May 4, 2024
29 mins read

ፕሪቶሪያና ሃላላ ኬላ – ኤፍሬም ማዴቦ

ሃላላ ኬላ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ አስደናቂና ውብ ቦታ ነው። ዳውሮ ዞን ውስጥ የሚገኘው ሃላላ ኬላ ስሙን ያገኘው ዳውሮን ከጠላት ለመከላከል ግንባታው በ16ኛው ምዕተ አመት ተጀምሮ በ18ኛው ምዕተ አመት አጋማሽ አካባቢ ካለቀውና ዳውሮን ዙሪያዋን የከበባትን ግንብ ስራ ካስጨረሰው ከንጉስ ሃላላ ነው። ዳውሮ ዳግማዊ ምኒልክ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ግዛት በተለያየ አቅጣጫ ሲያስፋፉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት ግዛት አካል ያደረጉትና፣ እስክ 1883 ዓም ድረስ የራሱ ተከታታይ ነገስታት የነበሩት ቦታ ነው። ሃላላ ኬላ በሰው ሰራሹ ሃላላ ግንብ፣ በጫካና በውኃ የተከበበ ተፈጥሮ ውበትን እንካ ብሎ ያደለው አይን የሚማርክ ውብ ቦታ ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ጆግራፊ ስንማር የራሳችንን ውብና ማራኪ ቦታዎች ትተን፣ ቪክቶሪያ ፎልስ፣ ናይግራ ፎልስ፣ጎልደን ጌት ቢሪጅ፣ ቻይና ግንብ፣ ታጅማሃል ወዘተ እያልን የሌሎችን አስደናቂ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ውበት ስለምንማር ነው እንጂ፣ የራሳችን የሆኑ ሃላላ ኬላን፣ሐርር ግንብን፣ሰሜን ተራራ፣ባሌ ተራራ፣ሶፎኦማርን፣አጆራ ፏፏቴን፣ጢስ እሳትንና ላሊበላ፣ጎንደርና አኩስምን የመሳሰሉ ታይተው የማይጠገቡ ቦታዎች አሉን።

እንግዳ ተቀባይ፣ ሰው አክባሪና ጨዋ የሆነ ህዝብ የሚኖርባት የዳውሮ ዞን ውብት ምልክት የሆነቸውን የሃላላ ኬላን ስም በጥሩ ከሆነ በቀር በክፉ ማንሳት አይቻልም። ዛሬ ሃላላ ኬላን ይዤላችሁ የመጣሁት መታጠቢያ ቤት መሄድ ሲገባቸው ከነቆሻሻቸው ሃላላ ኬላ ሄደው በዚህች ውብና ታሪካዊ ቦታ ላይ አሳፋሪና ታሪካዊ ክህደት የፈጸሙትን ህወሓትን እና ብልጽግናን ለማንሳት ነው እንጂ፣ ሃላላ ኬላማ ምን ግዜም ሃላላ ኬላ ናት።

የፕሪቶሪያው ስምምነት 15 አንቀጾችና ብዙ ንዑስ አንቀጾች አሉት። ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት ግዜና ከሥልጣን ከተወገደም በኋላ በተለይ ከ2013-2015 ድረስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ይህ ነው ተብሎ የማይነገር በደልና ሰቆቃ ለሚያውቅ ለማንም ሰው የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹና በቅድሚያ ተግባራዊ መሆን የነበረባቸው የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጾች ናቸው። የህወሓት ማን አለብኝነት የሚመነጨው ከዕብሪቱ ነው፣ የዕብሪቱ ምንጭ ደሞ የታጠቀው የጦር መሳሪያ ነው።

 

  • ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው
  • የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበት (Disarmament)፣ከወታደራዊ ህይወት የሚላቀቁበት (Demobilization) እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት (Reintegration) ሁሉን አቀፍ ፕሮግራም ይዘጋጃል
  • የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ከ5 ቀን በኋላ የሁለቱ ኃይሎች (የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት) ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ተገናኝተው የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት መንገድ ተወያይተው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ሁለቱ ኃይሎች ተገናኝተው ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ባሉት 10 ቀኖች ውስጥ ህወሓት ከባድ መሳሪያውን ሙሉ በሙሉ ይፈታል
  • የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ በ30 ቀን ውስጥ ህወሓት ቀላል መሳሪያውን ይፈታል።
  • ሁለቱ ኃይሎች (የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት) ተነጋግረው ትግራይ ውስጥ ሁሉን አቀፍየሽግግር መንግስት ያቋቁማሉ

የፕሪቶሪያዉ ስምምነት የተፈረመው ጥቅምት 23,2015 ዓም ነው። አሁን ያለነው ሚያዚያ 2016 መገባደጃ ላይ ነው። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ህወሓት ህዳር 23 ቀን 2015 ዓም የታጠቀውን ትጥቅ (ከባድና ቀላል መሳሪያ) ሙሉ በሙሉ መፍታት ነበረበት። ሆኖም የህወሓት የክርስትና ልጆች የነብስ አባታቸው ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ ባለመፈለጋቸው የሀወሓት ወራሪ ሠራዊት በያዝነው ወር ራያ ገብቶ አንዳንድ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥሯል። ከሰሞኑ ደሞ የትግራይ ክልል ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ህወሓትና ብልፅግና ወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ላይ የደረጉት ስምምነት ምን እንደሚመስል በይፋ ተናግረዋል።

ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓም በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኤታማጆር ሹም ብርሃኑ ጁላና በህወሓት ከፍተኛ ወራደራዊ ባለሥልጣን ታደሰ ወረደ የሚመራ ቡድን ናይሮቢ ላይ ተገናኙ። እነዚህ ከአዲስ አበባና ከመቀሌ የሄዱ ባለሥልጣኖች ናይሮቢ ላይ መልካቸውን ነው ያሳዩን እንጂ ምን አይነት ስምምነት ላይ እንደደረሱ ለጉዳዩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ያሳወቁት ነገር አልነበረም። ከጥቂት ቀናት የናይሮቢ ሠርግና ምላሽ በኃላ በጠሚ አቢይ አህመድ የሚመራ የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ቡድንና የህወሓት መሪዎች ሃላላ ኬላ ላይ ስብሰባ መቀመጣቸው ተነገረ። የሃላላ ኬላው ሰርግና ምላሹ፣ግብዣው፣መንቆለጳጰሱ፣ መተቃቀፉና መሸላለሙ መሃል አዲስ አበባ እስከሚገኘው ወዳጅነት ፓርክ ደረሰ። ሁለቱ ህዝብ ያፋጁት ከሃዲዎች ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ተቃቀፈው ተሳሳሙ። ልጇ እንደወጣ የቀረባት የትግራይ እናት፣ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጇ የተደፈረባት የአማራ እናት፣ ባሏ የሞተባት ሚስትና ልጆቹ የተበተኑበት አባትና የታንንክ፣የመድፍና የሌላም ከባድ መሳሪያ ጥይት በተከታታይ እንድ ዝናብ የወረደበት የአፋር ህዝብ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ምን ጉድ መጣ እያለ አለቀሰ።

ምንድነው ህወሓትና ብልፅግና ሃላላ ኬላ ላይ የተስማሙት? Politically correct መሆን የፈለገ ሰው እነሱ አልነገሩንም፣እኔም ቦታው ላይ አልነበርኩም ስለዚህ አላውቅም ሊል ይችላል። ይህንን ጥያቄ የብልፅግና ደጋፊዎችና የአቢይ አህመድ አምላኪዎች ቢጠየቁ መልሳቸው ጠሚ አቢይ ኢትዮጵያን የሚጠቅም እንጂ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ስምምነት ላይ አይደርሱም የሚል ነው። እኛስ የፕሪቶሪያው ስምምነት ምን እንደሆነ የምናውቅ፣ ከሃላላ ኬላ በኋላ የፕሪቶሪያው ስምምነ የት እንደደረሰ የምናውቅና እንዲሁም ራያ ውስጥ ሀወሓት ያካሄደውን ወረራና በዚህ ሳምንት ታደሰ ወረደ ራያንና ወልቃይት ጠገዴን አስመልክቶ ያፈረጠውን እውነት በጆሯችን የሰማን ሰዎች፣የሃላላ ኬላው ስምምነት ምንድነው ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምንድነው የሚሆነው?

ሃላላ ኬላ ላይ ህወሓትና ብልፅግና ያደረጉት ስምምነ በአገር ላይ የተሰራ ክህደት መሆኑን ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ የለብንም። ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓም ዕለተ ሰኞ ወደማክሰኞ ከመለወጡ በፊት 100% የታጠቀውን ትጥቅ መፍታት የነበረበትና ሰራዊቱም መበትን የነበረበት ህወሓት በያዝነው ሚያዚያ ወር (2016) አማራ ክልል ገብቶ በጦርነት ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠር እንዲችል መንገድ የጠረገለት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይሆን የሃላላ ኬላው ክህደት ነው። ህወሓት ትጥቁን ሳይፈታ የፌዴራል መንግስት በሌለበት ቦታ ህወሓቶች ብቻ ተሰብስበው ህወሓት ብቻ ያለበትን የሽግግር መንግስት እንዲመሰርት ያደረገው የሃላላ ኬላው ክህደት ነው፣በሌላ በኩል ደሞ ህወሓት አገርን ማሸበር እንዲችል የልብ ልብ ከሰጠው ሙሉ ትጥቅና ከ250ሺ በላይ የታጠቀ ሰራዊቱ ጋር ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ ያደረገውም የሃላላ ኬላው ክህደት ነው።

የሃላላ ኬላው ስምምነት ከተደረገ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው የሚል ህግ ያወጣው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ለምንድነው ህጉ ወጥቶ ሳይውል ሳያድር አማራን ትጥቅ ለማስፈታት ጦር ይዞ አማራ ክልል የዘመተው? የጠሚ አቢይ መንግስት በአንድ በኩል ከአማራም ከፌዴራል መንግስትም ጋር ፊት ለፊት ጦርነት የገጠመውን ህወሓትን በአደባባይ እየሸለመ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ያደረገውን የአገርህን አድን ጥሪ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ከአደጋ ካዳነው ከፋኖና ከአማራ ልዩ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት የቸኮለው ለምንድነው?

 

በአንድ ወቅት ጠሚ አቢይ አህመድና የጦር መሪዎቻቸው አመድ አደረግነው ብለው የፎከሩበት ህወሓት ከሞት እንዲነሳና ከዕብሪቱና ከሙሉ ትጥቁ ጋር ህወሓት ሆኖ እንዲቀጥል ከሆነ የተፈለገው፣ ያ ሁሉ የፌዴራል ወታደር፣ ያ ሁሉ የአማራና የአፋር ወጣት ለምን ሞተ? ለምንስ የአገር ኃብት በከንቱ ባከነ? ባጠቃላይ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ከፍታዋ መመለስ የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው ብለው የተናገሩት ጠሚ አቢይ አህመድ፣ እቺኑ ኢትዮጵያ ጠላት ብሎ ፈርጆ የወጋት ህወሓት እስካፍንጫው የታጠቀውን መሳሪያ እንዲፈታ ያልፈለጉት ለምንድነው?

የአገር መከላከያ ሠራዊትን በተኛበት ያረደ፣በቅርብ ግዜውም በሩቁም የኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ የጦር ወንጀል በአፋርና በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመውና፣ የኢትዮጵያን እንደ አገር መቀጠል ትልቅ አደጋ ላይ ጥሎ የነበረው ህወሓት፣ ለእንደዚህ አይነት ክፋትና ዕብሪት ያበቃውን ትጥቅ ሳይፈታ መንግስት መስርቶ እንደገና ትግራይን እንዲመራ የተደረገው ለምንድነው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያለው የሃላላ ኬላው ስምምነት ላይ ነው። ይህ ስምምነት ነው አማራን የህልውና ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያስገደደው፣ ይህ ስምምነት ነው ህወሓት አማራ ክልል ገብቶ አላማጣንና አካባቢውን እንደገና የጦርነት ቀጣና እንዲያደርግ የፈቀደለት። የሃላላ ኬላው ስምምነት ነው ታደሰ ወረደ ሜዲያ ላይ ወጥቶ ወልቃይትና ራያ ላይ የትግራይ አስተዳደር ይመሰረታል እንዲል ያበቃው። የሃላላ ኬላው ስምምነት ነው ከህወሓት ጋር በተደረገው የሁለት አመት ጦርነት ለኢትዮጵያ አጋር የሆኑ ኃይሎች ተክደው ጭራሽ እንደ ጠላት እንዲታዩ ያደረገው።

ለምንድነው ብልፅግና እና ህወሓት ፕሪቶሪያን ትተው ሃላላ ኬላ ላይ ሌላ ስምምነት የተስማሙት? ከ1966ቱ አብዮት በኋላ ህወሓቶች ጫካ ገብተው የትግል ማኒፌስቷቸውን ሲጽፉም ሆነ ታጣቂዎቻቸውን የፖለቲካ ትምህርት ሲያስተምሩ ጠላት ነው ብለው የፈረጁት አማራን ነው። ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት 27 አመት ኢትዮጵያ ውስጥ በማንነቱ ከፍተኛ በደል የደረሰበት የአማራ ህዝብ ነው። በሰኔ ወር 2013 ዓም ህወሓቶች ልኩን እናሳየዋለን ብለው ውጊያ የከፈቱት በአማራ ህዝብ ላይ ነው። የማይካድራ፣የቆቦ፣የጭና በቅርቡ ደሞ መርዓዊ ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል የተፈጸመው በአማራ ህዝብ ላይ ነው።

ባለፉት ሃምሳ አመታት የኦሮሞ ልህቃን የኦሮሞ ናሺናሊዝምን ሲገነቡ ገዝቶናል፣ረግጦናል፣ጨቁኖናል ብለው እንደጠላት የተመለከቱት አማራን ነው። ደርግ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያው ሁለትና ሦስት አመታት ያለምንም መከልከል አርሲ፣ሐረርጌና ወለጋ ውስጥ በግፍ የተገደሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቤዎች በጅምላ የተጨፈጨፉትና አሁንም በግፍ እየተገደሉ ያሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው። የኦሮሚያ ክልል መንግስት አዲስ አበባ አትገቡም እያለና ከአውቶቡስ ላይ እያስወረደ የሚያንገላታው የአማራን ተወላጆች ነው። ባለፉት ሦስት ወራት አዲስ አበባ ውስጥ በጅምላ የታሰሩትና አሁንም በመታሰር ላይ ያሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው። እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን የተለያዩ ወንጀሎች በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙት ደሞ ህወሓት፣ ኦነግና ብልፅግና ወይም የእነዚህ ኃይሎች ጥምረት ነው። የሃላላ ኬላውን ስምምነት የተስማሙትም ከእነዚህ ሦስት ኃይሎች ውስጥ ሁለቱ ናቸው።

የኦሮሞ ልህቃንና የትግራይ ልህቃን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በተመለከተ የሚጋሩት ትልቅ እሴት አለ፣ ይህ እሴት የብሔር ፖለቲካ ነው። ለሁለቱም ልህቃን ኢትዮጵያ የሚለው ስም የሚዋጥላቸው የብሔር ፖለቲካ እስከቀጠለና የሁለቱን ልህቃን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅምና ፍላጎት ተራ በተራ እስካስጠበቀ ድረስ ብቻ ነው። የብሔር ፓለቲካና የዚህ ፖለቲካ መሠረት የሆነው ህገመንግስት ሳይሸራረፍ መከበር አለበት የሚለው አቋም ደሞ ብልፅግናዎችም ደረታቸውን ነፍተው የሚናገሩት አቋም ነው። እነዚህ ሁለት ኃይሎች የብሔር አጀንዳቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ማድረግና ኢትዮጵያ እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ ብቻ እንድትሄድ ይፈልጋሉ። ትናንትም፣ዛሬም ነገም ይህ እርኩስ አላማቸው ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ነው ብለው የሚያስቡት የአማራን ማህበረሰብ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህወሓቶች ተቋማዊ መልክ የሰጡት የብሔር ፖለቲካ የትግራይና የኦሮሞ ልህቃንን ከየትኛውም የኢትዮጵያ ልህቅ በተለየ መልኩ ያቀራርባቸዋል። ይህ ደግሞ ከህወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት፣ በወልቃይት ጠገዴ ጥያቄና በቅርቡ የኦሮሞ ኃይሎች የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለመከፋፈል ባደረጉት ጥረት በግልፅ የታየ ሃቅ ነው። የብሔር ፖለቲካን፣ የብሔር ፌዴራሊዝሙንና ባጠቃላይ ዛሬ በስራ ላይ ያለውንና ሁለቱ አብረው የጻፉትን ህገ መንግስት ለማስቀጠል የትግራይና የኦሮሞ ልህቃን እጅና ጓንት ሆኖ መስራታቸው አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይና የኦሮሞ ልህቃን በአማራ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፣ሁለቱም አማራ ትንሽ ሆኖ ማየት ይፈልጋሉ፣ ደግሞም ከሃላላ ኬላው የብልፅግና እና የህወሓት ስምምነት በኋላ በግልጽ እንደታየው እነዚህ ሁለት ኃይሎች ፀረ-አማራ ግንባር ከመፍጠር የማይመለሱ ናቸው። ይህንን ደሞ የራሳቸው በተለይ የብልፅግና በለሥልጣኖች ሳይደብቁ ተናግረዋል። After now its all about connecting the dots.  እርግጠኛ ነኝ ነጥቦችን ማገናኘት የሚችል ሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ተጥሎ ሃላላ ኬላ ለምን እንደተፈለገ ለማወቅ ግዜ የሚወስድበት አይመስለኝም።

ከHigh School ጀምሬ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ ተከታትያለሁ። ያለፉት 30 አመታት ህይወቴ ከፖለቲካ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነበር። ባለፉት 10 አመታት ደሞ ሙሉ ህይወቴን ለኢትዮጵያ ፓለቲካ ሰጥቻለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማን ማነው የሚለውን በሚገባ እንድገነዘብ ረድተውኛል። በተለይ ከ2010 ዓም መጨረሻ እስከ ግንቦት 2015 ድረስ በነበሩት 5 አመታት አገር ውስጥ ሆኜ ከአገር መሪ፣ከከፍተኛ የክልል ባለሥልጣኖች፣ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ከሲቪክ ድርጅት መሪዎች፣ ከወጣቶች፣ክሴቶችና ከተለያዩ ምሁራን ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት ዕድል አግኝቻለሁ። ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው፣ በዚህ ጽሁፍና ወደፊትም በምጽፋቸው ጽሁፎች ላይ የሚንጸባረቁ ብዙ ህሳቦች ከዚህ የረጂም ግዜ ልምድ የሚመነጩ ናቸው። እንዲህ ሲባል ግን ከልምድ የሚመነጩ ናቸውና እንዳለ ውሰዷቸው ወይም ሁሉም ትክክል ናቸው ማለት አይደለም። አንድ ነገር ግን ደፍሬ መናገር እችላለሁ፣ ህወሓትና ብልፅግና አማራ ላይ ያነጣጠረ ግዜያዊ ጥምረት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይህንን ለማለት የደፈርኩት ብልፅግና እና ህወሓት ሃላላ ኬላ ላይ ከተገናኙ በኋላ እንዳይሆን የተደረገውንና እየሆነ ያለውን ክስተት ከተመለከትኩ በኋላ ነው።

ህወሓቶች ተንኮለኞች ናቸው፣ ምንም ነገር ላይ ሲደራደሩ የራሳቸውን እቤታቸው አስቀምጠው በሌላው ድርሻ ላይ ነው የሚደራደሩት እንጂ፣ የነሱ የሆነውን ለድርድር ይዘው አይመጡም። ከብልፅግና ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም ስምምነቱ እነሱን ወደፊት አጉልቶ የማያመጣ ከሆነ ግዜ ለመግዣ የሚሆን ሃሳብ ይዘው ይመጣሉ እንጂ ሰጥቶ መቀመል (Compromise) የሚባል ነገር አያውቁም። የብልፅግና አሸሼ ገዳሜዎች ግን እንደ በሬው ሰርዶ ሰርዶውን እንጂ ገደሉን በጭራሽ አያዩም። ደሞም ህወሓቶች ብልፅግናዎችን በሚገባ ያውቋቸዋል . . .  ወልደው፣ኮትኩተው ያሳደጓቸው እነሱ ናቸዋ! ብልፅግናዎች ህወሓቶችን በፍጹም እንደማያውቋቸው ወይም ምንግዜም እንደ ክርስትና አባታቸው እንደሚመለከቷቸው ግና 3 ዙር ከህወሓት ጋር የተዋጋነው ጦርነት፣ከጦርነቱ በፉት የነበሩት ሁለት አመታትና የሃላላው ኬላው ስምምነት በግልጽ አሳይቶናል።

ስለዚህ ብልፅጋና እና ህወሓት ፀረ-አማራ ጥምረት ፈጥረው መንግስት ቢመሰርቱም፣ የኦሮሞ ልህቃንን በተመለከተ ጥምረቱ የሚዘልቀው ከዚህ በፊት ኦፒዲኦና ህወሓት በተጣመሩበት መልክ ሆኖ የጥምረቱ መሪ ኦሮሞ ከሆነ ብቻ ነው። ነገር ግን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ህወሓት የሁለት አመቱ ጦርነት ያጎበጠው ጀርባው ቀና እስኪልለት ድረስ ከብልፅግና ጋር ተስማምቶ ሊሰራ ይችላል፣ የነሱ ሚና ሁለተኛና ሶስተኛ ሆኖ ግን ከብልፅግና ጋር ለዘለቄታው በፍጹም አይቀጥሉም። ለዚህ ነው ብልፅግና እና ህወሓት አማራ ላይ ቢጣመሩም ጥምረቱ ግዜያዊ ነው ያልኩት። እዚህ ላይ የሚያሳዝነው ግን ሁለቱ ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንደሚባለው፣ የህወሓትና የብልፅግና የፖለቲካ እሹሩሩ ብልጭ ድርግም እያለ በቆየ ቁጥር የምትጎዳው አገራችን ኢትዮጵያ ናት። ስለዚህ የብልጽግናን እና የህወሓትን ጥምረት. . . . . ህወሓቶች ባበዱ ቁጥር ልጆቹ ላይ የጥይት ዝናብ የሚወርድበት የትግራይ ህዝብ፣የሃላላ ኬላው የህወሓትና የብልፅግና ስምምነት የህልውና አደጋ ውስጥ የከተተው የአማራ ህዝብ፣ምንም ጥቅም ላያገኝ ነገር በቃኝን የማያውቁ ልጆቹ በየቀኑ በሚሸርቡት የፖለቲካ ሴራ እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም የሚቃጠለው የኦሮሞ ህዝብና፣ የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል አደጋ ውስጥ በገባ ቁጥር የወደፊት ዕጣው ምን እንደሆነ እንኳን በውል የማያውቀው የደቡብ ኢትዮጵያ፣የጋምቤላ፣ የአፋርና የሱማሌ ህዝብ፣ አንድ ላይ ሆነው ለህወሓትና ለብልፅግና ዕብደት ፍቱን መድኃኒት መፈለግ አለባቸው። እንዲህ አይነቱ አንድነትና እንዲህ አይነቱ ጥምረት ብቻ ነው ትግሬውንም፣ አማራውንም፣ ኦሮሞውን እና የደቡብ፣ የምስራቅ፣የሰሜን ምስራቅና የምዕራብ ኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም፣ መረጋጋትና ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መበት መከበር ማረጋገጥ የሚችለው። እንደዚህ አይነቱ ትብብር ብቻ ነው ብልፅግናን አስገድደን ሁላችንም እናታችን ብለን የምንጠራትን ኢትዮጵያን በጋራ መፍጠር የሚያችለን !!!

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop