አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከቀድሞ የሰማያዊ ፕርቲ መሪ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር፣ በዋሺንገትን ዲሲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ከሆኑት፣ ሚስተር ማሲንጋ ጋር ውይይቶች አድርገዋል፡፡ በጋራ የተነሱትም ፎቶ ይፋ ሆኗል፡፡
አቶ ገዱ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩ ናቸው፡፡ የርሳቸው በዚህ መልኩ ወደፊት መምጣት እጅግ በጣም ትልቅ ክስተት ነው፡፡ በግሌ በአዎንታዊነት ነው የምቀብለው፡፡ ለአገዛዙም ትልቅ የዲፕሎማሲ ሽንፈት ነው፡፡
ማሲንጋ ከአቶ ገዱ ጋር በዚህ መልኩ ፎቶ ተነስተውም መልቀቃቸው፣ በራሱ ትልቅ መልእክቶች አሉት፡፡ አንደኛው የብልጽግና መንግስት አገር ማስተዳደር እንዳልቻለና አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ከድምዳሜ መድረሱን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉንም ፋኖዎችን የሚወክል የፖለቲካ መሪ ስለሌለ፣ አቶ ገዱና ምን አልባትም ኢንጂነር ይልቃል፣ በፋኖዎች መካከል እንደ መካከለኛ እንዲያገለግሏቸው ሳያስቡም አልቀረም፡፡
አቶ ገዱ፣ በዚህ መንገድ በይፋ ወደ ትግሉ መምጣታቸው የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ለአቶ ገዱ ያለኝ አክብሮት እንደተጠበቀም፣ በርሳቸው ዙሪያ አንድ በትልቁ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ግን አለ፡፡ እኔም ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ፡፡
አቶ ገዱ ለረጅም ጊዜ ብአዴን የነበሩ ሰው ናቸው:: ባልሳሳት አሁንም አስተሳሰባቸው ወያኔና ኦነግ ጠፍጥፈው በሰሩት በአማራ ክልል ማእቀፍ ውስጥ ያሉ ነው የሚመስለኝ:: ይህንን እንዲሁ አይደለም የምለው፡
1ኛ እርስቸው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የነበሩ ጊዜ ከአማራ ክልል ውጭ ስላለው የአማራም ሆነ አማራ እየተባለ ግፍና ሰቆቃ ስለደረሰበት ማህበረሰብ ይህ ነው የሚባል ያደረጉት ነገር የለም፡፡
2ኛ ባለፍው ጊዜ በአማራ ክልል የተጀመረውን ጦርነት በፓርላማ በይፋ መቃወምቸው በኔም ሆነ በብዙ ህዝብ ዘንድ ትልቅ አድንቆትን ያተረፈላቸው ቢሆንም፣ ያኔ በተናገሩት ንግግር፣ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርበው፣ የሽግግር መንግስቱ ያሉት ግን፣ የፌዴራልን ሳይሆን የአማራ ክልል መንግስት ነበር፡፡ ያ አነጋገራቸው፣ ባህር ዳር የመስተዳደር ለውጥ እስከመጣ ድረስ አራት ኪሎ እነ አብይ አህመድ ይቀጥሉ የሚለውን እንደመቀበል ተድርጎ የሚቆጠር ነው፡፡
እነ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ ብዙ ጊዜ የአማራ ክልል መንግስት መስተዳደሮች ተቀያይረዋል፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተነስተው፣ በተጠባባቂ ር እስ መስተዳድርነት አቶ ላቀ አያሌው፣ አቶ ላቀ አያሌው ተቀይረው፣ ዶር አምባቸው መኮንን፣ የዶር አምባቸው መኮንን ህልፈት ተከትሎ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተነስተው አቶ አገኘው ተሻገር፣ አቶ አገኘው ተሻገር ተነስተው ዶር/ ይልቃል ከፍያለ፣ ዶር ይልቃል ከፍያለ፣ ፋኖ ሲያባርራቸው አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርእስ መስተድደር ሆነዋል፡፡ በስድስት አመት፣ በኦሮሞ ክልል አንዱ ሺመለስ አብዲሳ ተቀምጦ፣ በአማራ ክልል ሰባት ርእስ መስተዳደሮች ተቀያይረዋል፡፡
አሁንም በአማራ ክልል የሽግግር መንግስት ተብሎ ሌላ ስምንተኛ ርእስ መስተዳደር ለመሾም ካልሆነ በቀር፣ የፌዴራል መንግስቱ በኦነጋዊምና ዘረኞች ስር እስካለ ድረስ የህዝቡ ስቃይና መከራ አያቆምም፡፡
ሌላው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከአብይ አህመድ ጋር እንጂ ከጨፍላቂ የኦሮሙማ ፖለቲካ ሓይሎች ጋር ችግር ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ በአስተሳሰቡ ሙሉ ለሙሉ ከአብይ አህመድ በምንም ከማይሻሉ ከነ ለማ መገርሳ ጋር አብረው ስሩ ቢባሉ ፍቃደኛ የሚሆኑ ነው የሚመስለኝ፡፡
ከስድስት አመታት በፊት ለውጥ የተባለው እንዲመጣ የአማራ ወጣት የተጫወተው ሚና የማይናቅ ብቻ ሳይሆን የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ነው፡፡ እነ አቶ ገዱ ህዝብን አሰልፈው፣ ህወሃት ላይ ባይነሱ ኖሮ፣ እነ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን አይመጡም ነበር፡፡ በነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትከሻ ላይ ነው እነ አብይ አህመድ ስልጣን የጨበጡት፡፡
አዎን እነ አቶ ገዱ እንደ አብዝኞቻችን፣ እነ አብይ አህመድና ለማ መገርሳ፣ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ፣ መደመር፣ ፍቅር፣ አንድነት .” ሲሉ ተታለው፣ አምነዋቸው፣ ኦህዴዶች አራት ኪሎ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ በዚያ አልወቅሳቸውም፡፡ ብዙዎቻችን ተታለን ነበርና፡፡
ሆኖም እነ አብይ አህመድና እነ ለማ መገርሳ ሲሉት እንደነበረ እንዳልሆነ እነ አቶ ገዱ አስቀድመው ነበር ያወቁት፡፡ ግን ከጅምሩ ቀይ መስመር አስምረው፣ ነገሮችን ማስተካከል ሲችሉ አላስተካከሉም፡፡ ለዚህም ሃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡ እነርሱ የኦሮሞ ኦነጋዊ ፖለቲከኞችን አምነው፣ ትልቅ ህዝብ ከጀርባቸው እያለ፣ በኦሮሞ ፖለቲከኞች አውትስማርት (outsmart) ሆነው ፣ ህዝቡ ለትልቅ ጥፋት ዳርገውታል፡፡ ለዚህም ይቅርታ የመጠየቅ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡
እስቲ ጥያቄዎችን ላቅርብ፡
አሁንም አቶ ገዱ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን የመለማመጥ፣ የማባባል ዝንባሌ ነው ያላቸው ?
ይህ ኦነግና ህወሃት የሸነሸኑት ኦሮሚያ የሚባለው ዘረኛና የምድር ሲኦል የሆነው ክልል መፍረስ አለበት ብለው ያምናሉ ወይ ?
ነው ወይስ አሁንም በናዝሬት፣ በአሰላ፣ በሸኖ፣ በዱከም፣ በወሊሶ፣ በሞጆ፣ በኪረሙ፣ በአብ ደንጎሮ፣ በፍቼ በመሳሰሉት ቦታዎች የሚኖረው አማራ ኦሮሚያ በሚባለው ለአስተዳደር አመች ባልሆነው ክልል ውስጥ እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት ?
አሁንም የአማራው ማህበረሰብ አቅም ቢስ የሆነ ይመስል፣ ኦህዴዶችን፣ ኦነጎችና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ማስቀየም የለብንም የሚል ደካማና ሽምድምድ አመለካከት ነውን ያላቸው ?
አሁን ያለው ዘረኛና ከፋፋይና ጸረ ኢትዮጵያዊ ስርዓት ስር ነቀል በሆነ መልኩ መቀየር አለበት፡፡ የዘር ክልል መፍረስ አለበት፡፡ አማራው የፈለገው ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተስማሙበት፣ ሁሉን አሸናፊ የሚያድርግ ሕግ መንግስትና አወቃቀር መኖር አለበት፡፡ ያለፈውን ኮተት ስርዓት ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ፣ አብይ አህመድንና ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ቀይሮ ለመቀጠል መሞከር ፣ የህዝቡን ትግል ማምከን ነው፡፡
ከአክብሮት ጋር ለአቶ ገዱ ፣ አመለካከታቸው ለውጭ አገር ዜጎች፣ ለአሜሪካኖች ለመናገር ከደፈሩ፣ ለህዝብ ወጥተው ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲመልሱ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ብዙ ሊሰሩ፣ ብዙ ሊያበረከቱ የሚችሉ ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ ሆኖም ነገሮችን ማጥራት አለባቸው፡፡ አቋማቸውን መስመሮቻቸውን ማጥራት አለባቸው፡፡ የነ አብይ አህመድ ጉድና ሴራ ማጋለጥ አለባቸው፡፡ መሽሞንሞኑና ከመጋረጃ ጀነርባ መቀመጡን ትተው፣ ከአገዛኡ ጋር ታንጎ ለሚደንሱ ህሊና ቢስ ብአዴኖች፣ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት በይፋ ጥሪ ማቅረብ መጀመር አለባቸው፡፡ በአማራ ክልል ሚሊሺያ፣ የአድማ ብተና ቡድን የሚባሉ፣ እነርሱ አራት ኪሎ እንዳይታዘዙ፣ ፋኖን እንዲቀላቀሉ መልእክት በይፋ ቢያስተላልፉ ብዙዎች ከሞት ሊያድኑ ይችላሉ፡፡
ተስፋ አለኝ፣ አቶ ገዱ ማጥራት ያለባቸው አጥረው፣ አመለካከታቸው ከህዝብ አመለካከት ግር ከሆነ፣ ምን አልባት ከፋኖዎች የፖለቲካ አመራር መካከል አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡