ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሰኔ 11፣ 2016(ሰኔ 18፣ 2024)
የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስተር ተብዬው በሲንጋፖር መንግስት በተደረገለት ግብዣ መሰረት ከጠዘኝ በላይ የሚሆኑ የካቢኔት ሚኒስተሮችንና ሌሎችንም ልዑካንን በማስከተል እ.አ.አ ከሰኔ 4-6 2024 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በሲንጋፖር ከተማ(City State) ቆይታ በማድረግ አንዳንድ ቦታዎችንም የመጎብኘት ዕድል አጋጥሟቸዋል። ጠ/ሚኒስተሩም ሆነ ተከትለውት የሄዱት ልዑካኖች የሲንጋፖር ከተማ ማሸብረቅና የኢኮኖሚ ዕድገቷ ሳያስገርማቸው የቀረ አይመስልም። በተለይም የጠ/ሚኒስተሩ ቃል አቀባይ የሆነችው ካናዳዊቱ ቢሌኒ ስዩም ሲንጋፖር እንደዚህ ካደገችና ካሸበረቀች እኛ ኢትዮጵያውያኖችንስ ምን ቢነካን ነው እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያልቻልነው? በማለትና በመገረም በአገሯ ምድርና እየኖረችበት ያለውን ሁኔታና የመንግስቷን ፖሊሲ የመገንዘብ ችግር ያለባት እስከሚያመስላት ስትናዘዝ ተሰምታለች።
በመጀመሪያ ደረጃ ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ከመግባታችን በፊት ለሲንጋፖር የኢኮኖሚ ዕድገትና የህዝቡ የኑሮ መሻሻል ዋና ምክንያት ወደ ሆኑ ጉዳዮች ጋ እንምጣ። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲንጋፖር እጅግ ወደ ኋላ የቀረች አገር ነበረች። የህዝቧም በዓመት የነፍስ ወከፍ ድርሻ ወደ $320 የሚደርስ ነበር።፤ በአሁኑ ወቅት ግን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ በአሜሪካን ዶላር ሲተመን & 60,000 የአሜሪካን ዶላር ነው። ታዲያ ይህ ዐይነቱ ዕድገት በስድሳ ዓመት ውስጥ ወይም በሁለት ያህል ትውልድ በሚያስቆጥር ጊዜ ውስጥ በዚህ ዐይነት ፍጥነት እንዴት ሊያድግ ቻለ? የሚለውን እንመልከት።
ሲንጋፖር ከእንግሊዝ ከቅኝ-.ግዛት አስተዳደር ከተላቀቀች በኋላ ከማሌሺያ ጋር በአንድ አገዛዝ ጥላ ስር ለመተዳደር ያደረጉት ሙከራ የቻይና ዘር ባላቸው ሲንጋፖሮችና የቻይና ዘር በሌላቸው ማሌሺያ ጎሳዎች መሀከል በየጊዜው ግጭት ይፈጠር ስለነበር ለአስተዳደርም ሆነ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝ ሁኔታ አልነበረም። በተለይም የማሌሺያው ጎሳዎች የቻይና ዘር ባላቸው ሲንጋፖሮች እንዋጣለን ብለው በመፍራትና በዚህም ምክንያት የተነሳ በየጊዜው ከፍተኛ ግጭት ይፈጠር ስለነበር ሲንጋፖር ያላት ምርጫ ከማሌሺያ መላቀቅና የራሷን አስተዳደር መመስረት ነበረባት። ይሁንና ግን ሲንጋፖር ሙሉ በሙሉ ነፃነቷን ስትቀዳጅ ህዝቧ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይኖር ስለነበር ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚያዊ የጥገና ለውጥና የኢኮኖሚ ዕድገት ካልተደገፈ ነፃነት ሊሆን እንዳማይችል በሚገባ የተገነዘቡት መሪዎች የግዴታ ሰፊውን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቀውን የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲና የከተማ ግንባታ ዕርምጃ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተገደዱት። ለዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለህዝቡም የኑር መሻሻል ደግሞ የግዴታ የመንግስቱ መኪና በሰለጠኑና የዕድገት አራማጅ በሆኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቅ ነበረበት። የመንግስቱ መኪና አወቃቀር የጠበቀ በመሆን፣ ሲንጋፖርም ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝ ሁኔታ የሚፈጠርባትና ከሙስናም የፀዳች ከተማ እንድትሆን መንግስት አስፈላጊውን እርምጃዎችን መውሰድ ተገደደ። የመንግስትም ሰራተኞች የግዴታ ከሙስና የፀዳ አሰራር መስራት አለባቸው። ማንኛውም ዜጋ በዕፅ ንግድ ሲሰማራ ቢገኝና በሙስና ተጠርጥሮ ማስረጃ ከተገኘበት በሞት ቅጣት እንደሚቀጣ በመታወጅ ለኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ የሚሆን ሁኔታ ተፈጠረ። በተለይም የመንግስታዊ መዋቅሩ ከሙስና አሰራር የፀዳ በመሆኑና በከተማው ውስጥም ማንኛውም ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የሚሆን ነገር፣ ለምሳሌ እንደ ዕፅ የመሳሰሉትን በጥብቅ በመከልከሉና የተሟላ ሰላምም ለማስፈን በመቻሉ የመጀመሪያው የዕድገት መሰረት ተጣለ። አገራዊ ስሜት የሌላቸውና ቡዳናዊ ስሜትን የሚያስፋፉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ክትትል ይደረግባቸው ስለነበር በበሊ ኩዋን ዬው የሚመራው አስተዳደር ቆራጥ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ለውጭ ኢንቪስተሮች አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። የመንግስቱም ዋና መመሪያ ሲንጋፖርን ከቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች ማፅዳትና ህዝቡንም ከድህነት ማውጣት ስለነበረበት ለዚህ የሚያመች የኢንዱስትሪ መሰረት አልነበረም። የታሪክ ግዴታ ሆኖ ለብዙ መቶ ዓመታት የሲንጋፖር ህዝብ በአሳ ማጥመድ ላይ በመሰማራት ኑሮውን በዚህ ላይ የመሰረተ ስለነበር ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚሆን ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች አልነበሩትም። ሰለሆነም ለአዲሱ መንግስት ወይም አገዛዝ የነበረው አማራጭ ለውጭ ኢንቬስተሮች አመቺ ሁኔታን በመፍጠር፣ ቀስ በቀስ ቴክኖሎጂዎን በመቅዳትና በማሻሻል ራስን መቻል ነበር። ሲንጋፖር ነፃነቷና ከተቀዳጀችበት እ.አ.አ እስከ 1972 ዓ.ም ድረስ አብዛኛው የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች በጃፓንና በአሜሪካን ኩባንያዎች የተያዙ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስተር ሊ መንግስት በፈጠረው አመቺ የመዋዕለ ነዋይ እንቅስቃሴና የንግድ ልውውጥ የተነሳና፣ በዚህ ላይ ደግሞ ዕቃዎችን እዚያው እያመረቱ ለአካባቢው አገሮችና ለዓለም ገበያ አመቺ የሚሆን ወደብ ሲንጋፖር ስላላት የውጭ ኢንቬስተሮች ኢንቬስት ከማድረግ የተቆጠቡ አልነበሩም። ስለሆነም በውጭ ኢንቬስተሮች ተሳትፎና በመንግስቱ በተፈጠረው አመቺ ሁኔታየተነሳ መታየት የጀመረው የኢኮኖሚ ዕድገት ከ1965 እስከ 1972 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ እስከ አስር በመቶ የሚጠጋ ዕድገት ያሳይ ነበር።
ከውጭ የሚፈሰውም ገንዘብ ቀስ በቀስ እየትረፈረፈ በመምጣቱና የመንግስቱ የቀረጥ ገቢም ለማደግ በመቻሉ የሊ መንግስት የተከተለው ሌላው ፖሊሲ ህዝቡን በማስተማር በዕወቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት ነው። በተጨማሪም ከተማውን ከቆሻሻ ነገሮች በማጽዳት ለንግድ እንቅስቃሴና ለጠራ ስራ አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነበረበት። ከዚህም በላይ የመመላለሻ መንገዶችን በተቀላጠፈ መልክ በመስራት የውስጡን ገበያ ማስፋፋትና ቀስ በቀስ ደግሞ ከውጭ ካፒታል ተፅዕኖ መላቀቅ ሌላው መሰረታዊ ስትራቴጂ ነበር። ስለሆነም የሲንጋፖር መንግስት የሰለጠነ አሰራር በመከተሉና ብሄራዊ የሆነ የአገር ወዳድነት ስሜትን በማስቀደምና ለዚኸኛው ወይም ለዚያኛው ጎሳ ሳያደላና ህዝባዊ ቅራኔም ሳይፈጥር ኢኮኖሚውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለገንባት ችሏል ማለት ይቻላል። የሲንጋፖር ከተማም በዓለም ውስጥ ካሉ ከተማዎች ውስጥ በጣም የፀዳችና ማንኛውም ግለሰብ ቆሻሻ መንገድ ላይ የሚጥል ከሆነ ይቀጣል። በተጨማሪም የመመላለሻ ትራስንፖርቴሽኖች እንደ ሜትሮና ትራም የመሳሰሉት ውስጥ አንድም ሰው ማስቲካ ሲለጥፍ ቢገኘና ቆሻሻም ቢጥል በከፍተኛ ቅጣት የሚቀጣባት ከተማ ነች። በዚህ ዐይነቱ ዲስፕሊን የተሞላበት አሰራር የመንግስት ሰራተኞችም ሆነ ህዝቡም በንፁህ አካባቢ መኖር የቱን ያህል ጠቃሚና ለፈጠራም እንደሚያመች ለመማር ችለዋል ማለት ይቻላል። ሲንጋፖርም በአሁኑ ወቅት እንደቬትናም በመሳሰሉት በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የመዋዕለ-ነዋይ ተሳትፎ ያላት አገር ለመሆን በቅታለች። በሌላ አነጋገር ከሰለሳና ከአርባ ዓመታት በፊት ራሷ ኢንቬስተሮች መጥተው አግሯ ውስጥ ኢንቬስት እንዲያድርጉ አመቺ ሁኔታን ትፈጥር የነበረችው አገር በአሁኑ ወቅት እነቬትናም በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ኢንቬስት በማድረግ ተቀዳሚውን ቦታ ለመያይዝ የቻለች አገር ነች።
ጠቅላይ ሚኒስተሩን ተከትለው የሄዱት ልዑካን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከሲንጋፖር ምን ትምህርት ቀምሰው እንደመጡ ለህዝብ እንዲያስረዱ በቴሊቬዝን ተጋብዘው የሆነውን ያልሆነውን ነገር ሲዘላብዱ ነው የሚከታተለው ህዝብ ሊያዳምጣቸው የቻለው። የዘጠኝ ልዑካኑ በቴሌቪዥን መጋበዝና ንግግራቸውን እየተከታተለ በጥሩ መልክ አቀነባብሮ ያቀረበው እንደሚነግረንና ትክክልም ነው፣ ልዑካኑም አንዳችም ነገር እንዳልተማሩ ነው ለመረዳት የቻልነው። የተጋበዙበት አርዕስትም ከሲንጋፖር ምን ተምራችሁ ነው የመጣችሁት? የሚል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ሲሆን፣ ክሲንጋፖር የተማርነው ነገር ቢኖር ሲንጋፖር በኢኮኖሚ ማደግ የቻለችው መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሆነ ነው ሲል፣ የትምህርት ሚኒስተር የሆነው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ደግሞ የለገሰ ቱሉን አባባል በመቃወም፣ ሲንጋፖር ለማደግ የቻለችው መሬት የግል ሀብት በመሆኑ ነው ይላል። ሁለቱም የትኛውን ዶኩሜንትና የስታትስቲክስ አሃዞች በመንተራስ የተለያየ ነገር ለመናገር እንደቻሉ የጋበዛቸው ጋዜጠኛ በፍጽም አላፋጠጣቸውም። ሌላው ልዑካንና ተጋባዥ ደግሞ ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ሲሆን፣ ሲንጋፖር የዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለችው ጭካኔ ስለኖረ ነው፤ ስለሆነም አንድ ትውልድ በጭካኔ ዓለም ውስጥ መኖር አለበት፣ ይህ ሲሆን ብቻ አንድ አገር በኢኮኖሚ ማደግ ትችላለች በማለት አዲስ ቲዎሪና ሳይንስ ያስተምረናል። የመንግስቱ ቃል አቀባይ ካናዳዊቱ ቢሌኒ ስዩም ደግሞ በጎ ተፅዕኖ ሳለለ ነው ሲንጋፖር ያደገችው በማለት የዲያቆን ዳንዔል ክብረትን አነጋገር ትንሽ ለስለስ ለማድረግ ትሞክራለች። የውጭ ጉዳይ ሚንሲተር ታዬ አሰቀሰላል ደግሞ ህዝቡ መሪውን ማዳመጥ አለበት፣ ችግሩንም ራሱ መፍታት አለበት በማለት እንደዚሁ አዲስና ቀደም ብሎ ያለተሰማ እሱ ለዕደገት ያማቸል የሚለውን ነገር ይነግረናል። በአጭሩ የእነዚህን የመንግስት ልዑካኖች ንግግር ወይም መልስ ላዳመጠ የሚረዳው ነገርና ከገጽታቸውም የሚነበበው ማሰብ እንደማይችሉና መንፈሳቸውና ልባቸው የደነደነ መሆኑን ነው፤ በፍጹም ርህራሄ የሌላቸውና ሰው መሆናቸውን እንዳልተገነዘቡ ነው መረዳት የሚቻለው። በሌላ በኩል፣ መነሳት የነበረባቸውና ለዑካኖቹን ማስጨነቅ የነበረባቸው ጥያቄዎች በእኔ ግምት በዚህ መልክ መቅረብ ነበረባቸው። ልዑካን ተብዬዎቹ ሲንጋፖር እዚህ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ምን እርምጃዎችን ወሰደች? የመሪዎቹስ ባህርይና የዕውቀትስ ደረጃ ምን ይመስላል? ምን ዐይነትስ ፖለቲካ ተከተሉ? የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውስ ምን ይመሳላል? ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለምሳሌ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ጋር የነበራቸው ግኑኝነትስ ምን ይመስል ነበር? የራሳቸውን መንገድ ነው ወይ የተከተሉት ወይስ ትዕዛዝ ተቀባዮች ነበሩ? በኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ላይ በተለይም እንደአሜሪካ የመሳሰሉት አገሮች በተዘዋዋሪ ግፊት ያደርጉባቸው ነበር ወይ? የውስጥ ፖለቲካቸውስ በከፋፍለህ ግዛው ላይ የተመሰረተ ወይስ ሰላምን የሚያሰፍነና ህዝቡን ለስራ የሚያነሳሳ? ልዑካን ነን ተብዬዎቹ እነዚህነና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎችን አላነሱም? ሌላ ጋዜጠኛም አንስቶ አላፋጠጣቸውም። እንደተመለከትኳቸው ከሆነ የልዑካኑ አዕምሮ ደንዝዟል። ስልጣን ላይ ለምን እንደተቀመጡ የገባቸው አይመስልም። የህዝቡን የተለያዩ ችግሮቾ ከመፍታት ይልቅ ያለውን የሚያባብሱ ነው የሚመስሉት። ባጭሩ በመንግስት በጀት በአውሮፕላን ተጉዘውና ተዝናንተው ነው የተመለሱት። የአንድ አገር ህዝብ ዕድል በመንግስቱና በአገዛዙ ትከሻ ላይ የወደቀ ለመሆኑ በፍጹም የገባቸው አይመስልም። ከተሟላ ዕደገትና ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና ማምታታትን የመረጠ የአንድ ሰው አገዛዝ አጫፋሪዎች ነው የሚመስሉት። በራሳቸው ህሊና የሚመሩና የተገለጸላቸውም አይደሉም። በትዕቢት የተወጠሩና ምንም ዐይነት ስሜት የሌላቸው መሆናቸውን ነው ከገጻቸውም ማንበብ የሚቻለው። ልዑካኑ ኢትዮጵያን ከሌሎች አደጉ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መነጠቁ ከሚባሉ አገሮች ጋር በማወዳደር፣ እኛን ለዚህ ዐይነቱ ውርደት፣ ጦርነት ወይም የሰላም ዕጦትና በግልጽ የሚታይ ድህነት የዳረገን ምን ነገር ነው? ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁና ቢያስጨንቁ ኖሮ ዋናው የዕድገትና የሰላም ጠንቅ፣ ወይም ለድህነትና ለከተማዎች መቆሸሽ፣ እንዲሁም ለብልግና መስፋፋት መንግስት ተብዬውና ራሳቸው ተጠያቂዎች መሆናቸውን መገንዘብ በቻሉ ነበር።
የጠ/ሚኒስተሩ ወይም የመንግስት ቃል-አቀባይ የሆነችው ቢሌኒን ጥያቄ በመጠየቅ መልስ ለማገኘት ያልቻለችው ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ ለመረዳት ባለመቻሏ ነው። ሲትዬዋ ካናዳ ብዙ ዓመታት የኖረችና ግድፈት የሌለበት ወይም አክሰንት የማይታይበት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው እያቀላጠፈች የምትናገረው። ይሁንና ካናዳ ብዙ ዓመታት መኖሯና የተቀላጠፈ እንግሊዘኛም መናገሯ ይህን ያህልም አስተሳሰቧን አላጠራውም፤ በአጭሩ የተገለጸላትና ምሁራዊ አስተሳስብ እንዲኖራት አላደረጋትም። ህሊና ቢኖራት ኑሮ ከዚህ ዐይነቱ በህዝባችን ላይ ጦርነትን ካወጀና ውድ አገራችንን ከሚያመሰቃቅል ዕብድ የሚመስል አገዛዝና የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት በሰፈነበት አገዛዝ ጋር አብራ ባልሰራች ነበር። ወይዘሮይቷ እየመላለሰች የጠየቀችው ጥያቄ፣ ይህች ምንም ዐይነት የጥሬ ሀብት የሌላት አገር እንደዚህ በአማረ መልክ ስትገነባና ከተማዋስ ንፁህ ሲሆን፣ እኛ የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና ልዩ ልዩ ሰብሎችና ፍራፍሬዎችን የሚያበቅልና ፍሬያማ መሬትና ቆንጆ አገር እያለን ምን ቢሳነን ነው ለማደግ ያልቻለነው? በማለት ነው በመገረም ጥያቄ ራሷን መጠየቅ የጀመረችው። ይህንና ለዕድገትና ለተሟላ ሰላም ማነቆ የሆነው ነገር አፍንጫዋ ስር እንዳለና፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የጦርነት ማገዶ ውስጥ የከተተው ሰውና አገዛዙ እዚያው አጠገቧ እንዳለ ለመረዳት በፍጹም አልቻለችም። ምናልባት የእግዚአብሄር እርግማን ሆኖ ታይቷት ሊሆን ይችላል።
ለማንኛውም ወደ ሲንጋፖር ተመልሰን ስንመጣ የሰለጠነና ከጭቆና ነፃ የሆነ አገዛዝ በጣም ወሳኝ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። የመንግስቱም ዋና ዓላማ ህዝቡን ከድህነት ማውጣትና አገሩን ማስከበር እንደሆነ እንረዳለን። ስለሆነም የመንግስቱ መኪና ከሰላዮችና ከሙስና የፀዳ መሆኑን እንገነዘባለን። አገዛዙ ይህንን ወይም ያኛውን ኃያል መንግስት በመለማመጥና ጥገኛ በመሆን ሳይሆን አገሩን እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ የቻለው በራሱ በመተማመንና ጥበብ የተሞላበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተሉ ብቻ ነው። ሲንጋፖርም ሆነ ሌሎች በቴክኖሎጂ ያደጉ ለምሳሌ እንደታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና አሁን ደግሞ ቻይና የእምሳሰሉት አገሮች እዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጋቸው አይደለም። በአነሳሳቸውም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በሚል ብቻ ሳይሆን ህዝባችንን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ማላቀቅ አለብን ብለው በአገር ወዳድነት ስሜት በመነሳታቸው ብቻ ነው። ሌላውና መሰረታዊው ጉዳይ የመንግስቱ መኪና ተንኮል የሚሸረብበት አይደለም። ማንኛውም የመንግስት አካል ችሎታውን በማስመስከርና በማረጋገጥ ብቻ ነው ስልጣን ላይ የሚወጣውና ስልጣንም ላይ ለመቆየት የሚችለው። ስለሆነም ጠቅላላው አገዛዙ የህዝቡ ጠበቃና አለኝታ መሆኑን እንገነዘባለን። ከዚህ በላይ ሲንጋፖር የተለያዩ ጎሳዎች ያሉባት ከተማ ብትሆንም በጎሳ ምክንያት የተነሳ ንትርክና ግጭት የሚታይባት አገር አይደለችም። ለሚኒስተርነት የሚታጭ ግለሰብ በኮታ ወይም ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው የመጣ ብሄረሰብ በማለት ሳይሆን ዕውቀትን መለኪያ ወይም መመዘኛ በማድረግ ብቻ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ ጎሳውን በመንተራስ ጎሳዬን ልጥቀም፣ ስለሆነም የበላይነቴን ማስፈን አለብኝ ብሎ የሚሯሯጥ ሳይሆን ሲንጋፖር ውስጥ የሚኖር የሲንጋፖር ተወላጅ የሆነ ሁሉ እንደ አንድ ዜጋ የሚታይባት ከተማ ነች። እያንዳንዱም ዜጋ ለማደግም የሚችለው የተከፈተለትን ዕድል በመጠቅምና ችሎታውን በማረጋገጥ ብቻ ነው። ሌላው የሲንጋፖር ልዩ ሁኔታ ሲንጋፖር የተለያዩ ሃይማኖቶች እዚህና እዚያ የራሳቸውን ቤተክርስቲያን በመክፈት የሚራወጡባትና ለዕድገት ዕንቅፋት የሆኑባት አገር ሳትሆን የጠቅላላው ህዝብ አስተሳሰብ በዕድገት ዙሪያ የሚሽከረከር ነው። ይሁንና ግን መንፈሳቸውን የሚያድስና ሞራላቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ ኃይማኖት የሚመስል ነገር የላቸውም ማለት አይደለም። ለማለት የምፈልገው በአገራችን ምድር እነመለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ ሲወጡ የያዙት ፈሊጥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለማዳከም ወይም ለመምታት ሲባል የጴንጤ ቆንጤን ሃይማኖት በሰፊው እንዲሰፋፋ ማድረግ ነው። በዚህ መሰረት ልቅ የሆነና ለዕድገትና ለጠራ አስተሳሰብ እንቅፋት የሆነ የተለያዩ ሃይማኖቶች በመስፋፋት ሰፊውን ህዝብ ግራ ማጋባት ችለዋል። ይህ ዐይነቱ ውዥንብር መንዛት በካፒታሊስት አገሮች እንኳ የሚታይ አይደለም። አቢይ አህመድ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ በቀጥታ በተለይም በኦርቶዶክስና በእስላም ሃይማኖት ላይ ዘመቻ በማድረግ የፔንጤ ቆንጤ ሃይማኖት እንዲስፋፋ ነው ለማድረግ የቻለው። ይህ ዐይነቱ የሃይማኖት መስፋፋት ደግሞ አስተሳሰብን የሚያጠራና ራስን ለማወቅ የሚያስችል አይደለም። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን ሃይማኖትን መከተል ይችላል። ነገር ግን ሃይማኖት መንዛዛት የለበትም። ማንኛውም ግለሰብ ሊኖር የሚችለው ሲሰራና ለራሱም ሆነ ለህብረተሰቡ አስተዋፅዖ ሲያደርግ ብቻ ነው። አንድ አገር ደግሞ ልታድግ የምትችለው በአጉል ሰበካ ሳይሆን በምርታማ ስራ በመሰማራትና ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመፍጠር ብቻ ነው። ስለሆነም በተለይም አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ያለውን ክፍተት ወይም አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ህዝብን፣ በተለይም ደግሞ ታዳጊውን ወጣት ማምታት ማቆም አለባቸው። ወደፊት የሰለጠነ አገዛዝ ስልጣንን ሲጨብጥ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መቻል አለበት። እያንዳንዱም የገቢ ምንጭ መታወቅና ቀረጥም መክፈል አለበት። ካለበለዚያ ህዝብን እያታለሉና ገንዘብ ከደሃው እየሰበሰቡ መንደላቀቅና ማሸብረቅ ለዕድገትና ለሰላም አመቺ አይደለም። እያንዳንዱ ዜጋ አስራ ስምንት ዓመት ከሞላው በኋላ በሙያ መሰልጠንና፣ ዕድሜው ደግሞ ከፍ ያለ ከሆነ የግዴታ በስራ ዓለም ውስጥ መሰማራት አለበት። በየፋብሪካዎችና በአገልግሎት መስኮች ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ክሌለ መንግስት ራሱ ልዩ የስራ መስክ የሚከፈትበትን ሁኔታ በማጥናት በሰበካ ስራ የተሰማራውን ሰው በስራ ዓለም ውስጥ እንዲካተት የማደግ አገራዊ ኃላፊነት አለበት። ስራ ራስን ማወቂያ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ማንኛውም ግለሰብ በስራ ሲወጠር ከብጥብጥና ከወሬ ይቆጠባል።
ከዚህ በተረፈ ለአንድ አገር የተሟላ ዕድገት የምሁራን የንቃተ-ህሊና ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው። ለተሟላና ዘላቂነት ላለው ዕድገት ንቃተ-ህሊናና ሳይንሳዊ ዕውቀት በጣም ወሳኝ ናቸው። ያለፉትን ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ስከታተል በአገራችንም ሆነ ውጭ ባለው ኢትዮጵያዊ ምሁር ነኝ ባይ ዘንድ ከፍተኛ የግንዛቤ ዕጦት ይታያል። በተለይም አንዳንዶች በትዕቢት የተወጠሩ ስለሆነ ግልጽነት ላለው ውይይትና ክርክር የተዘጋጁ አይደሉም። አንድ ነገር ተነስቶ እሱ ላይ ከመረባረብና መስመር ከማሲያዝ ይልቅ ሌላ አጀንዳ በመክፈት የሰውን አስተሳሰብ ሲበትኑ ይታያሉ። አገሬን እጠቅማለሁ፣ ለተሟላ ዕድገት የቆምኩኝ ነኝ፣ ህዝቤም ከድህነት መላቀቅና የተከበረች አገር መገንባት አለባት የሚል ግለሰብ ሁሉ አስተሳሰቡን ግልጽ ማድረግ አለበት። የተሳሳቱ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰቦችን በማስፋፋት አገራችንና ህዝባችንን ከአንድ የትርምስ ሁኔታ ወደሌላ የትርምስ ሁኔታ ውስጥ መክተት የለበትም። ያረጀው ትውልድ አርጅቷል። ቢጠሩት የሚሰማ አይደለም። መልዕክቴ ለታዳጊውና መሰረታዊ ለውጥ ለሚፈልገው ወገናችን ብቻ ነው።
ያም ተባል ይህ ከዛሬው የአቢይ አህመድ አገዛዝ የሚጠበቅ ነገር የለም። ሚኒስተሮችንም እንዳየናቸው ከሆነ የበደኑና ለሰው ልጅ ርህራሄ የሌላቸው ናቸው። ሰው መሆናቸውን ያልተገነዘቡ ናቸው። ማንኛውም የስው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን መሰረታዊ ነገሮች፣ ለህሊና መገዛት፣ ለሌላው መሰማትና መቆርቆር፣ ሞራልንና ስነ-ምግባር፣ እኩልነትና ፍትሃዊነት፣ እንዲሁም ግድያንንና ማሰቃየትን መጸየፍ…ወዘተ. የመሳሰሉት ነግሮች መንፈሳቸው ውስጥ የሌላችው ወይም በመንፈሳቸው ውስጥ ያልተቀረጹ ናቸው። ስለሆነም አቢይ አህመድም ሆነ ጠቅላላው በአገዛዙ ውስጥ የተካተቱት በሙሉ ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይደሉም። ለስልጣንም የሚገቡ አይደሉም። ስለሆነም ህዝባችንና አገራችን እፎይ ብለው ኑሮን በሰላም እንዲኖሩ ከተፈለገ ከጭቆና አስተሳሰብ ነፃ የሆነ አዲስ አገዛዝ መመስረት አለበት። ግለሰባዊ አምባገነንነት ወይም የቡድን አምባገነንነት በአገራችን ምድር ቦታ እንዳይኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲህን ሲሆን ብቻ ነው ቀስ በቀስ በራሳችን በመተማመን ከታች ወደ ላይ ህዝባችንን ያቀፈና ህዛብችንን የሚጠቅም የተሟላ ዕድገት ማምጣት የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!