረዝ የአጋንኖ አልጨምርበትም። የጦርነትን አቅጣጫ እሱ ባለቤቱ እያዘወረው ነው እንጂ እልቂቱ ከተጀመረ ውሎ አድሮአል። “ተነስ” የሚልህስ ማነው? ተኝተሃል እንዴ ተነሥ የምትባለው?
  ገብረመድኅን አርአያ ለብዙ ጊዜያት ብቻውን በምድረ በዳ የሚጮኽ ባህታዊ ሆኖ ቆይቶአል። ጓደኞቹን እንኳ ሳያስተርፍ፣ ለጥላቻቸው ዋጋ ሳይሰጥ ይህንን የኢትዮጵያ አንድና ዋነኛ የሕዝብ ክፍል ለመጨረስ የወያኔን እቅድ ገልጦልን ነበር። ምዕራፍና ቁጥር እየጠቀሰ። ከየትም አቅጣጫ ከማንም ግለሰብ ማስተባበያ አልተሰጠበትም። “በዓለም ላይ በአንዳች ሥፍራ አንድን የሕዝብ ክፍል ለመጨረስ የሚቀነባበር ሴራ ሲያጋጥማችሁ አመልክቱ” የሚለው ከሩዋንዳው እልቂት በኋላ የወጣ መግለጫ ነበር።
(ተስፋዬ ገብረአብ)
ጅብ ቲበላህ... በልተኸው ተቀደስ - ከጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ (የቀድሞው ጦቢያ መጽሄት አምደኛ)   1

በኢትዮጵያ ሁኔታ በሁሉም ሕዝብ ላይ ለሚቀነባበረው ሴራ ፊሽካ ነፊው ወያኔ ነው። የእልቂት አሰልጣኙ ወያኔ ነው። እንደ ሩዋንዳ እልቂት ዝግጅት 1400 ካድሬዎችንና የግድያ ቡድኖችን አሰልጣኝና ቦታ ቦታ አስያዥ ወያኔ ነው። ምናልባት ተኳሾቹ ኦሮምኛ የሚናገሩ ወይም መናገር የሚችሉና በኦሮሞ ስም ኬላውን ለማለፍ የሚችሉ ይሆናሉ። ትርኢቱ የወያኔ፣ ደራሲው ወያኔ፣ መሪው ወያኔ! ዝግጅቱ ብዙ ዘመን ጠይቆአል። ወያኔዎች ለድርሰቱ አልተቸገሩም። ተስፋዬ ገብረአብ የተባለ ወጣት ፕሮፖጋንዲስት ትከሻ ላይ ኅላፊነቱን ሁሉ መጣል ውጤት ያስገኛል ብለው ጣጣቸውን ጨርሰውታል። ተስፋዬ በቃላት መጫወት ይሆንለታል። ቃላትን ከድንጋይ ጋር ያወያያቸዋል። በአንድ ክፍል ውስጥ “ቃላት” ሰብስቦ ያለ ተናጋሪ ያንጫጫል። አዎን ተስፋዬ- ማናቸውም ባለቋንቋዎቹ በማይሆንላቸውና በማይደፍሩበት ሁኔታ ደስታውንና መከፋቱን፣ ዳር ድንበር የሌለውን የወሲብ ረሃቡን የሚናገርለትና የሚናገርበት አማርኛ አለው። ይኸ ጥበብ (ታለንት) ገበያ መውጣት ነበረበት። ወጣ- የቡርቃ ዝምታ ተወለደ። ይኸ የተስፋዬ መንፈስ ዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ይገኛል። ሐውልት አሠርቶአል። ጦር አማዝዞአል።

 ሁላችንም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመሮጥ ሞክረናል። ተስፋዬ ብቻ ያወቀውና የሚያውቀው ታሪክ ሌላ ነው። ይኸውም በቡርቃ ዝምታ መጽሐፉ ውስጥ አጤ ምኒልክ የጨረሱአቸው የኦሮሞ ጀግኖችና ጡታቸውን የተቆረጡ ሺህ በሺህ ሰዎች ናቸው። ተስፋዬ ይህን መሳይ እንቁላል ጥሎ ወደ ስደት እንደ ሄደ ይነግረናል። ባይነግረንም እናውቃለን። ከዚያ በኋላ ደግሞ እንደገና በቃላት አፍዝ አደንግዝ (ሒፕኖታይዝ ሲያደርገን) የጋዜጠኛው ማስታወሻን፣ የደራሲው ማስታወሻንና በመጨረሻም የስደተኛው ማስታወሻን አዘጋጀልን። “ የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ! ጠላቶችህ በዛሬ ቀንና በዚሁ ሥፍራ በእጅህ ገብተዋልና ዝምታው ምንድነው? አታውቅም እንጂ አማራ አያት ቅድመ አያትህን ጨርሳለች። አንተንም ቢሆን ገድላሃለች- አላወቅህም እንጂ!” ካለ በኋላ ለእኛ ለውጭዎቹ ደግሞ የትኛው የወያኔ ሹም ከየትኛይቱ ኮረዳ…ካልሆነም መለኮን ጋር እንደ ተዳራ፣ ምን እንደ ተጠጣ..ማን ኮንትራባንድ እንደሚነግድ ..ማን ብዙ እንደሚሰክር..ነገረን። ይኸ ቅማል ነበር እንዴ የበላን? የተስፋዬ በማርታ አሻጋሪ ዘፈን እንደ ወንድ አህያ አውሬአዊ የወሲብ አመሉን በሕዝብ እይታ ፊት መፈጸም ም ይፈይድልናል? በቋንቋው ኅይል ያንከራተታቸው ሰዎች አሉ። መሞታቸውን ከእሱ የሰሙ። ታሪካቸውንና ውርደታቸውን ከእሱ ያነበቡ። እስከ ዓለም ምሕረቱ!
 ተስፋዬ በስደቱ ዓለም በቆየባቸው ዓመታት ልብ ወለድ መጽሐፉ- የቡርቃ ዝምታ- በአገር ቤትም ሆነ በውጭው (ዳያስፖራ) የፈጠረችውን ቱማታ መለካቱ አልቀረም። “ኦሮሞ ነን” የሚሉ ጉርባዎችን አስከትሎ “ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ወዳጅ” ተብሎ በሚሞገስበትና በሚሸለምበት ሥፍራ ሁሉ ዲስኩር አድራጊ ሆነ። ጥፋትን አብሮ በማቀድና አብሮም በአንድ ግብ ስር ተሰልፎ ወደ አፈጻጸሙ የመንደርደር ተግባር ሁሉ እስካከናወነ ድረስ በእኔ በኩል ተስፋዬ ምን ጊዜም ከወያኔ ጋር የሚያስተሳስረው እትብቱ አልተቆረጠም። ይልቁንም ልብ ወለድ ድርሰቱ ሐውልት ሊያሠራ መቻሉና የገንዘብና የማቴሪያል ጥቅም ማግበስበስ ላይ መገኘቱ ቀላል ግምት አያሰጠውም። እነሆ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሐልም የሚቆም የጥላቻ ግድግዳ፣ የበቀል ግንብና ለትውልዶች የሚተላለፍ መርዝ አበረከተ። መርዝ መርዝ! ነብዩ ኢያሱ በአፍሪካ ቀንድ መጽሔት ላይ ያወጣት አንዲት ግጥም ትዝ አለችኝ። “ወይ ውረድ ወይ ፍረድ!” ነበር የምትለው ( በነገራችን ላይ ተስፋዬ ገብረአብ በግል እኔን ያሞጋገሰኝ ሰው ነው። እንዳልናገር በቅድሚያ የተከፈለ ጉቦ ከሆነ የከመረብኝን ቋንቋ ሁሉ ይውሰድልኝ) በታሪክ ካላደረቅኋችሁ ጥቂት ጊዜና ትዕግስት ስጡኝ። ወጌን አላበቃሁም። አንድ ቃል ልጨምር። ከ “የቡርቃ ዝምታ” በኋላ ነው የስደት ማስታወሻ ቢያንስ በነፃ የተለቀቀው። አነበብሁት። ኢትዮጵያንና አማራ የተባለውን ሕዝብ የሚገልጥበት፣ ተጨቁነዋል የሚላቸውን የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አሥር ቶን በሚሆን ውሸት የሚያንቆለጳጵስበትን ሁሉ አንብቤለታለሁ። መላልሼ ለራሴ ያቀረብሁት ጥያቄ “ለምን ይሆን ተስፋዬ ይህን ሕዝብ ይህን ያህል ለመጥላትና በመቃብሩ ላይም ድንጋይ ለመመለስ የፈለገው? ኢትዮጵያስ በአንድ ሰው ተመስላ የበደለችው ምን ይሆን? ሕዝቡ እንዲጫረስ መንፈሱን ያነሳሳው ምንድነው?”
 እንደሚወራው ተስፋዬ በብዙሃኑ ዲያስፖራ የማርያም ጠላት ቢባልም ለራሳቸው አዲስ ስያሜ የሰጡትና አንዲት ቅጠል የኢትዮጵያን ታሪክ አንብበው የማያውቁ ግለሰቦች ደግሞ እጅብ እጅብ እያደረጉት ነው። በሦስተኛው ክፍል ጥቂት አሹዋፊዎች አሉበት። ተስፋዬ የሚነግረን ሁሉ ትክክል ነው። ይህን ሁሉ መከራ እንዴት ቻልነው? ሳናውቀውና ሳይሰማን እንዴት እስካሁንዋ ቀን ደረስን? ይሉታል። ለካንስ ይህን ያህል ተበድለን ነበር? ከተገረፈው ገላችን፣ ከቆሰለው አጥንታችን በላይ የተስፋዬ ቃላት ይናገራሉ። ለካ አልቀን ነበር? የተስፋዬ የእልቂት አዋጅ የሆነው የቡርቃ ዝምታ በሌላውም ምሽግ የምትታወቅ ከሆነች መልሱ “ጅብ ቲበላህ..በልተኸው ተቀደስ” መሆን አለበት። ጋንዲንና ማርቲን ሉተርኪንግን ተዋቸው።  

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ |

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop