April 30, 2011
14 mins read

ይድረስ ለእንግሊዝ ሠርገኞች

(by Daniel Kibret) አየ ሠርግ አየንላችሁ፡፡ እንዴው ምን ነክቷችሁ ነው እቴ፡፡ እናንተ አሁን ንጉሣውያን ቤተሰቦች ትመስላላችሁ፡፡ አካሄዳችሁ፣ አለባበሳችሁ፣ ንግግራችሁ፣ መኪናችሁ፣ ሥነ ሥርዓታችሁ ሁሉ ዘመናዊነት የጎደለው፣ ጥንታ ጥንት ብቻ፡፡ እንኳንም እኛ ሀገር አልሆናችሁ፡፡ እንዲህ ያለውን የጥንት ወግ ስታደርጉ ብትታዩ ምን ምን የመሳሰሉ ስሞች ዳቦ ሳንቆርስ እናስታቅፋችሁ ነበር፡፡

ነፍጠኛ፣ ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ፣ ፊውዳል፣ ርዝራዥ፣ አድኃሪ፣ ጎታች፣ አክራሪ፣ ወገኛ፣ ያልገባው፣ ኧረ ስንቱ፡፡ እንግሊዝ ሆናችሁና ተረፋችሁ፡፡ አሁን እንደዚህ ጥንታ ጥንት ነገር ሰብስባችሁ እኛ ሀገር ሠርግ ብትሠርጉ እንኳን በቴሌቭዥን ልትታዩ ማንስ ይመጣላችኋል፡፡

ለመሆኑ የጥሪ ካርዳችሁ ከየት ነው የመጣው? እዚያው እንግሊዝ ነው የተሠራው እንዳትሉ ብቻ፡፡ ይኼው ድፍን አበሻ ከአሜሪካ አይደል እንዴ የሠርግ ካርድ የሚያስመጣው፡፡ የኛ መንግሥትኮ የወረቀትን ግብር ለሠርግ ካርድ ቢያደርገው ኖሮ እንኳን የሚያማርረው ትዝ የሚለው አይገኝም ነበር፡፡ የሚያማክር አጥታችሁ ነው እንጂ እንዴት ሀገር ውስጥ በታተመ የሠርግ ካርድ ትጋባላችሁ? ሠርጋችሁስ ላይ ምን ተብሎ ይወራል? መቼም ሠርግ ለወሬ ነው እንጂ ለዕድገት ወይንም ለጽድቅ ተብሎ አይደለም፡፡

አንቺስ ሙሽሪት ለመሆኑ ምን ስትይ ነው እንደዚያ በአያቶችሽ ጊዜ የተለበሰ የሚመስል የጥንት ቬሎ ዓይነት የለበስሺው፡፡ ነውርም አይደል እንዴ? ስንት ዓይነት ዘመናዊ የሆነ ብትፈልጊ ደረት፣ ብትፈልጊ ጡት፣ ብትፈልጊ ወገብ፣ ብትፈልጊም ሌላ ነገር የሚያሳይ ቬሎ ሞልቶ፣ በሀገርሺም ከጠፋ ከውጭ ሀገር ማስመጣት እና ሀገር ጉድ ማስባል ሲቻል ምነው ምነው ልጄ፡፡

አይ እንግሊዝ መሆን፡፡ ለዚህ ለዚህ ጊዜ ነበር አበሻነት የሚጠቅመው፡፡ አታይም እንዴ እኛ ሀገር የባህል ልብስ ለብሰው የሚያገቡትን እንዴት እንደምናንጓጠጣቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንኳን ባህላዊ የሆነ ቬሎ እንሠራለን ሲሉ አዳሜ የሠርጉን እንጀራ ሲያነሣ ስማቸውንም በቢላዋ እያነሣ ይውላል፡፡ ሠርጉ ላይማ «አንቺ ቬሎውን ከየት ሀገር ነው ያመጣችው? ማነው የላከላት? እኅቷ ውጭ ናትኮ? እርሱም ከውጭ ነው የመጣው ይዞት መጥቶ ነው አሉ፡፡ ማንም ያልለበሰው አዲስ እንደ ወረደ ነው ይባላል» እየተባለ ካልተወራ ምኑን ሠርግ ሆነው፡፡

በተለይ ሙሽሪት የምትገርሚ ነሽ የኔን የሠርግ ልብስ የምትሠራው እንግሊዛዊት መሆን አለባት ብለሽ ነበር አሉ፡፡ እናንተ ሀገር «ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ እንስጥ» የሚለው መፈክር ሠርቷል ማለት ነው፡፡ የሚገርማችሁ ግን ይህንን መፈክር በየኤግዚቢሽን ማዕከሉ የሚያሰሙት የሀገራችን ነጋዴዎች ይህንን መፈክር ሲያሰሙ እንኳን አንድም የሀገር ውስጥ ምርት አይለብሱም፡፡ እኛ ሀገር ይኼ መፈክር የሚሠራው ለድኻ ነው፡፡ እናንተ ጋ ለሀብታም መሥራቱ ገረመኝ፡፡ ሳስበው ሳስበው ግን አሜሪካ የሚኖር ዘመድ ያላችሁ አይመስለኝም፡፡ ምነው ዲቢ ሞልታችሁ ጥቂት ጊዜ እዚያ ሰንብታችሁ ብትመጡ ኖሮ፡፡ ብታጡ ብታጡ እንዴት ዱባይ ዘመድ የላችሁም፡፡

እኔ ያፈርኩባችሁ መኪናችሁን አይቼ ነው፡፡ ወይ የንጉሥ ልጅ መሆን፡፡ እኛ ሀገር እንኳን የንጉሥ ልጅ የድኻውስ ልጅ ቢሆን አፍንጫውን ነክሶ ተበድሮ በሊሞዚን ይሄዳል እንጂ ጋሪ የመሰለ መኪና ለዕድሉም አያሳየው፡፡ ርግጥ ዛሬ በሠላሳ ሺ ብር ሊሞዚን የተጓዘውን ሙሽራ በቀጣዩ ሳምንት ታክሲ ሲጋፋ ልታገኙት ትችሉ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ቢሆንም ለታሪኩስ ቢሆን፡፡ ኧረ ዋናው ለቪዲዮው፡፡ «ሠርግ አላፊ ነው፣ ቪዲዮ ቀሪ ነው» የሚለው ተረት እናንተ ሀገር የለም እንዴ? በርግጥ ያ ሁሉ ወጭ የወጣበትን ቪዲዮ ሙሽሮቹ ሳያዩት አምስት ዓመት ሊሆነው ይችላል፡፡ ቢሆንም፡፡

አስታወሳችሁኝ፡፡ ለመሆኑ ቪዲዮ ቀራጮቹ የት ላይ ነበሩ፡፡ ወይስ ጭራሽ አልነበራችሁም፡፡ እናንተ እንግሊዞች ስትባሉ የማታመጡት ነገር የላችሁምኮ፡፡ ከፊት ከፊታችሁ እየተደረደሩ «ያዛት፣ ተያያዙ፣ ቀስ በሉ፣ መሥመሩን አስተካክሉ» ካላሏችሁማ አልተቀረፃችሁም ማለትኮ ነው፡፡ ተሸውዳችኋል፡፡

የወንድ ሚዜዎችን ኮት ሴቶች ሳይይዙ፣ ወንዶቹ ሴቶች ላይ፣ ሴቶቹ ወንዶች ላይ ሳይደገፉ፣ ሁለት ሁለት እየሆኑ ሳይለቀቁ፣ እንዴት ቪዲዮ ይቀረፃል? ለመሆኑ የናንተን ሠርግ የመራው ማነው? እኛ ሀገር ሠርግ ምርጥ የሚሆነው ቪዲዮ ቀራጭ ሲመራው ነው፡፡ ቁም፣ ተቀመጥ፣ ያዝ፣ ልቀቅ፣ ቀና፣ ደፋ፣ ሳቅ፣ ፈገግ፣ ና፣ ሂድ፣ ውረድ፣ውጣ፣ እዚህ ዛፍ፣ እዚያ ዛፍ፣ እያለ እንደ ኮንዳክተር ካልመራውማ አልተጋባችሁም ማለት ነው፡፡

ኧረ ደግሞ የገረመኝ በሀገራችሁ መንገድ ጠፍቶ ነው አያቶቻችሁ በሄዱበት መንገድ በሠረገላ የሄዳችሁት፡፡ ምነው እኛ ሀገር ብትመጡ ኖሮ፤ በቀለበት መንገድ፣ በወሎ ሠፈር፣ በጎተራ መሣለጫ መንገድ፣ በመገናኛ አዲሱ መንገድ፣ በስድስት ኪሎ፣ በአራት ኪሎ፣ በላፍቶ፣ በጉለሌ በስንቱ እናዞራችሁ ነበር፡፡ ያውም ጲጵ ጲጵ ጲጵ እያስባልን፡፡ ደግሞ የመንገድ ላይ ደሴት ስናገኝ ቪዲዮ ቀራጩ ያሰልፋችሁና አዙሪት እንደ ለከፈው ሰው ደሴቱን ስትዞሩት ስትዞሩት መዋል ነው፡፡ ለቪዲዮ አሪፍ ነዋ፡፡ በርግጥ ያንን መንገድ ከልጅነታችሁ ጀምሮ የሄዳችሁበት ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ማን አድርጎ ማን ይቀራል፡፡

አንድ ያላማረባችሁን ነገር ልንገራችሁ፡፡ እንዴት የንጉሥ ልጅ ሆናችሁ ቤተ ስኪያን ገብታችሁ ተጋባችሁ? ለክብራችሁ ጥሩ አይደለም፡፡ አይ እኛ ሀገር አለመሆናችሁ ጎዳችሁ? እኛ ሀገር የበላይ መሪዎቻችን በተስኪያን ገብተው አይተን አናውቅም፡፡ ነውር መስሎን ነበርኮ፡፡ እናንተ ግን ስትገቡ ዝም ተባላችሁ? የናንተ ሀገርት ፓርቲ አይከለክልም? አንዱ በተስኪያን ገብታችሁ ከሌላው ስትቀሩ «መብታችን ተነካ፣ የሃይማኖት አድልዎ ተደረገብን፣ እነ እገሌ በተ ስኪያን ተገብቶ እኛጋ ለምን ይቀራል?» የሚል የለም እንዴ? አይ እንግሊዝ መሆን፡፡ ኢትዮጵያ ብትሆኚ አድልዎ ፈጽመሻል ተብለሽ ትገመገሚያት ነበር፡፡

አንድ ሌላ የገረመኝ ነገር አለ፡፡ እናንተ ሀገር ያሉት የቤተ ክርስቲያን መሪ ምነው በደንብ ሳናያቸው ቀረን፡፡ እንዲህ የንጉሥ ልጅ አግብቶ ቀርቶ አንድ የታወቀ ነጋዴስ ሲሞት በሚገባ መታየት አልነበ ረባቸውም፡፡ ትዝብት ነው ትርፉ፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ነበርኮ የንጉሥ ወዳጅ መሆናቸውን ጎላ ጎላ ብለው ማሳየት የነበረባቸው፡፡ ተሳስተዋል፡፡ መቼም መካሪ አሳስቷቸው መሆን አለበት እንጂ እርሳቸው ደፍረው አያደርጉትም፡፡ ለወደፊቱ ባይደገም ጥሩ ነው፡፡

ምን ነው ግን የካንትበሪው ሊቀ ጳጳስ ባለ ሥልጣን አይመስሉምሳ፡፡ ከግራ ከቀኝ የሚደግፋቸው፣ ጎንበስ ቀና የሚያደርግላቸው፣ ሕዝቡን የሚገፋላቸው አጃቢ የላቸውም፡፡ በሰው ሠርግስ ቢሆን መወድስ ምናምን አይቀርብላቸውም እንዴ እንዴት በሼክስፒር ሀገር ቅኔ ሳይወርድ ቀረ? አይ እኛ ሀገር ቢሆን እንኳን እንዲህ በቴሌቭዥን የሚተላለፍ ሠርግ ቀርቶ በፎቶ ግራፍ የሚተላለፍም ከተገኘ ማን ይለቅቃል፡፡ ከብለል ከብለል የሚሉ አጃቢዎች መድረኩን ይሞሉላችሁ ነበር፡፡ ወይ ነዶ፤ ወይ እንግሊዝ መሆን፡፡

ግን እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ አደባባይ የወጣው በገዛ ፍቃዱ ነው ወይስ በቀበሌ በኩል ተነግሮት፡፡ መቼም መመሪያ ከዴቪድ ካሜሮን ተላልፎ መሆን አለበት፡፡ እርግጥ ብዛቱ ደስ ቢልም የአደረጃጀት ችግር ግን አለበት፡፡ እንዴት አንድ የረባ መፈክር አይያዝም፡፡ ሲሆን ሲሆን ከበላይ አካል አምስት ስድስት መፈክር ተጽፎ በመመርያ መልክ መተላለፍ ነበረበት፤ ካልሆነም በቀበሌ በኩል መዘጋጀት ይገባ ነበር፡፡ ደግም አልሠራችሁ፡፡

አንድ ነገር ልምከራችሁ፡፡ ይህንን ቢቢሲ የሚባል ቴሌቭዥን እናንተ ሥልጣን ስትይዙ መቅጣት አለባችሁ፡፡ «በሠርጉ ሕዝቡ መደሰቱን ገለጠ፤ ሠርጉ ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠየቀ፤ ይህ ሠርግ ለሌሎች አገሮች አርአያነት እንዳለው ተጠቆመ፣» እያለ እንዴት ዜና አልሠራም፡፡ እንዲህ ያለውን ከቴሌቭዥን አትቁጠሩት፡፡

ይህንን ሁሉ የለፈለፍኩት ታዝቤ ታዝቤ ሳልነግራችሁ ብቀር አምላካችሁ ይታዘበኛል ብዬ ነው እንጂ ባህላችን ስለሆነ አይደለም፡፡ እንደ ባህላችንማ ሠርግ ላይ ተገኝቶ እየበሉ ማማት እንጂ ያሙትን መናገር ነውር ነበር፡፡ በሉ ይኼ በናንተ ያየነው በለሌሎች እንዳይደገም ቢቢሲ ባለሞያዎችን ጋብዞ ውይይት ያካኺድበት፡፡

በሉ ጋብቻችሁን የአብርሃም የሣራ ያድርግላችሁ፤

ያልተጋበዘው ታዛቢያችሁ ከአዲስ አበባ

Go toTop