(ከአሁንገና ዓለማየሁ)
እጅግ ብዙ ጥፋትና ውድመት ዘላቂ ቁርቁዝና ባገራችን ላይ ያደረሰውን የፋሺስት ጦርነት አባቶቻችን በፈጣሪ እርዳታ ድል ያደረጉባትን ይቺን እለት አስበናት እንውል ዘንድ እንጂ ተጋድሏቸውን የሚመጥኑ ግጥሞች ሆነው አይደለም።
ፋኖ አምናና ዘንድሮ
በታቻምናው ፋኖ ጠላት እንደትንኝ ከተረፈረፈ
ሰማንያ አመት ሞልቶ አራትም ተረፈ
ያኛው ሙሶሎኒ
በአምስተኛው አመት ሲወጣ ተካልቦ በርትቶበት ዱላው
ጥቁሩ ሙሶሎኒ ቀለሙ ጠቅሞታል ሰባት አመት ሞላው
ያኔ ግራዚያኒ ላይ የወረወሩበት የጣሉበት ፈንጅ
ሳይወልዱ ተገድለው ሊያፈሩ አልቻሉም ልጅም የልጅ ልጅ
የነሱን ውርዋሮ የዒላማ ችግር በደንብ አስተካክሎ
ጥቁሩን ግራዚያኒ ማነው ሚጸድቅበት ከጭንቁ ገላግሎ?
እያለ የሚያስብ ብዙ ምስኪን አለ የጣሉት በጫካ ቤት እያፈረሱ
አያውቅም በጭራሽ ሌሎቹ እያዩት “በሶ ጨብጧል ወይ?” እንደሚሉት እሱ።
ተገልጦ ሲነበብ
ካምና ፋኖዎች ድል ነጩን ሙሶሎኒ ካገር ከነቀለ
ምሥጢር ይገኝ ይሆን?
የሚነቀልበት ጥቁሩ ሙሶሎኒ ባገር የበቀለ
ከበላይ ዘለቀው፣ ከዘርዓይ ደረሱ ክነአብዲሳ ገድል
አብነት አይጠፋም ለአዲስ ትውልድ ፋኖ ጠላት ለመንሻ ድል።
የፋኖ ስንክሳር
የአርበኞች ድርሳን
ተገልጦ ሲነበብ በአዲስ ትውልድ ልሳን
“ያምናን ፋና ውጋ፣ ያን ዒላማ አንሳ፣ እንዳርበኞች ፈልም
አቀናጅተህ ጥመድ፣ ፈር አውጥተህ ተልም
ከምር እንዲሠምር ያዲስ ትውልድ ፋኖ የወጣህበት ህልም”
የሚለን አይመስልም?
ያኔም እንዲህ ነበር
በቤትም በደጂ
በየቦታው ፈንጂ
የቀለም ለውጥ እንጂ
ወንድሜ
አዲስ ነገር የለም አምናም እንዲህ ነበር በሰላቶ ዘመን
ሰላሳ እንኳን ዲናር በማይሞላ ተመን
ለሽሮ ለጎመን
ባንዳው ፈልቶ እንዳሸን
ወጣትም ተይዞ በጅምላ ሲረሸን
በቦምብና በመርዝ ከሰማይ ሲጠቃ ምስኪኑ ወገኔ
በምድር ሲንጣጣበት ሞርታርና ዲሽቃ መትረየስ አዳፍኔ
እጅግ ክፉ ነበር የወረራው ጽናት እንደዛሬው ያኔ።
ዳገት ቁልቁለቱን ሰርጥና ዋሻውን ቀድሞ ተቆጣጥሮ
ደፈጣ እየጣለ በምርኮ መሣሪያ አቅሙን አጠንክሮ
ያምናው ትውልድ ፋኖ ነጩን ሙሶሎኒ ኋላ ከከተማ እንዳወጣው ነቅሎ
ያዲስ ትውልድ ፋኖም ጥቁሩን ሙሶሎኒ እየታገልክ ቆየው ይመጣል በቶሎ።
ይታረም
አብሮ በቅሏል አዎ
ሰይጣን ብልጽግና በሌሊት የዘራው
አሁን ተከሥቷል
ቡቃያውን አልፎ ሲታየን አዝመራው
ይነቀል ይታረም
አብሮማ አይክረም
ፋኖ ስንዴ ሆኖ ሕዝብ እንዲያገኝ ጤና
ይታረም ክርዳዱ
በሌሊት የዘራው ዲያብሎስ ብልጽግና