ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ

ክፍል 14
የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የመጠንም የአይነትም እመርታ እንዲያሳይ፤
- የአማራ ህዝብና የፋኖ እንቅስቃሴ የአማራን ህዝብ የህልውና አደጋ ለመመከት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየው ፈጣን ወታደራዊና ድርጅታዊ እድገት በቂ ውዳሴ አግኝቷል። እሱን በመድገም ወይም እድገቱን በዝርዝር በማሳየት ግዜ ማጥፋት ተገቢ አይደለም። የትግሉ መሪዎችም ሆኑ ደጋፊዎች ጊዜያቸውን ማጥፋት ያለባቸው፣ እንዴት ይህ ትግል በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየውን እድገት ወደላቀ ደረጃ በማሳደግ የአማራን ህዝብ ስቃይ ማሳጠር ይችላል ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት ነው።
- መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው ሃቅ የአብይ መንግስት “እንደ ደፈጣ ተዋጊ ጦርነቱን በማራዘም የአማራን ህዝብ ስቃይ በመጨመር፣ ፋኖ ባላበት እንዲረግጥ በማድረግ የተራዘመ የጦርነት ስልት አሸናፊ ሆኘ እወጣለሁ” የሚል ስትራተጂ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው። አብይ አህመድ “ጦርነቱን፣ እልቂቱን፣ ሰላም መጥፋቱን፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀቱን እና ማህበራዊ ቀውሱን በማባባስ በማራዘም በህዝብና በፋኖ መሃከል፣ በፋኖ እና በፋኖ መሃካል ክፍተት እንዲፈጠር፣ አንድነታቸው እንዲላላ በማድረግ ለድል እበቃለሁ” የሚል እምነት ይዟል። በአማራ ክልል አገዛዙ እያደረገው ያለው ይህንን ነው። ይህ እውነታ ፋኖን የሚመሩ አካላትን “እንዴት ይህንን ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል ማጠናቀቅ እንችላለን?” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያስገድድ ሆኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀጣጥሎ የነበረው የአማራ ህዝብ ትግል ለምን ባላበት መርገጥ ጀመረ ምላሽ የሚያስፈለገው ጥያቄ ነው።
- የዚህ ጥያቄም ምላሽ የሮኬት ሳይንቲስትነት ብቃት የሚጠይቅ አይደለም። እንደኩሬ ወሃ ኩልል ብሎ የሚታይ ነው። የአማራ ህዝብ የህልወና ትግል ባላበት መርገጥ የጀመረው ትግሉ ሲጀመር የነበረው የተበታተነ አመራር ፈጥሮት የነበረው የተቀላጠፈ ጠላትን የማዋከቢያ የጦርነት ስልት አገልግሎቱን የጨረሰ እለት እንደሆነ ይታወቃል። ባላበት የመርገጡ ችግር መከሰት የጀመረው አሁን ትግሉ የደረሰበት ደረጃ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅምን በፍተኛ ደረጃ አስተባብሮ ወሳኝ የሆነ ምት በጠላት ላይ ማሳረፍን የሚጠይቅ መሆኑን እና ይህን ሃይል ለማስተባበር የሚያስችል ተቋም ፋኖዎች መመስረት አለመቻላችው ነው። ይህ ችግር ለማቃለል የሚደረገው ጥረት በተጓተተና በተሰናከለ ቁጥር የህልውና አደጋው ትግል አብይ አህመድ ወዳዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ በመግባት ህዝብም ትግሉንም ታጋዮችም አታጋዮች ከፈተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቁ መታወቅ አለበት ።
- ፋኖ አንድ ወጥ የሆነ የፖለቲካና ወታደራዊ የጋራ አመራር መፍጠር አለመቻሉ በበርካታ መስኮች ከትግሉ ጋር ተያይዘው መከናውን የሚገባቸውን አጋዥ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ቀይዶ ይዟቸዋል። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተለያዩ ርእሶች ስር ባቀረብኩት ሃተታ፣ የፋኖ የጋራ አመራር የመፍጠር ስራ የወቅቱ የስራዎች ሁሉ ቁንጮ ስራዎች እንደሆነ ለማሳሰብ ሞክሬያለሁ። ይህ ስራ እንዲከናወን መወትውት መማጸን ብቻ ሳይሆን የችግሩን ምንነት ተገንዝቦ መፍትሄ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህ መፍትሄ ምን መምሰል እንደሚችል በሌሎች ሰነዶች ተሰንዶ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያዩት ስለተደረገ እዚህ ላይ ሰፊው የትግሉ ደጋፊ ማህበረሰብ እንዲያወቀው ብቻ ችግሩን እና መፍትሄውን ባጭሩ ማቀርብ ይገባል።
- በራሱ የጎበዝ አለቃ እየተመራ ትግል የጀመረን ፋኖ “ከላይ ወደታች የሚጫኑ መሪዎች ይኑርህ” የሚል የተሳስተና ሁኔታውን ግምት ውስጥ ያላስገባ የአደረጃጀት እሳቤ የፈጠረው ችግር ነው። የአማራ ፋኖ ወደ እዛ አይነት አደረጃጀት ከማደጉ በፊት በቅድሚያ ማለፍ ያለበት የአደረጃጀት የእድገት ደረጃ አለ። የመጀመሪያ አደረጃጀት በየክፍለው ሃገሩ የሚገኙ የተበታተኑ አደረጃጀቶችን በአንድ የጋራ አመራራ ስር ማሰባሰብ ነው። ይህ ከታች ከወረዳም ሊጀመር ይችላል። ይህ መሰባሰብ በአንድ ግለሰብ መሪ ስር ማሰባብሰብ ማለት አይደለም። የጋራ አመራር የሚለውን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል። በስምምነት አንድን ግለሰብ መሪ ማድረግ የሚችሉ ክፍለሃገሮች ካሉ አንድ መሪ ቢመርጡ ችግር የለውም። ይህን በማይቻልባቸው ቦታዎች መሪ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው አካላት የሚሳተፉበት የጋራ አመራር መፍጠር ትክክለኛው መንገድ ነው።
- ይህ የጋራ አመራር የፖለቲካና ወታደራዊ ክፍሎቹ ተለይተው እንዲደራጁ ማድረግ ይገባዋል። ወታደራዊ አደረጃጀቱ ለብቻው ይሁን የሚባለው ኦፕረሽናል ነጻነት እንዲኖረው እንጂ ስራው በፖለቲካ እይታ የሚመራ ነው።
- በየክፈለ ሃገሩ የሚገኙ የፋኖ አካላት በዚህ አይነቱ የጋራ አመራር ስር ከተሰባሰቡ በኋላ በአማራ ደረጃ የሚፈጠረውን የጋራ አመራራ ከእነዚህ ክፍለ ሃገሮች በተመረጡና በተወከሉ ሰዎች የጋራ አመራር ማቋቋም ይቻላል። ይህ አደረጃጀት ብቻ ነው፤ የግለሰቦችን እና የቡድኖች እኔ ካልመራሁ የሚል ፉክክር አስቀርቶ የአማራ ህዝብና ትግሉ የሚጠይቀውን አንድ ወጥ አመራር በቀላሉ ማምጣት የሚችለው። በሂደት ይህ የአመራራ ስልት እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል።
- በየክፈለ ሃገሩ ከጎናቸው ከተደራጁ የፋኖ አካላት ጋር አንድነት መፍጠር ያልቻሉ የፋኖ አካላት፣ ክፍለ ሃገር አቋርጠው ከሌሎች ክፍለ ሃገር ፋኖዎች ጋር አንድ ድርጅት ፈጥሬያለሁ ማለት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ትርጉሙ ወደዜሮ የተጠጋ ድርጊት መሆኑን ማወቅ አለባቸው። በዚህ አይነት አደረጃጃት እንዴት ሆኖ ነው ትግሉ የሚጠይቀውን በአንድ አካባቢ በሚገኝ የጠላት ሃይል የተቀናጀ ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘር የሚችሉት? እንዲህ አይነቱ አደረጃጀት ግብዝነትን የሚያሳይ ነው። ተአሚኒነት ሊኖረው የሚችል ድርጊት አይደለም። ይህ አሰራር በአንድ ክፍለ ሃገር ውስጥ ሁለትና ሶስት የተለያዩ አደረጃጀቶች በመፍጠር የተቀናጀ ትግል እንዳይደረግ እንቅፋት ከመሆን አልፎ በተላያዩ ድርጅታዊ ስሜቶች ፋኖዎች እርስበርስ እንዲገፋፉ በማድረግ ጠለትን ተትው እርስ በርሳቸው እንዲካሰሱ፣ እንዲታኮሱ የሚያደርግ ነው። እንዲህ አይነት ፍንጮች እየታዩ ነው። ይህን አደጋ ማስቀረት ለአማራ ህዝብ ህልወና መከበር ማንኛውንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ከሚል የፋኖ አመራር የሚጠበቅ ነው።
- በአንዳንድ ቦታዎች በፋኖዎች መሃከል የሚታይ የግፍጭ ሂደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። ይህ ሂደት በጊዜ መቀጨት አለበት። በአስቸኳይ ሁሉንም የአማራ ፋኖዎች በአንድ የጋራ አመራራ ስር የሚያስገባ አደረጃጀት እንዲፈጠር የማድረጉ ስራ ለነገ በይደር የሚቀመጥ ስራ አይደለም። ከሚገባው በላይ የተጎተተ ለአማራ ህዝብ መከራ መራዘም፣ ለአማራ ጠላቶች ብርታትን የሰጠ መፍትሄ የሚሻ ቁልፍ የቤት ስራ ነው። ለአማራ ህዝብ ህልወና መከበር እቆማለሁ የሚል ማንኛውም ፋኖ እና የፋኖን እንቅስቃሴ ከልቡ የሚደግፍ ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ከዚህ የሚቀድም ወይም የሚልቅ ወቅታዊ ስራ ሊኖርው አይገባም። በውጭ የሚገኙ ሚድያዎችም በቲፎዘነት ተቧድነው የጋራ አመራር እንዳይመጣ የሚያሰራጩትን መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ አቁመው ለሁሉም አማራ የሚበጀውን፣ ለማንም የማይወግነውን ማንንም የማንገስ አላማ የሌለውን አሰራር ሁሉም የፋኖ መሪዎች እንዲቀበሉ መጣር ይገባቸዋል።
ውድ ወገኖቼ የአማራን ህዝብ ትግል በተመለከተ በ14 ክፍል ከፋፍዬ የጻፍኩት የግል ምልከታዬ በዚህ አበቃ።