የዛሬውን የአቶ ስብሐትን ሁናቴ ሳሰላስል፣ ከፊቴ የተደቀኑብኝ በጭንቅላቴ ለብዙ ዓመታት ተሸንቅረው የኖሩት ሁለት ጉዳዮች ናቸው።አንዱ ወያኔዎች ልክ ሥልጣን እንደያዙ፣ መጨረሻቸውን የሚመለከት ሲሆን፣ ይኸውም “በዐየር እንደመጡ ልክ እንደነፋስ ተንነው፣ እንደጉም በንነው ይጠፋሉ” የሚል የባሕታውያን ትንግርት እንደሆነ ይነፍስ የነበረው ወሬ ነው።
ሁለተኛው የዛሬ ዐምስት ዓመት አካባቢ ይሆናል፣ በአማራ ክልል የጐንደር ሕዝብ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ይዞ የወጣው መፈክር ሲሆን፣ እሱም “ስብሐት ነጋ፣ ኢትዮጵያ አትፈርሰም። አንተና የማፊያ ሕወሓት [ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ] ቡድንህ ታሪክ የምትሆኑ መባቻ ላይ መሆናችሁን ዕወቁ” የሚል ነበር።
ዛሬ የተፈጸመው ይኸው ሐቅ ነው። እኔ ግን የሕወሓትና በአምሳሉ የፈበረከው ኢሕአዴግ [የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር] ውድቀታቸው እጅግ መጥፎና አይቀሬ መሆኑን በጥልቅ ባምንም፣ በሕይወቴ ዘመን ይኸ ይፈጸማል ብዬ መቼም አልተጠባብቅሁም። አቶ ስብሐት ነጋ ተራ የሕወሓት አባል አይደለም። ሕወሓት ማለት ስብሐት ነጋ ነው፤ ስብሐት ነጋ ደግሞ ሕወሓት ነው፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። አባባሌ ግልጽ መሰለኝ። ካልሆነ እንዳብራራው ይፈቀድልኝ።
አቶ ስብሐት ነጋ የሕወሓት መሥራች፣ የድርጅቱ ራእይ አፍላቂና አስፈጻሚ ብቻ ሳይሆን፣ ለዐሥር ዓመት ከ1971-1981 በሊቀመንበርነት መርቶታል። የሕይወቱ ስንክሳር የሚያሳየን በደቡብ ኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጣሪነትን ትቶ፣ ወደአድዋ ተዛውሮ የትምህርት ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ ሲሆን፣ ሹመቱን የተጠቀመው የወጣቱን አእምሮ በዕውቀት ለማነጽ ሳይሆን ለፀነሰው እኩይ ድርጅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችንና የአካባቢውን ወጣት ለመመልመል እንደነበር ነው። ስለዚህ በአዲሱ ሹመት ብዙም ሳይቈይ፣ የጥንቱ ወልደሥላሴ፣ ስብሐት በሚል አዲስ ስም ተጠምቆ ወደትግል ሜዳ ገባ። ሕወሓት ከተመሠረተበት ጀምሮ፣ ከአዲስ አበባ ኮብልሎ ወደትውልድ አካባቢው ተመልሶ ገብቶ፣ እንደጠላት በፈረጀበት አገሩ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስካወጀበት ጊዜ ድረስ፣ አቶ ስብሐት የድርጅቱ አባት ብቻ ሳይሆን ብቸኛው ፈላጭ ቈራጭም ነበር ማለት ይቻላል። የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ራሱ ከድሮው ወልደሥላሴ፣ ከኋላው ታጋዩ ስብሐት ጋር በጋብቻና በአምቻ የተሳሰሩ የቤተሰቦች ጥርቅም እንጂ ሌላ አልነበረም። ስለዚህ አቶ ስብሐት የሕወሓት የምሥረታውም ሆነ የራእዩ አባት ነው። “አቦይ ስብሐት” የሚለው የክብር ቃልም እሱ የድርጅቱ ቁልፍ ሰው እንደሆነ የሚያመልክት ትክክለኛ መጠርያው መሆኑ አይካድም።
አቶ ስብሐት ዋነኛ መለዮው አማራ ብሎ ለፈረጀው ብሔረሰብና ለኦርቶዶክስ እምነት ያደለበው ጥልቅና ጭፍን ጥላቻ ብቻ ሳይሆን አሁን አገሪቷ የተዋቀረችበት የጐሣ ሥርዐትም መሀንዲስ በመሆኑ ነው። እንደዚህ መረን የለቀቀ ጥላቻ ከየት መጣ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ረገድ ምንም በርግጠኝነት የሚባል ነገር የለም። ይሁንና ፍንጭ ሊሰጡን ከቻሉ የትምህርቱንና የቤተሰቡን ዳራ መፈተሽ ጠቃሚ መስሎ ይታያል። በትምህርት ጥርሱን የነቀለው አቡጊዳውን ባጠናቀቀው በሉተራውያን ገዛ ኬኒሻ ሲሆን፣ አጎቱም አባቱም ባንዳዎች ነበሩ የሚባል ወሬ እንዳለ ለአንባቢው ማውሳቱ ይረዳ ይሆናል። በተለይም አጎቱ በደቡብ ክንፍ ከኢጣሊያን ሲዋጋ በክፉኛ ቈስሎ የነበረውን የኢትዮጵያን ጀግናውን ዐርበኛ ራስ ደስታ ዳምጠን በተደበቁበት በጭካኔ ከገደለ በኋላ ራሳቸውን ረግጦ በመቆም ፎቶግራፍ በመነሣት ለጌታው ኢጣሊያን ግዳይ እንደጣለ እንደሚነገርም ልብ ማለት ይገባል።
“ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንደሚባል፣ አቶ ስብሐትንም የገጠመው የሱን ዐይነት ተግባር የፈጸሙት ሰዎች ዕጣ ፈንታ ስለሆነ አይገርምም። እሱም ግንባርቀደምት መሳዮቹ የሚታወቁት በሁለት ነገር ሲሆን፣ እነዚህም ዐምባገነንነትና ቅጥ ባጣ የጥላቻ ስብከት ሕዝብን ርስበርስ ማበላላትና ማራራቅ ናቸው። በዚህ መስክ ከተካኑት ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ መጨረሻቸው ያው መሆኑን ለማወቅ ወደኋላ ተመልሰን ሩቅ ሳንሄድ የቅርብ ጊዜ ተዋናዮቹን እንደሂትለር፣ ሙሶሊኒ፣ ፖልፖት፣ ሳዳም ሁሴንና ገዳፊ የመሳሰሉትን እንደአብነት መጥራት ይበቃል።
አቶ ስብሐት ለዚህ አሳፋሪ ውድቀቱ ከመዳረጉ በፊት “ትግራይ ውስጥ ትግራይን፣ ከትግራይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕወሓትን የሚተካ የፖለቲካ ኀይል የለም” ሲል በፈረንጆች አቈጣጠር በጥቅምት ለእንግሊዙ ቢቢሲ ጋር ባደረገው ቈይታ መግለጹ ይታወሳል። ነገሩ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራልና”፣ ለሱም አለሕወሓት ኢትዮጵያም ትግራይም እንደሚፈርሱ ግልጽ ነበር። ደስ የሚለው እንደግርፉ አቶ መለስ የሞት ጽዋ ሳይቀምስ ምን ያህል ቅዠታምና መተተኛ መሆኑን፣ ትግራይም ሆነች ኢትዮጵያ ሳይፈርሱ ይልቅስ በሱ ውድቀት ሲቦርቁ፣ ለማየት መታደሉ ነው።
የአቶ ስብሐት ውድቀት ፈሩን ለመከተል ለሚዳዱት ሁሉ ጥሩ ትምህርት ይሆናል ተብሎ ቢታመንም፣ ታሪክ ደጋግሞ የሚያሳየን ሐቅ ቢኖር ግን ልበ ደንዳኖች ይኸንን ለማስተዋል ሥነልቦናቸው ዕውር መሆኑንና ከቶውኑ አለመታደላቸውን ነው። ስለዚህም ዐደብ ገዝተው ከእኩይ ተግባራቸው ከመቈጠብ ይልቅ፣ በተረኝነት መንፈስ ተገፍተው ሲደግሙትና ውርደታቸውን ሲቀምሱ ይታያሉ። ይሁንና የነሱ ልግምተኝነት መቼም ቢሆን ታሪክንና ጊዜን ዐላፊነታቸውን ከመወጣት አያግዳቸውም።