March 25, 2024
30 mins read

የዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ክፉ አዙሪት መሰበሪያው እንዴትና መቼ ይሆን?

March 25, 2024

ጠገናው ጎሹ

ይህ ጥያቄ እጅግ ግዙፍ፣ ፈታኝና ዘመን ጠገብ እንጅ አዲስ እንዳልሆነና ሊሆንም እንደማይችል በሚገባ እገነዘባለሁ ። ለዘመን ጠገቡ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ የቀጠለውን የባለጌ፣ የሴረኛ፣ የሸፍጠኛ፣ የፈሪና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች የፖለቲካ ሥርዓት አስወግደን ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓተ ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ ያልተሳካልን ይህንኑ ቁልፍ (ወሳኝ) ጥያቄ በአግባቡና ወደ ውጤት ሊተረጎም በሚችል ሁኔታ ለመመለስ ባለመቻላችን ነውና አሁንም ከመሪሩ ውድቀታችን ተምረን ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እስካልቻልን ድረስ ጥያቄው ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል። የሚሻለው ብቻ ሳይሆን ብቸኛውና ትክክለኛው ፍኖተ መፍትሄም ይህንኑ ከምር ተረድቶ ጥያቂውን በአግባቡ መመለስ ነው።

ቀድምት በሆኑ የፖለቲካ ሥርዓቶች የተፈፀሙት አስቀያሚ ስህተቶች በዘመኑ ከነበረው የህሊናዊ ንቃትና ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሊታዩና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገባ የመሆኑ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ጎሳን/ዘርን ፣ ጥላችን፣ መለያየትንና መገዳደልን ህገ መንግሥታዊ ያደረገውን የሩብ ምዕተ ዓመት ህወሃት/ኢህአዴግ) መራሽ ሥርዓተ ፖለቲካ እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚሁ ሥርዓት ውላጆች በሆኑ የኦሮሙማ/የኦነግ/ ፖለቲከኞች የበላይነት እየተካሄደ ያለውን ሰቆቃዊ አገዛዝ ከምር ከመፀየፍ፣  ከመታገልና ለዜጎች ሁሉ የሚመች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ከማድረግ ይልቅ ከመከራና ከውርደት ጋር እየተለማመድን ቀጥለናል።

ይህ ደግሞ በተራው ዘመን ጠገብና በእጅጉ አስከፊ የሆነን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችል አዳዲስ አስተሳሰብና አሠራር ከመሞከር ይልቅ ለዘመናት የመጣንበትንና የወደቅንበትን አስተሳሰብና አካሄድ እየደጋገመን አዲስ ወይም የተለየ ውጤት የምንጠብቅ ጉዶች (ደካሞች) አድርጎናል።

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳው ዒላማ ያደረጋቸውን የየሃይማኖት ተቋማት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አባላትን ሰብስቦ የተወነውን እጅግ የወረደና አዋራጅ ተውኔተ ሴራ ከምር ያስተዋለ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው መከራንና ውርደትን ከመለማመዳችን የተነሳ አገርን ምድረ ሲኦል ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖች በእግዚአብሔር ስም እያወደስን በራሱ በፈጣሪ ላይ የምንሳለቅ ጉዶች የመሆናችንን መሪር እውነት የሚስተው አይመስለኝም።

“ተሞክሮ ያልሠራን ተመሳሳይ ነገር እየደጋገሙ የተለየ ውጤት መጠበቅ ቂልነት/ጤናማ ያልሆነ ባህሪ/ የአእምሮ ሸውራራነት/እብድት ነው (insanity is doing the same thing over and over again and expecting different results.)” ይህ አባባል የሳይንቲስት አልበርት ኤንስተይን እንደሆነ የሚነገርለት ቢሆንም ትክክለኛው ባለቤት በትክክል ማን እንደሆነ እስካሁን በተሟላ ሁኔታ ስምምነት ላይ የተደረሰ አይመስለኝም።

ባለቤትነቱ የሳይንቲስቱም ይሁን የሌላ ሰው ትልቁ ጉዳይ አባባሉ ለየትኛውም አይነት የሰው ልጅ የህይወት ዘርፍ እውነትነት ያለው ፣ትኩረት የሚሻ እና በሰፊው የሚጠቀስ ከመሆኑ ላይ ነውና በዚሁ መሠረታዊ ግንዛቤ ወደ ተነሳሁበት የእኛው ጉዳይ ልለፍ።

አንድ ነገር (አስተሳሰብና አካሄድ) የሚያሳየውን የአወንታዊ ለውጥ ውጤት አበረታችነት በመገምገም ለተወሰነ ጊዜ መታገሥና አስፈላጊ ከሆነም በድጋሚ መሞከር ትክክል ነው። ለዘመናት የተሞከረንና ለመቁጠር እጅግ በሚያስቸግር ሁኔታ ደጋግሞ የወደቀን (ያልሠራን) አስተሳሰብና አካሄድ የሙጥኝ ማለት ግን እንኳንስ ልዩ የማሰቢያ አእምሮ እና ብቁ አካል ለተቸረው ሰብአዊ ፍጡር ለደመነ ፍስ እንስሳትም አይሆንም። እንስሳት አደጋ ባጋጠማቸው ቦታና አካባቢ ወይ አይሄዱም ቢሄዱም ደመ ነፍስነታቸው በፈቀደላቸው መጠን ተጠንቅቀው ነው። ይህንን ተገንዝበን ነፃነትና ፍትህ እንደሚፈልግ ሰብአዊ ፍጡርና እንደ ማህበረሰብ (እንደ ህዝብ) መሆን የሚገባንን ባለመሆናችንና ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን ነው እንደ አብይ አህመድ አይነት ህሊና ቢስ ፣ባለጌና ጨካኝ ገዥዎቻችን ለመግለፅ በሚያስቸግር ደረጃ የመከራና የውርደት ማራገፊያቸው ያደረጉንና እያደረጉን የቀጠሉት።

አዎ! ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን የአገራችንን ዘመን ጠገብ ፣ ሁለንተናዊ ፣ ተደጋጋሚና አስከፊ ቀውስ (ውድቀት) ከምር ልብ ካልነው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ በእጅጉ ያሳፍራል፤ ያስደነግጣልም። ለነገሩ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ከመከራውና ከውርደቱ ጋር ስላለማመዱን ማፈርና መደንገጡም ከጊዜያዊ ግልብ ስሜት የማያልፍ እየሆነብን ከተቸገርን ዘመናትን አስቆጠርን። ከዚህ የከፋ የምንነትና የማንነት ቂልነት/ውርደት/ስንኩልነት (insanity) ይኖር ይሆን?

ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ይውል ዘንድ በአብይ አህመድና በካምፓኒው (በአገዛዙ) በታሰበበትና በተዘጋጀ መድረክ አዲስ አበባን ጨምሮ በለየለት ደጋፊነታቸው የታወቁትን፣ የእውቀት ማነስ ያለባቸውንና የምን ቸገረኝነት ባህሪ ማንነት ሰለባዎች የሆኑትን ግለሰቦች ከየክልሉ በካድሬዎቹ አማካኝነት እያስመለመለ (እያስመረጠ) በመሰብሰብ ሊፈላሰፍባቸው፣ ሊሳለቅባቸው፣ ከፋፍሎ በማላተም የሴራውና የሸፍጡ ሰለባዎች ሊያደርጋቸው፣ ወዘተ ሲሞክር እና በከፊልም ቢሆንም ሲያስጨበጭባቸው መታዘብ ሚዛናዊና ክፉ ነገርን የሚፀየፍ ህሊና ላለው ሰው በእጅጉ ያማል።

ብዙውን ጊዜ በሌሎች ወይም በራሳችን ወይም በሁለቱም ምክንያት ከወደቅንበት አለመነሳት ብቻ ሳይሆን ይበልጥ አስከፊ የሆነን የውድቀት አባዜ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፍን የቀጠልነው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ራሳችንን ለምንና እንዴት? ብለን ከምርና ከቁጭት በመጠየቅ ተገቢና ዘላቂ መፍትሄ አምጦ ከመውለድ ይልቅ በክስተቶች የትኩሳት ፈረስ ስንጋልብ የእነ አብይ አይነት ሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ወጠመድ ሰለባዎች ስለምንሆን ነው።

ይህ ደግሞ የምንመራው እርኩስነትን/እኩይነት በሚፀየፍ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነው የሚሉትን የየሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ሊቃውንትና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላትንም ሰለባዎቹ ሲያደርጋቸው  የፈተናችን ክብደት ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል። የሰሞኑ የቤተ መንግሥቱና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች መድረከ ተውኔት አዲስ ወይም የሚገርም ባይሆንም የደረስንበትን የውርደትና የአዋራጅነት ደረጃ በግልፅና በቀጥታ አሳይቶናል (ነግሮናል) ።

 እጅግ ከባዱ ጥያቄ ይህ መሪር እውነታ ትምህርት ሆኖን ለእልህ አስጨራሽ ትግልና ለእውነተኛ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን መሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳለን ወይንስ ገና ከዚህ የከፋና የከረፋ ውርደትና አዋራጅነት እንጠብቃለን? የሚለው ነው።

ገና መንበረ ሥልጣኑ ላይ እንደ ተሰየመ የሃይማኖት ተቋማትን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንዴት አድርጎ የርካሽና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታው አካል ሊያደርጋቸው እንደሚችል አስቦና አቅዶ በአስታራቂነት ስም በመቅረብ፣ “ብረትን እንደ ጋለ ምታ” ነውና በራሱ የጉዞ አውሮፕላን አሳፍሮ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ፣ ወደ አገር ቤት ከተመለሱም በኋላ “የዘመናችን ሙሴ ነህ”  የሚል ውዳሴ አብይ አህመድ እንዲቀኙለት አድርጎቸዋል። ከአምስት ዓመታት በላይ በሆነው የመከራና የውርደት አገዛዙ ደግሞ  በቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችና ተከታዮች ፣ እና በአጠቃላይ በሌሎች ንፁሃን ዜጎች ላይ  የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ እዚህ ግባ የሚባል ተገቢ እርምጃ ያልወሰዱ መሆናቸውን በሚገባ አውቋቸዋል።

ለዚህም ነው በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ያመፁትን የዘር ልክፍተኛ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆፖሳት ተብየወች በእርሱ ርካሽ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አማካኝነት ቀኖናን ሽረው ሲሾሙለት ጨርሶ የናቃቸውና በእንወያይ ስም ጽ/ቤቱ ድረስ እየጠራ የሚሳለቅባቸው። ከሰሞኑ ደግሞ  ያሾማቸውን ካድሬዎች  ልብሰ ተክህኖና ልብሰ ጵጵስና አልብሶ እና መስቀል አስጨብጦ የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳው ተዋንያን በማድረግ የዚህ ትውልድ ማንነት፣ ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በእጅጉ ፈትኖታልና ፈተናውን መወጣት የዚህ ትውልድ የቤት ሥራና ሃላፊነት ነው የሚሆነው።

ለማሳያነት ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን እንደሚከተለው ልጥቀሳቸው፦

·         ከስድስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በየሰዓቱና በየቀኑ አገር ምድረ ሲኦል ስትሆን እንኳንስ ለማስቆም “ለሆነውና እየሆነ ላለው አሳዛኝ ሁኔታ ሁሉ ሀዘኔን እየገለፅሁ ፤ይህ ይቆም ዘንድም እንደ የአገር መሪ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ለማለት የገደደው ሴረኛና ጨካኝ ሰው በሃይማኖት መሪነት ስም ጠርቶ ላናገራቸው ወገኖች “በዚህ በፆም ወቅት እስኪ ኑ እና እንነጋገር ያላቸው የመጀመሪያው መሪ” እንደሆነና እድለኞች እንደሆኑ ያምኑ ዘንድ ይሳለቅባቸዋል።ባይገርምም ህሊናን በእጅጉ ያቆስላል።

 

·         ሌላው ሁሉ ቢቀር ስለ ጣልቃ ገብነቱ የቤተ ክህነት አልባሳት ለብሰው የጎሳ/የዘር ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ካድሬነታቸውን በግልፅና በቀጥታ ካስመሰከሩ የሲኖዶሱ አባላት ተብየዎች የተሻለ ማስረጃ  የሚገኝ ይመስል “በሃይማኖታዊ ተልእኳችሁና ሥራችሁ ፈፅሞ ጣልቃ ገብቸ የማላውቅ ድንቅ መሪ ነኝና ልታደንቁኝ ይገባል” በሚል አይነት እጅግ አስቀያሚ የግብዝነት ሰብእና አፋቸውን ሊያዘጋቸው ሲሞክር፤ ካድሬዎቹ ወደ ፈጣሪነት የሚጠጋ አድናቆት እንዲያስተጋቡለት ያለ ንግግር ሲግባባቸው ፣ ሃይማኖትን እንጀራ መብያ ያደረጉ አብዛኛዎቹ ተሰብሳቢዎችን  ደግሞ በጭብጨባና አንገት መነቅነቅ ድንቅ መሪነቱን እንዲያረጋግጡለት ሲያማልላቸውመታዘብ ትእግሥትን በከፍተኛ ደረጃ ይፈታተናል።

 

·         ለስድስት ጊዜ ያህል ወደ ፓትርያርኩ የሄበደት ምክንያት እኩይ ዓላማውንና እቅዱን ከቻሉ እንዲደግፉለት ፣ ካልሆነ ግን ቢያንስ አርፈው እዲቀመጡ ለማስድረግ መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር ይመስል “ብቸኝነት ይሰማቸው ይሆናል በሚል ስድስት ጊዜ ወደ ቢሮቸው ሄጃለሁ” በሚል መጀመሪያም ለርካሽ የፖለቲካ ተውኔት የተዘጋጀውን መድረክ ይበልጥ አርክሶታል።

 

·         የፖለቲካ ወላጆቹን፣ አሳዳጊዎችንና አሰልጣኞችን (የህወሃት ኤሊቶችን) የበላይነት በተሃድሶ ለውጥ ስም ከቤተ መንግሥት መንበረ ሥልጣን አስወግዶ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ስሪቱን ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ብልግና፣ ሴራ፣ ሸፍጥ እና የጭካኔ ሰይፍ ያስኬደበትንና እያስኬደ ያለበትን ግዙፍና መሪር ሃቅ የተትረፈረፈ ነፃነትን ከማስተዳደር (ማኔጅ ከማድረግ) ከባድነት ጋር በማያያዝ ከደሙ ንፁህ እንደሆነ ሲነግራቸው (ደንቆሮዎች እንደሆኑ ሲሳለቅባቸው) ፀጥና ረጭ ብለው የሚያዳምጡ አዳራሽ ሙሉ የሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አባላትን እየመረረንም ቢሆን እንድንታዘብ አድርጎናል።

 

·         የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን ህንፃን በነፃና በእርሱ ችሮት የመለሰላት ይመስል ህንፃ መለስንላችሁ፤ እኛ እኮ አድልኦ አናውቅም ፤ የትኛው መንግሥት ነው …? ” ሲል ተሳልቆባቸዋል።

 

·         “የሰጠናችሁን ቦታዎች አቆሽሻችኋልና ቆሻሻን መፀየፍ አለባችሁ” ሲል አስተማሪ ተማሪዎችን ሊመክርበት (ሊተችበትና ሊያርምበት) ከሚገባው በታች በወረደ  አቀራረብ ሲወርፋቸው ( ሲያጎሳቁላቸው) ማየትና መስማት በእጅጉ ያሸማቅቃል። የታዘበው የቦታ አያያዝ ችግር ቢኖር እንኳ ሲሆን ለቤተ/ክህነቱ ጽ/ቤት ካልሆነም እንደ ማሳሰቢያ ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ መግለፅ ሲቻል በመሪዎች በኩል ቤተ ክርስቲያኗንና ተከታዮቿን ዝቅ ያደረገ መስሎት የለመደበትን የሸፍጠኝነትና የብልግና አንደበቱን ሲከፍት መታዝብ እውነተኛውንና ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊ ጨዋነት ከልብ ለሚያውቅ የአገሬ ሰው በእጅጉ ይረብሻል።

 

·         ስድስተኛ ዓመቱን ሊደፍን ቀናት ብቻ በቀሩት የመከራና የውርደት አገዛዙ ምክንያት ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል ስለ አደረጋት አገር በችግሩ ልክ ደፍረው ባይናገሩም አሳምረው የሚያውቁትን ተሰብሳቢዎች  “ጥቃቅን ክስተቶችን እየተከተላችሁ ትልቅ ችግር እንዳለ ማጋነኑ ይቅርባችሁ፤ አይጠቅማችሁም/አይጠቅመንም” በሚል በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲሳለቅ መታዘብ ትእግሥትን በእጅጉ ይፈታተናል።

 

·         አገርና ህዝብ ከሚገኙበት ለመግለፅ የሚያስቸግር ሁለንተናዊ ውድቀት (ቀውስ) አንፃር እጅግ ግዙፍ፣ አንገብጋቢና ጥልቅ የሃሳብ ልውውጥና ፍጭት ሊነሱበት ይገባ የነበረውን መድረክ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ 326 መግለጫዎች አወጣችሁብኝ በሚል በለመደው የብልግና (ያልተገራ) እና አደገኛ በሆነ አንደበቱ ሲዘላብድ መታዘብ የሚነግረን መሪር እውነት ይህ ትውልድ በትእግሥትና በሌለ ሰላም ስም ከመከራና ከውርደት ጋር እየተለማመደ ከመኖር (መኖር ከተባለ)  ክፉ አባዜ ለመላቀቅ የተሳነው መሆኑን ነው።

 

·         የሃይማኖት መሪዎችን እየጠሩ የማስጠንቀቂያ ሥልጠና በመስጠትና ከካድሬዎች በተሻለ አቀራረብና ይዘት እንዲያስተላልፉ (እንዲያስጠነቅቁ) በማድረግ እና በየሰፈሩ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በማካሄድ ተከበሩ የተባሉትን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት “በተትረፈረፈ ሰላምና ፍስሃ ያስከብርኩላችሁ ድንቅ መሪ እኔ ነኝ” የሚል አይነት የግብዝነት ዲስኩር ሲደሰኩርባቸው መታዘብ ለኦርቶዶክስ ብቻ ሳይሆን ጤናማና ሚዛናዊ ህሊና ላለው ለየትኛውም ሃይማኖት አማኝ የአገሬ ሰው ምነው ይህን ያህል ቁልቁል መውረዳችን? ያሰኛል።

 

·         የአገር መከላከያና የፅታ ሃይሎች ተብየዎች በቤተ ክርስቲያንና በተከታዮቿ ላይ  ለዓመታት የመከራና የጥፋት ዶፍ ሲያወርዱ እንደ ህግና ሥርዓት አስፈፃሚ የመንግሥት አካል መሪነቱ ምን እንዳደረገና ምን እያደረገ እንደሆነ ሲጠየቅ ጠያቂው ሊቀ ጳጳስ በማሳያነት የጠቀሷቸው አካባቢዎች ሃገረ ስብከት ሃላፊ በመሆናቸው ብቻ “ገዳዮችና ተገዳዮች ለእርስዎ ነው የሚቀርቡዎት” የማለቱን ልክ የሌለው የብልግና እና  የትዕቢት ድፍረት ከምር ለታዘበ ባለ ጤናማ ህሊና ሰው የሚሰማውን መሪር ስሜት ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

 

·         “ከአገር ቤት አልፎ በአረብ አገር ቦታ እንዲሰጣችሁ አድርጌያለሁና በቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ላይ ስለደረሰው መከራና ጥፋት አትጠይቁኝ” አይነት ምላሽ ሲሰጥ ህሊናው የማያስጨንቀው ሰው መሪ ከሆነባት አገር የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን መጠበቅ ራስን ከማታለል አያልፍም።

 

·         የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላትን ሰብስቦ ሥልጣነ መንበሩን ለመንጠቅ ወደ ላይ የሚንጠራሩትን (መሰላሉን የሚረግጡትን) ነቅተው ይከላከሉለት ዘንድ በእንስሳት ምሳሌነት ሲነግራቸው በአድናቆት ፈዘው ሲያደምጡት ከምር ለታዘበ ባለ ሚዛናዊ ህሊና ሰው ምነው ምኑ ነካን የሚል ከባድ ቁጭት ሳይፈጥርበት የሚቀር አይመስለኘም።

 

·         ከእስልምና ሃይማኖት መሪዎችና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላት ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ የተቸረው ውደሳና ምርቃት ደግሞ ምነው እነዚህ ናቸው እንዴ “እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው” የሚለውን ድንቅ ትርጎሜ የሚሰብኩን? የሚል ፈታኝ ጥያቄ ያስነሳል። ስድስት ዓመታት ሊሞላው ቀናት ብቻ በቀሩት የአገዛዝ እድሜው በንፁሃን ዜጎች ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የመከራና የውርደት ዶፍ ያወረደውንና እያወረደ ያለውን የአገር መሪ ተብየ ያለምንም ይሉኝታ የእግዚአብሔርን (የአላህን) ስም  እየጠሩ የአድናቆት፣ የምሥጋና እና የምርቃት ቃላትን የማዥጎድጎዱ አሳዛኝ እውነታ (tragic reality) የሚነግረን ውድቀታችን የአንድና የሁለት የሃይማኖት ተቋማት ሳይሆን የሁሉም መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

እኩያን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ፈጣሪዎችና ቁማርተኞች ደግሞ ይህንን ዘመን ጠገብ የሆነ የአስከፊ ውድቀት ልማዳችንን አሳምረው ስለሚያውቁ አሳምረው ተጫውተውብናል፤ አሁንም ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ይጫወቱብናል ።

መቸም የአገራችን የሃይማኖት ተቋማት በንፁሃን መከራና ደም ለሚነግዱ ነጋዴዎች ሰለባነት ራሳቸውን አሳልፈው በሰጡና እየሰጡ በቀጠሉ “መሪዎቻቸው” ምክንያት ምን ያህል አሳፋሪ  ሁኔታ ላይ እንደ ወደቁ ስድስት ዓመታት እየሆነው ካለው የአብይ አህመድና አገዛዝ ግዙፍና መሪር ሃቅ  በላይ የተሻለ ማስረጃ አይገኝም።

የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ሊቃውንትና ሰባኪዎች ይህንን ግዙፍና መሪር እውነታ ከትናንት ዛሬ ከምር ተረድተውና እጥፍ ድርብ የሆነውን (የመንፈሳዊና የመልካም ዜግነት) ሃላፊነትና ተግባር ተወጥተው እኩያን ገዥ ቡድኖች ምድረ ሲኦል ያደረጓትን አገር ለመታደግ መስዋዕትነት መክፈል ቢሳናቸው እንኳ ፖለቲካ ወለድ የሆነውን መከራና ውርደት በሚመጥን አቋምና ቁመና ለመገዳደር ይሞክሩ ይሆናል ብሎ የጠበቀው ወገኔ ቁጥር ቀላል የነበረ አይመስለኝም።

ከሰሞኑ ያየነውና የታዘብነው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው። ይህ ደግሞ የሚነግረን (የሚያሳየን) ዘመን ጠገብና አስከፊ ከሆነው አጠቃላይ ማለትም ከፖለቲካዊ፣ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማህበራዊ፣ ከሞራላዊ፣ ከሥነ ልቦናዊ፣ ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ የቀውስ (የውድቀት) አዙሪት ሰብረን ለመውጣት የሚጠብቀን ፈተና በእጅጉ ከባድ መሆኑን ነው።

 

ታዲያ ከዚህ ክፉ አዙሪት ለመውጣት አማኝነታችን፣ ፆማችን ፣ ፀሎታችን፣ እግዚኦታችን ወይም ሞህላችን ፣ ስብከታችን፣ ስግደታችን፣ ነቢይነታችን፣ የሃይማኖት አባትነታችን (መሪነታችን)፣ ወዘተ ወደ ተግባር ሊተረጎም የሚችል እና በነፃነት ጥረንና ግረን እንኖር ዘንድ ፈጣሪ በአምሳሉ እንደፈጠረን ሰብአዊ ፍጡርነታችን የሚስማማንን ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ከምር ማረጋገጥ ይኖርብናል።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop