April 27, 2025
ጠገናው ጎሹ
የአስተያየቴ ዓላማ ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም በባሰ ሁኔታ የምንገኝበት አስከፊ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ጠርናፊዎች አንዱና ዋነኛው ስልት የእውነትን ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት የጨካኝ ሰይፋቸው ዒላማ/ሰለባ ያደረጉበትንና እያደረጉ ያሉበትን መሪር እውነት ለማየትና ለማሳየት መሞከር እና ይህንኑ የሚጋራ አንባቢ ወገን የሃሳብና የአስተሳሰብ ልውውጥ/መንሸራሸር ያደርግ ዘንድ ለማሳሰብ እንጅ ስለ እውነት ንድፈ ሃሳባዊ ትንተና ለማድረግ አይደለም።
በቀላል አገላለፅ እውነት (truth) በአየር ላይ የሚንሳፈፍ አንዳች አይነት መንፈስ ሳይሆን በሰው ልጅ ሁለንተናዊ መስተጋብራዊ ሂደት ውስጥ የሚፈጠር፣ የሚኖርና ሊረጋገጥ የሚችል ነገር ነው። በሌላ በኩል እውነታ (fact) ብዙ የማሳመንና የመተማመን ክርክርና ውዝግብ ሳያስፈልገን ልናውቀውና ልንረዳው የምንችለው ነገር ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ካልሆነ በስተቀር ከእውነት (truth) በመሠረተ ባህሪው (በመሠረታዊ ምንነቱ) የተለየ አይደለም።
እንኳንስ በእንደኛ አይነት ለመግለፅ በእጅጉ በሚከብድ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሥር በወደቀ አገር በአንፃራዊነት እጅግ በተሻለ የዴሞክራሲና የስልጣኔ ደረጃ ላይ በሚገኝ አገርም በእውነተኝነት እና በሃሰተኝነት/በሸፍጠኝነት መካከል ሊኖር ከሚችል ግጭትና አሉታዊ ተፅዕኖ ፍፁም ነፃ መሆን ከቶ አይቻልም ። ማድረግና መሆን የሚቻለው በተቻለ መጠን ሃሰተኞች፣ሴረኞች፣ባለጌዎች፣ጨካኞች፣ ወዘተ ወደ ሥልጣን እንዳይወጡ ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እና ሥልጣነ መንበር ላይ ወጥተው ከሆነም ብዙ መከራና ውርደት ሳያደርሱ ለቀው እንዲወጡ በማስገደድ በአንፃራዊነት (ፍፁምነት የለምና) መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በእውነተኛ ሃላፊነትና ግዴታ ለመፈፀምና ለማስፈፀም ታማኝነቱና ችሎታው ባላቸው መተካት ነው።
ከዚህ ውጭ ሌላ የእውነትን አሸናፊነት እና የሃሰትን/የአጭበርባሪነትን ተሸናፊነት እውን ማድረጊያ መፍትሄ (መንገድ) ፈፅሞ የለም፤ አይኖርምም። በሌላ አገላለፅ የእውነት አሸናፊነትን እና የሃሰት/የውሸት ተሸናፊነትን ከመራራና ከፅዕኑ የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት፣ የመከባበር ፣ የሰላም እና የጋራ እድገት ተጋድሎ ውጭ መመኘትም ሆነ መጠበቅ ፈፅሞ የገሃዱ ዓለም እውነታ አይደለም።
ለዘመናት ከመጣንበት እና ከሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚያው ዘመን ሥርዓት (ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግ) ውላጆችና አሻንጉሊቶች የነበሩ ተረኛ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች አብይ አህመድ በሚባል የሃሰተኝነት/የአጭበርባሪነት ልክፍተኛና ጨካኝ ግለሰብ እየተመሩ ከሚያደርሱብን እጅግ አስከፊ መከራና ውርደት ሰብረን እንዳንወጣ ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ እውነትን አሸናፊ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ/የተባበረ ተጋድሎ ከማድረግ ይልቅ “እውነት ያሸንፋል!” በሚለው አጠቃላይ መፈክር ራሳችንን ከመሸንገል ( ከማታለል) ክፉ ልማድ ሰብረን ለመውጣት አለመቻላችን ነው።
ይህ ደግሞ በየዲስኩሮቻችንና በየስብከቶቻችን የምጠቀምባቸውን/የምንጠቅሳቸውን አጠቃላይ እውነቶች ወደ እኛው ተጨባጭ ሁኔታ አውርደን ምንና እንዴት ስናደርግ ነው የእኛ እውነት የእኩያን ገዥ ቡድኖችን ልክ የሌለውና አደገኛ ውሸት/አታላይነት ድል የሚያደርገው (የሚያሸንፈው)? የሚለውን ፈታኝና ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ ያለመቻላችን ውጤት ነው።
እናም እውነትንና የእውነት አሸናፊነትን እውነትን በመፈለጋቸው፣ በማራመዳቸው፣ እና የባለጌና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችን እውነት ደፍጣጭነትን ፀንተው በመቃወማቸው ምክንያት የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ ሰለባ ከሆኑና በመሆን ላይ ከሚገኙ ንፁሃን ወገኖች ለይቶ ማየት ፈፅሞ የአገር (የህዝብ) ወዳድነት ወይም የነፃነትና የፍትህ አርበኝነት ስሜት የለውም።
እነዚህን ንፁሃን ወገኖች በግፍ መግደልና በቁም ማሰቃየት እውነትን ራሱን መግደልና በአፍጢሙ መድፋት ካልሆነ ሌላ ምን?
ዘመን ጠገብ የሆነውንና በተለይ በአሁን ወቅት እጅግ አስከፊ፣ አስፈሪና እንደ ህዝብ አሳፋሪ እየሆነ የቀጠለውን የንፁሃን ወገኖች/ዜጎች የቀን ተቀን የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ እያየንና እየሰማን በድርጊት አልባ የእውነት ያሸንፋል መፈክር ወይም ሃይለ ቃላት እስከመቼ?
እውነትን አሸናፊ የሚያደርገው መከረኛው ህዝብ በእኩያን ገዥ ቡድኖች በግፍ እየተገደለና የቁም ሞት እንዲሞት እየተፈረደበት እውነት በየት በኩል አልፎ ነው አሸናፊ የሚሆነው?
በእውነት ስለ እውነት ለመናገርና ለመነጋገር ወኔው ካለን እውነትና እውነተኞች ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ በዘለቀውና አስከፊ እየሆነ በቀጠለው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት ጨካኝ ሰይፍ ሲሰየፉ እና ለቁም ሞት ሲዳረጉ እያየንና እየሰማን “የእውነት ያሸንፋል” አጠቃላይ እውነት ደስኳሪዎችና ሰባኪዎች የመሆናችን አባዜ ከምር አይሰማንም እንዴ?
በሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌና ጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በአስከፊ ሁኔታ የተጎሳቆለውን/የተደፈጠጠውን እውነት/እውነታ ነፃ አውጥተንና ለአሸናፊነት አብቅተን ለዘመናት ከመጣንበትና ከሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝበትን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የሞራል፣ የመንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ እምነት ግዙፍና መሪር የውድቀት እውነት (truth) ሰብረን ካልወጣን ስለ እውነት አሸናፊነት ባዶ (ተግባር አልባ) ዲስኩር/ስብከት እየደሰኮርንና እየሰበክን የት ነው የምንደርሰው?
አዘውትረን የምንጠቅሳቸውን ብዙ ፅንሰ ሃሳቦች (ሃይለ ቃላት) ምንነትና እንዴትነት በአግባቡ ካልተረዳናቸውና ካልገለፅናቸው የተለመዱ አባባሎች ይሆኑና የምንገኝበትን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት የሚመጥን የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ለማካሄድ እንቸገራለን ። ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም በአስከፊ ደረጃ የምንገኝበትን ግዙፍና መሪር ፖለቲካ ወለድ ትውልዳዊ ፈተና ለመጋፈጥ እና የምንፈልገውን የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ እድገት ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ለማድረግ ካልቻልን ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች እየዘቀዘቁ በሚያስነብቡንና በሚያስደምጡን ፀረ እውነት ዘመቻ እየተጠለፍን ከመውደቅ አስከፊ፣ አሳፋሪና አስፈሪ አዙሪት ሰብረን አንወጣም።
በዚህ ረገድ ካሉብን ጎደሎዎች መካከል አንዱ እውነት ያሸንፋል! እውነት በሃሰት አይሸነፍም! እውነትን የያዘ አሸናፊ ነው ! ወዘተ የሚሉ አጠቃላይ የእውነትነት ምንነትን (the very essence of general truth) የሚያስተጋቡ (የሚገልፁ) ሃይለ ቃላትን እንዴትና መቸ ? የሚለውን ሰፊና ጥልቅ ጥያቄ ዘላቂነት ባለው አቀራረብ ለመመለስ እና ወደ ተጨባጭ መሳሪያነት ለመለወጥ ያለመቻላችን ጉዳይ ነው። አዎ! እውነት ነው እውነትና እውነተኛነት ምንጊዜምና የትም የሰማያዊውም ሆነ የገሃዱ ዓለም ህይወት ሃያል እሴቶች ናቸው።
እርግጥ ነው እጅግ ውስብስብ ከሆነው የሰው ልጅ ባህሪ፣ ፍላጎት፣ ጥቅም፣ ወዘተ አንፃር ፍፁም (ሁል ጊዜና በየትኛውም ሁኔታ) የእውነት አፍቃሪ፣ ጠበቃና ዋስትና መሆን የሚጠበቅ አይደለም። ዘመን ጠገቡ የእኛው ሁኔታ ግን ከጊዜ ርዝማኔም ሆነ ከአስከፊነት ደረጃ አንፃር በእጅጉ ለማመን የሚያስቸግር ነው።
ለዚህ ነው እውቀትን፣ የረጅም ጊዜ ልምድንና እጅግ መሪር ተሞክሮን በአግባቡ በመጠቀም እና ከምር ስህተትን በማረም ከህዝብ፣ በህዝብና ለህዝብ የሚሆን ሥርዓተ ፖለቲካን እውን ለማድረግና ለማጎልበት የሚያስችል መራራ የጋራ ትግል የግድ መሆን ያለበት ።
ይህንን ሆኖና አድርጎ ለመገኘት ደግሞ እውነት የተሸከሙትንና እውነተኛ ንፁሃን ዜጎችን በመግደልና የቁም ሙቶች በማድረግ እውነትን ገድለው ሃሰትን የሥልጣነ መንበራቸው ማስጠበቂያ የሚያደርጉትን እኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸውን አስወግዶ በሽግግር ፍትህ አግባብ ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድርግ አማራጭ የሌለው ፍኖተ መፍትሄ ነው። ያኔም ነው እውነት በሃሰት ላይ ዘላቂና የማያዳግም ድል አድራጊነትን (አሸናፊነትን) የሚጎናፀፈው!!!
ለዚህ ደግሞ ከአገራችን የረጅም ጊዜና እጅግ አደገኛ ከሆነ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት የሚመነጩ ፈታኝ ሁኔታዎች የመኖራቸው እውነትነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በይፋ ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረውና በአንፃራዊነት እጅግ በተሻለና ተስፋ ሰጭ በሆነ አቋምና ቁመና ያለው የአማራ ፋኖ እና የትግሉ ተጋሪ ሌሎች ወገኖች የሚያካሂዱትን የህልውና፣ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ ወዘተ ተጋድሎ ገንቢ በሆነ ሂሳዊና ሁለንተናዊ ድጋፍ አጅቦ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንዲበቃ ማድረግ ትውልዳዊ ሃላፊነትና ግዴታ መሆን አለበት።
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!!!