ስለ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 2016 ዓ.ም
አብይ አህመድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ገደል ለመክተት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደረ ነው :: ነገ ዛሬ ሳይባል የመንግስት ሃላፊነቱን በሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎ ለሚታቀፍ የሽግግር መንግስት ማስረከብ አለበት :: ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማስቀጠልና ሕዝቡን አሁን ከሚታየው የባሰ እልቂት ለማዳን ሌላ አማራጭ የለም :: በአንድ ወፈፌ አምባገነን ማን አለብኝነትና የጥፋት ውርጅብኝ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ሊፈርስ አይገባም ::
የሀገራችን ሕዝብ : አእምሮው የታወከ ፍፁም ጨካኝ አምባገነን የሀገር መሪ ነኝ ባይና : እሱ ሥር በተኮለኮሉ አሽከሮቹ : ለከት የለሽ የሥልጣንና የዘረፋ ፍላጎት : ሥር የሰደደ ክፋትና የማያቋርጥ የደም ጥማት የተነሳ : ዛሬም እንደገና በጦርነት እሳት እየተለበለበ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል : ልብ ያቆስላል ::
ባለፉት አምስት አመታት በተካሄዱት ፍፁም አላስፈላጊ የእርስበርስ ጦርነቶችና የሰላማዊ ዜጎች አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች : በመላው ኢትዮጵያ በከንቱ የፈሰሰው ተሰፍሮ የማያልቅ የምስኪን ሕዝብ ደምና : የወደመው የሀገርና የሕዝብ ንብረት : በዚያም ሂደት የደበዘዘው የአብሮነት እሴት ያነሰ ይመስል ፤ የመንግስት ሥልጣን በያዙ ጥቂት ጨካኝ ግለሰቦችና ቡድኖች እኩይ ዓላማና ማንአለብኝነት የተነሳ : ሀምሳ አመት ሙሉ እፎይታ ያጣው ሕዝባችንና ድሃ ሀገራችን : እንደገና ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ መነከራቸው የግፍ ግፍ ነው ::