ኢትዮጵያዊነት፡- በኮሪያ ምድር ላይ ከፍ ያለ ታላቅና ክቡር የነጻነት
ከኮሪያ፤ ሴዎል ከተማ (ከኮሪያ የጦር መታሰቢያ ሙዚየም)
እንኳን ለ84ኛው የአርበኞች/የድል በዓል አደረሰን!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤
‹‹…. እናንተ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታችን፤ ለክብራችን፤ ለዑላዊነታችን- መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታችሁን የሠዋችሁልን የክፉ ጊዜ፤ የመከራ ዘመናችን… የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችን ናችሁ… እናንተ በዚህች በእናት ምድሬ፤ በኮሪያ አፈር ላይ ለነጻነታችን፣ ለክብራችን- ደማችሁን፤ ላባችሁን እና እንባችሁን ከአፈራችን ጋር የቀላቀላችሁ የሰላም አርበኛ፤ የሰላም ጀግኖች፤ የሰላም ሰማዕታቶቻችን ናችሁ!!››
‹‹ታውቃለህ ወዳጄ፤ ምንጊዜም አንረሳችሁም፤ በልባችን ፅላት ውስጥ ታትማችኋል… መቼም አዎ! መቼም አንረሳችሁም…!! ለእኛ ያላችሁን አጋርነታችሁን በደም ማሕተም ያተማችሁ የሁልጊዜ ባለውለታዎቻችን፤ የልብ፤ አዎን! የልብ ወዳጆቻችን ናችሁ!!››
ይሄ ልብን በአድናቆት ቀጥ የሚያደርግ የሚመስል በባለውለታነት፤ በባለ ዕዳነት መንፈስ ከጆርዬ አልፈው አጥንቴና ደም ሥሬ ውስጥ የመዝለቅ ጉልበትን ያገኙ እነዚህ- ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ ውብ ቃላት የኮሪያውን የጦር መታሰቢያ ሙዚየም ያስጎበኘችኝ ኮሪያዊት ወዳጄ ናቸው።
ግዙፉንና ባለ ግርማ ሞገሱን የኮሪያን መታሰቢያ የጦር ሙዚየም ምታስጎበኘኝ ይህች ወዳጄ፤ የሦስተኛ ዲግሪ/የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቷን በአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እየተከታተለች የምትገኝ ስትሆን፤ በ‹Universal Peace Federation› በተባለ በመንግሥታቱ ማኅበር/United Nations (UN) ዕውቅና ባለው ተቋም ውስጥ አብረን ሰላም አምባሳደር ሆነን እያገለገልን የምትገኝ ኮሪያዊት ሴት ናት፡፡
በኮሪያዋ ውብ ከተማ ሴዎል የተገኘነውም ይኸው ‹Universal Peace Federation› የተባለ በሰላም ላይ የሚሠራ ተቋም በጠራው ዓለም አቀፍ የሰላም ኮንፈረስ ላይ ለመሳትፍ ነበር፡፡
ከዚህ የሰላም ጉባኤው ጎን ለጎንም ለኮሪያ ሰላምና ነጻነት መሥዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ የታነጸው የኮሪያ የጦር ሙዚየም ደግሞ አንዱና ዋንኛው የጉብኝታችን አካል ሆኖ ነበር። ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 የሚሆኑ ሀገራት በ‹UN› ስር ሆነው የተሳተፉበትን ትልቅ ታሪክና ቅርስ በያዘው በኮሪው የጦር መታሰቢያ ግዙፍ ሙዚየም ጉብኝታችን ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያውያን ውለታና ጀግንነት አብዝታ የምትብሰለሰልና ነፍስ ያልቀረላት እስኪመስል ድረስ በአድናቆት ልቧ የተሞላው ኮሪያዊት ወዳጄ – በታላቅ ግርማ ሞገስ በኮሪያ ምድር፣ በሴዎል ከተማ እምብርት ላይ ከፍ ብሎ የሚውለበለበውን፤ በጀግኖቻችን ደምና አጥንት የከበረውን የሀገሬን፤ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያመላከተችኝ፤
‹‹ተረፈ በእውነት በጀግኖች አባቶቻችሁ ልትኮሩ፤ ልትደነቁ ይገባችኋል… ይህ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ዓርማችሁ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን የነጻነት ትእምርት/Symbol የአይበገሬነት መገለጫ ነው፤››
ቀጠለችናም፤
‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን እኮ ከዐድዋ ተራራ እስከ ፀረ-ፋሽስት የ5ቱ ዓመት የአርበኞቻችሁ ተጋድሎ- የነጻነትን ክቡር መንፈስ በጭቆና ቀምበር ስር ሆነው ሲማቅቁ ለነበሩ አፍሪካውያን ወንድሞቻችሁና ለሰው ልጆች ሁሉ የናኛችሁ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ… የነጻነትን ዋጋ በደማችሁ ከፍ ያደረጋችሁ የጥቁር የሕዝብ ኩራት…፡፡››
ይህቺ ወዳጄ ዐድዋንና የ5ቱን ዓመት የአርበኞቻችንን ተጋድሎ ስታነሳ አንዳች የነጻነት ስሜት በውስጤ፣ በደሜ ውስጥ እንደ እሳት ቋያ ሲንቀለቀልብኝ ተሰማኝ… እናም ለአስጎበኚዬ፤
ወዳጄ እውነት ብለሻል- ዐድዋ የሰው ልጆች ሁሉ የነጻነት ክብርና የመንፈስ ልእልና መገለጫ፣ የፀረ-ባርነት/የፀረ-ኮሎኒያሊዝም የኢትዮጵውያን ተጋድሎ ሕያው አሻራ፤ የጥቁር ሕዝብ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ማንነት፤ አንድነትና መንፈሳዊነት ምስክር የሆነ ታላቅ ድል ነው፡፡
ይህን የዐድዋን ታሪካዊ እውነት በተመለከተም፤ ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የነጻነት አርበኛ፤ የሰላምና የይቅርታ ሰው፤ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ- ዐድዋን የገለጹበትን ንግግራቸውን እንዲህ ጠቀስኩላት፤
“… the Adowa Victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality, and freedom from colonialism.”
ኮሪያዊቷ ወዳጄ ንግግሬን በርጋታ ሆና ካዳመጠች በኋላም እንዲህ አለችኝ፤
“… በእውነት ሁሌም ይገርመኛል ከአፍሪካ እስከ ኮሪያ ልሣነ-ምድር ስንት ሺሕ ኪሎ ሜትር አቋርጣችሁ መጥታችሁ በዚህ በሀገሬ፤ በኮሪያ ምድር የነጻነትን ሰንደቀ በደማችሁ ከፍ ያደረጋችሁልን የነጻነት ተዋጊዎች፤ የሰላም ጀግኖች፤ የሰላም አርበኞች… እናንት አስደናቂ ኢ-ት-ዮ-ጵ-ያ-ው-ያ-ን…!!”
ይህ በጽሑፌ ለመግለጽ የሞከርኩት የኮሪያዊት ወዳጄ/አስገብኚዬ ስሜት ነው። በእውነት ነው የምላችሁ ይህቺ ኮሪያዊት ሴት- በእያንዳንዱ በምትናገረው ቃላት ውስጥ ያለውን ክቡርና ክቡድ የሆነውን የነጻነትን ውድ ዋጋ ለመግለጽ የሚቻል አይደለም፤ በጠራው ቆዳዋ፣ በፊቷና በግንባሯ ላይ በሚታዩት የደም ስሮቿ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት የነጻነት – ታላቅ፤ ሕያውና ክቡር መንፈስ በመላ እርሷነቷ ውስጥ እፈሰሰ፤ እየናኛ ያለ መስሎ ይታያችኋል፤ ይሰማችኋል፡፡
ይህች ሴት ከአንደበቷ በሚወጡ ቃላት ውስጥ ነ-ጻ-ነ-ት የሚለው ቃል ከአንደበቷ ብቻ ሳይሆን ከደሟ፤ ከልቧ፤ ከነፍሷ ጭምር ሚፈልቅ የቃላት ምንጭ ነው የሚመስለው… በደም ስሮቿ ውስጥ ኮለል ብሎ የሚፈስ የ-ነ-ጻ-ነ-ት ጅረት ድምፅ… ሰው የመሆን ልእልና፤ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ታላቅ ከፍታ!!
በኮሪያው የጦር መታሰቢያ ሙዚየም ቆይታችን ከአስገብኚዬ ወዳጄ ጋር ልቤን ወደገዛው ሌላኛው የጦር ሙዚየሙ ትእይንት አብረን አዘገመን።
ይኸውም በኮሪያ ምድር ክቡር ሕይወታቸውን የሠዉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ስም ዝርዝር የተጻፈበት የመሥዋዕትነት፣ የክብር ሐውልት፡፡ በዚህ ሐውልት ላይ ለኮሪያውያን ነጻነት፤ ልዑላዊነትና ሰላም ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉ የጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ስም ታሪክ በወርቅ ቀለም ከትቦት ደምቆና ከፍ ብሎ ይታያል፡፡
ከዚህ የነጻነት፤ የመሥዋዕትነት ሐውልት ግርጌ በአንድ ወቅት ይህን የጦር ሙዚየም የጎበኙና ዛሬም በሕይወት ያሉና ኢትዮጵያውያን የኮሪያ ሰላም አስከባሪ ዘማች የሆኑ ሁለት አረጋውያን አባቶች ፎቶ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ በኮሪያ ምድር የጀግንነት ገደል የፈጸሙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች- ሻለቃ ባሻ ሺፈራው ቢራቱ እና መቶ አለቃ ተረፈ ግዛው፡፡
በምስሉ ላይ እነዚህ የኮሪያ ዘማች አባቶች በኮሪያ ምድር ለሰው ልጆች ነጻነት፤ ለኮሪያውያን ሰላምና ነጻነት ሲሉ ደማቸውን ከኮሪያ አፈር ጋር በመቀላቀል የተሰዉ ጀግኖች ስም ዝርዝር ግድግዳ ላይ ዓይናቸውን ተክለው የጀግኖች ጓዶቻቸውን ስም በጥልቅ የትዝታ ስሜት ውስጥ ሆነው በእጆቻቸው ሲዳስሱ ይታያሉ፡፡
በጦር መታሰቢያ ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ውስጥ የነበረንን ቆይታ አገባደን ወደ ውጪ ስንወጣ በኮሪያ የሰላም ማስከበር ዘመቻ በተባበሩት መንግሥታት ስር የዘመቱ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ወደ በሚውለበለብበት የሙዚየሙ ግቢ አመራን፡፡
ከወዳጄ ጋር እያወጋን በቀስታ የኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ከፍ ብሎ ወደሚውለበለብበት ቦታ ደረስን፡፡ ለአፍታ ቆም አልኩና በሀገራችን ሰንደቀ ዓላማ ዘንግ ላይ በተለጠፈው ብረት ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ አነበብኩት፡፡ እንዲህ ይላል፤
“ኢትዮጵያ በኮሪያ ዘመቻ 6037 ወታደሮችን ሲሆን ያዘመተችው አንድም ወታደሮቿም አልተማረኩባትም፤ በግዳጅ ላይ ሳሉ የተሰዉ ወታደሮች ቁጥር 536 ሲሆን የቆሰሉ ደግሞ 122 ናቸው፤” ይላል፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በኮሪያው ሰላም ማስከበር ግዳጅ አንድም ሰው ያላስማረኩ በሁሉም ሀገራት ዘንድ አድናቆትን ያተረፉ ጀግኖች፤ አይበገሬዎች መሆናቸው ልብ ይሏል፡፡
በኮሪያ ሰማይ ላይ በግርማ ሞገስ ከፍ ብሎ ከሚውለበለበው ሰንደቅ ዓላማችን ስር ባለው የእምነበረድ ሐውልት ስርም የሚከተሉት ስንኞች በአማርኛና በኮሪያኛ ቋንቋዎች ተጽፎ ይነበባል፤
ዛሬም ይናገራል!!
ዘመናትን አልፎ አድማሳትን ተሻግሮ፤
ብዙ ሁነት ረግጦ ዓመታትን ቆጥሮ፤
ከቶ አልደበዘዘም አሁንም ያበራል፤
እንደ አልማዝ ይፈልቃል፤
በታሪክ ማማ ላይ ደምቆ ይንተገተጋል፤
የቃኘው ሻለቃ የኮሪያ ገድል፤ ዛሬም ይናገራል፡፡
የዓለም መንግሥታት በተሰለፉበት የጦር አውድማ ላይ፤
ከአኅጉረ አፍሪካ የብቻ ነጻ ሀገር ብቸኛው ተጋዳይ፣
በምድረ ኮሪያ በሩቅ ምሥራቅ ጸሐይ፤
ስምህ ለዘላለም ነው ከመቃብር በላይ፡፡
ኢትዮጵያ ማኅፀነ መልካም ሁሌም ደስ ይበልሽ፤
በጀግኖች ልጆችሽ ስምሽ ከበረ እንጂ ከቶ አልጠለሸም፡፡
በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ጥላሽ ስር፤
አንድም ስንኳ ቢሆን ምርኮኛ አልተገኘም፡፡
ምስጋና ለቃኘው ለትንታግ ተዋጊሽ፤
በድል ዓርማ ደምቋል የጦር ተልእኮሽ፤
ወኔ በተሞሉ በአናብስት ልጆችሽ፣
ሸማሽ በድል ጊጧል፤
በዓለም አደባባይ የነጻ አውጪነት ክብርሽ፡፡
እኔና ኮሪያዊት አስጎብኚዬ በመልእከቱ ሐሳብ ላይ ጥቂት ከተነጋገረን በኋላ ከጉብኝታችን እረፍት ለማድረግና የኢትዮጵያን ቡና ለመጠጣት በሙዚየሙ አቅራቢያ ወደሚገኘው ካፌ ጎራ አልን፡፡ በጭውውታችን መሃልም ኮሪያዊቷ ወዳጄ የአደራና የቁጭት ስሜት በተጫነው ድምፀት እንዲህ አለችኝ፤
It is wonderful to honor the heroic achievements of the Ethiopian peacekeeping force, but I don’t think we should end it there. What was the reason for the lives they lost and shed? The Korean Peninsula remains divided to this day. That means their sacrifices have only been sacrifices.
I would like to see the focus shift to ensuring that the Korean Peninsula is peacefully restored to one country, and I would like Ethiopia to put its efforts into cooperating with activities to achieve this.
እናንተ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በኮሪያ ምድር የከፈላችሁት ሕይወት መሥዋዕትነትና ያከናወናቸውን ጀግኖች ማክበር ድንቅ ነው፤ ግን በዚህ ብቻ ማብቃት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችሁ መሥዋዕትነት የከፈሉበት ምክንያት ምን ነበር? የኮሪያ ልሣነ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ለሁለት እንደተከፈለ ነው፤ ያ ማለት መሥዋዕትነታቸው መሥዋዕትነት ብቻ ነበር ማለት ነውን?!
የኮሪያ ልሣነ-ምድር በሰላም ወደ አንድ ሀገርነት እንዲመለሱ እንፈልጋለን፤ እኛ ኮሪያውያን ወደ አንድነት እንድንመጣ ዓለም ወደ ሰላምና አንድነት ትኩረቱን እንዲያደረግ እንሻለን፤ ይህንንም ለማሳካትም ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ዛሬም ጥረቷን እንድታደርግ፤ እንድትቀጥል እንወዳለን…፡፡
እንደ መውጫ፤
ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ተቋም/Addis Ababa University Institute of Peace and Security ዳይሬክተር፤ በአሁን ሰዓት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ ‹‹Africa in the Global Security Governance: A Critical Analysis of Ethiopia’s Role in the UN Peacekeeping Operations›› በሚል ርእስ እ.አ.አ. በ 2018 ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤
‹‹… የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ ከ 1948 እስከ 2013 በዓለም ዙሪያ 67 የሰላም ማስከበር ዘመቻዎችን ማካሄዱን በመጥቀስ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ የሰላም ማስከበር ተልእኮ እ.አ.አ ከ 1950ዎቹ እስከ 2017 በ 12ቱ ተልእኮዎች ውስጥ መሳተፏንና በአጠቃላይም እ.አ.አ. እስከ 2017 ድረስ 90 ሺሕ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችም በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ዘመቻ በመሳተፍ አኩሪ የጀግንነት ገድል መፈጸማቸውን…፤›› በዚሁ ለሕትመት በበቃው ጥናታዊ ወረቀታቸው ጽፈዋል፡፡
የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን- ከባለ ቃል-ኪዳን አገሮች ማኅበር/League of Nations እስከ ተባበሩት መንግሥታት/United Nations መቋቋም ድረስ ብቸኛ አፍሪካዊትና የጥቁር ሕዝቦች ተወካይ በመሆን ደማቅ የሆነ አሻራዋን አኑራለች፡፡
የአፍሪካ ሕዝቦች ሰላም፣ አንድነትና የወንድማማችነት እንዲሰፍን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን/Organization of African Union፣ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን /African Union/ በማቋቋም ግንባር ቀደሙንና ትልቁን ሚና የተጫወተች ባለ ታላቅ ታሪክ አገር ናት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ካረቢያና ጃማይካ፣ ከኮሪያ ልሣነ ምድር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮትዲቯር፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳና በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በሰላም አስከባሪነት ጀግና ልጆቿን በመላክ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም አገራት ሁሉ ትልቅ ባለውለታ ናት፡፡
ከዚህ የታሪክ እውነታ ጋር ተያይዞም የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ 2020 ባወጣው መረጃ መሠረትም፤ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ- በአፍሪካና በመላው ዓለም ባደረገችውና አሁንም እያደረገችው ባለው የሰላም አስከባሪነት የጎላ ተሣትፎዋ ምክንያት- በአፍሪካ የአንደኝነትን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሁለተኛነት ደረጃ እንደሚያስቀምጣት እንዲህ ሲል የሚከተለውን ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፤
“Besides being a seat to various International Non-Governmental Organizations (NGOs) and Diplomatic Seats, Ethiopia is the Political Capital City of Africa.
This ancient state has been wholeheartedly and constructively contributing to world peace and stability in line with the principles and missions of the UN so that the world could enjoy peaceful coexistence. Evidently, it is number one in Africa and the world’s second-largest peacekeeping force producer…”
ትናንትናም ሆነ ዛሬ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ግዳጅ- ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በተሰማሩበት ሀገራት ሁሉ የሰላም ተልእኮ ዘመቻቸው በአኩሪ የጀግንነት ገድል ኃላፊነታቸውን ማስመስከር መቻላቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ይህ ከአኅጉረ አፍሪካ (ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኡጋንዳ…) እስከ ኮሪያ ልሣነ-ምድር ድረስ የተሻገረው ከፍ ያለ “የሰላም ማስከበር” አኩሪ የታሪክ አሻራ እንዲኖረን ያደረጉ ጀግኖቻችን ደግሞ የሚገባው ዕውቅና እና ክብር ሊቸራቸው ይገባል፡፡
በዚህ ረገድም፤ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ታላቅ የጀግንነት ገድል የፈጸሙና ለሰው ልጆች ሰላም ሕይወታቸውን የከፈሉ፤ ታሪካቸውን በደማቸው ለጻፉ ጀግኖች መታሰቢያ የሚሆን፣ ትውልድ ታሪካቸውንና የጀግንነት ገድላቸውን የሚማርበት ቤተ-መዘከር/ሙዚየም፣ አደባባይና ሐውልት ይገባቸዋል፡፡
የእነዚህ ከሶማሊያ በረሃዎች እስከ ኮሪያ ልሣነ-ምድር የሰላም ሰማዕታት የሆኑ ጀግኖቻችን አኩሪ ታሪክና ቅርሶቻቸው በአንድነት በክብር ተቀምጠው የምናይበት ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ተገንብቶላቸው፤ አደባባይና ሐውልት ቆሞላቸው ለማየት የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ናፍቆትና ጉጉትም ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!!
ክብር፤ የኢትዮጵያዊነት የነጻነት ሰንደቅን በዓለም አደባባይ ከፍ ላደረጉልን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞቻችን ሁሉ!!