ጣቱን እያፍተለተለ ድስኩር የሚደሰኩረውን ወላዋይና አድር ባይ ምሁር ከማዳመጥ ተእያንዳንዱ ቆራጥ ፋኖ አንደበት የሚወጣውን ቃል መስማት መንፈስን እንደ መስከረም አበባ ያድሳል፡፡ ሕዝባቸውን ከዘር ፍጅት ለማዳንና አገር ለመገንባት ወጣቱን የሚያነቁት ፋኖዎች “የተጎዳችውንና የጠፋችውን ኢትዮጵያን እየፈለግን ነው” ሲሉ ይደመጣል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ወጣት ፋኖዎች ያደጉት ኢትዮጵያ እየተጎዳች ባለበት እርጉሙ ይህ አድግ ዘመን ቢሆንም የተጎዳችውና የጠፋችዋ ኢትዮጵያ ምን ትመስል እንደነበር ልባቸው፣ ደማቸው፣ አጥንታቸው፣ መንፈሳቸውና ታሪካቸው እንደሚነግራቸው ቃላቸውና ምግባራቸው ይመሰክራል፡፡
ታሪክ በብራና የጣፈው ፋኖ ክፉኛ የተጎዳችውን ኢትዮጵያ መስራች፣ ገንቢና ጠባቂ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ይህቺ ፋኖ የሚፈልጋት የጠፋችዋ ወይም ክፉኛ የተጎዳችዋ ኢትዮጵያ የምትመስለው ምንድን ነበር?
አንደኛ፡-ሊጥ የሚሰረቅባት ቀርቶ ወድቆ የተገኘ የወርቅ ክምርም የማይነካባት አገር!
አንድ በቅርቡ ቶክዮ ጃፓን ለጉብኝት ሄደው የተመለሱ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰው ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት ቦርሳቸውን ከእነገንዘባቸው ባቡር ውስጥ ዘንግተውት ይወርዱና ሆቴላቸው ሲደርሱ አስታውሰው ደንግጠው ሲብከነከኑ የሆቴሉ ሰራተኞች ያዩአቸዋል፡፡ የሆቴሉ ሰራተኞችም “ጃፓን አገር ወድቆ የተገኝ ነገር መውሰድ ነውር ስለሆነ አይስጉ ይገኛል” ብለው ቢያጥናኗቸውም አላምን ብለው ተስፋ ቆርጠው ይተኛሉ፡፡ በነጋታው ተጠርተው ቦርሳቸውን ከእነገንዘባቸው ሲወስዱ በዚች ምድር እንደ ጃፓን ያለ አገር እንደሌለና ኖርም እንደማያውቅ ደምድመው ይመለሳሉ፡፡ በተመልሱ በሳምንት ውስጥ ይኸንን ሲያጫውቱኝ እኔ ያደኩበት ማህበረሰብ እንኳን ወድቆ የተገኘ እቃ ወይም ገንዘብ ሊወስድ ገንዘብ እንካ ብለው ሲሰጡት እጅዎን ሲዘረጉም እንደ ክብረ ነክ እየቆጠረ እምቢ የሚል ነበር ስላቸው ለጉብኝት ሄደው የይህ አድግን “ኢትዮጵያ” አይተው ስለነበር ለማመን ተቸገረው ከንፈራቸውን ሸርመም አርገው የጥራጣሬ ፊት አሳዩኝ፡፡ ይህ አድግ ክፉኛ የጎዳትና ፋኖ ፈልጎ እንደገና ተክብሯ ለማቆም ደሙን የሚያፈስላት ኢትዮጵያ እንኳን ሊጥ ተእነ ቡሀቃው (የሊጥ እቃ) ልትሰርቅ ወድቆ የተገኝን ወርቅም የማታነሳ ቀብራራ ወይዘሮ ነበረች፡፡
በዚች ቀብራራ ኢትዮጵያ ሳድግ በሰባት ዓመት እድሜዬ አካባቢ ተቤታችን አጥር ግቢ ውጪ ስጫወት ሁለት አስርና አንድ አምስት ሳንቲሞች አገኘሁ፡፡ የአገኘኋቸውን ሳንቲዎች በቀኝ እጄ ያዝኩና ወደ ቤታችን ሮጬ እናቴን “እቴቴ ሃያ አምስት ሳንቲም አገኘሁ!” ስል ጮህኩ! ተዚያም የልጅ ጣቶቼን ፈልቅቄ ሳንቲሞቹን አሳየሁ፡፡ እናቴ ተእጆቼ ያሉትን ሳንቲሞች ላለመንካት እግዜርን እንደሚለማመን እጇን ወደ ሰማይ ዘረጋችና ሁለት ሜትር ያህል ወደ ኋላ ተስፈነጠረች፡፡ እጆቿን ወደ ጣራው እንደዘርጋችም “የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው!! ሂድ ታገኝህበት ጣልና እጅህን በሳሙና ሶስት ጊዜ ታጠብ!” ስትል አዘዘችኝ፡፡ በታዘዝኩት መሰረት ሳንቲሞቹን ታገኘሁበት ጣልኩና ሶስት ባለችው ላይ አራት ጨምሬ ሰባቴ ታጥቤ ቁንቋኑን ተእጆቼ አስወገድኩ፡፡
ከብዙ ዓመታት በኋላ ዛሬም “የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው!” የሚለው የእናቴ ድምጥ እንደ ቤተክርስቲያናችን ደወል ይሰማኛል፡፡ በዚህ የእናቴ ቅዱስ ቃል የይህ አድግ ዘመን የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሚዘርፉ ወሮበላ ካህናትን ስመዝናቸው ዲያብሎስ ያሰገዳቸው ውቃቢዎች መስለው አንደ አባጨጓሬ በሃምሳ እግር አፈር ላፈር ሲርመሰመሱ እንደ ምስጥም የሰው ሥጋ እያነከቱ ሲበሉ ይታዩኛል፡፡ እነዚህ ለዲያብሎስ የገበሩ ካህናት እንኳን የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን አምነው የሰው ኪስ ሊምሩ ተክርስቶስ ኪስም እየዘረፉ ምድራዊ ፍላጎታችውንና ስስታቸውን ሊያረኩ ተገዳማቸው ወጥተው እንደ ፓስተሮች በየከተማው ሲቅበዘበዙ ይታያሉ፡፡ ሕዝቡን ተጠመቁ እያሉ እነሱ በምእምናን አስራት አሜሪካና አውሮጳ ቁርጠትና ትውኪያ ይታከማሉ፡፡
በተመሳሳይ መንገድ የይህ አድግ ዘመን ነፍሰ-ገዳይ ባለስልጣኖች በድሃ ጉረሮ እንጨት እየሰደዱና የአገሪቱን ሀብት እየዘረፉ የውጭ አገር ባንኮችን ያደልባሉ፡፡ ጎስቋላ ሕዝብ ሥም እየተበደሩና እየለመኑ ልጆቻቸውን በውጪ አገር ሽቅብ እስተመሽናት ያደርሳሉ፡፡ ሚስቶቻቸውን በሰዓታት ውስጥ እስከ አንድ ሚሊዮን ያሜሪካ ዶላር ለሸቀጥ ልብስ ሺመታ እንዲያጠፉ ያስችላሉ፡፡ የጎሰጎሱት ቁንጣንና ቁርጠት በሆናቸው ቁጥር “በቻርተር” አውሮፕላን እየበረሩ አሜሪካ፤ አውሮጳ፣ ኤሽያ፣ እስራኤልና ደቡብ አፍሪካ መታከሚያ ያደርጋሉ፡፡ ቁንቋኑ የሰው ገንዘብ እንደ ሂትለር፣ ኢዲ አሚን፣ ጋዳፊና ለገሰ ትቢያ ተመሆን እንደማያድናቸው መገንዘብ ተስኗቸው ሳይበሉት መቃብር ገብተው ተሰማይ ቤት ለችሎት ይቀርባሉ፡፡
ያለ ቀደምት ታሪኳ ኢትዮጵያ ቤተመንግስቷም ሆነ የሃማኖት ተቋሞቿ ሊጥ ሳይቀር በሚዘርፉ ቀማኞት ስለተሞሉ ፋኖዎች ኢትዮጵያ በእነዚህ ወሮበሎች የተሰወረችዋን ኢትዮጵያ መልሶ በሁሉት እግሯ ለማቆም ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡
ሁለተኛ፡-ሰው በሰውነቱ የሚከበርባትና ቤት ለእምቦሳ ብሎ ለእንግድነት ሲመጣም እንግዳ አስተናጋጁ ድግስ ደግሶና አልጋውን ለቆ የሚያስተናግድባት አገር!
አማራ እግዚአብሔር ሰውን ባምሳሉ ፈጠረው ብሎ ስለሚያምን የማያውቀው ሰው ከቤቱ ሲመጣ የሚለው የእግዚአብሄር እንግዳ መጣ ነው፡፡ ይህንን የእንግዚአብሔር እንግዳም እርሱ አዘውትሮ የማይበላውን ድንቅ ድግስ ደግሶ ያበላል፤ የክት ጋቢውን አውጥቶ ያለብሳል፤ አልጋውን ለቆ ያስተኛል፡፡ እንኳን በእንግድነት የሄደውን ለንግድና ለትርፍ የሄደውን ሁሉ አብልቶ አጠጦ ያሳድራል፡፡ በልጅነታቸው አባይን እየተሻገሩ ይነግዱ የነበሩት አቶ ደብላ ዲንሳ በአንድ ወቅት “ጎጃም ስትነግድ ስንቅ አያስፈልግም” ያሉትን ልብ ይሏል፡፡ ኢመለኮታዊና ኢሰብአብዊ የሆነው ጭራቅ ይህ አድግ ከመጣ ጀመሮ ሰው የሚታወቀው በሰውነቱ ሳይሆን በቋንቋ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዱ ቋንቋ ተናገሪ ሌላውን እንደ ጠላት ወይም እንደ ሌላ ፍጡ እየቆጠረ እንኳን በእንግድነት ሊያስተናግድ ከሰፈሩና ከቤተ እምነቱ እየገባ አንገቱን በገጀራ የሚቆርጥባት፣ ብልቱን በካራ የሚከትፍባት፣ እሬሳውን እንደ በግ ዘቅዝቆ የሚሰቅልባት፣ ከእነነፍሱ በእሳት የሚቃጥልባት፣ አስከሬን ምድር ለምድር የሚጎትትባት አገር ሆናለች፡፡ በዚህም ምክንያት የድሮዋ ኢትዮጵያ የጠፋችበት ፋኖ ፈልጎ እንደገና ሰው በሰውነቱ የሚከበርባትና ሰብአዊነት የሰፈነባት አገር እድትሆን ተጭራቆች ጋር በዋደቅ ላይ ይገኛል፡፡
ሶስተኛ፡-“የተናገርኩት ከሚጠፋ የወለድኩት ይጥፋ” የሚሉና በቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ፈርደው ዝንፍ የማይል ፍርድ የሚሰጡ ሽማግሌዎች አገር!
አውሮጳውያንና በተለያየ ጣኦት በሚያመልበት ዘመን በአንድ አምላክ ማመንን ያስተማረችው ኢትዮጵያ መለኮት በሰራው ሚዛን ለክቶ በፍትህ የተሽሞነሞነ የሽምግልና ፍርድ የሚሰጥባት አገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ለራሳቸው ልጅ፣ እናት፣ አባት ወይም እህትና ወንድም ፍጡም ሳያደሉ ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጡ ሽማግሌዎች የሚኖሩባት ምድር ነበረች፡፡ ልጅ ሳለሁ ሁለት ጎረምሳ ወንድማማች ያጎቴ ልጆች መንገድ ገፍተው የተከሉትን ተክላቸውን የረገጠ አንድ ሰው ፈነከቱ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ፈንካቾችና ተፈንካቹ ለእርቅ ተስማሙ፡፡ የፈንካቾቹ አባትና ሌሎች አጎቶቼ ሽማግሌ የመምረጡን ዕድል ሙሉ በሙሉ ለተፈንካቹ ሰጡ፡፡ ይህንን ሽማግሌ የመምረጡን እድል የተረከበው ተፈንካችም የፈንካቾችን አባት፣ አጎታቸውንና የእኔን አባት ለሽምግልና መርጧቸው እርፍ አለ፡፡ ተፈንካቹ ለሽምግልና የመረጣቸው የፈየንካቾች አባት፣ ሌላው አጎታችንና አባቴ የተጣለባቸው አደራ ከሰማይ የወረደ ያህል ተሰማቸው፡፡ ይህ አደራ የከበዳቸው እነዚህ ሽማግሌዎች ባንድ ድምፅ በልጆቻቸው ፈርደው ከዚያ በፊት በዚያ ዘመን ለእንደዚህ ዓይነት እርቅ ተከፍሎ የማይታወቅ ገንዘብ እንዲከፍሉና ድንጋይ ተሸክመው እግሩ ስር ወድቀው ተፈንካቹን ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገው አስታረቁ፡፡ በሽማግሌዎች ፍትሐዊ እርቅ የረካው ተፈንካችም “ፍትህ ይበቃኛል” በሚል መንፈስ የሰጡትን ገንዘብ አልቀበልም ብሎ መለሰው፡፡ ፈንካቾችም ገንዘቡን አንቀብለም ብለው ትተውለት ሲሄዱ ሌላ ጊዜ ከደጃፋቸው ጣለለቻው፡፡ ሽምግልናው እርቅን ወለደ እርቅም ፍትህን አነገሰ፡፡ ፍትህን ያነገሰው እርቅም ሰላምና ፍቅርን አሰፈነ፡፡ የሰፈነው ፍቅርም ለጋብቻ አደረሰ፡፡
በይህ አድግ ዘመን እንደ አረም የበቀሉ እንደ ኤፍሬም ይስሀቅና አንዳንድ ለነፈሰ ገዳይዎች በሎሌነት የሚላላኩ አውደልዳይ ካህናትና ጳጳሳት ቢሆኑ ኖሮ ግን የተፈነከትው ከፈንካቾች እጅ ወድቆ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያደርጉ ነበር፡፡ ፋኖዎች በኤፍሬም ይስሃቅ ወለፈንዲ የድርድር መንገድ የሚወላገዱ ሆዳምና ሎሌ የእንጨት ሽበቶች፣ ካሃናት፣ ጳጳሳት፣ አቡንና ሼሆች ለውሸት ድርድር ሲያረጠርጡ ደጋግመው ስላዩ ኢትዮጵያ ጠፍታለችና ፈልገን አግኝተን የጥንቱን የክብር ካባ እናልብሳት ብለው ቁልቁለቱን ይወርዳሉ፣ ታራራውንም ይወጣሉ፡፡
አራተኛ፡-ከሀዲና ባንዳ ገዥ መሆን ቀርቶ አንገቱን አቀርቅሮ ለመኖርም የሚሸማቀቅባት ምድር!
በኢትዮጵያውያን ባህል ባንዳ መሆን ክርስቶስን አሳልፎ ከሰጠው ይሁዳ የበለጠ ያዋርድ ነበር፡፡ በሞሶሎኒ አገልጋይ ልጆች የተዋቀረው ይህ አድግ ወንበር ተያዘ ጀምሮ ግን ባንዳነት የሚያስሾምና የሚያስከብር ሆኖ አረፈው፡፡ ይህ አድግ እንኳን ለምእራባውያን ማገልገል ለሱዳንም ለም ምሬት የሚሰጥ ባንዳ ሆኖ ሰላሳውን ዓመት እንዳለፈው መላው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው፡፡ ይህ አድግ ቁጥር አንድም ሆነ ቁጥር ሁለት ለአማራ የሚሾመው አማራውን የሚያስጨፈጭፍና የሚያደሀይ የአማራ የእንግዴህ ልጅ ባንዳ በላንባ ዲና ፈልጎ ነው፡፡ ለሌላው የማህበረሰብ ክፍልም ገዥ የሚመርጥለት የወጣባትን ማህበረሰብ እያወረደ ለይህ አድግ ባንዳ ገዥዎች የሚያስገብር ባንዳ መርጦ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ ያለ ታሪኳ በባንዳዎች የተሞላችና የምትገዛ ስለሆነች ለፋኖ ጠፍታበት ፈልጎ አግኝቶ መልሶ “አንተ ማነህ እኔስ ማነኝ” በሚሉና በራሳቸውና በሕዝባቸው በሚተማመኑ ብቁ መሪዎች የምትመራ አገር ለማድረግ በመዋተት ላይ ነው፡፡
አምስተኛ፡-የእምነት ፈናፍንቶች፣ ነፍሰ-ጋዳይ አገልጋዮችና ሆዳሞች የቤተክርስትያን ጳጳሳትና የመስጊድ ሼሆች የሚሆኑባት ሳትሆን ከእምነት ብቃታቸው የተነሳ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከዋሻና ገዳማቸው የሚኖሩ የዱር እንሰሳት የሚያከብሯቸው የእምነት አባቶች አገር!
የበቁት ቀደምት የኢትዮጵያ አባቶች በመንፈስና በእምነት ብቃታቸው ድርቅ እንደሚመጣ ሲታያቸው ሕዝብን የማሳወቅ ችሎታ ነበራቸው፡፡ ጠላትን መቼ አገር ሊወር እንደሚችልም ተንብየው ሕዝብን እንዲዘጋጅ የማድረግ ኃይል ነበራቸው፡፡ ቀደምት የኢትዮጵያ የእምነት አባቶች እምነትን ከሕዝብ የእለት ከእለት ኑሮ ጋር በማቆራኘት ችሎታቸው በዓለም አቻ ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያውያን የኩታና የቀሚስ ጥለቱ፣ የጸጉር አያያዙ፣ የሐዘንና የደስታ ወጉ ሁሉ ኢብራይስጡም፣ ክርስትያኑም ሆነ እስላሙ ከሚጋራው ብሉይ ኪዳን ወስደው በኢትዮጵያውያን ኑሮ ውስጥ የቀረጹት ብዙ ትርጉም ያለውና ወደር የሌለው መንፈሳዊ ሐብት ነው፡፡ የዛሬዎቹ የሃይማኖት መሪ ተብዮች ግን የሚሰሩት ሁሉ የእነሱን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የአሁኖቹ ጳጳስ፣ አቡንና መጅሊስ ተብዮዎች የሚመረጡት በባንዳ መሪዎች፣ የሚያገልግሉት እግዚአብሔርንና ሕዝብን ሳይሆን ቀጭን ትእዛዝ የሚሰጧቸውን ባንዳ መሪዎች ነው፡፡ የሚሰግዱትም እምነትና እውነትን አጣምሮ ለያዘው መለክኮት ሳይሆን ወንበር ለሰጧቸው ነፍሰ-ገዳይ ገዥዎች ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ፋኖ የእነዚያ የእውነተኛ እምነት አባቶች የእነ ቅዱስ ዘራብሩክ፣ ቅዱስ ተክለሃይማኖት፣ ክርስቶስ ሰምራና ቢላል አገር ኢትዮጵያ ጠፍታበት ፈልጎ አግኝቶ መልሶ እግዚአብሔርን የሚታዘዙና ምእመናን የሚያገለግሉ አገር ለማድረግ እንደ ቅድመ አያቶቹ እየተዋደቀ ነው፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያ ከሊጥ ዘራፊዎች፣ ከባንዳዎችና ከሰይጣናዊ የቋንቋ ካራ የጸዳች፣ ሰው በሰውነቱ የሚከበርባት፣ እንግዳ በድሎት አምሽቶ የሚያድርባት፣ “የተናገርኩት ከሚጠፋ የወለድኩበት ይጥፋ!” እያሉ ዝንፍ የማይል ፍርድ በሚሰጡ ሽማግሌዎች የተሞላች፣ እንደነ ነቢዩ ኢሳያስ በእምነታቸው ጸንተው የወደፊቱን መንተንበይ የሚችሉ የበቁ የእምነት አባቶች አገር እንድትሆን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ ማነው? የጠፋችዋን ኢትዮጵያን ፈልጎ አግኝቶ የተጎዳውን አካላዊና መንፈሳዊ ጎኗን ለመጠገን የሚታገለውን ፋኖ የማይደግፍ ኢትዮጵያዊ በምን ቀን የተፈጠረ ነው?
ጥር ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.