የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በታዳጊዋ ሄቨን አሰቃቂ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን አሁንም በድጋሜ ይገልፃል::
ሐምሌ 25 / 2015 ዓ/ም በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ በ7 አመቷ ታዳጊ ህጻን ሄቨን ላይ በተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊትና ህልፈተ ህይወት ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በእጅጉ ማዘኑን ገልፆ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።
በህጻናት ላይ የሚፈጸምን ማንኛውም ጥቃት መከላከል በዋነኛነት የመንግስት ሃላፊነት ሲሆን በሌላ በኩል የሁሉም አካል ተመሳሳይ ድርሻ ያለው መሆኑን የገለፀው ከተማ አስተዳደሩ እንደዚህ አይነት አስነዋሪና አሳፋሪ ድርጊት በከተማችን በመፈፀሙ በእጅጉ ዛሬም በድጋሜ እንዳሳዘነው ገልጿል ።
የባሕር ዳር ከተማ ህዝብ ሰው ወዳድ፣ ሁሉን አክባሪ፣ ባህሉን፣ ወጉንና ታሪኩን ጠባቂ አስተዋይ ጨዋ ህዝብ ነው ። በዚህ እሴትና ባህል በተገነባ ማህበረሰብ ውስጥ የተፈፀመው ድርጊት በፍፁም ነውረኛና የከተማውን ህዝብ የማይገልፅ ሁሉም ሰው ሊያወግዘው የሚገባ ዘግናኝ ተግባር ነው ።
ሁሉም እንደሚያስታዉስዉ ወንጀሉ እንደተፈፀመ የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከሚመለታቸው ተቋማት በዋነኝነትም ከፖሊስ ፣ ከጤና ተቋም ፣ ከፍትህ እንዲሁም ከተበዳይ ወገኖች ጋር በመቀናጀት ጉዳዩ በህግ እንዲያዝ በማድረግ ልዩ ትኩረትና ክትትል በማድረግ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ተይዞ በ20/06/2016 ዓ.ም በከፍተኛ ፍርድ ቤት የ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበት ባህርዳር ማረሚያ ቤት እንዲገባ ተደርጓል።
በዚህ አጋጣሚ ከተማ አስተዳደሩ የፍርድ ቤቱን የዳኝነት ነፃነት የሚያከብር ቢሆንም ከተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊትና የማህበረሰቡን ሞራልና ክብር ዝቅ ያደረገ ወጀል በፈፀመው ወንጀለኛ ላይ የተሰጠው ፍርድ አስተማሪነት የሚያንሰው መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ በፅኑ ያምናል ።
ከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን በጥብቅ ለመከታተል ባለው ፅኑ አቋም ክልሉን ባጋጠመው ቀውስ ወንጀለኛው ከማረሚያ ቤት አምልጦ የወጣ መሆኑን እንዳወቀ በልዩ ሁኔታ የፀጥታ ሀይሉ ክትትል እንዲያደርግ አመራር ተሰጦ ወንጀለኛው ተይዞ ድጋሜ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገባ ተደርጓል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት ወንጀለኛው ይግባኝ የጠየቀ እንደሆነ እና ጉዳዩ ለጥቅምት 20/2017 ዓ.ም ፍ/ቤቱ ቀጠሮ የሰጠ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ያውቃል። የፍርድ ቤቱን ነጻነት በጠበቀ መልኩ ከህግ አኳያ የይግባኙን ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት የምንከታተለው እና ፍትህ እንዲረጋገጥ በፅናት የምንታገል እንደሆነ ለማረጋገፅ እንወዳለን።
ስለሆነም ከተማ አስተዳደሩ በልጃችን ህፃን ሄቨን ለደረሰው ግፍ ፍትህ ሲጠይቅ ፣ለጉዳዩ ለሰጠው ትኩረት እና እያደረገ ላለው ትግል ለመላው የህብረተሰብ ክፍል ምስጋና እያቀረብን በቀጣይም ለፍትህ መረጋገጥ ለምናደርገው ትግል ህብረተሰቡ ከጎናችን እንዳይለይ ጥሪያችን እያቀረብን በቀጣይም የህፃናት ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ስለሆነ በትብብር መስራት ይጠበቅብናል።
ነሐሴ 12/2016ዓ.ም
ባሕር ዳር .