አውራምባ ታይምስ፡ (አዲስ አበባ) ዛሬ ጧት የተሰበሰበው ፓርላማ ግንቦት 7 የዴሞክራሲ የፍትህና የነጻነት ንቅናቄን ጨምሮ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አልቃይዳና አልሸባብ አሸባሪ ቡድኖች ናቸው ሲል የውሳኔ ሀሳብ አስተላለፈ፡፡
ባለፈው ዓመት የጸደቀው የጸረ ሽብር ህግ አንድ ግለሰብ ወይም ተቋም በሽብርተኝነት እንዲከሰስ በቅድሚያ ፓርላማው ‹‹አሸባሪ ነው›› ብሎ የውሳኔ ሀሳብ ማስተላለፍ አለበት ሲል የደነገገ ሲሆን በዚህ መሰረት ፓርላማው በዛሬው ዕለት ከላይ የተጠቀሱ ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉ በሽብርተኝነት ፈርጇል፡፡ በዚህ መሰረት ስለ እነዚህ ድርጅቶች ምንም አይነት የዜና ሽፋን የሚሰጥ የሚዲያ ተቋም ‹‹ሽብርተኝነትን ማበረታታት›› በሚል የአዋጁ ንዑስ አንቀጽ ስር ከ20 ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
ኢህአዴግ 99.6 በመቶ በተቆጣጠረው ፓርላማ ውስጥ ብቸኛ ተቃዋሚ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የውሳኔ ሀሳቡን የተቃወሙ ሲሆን ‹‹ቡድኖቹ ወደ እንደዚህ አይነት መንገድ የገቡት ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ሁሉንም በብቸኝነት ልቆጣጠር በማለቱ አማራጭ አጥተውና ተገደው ነው›› ሲሉ ለአውራምባ ታይምስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡ ለብሄራዊ መግባባት በር የዘጋ ነው ያሉት አቶ ግርማ ‹‹የ2002ቱ ምርጫ ውጤት በራሱ ዜጎች በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዲቆርጡ ምክንያት ሆኗል›› በማለት መንግስት ከወረቀት ባለፈ ለፓርቲዎች አመቺ ሁኔታ መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡