እንዲህ እንደዛሬው ዋጋው መሳ ሳይሆን፣ እኩል ከእራፊ ጨርቅ፣
ለሀገር ክብር ሲባል፣ ከባንዲራ በፊት፣ ሰው ነበር የሚወድቅ፡፡
መሣፍንቱ በጎጥ፣ ሸንሽኖ ከፋፍሎ፣ የማሽላ ዳቦ ያረጋትን ሀገር
ገብርዬ ሲለካት፣ እቅጩን ሁለት ክንድ፣ በሆነች ባንዲራ ገጣጥሞ በማሰር፣
አንድን ህዝብ፣ አንድ አርጎ፣ ማኖር እንደሚቻል፣ ከተዋበች በቀር፣
ህዝቡም፣ ሹማምንቱም፣ እራሱ ቴድሮስም፣ ከቶ አያውቅም ነበር፡፡
የዚያን ቀን ሌሊት ግን እንደ ነገ ጠዋት፣
ደረስጌ ማርያም ላይ፣ ንግሥና ሊቀባ ክፉኛ ሐሳብ ይዞት፣
እንቅልፍም እንደሰው፣ ሙልጭ አርጎ ክዶት፣
እልፍኝ ውስጥ ሆኖ፣ ስለ አንዲት ሀገሩ፣ ስለ አንዲት ዉዳጁ፣ ቋፍ ላይ ስላለች፣
ለሐሳቡ ማሠሪያ፣ አጥቶ እግር ተወርች፣
እንዲህ ሲንጎራደድ፣ ሌላኛው ውዳጁ የሴት ባለመላ ተዋበች አሊ ግን ልታነቃው አለች፡
‹‹ካሳ መከታዬ፣ ሐሳብ ለምን ገባህ፣ አልልም የእኔ አባት፣
ቅድምም አየሁህ፣ ማ’ዱን ስትገፋው፣ አልዋጥህ ብሎ፣ ባፍህ ሲንከራተት የጎረስከው እራት፣
አውቃለሁ ጌታዬ፣ የእንቅልፍህ፣ የዕረፍትህ የአንዠትህን ጠላት፣
ይህችው ሀገርህ ናት፡፡
ደግሞ ምን አባቱ! እንቅልፍስ ይቅርብህ ወዴት ታውቀውና
እጣህን የማንቃት አድርጎት ሲያበቃ ምኑን ታርፈዋለህ፣ ይኸው ጎበጥህ አይደል ሀገር ስታቀና
እንቅልፍስ ይቅርብህ ወዴት ታውቀውና››
ቁስሉን ነካችበት …
ብሶቱን፣ ልፋቱን፣ መከራውን አልፋ ህልሙን አየችበት፡፡
ካሳ አንገቱን ደፋ፣ እሷ ፊቷን ዞረች፤
እንዲህ የሆነለት ከ’ሱና እሷ በቀር፣ ባዕድ የማያውቃት፣ የዓይኑን ገደብ አልፋ የምትፈስ እንባ አለች
ያች እንባ ጠብ አለች፡፡
‹‹እንግዲህ›› አለ መይሳው
‹‹እንግዲህ … በኔ ልፋትና በእኔ ድካም ሳይሆን በእግዜር ይሁን ማለት
ለዚህ ማዕረግ መርጦ ሰጠኝ ይህን ሹመት
እኔ ስሰነዝር፣ እሱ ከእኔ ቀድሞ ባላንጦቼን እየጣለ
ወሰኔን እያሰፋ የታጠቅ ጉልበት እንደቻለ
ሞገሴን እያገዘፈ፣ እንደልቤ መሻት፣ እርከኔን እያከለ
እግዚሃር ይመስገን ይኸው ለዚህ በቅቻለሁ
ተመስገን ከማለት ውጪ ለስለት እከፍለውስ ምን የከበረ አስገባለሁ?
‹‹ግን›› አለ መይሳው …
‹‹ግን ነገ ማለዳ፣ ቅባቱን ተቀብዬ ዘውዴን ስደፋ
ህዝቡ፣ ይጠብቃልና እገባለት ቃል ኪዳን ፈቅደህ ስጠኝ ስለው ይህችን ትልቅ ሀገር
ምን ይዠ ልማልለት፣ ምን ጨብጨ ልቁረብለት፣ ምንስ ብዬ ልናገር?
እስኪ መላ ካለሽ ተዋቡ ከአንቺ እንኳ ልበደር፡፡ …
በማተቤ እዳልምል፣ የባለ ሌጣ አንገቱ የእስላሙም ናት ይህች ሀገር
በግዮን እዳልምል፣ ኦሞ፣ ጉደር፣ አዋሽ፣ ቦርከና፣ ባሮ፣ ተከዜ፣ ጉማራ በይው ሎጊያ
ሁሉም ገንዘቧ ነው፣ የትኛው ተየቱ በልጦብኝ በየትኛው ልማልላት ለኢትዮጵያ?
ሺናሻ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ አገው፣ ወላይታ፣ ትግሬ በይው አማራ
በምድሯ የተቀነበበው ሁሉ በስሟ ነው የሚጠራ!››
‹‹ህም!›› አለች ተዋቡ …
‹‹ህም! … አሁን እስላም ስትል፣ ሸማኔው ትዝ አለኝ እጀ ወርቅ የሚሉት አህመዴ ቦጋለ
በል ቶሎ በል ካሳ፣ አሽከር አስጠራልኝ፣ ገብርዬ የታለ
ገብርዬን አስጠራው፣ እሱ ነው የልቤ፣ ሲጋልብ የሚነፍስ
ከጎህ ቅዳጅ በፊት፣ መልዕክቴን ይዞልኝ፣ ከደጁ የሚደርስ፡፡››
ካሳን ግራ ገባው፤ ግን አይጠይቃትም …
አምስት ስድስት ጊዜም፣ እንደዚህ አዋክባው፣
እሷው ነድፋ፣ እሷው አባዝታ፣ እሷው አድርታ እሷው ፈትላ
ባመጣችው ሀሳብ ባሳየችው መላ፣
ብትንትን ሐሳቡን ገጣጥማ ስትሰፋው አይቷልና ባይኑ
‹‹ለምን?›› ማለት ትቶ፣ ‹‹እንዴት?›› ማለት ትቶ፣ ‹‹ገብርዬ ይጠራ!›› አለ ወዲያዉኑ፡፡
ገብርዬ …
ከታንጉት ሙቅ እቅፍ፣ በውድቅት ተላቆ ከነጋሻ ጃግሬው ገና እንደደረሰ
‹‹እሰይ የኔ አንበሳ!›› ስትለው ተዋበች፣ ገና እንኳን በወጉ፣ የወጉን እጅ መንሳት ሰጥቶም አልጨረሰ፡፡
‹‹እሰይ የኔ አንበሳ! እንትፍ እቺ ምራቅ ምድር መትቷት ሳትከር፣
ስትገሰግስ ሄደህ፣ ደገኞቹ መንደር፣
አህመዴ ለሚባል እጀ ወርቅ ሸማኔ፣ ቃሌን ቃል ሳትጨምር፣ እንዲህ ብለህ ንገር፤…
በአገር ሰማይ ስትፈልቅ፣ የቅርቡም የሩቁም እኩል እንደሚያያት የማርያም መቀነት
እዚህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት፣
አንተ ስትለካት፣ ሁለት ክንድ የሆነች፣ ጥብቅ ምት ባንዲራ
ዉብኛ አርጎ ሠርቶ፣ ነገ ማርያም ድረስ ይዞ እንዲመጣ፣ አጥብቀህ አርቀህ ንገረው አደራ፡፡››
በማለት ተዋበች ….
ግብጦች ለእጅ መንሻ፣ ከላኩላት መሃል፣ የሀር የሆነውን ጥለት ጥድፍ ብላ
ለገብርዬ ሰጥታው፣ እሱም ጥድፍ ብሎ፣ ከነጀሌዎቹ ከወጣ በኋላ
ካሳ ፈገግ አለ …
የጥድፈቷ ምስጢር፣ ቋጠሮው ተፈትቶ፣ ብትንትን ሐሳቡን በአንድ ስላዋለ
ካሳ ፈገግ አለ፡፡ …
* * *
ሺህ ስምንት መቶ አርባ አምስት ዓመተ ምህረት፡፡ …
የተራራው አናት ገና ሳይላቀቅ ከአድማስ ጥቁር እግር
በአህመዴ አማርኛ ሰማዩ ሳይቀላ በአግባቡ ሳይፈጅር
አህመዴ ቦጋለ፣ የንጋት ስግደቱን አሰላምቶ አብቅቶ ልክ ፊቱን እያበሰ
ፊታውራሪ ገብርዬ፣ ከነጀሌዎቹ ደጁ ላይ ደረሠ፡፡
የፈረሶች ኮቴ፣ ደጁን ሲረመርም የሰማው አህመዴ፣
ልቡ ድንግጥ አለ፤ ‹‹እንዲህ በማለዳ የሚደርስ ደጄ፣
መርዶ ነጋሪ ነው፣ ደግሞ ማን ተለየኝ፣ የትኛው ዘመዴ
ከቶ የእኔ ሐዘን፣ ዳርም የለው እንዴ?!›› …
‹‹እንዴ…ት አደራችሁ?››
ይህን ድምፅ ያውቀዋል፣ ይበልጥ ተሸበረ፤
ምላሽም አልሰጠ፣ በርም አልከፈተ፣ ድርቅ ብሎ ቆሞ፣ ‹‹ወይ ወንድሜን!›› አለ፡፡
… ‹ክተት!› ሲባል ከትቶ፣ ከመይሳው ጋራ አብሮ የዘመተ
አንድ ወንድም ነበረው፣ ያ ወንድሙ ሞተ ……
‹‹ቤቶች!!›› ….
ገብርዬ ጥሪውን፣ እንዲህ ሲደጋግም
ገፋ አድርጎ ወጥቶ፣ የጎጆውን ግርግም …
‹‹ድሮ አውቄዋለሁ!
ድሮ አውቄዋለሁ! ለደግም አልነበር፣ አደባባይ ቆሜ
ሸማ ሳውለበልብ፣ ያየሁት በህልሜ
ወይ ወንድሜ! ወንድሜ! ….››
‹‹የለ እንደሱም አይደል፤›› … ገብርዬ አቋረጠው፤
‹‹ተዋበች ልካን ነው፤›› አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለቱን ሰጠው፡፡
አስከትሎ ደግሞ …
‹ቃሌን ቃል ሳትጨምር› ያለችውን መልዕክት፣ ቃሏን ቃል ሳይጨምር እረግጦ ሲነግረው፣
የመናሙ ተፍሢር፣ ብሥራት ሆኖለት … እጀ-ወርቅ ደስ አለው!
አለ’ም፡
‹‹እንዴት ያ’ንድ እናት ሆድ፣ አንድ ላይ ያበቅላል፣ አንድ ደህና አንድ ጠፍ
ብረገም ነው እንጅ፣ ‹ክተት› ሲል ከትቼ፣ እንደዚያ ወንድሜ፣ ከመይሳው ጋራ ጎኑ እማልሰለፍ
ብዬ እቆጭ ነበር … ይኸው ዛሬ ግና፣
አላህ ያለ ለታ፣ ላገር ሥራ ሲለኝ፣ ረብ ያለው ሥራ
ያውም የመይሳውን፣ ያውም የኢትዮጵያን፣ ያውም የሀገሬን ባንዲራ
ያውም በእኔ ጥበብ፣ ያውም በሰው እጆች፣ ከሰውም በ’ኔ እጆች በሸማ እንድሠራ
ታሪክ እድል ሰጠኝ፣ ብሞትም አይቆጨኝ፣ ከዚህስ በኋላ!!›› …
አህመዴ ሸለለ … አህመዴ ፎከረ፣
በደስታ ሰከረ … በደስታ አለቀሰ
ሩጦ ቤቱ ገባ፣ ሦስቱንም ልጆቹን፣ ሚስቱን ቀሰቀሰ፡፡
ነገራት ለሚስቱ … ከምርጥ ዘሃ መሀል ምርጡን ዘሃ መርጣ
እንድታቀርብለት ቶሎ ብላ ዘግታ
አዘዘ ልጆቹን፣ ቱባ ተከፋፍለው፣ ከእያንዳንዱ ጥለት
አስር አስር ቀለም እንዲያዳውሩለት፡፡
ሦስት ሰዓትም አልፈጀ፣ …
መቀነት ሸማ’ቃው፣ ከኖረበት ወርዶ፣
ዝግ ዘሃው ተቋጥሮ፣ ጥለቱ ተጥሎ፣
ድምድሙ ተመትቶ፣ ባንዲራው ሲቆረጥ
ሦስት ሰዓትም አልፈጀ፡፡
በቅሎው ከጋጥ ወጥቶ
በጌጥ ተሸልሞ፣ አህመድ ከነሚስቱ እጋማው ላይ ወጥቶ
እሱ ሲኮለኩል፣ በቅሎው ንሮ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ ….
ደረስጌ ማርያም ላይ፣ ደርሰው ሆታው ሲቀልጥ
በዚያ መሐል አልፈው፣ አህመድ ለመይሳው ባንዲራውን ሲሰጥ
ሰአትም አልፈጀ፡፡
መይሳው ደስ አለው! …
የወርዱ ምጣኔ፣ የጠርዙ ጥብቅነት፣ የጥለቱ አጣጣል ጥበቡ ደነቀው
‹ተባረክ እጅህን ቁርጥማት አይንካው!›
በሆዱ መረቀው፡፡
ካሳ ዞሮ ሄደ፤ አህመዴ ተጣራ፣
መይሳው ዞር አለ፣ ባንዲራው ሲሰራ
ተርፎ ስለነበር፣ ብዙ የሀር ጥለት
ካቁማዳው አውጥቶ፣ እሱን ዘረጋለት፡፡
ካሳ …
የዚህን ደሀ ሰው፣ ፍፁም ታማኝነት
ገራገር ልቦና ባስተዋለ ጊዜ
የጎንደር አዝማሪ ያቀነቀናትን
በልቡ እያዜማት፣ በልቡ ያላትን
ያችኑ ምርቃት …
‹‹ተባረክ እጅህን አይንካው ቁርጥማት!››
በአፉ ደገማት፡፡
የጎንደር አዝማሪ፣ በነአህመዴ ዘመን፣
”እስላም አልኩሽ እንጅ፣ እጁ የሚታመን
ሸማኔማ ሞልቷል፣ ደሞ ለመሸመን!”
ይል ነበር:: ……
– በገጣሚ ኑረዲን ዒሣ