ሰማእታት ቅዱሳን ይኸን ጉድ አላዩ!
እነ አቡነ ጴጥሮስ ይኸን አልታዘቡ፡
አድማሱ ጀምበሬ ይኸንን አልሰሙ፣
ፓትርያሪክ ጳጳሳት ለፋሽሽት ሲሰግዱ፡፡
ተምእመናን አስራት ደሞዝ እየዛቁ፣
አስራት አስገቢዎች በድሮን ሲመቱ፣
በእንጀራ ታፍነው ጳጳሳት ጪጭ አሉ!
በበጎቻቸው ደም ስልጣን አስከብረው፣
ተበግ አራጆች ጋር ሲያድሩ ተወባርተው፣
የደመ-ነፍስ ያህል ስግጥጥ እንኳ አይላቸው፡፡
ለሕዝብ መድህንነት ሲሰቀል ጎልጎታ፣
ለራሱ ድሎት ሲል ጳጳስ ሕዝብ አሰዋ፡፡
ጴጥሮስና ጳውሎስ በቄሳር ሲቀሉ፣
የዛሬ ጳጳሳት ሹመት ተቀበሉ፡፡
ተመሐል ደረት ላይ መስቀል አንዠርገው፣
ተራስ ቅላቸውም ያማረ ቆብ ደፍተው፣
ለአባይ ሲታዘዙ ትንሽ አይከብዳቸው፡፡
ገዳማት ተቃጥለው ባህታውያን ሲያልቁ፣
ፓትርያሪክ ተባይ አቡኑ ጳጳሱ፣
ተአቃጣዮች ጋራ ግብር ይበላሉ፡፡
እንዲናገር ቢያዝዝ ነፍስ እስተንፋስ ያለው፣
የደም የስደት ጎርፍ በዓይን ብረት አይተው፣
ጳጳሳት ጪጭ አሉ በቀፈት ታፍነው፡፡
አማሮች ተአሕዛብ ተአውሬ ሲፋለሙ፣
በአማራ አስራት መፅዋእት የሚንፈላሰሱ፣
እንጀራው አንቋቸው ጳጳሳት ጪጭ አሉ፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ህዳር ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.