ሃምሌ 21 ቀን 2016 ዓም(28-07-2024)
በዛሬው የሳምንቱ መዝጊያ እሁድ ቀን በአመስተርዳም ከተማ በዬሳምንቱ በሚደረገው የፍልስጤምን ሕዝብ ለመደገፍና የጽዮናውያኑን ጭፍጨፋ ለመቃወም በሚካሄደው ሰልፍ ላይ በመገኘት ግፍና በደልን ስቃወምና ሳወግዝ ውያለሁ።እንዲህ ባለው ዓለም ዓቀፍ ጉዳይ ላይ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ ባይሆንም በእለቱ ግን የሰልፈኞቹን ቁርጠኝነትና ዝግጅት ሳይ በልቤ ቅናት አሳደረብኝ።ከተለያዩ የአረብ አገሮች የመጡ ፣የኔዘርላንድና የሌላ አውሮፓ አገር ነዋሪዎች የተሳተፉበት በመሆኑ እለቱን ዓለም አቀፋዊ መልክና ይዘት አላብሶታል። የእኔም ትውልድ በዓለም አቀፋዊነት መርሆ በቅኝ ግዛት መዳፍ ስር የወደቁ ሕዝቦች ላደረጉት የነጻነትና የዴሞክራሲ ትግል ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚካድ አይደለም። የአሁኑን አያድርገውና ለአፍሪካ ወጣቶች ምሳሌና ምልክት ነበር።አሁን ግን በራሱ አገር ላይ በጎሰኞች መዳፍ ሲታሽና አገሩም ለመበታተን ስትንደረደር በአንድ ላይ ቆሞ ለመመከት አልቻለም፤ይባስ ብሎም በጎሰኞች ሰንሰለት ውስጥ ተተብትቦ በሰፈር ማንነት ተቧድኖ የጥፋቱ ተባባሪ ሆኗል።ጥቂት ቆራጦች እምቢ ብለው ሲነሱ ከመከተል ይልቅ አሳልፎ እዬሰጠ በታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እዬፈጸመ ነው።ከአገርና ከወገን ይልቅ የራሱ ጥቅም እያታለለው በክህደትና በፍርሃት ባሕር ውስጥ ሲዋኝ ይታያል።ነገ ለመኖሩ ዋስትና ሳይኖረው ሃብትና ንብረት በመሻማቱ ላይ ተዘፍቋል።እንኳንስ ተራው የሃይማኖት አባት የተባሉትም ከሃብት ውድድሩ ውስጥ ተዘፍቀው የፈጣሪን ቃል በሰይጣናዊ ምግባር ተርጉመውታል።በዚህ የቆሰለው ልቤን ይዤ ከሰልፉ ስገባ ይባስ ቁጭትና ብስጭት በፈታተነኝም የሰልፉ ስነሥርዓትና የሚያስተጋባው የጋራ ድምጽ የመንፈስ ቅናት አሳደረብኝ።
ወደ ሠልፉ የተቀላቀልኩት ግን ባዶ እጀን አልነበረም ትልቅ የድል መሣሪያ ታጥቄ እንጂ።ያም በቅኝ ግዛት ስር የሚማቅቁትን በተለይም ለጥቁር ሕዝብ የነጻነት ምልክት የሆነችውን በጎሰኞች የኮከብ ቀለም ያልተጨማለቀችውን ንጹህ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ታሪካዊ ሰንደቅዓላማዬን (ዓላማችንን)በመያዝ ነበር።ሜዳውን ካጥለቀለቀው የፍልስጤማውያን ባንዲራ ጎን በብቸኝነት ስትውለበለብ የዋለችው የያዝኳት ሰንደቃችን ነች፤የብዙ ሰዎችንም ትኩረት ስባለች።ሰላማዊ ሰልፉንም በትንሹም ቢሆን ዓለምቀፋዊ መልክ እንዲኖረው አድርጋለች።
ለፍልስጤማውያን በዚህ የመከራ ወቅት ከጎናቸው ለመቆም ያስገደደኝ በደልና ጭቆናን ከሚጠላ ትውልድና በነጻነት ከኖረ ሕዝብ የመጣሁ በመሆኔ ከዛም በላይ አሁን በመፈጸም ላይ ያለው ኢሰብአዊና የፋሽስቶች ድርጊት ለሚፈሰው የንጹሃን በተለይም የህጻናት የሴቶችና የአዛውንቶች ደም መፍሰስ የህሊና እረፍት ስለነሳኝና ሰብአዊ ስሜቴ ስላስገደደኝ ነው።አስር ወራት ባስቆጠረው በዚህ የጽዮናውያን ጭፍጨፋ ከ40 ሽህ በላይ ህይወት ጠፍቷል ከዚያም ውስጥ ከሃያ ሽህ የማያንሱት ህጻናት ናቸው።የመቀነስና የመቆሙም ጭላንጭል አይታይም።በዬእለቱ የሚታይ የተለመደ ትእይንት ሆኗል።ይህንን ግፍና በደል ለመቃወም የግድ ፍልስጤማዊ መሆን አይጠይቅም።እኔም ስቃወም የፍልስጥኤም ተወላጅ ሆኜም አይደለም።በአይሁድ እምነትና ተከታዮች ላይም ጥላቻ ኖሮኝ አይደለም።በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ሰንሰለት የሚታገዝ ወራሪና ጨፍጫፊ የሆነውን ጽዮናዊነትን በመቃወም እንጂ።ለሰው ልጆች መብትና እኩልነት የቆሙ ይሁዳውያንም መኖራቸው መዘንጋት የለበትም።
ይህ የጽዮናውያን መስፋፋትና ሽብር ትናንት የጀመረ ሳይሆን አስርታት ዓመታት ያስቆጠረ ነው።ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በዃላ በ1948 ዓመት እንግሊዞች ቦታውን ለቀው ሲወጡ ከያገሩ የተሰባሰቡ የአይሁድ እምነት ተከታይ የሆኑ በጽዮናዊነት የሚያምኑ ቦታውን እንዲቆጣጠሩና እስራኤል በሚል ስም አገር እንዲመሰርቱ በተደረገው ሴራ ምክንያት ነው።ከአምስት መቶ የማይበልጡ አይሁዳውያን በሚኖሩባት ፍልስጥኤም ውስጥ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ፍልስጥኤም ይኖር ነበር።ከእስራኤል ምስረታ በዃላ ግን ነባሩ ሕዝብ ከቦታውና ከቤቱ እዬተባረረ በመጤ አውሮፓውያን አገሩን ተቀምቶ ላለፉት 75 ዓመታት ብዙሃኑ በድንኳን በዬጎረቤት አገሩ ተሰዶ እንዲኖር ተገደደ፤የቀረውም ያም በዛብህ ተብሎ በቀረችው ቁራሽ መሬት ላይ እንዳይኖር በመሬትና በአዬር ጥይትና ቦምብ ይዘንብበት ጀመር።ታዲያ ይህንን አለመቃወም ይገባል?በራስ ላይ ቢደርስስ ያስችላል?ለዚያም ነው በአንዱ ቦታ ላይ የተፈፀመ ኢፍትሃዊ ድርጊት በሁሉም ላይ የተፈጸመ ኢፍትሃዊነት ነው የሚባለው።Injustice somewhere is injustice everywhere! ይህ ችግር በትክክልና በአስቼኳይ ካልተፈታ ለዓለም ጦርነት የሚያበቃ መዘዝ ይሆናል።የጦር መሣሪያ ግንባታውም ለዚያ መሆኑን መረዳትና በጊዜው መቃወም የሁሉም አገር ዜጋ የዓለም ህብረተሰብ የሆነው ሁሉ በአንድ ላይ ቆሞ መታገል ይኖርበታል።
የእስራኢልን አገራዊ ምስረታና መስፋፋት ሂደትና ብሎም በመሪነት ቦታ የተቀመጡት ሰዎች እነማን እንደሆኑና ከዬት እንደፈለሱ የሚከተለውን ማስረጃ ይመልከቱ።ጊዜውም የተገለጸው በአውሮፓውያን አቆጣጠር መሆኑን ልብ ይበሉ።
ምስሎቹ ከያገሩ ተለቃቅመው በእስራኤል ጦር ሃይል ውስጥ በመግደልና በመሞት ላይ የተሰማሩትንና ከያገሩ ተለቃቅመው የመሪነት ቦታ የያዙትን የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ልጆችም በችግርና ፈላሻ በሚል ስም ደርግ ሸጧቸው ካገራቸው በመውጣት በዚህ ወንጀል ላይ ተሰማርተዋል።የነጻነትና የፍትህ አርማ የሆነችው ሰንደቅ ዓላማችንም ለገዳዮቹ ስብስብ መታወቂያ ሆና ቀርባለች። በተሳተፍኩበት በትናንትናው ሰልፍ ላይ ግን በትክክለኛው ቦታ ስትውለበለብ ውላለች።
1 ዳቪድ ግሩን የሚታወቅበት ስሙ ዳቪድ ቤንጎሪዎን፣የተወለደበት ሃገር ፖላንድ ከ1948-1953 ከ1955-1963 ዓም የመጀመሪያው ጠ/ሚኒስትር የነበረ ሲሆን የአይሁዳውያን ድርጅት መስርቶ 500 ፍልስጤማውያንን በመግደል 1948 ዓም ሃገር ምሥረታ የተሻገረ ፣ አገራዊ መንግሥቱም እስራኤል ተብሎ እንደሚጠራ ያወጀ።በዚህ ጉዞው ከእንግሊዞች ካገኘው ድጋፍ ጋር ተደምሮ ከ750ሽህ በላይ የሚሆኑት ቤታቸውንና ንብረታቸውን ተቀምተው ሲፈናቀሉ ከ10 ሽህ በላይ ፍልስጤማውያን ተጨፍጭፈዋል። 60% የሚሆነውን መሬት በመንጠቅ ከያገሩ የፈለሱ ይሁዲዎች እንዲሰፍሩበት አድርጓል።
2 ሞሸ ሸርቶክ የትውልድ ሃገር ኡክሬን(ሩስያ) ከ1954-1955 ለአንድ ዓመት ብቻ ጠ/ምኒስትር የነበረ ሲሆን በዚህ አጭር የሥልጣን ዘመኑ የጽዮናውያን አስተሳሰብን የነደፈና የወለደ አባት ተደርጎ የሚቆጠር ነው።የተባረሩት ፍልስጤማውያን ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ ያገደ፤እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ የሆነ መመሪያ ያወጣ።
3 ሌቪ ሽኮልኒክ-ሌቪ ኢስኮል በመባል የሚታወቀው የኡክሬኑ ተወላጅ ከ1963-1969 ሦስተኛው ጠ/ ምኒስትር የነበረ፤ማጋናህ የተባለ የጨቃኝ ጽዮናውያን ድርጅት አቋቁሞ ለብዙ ፍልስጤማውያን መጨፍጨፍ ተጠያቂና ለ1948 ዓም አገር ምሥረታ መንገድ ከቀደዱት አንዱ።
4 ጎልዳ ማቦቪች( ጎልዳ ሜዬር በመባል የምትታወቀው) የኡክሬኗ ተወላጅ ከ1959-1974 ድረስ የመጀመሪያዋ ሴት ጠ/ምኒስትር የነበረች፤በሥልጣን ዘመኗ የአይሁዶችን ሰፈራ ያስፋፋች፤የእርሻ ሰብሎችን በማቃጠልና በመበከልየመቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን ያቋቋመች።
5 ማናኬም ቤጊን የትውልድ አገር ቤላሩስ ከ1977-1983 ድረስ 6ኛ ጠ/ ሚኒስትር የነበረ፤ከ1948 ዓም በፊት ኢርጉን የተባለ የጽዮናውያን አሸባሪ ድርጅት የመሰረተና የመራ፣ብዙ ፍልስጤማውያንን የጨፈጨፈ፣በንጉሥ ዳዊት ስም ይጠራ የነበረውን ዝነኛ ሆቴል በአውሮፕላን የደበደበ፣የመስፋፋቱን ሥራ በምዕራቡ የባህር ዳርቻና በጋዛ ያከናወነ።
6 ኢቻክ ጃዜሚኒኪ ይዛክ ሻሚር በመባል የሚታወቀው የቤላሩስ ተወላጅ ከ1983 -1984 ከዚያም ከ1986-1992 ዓም ድረስ የአገሪቱ ሰባተኛ ጠ/ምኒስትር ሆኖ የመጀመሪያውን የፍልስጤማውያንን ተቃውሞ 80 ሽህ የአይሁድ ወታደሮችን አሰማርቶ ያጨናገፈ፤1087 ሰዎች ተጨፍጭፈው ከዚያም ውስጥ 240 ሕጻናት ናቸው፣120ሽህ ቁስለኛና ከ600 ሽህ በላይ በእስር ቤት እንዲማቅቁ ያደረገ ጨካኝ
7 ሺሞን ፕርስኪ የሚታወቅበት ስሙ ሲሞን ፐሬዝ የትውልድ ሃገር ቤላሩስ ከ1984-1986፣ከ1995-1996 ስምንተኛው ጠ/ ምኒስትርና “ ሰፈራ በሁሉም ቦታ”በሚለው መፈክር የሚታወቅ መናጢ
8 ኢሁድ ብሮግ(ኢሁድ ባራክ)የትውልድ አገር ፍልስጥኤም ከ1999-2001 አስረኛው ጠ/ምኒስትር የነበረ፣ያስር አራፋትን ለመቋቋም ያልቻለ፣በአሜሪካ በተካሄደው ካምፕ ዴቪድ ውይይት ላይ 9 በ1 እጅ (9 ለ1 ወይም 9% ለ1% የሆነ የመሬት ባለቤትነት ሃሳብ አቅርቦ ያልተሳካለት ብልጣብልx
9 አሪክ ሸይርማን( አሪያል ሻሮን) የትውልድ አገር ፍልስጥኤም ከ2001-2006 አስራአንደኛው ጠ/ምኒስትር የነበረ በጨካኝነቱ የመለያ ቅጽል ስሙ ቡልዶዘር እና የሰፈራ አባት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የአይሁዳውያን መስፈሪያ መንደሮችን የቆረቆረ፣ፍልስጤማውያንን ኢያባረረ መኖሪያ ያሳጣ፣የኦስሎን smeምነት ጥሶ 700 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የብረትና የግምብ የአፓርታይድ አጥር የገነባ።
10 ኢሁድ አልመርት የትውልድ አገር ፍልስጥኤም፤2006-2009 አስራሁለተኛው ጠ/ምኒስትር፣ በ2007 ዓም በጋዛ ላይ ማእቀብ የጣለ፣የሰውም ሆነ የቁስ እንቅስቃሴ ያገደ፣በዓለም ላይ ትልቁን የሕዝብ እስር ቤት የከፈተ ለአሁኑ የሰብአዊ ቀውስ መንደርደሪያ የድርሻውን ያበረከተ ወንጀለኛ
11 ቤንዝዮን ሚሌኮዊስኪ(ቤንጃሚን ነታኘሁ)የትውልድ አገር ፍልስጥኤም፤ከ2009-እስከ አሁን ድረስ ሲወጣ ሲወርድ የቆዬ ፣ተደጋጋሚ የውድመትና ጭፍጨፋ ዘመቻ ፣የማፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ ያካሄደና በማካሄድ ላይ የሚገኝ የዘመናችን ሂትለር
ባለፉት አስር ወራት በተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ ከ40 ሽህ በላይ ፍልስጤማውያን ከነዚያም ውስጥ ከ16 ሽህ በላይ ህጻናት በገፍ ተጨፍጭፈዋል፤ሆስፒታሎች፣ትምህርት ቤቶችና ልዩልዩ መሠረታዊ ተቋማት ወድመዋል፤ ከተማዎች ፈራርሰዋል።ሕዝብ የሚልስ የሚቀምሰው አጥቶ ይሰቃያል።ለወንጀለኛ ነጋዴዎች ተጋልጧል፤ውሃዳር የሚኖረው ሕዝብ ኩባያ የሚጠጣ ውሃ ተነፍጎታል።ሞትና ለቅሶ የተለመደ ሆኗል።ይህንን ወንጀል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲታይ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ክስና አቤቱታ አቅርቦ ነበር።ሆኖም ግን በጡኝቼኞቹ የምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካኖቹ በኩል ተድበስብሶ እንዲቀር ማድረግ ብቻም ሳይሆን ለጽዮናውያኑ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ብሎም የፖለቲካ ድጋፍ እያዥጎደጎዱ ፍትሕን ዋጋ ቢስ አድርገውታል።የአረቦቹም መንግሥታት እንዲሁ እቂጡ ላይ ክንታሮት ያለው እንደልቡ አይቁነጠነጥም እንዲሉ ድምጻቸውን አጥፍተው ተቀምጠዋል፤አልፎ አልፎ ደረቅ ምግብ ከማቀበል ያለፈ ተቃውሞ ለማሳዬት አልደፈሩም።የፍልስጤማውያን ጭፍጨፋና የሰቆቃ ኑሩ ተባብሶ ቀጥሏል።ይህንን የሚያይ የሰው ልጅ ከቶም ቢሆን በዝምታ መቀመጥ የለበትም፣ሁኔታው ከቀጠለ አስፈሪው የሶስተኛው ዓለም ጦርነት ማዋለጃው ላለመሆኑ ዋስትና የለም፤ ዝግጅቱም ሁሉ ወደዚያው የሚያመራ ይመስላል።
እንደ አንዱ የዓለም ዜጋ፣እንደ ሰው ልጅ ድምጼን ለማሰማት ከወሰንኩኝ ሰንበትበት ብሏል፤በትናንትናውም እለት በ28-07-2024 በአምስተርዳም ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳትፌአለሁ፤ አሁንም በሚከተለው “ ድንቄም ዴሞክራሲ” በሚለው የግጥም ስንኝ እመሰክራለሁ።
ድንቄም ዴሞክራሲ
ድንቄም ዴሞክራሲ ለመብት መቆርቆር፣
ሕዝብ በአንድነት ተከባብሮ እንዳይኖር ፣
ከፋፍሎ ማጫረስ በሃይማኖት በዘር፣
ለመውረር ለመዝረፍ የሌላውን አገር፣
ይህ ነው ዴሞክራሲ የነሱ መፈክር።
አገሩ ተወሮ ሲቀማ መሬቱ፣
ከኖረበት ምድር ተባሮ ከቤቱ፣
አገር አልባ ሆኖ ብዙዎች ሲሞቱ፣
ተሰዶ ከኖረ ሰባአምስት ዓመቱ።
የምዕራቡ ዓለም አንድ ላይ አድሞ፣
እስራኤል የሚባል ማንነት ሰይሞ፣
ነጩንና ጥቁሩን ሰብስቦ ለቃቅሞ፣
በጉልበት ይኖራል ነባሩን አውድሞ።
ሕዝብ ሰላም አጥቶ ሲቸገር ሲታመስ፣
ከተማ ሲወድም መኖሪያ ቤት ሲፈርስ፣
የሰው ልጅ አስከሬን ባካፋ ሲታፈስ
ሕጻን ሽማግሌው የደም እምባ ሲያለቅስ፣
አካሉ ፈራርሶ ደሙ ሲንቆረቆር፣
ስጋው ተተልትሎ አጥንቱ ሲሰበር፣
በጅምላ ተገሎ በጅምላ ሲቀበር፣
እንዳልባሌ ዕቃ ምናምንቴ ነገር፣
ለምን አልቃወም ለምን አልናገር፣
የደም ገንዳ ሲሆን የእዬሱስ ክርስቶስ የነማርያም አገር።
በሰቀሉት ሰዎች ዳግመኛ ሲሸበር።
ለዓለማችን ሰላምና ለፍትህ መስፈን አንድላይ እንቁም!!
አገሬ አዲስ