ሃይማኖታችን የቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ የሚባል ነገር አያውቅም እንዴ?

November 11, 2023

November 11, 2023

T.G
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንኳንስ ለህዝብ እረኝነት ሃላፊነትና ተልእኮ ተሰጥቶናል  በሚሉት ልክ በአንፃራዊነት ይበል በሚያሰኝ መጠንና ደረጃ ላይ ያለመገኘታቸውን  መሪር እውነት አግባብነትና ገንቢነት አለው ብየ በማምንበት መጠንና ደረጃ  መሠረት ከዚህ በፊት ባቀረብኳቸው አስተያየቶቼ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ይህ የአሁኑ አስተያየቴም ከዚሁ ግልፅና ቀጥተኛ እምነትና አቋም የሚነሳ ነው ።

አዎ!  የጎሳ አጥንት ስሌት ፐለቲካ ቁማርተኞች እና ሃላፊነታቸውን በሚጠበቅባቸው ደረጃ  ለመወጣት በተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎች መካከል ባለው አስነዋሪ መተሻሸት ምክንያት ከገባንበት  አዙሪት መውጣት ካለብን እና ለሁላችንም  እና ሃይማኖትን ጨምሮ ለሁሉም አይነት ነፃነቶቻችን የሚተበጅ አገርና ሥርዓት እውን ማድረግ ካለብን መናገርና መነጋገር ያለብን በዚህ ልክ ነው።

በሃይማኖት ስም በምናደርገው አላስፈላጊ መሽኮርመም እና ነውርና ሃጢአት ያልሆነውን ነውርና ሃጢአት እያስመሰልን እኩያን ገዥዎች አደንቁረው የሚገዙትን መከረኛ ህዝብ ይበልጥ ማደንቆር በፍፁም ልንታገሰው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ይህንን አስቀያሚ ሁኔታችንን ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር የፈጠረን እውነተኛው አምላክም ይፀየፈዋል።

ይህንን ስል የሃይማኖት አባቶችን መተቸት (ማሄስ) ስህተት ብቻ ሳይሆን ሃጢአት እንደሆነ ተደርጎ እንዲያምን የተደረገ እጅግ አብዛኛው የዋህ አማኝ ቁጥሩ የትየለሌ እንደሆነ በሚገባ እገነዘባለሁ። ለዚህ ያለኝና የሚኖረኝ ምላሽ ዘመን ጠገብ ለሆነው እና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ለቀጠለው አገራዊ መከራና ውርደት ፍፃሜ እንዳያገኝ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሃይማኖታዊ እምነት እና የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓቱ በአስከፊ ሁኔታ ሲደበላለቁ አፋዊ ሳይሆን መሬት ላይ ወርዶ በጎ ውጤት ሊያስከትል በሚችል አቋምና ቁመና ሃላፊነቱንና ግዴታውን የሚወጣ  የሃይማኖት አባት ፈልጎ ለማግኘት ብርቅ ሲሆንብን የሃይማኖት አባትነትን አይነኬ ወይም አይደፈሬ ማድረግ ፈፅሞ ትክክል አይደለምና የሚሻለው መሪሩን እውነት መጋፈጥ  የሚል ነው።

ዛሬም እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ ድህረ ገፆችን ስጎበኝ በምድረ አሜሪካ (USA) በካሊፎርኒያ ግዛት ለታቀደው የገዳም ምሥረታና ግንባታ በእሸቱ መለሰ (ዶንኪ ቲዩብ በሚልው) ሶሻል ሚዲያው አማካኝነት የተካሄደው ዘመቻ መሳካቱን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የእናመሰግናለን እና ስለ ቀጣይ የገንዘብ (የዶላር) መዋጮ አስፈላጊነት በአንፅንኦት የተጠየቀበትን አጭር ፕሮግራም በአንክሮ ተመለከትኩት (ተከታተልኩት)።

ሁሌም እንደምለው እንደ መርህና እንደ አጠቃላይ አወንታዊ እውነት ጤናማና ሚዛናዊ ህሊና ያለው ሰው እንኳንስ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ሌላም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተቋማት በዓለም ዙሪያ ቢስፋፉ ስለ ዓላማቸው ትክክለኛነት፣ ስለ ተግባራዊነታቸው ሂደት እና  ስለ ግባቸው  ውጤታማነት ጥያቄ  ያነሳ እንደሆነ እንጅ ለምን ይስፋፋሉ የሚል ደምሳሳ አስተያት ወይም ቅሬታ የሚያቀርብ አይመስለኝም።

ዘመን ጠገብ የሆነውና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የእኛነታችን፣ የምንነታችና የማንነታችን መሪር እውነታ ግን ከዚህ አጠቃላይ መርህና እውነት በእጅጉ የራቀና የተለየ ነው።  ሃይማኖት የሰው ልጅ  በገዛ እጁ ከገባበት መከራና ፍዳ ነፃ ለመውጣት እንዲችልና በሚሠራው በጎና ገንቢ ምድራዊ ሥራው ተስፋ የሚያደርገውን ከሞት በኋላ ህይወት ይወርስ ዘንድ  ተፈጠረ  እንጅ ሰው ለሃይማኖት የተፈጠረ ይመስል ህዝብ ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል እየማቀቀ በሚገኝበት መሪር እውነታ ውስጥ  ለባህር ማዶ ገዳምና ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት የገነት በር መክፈቻ ቁልፍ እንደሆነ አድርጎ መስበክ በፍፁም ትክክል አይሆንም።

አገረ እግዚአብሔር ናት የምንላት ኢትዮጵያ በባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ምክንያት የለየላት ምድረ ሲኦል እየሆነች በቀጠለችበት በዚህ መሪር ሁኔታና ወቅትም “ለባህር ማዶ የገዳም ማሠሪያና ማስፋፊያ ለሰጣችሁን ዶላር እግዚአብሔር ደስ ብሎታል ፣ እኛም ደስታችን ወሰን የለውም”  የሚል የምሥራች ሲነግሩን የዚያን ህዝብ  ልክ የለሽና አሰቃቂ  መከራና ውርደት የሚያስተውል ዐይነ ህሊና  ቢኖራቸውና የሚሰማቸውን ቢነግሩን ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር።               እንኳንስ ስለ ገዛ ወገን ስለማነኛውም ሰብአዊ ፍጡር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ  የማይገደው የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት ምን አይነት መሪነት  እንደሆነ ለመረዳት የሚቻል አይመስለኝም።

በየመንገዱ፣ በየጓሮው፣ በየአደባባዩ ፣ በየሸንተረሩና በየጫካው  የሚጎርፈውን የአያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ደም እና እንባ  በአይነ ህሊናቸው ፣ በቅንና ሚዛናሚ ሰብአዊ ፍጡርነታቸው፣ እና መልእክተኞቹ ነን በሚሉት  በፈጣሪ ስም ተመልከተው እና የባህር ማዶ ኢሚዛናዊነትና አሳሳችነት (highly skewed and  delusional) ፕሮጀክታቸውን ተመልሰው በእውነተኛ የሃይማኖት አርበኝነት መንፈስ ከምር ቢመረምሩት መልካም ነው።  ።

የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ናችሁ እያሉ የሚሰብኩት (የሚያስተምሩት) እጅግ አያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ወገን የሚኝገበትን መሪር እውነት በቃልም ሆነ በተግባር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት  ለመስጠት በሃይማኖት መሪነት የመጀመሪያው  ረድፍ ላይ መገኘት ባይቻላቸውም እንኳ ማነኛውም ቅን ልቦና እና ሚዛናዊ ህሊና ወይም የሞራል ልዕልና ያለው የአገሬ ሰው ሊረዳውና ሊያደርገው በሚችለው መጠንና ደረጃ ላይ ለመገኘት ሲቸገሩ መታዘብ በእውን ያሳዝናል፤ የስፈራልሞ። አዎ! ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ህይወት የምትበጅ አገርና ለሁሉም ልጆቿ የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ የሚደረገውን እጅግ መሪርና እልህ አስጨራሽ  ህዝባዊ ተጋድሎ ለማምከን በህዝብ ላይ እጅግ ጨካኝ ሰይፋቸውን የመዘዙ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥዎችንና ግብረ በላዎቻቸውን በቀጥታና በግልፅ ለመገሰፅ ወኔ የሚገደው የሃይማኖት መሪና ሰባኪ በአንፃራዊነት ከመሠረታዊ አገልግሎት በላይ የሆኑ አገልግሎቶች ያልገደዱትን የአሜሪካ ኗሪ ዳያስፓራ ቤተሰብን ለዘመናት በዘለቀ እና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም የሚከብድ የመከራና የውርደት ዶፍ እየወረደበት ካለው የአገር ቤት ቤተሰብ (ህዝብ) እኩል አሳሳቢ አስመስሎ በማቅረብ በሚሊዮኖች የሚሰላ ዶላር  ለምናሠራው ገዳም የቅድሚያ ቅድሚያ ስጡልን በሚል ዘመቻ መጠመድ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች ነው።

የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ ግድ የሚለውን የመከረኛውን ህዝብ መሪር እውነት  የሳተውን የሃይማኖት “መሪነታቸውን” በአገር ውስጥ ምንም እንዳልተፈጠረና እየተፈጠረ እንዳልሆነ የሚያስመስሉ እና የሶሻል ሚዲያ ቢዝነስን የሚያሳልጡ ቪዲዮችን በማዘጋጀትና በማቅረብ በሚታወቅ የሶሻል ሚዲያ መስኮት ብቅ ብለው  የፈጣሪ ድንቅ ሥራ ስለመሆኑ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ  ህሊናቸው  ሊሞግታቸው አለመቻሉ  ባይገርምም ያሳዝናል።

አዎ! ሌላው ቢቀር በዚህ “የእንኳን ደስ ያለንና የእናመሰግናለን” መድረክ ላይ የመከረኛውን ህዝብ መከራና ስቃይ ሳያነሱ (ሳይጠቅሱ) እና ምን መደረግ እንዳለበት ሃሳብ ሳይሰጡ የማለፋቸው ወለፈንዴነት (paradox) ሃይማኖትን የሰብአዊ መብት የማይገደው አስመስለውታል።

አዎ! በዚህ አይነት አጋጣሚ ግዙፍና ግልፅ ስለሆነው የንፁሃን ዜጎች መከራና ሰቆቃ ጠቅሶ ለማለፍ አለመፈለግ ወይም ሆን ብሎ መዝለል ከምር የሆነ የሃይማኖት መሪነትን  ፈፅሞ አያሳይም። ለዚህም ነው እንዲህ አይነቱ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ ከሚጠይቀው ፈታኝ ሁኔታ እየሸሹ ለፈጣሪ ማደሪያ የሚሆን ቤተ እምነትና ገዳም እየሠራ ስለሆነ ወይም ልናሠራ ስለሆነ ዶላር በመልገስ የፅድቅን መንገድ አዘጋጁ ማለትን ባርኮ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ የለም ብሎ መከራከር ስህተት የማይሆነው።

ለመሆኑ በእኩያን ገዥዎች በተከፈተውና እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ፀሎት እና ምስጋና ማድረሻ ቤተ ክርስቲያን ከማጣታቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውና የእምነት ልጆቻቸው በህይወት ለመኖር በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ የመሆናቸውን ግዙፍና መሪር ሃቅ በዐይኑ በብረቱና እያየና በጆሮ እየሰማ ከታላቁ መጽሐፍ ጥቅሶችንና ስሞችን እየጠቀሰ “የባህር ማዶ ገዳም ማሠሪያ መዋጮውን አጠናክራችሁ ቀጥሉ” የሚል የሃይማኖት መሪን ከምር መቀበል እንዴት ቀላል ይሆናል?

በመከራ ውስጥ ለሚገኘው ወገን ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ ማድረግ የእውነተኛው አምላክ ፍላጎት እና የእውነተኛ አማኝነት ግዴታ ሆኖ ሳለ ባህር ማዶ ለሚኖር ዳያስፖራ ( ያውም በአንፃራዊነት ከየትኛውም አገር በተሻለ የዓለም ክፍል ለሚኖር)  ታሪካዊ  ገዳም “ካልሠራንለት” በሚል በአስከፊ ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ የዓለምን ምፅዋዕት ከሚማፀነው ወገን እየተሻሙ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መሰብሰብና አሁንም ጣል ጣል አድርጉ የሚል ዘመቻ ማካሄድ እንኳንስ ለሃይማኖት መሪ ሚዛናዊና አስተዋይ አእምሮ ላለው የእኔ ቢጤ ተራ ሰው (ordinary person) ጨርሶ አይመጥንም። ሲሆን በተወሰነ ወቅት ሥፍራው ድረስ በመሄድ የመከረኛውን ህዝብ መከራ መጋራትና ማፅናናት ፤ ካልሆነም ቢያንስ ዳያስፓራው የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ባለመሻማት ለመተባበር የሚሳነው የሃይማኖት መሪነትን ወይም አባትነትን ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅ ከትክክልም ትክክል እንጅ ስህተት ወይም ድፍረት ፈፅሞ አይደለም።

ውድ እውነተኛ አማኝ፣ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ፣ አገርና ወገን ወዳድ ወገኖች ሆይ! እስኪ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የሆነውንና አሁን በዚህ ወቅትና ሰዓት በንፁሃን ላይ እየደረሰ  ያለውን አሰቃቂ ግድያ፣ የርሃብና የበሽታ ቸነፈር፣ የመፈናቀል፣ ከትምህርት ገበታ ተነቅሎ ተስፋ ቢስ የመሆን  ፣ ወዘተ መሪር እውነት  እና የባህር ማዶ ገዳምና ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት አያሌ ሚሊዮን ዶላር በሚያሰበስቡና በሚሰበስቡ  የሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለውን እጅግ ሰፊና አስከፊ ልዩነት ራሳችሁን በመከረኛ ወገን ቦታና ሁኔታ ላይ አድርጋችሁ ከምር አጢኑት!!!

 

የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረታችንና ርብርባችን የእኩያን ገዥዎች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሰለባ ለሆኑት አያሌ ሚሊዮኖች የነፍስ አድን ዘመቻ ከማድረግ እና ለዘላቂው የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን መሆን የሚያደርጉትን ተጋድሎ  ከማገዝ ይልቅ ባህር ማዶ እንገነበዋለን የምንለውን ገዳም ወይም ቤተ ክርስቲያን ባርኮ የሚቀበል እውነተኛ  አምላክ የለም። እናም ወይ ቆም ብሎ በማሰብ ለምድሩና ለሰማዩ የሚጠቅመውን ማድረግ ወይንም  ደግሞ “የእኛ የገቢ ምንጭና መጦሪያ ቢሆንስ ምን ችግር አለው” ብሎ በቁርጡ ራስን ግልፅ ማድረግ ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

p9hj9hihj
Previous Story

በአንበሶቹ ግዛት ቀበሮ ነግሰ ዘር እየቆጠረ የሰው ልጅ አነሰ

orthodox Church
Next Story

አቡኑ ጳጳሳት በእንጀራ ታነቁ!

Go toTop