ደረጀ መላኩ ( የሰብአወዊ መብት ተሟጋች)
ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም.
እንደ መግቢያ
የፕሮፌሰር መስፍን ፋውንዴሽን እሁድ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከ7፡30 ጀምሮ እስከ 11፡30 ድረስ የፕሮፌሰር መስፍንን 3ኛ አመት አስመልክቶ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲያዘጋጅ ለመገኘት በመቻሌ እኔም ስለ ፕሮፌሰር አጭር ማስታወሻ ለማስፈር ህሊናዬ ጎተጎተኝ፡፡ ለማናቸውም፡-
ይህን አጭር ጽሁፍ ለማዘጋጀት ስነሳ የሚከተሉት ጥያቄዎች በህሊናዬ ላይ ይመላለሳሉ፡፡ እነኚህም፡-
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዴት ተመሰረተ ? መቼ ተመሰረተ? እነማን መሠረቱት ?ለምን ተመሰረተ ?አለማውስ ምን ነበር? የሚሉና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዴት ተመሰረተ ?
ኢሰመጉ ሊመሰረት የቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰብአዊ መብት ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወደ 28 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በአቶ አስራት ገብሬ ቢሮ መሰባሰብ ከቻሉ በኋላ እንደነበር ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ የኢሰመጉ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩ አስታውሳለሁ፡፡ ሆኖም ግን ኢሰመጉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመብት ተሟጋች እንዲሆን ሃሳቡን ያመነጩት ፕሮፌሰር መስፍን ሲሆኑ ሃሳባቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ካወያዩ በኋላ ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንደቻሉ አቶ ነጋሽ ገሠሠ በህይወት በነበሩበት ግዜ ለኢሰመጉ የሥራ ባልደረቦች ከሰጡት ቃለምልልስ ለመረዳት ችለናል፡፡
ኢሰመጉ መቼ ተመሰረተ?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሀ ብሔር ሕግ ከቁጥር 404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት የተቋቋመ፣ መንግስታዊ፣ፖለቲካዊና አትራፊ ያልሆነ ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚከራከር ድርጅት ነው፡፡ መስራቾቹ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ 32 ግለሰቦች ናቸው፡፡ በአሁኑ ግዜ ከ300 በላይ አባላት አሉት፡፡በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 9 ቅ/ጽ/ቤቶች አሉት፡፡
ለምን ተመሰረተ ? አላማውስ ምን ነበር ?
ኢሰመጉ የተመሰረተበት ዋነኛ አላማ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ነው፡፡
የኢሰመጉ አላማ
ኢሰመጉ የተቋቋመው፡-
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለዲሞክራሲያዊ አኗኗር፤ለሕጋዊነት መሰፈን እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አንዲሆን ለመታገል፣
በኢትዮጵያ ውስጥ መብቶች ሲጓደሉ ሁኔታውን ለመከታተል እና ይፋ ለማውጣት፣ እንዲታረሙም ለመጠየቅ፣ ሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችን እና የጋራ መግለጫዎችን ኢትዮጵያ እንድትቀበል ለማበረታት ስብሰባዎችን፣ውይይቶችን፣ንግሮችንና የጥናት መድረኮችን በየግዜው በማዘጋጀት ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበትን፣ እንዲሁም ህጋዊነትና የዲሞክራሲያዊ አኗኗር ሥርአት የሚጠናከርበትን መንገድ ለመጠቆም፣
ስለ ሰብአዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ አኗኗር የሚያስረዱ መጽሔቶችን፣ ጋዜጦችንና መጽሐፍቶችን ለማሳተምና ለማሰራጨት፡፡
ኢሰመጉ የመንግሥትን ሥልጣን ተገን ያላደረገ ግለሰብ በግሉ የሚፈጽመውን የመብት መጋፋት ጉዳይ አይከታተልም፡፡ይህ ተራ ግለሰብ የሚፈጽመው ተራ የወንጀል ጉዳይ ስለሆነ ጥፋተኛውን ለፍርድ ማቅረብ የመንግሥት ፋንታ ነው፡፡
ስለ ፕሮፌሰር መስፍን የምናገረው የእውነትን ምንነት ስላስተማሩኝ ነው፣ በእውነት ኑሬ፣ ለእውነት ስል፣ በእውነት ምክንያት የቀራንዮን መንገድ እንድከተል ተምሳሌት ከሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዱና ዋነኛው ምሁር ስለሆኑ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ምሁራን የአደባባይ ምሁራን እንዲሆኑ፣ ለእውነት እንዲቆሙ በብዙ መልኩ የደከሙ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋጽኦ ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡
በምእራቡ አለም ታሪክ ሶቅራጥስ የእውነትን ሃያልነት በመናገሩ ምክንያት የሞት ፍርድ ሲበየንበት በፍርሃት አልተርበደበደም ነበር፡፡
እንደ ፕላቶ ገለጻ ከሆነ ሶቅራጥስ በሚያደርጋቸው ንግግሮች ብዙዎች ሊጠሉት እንደሚችሉ፣ ብዙዎችን እንደማያስደስት፣ ሆኖም ግን ሶቅራጥስ ስለ እውነት እንደሚናገር እምነት ነበረው፡፡
According to Plato, Socrates said, “I know that my plainness of speech makes them hate me, and what is their hatred but a proof that I am speaking the truth?”
በነገራችን ላይ የሶቅራጥሥ እውነት የተመሰረተው በእውነት ላይ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ሌሎች እውነት ነው ብለው ስለሚያምኑት ጉዳይ መጠየቅ ልምዱ ነበር፡፡
የአደባባይ ምሁር ፖሊሲዎችንና የሀገር ጉዳዮችን በተመለከተ ለማስረዳት፣ ለመተንተን ድምጽ ለሌላቸው፣ ጉልበት ለሌላቸው ሰዎች፣ አጋዥ ለሌላቸው ሰዎች ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ አይነት ሰው የነበሩ ይመስለኛል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍንን የመሰሉ እውነተኛ ምሁራን እንደ ሻማ እየቀለጡ በአንዲት ሀገር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን የሚባጁ ናቸው፡፡ የራሳቸውን እውነት ይናገራሉ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘትም ሆነ በተለያዩ ስብሰባዎች፣ አውደ ጥናቶችና ( በተለይም በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩቱ)፣ እርሳቸው በሰጡት አንድ ስልጠና ላይ ተካፋይ በመሆኔ ለበርካታ ጊዜያት የማግኘት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በእውነቱ ለመናገር ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ለሰአታት ተገናኝቶ ማዳመጥ በዩንቨርስቲ ውስጥ ለአመታት ቆይቼ ካገኘሁት የበለጠ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚያነሱት ነጥቦች ሁሉ ጥልቀት እውቀትን የሚመገቡ ሰው ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ኢትዮጵያ የቀደመ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ትንታኔ ሲሰጡ ሁሉም ሰው በታላቅ አርምሞ ነበር የሚያዳምጣቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ሰው ነው በወርሃ መስከረም 2013 ዓ.ም. ያጣችው፡፡ ያሳዝናል፡፡
አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በጥር 2020 በህይወት ታሪካቸው ላይ የሚያጠነጥን ጥናታዊ ፊልም ‹‹ የፕሮፌሰሩ መቀስ የተሰኘ ጥናታዊ ፊልም ›› እንደተመለከትኩ አስታውሳለሁ፡፡ ፊልሙን የተመለከትኩት በብሔራዊ ቲያትር ቤት አዳራሽ ነበር፡፡ ፊልሙ ማራኪና ትምህርታዊ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በፊልሙ ሰክሪን ላይ የሚናገሩት ስለ እውነት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ነጻነትን ለመጎናጸፍ እረጅም መንገድ የተጓዙ ጎምቱ ምሁር ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር የፕሮፌሰር ማእረጋቸውን ከማግኘታቸው በፊት በርካታ የምርምር ጽፎችን አቅርበዋል፡፡ የምርምር ጽሁፎቻቸው ያተኩሩት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ ጥልቀት ያላቸው ነበሩ፡፡ ከብዙ ሰዎች ሳይግባቡ መኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ብቸኝነትም ፈታኝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እውነት ተናጋሪዎች ጓደኞች የላቸውም፡፡ ስልጣን ያላቸው እውነቱን ፍርጥ አድረገው የሚነግሯቸውን ሰዎች ማቅረብ አይፈልጉም፡፡ ስልጣን የሌላቸው ደግሞ በፍርሃት ምክንያት ከእውነት ተናጋሪዎች ጋር መታየት አይፈልጉም፡፡ በአጭሩ በኢትዮጵያ ምድር እውነትን የሚፈልጉ፣ ለእውነት የቆሙ ሰዎች ጓደኞቻቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ለእውነት በመቆማቸው ብቻ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፣ ታስረዋል፡፡ ሆነም ግን ይሁንና ከእውነት አንዲት ጋት ፈቀቅ አላሉም፡፡ በተቃራኒው ፕሮፌሰር መስፍን እስከመጨረሻው ድረስ ህዝብን ማስተማራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በእኔ በኩል ለፕሮፌሰር መስፍን ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ እርሳቸው የአደባባይ ምሁር፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ጠባቂ፣ ጥሩ እና ታማኝ ሰው ነበሩ፡፡ አድርባይነት የእርሳቸው ባህሪ አልነበረም፡፡ ሊሆን የሚችለውን ነገር ምክንያት አያስቀረውም ባይ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ጨለማ በነበሩት አመታት አንጸባራቂ ኮከብ የነበሩ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው ስለ ኢትዮጵያ የጻፉ፣ የተናገሩ፣ ያዳመጡ፣ ተምሳሌት የነበሩ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
አዳፍኔ በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ‹‹ ኤመርሰን ›› የአለም አይን መሆኑን እንዳሳየው እርሳቸውም የኢትዮጵያ አይን መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በመጽሃፋቸው ላይ የኢትዮያን ታላቅነት አብራተዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልደ የአባቶቹን ታሪክ በመዘንጋቱ የትውልድ መቆራረጥ ሊከሰት እንደቻለ በሀዘን አስፍረዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የእኛ አቅጣጫ ጠቋሚያችን ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የት እንደነበሩ፣ ወደፊት ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳዩን ሰው ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ወጣት በእጅጉ የሚጨነቁ፣ የሚጠበቡ ሰው ነበሩ፡፡
እንደሚመስለኝ ‹‹ አዳፍኔ ›› የተሰኘው መጽሀፋቸው ማስታወሻነቱ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወጣቱ ትውልድ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚስተዋለው ወጣቱ ትውልድ በማንነት ቀውስ ውሰጥ እንዳይዘፈቅ ፣ የኢትዮጵን ታሪክ በቅጡ እንዲረዳ በብርቱ አስጠንቅቀውት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ለወጣቱ ትውልድ በርካታ ሃላፊነቶችን ሰጥተውትም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እንደሚከተለው ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያን ከሞት ማዳን የምትችሉት ከጎሰኝነትና መንደርተኝነትነ እሳቤ ገሸሽ ለማለት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ስትችሉ ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ማዳን የምትችሉት የተቋረጠውን የትውልድ ቅብብሎሽ ለማስቀጠል ስትችሉ ነው
ኢትዮጵያ የምትድነው ወጣቱ ትውልድ ለሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለህግ የበላይነት መከበር ሲል በሰውነት ደረጃ መቆም ሲችል ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣት የጎሰኞችን እና የጎሳ አምበሎችን የሴራ ገመድ በጣጥሶ ኢትዮጵያን ከሞት መታደግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት በውጭ ሀገር የተሻ ኑሮ ስለሚመሩ ኢትዮጵያውያን ሲናገሩ ፣ በአሜሪካን ያለው ህይወት መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር ማግኘት አይቻላችሁም፡፡ አንድ ቀን ኢትዮጵያን ተስፋ አደርጋለሁ ብለው ነበር፡፡ አንዳንድ የህሊና ሚዛናቸው ያልተሰበረ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) ኢትዮጵያውያን የፕሮፌሰሩን ፍልስፍናዊ ትንቢት ለመረዳት ይሞክራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በእኔ አስተያየት የአንድ ሰው ታላቅነት የሚለካው ጉልበት ለሌላቸው፣ ለተራቡ፣ ለታረዙ፣ ለተጠሙ ሰዎች የእውነትን ሃይል መናገር ሲቻለው ይመስለኛል፡፡
ማናቸውም ሰው ይኖራል፣ ኋላም ይሞታል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እረጅም እድሜ ለመኖር የታደሉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያታዊ ህይወት ኖረዋል፡፡ ስልጣን ለሌላቸው፣ ለተራቡና ለተጠሙ ኢትዮጵያውያን የእውነትን ሃይል በተመለከተ እድሜ ልካቸውን ተናግረው አልፈዋል፡፡
ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደጻፈው ‹‹ የአንድ ሰው ማንነቱ መለኪያው በተመቻቸ እና በጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይሆን፣ በአስቸጋሪ እና አወዛጋቢ ጊዜያቶች በሚሳየው አቋሙ ነው፡፡ እውነተኛ ጎረቤት ለሌሎች ደህንነት ሲል የራሱን ስልጣን፣ ክብር እና ህይወቱን ጭምር አሳልፎ የሚሰጥ ነው፡፡
.
Dr. Martin Luther King, Jr. wrote, “The ultimate measure of a man is not where he stands in moments of comfort and convenience, but where he stands at times of challenge and controversy. The true neighbor will risk his position, his prestige, and even his life for the welfare of others.”
ፕሮፌሰር መስፍን እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሳለፉ ይመስለኛል፡፡ በብዙ ፈተናዎች እና አደጋ ውስጥ ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ ህይወታቸው፣ነጻታቸው፣ ንብረታቸው፣ ክብራቸው፣ ወዘተ በአደጋ ውስጥ ብዙ ግዚያትን አልፏል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ነጻ ሆነው ኖረዋል፡፡ በነጻነትም ሞተዋል፡፡ ስለሆነም ‹‹ በነጻነት መኖር፣ በነጻነት መሞት›› ፕሮፌሰር መስፍን ትተውልን ያለፉት አስተምህሮ ነው፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 2015 ‹‹ የት እንድንሄድ ይፈልጋሉ ? ›› በሚል ርእስ ባቀረቡት አስተያየት፡
የትም እንደማይሄዱ ለወያኔዎች አሳይተዋቸዋል ( አረጋግጠውላቸዋል)፡፡
በኢትዮጵያ ምድር በነጻነት ኑረው በነጻነት እንደሚሞቱ አሳይተዋቸዋል፡፡
በሞት ማሸነፍ እንደሚቻል ጽፈው አልፈዋል፡፡
ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሞታቸው ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ አይን፣የኢትዮጵያ ጸሃፊ፣ስለ ኢትዮጵያ ተናጋሪ፣ስለ ኢትዮጵያ አድማጭ፣ የኢትዮጵያውያን ተምሳሌት፣ለሰብዐዊ መብት ተሟጋቾች ተምሳሌት በመሆኖ አመሰግናለሁ፡፡ ለሁሉም ሥራዎቾ አመሰግናለሁ፡፡ የእውነትን ሃያልነት ተናጋሪው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አፈሩን ገለባ ያድርግልዎ፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን ማስታወሻ ( ከ 1922- 2013 ዓ.ም.)
የመንፈሰ ጠንካራውን፣ አይበገሬውን እና ልበ ሙሉውን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መስከረም 19 ቀን 2013 እኩለ ለሊት ላይ ህልፈታቸው ሲሰማ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በከባድ ሀዘን ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ መንግስት የመጨረሻ አመታት ፕሮፌሰር መስፍን የወሎ ርሃብ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በማድረጋቸው ታሪክ ስፍራን አይነሳቸውም፡፡ በ1984 ዓ.ም ደግሞ ኢሰመጉን ከ32 ጓደኞቻቸው ጋር ነሆን መስርተው የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ላደረጉት ታላቅ ሥራ ሻምዮንነቱን ማንም ሊነጥቃቸው አይቻለውም፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ የዲሞክራቲክ ባህል እንዲዳብር በህትመት ውጤቶችም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሃሳባቸውን በማካፈል የሚታወቁ ብርቱ ሰው ነበሩ፡፡ ለእነኚህና ለሌሎች ጊዜ ለማይሽራቸው አብርክቶቻቸው የአለም ኖቤል ሰላም ተሸላሚ መሆን የሚገባቸው ኢትዮጵያዊ ነበሩ ተብሎ ቢጻፍ የሚመግት ሰው ይኖር ይሆን ?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የተመሰረተው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በወርሃ መስከረም 1984 ነው፡፡ መስራቾቹም ወደ 32 የሚጠጉ ኢትዮጵውያን ሲሆኑ፣ ከሙያ አኳያ የዩነቨርስቲ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ አስተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅት፣ ኢሰመጉን ለመመስረት የሃሳቡ አመንጪ ከሆኑት ግንባር ቀደም ሰዎች አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደሆኑ ከተለያዩ ምሁራን ጽሁፎች ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ለኢሰመጉ መወለድ የ28ቱ ሰዎች ጊዜ የማይሽረው፣ ጊዜ የማይከዳው ስራቸው ዘላለማዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የፕሮፌሰር መስፍንን ልእለ ሥራዎች ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባት በማለት የግል አስተያየቴን ለማቅረብ የደፈርኩት ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት ያለመታከትና ያለመሰልቸት፣ እንዲሁም ያለፍርሃት፣በልበ ሙሉነት፣ በእውነት መሰረት ላይ ሆነው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተለይም ሃሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ መብት፣ ስለ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የህግ የበላይነት መከበር ወዘተ ወዘተ በመጻፋቸው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እስከመጨረሻው ድረስ ኢሰመጉን እንደ ልጃቸው ያዩ የነበሩ፣ ከዚህ ባሻግር የኢሰመጉ መጻኢ እድል በብርቱ የሚያሳስባቸው ሰው ነበሩ፡፡ ኢሰመጉን የስራ ሃላፊዎችና አባላት በሚያገኙበት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢሰመጉ አጠቃላይ ስራዎች ሳይጠይቁ አያልፉም ነበር፡፡ ምክንያታዊ መልስ ካላገኙም ፊትለፊት ይገስጹ፣ ይመክሩም ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ኢሰመጉ መንግስታዊ፣ ፖለቲካዊና አትራፊ ያልሆነ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለህግ የበላይነት የቆመ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡
የታላቁ ሰው ህልፈተ ህይወት በተሰማ ማግስት የኢሰመጉ ቦርድ አባላትና እና የጽ/ቤት ሃላፊ በስማቸው አመታዊ ሸልማት ለማዘጋጀት፣ የኢሰመጉ ቤተመጽሐፍት ቤት በስማቸው እንዲሰየም መወሰናቸውን አቶ አመሃ መኮንን የኢሰመጉ የቦርድ ሊቀመንበር ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት መግለጫ ተሰምቷል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ለኢሰመጉ ቤተሰቦችና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሁኔታ ለሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመንፈስ ብርታትን የሚሰጥ ነበር፡፡
እንደ መደምደሚያ
ከልጅነት እስከ እውቀት፣ ማለትም እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በዩንቨርስቲ ተመራማሪነት፣ ፖለቲከኛነት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት፣ የእውነት ሃያልነትን በመናገር ያሳለፉት ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ በህይወት አጠገባችን የሉም፡፡ ሁላችንም ወደማንቀርበት ሞት ነጥቆናል፡፡ ወደር የማይገኝለት ስራቸው ግን ህያው ሆኖ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ለእውነት ኖሮ በዘጠና አመት ከዚህ አለም መለየት ክብር ነው
ፕሮፌሰር መስፍን ታላቅ ምሁርና ዋርካ ነበሩ ። ማንንም የማይፈሩ ለሀቅ የቆሙ የመብት ተሟጋች ነበሩ ። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ላለፉት ስልሳ አመታት ካገራቸው ጋር ጥብቅ የሆነ መተዋወቅ ኖሯቸው ያገር ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓገዋል ። ፕሮፌሰር መስፍን አመመኝ ደከመኝ ሳይሉ ሳያቋርጡ ሁሌ ፕሮጄክቶች አሏቸው ። ሳይደክሙ ይጽፋሉ ። ሀሳቡቸውን ያጋራሉ ። ይሟገታሉ ። ይከራከራሉ ። ይጣላሉ ። ቂም ግን አይዙም ። ጠባቸውም ሳይቀር ለማስተማር ነው ።
ፕሮፌሰር መስፍን ጥልቅ ተመራማሪ ነበሩ ። የሚወዱትን የኢትዮጵያን ጆግራፊና የገጠር ኢኮኖሚ መረጃ የሚሰበስቡት በየአካባቢው በመሄድ በግና ፍየል በመቁጠር ብቻ ሳይሆን ፣ ኩበትና ጭድ ፣ ወዘተ በመቁጠር ላይ የተመሰረተ እስካሁን ቤታቸው መረጃው የሚገኝ ጥናት ላይ የተመሰረተ ጥናት መሰረት ያደረገ ነው ። ምርምራቸው የጂዎግራፊ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የአማርኛ የቃላትን ጥንታዊ አመጣጥና አጠቃቀም በተመለከተ ለወደፊቱ ምሁራን የሚመራመሩበት ገና ያልታተሙ ብዙ ስብስብ ቦታ በጠባብ ቤታቸው እንዳለ ተማሪያቸው የነበሩት ዶክተር አበበ ሀረገወይን በአንድ ጽሁፋቸው ላይ አስቀምጠውታል፡፡
ለእኔ የሚዸንቀኝ ጉልበታቸውንና ጽናታቸውን ከየት እንደሚያመጡት ነው ። የአእምሮው ላንድ ሰከንድ አለማረፍና ምንም እድሜ የማይወስነው አዲስ ነገር ለመማር ያላቸው ሌላው ልዩ ተሰጥኦው እንደሆነ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ነው ። ፍራቻ የሚባለው እርሳቸው ዘንድ ይርሽ ብላ አታውቅም ። የሰው አምበሳ ናቸው ። እውነትን የያዘ ፍርሀት የለውም ። በመታሰርና በመንገላታት ከፍለውበታል ።
ፕሮፌሰር መስፍን የዘመናዊ ትውልድ መቋጫና በልዩ መልኩ መደምደሚያ ናቸው ። ያገራችንን ታላላቅ አርበኞችና ባለውለታዎች በልባችን ህያው እንደሆኑት እርሳቸውም መምሕራችንና አባታችን ህያው ይሆናሉ ።
ፕሮፌሰር መስፍንን የሰጠን ቸሩ አምላካችን ይክበር ይመስገን ።
ይህ እውን እንዲሆን ግን የሚከተሉት ተግባራት በመንግስትና ኢትዮጵያዊ ወዳጆቻቸው እንዲከወን ስጠይቅ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው፡፡
ለአካዳሚክ ነጻነትና በጂኦግራፊ የትምህርት ዘርፍ ላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ሲባል የስድስት ኪሎ ዋናው ካምፓስ በስማቸው እንደሰየም የግል ሃሳቤን አቀርባለሁኝ
የነጻነት አደባባይ በሚል ስያሜ ሃውልታቸው ቆሞ ወጣቱ ትውልድ የነጻነት ትርጉም ቢረዳ የሚለው ሌላው የግል አስተያየቴ ነው፡፡
የፍትህ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ብርርቱ እንዳሰሰበውና በአክብሮት እንደጠየቁት እኔም ለብዙ አስርተ አመታት የኖሩበት አፓርትሜንት ላይ የሚገኘው የቤት ቁጥር 1 መኖሪያ ቤታቸው ሙዚየም እንዲሆን የኢትዮጵያን መንግስት መማጸናችን የሚታወስ ነው፡፡ ይህ ውትወታ ቀና ምላሽ ከፌዴራል ኪራይ ቤቶች ባለስልጣን ስለተሠጠው መኖሪያ ቤታቸው የእርሳቸውን ልእለ ስራዎች የሚያሳዩ የምርምር ውጤቶች ለተመራማሪዎች ክፍት የሚሆንበት ጊዜ መድረሱን ከፕሮፌሰር መስፍን ፋውንዴሽን መስራቾችና ሃላፊዎች መበሰሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ለማናቸውም፡-
እስቲ ብሔራዊ ተምሳሌቶቻችንን ማክበር፣ ከእነርሱ መማር እንጀምር፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ተማሪ፣ አድናቂ፣ ተከታይ፣ አክባሪ፣ ወዘተ የእርሳቸውን ሌጋሲ ለማስቀጠል ሁላችንም ለህሊናችን ቃል እንግባ፡፡ As to us, his students, we will carry on his legacy
May God bless Professor Mesfin Wolde Mariam, and may he rest in eternal peace