ግንቦት 2017
አንዳርጋቸው ጽጌ
የዚህን ጽሁፍ ርእስ የሚያዩ የአብይ አህመድ አገዛዝ ባለስልጣናትና የዲጂታል ሰራዊት አባላት ምራቃቸውን ሲውጡ ይታየኛል። “አላልናችሁም ይሄው አንዳርጋቸውም ጉዱን አወጣው። የጤና ባለሙያተኞች ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው አለ።” ለማለት ሲዘጋጁ ይታየኛል። አንዳንዶቹም ርእሱን አንጠልጥለው ወደ ማህበራዊ ሚድያ ሲሮጡ ይታየኛል። በቅድሚያ እነዚህን ሰዎች ተረጋጉ፣ የሚከተለውን በጥሞና አንብቡ ማለት እሻለሁ።
የጤና ሙያተኞች “እየተራብን ነው። ስራ መስራት አልቻልንም። ረሃብ ማስታገሻ የሚሆን የደሞዝ ማስተካከያ ይደረግልን” የሚል ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት፣ ዛሬ ሳይሆን፣ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት ነው። በዛን ወቅት እነዚህን የጤና ባላሙያተኞች “የደሞዝ ጫማሪ ጥያቄ አቅርቡ” እያለ ሲጎተጉታቸው የነበረ ተቃዋሚ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። በዛን ወቅት፣ ሌላው ቀርቶ የአብይ አህመድ አገዛዝና የህወሃት ጠብ ገና አልተጠነሰሰም ነበር።
ሃኪሞቹ ጥያቄ ያቀረቡ እለት፣ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሰዎችና (እኔንም ጨመሮ) የፖለቲካ ድርጅቶች “አብይን አሻጋሪ፣ ሙሴ” የምንልበት፤ የኢትዮጵያ እናቶችና አባቶች አብይ ክፉ እንዳይነካው ምስሉን በቴሌቪዥን ሲያዩ ምራቃቸውን እንትፍትፍ የሚሉበትና የምጸልዩበት ጊዜ ነበር። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም “ኢትዮጵያ አምላኳ ጥሎ አይጥላትም፣ የተጠማችውን የሰላም፣ የፍቅርና ይቅርታ ጥም የሚያረካ ልጅ ፈጣሪ ላከላት” የሚልበት፤ አብይም “በይቅርታ እንሻገር በፍቅር እንደመር” የሚል ድግምቱን የሚደግምበት ወቅት ነበር።
አብይ አህመድ ሸሚዙን ጠቅልሎ በአደባባይ፣ “ሙስናን እዋጋለሁ፣ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ የሚደረገውን ስብሰባና ለስብሰባ ተብሎ የሚወጣን የውሎ አበል፣ የአዳራሽና የመጓጓዣ ወጪ አስቀራለሁ” የሚልበት ወቅት ነበር። “የመንግስት ባለስልጣናት ኑሯቸው እንደ ኤርትራ መሪዎች የህዝቡን ኑሮ መምሰል አለበት፣ እዩት የሚኖሩበትን ቤት፣ እዩት እንዴት ቡና እንደሚጠጡ፣ እዩኝ ይህ ህይወታቸው ስላስደመመኝ በኢሳያስ መኖሪያ ቤት ቡና እና የቡና ቁርስ አስተናጋጅ ሆኘ ሳገለግል” እያለ በቴሌቪዥን ድርጊቱን እና ቃሉን የሚያቀርበበት ወቅት ነበር።
አብይ በፓርላማ ስብሰባ ላይ አፉን ሞልቶ “አሸባሪው የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ ኢትዮጵያ አሸባሪ ድርጅትና ዜጎች ኖሯት አያውቅም፣ ያለማስረጃ አናስርም፣ መግረፍ ሰቆቃ መፈጸም ከዚህ በኋላ አይታሰብም፣ መግረፊያ ቤቶቹ ወደሙዚየም ይቀየራሉ፣ መግደል መሸነፍ ነው” የሚልበት ወቅት ነበር።
በዛን ወቅት ለአብይ “ደሞዛችን በቂ አይደለም እየተራብን ነው” የሚል ጥያቄ ያቀረቡለትን የጤና ሞያተኞች ከጥያቂያችሁ ጀርባ የፖለቲካ ሰዎችና እጆች አሉበት አላላቸውም። ሌላ ሌላ ነገር ቢላቸውም። ምክንያቱም በዛን ወቅት በአብይ አህመድ አገዛዝ ላይ አመጽ እንዲነሳሳ የሚፈልግ ማንም ሃይል አልነበረምና። የሃኪሞቹ ጥያቄ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ እንጂ ሌላ የፖለቲካ አላማ አልነበረውም።
ከስድስት አመታት በኋላ እነዚህ የጤና ባለሙያተኞች ተመልሰው የሚያነሱት የዳቦ ጥያቄ ከዳቦ አልፎ ፋጸሞ የፖለቲካ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳየው መረጃ እነሆ።
በስድስት አመት ውስጥ የአንድ ዳቦ ዋጋ ምን ያህል ጨመረ? በዚሁ ዘመን የጤና ሙያተኞች ደሞዝ ምን ያህል አደገ?” የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳትና ለጥያቄዎቹም በሚሰጠው ምላሽ ውስጥ መረጃው ያለው።
የዛሬ ስድስት አመት በአዲስ አበባ ከተማ አንድ 100 ግራም ዳቦ በሁለት ብር ይሸጥ ነበር። በዛን ወቅት ራበን የደሞዝ ማሻሻያ ይደረገልን ብለው የጠየቁ የጤና ባለሙያተኞች በስድስት አመት ውስጥ በደሞዛቸው ላይ የአንድ ሳንቲም ጭማሪ አልተደረገላቸውም። ባለፉት 6 አመታታ ውስጥ የዳቦ ዋጋ ግን በሰባት እጥፍ ጨምሮ፣ አሰራ አራት ብር ሆኗል። ከዛም ሳይበልጥ አይቀርም። ጤፉም፣ ሹሮውም፣ የቤት ኪራዩም፣ ወሃውም መብራቱም፣ የመጓጓዣ ክፍያውም ሌላም ሌላውም ከዳቦው ባልተናነሰ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህ ሃቅ የሚጠቁመው የዛሬ ስድስት አመት ያለመንም የፖለቲካ ድርጅት ወይም ግለሰብ ጎትጓችነት የደሞዝ ጥያቄ ያቀረቡ ሰራተኞች ዛሬ ከቀደመው ዘመን የባሰ፣ ሰባት እጥፍ ረሃብ ውስጥ መገኘታቸው ነው። በመሆኑም እነዚህ ሰራተኞች ዛሬ የደሞዝ ጭማሪ ለመጠየቅ፣ የነጻነትና እኩልነትን፣ የእናትን፣ የኢህአፓን፣ ወይም የኦፌኮን ወይም ሌሎችም መተንፍሰ የተሳናቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም የፋኖን ወይም የኦላን፣ የኦብነግን፣ የህወሃትን ወይም የኢሳያሳን፣ የአልቡርሃን፣ የሃሰን ሼክ መሃመድን፣ የእስማኤል ኡመር ጉሌህን ወይም የአልሲሲን ጉትጎታ ያስፈልጋቸዋል ወይ ብሎ መጠይቅ ተገቢ ነው። መልሱ አያስፈልጋቸውም። የኑሮ ስቃያቸው በራሱ በቂ ነውና።
ይህ እውነታ አገዛዙ የሃኪሞቹን ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አሳፋሪ መሆኑን ያሳየናል። የጤና ሙያተኞች የዛሬ ስድስት አመት “ተርበናል ብለው” ጥያቄ ካቀረቡ አሁን ባላው እጀግ አስከፊ የኑሮ ውድነት ለአብይ አህመድ አገዛዝ የሚያስተላልፉለት መልእክት “ተርበናል ስንልህ አልሰማህም። እና ልንበላህ ነው” የሚል ቢሆን እንኳን አላሉም እንጂ የሚስገርም አይሆንም ነበር።
ሃኪሞቹ ግን ህግን፣ ሰላማዊነትንና ጨዋነትን መሰረታቸው አድርገው አገዛዙን “በቃን ከዚህ በላይ መሄድ አልቻልንም። የዛሬ ስድስት አመት ለጠየቅንህ ጥያቄ መልስ ስጠን ነው” ያሉት።
“መንግስት ይቀየር፣ አብይ ከስልጣን ይውረድ” አላሉም።
“ጦርነት እያካሄድ የምታቆስለውን ህዝብና ደሃ ወታደር በባዶ ሆዳችን ማከም አቅቶናልና የስራ ጫና እንዲቀንስልን ጦርነት አቁም” አላሉም።
“በየእስር ቤቱ ሰቆቃ እየፈጸምክባቸው ወደ እኛ እየላክ ስቃያቸውን እያየን እንድንሰቃይ፣ ያለችንንም የተጨናነቀች የስራ ጊዜ ለሌሎች በሸተኞች እንዳናወል አታድረገን” አላሉም።
“ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችን በድሮንና በከባድ መሳሪያ አትደብድብ፣ የስራ ባላደረቦቻችንንም አትግደል” አላሉም።
“የህክምና መሳሪያና የመድሃኒት እጥረት ያስከተለውን፣ ስራችንን በተገቢ ደረጃ እንዳንሰራ ያደርገውን፣ ህዝባችንን ለስቃይ እየዳረገ ያለውን ችግር ለማቃለል፣ በ300 ሚሊዮን ብር የልጆቻቸውን ሰርግ የሚደግሱ፣ ለአንድ ሰርግ 25 ሰንጋ በሬ የሚያርዱትን የባለስልጣናቶችህን የህዝብ ሃብት ዘረፋ ወንጀል አስቁምልን” አላሉም።
ሌሎችም ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ባይጠፋቸውም፣ ሌላ ያነሱበት ጉዳይ የለም። ጥያቄያቸው የፖለቲካ ስላልሆነ። “ራበን ዳቦ መግዣው ላይ ትንሽ ፍራንካ ጣል አድርግልን” የሚል ልመና ነው የያዙት ።
የጤና ባለሙያተኞች እንደማኛውም ዜጋ የፖለቲካ ጥያቄ የማንሳት መብት ያላቸው ቢሆንም ይህን መብት እርግፍ አድርገው ትተው፣”ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለም” ብለው በአደባባይ አውጀው ነው ጥያቄያቸው ያቀረቡት። በዚህ ደረጃ የዜግነት መብታቸውን እንዳይጠቀሙ አድርጎ “ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለም” እንዲሉ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የጨመራቸው አረመኔ አገዛዝ ማፈር ሲገባው ጭራሽኑ አይን አውጥቶ “ጥያቄያችሁ ፖለቲካዊ ነው፣ ከጀርባው የፖለቲካ ድርጅቶችና ሰዎች አሉበት” ሲል ሃፍረት አይሰማውም። እንደኢዜማ አይነቶች የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ደጋፊዎቹና የሚድያ ሰራዊቶቹም፣ አይን ቀቅለው የበሉ ሃፍረተ ቢሶች ስለሆኑ፣ ይህን የአገዛዙን ክስ እንደበቀቀን ሲያስተጋቡት አያፍሩም።
የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃኪሞቹ ጥያቄ
በሌላ በኩል ግን የጤና ባለሙያተኞች ጥያቄ፣ እነሱ የፖለቲካ እንዳልሆነ የተናገሩት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ “የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ሊያዩት ይገባል?” የሚል ጥያቄ መነሳት ይኖርበታል።
ሲጀመር የጤና ሙያተኞች ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለምና ማንም የፖለቲካ ድርጅት ወይም ግለሰብ አስተያየት መስጠት አይችልም የማለት መብት እንደሌላቸው መታወቅ አለበት ። እነሱም አላሉም። የፖለቲካ አይደለም የሚለውን አቋማቸውን ግን በግልጽ አስቀምጠዋል። ሃኪሞቹ የሚኖሩበትን ሃገራዊ ሁኔታና የአገዛዙን ባህሪ የሚረዳ ማንም የፖለቲካና የፖለቲካ ያለሆነ ሰው አይፈርድባቸውም።
ሆኖም ግን እራሱን የፖለቲካ ሰው ወይም ድርጅት አድርጎ የሚያቀርብ አካል ጤናን የመሰለ ወሳኝ የማህበራዊ አገልግሎት ችግር ላይ ሲወድቅ፣ “ገና ለገና በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ብሰጥ መንግስት የጤና ሙያተኞችን ጥያቄ የፖለቲካ ያደርግባቸዋል” በሚል ሰበብ ወይም ፍራቻ፣ አስተያየት ከመስጠት፣ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ ሃሳቦችን ከማቅረብ ቢቆጠብ አሳፋሪ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ተፈጥሮዋቸው አይፈቅድላቸውምና። ይፈቅድናል የሚሉ ካሉ መዘዙን እንመልከት።
ነገ ጠዋት መምህራን ተነስተው “ኑሮ ተወደደ፤ ችጋር ጠበሰን” ቢሉ፣
ወታደሮች ተነስተው መሞትና መግደል በቃን ቢሉ፣
የፋብሪካ ሰራተኞች ተነስተው “አቅማችን በረሃብ አለቀ መስራት አልቻልንም” ቢሉ፣
ነጋዴዎች “ግብሩ በዛብን ቀንሱልን” ቢሉ፣ ህዝብ ተንሰቶ “መዘረፍና በመልካም አስተዳደር እጦት ጎበጥን” ቢል፤
ይህን የህዝብ ጥያቄና ሮሮ ሰምተን ለሚታዩት ችግሮች መፍትሄ ብናቀርብ፣ የጠያቂዎቹን ጥያቄ ፖለቲካዊ ያደርግባቸዋል” በሚል ተልካሻ ምክንያት አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ግለሰብ ዳር ይዞ ቆሞ የህዝብን መከራ እንደሲኒማ ሊመለከተ ነወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህን አይነት ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ መመለስ ከፖለቲካ ድርጅቶች ምንነትና ማንነት ጋር የሚጻረር ነው።
የአንድን ማህበረሰብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ የማህበራዊ፣ የደህንነት ጥያቄዎችና ችግሮች እየመረመሩ አስተያየት ከመስጠት፣ ፖሊሲ ከመቅረጽ፣ መፍትሄ ይሆናሉ ብሎ የሚታሰቡ ሃሳቦችን ከማቅረብ ውጭ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የማንንም ጎፈሬ ለማበጠር አይደለም ወደ እዚህ አለም የመጡት። የሚያበጥሩት ጎፈሬ በሙሉ ፖለቲካዊ ነው።
ሰለዚህ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው የኢትዮጵያን የጤና ሙያተኞችን ጥያቄ አስመልክቶ የሃገሪቱ ፖለቲካ ድርጅቶች አቋም ምን ይሆናል ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች በግልጽ በአደባባይ አቋም መያዝ፣ የመፍትሄ ሃሳባቸውን መግለጽ አለባቸው። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች እያመነቱም ቢሆን አቋማቸውን መግልጽ ጀምረዋል። ይህን በማድረጋቸው ተገቢውን የሆነ የስራ ሃላፊነትና ግዴታቸውን እየተወጡ ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል።
አቋማቸው የጤና ሙያተኞች ጥያቄ ፍትሃዊ ነው አይደለም? ከሚል የሚጀመር መሆን ይኖርበታል። የነጻነትና እኩልነት፣ የእናት ፣ ኢህአፓና ኦፌኮን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከጤና ሙያተኞች ጎን ቆመዋል።
በሌላ በኩል ግን፣ “ይህ ዘርን እምነትንና ሌላንም ህዝብን መከፋፈያ መሳሪያ ተጠቅሞ በመከፋፈል ማዳከም እንደማይቻል ሆኖ የተነሳ የጤና ሞያተኞች ጥያቄ፣ ሌሎችን የተራቡ የማህብረሰብ ክፍሎችንም ጭምር አነቃንቆ የአብይን አገዛዝ ችግር ላይ ይጥለዋል” ብለው የሰጉ እንደ ኢዜማ አይነት ድርጅቶች አሳፈሪ አቋም ሲወስዱ ታየተዋል። በብልጽግና ቋንቋ የጤና ሙያተኞችን ፍትሃዊ ጥያቄ የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሴራ አድርገው ሲያወግዙት ተስተውሏል።
ብልጽግና ከተንኮታኮተ እንደኢዜማና እንደአብን ያሉ ድርጅቶች እንኳን እንደ ፖለቲካ ድርጅት መትረፍ ሳይሆን፣ መሪዎቻቸው በሰላም የሚኖሩበት ሆኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር እንደማይችል ያውቁታል። ስለሆነም እነዚህ ድርጅቶች እንደብልጽግና ፓርቲ የተሸበረ መግለጫዎች ቢያወጡ አይገርምም። ውሻ በበላበት ይጮሃል ነውና።
ለገዢው ፓርቲ በወዶ ገብ ግርድና ከገቡት እንደ ኢዜማና አብን የመሳሰሉ ድርጅቶች ውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የጤና ባለሙያተኞችን ጥያቄያዎች በማጤን በጊዜያዊነት መፍትሄ እንዴት ሊያገኝ እንደሚችል፣ “ወደፊት በቋሚነት እንዴት ይቃለላል” የሚሉ ነጥቦችን ያካተተ መግለጫዎችን መስጠት ይጠብቅባቸዋል።
ይህ ከኑሮ ውድነት ጋር የተሳሰረ ጥያቄ የጤና ባለሙያዎች ብቻ ጥያቄ አይደለም። የመምህራኑ፣ የፋሪካ ሰራተኛው፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ የወታደሩ፣ የፖሊሱ፣ የዝቅተኛው ነጋዴ የሌሎችም የኑሮ ውድነት የደቆሳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጥያቄ መሆኑን ለአገዛዙ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል።
ኑሮ ውድነት ለሚያስቃያቸው ወገኖችቸው በሙሉ “የጤና ሙያተኞች ወንድሞቻችሁን እና እህቶቻችሁን አግዙ፤ ድምጽ ሁኗቸው።” የሚል ጥሪ የማቅረብ መብት አላቸው። ግዴታም አለባቸው። ኢኮኖሚውን በደንብ ተነትነው፣ የህዝቡን የኑሮ ውድነት ለማቃለል መንግስት ገንዘብ ከየት ማግኘት እንደሚችል በመረጃ ላይ የተመሰረተ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ አለባቸው። ተቃዋሚዎች ስልጣን ቢይዙ ይህን ልጓሙ የተበጠሰውን የኑሮ ውድነት እንዴት ሊያስቆሙት እንደሚችሉ ፖሊሲያቸውን ለህዝብ ማጋራት አለባቸው።
እንዲህ አይነቱን አቋም መውሰድ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል ለሚያደርጉ ድርጅቶች ብቻ የተሰጠ መብትና ግዴታ አይደለም። የፖለቲካ ግብ አለን ብለው የሚያስቡ የትኞቹም በአመጽ አገዛዙን የሚገዳደሩ ድርጅቶችም መብት ነው። እንዲህ አይነት ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ በሚነሳበት ወቅት ጉዳዩን እንዴት እንደሚያዩት በአደባባይ መናገር አለባቸው።
የአማራ ፋኖ ሁለቱም ድርጅቶች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት፣ ከዛም አልፎ ራሱ ህወሃትም በዚህ ጉዳይ ላይ አቋማቸውን ግልጽ ማድረግ አለባቸው። ጦርነት በሌላ ስልት የሚከወን ፖለቲካ ነውና “የጠመንጃ ትግል የማደርግ ደርጅት ነኝ” በሚል ሰበብ በህክምና ባለሙያተኞች ጥያቄ ላይ አቋም ከመውሰድ ማምለጥ አይቻልም። መሳሪያ ተሸክሞ በረሃ ለበረሃ የሚንከራተተው ታጋይ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶች፣ ወንድሞች፣ ልጆች፣ የቅርብና የሩቅ ዘመዶች ህክምና የሚያገኙት በእነዚህ በጭካኔ በተገፉ፣ መብላት በተሰናቸው የጤና ባለሙያተኞች መሆኑ መረሳት የለበትም። ጉዳዩን ከፖለቲካ ወደ ሞራልም ከፍ የሚያደርገው ይህ ነው።
የጤና ባሙያተኞች፣ “ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለም” ብለዋል። እኔም እንዳልሆነ፣ የዛሬ ስድስት አመት ጥያቄው አብይ ክንፍ የቀረው መልአክ ሆኖ በሚታይበት ወቅት የቀረበ መሆኑን በማሳየት አረጋግጫለሁ።
በሌላ በኩል ግን ይህን የጤና ባለሙያተኞች ጥያቄ የፖለቲካ ድርጅቶች ማስተጋባትና በፈለጉት መንገድ መተርጎም፣ መግለጽ መብታቸው ነው። ሲፈልጉ የፖለቲካ ተቃውሟቸውን እንደ ብልጽግና እንደ ኢዜማ በማስፈራሪያና በማጭበርበሪያ እያሽሞነሞኑ መግለጽ ይችላሉ። ከዚህ አይነቱ ነውረኛ አካሄድ መራቅ ከፈለጉ የጤና ሙያተኞች ፍትሃዊ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ ከሙያተኞቹ ጎን መቆም ህዝብም በጋራ ተነሳስቶ ለሃኪሞቹ ጥያቄዎች አገዛዙ ፍትሃዊ ምላሽ እንዲሰጥ፣ ከጤና ሙያተኞቹ ጎን በጋራ እንዲቆም ጥሪ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
የሃገሩ ገዥዎች ራሳቸውን እንኳን ሲያማቸው ለህክምና የት እንደሚሄዱ ይታወቃል። የጤናው ዘርፍ ቀውስ እነሱን አይመለከታቸውም። ከማንም በላይ ቀውሱ የሚጎዳው ራሱን ህዝብን ነውና አገዛዙ ሃኪሞችን ማሰር፣ ማንገላታትና መደብደብ አቁሞ ለጥያቄያቸው አስቸኳይ መልስ እንዲሰጥ ህዝብም የአገዛዙን ማንቁርት ማነቅ ይገባዋል።
ውድ ወገኖች ማጋራቱን አትርሱ